አልማዝ አሰፋ
Wyoming, USA
IMZZASSEFA5@gmail.com
የዛሬ አምስት ዓመት አንተ አብይ እህመድ የኢትዮጵያውያንን ልብ ለመንካት ያሰማኸው የቆንጆ ቃላቶች ጋጋታ እውነተኝነት የሌላቸው ስብእና የተሳናቸው ሂትለር በቦን ጀርመኒ : ሙሶሎኒ በሮም ጣልያን : ከተናገሯቸው መደለያና የጀርመንና የጣልያንን ሕዝቦችን በማጭበርበር አውሮፓን ለሁለተኛው ዓለም ጦርነት ካበቁት ሃሰተኛና የሁለት ሰዎችን የስልጣን ጥማት ከማርካት ያልተለዩ መሆናቸውን መገንዘብ የሚያቅትህ አይመስለኝም:: አንተ ሃቀኛና ታማኝ ኢትዮጵያዊ ነህ በማለት ከሽምግልና እድሜ እስከጮርቃ ወጣት እድሜ ያለው ኢትዮጵያውያን በሙሉ ኢትዮጵያ እንደ አገርና ኢትዮጵያውያን እንደ ሕዝብ በፆም በፀሎት እየለመኑ የጠበቀቱ ሙሴ መጣ ብለው ተስፋ የጣሉብህ መሪ እንዲህ ሳይታሰብ አረመኔነትን እንደተጎናፀፍክ ለመገመት ያስቸግራል::
ይህችም ፀሐፊ ለአምስተ አስራት ዓመታት በኖረችቡት ባእድ አገር ውስጥ ስለተወለደችባት ኢትዮጵያ የፖለቲካ ሁኔታ በሩቅ ሆና ለዘመናት በመከታተል የደረሰችበት ጥያቄ : መቼ ይሆን ይህች ኢትዮጵያ አገርና ሕዝቧ ሰብዓዊነትን የሚያከብር : የጎሳን ልዩኑት የሚያጠፋ : የሰዎችን እኩልነት የሚያንፀባርቅ : አገርን በማልማት ለዘመናት በኢትዮጵያና በሕዝቧ ላይ እስክስታ የሚወርደውን እራብ የሚያስወግድ : ሕዝብ መንግስት መስሪያ ቤት ቢሮ ሄዶ ጉዳዩን ያለጉቦ የሚያስፈፅምበት : የአገሪቱ ኢኮኖሚ በደላላ ሳይሆን በገበየተኛው ፍላጎትና በአቅራቦት የሚመራ : የሕዝቡ ጤንነት ጥበቃ ቅድሚያ የሚሰጥበት : ሰውነትና ኢትዮጵያዊነት እንጂ የትውልድ ጎሳ የማይጠየቅበት አስተዳደር የምታገኘው ነው ነበር:: የዛሬ አምስት ዓመት ይህንን ሁሉ ጠይቀን በየጥያቄው የተቀመጡትን የአዎንና የአይደለምን ሳጥኖች ላይ ምልክት እንድናደርግ ስንመርጥ : አንተ የባሻሻ ጮካ ያሳየህን ምልክት የአዎን ሳጥንን ቼክ እንድናደርግ ነበር:: አይ የዋህነት!! ምን ይደረግ! በኢትዮጵያ ውስጥ መልካም መሪ ለማየት የነበረው ጉጉት ከእኔም ዕድሜ በላይ የረዘመ ስለነበረ : አንተ ስልጣን የተጠማኸው የኦሮሞ ጎሰኛ በስሜታችን ተጫውተህ የኖቤል ተሸላሚ ሆነህ ዝናን አተረፍክ:: ከአጋሮ መንደር : ከደሳሳ አንድ ክፍል ወጥተህ : የ127 ሚሊዮን ሕዝብ መሪ ሆንክ:: በዓለም ደረጃ የታላቋ የጥንቷ የአገሮች ቀዳማዊት : የዓለም የነፃነት ተምሳሌት : የንግስት ሳባና የሰዎች መጀመሪያ የሉሲ አገር መሪ በመሆን ታወቅህ:: ይህን ክብር ያገኘኸው የምድረበዳ ወይም በቅኝ ግዛት ተገዝተው ነፃ የወጡ ሕዝቦች አገር ሳትሆን : የታላቂቱ የለምለሟ (በመሪዎች ቸልተኝነት ደረቅ መሬት ሆነች እንጂ) ኢትዮጵያ ሕዝቦች መሪ በመባል ነው:: ይህንን ሕዝብ ሰላም ከመስጠት