በክፍል አንድ የእገታውን ወንጀል አስመልክተን ወንጀሉን ፈጸሙት ከሚባሉት መካከል (ዐቢይ አህመድ፣ ሸኔ፣ ኦነግ፣ ሕወሃት) ወንጀል ፈጻሚው የትኛው አካል ሊሆን እንደሚችል የወንጀል ምክንያትን በመመርመር ሕወሃት ላይ ጣት ጠቁመናል። ወንጀሉ እንደተፈጸመ አቢይ አህመድ ማስረጃዎቹን ሁሉ ወዲያው ከሰበሰበ በኋላ ለምን ደበቃቸው? ሕወሃትስ ወንጀሉን ከፈጸመችው አቢይ ለምን ሕወሃትን ለማጋለጥ አልተጠቀመበትም? ብለን ጠይቀን ነበር። ክፍል አንድን ለማንበብ ማስፈንጠሪያውን ይጫኑ _____________
በዚህ በደምቢዶሎው እገታ ዘመን ብዙ ወንጀሎች በሸኔ (መግሥታዊም ጫካዊም) መዋቅር ሲፈጸሙ የነበሩ ቢሆንም የሕወሃት የሽብር መዋቅርም ስዩም መስፍን እና አባይ ጸሐዬ አስቀድመው በቴሌቪዥን ቃል በገቡት መሠረት እጅግ ብዙ የሽብር ጭፍጨፋዎች ያካሄድ እንደነበር ለማወቅ ይቻላል። ለምሳሌ የጂጂጋው የአማሮችና የተዋሕዶ ምእመናን ጭፍጨፋ በሕወሃት ወኪሎች የተቀነባበረና የታገዘ ነበር። በመተከልም ጭፍጨፋ በወቅቱ እንደተጋለጠው ከሸኔ በተጨማሪ የሕወሃት ኃይሎችም እጅ ረጅም ነበር። ሕወሃትና ሸኔ በከሚሴና አጣዬም ይፋዊ ግንባር ፈጥረው አማራን ጨፍጭፈዋል።
በመጨረሻም የቡርቱካን ዶክመንተሪ በኢቢኤስ ያለ አቢይ አህመድ ፈቃድ ወይም እውቅና ተዘጋጅቶ እንደማይተላለፍ እምነቴ ነው። ይህ ከሆነ አቢይ ይህንን ለምን አደረገ? የአቢይን ሥልጣን እያሰጋ የመጣ አዲስ ክስተት ምንድን ነው? እንደኔ ግምት ከጥቂት ወራት ወዲህ አቢይ የሕወሃት፣ ሻዕቢያና አማራ ግንባር ሊፈጠርብኝ ይችላል የሚል ሥጋት እያቃዠው ነው። ጌታቸው ረዳም በአደባባይ እንደመሰከረው ከፋኖና ከኤርትራ ጋር ተባብሮ አቢይን ለማስወገድ የሚፈልግ የሕወሃት ግዙፍ ክፍል አለ። ስለዚህ አቢይ አህመድ አማራና ሕወሃትን ለማቆራረጥ ቆልፎ ካስቀመጣቸው መረጃዎች ጎምቱ ጎምቱዎቹን ለቁርጥ ቀን ሊጠቀም ይችላል። ከነዚህ ውስጥ የደምቢ ዶሎው እገታ አንዱ ነው። ምናልባት ትክክለኛውን መረጃ በማውጣት 1. የሕወሃቶችን ተሳትፎ ለማሳየት ወይም 2. አስቀድሞ ለነሱው አሳይቶ ለመደራደር ሊጠቀምበት ይችላል። የብርቱካን ዶክመንታሪም መሠራቱ ይቺን ነገር በምልክትነት ብልጭ ሲያደርግላቸው ይሆናል።
ለዚህ ማጠናከሪያ የሚሆነን ይህ የሕወሃትና የፋኖ ትብብር ወሬ መናፈስ በጀመረበት የዛሬ 3 ወር አካባቢ ማንም ሳይጠራው ወንጀሉ ከተረሳ አምስት አመታት በኋላ ብርሃኑ ጂሎ የደምቢ ዶሎ እገታን ወሬ አንስቶ አጋቹ ጃል ጫላ ወይም በሌላ ስሙ አሸናፊ ጎንደሬው ነው ያለበትና ቀሺም ውሸቱ የተጋለጠበት ቪድዮ ነው። የቁጩው ማርሻል “አሸናፊ ጎንደሬው የአብን አባል እና ሸኔ ውስጥ አስርገው ያስገቡት አማራ ነው” ሲል ሲሳይ አጌና እንኳን በቅጥፈቱ ተገርሞ “ጎንደሬ ያስገባሉ ኦነጎች?” ብሎ ሲጠይቀው ምርኮኛው ጄኔራል ተደናግጦ ደምቢ ዶሎ ተወልዶ ያደገ አማራ ነው ቋንቋውን ያውቃል አላለም! አሸናፊ ጎንደሬው እየተባለ እዚያው ተወልዶ ያደገ ሰው ጃል ጫላ ተብሎ እዚያው ደምቢ ዶሎ የሸኔ አባል ሆኖ ሠርጎ ገብ ሆኖ ሲሠራ አይታያችሁም? ማነው ጂሉ? ብርሃኑ ጂሎ ወይስ ሸኔ? ወይስ የደምቢ ዶሎ ሕዝብ?
