May 14, 2022
62 mins read

አስፈሪው የውድቀት አዙሪት – ጠገናው ጎሹ

April 14, 2022
ጠገናው ጎሹ

በዚህ ርዕስ ሥር በማነሳቸው ጉዳዮች (ነጥቦች) ላይ ሂሳዊ አስተያየቴን ስገልፅ ጉዳዮቹ አዲስና አስገራሚ ናቸው ከሚል የፖለቲካ አስተሳሰብ ቂልነት አይደለም። ከሩብ ምዕተ ዓመት በላይ (1983 -2010) በፈጣሪውና በበላይ ተቆጣጣሪው የህወሃት ቡድን ሲዘወር በቆየው እና ከአራት ዓመታት (ከ2010 ወዲህ) ደግሞ በተረኛው የኦህዴድ (የኦነግ) ቡድን የበላይነት እየተዘወረ ባለው የጎሳ አጥንት ማንነት ፖለቲካ ሥርዓት የተፈፀሙና እየተፈፀሙ ያሉ አሰቃቂ ፖለቲካ ወለድ ወንጀሎች አዲስና አስገራሚ መሆናቸው እየቀረ በአሳዛኝ ሁኔታ እንደማነኛውም ችግሮቻችን እየተለማመድናቸው ከመጣን ወራት ሳይሆን ዓመታት ተቆጥረዋል። አዎ! መግለፅ የሚያስቸግረውን የረጅም ጊዜና  እጅግ አስከፊ ህመማችን ዋነኛ ምክንያት ህወሃት/ኢህአዴግ ሠራሹ እና አሁን ደግሞ ኦህዴዶችና አሽከሮቻቸው የሚዘውሩት ሥርዓት መሆኑ እየታወቀ ለዚህ የሚመጥን የጋራ ትግል ካለማድረግ ውድቀት የሚመጣ የመከራና የውርደት ዶፍ ከቶ ሊያስገርም አይችልም።

እጅግ በጣም የሚገርመውና ለመረዳትም የሚያስቸግረው እንቆቅልሽ ለብዙ ዓመታት የመጣንበትና ትናንት (ከአራት ዓመታት) ወዲህም እየሆነ ያለው ለመግለፅ የሚያስቸግር ፖለቲካ ወለድ መከራና ውርደት ዋነኛ ምክንያት በሥልጣን የበላይነት ሽኩቻ ከሁለት አንጃ የተከፍሉ ሁለት የአንድ አይነት ጭራቃዊ የጎሳና የቋንቋ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ሥርዓት  ቁማርተኞች የመሆናቸውን መሪር ሃቅ እየሸሸን አንደኛው (የአራት ኪሎው) ከሁለተኛው (ከመቀሌው) ይታደገን ዘንድ ጩኸትና ተማፅኖ ከማሰማት እጅግ አሳፋሪ ወይም ወራዳ የፖለቲካና የሞራል ውድቀት ሰብረን ለመውጣት አለመቻላችን ነው።

የአሁኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዙፋኑን ሲረከብ ድንቅ የፖለቲካ ቁማር ደርሰቱን አዘጋጅቶ ለማታለያነት ባሰለጠነው አንደበቱ ከደረሰኮረልንና “ምድራዊው ክርስቶስ” የሚል የአምልኮ ውዳሴ እንድናደርስ ካደረገን ማግሥት ማየትና መስማት የጀመርናቸው ፖለቲካ ሠራሽ ኢሰብአዊ ወንጅሎች ስፋት ፣አይነትና አስከፊነት እንኳን ገና የመከራው ዶፍ በቅጡ ባልተገታበት በዚህ ወቅት ሁልጊዜም እየተመላለሱ ህሊናን መፈታተናቸው አይቀርም ።

በተለይ አንዳንድ ፖለቲካ ወለድ ወንጀሎች ለምን እንደተፈፀሙ ነገን በተስፋ ለሚጠብቅ ታዳጊ ትውልድ ለማስረዳት በእጅጉ ይጨንቃል። የሆነውን መንገርና ማስረዳት ምን ይጨንቃል? የሚል የዋህ አይነት ጥያቄያዊ መከራከሪያ ሊቀርብ እንደሚችል እገምታለሁ ። አዎ! የሆነውን መሪር እውነታ መንገርንና ማስረዳትን እንደ አጠላቃይ ተገቢ ነገር መቀበል ትክክል ነው።

ከባዱ ወይም አስጨናቂው ጉዳይ ግን ምነው ዘመን ጠገብ ከሆነ እና መግለፅ ከሚያስቸግር ፖለቲካ ወለድ (ሠራሽ) መከራና ውርደት ተምራችሁ የተሻለ ዛሬን ለመፍጠር እና በእጅጉ የተሻለ ነገን ለእኛ አይነቱ ትውልድ ለማስተላለፍ ተሳናችሁ?  ስንትስ ትውልድ ነው በዚህ አይነት እጅግ አስከፊና አስፈሪ የሁለንተናዊ ውድቀት አዙሪት ውስጥ ማለፍ ያለበት?  ለዘመናት ተፈትነው የወደቁ የባለጌና የወንጀለኛ ሥርዓት ቁማርተኞችን ውጤታማና ዘላቂ በሆነ የጋራ ተጋድሎ አስወግዶ ለሁሉም ዜጋ የሚበጅ ሥርዓትን እውን ማድረግ ሲገባ ጨቆኑን፣ በእሥር ቀጡን፣ ፍትህ ነፈጉን፣ ገልብጠው ገረፉን፣ የሥነ ልቦና ጦርነት አካሄዱብን ፣ ዘር ማጥፋት ፈፀሙብን፣ ከገንዛ አገራችንና ቀያችን አፈናቀሉን፣ እናቶቻችንና  እህቶቻችን ደፈሩብን፣ ይህንና ያንን ቦታችን ሊቀሙን ነው፣ ማቆሚያ በሌለው ጦርነት ውስጥ ዘፈቁን ፣ አማራንና ፋኖን በጠላትነት ፈረጁት ፣ የህዝቡን የአብሮነት ክር (ገመድ) በጣጠሱብን፣  እና በአጠቃላይ አገራችን እያፈራረሱብን ነው ፣ ወዘተ እያሉ መጮህ ወይም እየየ ማለት ምን ማለት ነውለሚሉ ጥያቄዎች ልንሰጠው የምንችለው መልስ በአብዛኛው ሰንካላ ሰበብ ከመደርደር የሚያልፍ አይሆንም።