ይልቅ : ከአንድ ክልል ጦርነት ወደ ሌላ ክልል ጦርነት በፉከራና በቀራርቶ መሄድህ ካለፈው አመራር ውድቀት ባለመማርህ ምን ዓይነት ደደብና ግብዝ እንደሆንክ በየቀኑ እያሳየህን ትገኛለህ:: በተናገርክ ቁጥር ድክመትህንም ሳታውቅ ታሳውቀናለህ:: በሁሉም የትምህርት መስኮች ያለኝ ዕውቀት ላቅ ያለ ነው በሚል መንፈስ በየአርእስቱ (ህክምናን ጨምሮ) አውቃለሁ ማለት ትወዳለህ:: በየንግግርህ ጥቅሶችና ትረካዎችን በመጥቀስ ችሎታህን ልታረጋግጥልን ትሞክራለህ:: ሁሉንም የማውቅ ችሎታ ያለው ፈጣሪ እንጂ አንድም ሁሉን አወቅ ሊቅ የሆነ የሰው ልጅ የለም:: ራስህን ባታጭበረብር ጥሩ ነው::
ጥቅሶችን በመጥቀስ አገር አይመራም:: ጥቅሶችን በየፓርላማው ስብሰባ ላይ በማንምበልበልህ ጠለቅ ያለ የአገር አስተዳደር ችሎታ አንደ መሪ አለህ ለማለት ያስቸግራል:: እንዲያውም ጥቅስ የሚያበዙ : የእውቀት ጥልቀታቸው እንደ መስኖ ቦይ ነው:: የመስኖ ቦይ የሚይዘው ውሃ እርሻውን እስኪያጠጣ ነው:: ከዚያ በሗላ ቦዩ ውሃ አልባ ይሆናል:: ጥቅስ የሚያበዛ መሪ እውቀቱ እንደ መስኖ ቦይ ጥልቀት የለውም:: እውቀቱ ጥቅስ ብቻ ስለሆነ ያንን ሲያራግፍ ልክ መስኖውን እንዳጠጣ ቦይ ይዘቱ ባዶ ይሆናል:: በጥራዝ ነጠቅ እውቀትህ ተማምነህና በጮካነት የያዝከው ስልጣን እያሳየ ያለው ለተቀመጥክበት የስልጣን ወንበር ብቃት እንደሌለህ ግልፅ እያደረገ ነው::
በጁላይ 2018 ከዋዮሚንግ ስቴት ሚኒያፖሊስ ሚኔሶታ 13 ሰዓት ነድቼ አንተን በሚኒያፖሊስ ታርጌት ሴንትር ለማየትና ለመስማት መጥቼ የኦኔግ ፅንፈኞችን ድርጊት ሳይና የኢትዮጵያ ባንዲራ በስቴጅ ላይ እንዳይውለበለብ በኦኔግ ጠባብ ጎሰኞች ሲጎተት አንዳችም ቅሬታ ሳታሰማ ስትቀር ይህ ሰው ሃይል የለውምና ሃይሉን እንዲገነባ ኢትዮጵያውያኖች ከጎኑ መቆም አለብን የሚል አስተሳሰብ ይዤ ነበር ወደ ዋዮሚንግ የተመለስኩት:: በውስጥም ሆነ በውጭ እንዳለው አብዘኛው ኢትዮጵያውያን ጊዜ ይሰጠው በማለት የግል ድጋፌን ለግሼህ ነበር:: ግን የሙሴነትህን ተስፋችንን ስትረግጠውን ስታኮላሸው ያረጋገጥክልን ኢትዮጵያ ውስጥ ጎሰኛ : ዘረኛ : ፅንፈኛ ያልሆነ ዲሞክራሲን የሚያከብር ታማኝ መሪ ባለንበት ዘመን ማግኘት እንደማይቻል ነው:: አጭበርባሪነትህ : ውሸታምነትህ : ጎሰኝነትህ ከእርኩስነት ጋር ሲጣመሩ አረመናዊነትን ይወልዳሉ:: ማወቅ ያለብህ አንተ ለሰው ልጆችና ለሰው ሕይወት ደንታ የሌለህ መሆንህና : በዓለማችን ውስጥ በአረመኔነታቸውና በጭካኔነታቸው ታሪክ ከሚፅፋቸው አንዱ እንደምትሆን ነው:: የሚያሳዝነኝ ባልፈፀሙት ወንጀል ልጆችህና የልጆችህ ልጆች የዚያ የአረመኔው አብይ አህመድ ዝርያዎች ተብለው በታሪክ ውስጥ መጠቀሳቸው ነው:: ይህንን ስያሜ ለዝርያህ መተው ያስኮራሃል?