ቁም ነገሩ ግን ኦህዴዶች ይቺን የደምቢ ዶሎን ወንጀል ማንሳትና ወደ አጀንዳነት ማምጣት የፈለጉበት ወቅት መሆኑ ነው። ለምን? ብለን እንጠይቃለን። በሌላ አተያይ ብርሃኑ ጂሎም እኛ እንደምንገምተው ጂል ሳይሆን ምናልባት “ጃል ጫላ፣ አሸናፊ ጎንደሬው የሚባል፣ አብን በሸኔ ውስጥ አስርጎ ያስገባው” ወዘተ ሲል በአሽሙር ማስተላለፍ የፈለገው “ጃል እግሌ፣ ጎይቶም ትግሬው የሚባል፣ ሕወሃት በሸኔ ውስጥ አስርጎ ያስገባው፣ ኦሮሚያ ውስጥ ተወልዶ ያደገ፣ ቋንቋውን የሚናገር ሰው ነበር” የሚለውን ቢሆንስ? ሕወሃትን እረፊ ለማለት አለዚያም ሳንዱቅ ውስጥ የቆለፉበትን መረጃ ሲለቁ አሃ! እንድንል። ለማንኛውም ወንጀለኞቹ በቀጥታ እነሱ (ኦነጋውያኑ) ከነበሩ የተረሳና የተዘነጋውን የደምቢ ዶሎ እገታ ወንጀል በብርሃኑ ጂሎ መሪነት እንዲህ ባላጦፉት ነበር።
ለኦህዴዶች/ኦነጋውያን ከሥልጣናቸው በላይ ምንም ነገር የለም። ያንን ሥልጣን ለማስጠበቅ ያስፈልጋል ያሉትን እርምጃ ደግሞ ከሁሉም ነገር የበለጠ ትኩረት ይሰጡታል። ስለዚህም የሥልጣን ስጋት የሚባለውን ለማስወገድ የቅድሚያ ቅድሚያ ሰጥተው ይሰራሉ፣ ከማንም ጋር ቢሆን ይተባበራሉ። እነሱ ተባብረው እንደጣሉ፣ ሌሎች ተባብረው እንድሚጥሏቸው ስለሚረዱ የሌሎችን ትብብር ለማክሸፍ/ለማምከን የሚችሉትን ሁሉ ያደርጋሉ። አማራና ትግሬን በሚመለከት ወልቃይት ብቻ አስተማማኝ ሽብልቅ ነው ብለው ተኝተው አያድሩም። እናም የትብብር ብልጭታ ወሬ ሁሉ ሲያቃዣቸው የሚዳድር ጉዳይ ነው።
ሌላም መላምት አለ። ኦዎ ኢቢኤስ የኤርትራውያን ንብረት ስለሆነ ዐቢይ ከኤርትራ ጋር ያለው ግንኙነት ሲሻክር ኤቢሲዎች ድራማውን ዐቢይን ለመጉዳት የሠሩት ነው የሚል ውሃ የማይቋጥር መላምትም ይደመጣል። ኢቢኤስ ስንት ሠርጎ ገብ የሀገር ማፍረስና የባሕል ሽርሸራ ሥራ የሚሠራበትን ወርቃማና ትርፋማ እድል በሚያስመልጠው መልኩ አንድ የአማራ ታጋች ምስኪን ታሪክ የአማራን ሕዝብ ቀስቅሶ ዐቢይ አህመድን የሚያስወግድ ጦስ ይሆናል ብሎ ተማምኖ ሊቆምር አይችልም። ሊሆን የሚችለው ግን ኢቢኤስን ለመውረስ ወይም ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር አቢይ ኢቤኤስ ውስጥ ካሉ የደህንነት አባላት ጋር ተጣምሮ የሠራው ወይም የተሳተፈበት ሥራ ነው። እንዲህ ዓይነት ሐሰተኛ መረጃን ሆን ብሎ በማሰራጨት ቁልፍ ግለሰቦችን ወይም ተቋማትን ከተአማኒነት ውጭ የማድረግ ልምድ አለውና። በቶሎሳ ኢብሳ ላይ ያደረገውን ሴራ ልብ ይሏል። የመቁሰል አደጋ እንደደረሰበት ለነቶሎሳ ሐሰተኛ መረጃ ከሰጠና እነሱም መረጃውን ከለቀቁት በኋላ በዚያው እለት በቲቪ ብቅ ብሎ በመታየቱ ለአመታት የገነቡትን እና ወያኔን አፈር ያስጋጡበትን ተአማኒነታቸውን ዱቄት ያደርገበትን ክሥተት ማለቴ ነው።
ቪድዮውን ከመጀመሪያውም ባለቤት ሆነው አልሰሩትም ቢባል እንኳን እነ አቢይና እነ ተመስገን ጥሩነህ የቪድዮውን መሠራት አስቀድመው እንደሚያውቁ ለሕዝብ ሳይለቀቅ በፊት እንዳዩትም ምንም አልጠራጠርም። ለዚህም አንዱ ማስረጃ ኦህዴዶችና ኦነጋውያን ጭምር ቪድዮውን አስቀድመው ያዩት መሆኑ ነው። በወቅቱ የነጃዋርን ልጥፎች ብቻ ሳይሆን ሳይጠራ የለፈለፈውን የደምቢ ዶሎ ዮኒቨርሲቲንም ኡኡታ መታዘብ ይቻላል። የኢቢኤሱ የብርቱካን ሙሉ ቪድዮ ደምቢ ዶሎን የሚጠቅስ ክፍል ቢኖርበትም በመጨረሻ ደረጃ ተቆርጦ በኢቢኤስ ለሕዝብ የተለቀቀው ቪድዮ ግን ደምቢ ዶሎ የሚለውን ቆርጦ ያወጣ እትም ነበር። ሕዝቡ ያየውን የተቆረጠ ቪድዮ ብቻ ከተመለከቱና አስቀድመው ሙሉውን ቪድዮ ካላዩ በስተቀር ኦህዴዶችና ኦነጋውያን ቪድዮው ገና እንደተለቀቀ ሳይጠሩ ከተፍ ብለው ደምቢ ዶሎ! ደምቢ ዶሎ! የሚሉበት ምክንያት አይኖራቸውም ነበር። ከዚህ በተጨማሪም ማስተባበያውን የኢቢሲ (ኢቲቪ/ፋና ወዘተ) ቪድዮም ጭምር አስቀድመው እንዳዩት ለማወቅ የነጃዌን ከማስተባበያው በፊት የተለቀቁ ልጥፎች መለስ ብሎ ማየቱ በቂ መረጃ ይሰጣል።
መንግሥት መረጃን በሚያፍንበት፣ ፍትሕን ለማዛባት ሆን ብሎ የተደናገሩ፣ የተጣረሱና የተሳከሩ ወሬዎችን በሚነዛበት፣ ፍትሕ ፈላጊዎችና ተቆርቋሪዎች የሆኑ ሰዎች የሚታወቁትን ነጠብጣቦች ገጣጥመው፣ መላ ምቶችን እየሰነዘሩ፣ ጊዜው ሲፈቅድ እነዚህን በትክክለኛ መረጃ እያጠናከሩ የሆነ ቀን ፍትሕ እንዲሰፍን ማድረግ አለባቸው። ተቋሞቹ በወንጀል ሲጠመዱ ዜጎች ደግሞ ወንጀሉን በጋራ ለማጋለጥ፣ ከሥር መሠረቱም ለመድረስ መሞከር ግዴታቸው ነው። ለዚያ የሚያግዝ ይሆናል በሚል ተስፋ የተጻፈ ጽሑፍ ነው።
በክፍል ሦስት እንገናኝ። የአጋቹን ማንነት በወንጀሉ ምክንያት መነሻነት መርምረን ጆሮን ጭው የሚያደርገውን እዚህ ያልተጠቀሰ የወንጀል ዓላማ እንገልጣለን።
በቸር ይግጠመን።