ጥቅምት 24/2013 ዓ/ም የፈሰሰው የኢትዮጵያ ጀግና ልጆች ደም የፍትህ ያለ ይላል ። እናም ፡- የማይክን ኃያል ድምፅ ፤
ሐመርን ኃያልነት … ብናውቅም ፤
እጃችን የእሳት ሰደድ ነውና
ፍትህን አስረግጠን
ፈርተን ዝም አንልም !!
( ሲና ዘ ሙሴ )
“ጦርነት ለወያኔ ዳንስ እንዴት ይሆናል ? ከራስህ አገር ዜጋ ጋር እየተጋደልክ ነው እንዴ ደንስ የሚሆነው ? ይህ ጦርነት እኮ ከውጫ ወራሪዎች ጋር የተደረገ ጦርነት አየደለም ? ” አለች ያቺ ቆንጂዬ ኢትዮጵያዊት ትግራይ ብለው ሰዎች በሰየሙት ክልል የተወለደች የእግዚአብሔር ንፁህ ፍጥረት ። ለኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እጆን ሰጥታ ጋዜጠኛ አርያ ተሥፋማርያም ለጠየቃት ጥያቄ በሠጠችው መልስ ።
በግድ ፣ በወያኔ ጉልበት ለጦርነት የተሰለፈችው ወጣት ። ጦርነት ዳንስ የሚሆነው ከጠላት ጋር ፣ ከውጪ ወራሪ ጋር ለሀገርህ ሥትዋጋ ብቻ እንደሆነ አሥተምራናለች ። ብራቮ ! “ ንፁሐን እንደ ቅጠል በክላሽና በድሽቃ በሣንጃ እያለቁ ነው እንዴ ? ” ጦርነት የባህል ጫዋታችን ነው ። የምንለወ ? “
ይህ ተደጋግሞ ፣ በገዛ ወንድም ላይ የተፎከረ የወያኔ ካድሬዎች ባዶ ጩኸት ፤ የባዶ በርሜል ድለቃ ነበር ። እና የገዛ ወገንን ጠልነት ፤ በአቶ ጌታቸው ረዳ ( ዛሬ ሥራው መርዳት መሆኑ የተገለጠ ። ከከባድ ሚዛኖች ጎን የሚቆም ። በሞቀበት አፋሽና አጎንባሽ የሚሆን ። ከአሸናፊው ጎን ተሠልፎ ያሸናፊውን መዝሙር የሚዘምር … መርህ በሌለው ሰው ፣ ተደጋግሞ ሲነገር ነበር። ከሁሉ የሚያሥቀው ” አብይን ኤርዶጋን አያድነውም ። ሳዳም ሁሴን አያድነውም ። ወዘተ ። ” ያለው ነበር ። አንድ ጊዜም ተሳስቶ አብይ ፣ አብቹ ። ብሎ እንደነበረ አትዘንጉ ። )
ይህንን ፅሑፍ ሥፅፍ የአሥቴርን “ለመድክ ወይ ” የሚለውን ዘፈን እያዳመጥኩ ነበር ።
” ለመድክ ወይ ውጩን ከተማ ደጁን …ለመድከው ሁሉን ከተማ ደጁን …ቻለው ወይ ልብህ …ያማረጥ ጀመረ ልብህ ሌላ ቆንጆ …አንደበትህ እኔን አሥሮኝ እየዋለ …እንዴት አሥቻለህ ተፈጥሮ …እንደው ትዝ እያለኝ … ” ወዘተ እያለች የምታጎረጉረውን ። እኔም
” ለመድክ ወይ የማይክ እና ሃመርን ነገር
ለመድክ ወይ ማይኩን እና ሃመሩን
ለመድክ ወይ ተግሣፁን እና ኩርኩሙን
ቻለ ወይ ህሊናህ የማይክን ቀጭን ትዕዛዝ …” እላለሁ ።
በእርግጥ የማይክ ሃመር የነገ ግብ የአሜሪካ መንግሥት እና የኢትዮጵያ መንግሥት ያውቁታል ። ከኢትዮጵያ ሠላም ያተርፋሉ ወይስ ያከሥራሉ ? ይህ በሚገባ ተገምግሟል ። አሜሪካንን የሚመሯት አንድ ፐርሰንት የናጠጡ ቱጃሮች አትራፊ እንደሚሆኑ ባያረጋግጡ ኖሮ ወደዚህ ሠላማዊ መንገድ ህውሃት እንዲመጣ አይፈልጉም ነበር ።