መረዳት ያለብህ አንድ ነገር አለ:: 2018 የተናገርካቸውና የለፈለፍካቸው አነጋገሮችና ዛሬ ያለህበት የፖለቲካ ሁኔታ 180 ዲግሪ ተቃራኒዎች ስለሆኑ ለማስተካከል የኦዴድ ብልፅግና ፓርቲንና የኦኔግን የፖለቲካ ምኞቶች ማግባባት ያስፈልግሃል:: ግን ይህንን ለማድረግ ከኦዴድ ብልፅግናና ከኦኔግ ቁጥጥር ውጭ የመሆን ችሎታ እንዳለህ ማረጋገጥ ይኖርብሃል:: ይህንን ለማሳካት የፖለቲካ ፅናት አለህ ብዬ አላስብም:: ምክንያቱም ስልጣን ላይ ለመቆየት የምትችለው እነ ሽመልስ አብዲሳንና የኦዴድን ፅንፈኞች በመያዝ ብቻ ነው:: እስቲ ፅናቱ ካለህ እነሽመልስ አብዲሳን ከነቤተሰቦቻቸው ሰርቀው ያከማቹትን ሀብት ያለአግባብ ነው ብለህ ውረስ:: እስቲ አዳነች አበቤን የከተማ አውቶብሶች እገዛሉሁ ብላ የሰረቀችውንና ያሰረቀችውን የሕዝብ ገንዘብ ላይ ቁጥጥር አድርግ:: ስለሙስና ስታወራ አዝማሚያህ ለሕዝብ ጆሮ ፍጆታ እንጂ ሙስናንና የባለስልጣናትን የስልጣን ብልግና ለማቆም እንዳልሆነ ያስታውቃል:: ያንተ ልምድ የሚያሳየው የምትናገረውና የምታደርገው ተቃራኒዎች መሆናችውን ነው::
ዛሬ በኢትዮጵያ የአስተዳደርና የአመራር ዘንግ ይዘህ እየሰራህ ያለኸው መለስ ዜናዊና የባንዳ ልጆች ስብስብ የሆነው ወያኔ የጠነሰሱትን የኢትዮጵያን አገራዊ ማንነቷን ማርከስ : የሕዝቧን አንድነት ማፍረስ : ጥንታዊ የነፃነት ታርኳን ማጠልሸት ነው:: የሚገርመው አንተና በዙሪያህ የሰበሰብካቸው የኦዴድ ብልፅግና ፓርቲ አባላት የኦሮሞን ጎሳ ተበዳይ አስመስላችሁ ቱሉቱላችሁን እየነፋችሁ ፅንፈኝነትን የምታራምዱ በስልጣን ተቀምጣችሁ የአገሪቱን ሀብት ከድሃው ጉሮሮ ፈልቅቃችሁ የምትሰርቁ ስግብግብ ጥቅመኞች ናችሁ:: የጎሣ ጥላቻ ፖለቲካችሁን እንደዱር እሳት በሕዝብ መሃል ስታቀጣጥሉ እናንተም የእሳቱ ተጠቂ መሆናችሁ የተረጋገጠ ነው:: ሕዝብን ክማገዳደል በተጨማሪ በክርስትና ሃይማኖት አንድ ተመሳሳይ ክፍል (SECT) ተከታዮች በመሆን ጥንታዊ የኦርቶዶክስና የእስልምና ሃይማኖቶችን አጥፍታችሁ የራሳችሁን የሃይማኖት ክፍልንና በተመሳሳይ መንገድ የኢየሱስ ክርስቶስን ምሳሌነትን የሚያወሩ ግን የማይከተሉ በእየሱስ ክርስቶስ ስም የሚነግዱ ገንዘብ ወይም ሞት የሚሉ ውሸታም ሐዋርያቶች የበዙበት እምነቶች እንደ አሸን እንዲፈሉ የምታራምዱ ፀረ-እግዚአብሔሮች ናችሁ:: ገንዝብ ከአማኝ ሰብስባችሁ ማንሽን ገንቡ : የምቾት መኪናዎች ግዙ : ከአገር ውጭ ንብረት አካቡ የሚል ትምህርት የትኛው መፅሐፍ ቅዱስ ላይ ነው የሚያስተምረው? በሰይጣን የተያዘውን በካራቴ ምቱና ሰይጣኑ ይለቀዋል የሚል ትምህርት የትኛው መፅሐፍ ቅዱስ ላይ ነው የሚያስተምረው? የኦርቶዶክስ ሃይማኖትን ውድቀት ስበኩ የሚል ትምህርት የትኛው መፅሐፍ ቅዱስ ላይ ነው የሚያስተምረው? የኦርቶዶክስና የእስልምናን እምነት ቤቶች እቃጥሉ አፍርሱ አስፈርሱ የሚል ትምህርት የትኛው መፅሐፍ ቅዱስ ላይ ነው የሚያስተምረው? የአንተ አስተዳደር የተያያዘው እነዚህን የንዋይ ፍቅር ያሰከራቸውን ውሸታም ሃይማኖተኞችን በመጠቀም የማሰብና የማስተዋል ችሎታ ወይም ብስለት የሌላቸውን ገለባዎችን በማብዛት ተዋህዶ ኦርቶዶክስንና የእስልምናን ሃይማኖቶችን ማቆርቆዝና ማጥፋት ነው:: ምክንያቱም የኢትዮጵያን ማንነትና ህልውና ለመለወጥ ተዋህዶ ኦርቶዶክስንና የእስልምናን ሃይማኖቶች ማኮላሸት ተቀዳሚ ድርጊት መሆን አለበት:: ለዚህ ስውር እጀንዳ መሸፈኛ የምትሰጠው ማባበያ የውስጡንና የውጩን ሲኖዶሶች አስታርቄ ተዋህዶ ኦርቶዶክስን አንድ እንዲሆኑ ያደረኩኝ ሰው ስለሆንክ ይህ ክስ አይገባኝም ነው::
ውድ እብይ:- ማንነትህን በእርግጥ ለማየት ከፌብርዋሪ 2018 ጀምሮ እስከ 2020 የተናገርካችውንና የለፈለፍካቸውን በምስል አይተህ በፅሁፍም አንብብና ሰው ከሚነግርህ አንተው ራስህ ስለማንነትህ በእርገጠኝነት ታዝበህ ምንያህል ውሸታም እንደሆንክ ማየት ትችላለህ:: አብዬ:- ቢቻልህኮ በቁም ቆዳችንን ልትገፍ ትችል ነበር:: ሰዎች እንዋሻለን:: ውሸትም በመጠኑና ሕይወት የማያጠፋ ሲሆን ጥሩ ነው:: እንዳንተ አገር እመራለሁ የሚል ሰው እንዲህ ዓይነት ነጭ ውሸት ያለአፍረት ተናግሮ : ድርጊቱ 180 ዲግሪ የንግግሩ ተቃራኒ የሆነበት መሪ በዓለም ታሪክ ውስጥ ተፈልጎ የሚገኝ እይመስለኝም:: የሚደንቀኝ አማኝ ነኝ ስለምትል : እንዴት አድርገህ መፅሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረውን ከሕይወት ማጥፋትና ሰውን ከማሰቃየት ጋር ታስታርቃለህ?
