ጠ/ሚ አብይ አህመድ ፣ ከረመዳን ፆም ቀድመው ፣ አዲስ ካርታ መዘዋል ። ጆከርን ። በአዲስ የፖለቲካ ቁማር ጫዎታ ብቅ ብለዋል ። ፆሙ በመግባቱ ዛሬ አላህ ልብ እንዲሰጣቸው እንለምንላቸዋለሁ ። መካሪ የሌለው ንጉሥ ሆነዋልና !
” የካርታ ፖለቲካ ወይም ፖለቲካዊ ፖከር ” በሚባል የማዘናጋት ፣ የማሳሳት ፣ ግልፅ ሐሳብን ያለማሳወቅ ፣ ዕድልና ብልጠትን አዋህዶ ቁማሩን የመጠቅለል ወይም የመብላት ጫዎታ ጠቅላያችን ብቅ እንዳሉ ፣ በትግራይ እና በአማራ ክልል ለመተግበር የፈለጉት ፖለቲካ በግልፅ የሚያሳብቅ ሆኖ አግኝቼዋለሁ ። የዛሬው ፖለቲካዊ ቁማር ጫዎታ በየጊዜው ከተሰጡን አጀንዳዎች ሁሉ ረቀቅ ያላለ እንደሆነም ከህዝቡ የተሰወረ አይደለም ። ካርታ ጫዎታ ገንዘብን አንድ ሰው ጠቅልሎ የሚወስድበት ፣ የአቋማሪና የቆማሪ ጫዎታ እንደሆነም ከህዝብ የተሰወረ አይደለም ። በዚህ የወገነ የፖለቲካ ቁማር ፣ ቆማሪዎቹና አቋማሪው የሚከብሩበት እንደሆነ ህዝቡ ያውቃል ። ( አሁን በዚች ሰዓት ከኢትዮጵያ ህዝብ ሥንት ፐርሰንቱ እንደሚወዳቸው የመረጃ ሹማቸውን እሥቲ ይጠይቁ ። እውነቱን ከነገራቸው ካልደነገጡ ራሳቸው ሌሎችን የተሳደቡበት ሥድብ ለራሳቸው እንደሚሆን ከወዲሁ ይገነዘቡት ። )
የእኛው ፣ የዛሬው ፖለቲካዊው ፖከር “ ስፔድስ “ ከተሰኘ የካርታ ጫውታም ፍፁም የተለየ ነው ። ይኽ ጫዎታ በ1930ዎቹ በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የተፈለሰፈ የካርታ ጫውታ ነው ። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በወታደሮች የሚዘወተር ጫወታ እንደነበር ይታወቃል ።
ዛሬ እና አሁን ዓለም እየተጫወተ ያለው ጫዎታ ግን ፖከር ነው ። ይኽ ጫዎታ በመጀመሪያ የተፈለሰፈው በቻይና ነው ። በ9ኛው ክ/ዘ ።
ዘመናዊ የፖከር ጫዎታ ፣ የመጀመሪያው ዙር ቁማር የሚጀምረው ሁለት ወይም ከዚያ በላይ ተጫዋቾች ካርታ ታድለው ነው ። ጫወታው የሚጀምረው ። ከዛም ካርታ በመሳብ ና ከአቋማሪው በመቀበል የቁማር ውርርዱ ይጧጧፋል ። በመደበኛ ፖከር እያንዳንዱ ተጫዋች እጁ ከሌሎቹ ተጫዋቾች ጋር ሲወዳደር ዋጋ አለው ባለው ባመነበት ካርታ ጫዎታውን ይጀምራል ። እያንዳንዱ ተጫዋች በተራው ከፍተኛውን የቀደመውን የቁማር ውርርድ በጫዎታው ሰዓት ተወራርዶ እንደ ጫዎታው ፍሰት ውርርዱን ከፍ በማጦዝ ፣ ደጎስ ያለ ገንዘብ ሊያገኝ ይችላል ። ሁሉም ተጫዋቾች ወደ መጨረሻው እየተንጠባጠቡ ይደርሳሉ ። ዙሩን አንድ ሰው ጠቅልሎት ቁማሩ ያበቃል። ከአንድ ተጫዋች በስተቀር ሁሉም በየትኛውም ዙር ላይ ሊታጠፉ ወይም ከጫወታው ውጪ ሊሆኑ ይችላሉ ። ከመጨረሻው የውርርድ ዙር በኋላ ከአንድ በላይ ተጫዋቾች በፉክክር ውስጥ ካሉ የካርታ ውድድር ተካሂዶ ከፍተኛ ነጥብ ያመጣ ገንዘቡን ጠራርጎ ይወስዳል ።