አዎ! እነርሱን የመሰሉ የአገራቸው ሰዎች እሬሳቸው ተዘቅዝቆ ተሰቅሎ ሰው እንደ መልካም ትርኢት ከቦ ሲያየው ለተመለከቱ  የእነርሱን እናት  የምትመስል  እናት ማህፀኗ በስለት ተዘንጥሎ አስከሬኗ በጉጉት የምትጠብቀውን/ቃትን የማህፀን ውስጥ ልጇን እንዲታቀፍ ሲደረገ  ለታዘቡ  እነርሱን መሰል ንፁህ ኢትዮጵያዊያን ወገኖቻቸውን በቁማቸው  በእሳት እቶን እያጋዩ የሚደሰቱና የሚሳለቁ ወገኖቻቸውን ለተመለከቱ  በርካታ ንፁሃን የአንድ ሰፈር ኗሪዎች በመጡበት ማህበረሰብና በሚያምኑበት ሃይማኖት ተለይተው ለስብሰባ ከተጠሩ በኋላ በታደሙበት የመስብሰቢያ ቦታ ውስጥ ሲረሸኑ ለታዘቡ በመቶዎች የሚቆጠሩ ንፁሃን ወገኖች በጅምላ ከተገደሉ በኋላ እንደ ቆሻሻ  በግሬደርና በኤክስካቬተር እየታፈሱ በአንድ ጉድጓድ ውስጥ ተወርውረው አፈር ሲመለስባቸው ለተመለከቱ ፣ እንደ እነርሱ  በፈጣሪ ፈቃድና አምሳል የተፈጠሩ  ወገኖቻቸው እኛን  አትመስሉም  በሚል በግፍ ከተገደሉ  በኋላ  ሬሳቸው በአደባባይ እየተጎተተ ሲበጣጠስ  ለተመለከቱ በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ንፁሃን ወገኖቻቸው  ከገንዛ አገራቸውና ቀዮቻቸው ተነቅለው  ወይም ተፈናቅለው ለሁለንተናዊ ምድራዊ ፍዳ ሲዳረጉ ለታዘቡ ፣ ሁለቱ እኩያን የኢህአዴግ አንጃዎች (ብልፅግና እና ህወሃት) በሥልጣን የበላይነት ሽኩቻ ምክንያት በፈጠሩት ጦርነት (የእርስ በርስ እልቂትና ውድመት) በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ንፁሃን ወገኖች የገንዛ  አገራቸው ማለቂያ ያልተበጀለት የምድር ላይ ሲኦል ስትሆን ለተመለከቱ ፣ እና የጠቅላይ ሚኒስትር ተብየውንና የአስተዳደሩን  ልክ የሌለው ውድቀት ለታዘቡ የአገሬ ታዳጊ ወጣቶች ለምንና እንዴት ? ብለው ለሚያቀርቧቸው ጥያቄዎች አጥግቢ ወይም አሳማኝ መልስ ለመስጠት በእጅጉ ይጨንቃል።

እንዲህ አይነት ትውልድ ገዳይ የፖለቲካ ሥርዓትን አስወግደን የሚበጀንን ሥርዓት እውን ለማድረግ ከምር እየፈለግን ከሆን ከትናንት ወዲያና ትናንት ብቻ ሳይሆን ከቀናት በፊት የተፈፀሙትን እጅግ ግዙፍና መሪር ፖለቲካ ወንጀሎች ሸፍጠኛ ፣ሴረኛ፣ ባለጌና ጨካኝ ተረኛ ገዥ ቡድች  እያዘጋጁ በሚያቀብሉን እጅግ ወራዳና አደገኛ አጀንዳዎች  እየተካን ከማልቀስና ከመላቀስ ክፉ የአዙሪት አባዜ ሰብረን መውጣት ይኖርብናል።

በፅዕኑ መርህ ላይ የተመሠረተ  ውጤታማና ዘላቂነት ያለው ትግል ለማደረግ ባለመቻላችን ምክንያት ለውጥ ተብየው የፈጠረብን የስሜት ትኩሳት አፍላው ሳያልፍ ከፖለቲካ ሠራሽ ሰቆቃዎች ጋር በአስደንጋጭ አኳኋን እየተለማመድን በመምጣታችን የምንሰማቸው ዜናዎች፣ ዜና ትንታኔዎችና መግለጫዎች ድንጋጤና ቁጭት የመፍጠር አቅማቸው እየደከመ የመምጣቱ እውነታ አሁንም እያሳሰበንና እያስፈራን አይመስልም።

ሰው ሞተ ወይም ሰዎች ሞቱ  በቁም ተሰቃዩ ፣ ተፈናቀሉ፣ ወዘተ ሲባል ብቻ ልባችን ያዝን እንዳልነበረ ሁሉ አሁን አሁን የሙታን የቁጥር ብዛትም፣ የቁም ሰቆቃው አይነትም ፣የመፈናቀል አሰቃቂነትም ፣ ወዘተ እንኳን ልባችንን ሊያውከው ወደ ልባችንም ዘልቆ የሚገባ አይመስልም። አዎ! ራሳችንን በማታለሉ ክፉ ልክፍት እንቀጥል ካላልን በስተቀር ይህን ያህል ነው ቁልቁል የወረድነው ። የዚህ መሠረታዊ ምክንያት ደግሞ ብዙ ትንታኔና ፍልስፍና ወይም የተለየ ሙያና እውቀት የሚጠይቅ ሳይሆን ጨርሶ ሊፈወስ በማይችል የፖለቲካ ካንሰር የተበከለውን ሥርዓተ ኢህአዴግ/ብልፅግና ከሥሩ ነቅሎ በመጣል የእውነተኛ ፈውስ መንገድ የሆነውን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን ለማድረግ የሚያስችል የጋራ ተጋድሎ የማድረግ ወይም ያለማድረግ ጉዳይ ነው።

እንደ ግለሰብ፣ እንደ ቤተሰብ፣ እንደ ማህበረሰብና በአጠቃላይ እንደ ህዝብ ነፃነትን፣ ፍትህን ፣እኩልነትን ፣ ተከብሮና ተከባብሮ መኖርን እና ከተመፅዋችነት መላቀቅን ማእከል ባደረገ የጋራ ትግል አውድ (ሜዳ) ላይ ራሱን ማገኘት የተሳነው ትውልድ ባለጌና ጨካኝ ገዥዎች እና የዓላማ ሽሪኮቻቸው የግፍ ሰይፋቸውን እየመዘዙ ሰቆቃ በፈፀሙበት ቁጥር የሚያወርደው ሙሾና የደም እንባ ጨርሶ የትም አያደርስም ወይም ጨረርሶ ስሜት የሚሰጥ አይደለም ።

የሰው ልጅ የተፈጠረበትን ዓላማ ይፈፅምበትና ያስፈፅምበት ዘንድ የተሰጠውን ረቂቅ አእምሮና ብቁ አካል በአግባቡ ባለመጠቀሙ ምክንያት ለሚደርስበት መከራና ውርደት ሃላፊነትንና ተጠያቂነትን የሚወስድ እውነተኛ አምላክ የለም። እውነተኛው አምላክ በድርጊት የሚገለፅ ሥራ ላይ በመሠማራት እና ድርሻችሁን በመወጣት  የአምላክነት በረከቴን ስትጠይቁ ፈጥኘ እደርሳለሁ” የሚል እንጅ “ ድርጊት አልባ ለቅሶ፣ እንባ፣ እግዚኦታ፣ ምህላ፣ ቅዳሴ፣ ዝማሬ፣ ቅኔ ማህሌት ፣ ሰበካ፣ አርምሞ ፣ ፆም፣ ፀሎት ፣ ወዘተ ከባርነትና ከመከራ መንጥቆ ያወጣል የሚል አይደለም ።  ይላል ካልንም ለእራሳችን ልክ የሌለው ውድቀት ሰንካላ ምክንያት ይሆነን ዘንድ በገንዛ አስተሳሰባችን (ጭንቅላታችን) ውስጥ የምንፈጥረው አምላክ እንጅ ሰውን ከሌሎች ፍጡራን ለይቶ ለድንቅ ዓላማ የፈጠረው እውነተኛው አምላክ አይሆንም።