ለማስታወስ ያህል አንድ ንግግርህን እዚህ ልጦቁምህ::
“በሃሳብ ብልጫ ዓላማን የማሳካት እውድ በተፈጠረበት በመገዳደል የፖለቲካን ዓላማ ማሳካት አይቻልም::” ~ ጠቅላይ ሚኒስቴር ዶ/ር አብይ አህመድ
ከላይ የተናገርከው የምታምንበት ሃቅ ከሆነ ታዲያስ ትላንትና በትግራይ ክልል ያካሄድከውና : ዛሬ በአማራ ክልል ውስጥ የምታካሄድው ጦርነት ውስጥ ለምን ገባህ? ከላይ ያልከው እውን ነው ብለህ ካመንክ ተቃዋሚዎችህን ማሰርና መግደልን የፖለቲካ ዓላማህ ማሳኪያ ለምን ታደርገዋለህ? አንተ ስልጣን እንደምትፈልግና በማንኛውም መንገድ ዙፋኑ ላይ መወዘፉ ግብህ መሆኑን ሁላችንም እንታዘባለን:: መወዘፉን ተወዘፍ:: መቆየቱንም ቆይ:: ግን እውነት እውነቱን ተናግረህ ብትወዘፍና ብትቆይ አይሻልም?
ይህችን ዙፋን ለመጠበቅ የምትችለው ተቀዋሚዎችህን በማሰር : በማጉላላትና በመግደል መሆኑን እያወቅህ ለምን “በሃሳብ ብልጫ ዓላማን የማሳካት እውድ በተፈጠረበት በመገዳደል የፖለቲካን ዓላማ ማሳካት አይቻልም::” በማለት ትዋሸናለህ? በ2018 በኢትዮጵያና በተለይ በጁላይ 2018 በእሜሪካ እየዞርክ በአሜሪካ የምንኖረውን ዲያስፖራዎች ከሗላችን እንዳስገባህብን አሁን እትችልም:: በተለይ የኦሮሞ ጎሰኞችና ፅንፈኞች በተለያየ ውንጀላ ሲያኳስሱህ አማራ ኢትዮጵያውያን የሰጡህን ድጋፍ ዛሬ እረስተህ አማራ ኢትዮጵያውያንን ለመጨቆን የወሰድከው አላስፈላጊ የጦርነት እርምጃ ማንነትህን እያጋለጠ ይገኛል:: መርሳት የሌለብህ ያለአማራና ያለደቡብ ሕዝቦች ድጋፍ ዛሬ ያለህበት ደረጃ አትደርስም ነበር:: ግን ለሁለቱም ሕዝቦች ውለታ የከፈልካቸው አማራ ላይ ጦርነት ማወጅ : ደቡብ ሕዝብን በትንንሽ ክልሎች ከፋፍለህ ኢትዮጵያዊነትን ማዳከምና ትንንሽ ክልሎች ፈጥረህ ለኦሮሞ የወደፊት መስፋፋት ማመቻቸት ሳይሆን አይቀርም:: አዎን! አሁንም ውሸትህን የሚቀበሉ አሉ:: ውሸትህን የሚቀበሉ ሁለት ዓይነቶች ናቸው:: አንደኛው ዓይነት የኦሮሞ ጎሳ ፅንፈኞች ሲሆኑ : ሁለተኛው ዓይነት : የግል ጥቅም ፈላጊዎች ናቸው:: በእርግጥም በሁለተኛው ዓይነት ውስጥ ከሁሉም ጎሳዎች ይገኛሉ::
አቢይ አህመድ:- ባለፈው ሶስት ዓመታት በኢትዮጵያ ላይ ያመጣኸው የጥፋት ደመና አደጋ ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ ነው:: ወያኔ ቋንቋን መሰረት ያደረገ ክልላዊ አሰላለፍ ፈጥሮ ልዩነቶችን ቢያመጣም : በስልጣን ለመቆየት ኢትዮጵያ እንደ አንድ አገር ህልውናዋ ተጠብቆ እንድትኖር : ሕዝቦቿ የትኛውም የኢትዮጵያ ክልል ሄዶ በመኖር ለመስራት ቤተሰብ ለማፍራትና ንብረት ለማዳበር ደህንነትን ማስጠበቅና የዜግነትን መብት ከጫፍ ወደ ጫፍ ማስከበር እስፈላጊ መሆኑን ተገንዝቦ እስፈፅሟል:: የአንተ ኦዴድ ግን አገሪቱን የኦሮሞ ብቻ በማስመሰል : ኦሮምኛ የማይናገር የአገሪቱ ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃ ዜጋነት እንዲሰማው የሚያደርገው ጥረት ለማንኛውም የኢትዮጵያ ዜጋ : እናንተን የኦሮሞን ፅንፈኞች ጨምሮ : በሰላም እንደማያኖረው መገንዘብ ያስፈልጋችሗል::