እናም ህውሃትን ከተቀበረበት መቃብር እንዲወጣ አድርገውታል ። ይህ ሰው በላና የጎደኞቹን አንገት የሚቆርጥ እጅግ ጨካኝ ( ከአይሲስ የከፋ ) ወደ ሥልጣን ከተመለሰ ለትግራይ ህዝብ ዳግም ሞት ነው ። የትህነግ ፖለቲካዊ ሃይማኖት ከአይሲሲመንፈሳዊ ሃይማኖት እጅግ የከፋ ሤጣናዊ ነው ።እናም በጨካኝነቷ የምትታወቀው ወያኔ ተመልሳ ለሥልጣን ከበቃች ይህ ለትግራይም ሆነ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ሞት ነው ።
ጥንት የፊውዳሎች ጭቆና ባሥመረራቸው ወያኔ በተባሉ ታጋዮች ሥም የሚጠሩ ሰው በላ ጭራቆች ዳግም ወደ ሥልጣን ወንበር ከተመለሱ ከሞትም ሞትነው ። ዓለም ምንም ፍትህ የሚባል ነገር እንደሌላትም በዚህ አሥቀያሚ ድርጊት ይገለፃል ። እና ማንም ማይክ እና ሐመር የያዘ ወይም የኒኩለር ጉልበተኛ መንግሥት ፣ ህገወጦችን ፣ ወንጀለኞችን ፣ ንፁሐንን አራጆችን እየደገፈ ነፃ የሆኑ አገራት መንግሥታትን እያሥፈራራና እጃቸውን እየጠመዘዘ ለድብቁ ብዝበዛው ማመቻቸት እንደሚችል የነቃው ጥቁር ህዝብ ይገነዘባል ።
ዛሬም እነ ማይክ እና ሐመር በንግግራቸው ከፍታ እያሥፈራሩ የአፍሪካን መሪዎች በፈለጉት አቅጣጫ እንዲጓዙ ያሥገድዷቸዋል ። ይህ ግን በኢትዮጵያ እንዲቀጥል ጀግኖች አይፈቅዱም ። የትግራይ ህዝብ ከአንድ ለአምሥት ጥርነፋ መላቀቅ ይገባዋል ። ኢትዮጵያም በካድሬ የማይመራ ፣ በደመነፍሰሰ እና በሥሜት ከጦዘ ኃይማኖታዊ ፖለቲካ የተፋታ መንግሥት ያሥፈልጋታል ።
በኢትዮጵያ ውሥጥ ፣ አንድ ሞኝ ሥለጮኸ፣ ሺ ብልጦች አብረውት መጮኽ የለባቸውም ። ሥለሣቀም ፣ ሥለጨፈረም አንዲሁ ። ወይም በተቃራኒው አንድ አሥመሳይ በገሃዱ ዓለም በአደባባይ ሥላለቀሰ ከእርሱ ጋር ማልቀስ የለባቸውም ። ይህንን ማድረግ የሚቻለው ደግሞ ቆም ብለን ሥናሥብ ነው ።
ቆም ብለን በማሰብ ፣ በዕውቀት ይህንን የሁለት ባለጉዳዮች ( two party’s ) የተሰኘውን የሥምምነት ሰነድ እንፈትሸው ። ለመሆኑ የኢትዮጵያን ምርጫ ቦርድ አላውቅም ብሎ ፣ በራሱ ጉልበት በክልሉ ምርጫ ቦርድ አቋቋምኩ ብሎ በጠመንጃው አሥፈራርቶ ከተመረጠና አንገት እየቀላ በማሥፈራራት የትግራይን ክልል በኃይል ከሚያሥተዳድር አረመኔ ጋር ቀድሞውንሥ የአንድ ኩሩ አገር መንግሥት በአንድ ጠረጴዛ ላይ መቀመጥ ነበረበት ወይ ? የሰነዱን ቁንፅል ሃሳብ ብቻ ይፋ በማድረግ ፣ ሙሉውን ሥዕል በመሸፈን ዘላቂ ሠላም ማምጣት ይቻላል ወይ ? ያ ሁሉ መሰዋትነት ከአረመኔ ፣ ከሰው አራጅ እና ለህግ ከማይገዛ ህሊና ቢስ ቡድን ጋር ለመደራደር ነባራዊው ሃቅ ይፈቅዳል ወይ ?
ኢትዮጵያን የማይክን ጫጫታ እና የሐማርን ገዳይነት ፈርተን ፍትህ ሥትጨፈለቅ ዝም ብለን እጃችንን አጣምረን ቆመን ማየት አንችልም ። የራሳችንን ጉዳይ ራሳችን እንፈታለን ። ሥንል ለእኔ ተንበርካኪ አንሆንም ማለት ነው ትርጉሙ ። ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ/ም ኢትዮጵያን ለገደሉ ሁሉ መህረት የለም ። ተገቢውን ህጋዊ ቅጣት ማግኘት አለባቸው ። በኢትዮጵያ አንደራደርም ። …