ይህ ትውልድ ከእንዲህ አይነት ፖለቲካዊ፣ ሞራላዊ፣ ሥነ ልቦናዊ እና መንፈሳዊ ጉስቁልና ለመላቀቀቅ እና ሰማያዊና ዓለማዊ እሴቶቹ ስኬታማና ጠንካራ ለሆነ የጋራ ህይወቱ የየራሳቸውን ተገቢ ሃላፊነትና ግዴታ እንዲወጡ ለማድረግ እስካልተቻለው ድረስ በወጉ የማይሸኝ የመቃብር ሙት እና የቁም ሙት ሰለባ እየሆነ ቢቀጥል ከቶም ሊገርመን የሚችል ነገር አይደለም።  ልክ የሌለው ውድቀታችንን ተጋፍጠን ለማሸነፍ ሲያቅተን (የውድቀት አዙሪት ሰለባ ስንሆን) ተልካሻ ሰበብ እየደረደርን ከገንዛ ራሳችን መሪር እውነታ የመሸሽ  አባዜ ካልሆነብን በስተቀር መሪሩ ሃቁ ይኸው ነው።

ለውጥ መጣ በሚል ዳንኪራ ረግጠን ሳናበቃ በባሰ የመከራና የውርደት አዙሪት ውስጥ ራሳችንን ያገኘነው እና ከአራት ዓመታት በኋላም ተራው የእኛ ነው የሚሉ ባለጌ፣ ሸፍጠኛና ሴረኛ የጎሳና የቋንቋ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ቁማርተኞች መሳቂያና መሳለቂያ ከመሆን ያልወጣነውም ለዚህ ነው።

የእነዚህ ገዥ ቡድኖች ዓላማና ግብ ግልፅና የማያሻማ እንጅ ልዩ ትንታኔንና ፍልፍናን የሚጠይቅ አይደለም። ለእነርሱ የእውነተኛ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን መሆን ማለት የብልግና እና የግፍ ፖለቲካ ቁማራቸው ምሽግ የሆነውና በህገ መንግሥት የደነገጉት የጎሳ/የመንደር አጥንት ስሌት ፖለቲካ ፍፃሚ ማለት ነው።  ይህ እውን ሆነ ማለት ደግሞ ፈፅሞ ልክ የሌለው ዝርፊያቸውና የብልግና አኗኗራቸው አበቃለት ማለት ነው።

ሁሉም ነፃነትና ፍትህ ፈላጊ አካል ያለምንም ፍርሃት ወይም ሥጋት የሚሳተፍበት ሥርዓተ ዴሞክራሲያዊ እውን ሊሆን የመቻሉ እድል ባቃዣቸው ቁጥር ሰይፋቸውን የሚመዙትም  ለዚህ ነው።  እናም በእነርሱ በሚዘወር “የተሃድሶ ለውጥ” ዴሞክራሲያዊት አገር እውን ትሆናለች ብሎ ከማሰብና ከማመን የከፋ የፖለቲካና  የሞራል ውድቀት አዙሪት ጨርሶ የለም።

ይህንን ተገንዝቦ የእራሱን ሃላፊነትና ግዴታ በመወጣት እራሱን የነፃነትና የፍትህ አገር ባለቤት ማድረግ ሲገባው ከአራት ዓመታት በኋላም “ጨቆኑን፣ ግፍ ሰሩብን፣ አሳደዱን፣ አፈናቀሉን ፣ በግፍ ገደሉን፣ አጋደሉን፣ አስራቡንና አስጠሙን፣ አረዱን፣ ሬሳችን ዘቅዝቀው ሰቀሉት፣በቁማችን በእሳት እቶን እጋዩን ፣ እንደ ቆሻሻ በአንድ ጉድጓድ ውስጥ ወርውረው አፈር አለበሱን፣ በፈጣሪያችን ስም ቀለዱብን፣ ፈጣሪንም የእኩይ አስተሳሰባቸውና ድርጊታቸው ተባባሪ እንደሆነ ነገሩን ፣ ንፁሃን ወገኖችን በየተራ እየሰወሩና እያሰሩ ቤተሰብን ለሰቆቃ ዳረጉብን ፣ ወዘተ” የሚል ሙሾ የሚያወርድ ትውልድ እንዴትና መቼ ከዚህ ክፉ እንቆቅልሽ እንደሚላቀቅ ንኳንስ በእርግጠኝነት ለመተንበይ ለመገመትም በእጅጉ አስቸጋሪ ነው።

የእየራሱ ተጨባጭ ሁኔታና ምክንያት እንደ ተጠበቀ ሆኖ በአጠቃላይ ግን የአልገዛም ባይነት ተጋድሎ በሌለበት መሪር የፖለቲካ እውነታ ውስጥ የእውነተኛ ነፃነትና ፍትህ ሥርዓት መወለድን ከመጠበቅ ወይም ተስፋ ከማድረግ የባሰ የውድቀት እንቆቅልሽ የለም።  በርህራሄ ወይም በችሮታ ወይም በተማፅኖ ወይም በርግማን ወይም ፈጣሪን እግዚኦ ካልወረድክ በማለት ብቻ የሚለወጥ ፖለቲካ ወለድ መከራና ውርደት ኖሮም አያውቅም፤ ዛሬም የለም፤ ወደ ፊትም አይኖርም። የሰው ልጅ የፖለቲካና የማህበራዊ እንስሳነት ታሪክ አካል ሆነው የኖሩት ፣ ዛሬም የሆኑት እና ሌላ ተአምር እስካልተፈጠረ ድረስ ወደ ፊትም የሚኖሩት በዋናነት ሁለት አማራጮች ናቸው።

ዛሬም በዚህ ትውልድ ፊት ተደቅነው የሚገኙት እነዚህ ሁለት አማራጮች ፦) እንደ ሰውም  ሆነ እንደ ዜጋ የሚገባውን አግኝቶና ተከብሮ የመኖር መሠረታዊ መብቱን ለማስከበር ሲል የከፈለውን የአልገዛም ባይነት ተጋድሎ በፖለቲካ ቁማር አስተሳሰባቸውና እጅግ ጨካኝ በሆነው የማስፈፀሚያ ሰይፋቸው ነጥቀው ለወሬ የማይመች የመከራና የውርደት ዶፍ እያወረዱበት ያሉትን ገዥ ቡድኖች ሥርዓት አስወግዶ የነፃነት፣የፍትህ ፣ የእኩልነትና የጋራ እድገት ራእዩን እውን ማድረግ   ለ) ከአልገዛም ባይነት የአርበኝነት ተጋድሎ ጋር ተሰናብቶ (ተቆራርጦ) በአሽከርነት ሲያገለግሉት የኖሩትን ፈጣሪያቸውንና አሳዳጊያቸውን ህወሃትን ከቤተ መንግሥት ፖለቲካ  የበላይነት አስወግደው ሥርዓቱን ግን በባሰ አኳኋን ያስቀጠሉት የኦህዴድ/ ብልፅግና ገዥ ቡድኖች  የሚያሸክሙትን የግፍ ቀንበር በፀጋ ተቀብሎ መኖር ናቸው  (መኖር ከተባለ) ።

አዎ! የዚህ ትውልድ እጅግ ከባድ ፈተና የሚሽከረከረውም ለእነዚህ ከባድና መሪር ጥያቄዎች ትክክለኛና ወቅታዊ ምላሽ ለመስጠት በመቻል ወይም ባለመቻል የፖለቲካና የሞራል አቋምና ቁመና ዙሪያ ነው።  በእውነት ከተነጋገርን ከአራት ዓመታት በኋላም ይህንን አይነት እጅግ ወሳኝ የነፃነትና የፍትህ ተጋድሎ እያየን ያለመሆኑ ጉዳይ በእጅጉ አስፈሪ ነውና ቆም ብሎ የሚበጀውን ማድረግ የግድ ነው።