ሚሊየን ሕዝብ መግደል ይቻላል:: ግን ከሕዝብ የተጣላ አስተዳደርና መሪ ዘለቄታ የለውም:: ከሕዝብ የተቃረረ መንግስትና መሪ የመንፈስ ዕረፍት ሳያገኝ እየፈራ : መሳሪያን ተገን ባደረጉ በታጠቁ ዘበኞች ተጠብቆ መኖር ዕድሉ ነው:: ይህም ከእስር ቤት የሚለየው ከሕዝብ ሳትቀላቀል ተለይተህ መኖርን ነው:: እስኪ የኦሮሞ ክልል ፕሬዝዳንትነትን አሳልፎ በመስጠት አንተን ለዚህ ያበቃህ ለማ መገርሳ እንዴት በሰላምና በነፃነት እንደሚኖር ተመልከት:: ስልጣንን በአግባብ ካልተጠቀሙትና ሕዝብን ከማቀፍ ይልቅ የሕዝብ ማሰቃያ ካደረጉት : አመራር ላይ ያሉትን ምቾት ይስጣቸው እንጂ ሰላምና ነፃነት አሳጥቷቸው እንቅልፍ ነስቷቸው የከንቱነት ስሜት ያሳድርባቸዋል:: ያ ደግሞ እንደዚያ ዓይነት መሪዎችን የጤንነት ጉድለት ያሳድርባቸዋል:: ጤንነት በተለይ በፀረ-ሕዝብ ድርጊታቸው : የማስተዋል ችሎታ የጎደላቸው መሪዎች : ተቃዋሚዎቻቸውን ማሰር : ሰብዓዊ መብቶችን መግፈፍ : ስዎችን ማሰቃየትና መግደል የአስተዳደራቸው ባህሪ ያደርጉታል:: የአንተም አመራር ይህንን የጭካኔ ሂደት የአገር ህልውናና አንድነት ለማስጠበቅ በሚል ምክንያት እያካሄደ ይገኛል::
ኧረ ለመሆኑ አቢይ አህመድ የኢትዮጵያን አገር ወይስ የኦሮሞ ብሔር እየመራህ ነው? በእርግጥ የያዝከውን ስልጣን አንተ ትቆጣጠረዋለህ ወይስ በኦሮሞ ብልፅግና ፓርቲ ውስጥ ተሰግስገው ያሉ ጠባብ የኦሮም ጎሰኞች አንተን እየተቆጣጠሩ ነው? በኦሮሞ ክልል አመራር ውስጥ የሚታየው የአስተዳደር ብልሹነት : ህገወጥነት : ፍትሕ መንፈግ : ሕገ መንግስቱን ያለማክበር : ወያኔን ማረኝ የሚያሰኝ ነው:: እንዲህ ዓይነት አይን ያወጣ ጎሰኝነትና ጎጠኝነት በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ታይቶ የሚታወቅ አይመስለኝም:: አማራ ኢትዮጵያውያንን ከተወለዱበትና ካደጉበት መሬት በጎሳ ስም መሬታቸውን ንብረታቸውን ተቀምተው ባዶዋቸውን ከኦሮሞ ክልል ሲባረሩ : የሁሉም ኢትዮጵያውያን መሪ ብትሆንና ሰባዊነት ቢሰማህ ኖሮ የለማራ ኢትዮጵያውያን ስቃይ ተሰምቶህ ሽመልስ አብዲሳን ከኦሮሞ ክልል ፕሬዝዳንትነት ባስወገድከው ነበር:: ከተማ በማሽሻል ስም አዲስ አበባ ዙሪያ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች በአረብ አገር ተሰድውና በአገራቸው ጉልበታቸውን ሸቅለው የሰሯችውን ቤቶች አማራጭ መኖሪያ ሳይዘጋጅላቸው በልማት ስም የኦሮሞ ክልል ሲያፈርስና ሜዳ ላይ ሲጥላቸው