የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራ ፍትሕ (ኢዜማ) ከሰኔ 28 እስከ 29 ቀን 2017 ዓ.ም ሲያካሂድ የነበረውን ሁለተኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ ማጠናቀቁን እና አዲስ ሊቀመንበር እና መክትል ሊቀመንበር መምረጡን አስታወቀ።
“በሃሳብ እንፎካከራለን፤ ስለ ሀገር እንተባበራለን!” በሚል መሪ ቃል በአዲስ አበባ ባካሄደው ጉባኤ ዶ/ር ሙሉዓለም ተገኘወርቅን የፓርቲው ሊቀመንበር አድርጎ መርጧል፤ አቶ ማዕረጉ ግርማን ደግሞ የፓርቲው ምክትል ሊቀመንበር አድርጓል። አቶ ዋሲሁን ተስፋዬ የፓርቲው ዋና ፀሐፊ በመሆን መመረጣቸውንም ጠቁሟል።
ከመላ ሃገሪቱ ከሚገኙ የፓርቲው የምርጫ ክልሎች የተወከሉ ከ600 በላይ አባላት በጉባዔው መሳተፋቸውን የጉባኤውን መጠናቀቅ አስመልክቶ ፓርቲው ዛሬ ሰኔ 30 ቀን 2017 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
የፓርቲው መሪ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ለጉባኤተኞች ባስተላለፉት መልዕክት ፓርቲው ከውስጥም ሆነ ከውጪ ሲሰነዘርበት የቆዩትን ተግዳሮቶች በመቋቋም የመድብለ ፓርቲ ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ባህል እና የዜግነት ፖለቲካ በጽኑ መሰረት ላይ እንዲቆም ጉዞውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል መግለጻቸውን አካቷል።
“ፓርቲው በ2018 ዓ.ም ለሚደረገው ሀገራዊ ምርጫ ከወዲሁ ዝግጅቱን መጀመር እንዳለበት” የፓርቲው መሪ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ አሳስበዋል ብሏል፡፡
በየሶስት አመቱ የሚከናወነው የኢዜማ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ የፓርቲው ከፍተኛ የሥልጣን እርከን ሲሆን፣ ከተለያዩ የሥራ ክፍሎች የቀረቡለትን የፓርቲውን የሶስት ዓመት የሥራ ክንውን፣ የሂሳብ እና የኦዲት ሪፖርት እንደዚሁም የደንብ ማሻሻያ እና ፓርቲውን ለመጪው ሶስት አመት የሚመሩ አመራሮችን በመምረጥ ጉባዔውን ማጠናቀቁን ገልጿል።
Ethiopia Today