በሰሜን ኢትዮጵያ፣ አማራ ክልል፣ ከሐምሌ ወር ጀምሮ በተቀሰቀሰው ግጭት በትንሹ 183 ሰዎች መሞታቸውን፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ የመብት ጥሰት ተመራማሪዎቹን ጠቅሶ አስታውቋል። ግድያ፣ ጥቃት እና የመብት ጥሰት እንዲቆምም ጠይቋል።
የመንግስታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብት ቢሮ ቃል አቀባይ ማርታ ሁርታዶ ጄኔቫ ለሚገኙት ጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ በክልሉ እያሽቆለቆለ ያለው ሰብዓዊ መብት እንደሚያሳስባቸው ተናረዋል።
“በኢትዮጵያ አንዳንድ ክልሎች እያሽቆለቆለ ያለው የሰብዓዊ መብት ሁኔታ እጅግ በጣም አሳስቦናል። በአማራ ክልል፣ በኢትዮጵያ ጦር እና በክልሉ ፋኖ ሚሊሻዎች መካከል የተቀሰቀሰውን ግጭት እና፣ ሐምሌ 28 የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተከትሎ ሁኔታው በጣም ተባብሷል። መስሪያ ቤታችን መሰብሰብ በቻለው መረጃ መሰረት፣ ግጭቱ ሐምሌ ወር ላይ ከተቀሰቀሰበት ግዜ አንስቶ ቢያንስ 183 ሰዎች ተገድለዋል።”
አዋጁ ለባለሥልጣናት፣ ተጠርጣሪዎችን ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ ለመያዝ፣ ሰዓት እላፊ ገደብ ለመጣል እና ሕዝባዊ ስብሰባዎችን ለመከልከል ሰፊ ሥልጣን እንደሰጣቸው የሰብዓዊ መብት ቢሮው ቃል አቀባይ ሁርታዶ ገልፀዋል።
ሁርታዶ በዚህ አዋጅ ስር ከአንድ ሺህ በላይ ሰዎች መታሰራቸውን የሚያሳዩ መረጃዎች እንደደረሳቸው ገልፀው “ከታሰሩት ውስጥ አብዛኞቹ የፋኖ ደጋፊዎች ናቸው ተብለው የተጠረጠሩ ወጣቶች ናቸው” ሲሉ አብራርተዋል።
አክለውም “ከነሐሴ ወር መጀመሪያ ጀምሮ በጅምላ የቤት ለቤት ፍተሻ እየተካሄደ ነው። በመሆኑም ባለሥልጣንቱ የጅምላ እስራት እንዲያቆሙ፣ ማንኛውም ነፃነት የመንፈግ ተግባር በፍርድ ቤት እንዲታይ እና በዘፈቀደ የታሰሩት እንዲፈቱ እንጠይቃለን” ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።
VOA