ይህ አግባብ አይደለም ብለህ ድምፅህን አሰምተሃል? አላሰማህም:: አታውቅም እንዳትባል በስርህ ያሉት በገሃድ በሕዝብ ላይ የሚፈፅሙትን ግፍ በሶሻል ሚዲያዎች ሳታየው አትቀርም:: ግን የኦሮሞ ጎሰኞችና ፅንፈኞች ስግብግብነትና ሁሉንም ነገር በተረኛነት መንፈስ የራሳቸው ለማድረግ መራሯጣቸውንና በአማራ ኢትዮጵያውያን ላይ የሚፈፅሙትን ግፍ ሲተች የኦሮሞ ጥላቻ ነው ብለህ ለመናገር ጊዜም አትፈጅም:: አዎን! ሚስትህ አማራ ኢትዮጵያውያን ነች:: በዚህ ምክንያት አማራ እንዴት እጠላለሁ ልትል ትችላለህ:: አማራ ኢትዮጵያውያን የምትጠላው ከስልጣን ሊያስወርዱኝ ስለሚችሉ በሚል ፍርሐት ነው:: ጠቅላላ የኦሮሞ ብልፅግና ትኩረቱ የኦሮሞ ሕዝብ ከተቀሩት የኢትዮጵያ ወንድሞች ጋር በሰላም ኖሮ : በኢኮኖሚ እንዲያድግ ሳይሆን : ከአንዱ ክልል ወደ ሌላ ክልል የእርስ በርስ ግጭት እየፈጠራችሁ እንደወያኔ ከትውልድ እስከትውልድ የኦሮሞ ወጣቶችን ለጦርነት መመልመያ ለማድረግ ነው:: ለኦሮሞ ሕዝብ የምትጨነቁ ቢሆን በአማራ ላይ ጦርነትን ከማንሳት በቦረና የተከሰተውን ርሀብ መግታት በጣራችሁ ነበር:: ለዚህ ነው እንተ የመላው ኢትዮጵያውያን መሪ ወይስ የኦሮሞን ፅንፈኝነት አዳብረህ ለሚቀጥሉ መቶ ዓመታት ኦሮሞን የኢትዮጵያ የበላይ ለማድረግ የሚያስቡ ዘረኞች እየመራህና እየተቆጣጠርክ ወይስ እየተቆጣጠሩህ ነው? የሚል ጥያቄ ማቀርብልህ::
ጋዜጠኛን ማሰር መግረፍ : የኦሮሞን ተረታዊና የውሸት ትረካ በማስረጃ የሚያከሽፉትን የታሪክ እዋቂዎችንና ተመራማሪዎችን ማፈን : አማራ ኢትዮጵያውያንን ወደ አዲስ አበባ አትገቡም በማለት ነጮች በደቡብ አፍሪካውያን ጥቁሮች ላይ የፈፀሙትን አፓርታይዳዊ ፖሊሲና ነጭ ዘረኛ አሜሪካኖች በጥቁር አሜሪካኖች ላይ ይፈፅሙት የነበረውን ዘረኝነት በኢትዮጵያ ውስጥ የኦሮሞ ክልል አመራር ሲያካሄድ አንተ መሪው ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ አታውቀውም አልሰማህም ማለት እጅግ ለማመን ይከብዳል::
በተለይ በአማራ ኢትዮጵያውያን ላይ የተነሳው የኦሮሞ ፅንፈኞች ጥላቻንና የጦር ዘመቻን አማራ ኢትዮጵያውያን የዘር ማጥፋት ነው ቢሉ አይደለም ለማለት አጥጋቢና አሳማኝ ምክንያት ሊኖርህ አይችልም:: ፍኖተ ሰላምን በድሮን: ቡሬን በመድፍ የራስን ሕዝብ መምታት : የሲርያው ባሽር አልአሳድ በ2013 ደማስከስ ከተማ እጠገብ ባለው ጉታ በሚባለው ሰፈር በንፁሃን ኗሪዎች ላይ ከጣለው ቦንብ አይለይም:: እንዲያው መለስ ብዬ እንደገና ልጠይቅህን “በሃሳብ ብልጫ ዓላማን የማሳካት እውድ በተፈጠረበት በመገዳደል የፖለቲካን ዓላማ ማሳካት አይቻልም::” ያልከውን በእማራ ክልል ያነሳኸውን ጦርነት : በአማራ ኢትዮጵያውያን ላይ የአማራን ዘር ለማጥፋት ነው ከሚል እምነት ጋር እንዴት ታስታርቃለህ?