ከዚህ ጋራ በተመሳሰለ በህብረት እስከ አምሥት ሰው የሚጫወተው የካርታ ጫዎታ አይነት አለ ። ያው ፖከር ነው ። 13 ካርታ ሰጪው ያድላል ። ካርታ አዳዩ ከአምስቱ ከፍተኛ ካርድ የደረሰው ሰው ነው ። 13 ካርድ ለአራቱ ተጫዎቾች ከማደሉ በፊት በደንብ ያሰባጥረዋል ( Paw ያደርገዋል )
ከዛም ለእርሱ አ14 ካርድ ይወስድና በየመልካቸው አሥተካክሎ አነሥተኛ ዋጋ ያለውን እና የማይጠቅመውን ካርታ ይጥላል ። በሥተቀኙ ያለው ተጫዎችም ካርታው ከጠቀመው አንስቶ ይወርዳል ። ወይም ሊዘጋ ይችላል ። በአጋጣሚ የተሰራ ካርታ ሊደርሰው ይችላልና ! ….
በዚህ ጫዎታ ብዙ ሴራዎች ፣ አሻጥሮች ፣ ከቁማሩ ጠረጴዛ ጀርባ ድርድሮች ሊኖሩ ይችላሉ ። ያላወቀ የገንዘብ እንጂ የህሊና ቱጃር ያልሆነ በወጥመዱ ይገባል ። አንድ ሁለቴ ያስበሉታል ። ( ይዘጋል ) ከዛ በኋላ ያልቡታል ። የነቃ ሲመስላቸው አንድ ሁለቴ እየሰጡ ያዘጉታል ። ኮድ አላቸው ። በአይን ይጠቃቀሳሉ ። አውቀው ይጣላሉ ። ደጋግሞ የሚዘጋውን ይሳደባሉ ። ያሽሟጥጣሉ ። ታላቢው በዚህም ይሸወዳል ። ይኽ ጫዎታ ከእኛ ፖለቲካዊ ሴራ ጋር ይመሳሰላል ። ካርታ ተጫዎቾቹን እንደ ፖለቲካ ፖርቲ ዓባላት ተጠሪዎች ውሰዷቸው ። የማዕከላዊ ኮሚቴ ዓባላት አድርጓቸው ። ወዘተ ። ሊሆኑም ይችላሉ ።
ፖከር የካርታ ጫዎታ ከ 20 ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ጀምሮ ተወዳጅነት ያገኘ እልህ የሚያሲዝ ቁማር ነው ። ዛሬ በትንሽ የአድናቂዎች ቡድን ብቻ ተወስኖ ከመቅረት ወደ መላው ዓለም ተሰራፍቶ ከመዝናኛነትም ከፍ ብሎ ለተሳታፊዎች በኢንተርኔት አማካኝነት በቀጥታ አሳታፊ ህኖ ተመልካቾችንም ጭምር የሚያዝናና የካርታ ጫዎታ ሆኗል ። አቋማሪው ብዙ ፕሮፌሽናል ተጫዋቾች በማሳተፍም በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር ያንቀሳቀስበታል ።
በእኛ አገር እየተካሄደ ያለውን በመንግሥት ደረጃ እየተከናወነ ያለውን ቁማር የጋሃዱ ዓለም “ፖለቲካዊ ፖከር ” ብዬዋለሁ ። ይኽ ፖለቲካዊ ቁማር ጫዎታ አጫዎቹና መጨረሻ ጠቅላዩም አንድ ሰው ነው ። የፈለገውን ካርታ በተገቢው ጊዜ በሁነኛ ሰዓት ፣ በተመቸ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ይመዛል ። ጆከር ፣ ጦር ፤ ልብ፣ ዳይመንድ ፣ ፍላዎር ፣ …ኬሻ፣ሸሌ፣ወለድ …23456789… ። እንደ አሥፈላጊነታቸው በወቅቱ መዘዝ አርጎ ያሰልፋቸዋል ። ለምሳሌ ዛሬ ከሁለት እስከ አሥር የቲዲኤፍ ጀነራሎችን ከአብይ ጎን ናቸው ። አንድ ጦር ፣ ጀነራል ታደሰ ወረደ ነው ። ወለድ ልብ ፣ ( ጄ ) ፃድቃን ገብረተንሣይ ነው ። ሞጆሪኖ ኪው ጦር ናት ። ኬሻ ዳይመንድ ወይም ኬ ፣ ደብረፅዮን ገ/መድህን ነው ። ጆከር ደግሞ ጌታቸው ረዳ ነው ። የትም ብታሥገባው የመሆን ችሎታ አለውና !
