ጠገናው ጎሹ
May 5, 2024
በዓለ ትንሳኤውን አስመልክቶ ከሃይማኖት ተቋማት መሪዎች እና ከጠቅላይ ሚኒስትር ተብየው የተላለፉትን የእንኳን አደረሳችሁና የመልካም ምኞት “መግለጫዎች” ዋው! በሚያሰኝ አኳኋን እንኳ ባይሆን ለዘመናት ተዘፍቀን የመጣንበትን፣ ከስድስት ዓመታት ወዲህ ደግሞ ከደመ ነፍስ እንስሳት በታች ያዋለንን እና የዓለም ከንፈር መምጠጫና መሳለቂያ ያደረገንን ፖለቲካ ወለድ መከራና ውርደት የሚመጥን ቁም ነገር ይኖረው ይሆን? በሚል አንድ ጊዜ ብቻ ሳይሆን ደግሜ ተከታተልኩት።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክዊ እምነት መሠረት ከዓብይ የፆምና የፀሎት ወቅት በኋላ የሚከበረውን የትንሳኤውን በዓል አስመልክቶ የእንኳን አደረሰንና የመልካም ምኞት መልእክት ማስተላለፍና መለዋወጥ የሚሰጠውን ጥልቅና መልካም የሆነ መንፈሳዊና ማህበራዊ ስሜት ለመረዳት (ለማወቅ) የሚዛናዊ፣ የቅን፣ የመቻቻል፣ የመከባበር ፣ ወዘተ ህሊና ባለቤት መሆንን እንጅ የግድ ሊቅነትን ወይም ሊቀ ሊቃውትነትን የሚጠይቅ አይመስለኝም።
ከምር በሆነ የሃይማኖታዊ እምነት አማኝነት እና የሰብአዊና የዜግነት መብት ተሟጋችነት አቋምና ቁመና ላይ ሆነን የባለጌዎችንና የጨካኞችን የጎሳ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ሥርዓት በቃ ለማለት ባለመቻላችን ጠቅላይ ሚኒስትር ተብየው በእርሱና በካምፓኒው (በግብረ በላ ሠራዊቱ) ምክንያት የሆነውንና እየሆነ ያለውን ግዙፍና መሪር እውነታ በአፍ ጢሙ ደፍቶ “እንደ ክርስቶስ እመኑኝ” ሲል በእውነተኛው የክርስቶስ ህማምና ትንሳኤ ላይ ተሳልቋል።
ከልጅነት እስከ ጎልማሳነት እጅግ መርዘኛ በሆነ የጎሳ አጥንት ስሌት ካድሬነት ብቻ ሳይሆን እጅግ ሥር በሰደደ የሰብእና ቀውስ ውስጥ የኖረው እና ከስድስት ዓመታት ወዲህ ደግሞ የዚህን ትውልድ በስሜት ፈረስ የመጋለብ እጅግ የወረደና አዋራጅ ፖለቲካዊና ሞራላዊ ቁመና ተጠቅሞ ዙፋኑን ከአሳዳጊዎቹ (ከህወሃቶች) የበላይነት በመንጠቅ አገርን ፈፅሞ ለማመን በሚያስቸግር ሁኔታ ምድረ ሲኦል ያደረገና ያስደረገ ጠቅላይ ሚኒስትር ተብየ ሁሌም እንደሚያደርገው የቃላትና የተግባር ውህደት ውጤትና ፍፁም ቅዱስ የሆነውን የክርስቶስ ህማምና ትንሳኤ ልክ የሌለው የርካሽ ፖለቲካ ቁማሩ አካል አድርጎታል።