አዎ! ራሳችንን ለመሸንገል (ለማታለል) ካልፈለግን በስተቀር  እንኳን ለራሱ ዘመን የሚመጥኑ አዳዲስ ድልድዮችን ሊዘረጋ የነበሩትን ጠቃሚ የግንኙነት መስመሮችን (ድልድዮችን) በማፈራረስ እጅግ ወራዳ ዘመቻ ላይ የተጠመደ ትውልድ  ስለ ዴሞክራሲና ስለ ዴሞክራሲያዊት አገር አጥብቆ የሚደሰኩረው (የሚሰብከው) ሁሉ ቅዠት እንጅ የገሃዱ ዓለም ራዕይ ነፀብራቅ አይሆነም።

በዚህ አገላለፄ ላይ ምነው የጅምላ ወቀሳ አይሆነም ወይየሚል ጥያቄ ሊነሳ እንደሚችል እገምታለሁ። የፈጣሪ ዕፁብ ድንቅ ሥራ መገለጫ የሆነውን የማህበራዊና ሰብአዊ ግንኙነት ብጥስጥሱን እያወጣና እያስወጣ  ስለ ድልድይና መንገድ አጥብቆ የሚደሰኩር  በፈጣሪ ረቂቅ ሥራና ፈቃድ ወደ ዚህች ምድር የመጡ የንፁሃን ወገኖችን የተስፋ ብርሃን ወደ ጨለማነት እየለወጠና እያስለወጠ ስለ ብርሃን አመንጩ የውሃ ግድብ አብዝቶ የሚተርክ ፣ የብዙ ሚሊዮኖችን የዛሬ አበባዎችና የነገ ፍሬዎች ህይወት እያጨናገፈና እያመከነ ስለ መንገድ ላይ አበቦቹ አጥብቆ የሚጨነቅ  ለመፈናቀልና ለርሃብ አሳልፎ የሰጣቸው ንፁሃን ሚሊዮኖች በነፍስ ግቢና ነፍስ ውጭ ላይ  በሚገኙበት መሪር እውነታ ውስጥ ቅጠል በጨው እና ዳቦን በሙዝ ተመገቡ እያለ  የሚሳለቅ  ፈጣሪ የባለጌና የግፍ አገዛዝ ተባባሪ ይመስል “እርሱ ካዘዘኝ ዝንፍ አልላልም” የሚል እጅግ ወራዳ ዲስኩር የሚደሰኩር ፣  የመከረኛው ለፍቶ አዳሪ ህዝብ የኑሮ መሠረት የሆኑት እንስሳት ለብዙ ወራት በዘለቀ የውሃና የመኖ እጦት ሲያልቁ ምንም ሳያደርግ ቆይቶ የተፈጥሮ የበልግ ዝናብ ሲዘንብ አውሮፕላኗ በአካባቢው ላይ ስታንዣበብ በቪዲዮ እያስቀረፀ  በማሳየት “ዝናብ አዘነብኩላችሁ” የሚል እጅግ ወራዳ ፕሮፓጋንዳ  የሚያስነግር ጠቅላይ ሚኒስትር የሚመራውን ሥርዓት በቃኝ ከማለት  ይልቅ “እባክህ ወደ መልካም መሪነት ተለወጥልን” በሚል የሚማፀንና የሚለማመጥ  ትውልድ እንዴትና መቼ የነፃነትና የፍትህ ትውልድ ለመሆን እንደሚችል ለመገመት በእጅጉ አስቸጋሪ ነው።

አዎ! ይህ ትውልድ አገረ ኢትዮጵያን ምድረ ሲኦል ያደረጋትን የሸፍጠኛና ግፈኛ ገዥ ቡድኖች ሥርዓት ቢያንስ አደብ ማስገዛት ሳይችል ይኸውና አራቱን ዓመታት አጠናቆ አምሥተኛውን የሰቆቃ ዓመት በማስቆጠር ላይ ይገኛል። ለዘመናት መላልሶ በመውደቅ ጉስቁልና ውስጥ ከመገኘት የባሰ አሳፋሪና አስፈሪ የፖለቲካና የሞራል ዝቅጠት ከቶ የለም። ሊኖሩ የሚችሉ እንከኖች (ስህተቶች) እንደ ተጠበቁ ሆነው ይህ መላልሶ የመውደቅ ክፉ አባዜ በተለይ ለእንደኛ አይነት ረጅምና አኩሪ ታሪክ ፣ ባህል፣ ወግ፣ አብሮነት ፣ ወዘተ አለኝ ለሚል ህዝብ በእጅጉ አንገት ያስደፋል (ያሳፍራል) ። በገንዛ ራሱ ልክ የሌለው ፍርሃት፣ አድርባይነት፣ መርህ አልባነት፣ የሞራል ልእልና እጦት ፣ ስንኩል የፖለቲካ አስተሳሰብ ፣ የእውነተኛ አርበኝነት (አገር ፍቅር) ጉድለት፣ የጋራ ትግል ውድቀት፣ ድርጅታዊ ስንኩልነት ፣ ወዘተ ምክንያት ለአገር አፍራሾች አሳልፎ የሰጣትን አገር “እንዳትፈርስብኝ በእጅጉ ያሰጋኛል” ሲል ምን እያለ እንደሆነ ራሱን ቆም ብሎ ለመጠየቅ ያልፈለገ (ያልተዘጋጀ) ትውልድ የሚመኘውን ዴሞክራሲ መቼና እንዴት እውን እንደሚያደርገው ለመረዳት ይቸግራል።

“ችግርና መከራ ሊያጋጥም የሚችል ነገር ነው ሊነጋ ሲል ይጨልማል ህይወት የመውጣትና የመውረድ ጉዞ ነው ኢትዮጵያም አያሌ ጊዜ በመከራ ውስጥ አልፋለችና አሁንም ታልፈዋለች  በእርሱ ፈቃድ ሁሉም በወቅቱ ይሆናል ወይም ለሁሉም ጊዜ አለው  ከመታገሥ ማትረፍ ይቻላል  ወዘተ የሚሉ እና አጠቃላይ እውነታን (general truth) የሚገልፁ አባባሎችን ለእኛ አይነቱ እጅግ ልክ ያለፈና አስከፊ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊ ማህበራዊ ሥነ ልቦናዊ ሞራላዊና መንፈሳዊ ዝቅጠት እንደ ሽፋን መጠቀም በራሱ የውድቀት አዙሪት አካል ነው። አዎ! ለዘመናት የዘለቀውንና አሁንም እጅግ አስከፊ ሆኖ የቀጠለውን የሸፍጠኛና ግፈኛ የጎሳና የቋንቋ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ቁማርተኞች ሥርዓትን በጋራ የአልጋዛም ባይነት ትግል አስወግዶ እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ለውጥን እውን ለማድረግ የተሳነው ትውልድ ሃይማኖታዊ እምነትን ጨምሮ የተለያዩ ሰንካላ ሰበቦችን (various clumsy excuses, including religious beliefs) እየደረደረ ራሱን የማታለሉ ክፉ ልማድ  የማያሳስበው የእውነተኛ ነፃነትና ፍትህ ሥርዓት ፈላጊ የአገሬ ሰው የሚኖር አይመስለኝም።

በዚህ ቀጥተኛና ግልፅ አገላለፄ ላይ “የተጋነነና ጨለምተኝነት ያለበት ነው” የሚል አስተያየት ሊሰጡ የሚችሉ የሥርዓቱ ካድሬዎችና አድርባዮች ብቻ ሳይሆኑ ብዙ ቅን ወገኖችም እንደሚኖሩ እገነዘባለሁ። ለዚህ የሚኖረኝ ምላሽ እንደዚህ አይነት አጠቃላይ አባባሎች ወይም አገላለፆች ለሩብ ምዕተ ዓመት (ከ1983 -2010) በህወሃት የበላይነት እየተመራ በንፁሃን የቁም ሰቆቃና ደም ሲጨማለቅ የኖረውንና አሁን ደግሞ 5ኛ ዓመቱን በያዘው  (ከ2010 – ወዲህ)  በኦህዴድ/ኦነግ የበላይነት እየተመራ  የመከራና የውርደት ዶፍ  በማውረድ ላይ የሚገኘውን  ህወሃት/ኢህአዴግ ሠራሽ ሥርዓት ምንነት፣ ማንነትና እንዴት ለመግለፅ በቂ ካለመሆናቸውም በላይ አሳሳቾችም ናቸውና ጥንቃቄን ይጠይቃሉ የሚል ነው።