በነፃ ሃሳብን የመናገርና የመፃፍ መብትን በመቃወም ጋዜጤኞችን ማሰቃየት : ማጉላላት : ማሰርና መደብደብን ማቆም ካልቻልክ ስለዲሞክራሲ ስትልፈልፍ የነበረው በዲሞክራቲክ ስርዓት ላይ አምነህ ሳይሆን በማስመሰል ስልጣን ለመቆናጠጥ ሕዝብን ማሞኛ ዘዴህ ነበር ያሰኛል:: የኦሮሞ ክልል እስተዳደር : ኦሮሞ ያልሆኑ ኢትዮጵያውያንን ከኖሩበት አካባቢ በደሃ እቅማቸው ያላቸውን ገንዘብ አውጥተው የገነቧቸውን ቤቶች በማፍረስ ከ”ሸገር” ከተማ ሲያባርራቸውና ልጆች በጅብ ሲበሉ እንደ ጠቅላይ ሚኒስትር አላየሁም : አልሰማሁም ካልክ የምታይበትንና የምታነብበትን ዓይንና የምትሰማበትን ጆሮ ማስመርመር ግድ ሳይልህ አይቀርም:: ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ ስትል የነበረውም የኦሮሞ ክልል አስተዳደር በልዩና በደህንነት ሀይል ተጠናክሮ የፌደራል መከላከያንም በጠባብ ኦሮሞ ጎሰኞች መቆጣጠር እስክትችል ድረስ ነበር ያስብላል:: ግን ሰሞኑን በአማራ ክልል ጦርነት ስታንሳ : መብቴ አልተከበረም : ማንነቴ ተገፏልና መብቴ ይከበር : እንደዜጋ አልታየሁምና የዜግነቴም መብት ይጠበቅልኝ : ተወልጄ ያደኩበትን : ኑሮዬን ከማካሄድበት የኢትዮጵያ ክልል ኦሮሞ እይደለህም ተብዬ በአማራነቴ ባዶ እጄን ተሰድጄ በገዛ አገሬ ተበድያለሁ ፍትሕ ይሰጠኝ ያለን ኢትዮጵያውያን ፅንፈኛና ወንበዴ እያልክ : በደሃው ሕዝብ ስም የተቋቋሙትንና በሕዝብ (የአማራን የኦሮሞንና የትግራይን ሕዝብ ጨምሮ) ገንዘብ የሚተዳደሩትን ሚዲያዎችንና የሕዝብ ተወካዮች (የሙታኖችና የበድኖች ቢባል ይሻላል) ተብሎ የሚጠራውን ፓርላማ በመጠቀም : ኢሰባዊ ድርጊትህን ተገቢ ለማስመል መጣርህ : ካለፉት ውዳቂ መሪዎች መማር አለመቻልህ ውድቀትህን እንደሚያመጣ ልትረዳ አልቻልክም:: የሚገርመው ባለፉት 5 አመታት የስልጣን ዘመንህ እንዲህ አገሪቱን የሚያምሰውና የአንድነት ኩታዋን ለመበጣጠስ የሚፈልገውና እየሰራ ያለው አገር አጥፊው ድርጅት የኦሮሞ ክልል ብልፅግና ፓርቲ መሆኑን አንድም ቀንም ልታይ አለመ ቻልህ : የኢትዮጵያና የኢትዮጵያዊያን መሪ ሳትሆን የኦሮሞ ብሔር መሪ ነው የሚለውን ግምትና አሉባልታ እውን ያሰኛል:: ይህም ለውድቀትህ አዘገጃጀት አንዱ ቅመማ መሆኑን ልትረዳም አልቻልክም::
ታሪክ የሚያስተምረን ነገር የሕዝብ ክፍልን በማሰር በማንገላታት በማሰቃየትና በመግደል ለተወሰነ ጊዜ ስልጣን ላይ መቆየት ይቻል ይሆናል:: እድሜ ልክ በሕዝብ ስቃይ እየተሳለቀና እየሳቀ የሚዘልቅ መሪ ወይም አስተዳደር የለም:: ከሕዝብ የተጣላና በሕዝብ የተጠላ አስተዳደር ውስጥ ያሉ ግለሰቦች ሰላማዊ እንቅልፍ እንደማይተኙ የተረጋገጠ ነው:: 80 ጎሳዎችን ጨቁኖ ዘርፎ አሰቃይቶ ና የበላይ ሆኖ በሰላም እለማለሁ እድጋለሁ ብሎ የሚያስብ ጎሰኛ አስተዳደር ካለ የሚያስብበትን ጭንቅላት ጤናማነት ያስጠይቃል::
ስለዚህ ጠቅላይ ሚኒስቴር ዶ/ር አብይ አህመድ ኢትዮጵያ ላይ በመሪነት እቆያለሁ ካልክ በመጀመሪያ ለዚህ ያደረሰህን የበፊቱን ኦዴድ የዛሬውን ብልፅግና ፓርቲ አመራሮችን ከጎሳ ጠባብነት ወደሰፊው ኢትዮጵያዊነት ማምጣትና ሰባዊነት የሚሰማቸው ሰዎች ማድረግ ይጠበቅብሃል:: የኦሮሞ ብልፅግና ፓርቲ በኢትዮጵያውያን ላይ የሚሰራቸውን ግፎች ማስቆም ዋነኛው ግዴታህ ማድረግ አለብህ:: አማራ ኢትዮጵያውያን በምንም ዓይነት ኢትዮጵያን ያለሌሎች ጎሳዎች ተሳትፎ በተለይ ያለኦሮሞና ትግራይ ኢትዮጵያውያን ተሳትፎ ብቻቸውን የመሩበት ጊዜ የለም:: አማራን ለማጥቃት በኦሮሞ ዘረኞችና ጎጠኞች የሚሰጠው የሃሰትና የፈጠራ ትረካን ከማስተጋባት ይልቅ : ይህንን የውሸት ትረካ ማስቆም የመሪነትህ ግዴታ መሆኑን ጠንቅቀህ መረዳት አለብህ:: አለበለዚያ ውድቀትህ ይፋጠናል::