ከሦስት አሥርተ ዓመታት በፊት በጎሳአጥንት ስሌት ላይ በተመሠረተ ህገ መንግሥት በይፋ ተግባር ላይ የዋለው የጥላቻ፣ የመለያየት፣ የመጠላለፍና የመጠፋፋት ፖለቲካ ከስድስት ዓመታት ወዲህ ደግሞ የፖለቲካ ብቻ ሳይሆን የሰብእና ቀውስ በተጠናወተው ጠቅላይ ሚኒስትር ተብየ መሪነት በአስከፊ አኳኋን እንዲቀጥል የተደረገው የእኩያን አገዛዝ ተወግዶ እንደ ሰብአዊ ፍጡርና እንደ ዜጋ ተከብሮና ተከባብሮ መኖር የሚቻልባትን ዴሞክራሲያዊት አገር እውን ለማድረግ ይቻል ዘንድ እንኳንስ ወዳጅን ጠላትንም የሚያስደምም ተጋድሎ እያደረጉ ያሉትን የነፃነት ፋኖዎችን/አርበኞችን/ጀግኖችን የጥፋት መልእክተኞች እና ራሱንና ግብረ በላዎቹን ግን ክርስቶሳዊያን አድርጎ ለማሳየት በመሞከር በህዝብ ላይ ብቻ ሳይሆን በራሱ በፈጣሪ ላይም ተሳልቋል ።
መቸም መሪሩን እውነታ መጋፈጥ ሲያቅተን ወይም እንደ ሰው እና እንደ ዜጋ የአገር ባለቤት ሆኖ ለመኖር የሚያስችለንን ፍኖተ ነፃነትና ፍትህ ከለየላቸው ፀረ ሰላም፣ፀረ ፍትህና ፀረ ነፃነት ገዥ ቡድኖች ሥርዓት አስለቅቀን ከህዝብ፣ በህዝብና ለህዝብ የሆነ ሥርዓት እውን ማድረግ ሲያቅተን በዚያው በመጣንበት የድንቁርና እና መከራን የመለማመድ ክፉ ደዌ እንቀጥል ካላልን በስተቀር በፈጣሪ አምሳል በተፈጠረውና ክቡር በሆነው ሰብአዊ ፍጡርነታችን ብቻ ሳይሆን በራሱ በፈጣሪ ላይም እየተሳለቁ መቀጠላቸውን በትእግሥተኞነት ስም እያሳበቡ ማለፍ ትእግሥት ሳይሆን ቦቅቧቃነት (ልክ የሌለው ፍርሃት/የቁም ሙትነት ) ነውና ልብ ያለው ልብ ይበል።
የሃይማኖት ተቋማት መሪዎችም የትንሳኤውን በዓል ምንነት፣ ለምንነትና እንዴትነት በተመለከተ ያስተላለፏቸውን መልእክቶች በአትኩሮት ተከታትያቸዋለሁ። በመሠረቱ እያንዳንዱ ሃይማኖታዊ በዓል የየራሱ መነሻና ታሪክ ስላለው ይህንኑ ለትውልድ የማስተማሩ፣ የማስጨበጡና እንዲጠቀምበት የማድረጉ አስፈላጊነት አያጠያይቅም። የህማማቱንና የትንሳኤውን ምንነት፣ ለምንነትና እንዴትነት በትክክል መረዳታችንና ማመናችን የምናውቀው ግን ከአገራችን ግዙፍና መሪር እውነታ አኳያ ለማየትና ለመረዳት ስንሞክር
ነው።
በሌላ አገላለፅ ጥያቄው የምናስተምርበትንና ቁም ነገር የምናስጨብጥበትን አቀራረብና ይዘት ለዘመናት ከመጣንበትና ከስድስት ዓመታት ወዲህ ደግሞ ፈፅሞ ከደመነፍስ እንስሳት በታች ያወረደንና እያወረደን ያለውን የጎሳ/የነገድ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ቁማርተኞችን ሥርዓት የሚመጥን ነው ወይ ? እንጅ ስለ በዓሉ ሃያልነት ለምን ትናገራላችሁ ወይም መግለጫ ትሰጣላችሁ አይደለም ጥያቄው።