ከልክ የለሹ የገዥ ቡድኖች የመከራና የውርደት አገዛዝ ከምር ተምሮ የነፃነትና የፍትህ አገርን እውን ከማድረግ ይልቅ ደጋግሞ በመከራና በውርደት አዙሪት ውስጥ በመዘፈቅ አጠቃላይ እውነታን የሚገልፁ ዓለማዊና ሃይማኖታዊ አባባሎችን እየቃረሙ በአገኙት አጋጣሚና አደባባይ ሁሉ የሰበካና የዲስኩር ማሳመሪያ ማድረግ ለእኩያን ገዥ ቡድኖችና ግብረ በላዎቻቸው ያግዛል እንጅ ከቶ የትም አያደርስም።

በሸፍጠኛና ሴረኛ የበላይ ባለሥልጣናቱ አዛዥነትና በብዙ ሚሊዮኖች በሚቆጠር የካድሬ ሠራዊቱ አስፈፃሚነት እጅግ አስከፊ በሆነ ፖለቲካ ወለድ ወንጀል የበሰበሰና የከረፋ ሥርዓት ወደ ዴሞክራሲያዊነት ይቀየራል በሚል እጅግ የወረደ የፖለቲካ አስተሳሰብ መስመር ውስጥ ሰተት ብለን የገባን እለት ነበር ለአራት ዓመታት በዘለቀውና አሁንም ትርጉም ያለው ማቆሚያ ባልተገኘለት የመከራና የውርደት አዙሪት ውስጥ መዘፈቃችን ግልፅ የሆነው ።

በእጅጉ የሚያስፈራው ደግሞ ከአራት ዓመታት በኋላም በፈፀምነው አስከፊ ስህተት ምክንያት ከደረሰብን ግዙፍና መሪር ተሞክሮ ትርጉም ባለው አኳኋን ተምረን ለእውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለውጥ እውን መሆን የሚበጅ ሥራ ላይ ያለመሆናችንን ውድቀት ላለመቀበል የሰበብ ድሪቶ በመደረት ክፉ ልማድ ላይ መጠመዳችን ነው። ስለ መፍትሄ አስፈላጊነት አብዝተን እየተረክን በድርጊት የሚገለፅ የመፍትሄ ዝርዝር ሃሳብና የተግባር ቀመር ግን የለንም ።

ለማሳያነት (ለምሳሌነት) ያህል  የግልና የቡድን መሠረታዊ መብቶች የሚከበርባት ፣ ዴሞክራሲያዊት የሆነች የነፃነትና የፍትህ መብቶች የሚጠበቁባትና የሚከበሩባት፣  እና ልዑላዊነቷ የተረጋገጠላት ኢትዮጵያን እውን ከማድረግ የበለጠ ራእይና ዓላማ የለንም የሚሉን እንደ ኢዴፓ፣ኢዜማ ፣ ባልደራስ፣ ህብር ኢትዮጵያ ፣ እናት ፓርቲ እና የመሳሰሉ አገራዊ የፖለቲካ ድርጅቶች በዚህ እጅግ አስከፊ ወቅትና ሁኔታ ውስጥ ለምንና እንዴት ከምር ለመመካከርና አብሮ ለመሥራት ተሳናቸው? ለሚለው የምር ጥያቄ  አሳማኝ መልስ  (convincing reason and justification) የሚኖር አይመስለኝም ።

እንደ ኢዜማ አይነት ፖለቲከኞች ደግሞ አብሮ በመሥራትና እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን እውን ለማድረግ ድርሻቸውን ከመወጣት ይልቅ የቤተ መንግሥቱን ፖለቲካ ከተቆጣጠሩት የኢህአዴግ አንጃ ቡድኖች (ኦህዴዶች/ብልፅግናዎች) ጋር በፖለቲካ ዝሙት መተሻሸት ከጀመሩ ዓመታትን አስቆጥረዋል። ከራት ዓመታት ለመስማትም ሆነ ለማየት የሚከብድ ፖለቲካ ወለድ መከራና ውርደት በኋላም በእንዲህ አይነት የወረደ የፖለቲካ ሥራ ተጠምደን የመገኘታችን መሪር እውነታ አሳፍሮንና ፀፀቶን በአስቸኳይ ወደ ትክክለኛው መውጫ መንገድ የማንሰባሰብ ከሆነ የመገደሉና የመገዳደሉ፣ የመታሠሩና የመገረፉ፣ የመሰደዱና የመሳደዱ፣ የመራቡና የመጠማቱ፣ በጤና ጉድለት የመጎሳቆሉ ፣ ታሞ ለመዳን የመቸገሩ ፣ እንደ ሰው በአግባቡ ወደ መቃብር ለመውረድ ያለመቻሉ፣ እና በአጠቃላይ ከደመ ነፍስ እንስሳት በታች የመኖሩ (ኑሮ ከተባለ) መሪር ሁኔታ ይቀጥላል።

ልክ የሌለውንና ለምድሩም ሆነ ለሰማዩ ህይወት የማይበጀውን መከራ ተሸካሚነት መንግሥተ ሰማያት እንደሚያስገባው እዮባዊ ትግስት እየተረጎምን  ከልክ ያለፈ መርህ አልባነትን እንደ ትክክለኛ ሰጥቶ የመቀበል መርህ እየቆጠርን  አድርባይነትን ወይም ወስላታነትን ወይም ልክስክነትን እንደ ትክክለኛ የኑሮ ዘዴ እየተከተልን  ልክ የሌለው ፍርሃትንና እኖር ባይነትን ከትክክለኛው የኢትዮጵያዊነት ጨዋነትና ትእግሥት ጋር እያደበላለቅን፣ ለአገር አፍራሾች ሥርዓት እምቢ አልገዛም ብሎ ማመፅን እንደ አገር ማፍረስና አጉራ ዘለልነት እየቆጠርን  በልሂቅነት (በምሁርነት)  ስም ወይም ሽፋን እራሰቸውን ፀያፍና አደገኛ ለሆነ  የፖለቲካ ዝሙት አሳልፈው የሰጡና የሚሰጡ ወገኖችን በአግባቡና ገንቢ በሆነ ሂስ ነውር ነው ለማለት እየተሽኮረመምን፣ የፈጣሪን ሐዋርያዊ ሃላፊነት የተሸከሙ ወገኖች ሃይማኖትን ለትክክለኛው ሰማያዊና ምድራዊ ህይወት የሚበጅ  ሥርዓት እውን ይሆን ዘንድ እኩያን ገዥዎችን ለመገሰፅ ወኔው ሲከዳቸው በግልፅ እየታዘብን ለምንና እንዴት ብሎ መጠየቅን ወደ ገሃንመ እሳት እንደ መግባት  አድርገን እያሰብን ፣ ወዘተ እንኳንስ ዴሞክራሲያዊት ከነባርነታችንና ድህነታችን የምንኖርባት አገር አትኖረንም።

ለዚህ ሁሉ የውድቀት አዙሪት ግንባር ቀደም ሃላፊዎችና ተጠያቂዎች ባለጌና እኩያን ገዥ ቡድኖች ፣ የፖለቲካ ቁማር ተጋሪዎቻቸው እና በተቀዋሚነት ስም የፍርፋሪያቸው ሰለባዎች ያደረጓቸው ወራዳ ፖለቲከኞች መሆናቸው እውነት ነው።

ይህ ግን በተለይ ምሁርና ልሂቅ ነኝ የሚለውን የህብረተሰብ ክፍል  ከፖለቲካና ከሞራል ውድቀት  ተጠያቂነት ነፃ አያደርገውም። እንዲያውም ለህይወት ስኬት ይበጀው ዘንድ የተቀበለው (ያገኘው) መደበኛም ይሁን ኢመደበኛ የቀለምና የክህሎት ሥልጠና የሃላፊነቱን ደረጃ ከባድ ያደርገዋል።  ለመግለፅ ከሚያስቸግር የአራት ዓመታት ፖለቲካ  ወለድ ሰቆቃ  ከምር ለመማርና የተሻለ ምሁራዊ ሥራ  በመሥራት መከረኛው ህዝብ ከተዘፈቀበት የውድቀት አዙሪት ሰብሮ እንዲወጣ  የበኩሉን እገዛ ያደርጋል  ተብሎ የሚጠበቀው አብዛኛው ምሁር (ልሂቅ) እርሱ እራሱ አይወድቁ ውድቀት ሲወድቅ ማየት በእጅጉ ያስፈራል።

ከዘመኑ የሥልጣኔ ግሥጋሴ አንፃር በትምህርት ዘርፉ በእጅጉ ወደ ኋላ የቀረን መሆኑ አጠያያቂ አይደለም። ራሳችንን አሁን ባለንበት እጅግ አስከፊና አስፈሪ ሁለንተናዊ ውድቀት ውስጥ ያገኘንበት ምክንያት ግን በዋናነት እውነተኛ የምሁርነትና የልሂቅነት እሴትን ከምር በሆነ የችግር መፍቻ መፍትሄነት ፣ የእውነተኛ ዴሞክራሲያዊት አገር እውን ማድረጊያ መሣሪያነት  የሞራል ልእልና መጎናፀፊያነት  ከእውነተኛ የአርበኝነት ስሜት አደርባይነትን (አሽቃባጭነትን) በፀያፍነት ከማየት  ለትውልድ ከመጨነቅ (ከማሰብ) ማንነት  ከሰብአዊ መብቶች መረጋገጥና መከበር አስፈላጊነት ወዘተ ጋር አቆራኝተን ለማየትና ለመጠቀም ያለመቻላችን ውድቀት ነው።

“እኔ ብልፅግና አይደለሁም ግን ብልፅግና በለገሰኝ ወንበር  ወይም ሥልጣን ላይ  ተቀምጨ የብልፅግናን አጀንዳና ፖሊሲ ለማስፈፅም የተዋጣልኝ የዚህ ወይም የዚያ የሙያ መስክ ባለሙያ ነኝ” ሲል ሃፍረት ጨርሶ የማይሰማው  ፈላስፎች በየህብረተሰቡ የእድገት ደረጃ የተነሱ ጥያቂዎችን ለመመለስ የተፈላሰፉበትን (የተጠበቡበትን) አስተሳሰብ እና የመፍትሄ ሃሳብ ከአብይ አህመድ  ሸፍጠኛና ሴረኛ  “የመደመር” ፖለቲካዊ ድርሰት ጋር አገናኝቶ ውዳሴ ከንቱ ሲያዥጎደጉድ  ጨርሶ ህሊናውን የማይኮሰኩሰው  የኦህዴድ/የኦነግ የፓርላማ አባል እና የአዲስ አበባው ከተማ ምክር ቤት አባል በህዝብ (በማህበረሰብ) ላይ ጋጠ ወጥ የስድብ ናዳ ሲያወርዱ ነውር ነው ከማለት ይልቅ ይባስ ብሎ ለማጣጣል ሲሞክር ህሊናውን ጨርሶ የማይኮሰኩሰው   አብይ አህመድ  በህገ ወጥ መንገድ (የምርጫ ህግና ደንብን በመጣስ ) በተካሄደ ምርጫ አሸንፍኩ ብሎ በህገ ወጥ መንገድ ሥልጣን ላይ ከሰነባበተ በኋላ ለይስሙላ ባካሄደው የፓርቲው ጉባኤ ተብይ አስመራጭና ተመራጭ በመሆን እጅ አስወጥቶ ራሱን በማስመረጥ የመከራና የውርደት ሥርዓቱን ሲያራዝም እያየ “እንኳን ደስ ያለን” ሲል ፈፅሞ ሃፍረት የማይሰማው ምሁር ለዚህ ትውልድ መልካም አርአያነት ይኖረዋል ብሎ ለመገመት በእጅጉ ያስቸግራል።

ይህ የውድቀት አዙሪት ፈተና በዓለማዊው ምሁርነት ብቻ ሳይሆን በሃይማኖታዊው (በመንፈሳዊው) ዓለምም ጎልቶ የሚታይ መሆኑን ማስተባበል የሚቻል አይመስለኝም። “ነብይ” በሚል ማዕረግ እርስ በርሱ እየተሿሿመ ወይም እራሱን እየሾመ እና ለማታለያነት የቀመረውን “የትንቢት” ትርክት ከየመፀሐፉ ምእራፍና ቁጥር ከቃረመው ጥቅስና ሃይለ ቃል ጋር እያስማማ ሃይማኖታዊ እምነትን (ፈጣሪን) የእኔ/የእኛ ነው ለሚለው ሸፍጠኛ፣ ሴረኛና ግፈኛ ገዥ ግለሰብ ወይም ቡድን ተባባሪ ለማድርግ ሲጥር ህሊናው ጨርሶ የማይወቅሰው ወገን እየበዛ የመምጣቱ መሪር እውነት በእጅጉ አስደንጋጭና አሳሳቢ ነው።

ዶ/ር የሚል የልሂቅነት ማእረግ ተሸክሞ የሳልሳዊው ቴዎድሮስን ትርክት (ንግርት) ከአብይ አህመድ ንግሥና ጋር ለማገናኘት የሚያስችለውን ድርሰት ለማዘጋጀትና ለዚሁና መሰል ዓላማዎች ባሰለጠነው አንደበቱ ለመደስኮር በእጅጉ ሲጨነቅ (ሲጠበብ) ማየት የእውነተኛ ነፃነትና ፍትህ ፈላጊ ዜጋ ህሊናን በእጅጉ ያቆስላል። ፍትህንና ነፃነትን የደፈጠጡ “ብልፅግናዎችን መገዳደር ፈጣሪን እንደ መገዳደር ነው” በሚል አይነት እጅግ ጨካኝ ዲስኩር  ሊያሳምነን ሲከጅለው ህሊናውን ጨርሶ አይኮሰኩሰውም ።ያንን ሁሉ የፈጠራ ትርክት (ትንቢት) ሲያነበንብ አንድም ቦታ ላይ የፍትህንና የሰብአዊ መብትን አስፈላጊነት ለመጥቀስ ያልፈለገው “ትንቢተኛ” ልሂቅ ስለ የማይደፈረው ብልፅግና ፓርቲና ስለ መሪው አብይ አህመድ መሲህነት (ክርስቶሳዊነት) በገደምዳሜ ነግሮን አሜን ሊያሰኘን ሲሞክር ማየትና መስማት የልሂቅነት (intellectualism)  ትርጉምና እሴት ምን ያህል እየተጎሳቆለ እንደመጣ ለመገንዘብ አይከብድም። እኛም እንዲህ አይነት ወገኖችን ነውረኝነታችሁ ልኩን እያለፈ ነውና አደብ ግዙ ለማለት ወኔው እያጠረን ተቸግረናል።