ኧረ ለመሆኑ መቼ ነው አማራ በአማራነት ኢትዮጵያን የመራው? የዛሬው የኦሮሞ ብልፅግና ፓርቲ የሚሰማውን የተረኝነት ስሜት ከወያኔ በስተቀር ማንም ጎሳ አሳይቶ አያውቅም:: ወያኔም የትንሽ ቡድን አመራር እንጂ ወያኔ ስልጣን ላይ ስለነበረ ተራው የትግራይ ተወላጅ አንዲት ቅንጣትም አላለፈለትም:: ወያኔ ትግራይ ኢትዮጵያውያንን የጥቅሙ መነገጃ አደረገ እንጂ ከችግር አላወጣውም:: እንዲያውም ወጣቱን አላስፈላጊ ጦርነት ውስጥ ከቶ አስጨረሰው:: አሁንም ይህ የተማሩ መሃይሞች ስብስብ የኦሮሞ ብልፅግና ፓርቲ ለኦሮሞ ሕዝብ የቆመ ሳይሆን ስልጣን ላይ ላሉት በስርቆት ሐብት የሚያከማቹበት መንገድ ነው:: አንተም እንደመሪ ፓርቲህ የሌቦች ክምችት እንደሆነ ደጋግመህ ተናግረሃል:: ግን ሌቦችን ማስወገድ አልቻልክም:: ለምን አልቻልክም? በኢሐደግ ጊዜ ወያኔ እንኳን በጎሳ ነጥሎ የትግራይ ተወላጅ ብቻ የሚል ሗላቀርነትን አላሳየም:: ፖለቲካውን የተስማማ ሁሉ የግለሰቡ ጎሳ ላይ ሳያተኩር በስርቆት ሀብት የማከማቸት ዕድል ይሰጥ ነበር:: የዛሬው የኦሮሞ ብልፅግና ፓርቲ በተረኝነት ስሜት ተነፍቶ ስርቆቱን እንኳን የጥቂት የኦሮሞ ባለስልጣናት በዋነኛ ደረጃ ሽመልስ አብዲሳና ቤተሰቦቹ : አዳነች አቤቤና ጏደኞቿ ያለሃፍረት ሀብት ማከማቸት ላይ ተሰማረዋል:: ይህንን አላውቅም ካልክ ኢትዮጵያን እመራለሁ አትበለን:: ወይስ ልክ ስልጣን ላይ እንደመጣህ ሰሞን ወያኔ ቢሮውን ከፍቶ እንደሚያስገባህ እንደነበር እነዚህ የኦሮሞ ፅንፈኞች ይቆጣጠሩህ ይሆን? ስልጣኑ በእጅ ውስጥ አይደለም? ስልጣን እንደሌለህና የጠቅላይ ሚኒስቴር ሹመትህ ለይስሙላ ከሆነ ቁርጡን ንገረንና ለአንተም ነፃነት እንታገልልህ:: ስልጣኑ ያንተ ከሆነ እነሽመልስ አብዲሳ : አዳነች አቤቤና የተቀሩት የብልፅግና ፓርቲ አባላት ለውድቀትህ ምክንያት እንደሚሆኑ ልግለፅልህ:: በጠባብ ጎሰኝነት የተነፉ ሰዎች አቅፈህ ኢትዮጵያን ታሻግራለህ ማለት ዘበት ነው:: የሚያስፈራው በዚህ የጎሰኝነት ነቀርሳ የተለከፉ የኦዴድ ሰዎች እንደ 1994 ርዋንዳ ኢትዮጵያን እልቂት ውስጥ እንዳይከቷት ነው::
ጋዜጠኛ ማፈን መደብደብ ማስፈራራትና ለአገር አንድነት የቆሙትን የጦር መሳሪያ ያልያዙትን በብእርና በወረቀት የሚታገሉትን : በቃላት የሚተነትኑትን አፍኖ ማሰር ዲሞክራሲንና ነፃ ሃሳብን የመግለፅ መብት የሚጠብቅና የሚያከብር ሳይሆን የሕዝብን እምነት ማጣቱን የተገነዘበ የስልጣን ሱስ ያጠቃው ደካማ መንግስታዊ አስተዳደር ነው:: የአንድ ጎሳን የበላይነት ምኞት ለማሳካት የሚሯሯጥ አመራር የአገርን አንድነት ያስቀድማል ማለት ያስቸግራል:: የኦሮሞ ክልል አመራር በኢትዮጵያና በኢትዮጵያውያን ላይ የያዘውንና ያለመውን የኦሮሞ የበላይነት ምኞትን አንተ ዶ/ር አብይ አህመድ ትክክል እንዳልሆነና ለኢትዮጲያ አንድነት እንቅፋት መሆኑን ግልፅ አድርገህ ካላስቆምክ የወደፊቱ ጉዞ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን የኦሮሞ ጠባብ ጎሰኞችን ጨምሮ የጨለማና የስቃይ እንደሚሆን አያጠራጥርም:: ዛሬ አማራ ክልል የሚካሄደው ጦርነት ነገ ኦሮሞ ክልል ተስፋፍቶ የአንተን አመራር ውድቀት እንደሚያመጣ ተገንዝበህ ሰላም እንዲሰፍን ብትጥር ይሻላል:: ትምክተኝነትና ማንያህለኝነት የውድቀት ምልክቶች ናቸው:: ሰዎች የሚጠሉህ የተናገርካቸውና ያደረካቸውና የምታደርጋቸው ባለመጣጣማቸው እንጂ በኦሮሞነትህ አይደለም:: ሕዝብ አንቅሮ ሲተፋህ ውጤቱ ውድቀትህ ነው::