አዎ! ፈታኙ ጥያቄ “በዓላትን ወይም ሌላ አጋጣሚን እየጠበቃችሁ የምትሰጡት መግለጫ ወይም ስብከት የመከረኛውን ህዝብ መንፈሳዊና ዓለማዊ ህይወት ምስቅልቅሉን ያወጡትንና እያወጡት ያሉትን እኩያን የጎሳ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ነጋዴዎች ሴራና ጭካኔ የሚመጥን አይደለምና ይህንን ለማማስተካከል ፈቃደኞች ካልሆናችሁ እና ተግባራዊ አርአያነታችሁን ካላሳያችሁኝ ባዶ ስብከት አትንገሩኝ (do not just tell me, show me)” የሚል የትውልድ ፈተናን ለመወጣት በሚያስችል አቋምና ቁመና ላይ ነን ወይ ? የሚለው ነው ።
መከረኛው ህዝብ ከተለመደ የፖለቲካና የአስተዳደር ብልሹነት አልፎ እጅግ አስከፊ የግፍ ጭፍጨፋ እና የሁለንተናዊ የሰብአዊ መብት ጉስቁልና ሰለባ የሆኑባት አገር የሃይማኖት መሪና አስተማሪ በመጀመሪያው የአጥፊነትና የተጠያቂነት ረድፍ ላይ ያሉትን እኩያን ገዥ ቡድኖችን በግልፅና በቀጥታ ለመገሰፅ የሞራል ልእልና የሚገደው ከሆነ እና በፈጣሪ አምሳል ለተፈጠሩ ንፁሃን ኢትዮጵያዊያን የሚበጅ ሥርዓት እውን ለማድረግ መስቻል የትንሳኤ መገለጫ መሆኑን አስረግጦ ለመናገር የሚሳነው ከሆነ ስለ ምን አይነት ትንሳኤ እንደሚያስተምር ለመረዳት ያስቸግራል። ለምን? ቢባል ክርስቶስ ህማሙን የታመመበትን፣ ስቅላቱን የተቀበለበትን እና በመጨረሻም ሞትን አሸንፎ የተነሳበትን ሚስጥር የሰው ልጆችን ከመታደግ የተጋድሎ ምንነት ጋር ካላያያዝነውና ለዚህም ሰብአዊ ተፈጥሯችንና ባህሪያችን በሚፈቅድልን መጠን አስፈላጊውን አድርገን ካልተገኘን ተግባር አልባ የሆነ እናምናለን ባይነት ፈፅሞ የትም አያደርሰንምና ነው።
አለመታደል ወይም የፈጣሪ እርግማን ሆኖብን ሳይሆን ከረቂቅ የማሰቢያ አእምሮና ከብቁ አካል ጋር የተፈጠርንበትን እጅግ ድንቅ ዓላማ ከፈጣሪ እገዛ ጋር ለማሳካት ያልቻልን ደካሞች በመሆናችን ምክንያት ዛሬም ማነፃፀሪያ በማይገኝለት ፖለቲካ ወለድ የመከራና ውርደት ማእበል ውስጥ እየጎጎጥን የቃልና የተግባር ውህደት ውጤት ስለሆነው ትንሳኤ የተፃፉትንና የተነገሩትን ድንቅ ሚስጥራት እየጠቀስንና እያጣቀስን ከመናገርና ከመንገር አላለፍንም።
የእኛና የአገራችን ትንሳኤ የሚረጋገጠው የመከራና የውርደት ባሪያዎች ያደረገንን እና ጥንብ ነው እያልን የምንጠራውን የጎሳ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ሥርዓት ከፈጣሪ እገዛ ጋር አጥብቆ በመታገልና ወደ ተሻለ ሥርዓት በመሸጋገር እንጅ ድርጊት አልባ በሆነ እግዚኦታ፣ ፀሎትና እናምናለን ባይነት ከቶ አይሆንም። እንዲህ አይነቱን ወለፈንዲነት ፈቅዶ የሚቀበል እውነተኛ አምላክ የለም። እውነተኛው አምላክ ወዲ የሚቀበለው ተግባራዊ በሆነ እና ከመከራና ከስቃይ ወደ ትንሳኤ የሚያሸጋግረውን መንገድ ነው። አስፈላጊውን የአእምሮና የአካል ስጦታ የሰጠን ከፈጣሪነቱ እገዛ ጋር እንደ ሰው ሰውና እንደ ዜጋ የአገር ባለቤቶች እንድንሆን እንጅ ሁሉን ነገር ለእርሱ (ለፈጣሪ) እየተውን መከራ ሲጫነን እግዚኦ እና መከራው የቀለለልን ሲመስለን ደግሞ ራሳችንን ፃድቆች የምናደርግ ገልቱዎች (ደካሞች) እንድንሆን አይደለም።
እጅግ በከፋ ሁኔታ ውስጥ የምንገኝበትን የአሁኑን እኛነት ጨምሮ ከሦስት አሥርተ ዓመታት ፖለቲካ ወለድ የግፍና የመከራ ዶፍ በኋላም የትንሳኤን ምንነትና እንዴትነት የገዛ ራሳችንን ግዙፍና መሪር እውነታ በሚያሳይና በሚመጥን አቀራረብና ይዘት ለመግለፅ አልሆነልንም። ይህንን ግልፅና ቀጥተኛ ሂሳዊ አስተያየት እንደ ፈጣሪ አልባነትና የሃጢአት መንገድ አድርገው የሚቆጥሩ ወገኖች ቢኖሩ አይገርመኝም። ይጣመንም ወይ ይምረረን ትንሳኤን አስመልክቶ በሃይማኖት መሪዎች የተላለፈው መግለጫ (መልእክት) ለዘመናት መሬት ላይ የሆነውንና በአሁኑ ወቅት እጅግ አስከፊ በሆነ ሁኔታ እየሆነ ያለውን ግዙፍና መሪር እውነት ፈፅሞ አይመጥንም። የሃይማኖት መሪ ከዚህ በላይ ምን ያድርግ? የሚል ጥያቄ ሊሰነዘር እንደሚችል እገምታለሁ። ለዚህ ያለኝ መልስ በፈጣሪ አምሳል የተፈጠረ ወገኑ የገዛ ወገኑ ፖለቲካ ጠለድ ጨካኝ ሰይፍ (የግፍ ግድያ) እና የቁም ሞት ሰለባ ሲሆን አስፈላጊውን (የሚችለውን ሁሉ) በማድረግ የማይታደግ የሃይማኖት መሪና ሰባኪ ስለ የትኛው መስዋእትነት፣ ሰማእትነትና ትንሳኤ ነው የሚሰብከንና እመኑኝ የሚለን? የሚል ነው ።
ለመሆኑ፦
· እጅግ ዘመን ጠገቡ፣ ግዙፉና መሪሩ ጥያቄ አምላክ በክርስቶስ አማካኝነት ወደዚህ ዓለም የመጣበት ፣ ሥጋ ለብሶ የተወለደበት ፣ ያስተማረበት፣ የፆመበት፣ በጥምቀተ ባህር የፈጣሪ ልጅነቱን ያገለፀበት ፣ ከስቅላቱ በፊት የቁም ስቃይ የተቀበለበት ፣ ለብልግና እና ለፍፁማዊ ሥልጣናቸው አደጋ እንደሆነ በሰጉ የዘመኑ ገዥዎች ወንበዴ ናቸው ከተባሉ ጋር በመስቀል ላይ የተሰቀለበት እና በመጨረሻ ግን ሞትን አሸንፎ የተነሳበት እጅግ ሰፊውና ጥልቁ ምስጢር የሰው ልጆች ድነትና ደህንነት ጉዳይ እንጅ አሜንና አናምናለን በሚል የመማልና የመገዘት ጉዳይ ብቻ ነው እንዴ?
· ይህንን የገዛ ራሳችንን ግዙፍና መሪር እውነታ ከፈጣሪ እገዛ ጋር ከመጋፈጥ ይልቅ ድርጊት አልባ የሃይማኖታዊ በዓል መግለጫ ( የመሃል ሰፋሪነት ስብከት) የት አደረሰን? የትስ ያደርሰናል?