 

አዎ! አብዛኛው ነገረ ሥራችን ግልፅና ግልፅ የሆነውን የመከራና የውድቀት ትርክት በማመንዠክ እና የአልቃሽና አስለቃሽ ሙሾ በማውረድ ላይ እንጅ ምን እና እንዴት መደረግ አለበት (what is to be done and how)? በሚሉ ቁልፍና ፈታኝ ጥያቄዎች ዙሪያ አለመሆኑ በእጅጉ ሊያሳስበን ይገባል ።

ልብ ብሎ ለሚታዘብ እውነተኛ ነፃነትና ፍትህ ፈላጊ የአገሬ ሰው ያለ ተግባራዊ መፍትሄ ወይንም ዘዴ የምንተርከውና የምንዘረዝረው የሰቆቃና የውርደት ትርክት ስለ እኛው ስለራሳችን አይመስልም። የዜና ፣ የትንታኔ፣ የዲስኩር ፣ የስብከት ፣ የውይይት፣ የእግዚኦታ፣ የምህላ ፣ የትንቢት ፣ የለቅሶ፣ የቀረርቶና ፉከራ፣ የቅኔ ፣ የዝማሬ ፣ የዘፈን ፣ ወዘተ ጋጋታ በራሱ ፋይዳው ምንድን ነው? ተብለን ብንጠየቅ ያንኑ የለመደብንን ሰንካላ ሰበብ እንደረድር እንደሆን እንጅ አጥጋቢ መልስ የሚኖረን አይመስለኝም። ባለጌና ግፈኛ የጎሳ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ቁማርተኞቻችንም በእጅጉ የናቁንና ያዋረዱን ለዚህ ነው። አዎ! ከሦስት አሥርተ ዓመታት እና በተለይም ከአራት ዓመታት እጅግ አስከፊ አገዛዝ በኋላም እዚህ ግቡ የሚባሉ አወንታዊ እርምጃዎችን ለማስቆጠር ያልሆነልንም ለዚህ መሆኑን ለመረ፞ዳት ብዙ መድከም አይጠይቀንም።

ይህ ባይሆንማ ኖሮ የሩብ ምእተ ዓመት እኩይ ከዥዎቻችን በሥልጣን ሽኩቻ ምክንያት  አንጃ ፈጥረውና አንዱ አራት ኪሎና ሁለተኛው መቀሌ መሽገው  በጎሳ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ቁማር ክፉኛ የሰከሩ  አጋሮቻቸውን በየአካባቢው አሰማርተው ፣ አንዳንድ የተቃውሞ ፖለቲካ ቁማርተኞችን የአድርባይነት ፍርፋሪ ተመፅዋቾቻቸው አድርገው፣  እጅግ በጣት ከሚቆጠሩት በስተቀር አብዛኛውን የሃይማኖት መሪና ሰባኪ ነኝ ባይን በሥጋዊ ፍላጎት ትኩሳት አቅሉን (ህሊናውን) አነሁልለው (አደንዝዘው) ፣ እና ከየመፅሐፋ እና ከየሰፈሩ የሚቃርመውን  ሁሉ “በትንቢተኝነትና በአነቃቂ ንግግር አዋቂነት (prophetic and motivational speaker) ስም  እያቀነባበረ መከረኛውን ህዝብ የሚያደነዝዝላቸውን ቀጥፎ አዳሪ ምሁር ነኝ ባይ የፍርፋሪያቸው ልክፍተኛ አድርገው ይኸውና ከአራት ዓመታት በላይ አይተነውና ሰምተነው የማናውቀውን የመከራና የውርደት ዶፍ እያዘነቡብን ባልቀጠሉ ነበር።

“ለዚህ ሁሉ ለማመን የሚያስቸግር ሰቆቃና ውርደት ዋነኛው ምክንያት የባለጌና የጨካኝ ገዥ ቡድኖች ሥርዓት መሆኑን ካወቃችሁ እና ይህ ደግሞ ሊለወጥ የሚችለው የግፍ፣ የመከራና የውርደት ቀንበር በቃን በሚል የተባበረ ትግል (አልገዛም ባይነት) ማስወገድ ሲኖርባችሁ ማቆሚያ የሌለው የሰቆቃ እሮሮ   እሮሮውና ለቅሶው አብዝቶ በመተረክ ላይ  የመጠመዳችሁ  መሪር እውነት የውድቀት አዙሪት ካልሆነ ሌላ ምን ይሆናል? “ተብለን ብንጠየቅ ምላሻችን እንኳንስ አጥጋቢ ከምር ስሜት የሚሰጥ የሚሆን አይመስለኝም ።  አሳማኝ መልስ እሰጣለሁ ብሎ ይበልጥ ከመንገታገትና ህዝብንም ይበልጥ ከማደናገር (ከማደንዘዝ) “አዎ! ወድቀናል፤ ከውድቀት ተምሮ ለመነሳት ግን ቁርጠኞች ነን” ማለቱ ትክለኛ መልስ ይመስለኛል።

በእውነት ስለ እውነት ከተነጋገርን የገንዛ ራሱን የውድቀት አዙሪት ከምር ተገንዝቦ ፣ ተቀብሎ እና ተፀፅቶ እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን እውን ማድረግ ሲሳነው ጎሳን ወይም የተወለዱበትን ማህበረሰብ ምሽግ በማድረግ የግፍና የዝርፊያ ፖለቲካ ሥርዓታቸውን ያስቀጠሉ ገዥ ቡድኖችን “እባካችሁ ሰይጣናዊ የፖለቲካ ባህሪያችሁን ወደ ምድራዊ መላእክትነት ለውጡና ከጫናችሁብኝ የመከራና የውርደት ቀንበር ገላግሉኝ” በሚል የሚማፀንና ማለቂያ የሌለው የመከራ ጩኸት የሚጮህ  ትውልድ የዓለም ከንፈር መምጠጫ ፣ መሳቂያና መሳለቂያ ቢሆን ለምንና እንዴት ይገርመናል?

ለዘመናት የመጣንበትና አሁንም እጅግ አስከፊ በሆነ ሁኔታ በተረኞች የቀጠለው የፖለቲካ ሥርዓት በዚህ ትውልድ ላይ ያስከተለውን ሰቆቃዊ አሟሟትና የቁም ሞት ለመረዳት የጤናማ ህሊና ባለቤት መሆን ብቻ በቂ ነው።   ከአራት ዓመታት ለመግለፅ የሚያስቸግር የሰቆቃ ተሞክሮ በኋላም ከአስከፊውና ከተደጋጋሚው የውድቀት አዙሪት ሰብሮ ለመውጣት የሚያስችል ግልፅ የሆነ የትግል ራዕይ ፣ ዓላማ ፣ መርህ፧  ፍኖተ ሃሳብ (ራዕይ)፣ እቅድ፣ ስትራቴጅ፣ የአፈፃፀም ዘዴ፣ መዋቅራዊ ሃይል (ድርጅት) ፣ ወዘተ እውን ሊያደርግ ያልቻለ ትውልድ አሁንኑ ቆም ብሎና ትንፋሽ ወስዶ ራሱን ለምንና እንዴት? ብሎ መጠየቅና ለራሱ እንቆቅልሽ ትክክለኛውን መልስ አምጦ መውለድ ይኖርበታል።