እናም በዚህ የፖለቲካ ፖከር መሠረት አቋማሪው የኢትዮጵያ ጠ/ሚ አብይ ጌታቸውን የትግራይ ክልል ጊዜያዊ ፕሬዘዳንት ማድረጋቸው ተገቢ ይመሥለኛል ። በፖለቲካዊ ፖከር ሊበሉት ያሰቡት ቁማር አለና !
ይህንን ” ራያ የተወለደ ጆከር ሰውዬ ፕሬዝዳንት በማድረግ የቁማሩን ካርታ መዘው ጠረጴዛው ላይ ሲያሥቀምጡ ግባቸው የታወቀ ነው ። የካርታ ጫዎታ እንደ ቼዝ ማሰብን ቢጠይቅም ብልጠትና ዘዴ ፣ የሌሎች ቁማርተኞችንም ቀልብ መሥረቅ ይጠይቃል ። እንግዲህ የእኛም ፕለቲካዊ ፖከር ተመሳስሎቱ እዚህ ላይ ነው ።
መና ከሰማይ የሚወርድልን ይመሥል ” አይዞን ይህንን ዘመን ከተሻገርን ቅቤ በአፍንጫችሁ ይንቆረቆራል ። ” ያሉን እነ ዳይቆን ዳንኤል ክብረትም ይህንኑ የሸፍጥ ፖለቲካ አይተው ነው ። ሰውያችን ጥሩ እያጎ ከጎኑ አሥቀምጧል ። በበኩሌ ጌታቸውና ዲያቆኑ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታ ናቸው ። ሁለቱም መተርተር ሆቢያቸው ነው ። እንዴ ምን ማለት ነው ፣ አጠቃላይ ኑሯችን ሲዖል ሆኖ ሣለ “ ወደፊት ዓለም በጎናችሂ ታልፋለች ። ላይፋችሁን ትቀጫላችሁ ። “ ማለት ። …
እርግጥ ዲያቆን ዳንኤልና መሠሎቻቸው ፣ ኑሯቸው ቤተመንግሥት በመሆኑ የተርታውን ህዝብ ሥቃይ እና መከራ ላይገነዘቡ ይችላሉ ። ዛሬ ወላጅ ልጆቹን ለማኖር ፆሙን እያደረ እንደሆነ ማን በነገራቸው ! … በሁሉም ዜጋ ላይ ፣ የምግብና የትራንሥፖርት ዋጋ በ2014 እና 2015 ዓ/ም ውስጥ ብቻ በእጥፍ መጨመሩን እና ኖሮን ለመቋቋም እንዳልቻለ እንዴት ሊያውቁ ይችላሉ ። ጊዜያቸውን ያሳለፉት የጠቅላዩን መፅሐፍ እያረቱ በመሆኑ አጠቃላይ ኑሮቸው ቤተመንግሥት በመሆኑ ። ሃቁ ግን ፣ በዓሉ ግርማ እንዳለው መኖርም መሞትም ከአቅማችን በላይ ሆኖብናል ።
ሥቃያችን በዝቷል ። እውነታውን ላይቀይሩ፣በታሪክ ጥቁር መዝገብ መፃፋቸው ላይቀር ፣ ከህዝብ ልብ ውሥጥ መውጣታቸውን እያወቁ ፣ ዛሬም በኃይል መግዛት እንችላለን በማለት በቀቢፀ ተሥፋ ፣ ሃቀኛ ምሁራንን ማሰቃየታቸውን እና ማሰራቸውን ግን “ ጊዜው የእኛ ነው !” የሚሉ ደናቁርታት ቀጥለዋል ።
የመቀነሥ ትውልድ አፍርተው የመደመር ትውልድ ይሉናል ። ጥላቻን እየዘሩ ፍቅርን አጨድን ብለው ለማታለል ይቃጣቸዋል ። እያሠቃዩ፣ እያሰሩ ፣ እያሥራቡ ና እየገደሉ “ እንደ ኢየሱስ የፅድቅ ሥራ እየሰራን ነው ። “ ማለት የለየለት የፖከር ፖለቲካ ሤራ ነው ።
ነገ አፈር የሚሆነው ደንቆሮ አሽከራቸው ከጥበብ በመራቁ የተነሰ ፣ እንደ ድሮ የፊውዳል እና የአምባገነኖች ገራፊ ፣ በትዕዛዛቸው መሠረት ያለርህራሄ ዜጎችን እያሰቃየ ነው ። እነሱም ከቁማሩ ዛሬ የሚያገኙትን የገንዘብ ትርፍ እንጂ ነገ ለልጅቻቸው የሚያተርፉትን ሥድብ፣ ውርደትና መሸማቀቅ ዛሬ ላይ ሆነው አይረዱትም ።
በፖለቲካዊ ቁማራቸው ሳቢያ ሃቀኛ የኢትዮጵያ ልጆች በራሳቸው ቅኝ ገዢዎች ፣ በራሳቸው መንግሥት አሣር መከራ ቢያዩም ( ጎምቱ ጋዜጠኛ ታዲዮስ ታንቱን ጨምሮ አያሌ የፖለቲካ እሥረኞች በቅኝ ገዢዎቻችን በየእሥር ቤቱ እየተሰቃዩ ነው ። )
በራሳቸው አገር እንደ ሁለተኛ ዜጋ ተቆጥረው እየተሸማቀቁ የሚኖሩ በ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ናቸው ። አለአግባብ እየታሰሩ በጉቦ የሚፈቱም በኦሮሚያ ክልል እንደበዙመ የአገሪቱ ደህንነት አያውቀውም ማለት አይቻልም ። በተቀናጀ መንግሥታዊ በሚመሥል አፈና እየታፈኑ በሚሊዮን እና በመቶሺ እየከፈሉ ከእገታ የሚፈቱ ጥቂቶች አይደሉም ።
በየተቋማቱ ጉቦ እየሰጡ መብታቸውን የሚያስከብሩም ጥቂት ዜጎች እንዳልሆኑ ይታወቃል ። እንግዲህ ይኽን የመሣሠለ ግፍና የዳቦ ችግር በሰፈነበት ህዝብ ላይ ነው ጠቅላዩ ጆከር መዘው “ ጌቾ ምላሡን “ የትግራይ ጊዚያዊ መንግሥት ፕሬዘዳንት አድርጌዋለሁ ያሉት ። ከታላቅ ህቡ ድርድር በኋላ የተመዘዘች የፖለቲካዊ ፖከር ካርታ ናት ። ጆከሯ ። …
ግና ፣ “ ይኽም ያልፋልና “ ጊዜ አልፎ ነፍሰ ገዳዮች፣ ዘራፊውች ፣ ጨካኞች ፣ አይጠረቄ ሥግብግብች ። ወዘተ ። ሁሉ በሰፈሩት ቁና እንደሚሰፈርላቸው ቅንጣት ያህል አልጠራጠርም ። እሥከዛው ግን ግፉ ና ፖለቲካዊ ቁማሩ ይቀጥላል ። የኢትዮጵያ ህዝብም አሥቀድሞ ባወቀው ቁማር እንደማይበላ ቢያውቅም በብሥለት እና በብልሃት ከህዝብ ባነሰው መንግሥት እያዘነ የመንግሥትን ፖለቲካዊ የካራታ ቁማር በአንክሮ ይከታተላል ።