· በአግባቡ አካፋን አካፋ ብሎ በመጥራት አገርን ምድረ ሲኦል እያደረጉ ያሉ እኩያን ገዥ ቡድኖች የሃይማኖታዊ በዓላትን እየጠበቁ ከሚደሰኩሩልን ዲስኩር አልፈው በንፁሃን ደምና የቁም ሰቆቃ የተጨማለቀ ማንነታቸውን ከክርስቶስ ህማም፣ ስቅለትና ትንሳኤ ጋር እያመሳሰሉ በንፁሃን አማኞች ላይ ሲሳለቁ ቢያንስ ነውር ነው ለማለት መሠረታዊ የሞራል አቅም ያላቸው የሃይማኖት ተቋም መሪዎችንና ሊቃውንትን ፈልገን ለማግኘት ያልቻልነው ለምንድነው?
· ለእኩያን የጎሳ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ቁማርተኞች ሽፋን ሰጭነት (አሻንጉሊትነት) ሲባል በአዋጅ ለተፈጠረው (ለተቋቋመው) አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ተብየ ኮሚሽነርነት ተሰይሞ (ቅብአተ ብልፅግና ተቀብቶ) በማገልገል ላይ የሚገኝ የሃይማኖት ተቋም መሪ የሚያስተላልፈው የእንኳን አደረሳችሁና የመልካም ምኞት መግለጫ ምን ያህል ሚዛን እንደሚደፋ ለመረዳት አያስቸግርም እንዴ?
· አብይንና ካምፓኒውን (ፓርቲውን) በይፋ በማሞገሥና በማወደስ በንፁሃን የግፍ አሟሟትና የቁም ሰቆቃ ላይ የተሳለቁ የሃይማኖት አልባሳት ለባሽ የብልፅግና ካድሬዎችን እሹሩሩ የሚልና ከላይ በተጠቀሰው ኮሚሽን ተብየ አባል ለመሆን የተማፅኖ ደብዳቤ የፃፈ እና በአጠቃላይ በቤተ ክርስቲያኗ ፣ በአገልጋዮቿና በተከታዮች ላይ የደረሰውንና እየደረሰ ያለውን የመከራ ና የውርደት ዶፍ ማስቆም ባይቻላቸውም እንኳ ትርጉም ያለው ሥራ ያልሠሩ የሃይማኖት መሪዎች በዓላትንና ሁኔታወችን እየጠበቁ በሚሰጡት መግለጫ ላይ ጥያቄ ማንሳት የሃጢአት መንገድ ይሆን?
· ሥልጣነ መንበሩ የእኛ ሆኗልና ደስ ይበልን የሚል አይነት እጅግ የወረደ አስተሳሰባቸውን በአደባባይ ሲነግሩን ህሊናቸውን ፈፅሞ የማይጨንቀው የፕሮቴስታንት ሃይማኖት ተቋማት መሪዎች ነን የሚሉ ወገኖች ጋዜጠኞቻቸውን ጠርተው ለሰው ልጅ ድነት፣ ደህንነት፣ ነፃነት ፣ ፍትህ ፣ እኩልነት ፣ ፍቅር፣ ሰላም፣ ወዘተ ሲባል የተከፈለውን መስዋእትነትና በትንሳኤው የታተመውን ወርቃማ ሃይማኖታዊ እሴት እነርሱም እየኖሩት እንደሆነ አስመስለው ሲነግሩን ንፁሃን ወገኖች (ዜጎች) መግልፅ በሚያስቸግር ፖለቲካ ወለድ የመከራና የውርደት ዶፍ ሰለባዎች ሲሆኑ የት ነበራችሁ? ምን አላችሁና ምን አደረጋችሁ? አሁንስ ምን እያደረጋችሁ ነው? ነገና ከነ ወዲያስ? ብሎ መጠየቅን እንደ ድፍረትና ሃጢአት የሚቆጥር እውነተኛ አምላክ አለ እንዴ?
· አዎ እርግጥ ነውእንኳንስ እንደኛ አይነት ከጥቂቶቹ በስተቀር ህዝበ አዳሙ/ሔዋኑ በህሊና ቢስና እኩያን ገዥ ቡድኖች ምክንያት ልክ የሌለው ሁለንተናዊ የድህነት፣ የመከራና የውርደት ዶፍ ሰለባ በሆነበት አገር በአንፃዊነት በዴሞክራሲያዊ እሴቶችና በኢኮኖሚ በልፅገዋል በሚባሉ አገሮችም የወገንን እርዳታ የሚሹ የህብረተሰብ አባላት አሉና ሁሉም የሚችለውን የማድረጉ አስፈላጊነት አያጠያየቀንምና እኛም ይህንኑ ማድረግ ከተገቢም በላይ ተገቢ ነው። በተፈጥሮም ሆነ በሠርቶ አዳሪ ህዝብ ያልቸገራትን አገር የድህነትና የተመፅዋችነት መናኸሪያ ለምን ሆነች ብለው የሚጠይቁትንና የሚቃወሙ ወገኖችን ብቻ ሳይሆን የጎሳ/የነገድ አጥንት ስሌት እያሰሉ በንፁሃን ላይ የግፍ ግድያ ሲፈፅሙና የቁም ሰቆቃ ሲያደርሱ ቆመን እያየን ወይም የመከራና የውርደቱን ምንጭ ለማድረቅ ጥረት ሳናደርግ ምፅዋት እየወረወርንና እየለመን ስንት ዘመን ሆነን? ስንትስ ዘመን ነው በዚህ አይነት እጅግ አስከፊ የመከራና የውርደት አዙሪት ውስጥ እየጓጎጥን የምንቀጥለው? ከመከራና ከተመፅዋችነት ጋር በአሳፋሪ ሁኔታ የመለማመዳችን አሳፋሪ እኛታችን የሚታዘብ ዓለም መሳለቂያና ከንፈር መምጠጫ ሆነን የምንቀጥለው እስከየትና እስከመቸ ነው? ትንሳኤውን ትንሳኤያችን የሚያደርግ ተግባራዊ (የሚጨበጥ) እና ትውልድ ተሻጋሪ ተጋድሎ ሳናደርግ የሃይማኖት በዓላትንና ሌሎች አጋጣሚዎችን እየጠበቅን የምናዥጎደጉደው ስብከትና ዝማሬ የት አደረሰን? የትስ ያደርሰናል? ይህንን አይነት ወለፈንዲነት የሚሰማና የሚባርክ እውነተኛ አምላክ አለ ወይ? እንኳንስ የተሻለ ዛሬንና በጣም የተሻለ ነገን ልንፈጥር እንደ ሰው ሰው ሆነን እና እንደ ዜጋ የአገር ባለቤቶች ሆነን ለመኖር ያልሆነልን ለበዚህ ምክንያት አይደለም እንዴ?
የፈጣሪን እገዛ ሳይዘነጉ ከተገፉት ወገኖች ጋር ሆኖ ግፍንና ግፈኞችን በመቃወም ለሁሉም የሚበጅ ሥርዓተ ማህበረሰብን እውን ከማድረግና ዘለቄታነቱን ከማረጋገጥ የበለጠ የትንሳኤ መንገድና ዋስትና የለም።
ሁሉንም አይነት የሰብአዊና የዜግነት መብቶች በሚጨፈልቅ የእኩያን ገዥ ቡድኖች ሥርዓት ሥር ተለይቶ የሚከበር እውነተኛ የሃይማኖታዊ እምነት መብትና ነፃነት ፈፅሞ አይኖርም። ኖሮም አያውቅም። በዓል እየቆጠርን የምንሰጠው የእንኳን አደረሰንና የመልካም ምኞት መልእክት የዘልማድ ድግግሞሽ እየሆነብን በእጅጉ የተቸገርነውም በዚሁ ምክንያት ነው።
እናም ለዚህ ነው በአማራ ፋኖዎች እና ምክንያታቸውንና ዓላማቸውን ተጋርተው ተጋድሎ በሚያደርጉ ወገኖች ግንባር ቀደም ተሰላፊነት ህልውና፣ ነፃነት ፣ ፍትህ፣ እኩልነት ፣ መተሳሰብ፣ ፍቅር ፣ ሰላምና የጋራ እድገት የሚረጋገጥባትን ኢትዮጵያ እውን ለማድረግ የሚያደርገውን ትግል ገንቢ በሆነ ሂሳዊ ድጋፍ መደገፍ የሞት ወይም የነፃነት ጉዳይ የሚሆነው ።