በተረኛ የኢህአዴግ አንጃ ቡድኖች ለአራት ዓመታት የተፈፀመውና አሁንም እየተፈፀመ ያለው ሁለንተናዊ ሰቆቃ ለምንና እንዴት መሪር ትምህርት አልሆነን አለ?  ይህንን እጅግ አስከፊ የውድቀት አዙሪት ለመለወጥ ለምንና እንዴት ተሳነን?  በቃኝ ሳይሉት በርህራሄና በለጋስነት ፍፃሜውን ያገኘ ወንጀለኛ የአገዛዝ ቡድን እንደሌና እንደማይኖር ከእኛው ከእራሳችን ተሞክሮ በላይ ማስረጃ ፍለጋ ርቀን መሄድ አለብን ወይ? ይህንኑ መሪር ፈተና በውጤታማነትና በዘላቂነት ለመወጣት የሚያስችል የጋራ ትግል ከማድረግ ይልቅ የጎሳ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ቁማርተኞች በሚቆጣጠሩት ቤተ መንግሥት ዙሪያ ለምንና እንዴት እንልከሰክሳለን?  የመከራችንና የውርደታችን ዘመን ከሚያራዝሙ ገዥ ቡድኖችና ግብረ በላዎቻቸውጋር የፖለቲካ ዝሙት እየፈፀምን ዴሞክራሲ ናፋቂዎች ነን ማለት ምን ማለት ነው ዓላመውና ግቡ ከሦስት ዓሥርተ ዓመታት በላይ (27+4) ግልፅና ግልፅ መሆኑ በመስማት ወይም በማየት ብቻ ሳይሆን በአስከፊ ድርጊታዊ ተሞክሮ የታወቀውን ኢህአዴግ/ብልፅግና ሠራሽ የጎሳና የቋንቋ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ሥርዓትን እንደ ሥርዓት ወደ ታሪክ ሙዚየም ለመሸኘት እና የምንናፈቀውንና አብዝተን የምንሰብክለትን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን ለማድረግ የተቸገርነው እውን አቅም ነው ወይስ የቅንነት፣ የታማኝነት፣ የሞራል ልእልና እጥረት ፣ የእውነተኛ የአገር ፍቅር (real sense of patriotism) እጦት ፣ ወዘተ ነው ?  እውን የምናወራውን (የምንደሰኩረውን) ያህል የአንዳችን መጠቃት የሌሎቻችን ወይም የሁላችን መሆኑ ይሰማናል?  ለሚሉና መሰል ጥያቄዎች ከግልብ ስሜት ክፉ አባዜ ወጥተን ተገቢውንና ወቅታዊውን መልስ ለመሥጠት ገና አልተሳካልንም።  የገንዛ ራሳችንን የፖለቲካና የሞራል ቀውስ ከምር ለመረዳትና ለመጋፈጥ  ወኔው እያጠረብን ተቸግገረን ነው እንጅ   በመከራና በውርደት የፖለቲካ ሥርዓት ሥር ከመጠን በላይ በቆየን ቁጥር ይበልጥ አምርሮ ከመታገል ይልቅ መከራውን ይበልጥ እየተለማመድነው የመምጣታችን ክፉ ልማድ በእጅጉ አስፈሪ ነው።

የእውነተኛ መብትና ነፃነት ባለቤት የሆነ መልካም ዜጋና ሰብአዊ ፍጡር ሆኖ መኖርን በእውን የሚሻ ትውልድ የጎሳ አጥንት ስሌት ፖለቲካን ምሽጋቸው ያደረጉ ቁማርተኛ ገዥ ቡድኖችን የመከራና የውርደት አገዛዝ ቀንበር ተሸክሞ ለዚህን ያህል ጊዜ የመዝለቁና አሁንም መሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ የሥርዓት ለውጥ እውን ለማስደረግ በሚያስችለው ሁኔታ ላይ ያለመሆኑ መሪር እውነት በእጅጉ ካላሳሰበንና ካላስፈራን አብዝተን የምደሰኩረው አገር ወዳድነት (patriotism) የውሸት (የይመስል) ነው የሚሆነው። ለዚህ ነው ሸፍጠኛና ጨካኝ ገዥ ቡድኖች ይሠራል ብለው ሲያስቡ መስማት የምንፈልገውን እየነገሩ በማነሁለል (በማደንዘዝ) እና ይህ አልሠራ ሲላቸው ደግሞ ጨካኝ ሰይፋቸውን እየመዘዙ የመከራውንና የውርደቱን ሥርዓታቸውን እጅግ በአስከፊ ሁኔታ በማስቀጠል ላይ የሚገኙት።

እጆቻቸው ለዘመናት በዘለቀ የንፁሃን ደም እንደተጨማለቁ ከተናዘዙና ይቅርታ ከጠየቁ በኋላ ብዙም ሳይቆዩ በባሰ ሁኔታ  ወደ ነበሩበት ተመልሰው በተዘፈቁ ኢህአዴጋዊያን (ብልፅግናዊያን) እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን ይሆናል ብሎ መጠበቅ የለየለት የፖለቲካና የሞራል ተሸናፊነት (ዝቀጠት) ነው። እናም መፍትሄው ይህንን በአስከፊና ጨርሶ ሊፈወስ በማይችል አኳኋን  በፖለቲካ ወለድ ወንጀል  የበሰበሰና የከረፋ ሥርዓት ፅእኑና ዘላቂ በሆነ  የአልገዛም ባይነት ተጋድሎ አስወግዶ እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን እውን ማድረግ ብቻ ነው።

ከገንዛ ራሳችንን መከራና ውርደት ተሞክሮ ተምረን ከዚህ አስከፊ የውድቀት አዙሪት ለመውጣት ሌላ አያሌ ዓመታትን እንደማይወስድብን ያለኝን ተስፋ እየገለፅሁ አበቃሁ!

የኦነግ

 

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Latest from Blog

አስቻለው ፈጠነ የኢትዮጵያን ባህላዊ ሙዚቃ ከዘመናዊ ተፅዕኖዎች ጋር በማዋሃድ ባሳየው ልዩ ችሎታ የተቸረው አርቲስት ነው ። ጥበባዊ ጥረቱ ብዙ ጊዜ የኢትዮጵያን ጥልቅ ባህላዊ ትሩፋት እና የሙዚቃ ልምምዶች በልዩ ሚዛን፣ ዜማ እና ዜማ

አሞራው ካሞራ | አስቻለው ፈጠነ

January 15, 2025
ፈራ ተባ እያልን እንጂ ስለፋኖ ትግልና አደረጃጀት ብዙ የሚባል ነገር አለ፡፡ እንዳጀማመሩ ቢሆን ኖሮ እስካሁን ፋኖ ኢትዮጵያን በአጠቃላይና አማራን በተለይ ከታወጀባቸው የመፈራረስና የዕልቂት ኦነግ-ኦህዲዊ ዐዋጅ ነጻ ባወጣቸው ነበር፡፡ ይሁንና በምናውቀውም በማናውቀውም በምንገምተውም

ይድረስ ለፋኖ አደረጃጀቶች በያሉበት – ነፃነት ዘገዬ

የአማራ ሕዝብ የኅልውና ትግል፦ ዘርፈ ብዙ የጥቃት ሰለባ የሆነ መንግሥት መር፣ ማንነት ተኮር እልቂት ለታዎጀበት ሕዝብ በጥብአትና በጀግንነት የሚከናወን የዘመናችን ሐቀኛ አብዮት ነው። አማራው በዋለበት እንዳያድር፣ ባደረበት እንዳይውል ተወልዶ ያደገበት ቀዬ ድረስ

ከአማራ ፋኖ አደረጃጀቶች የተሰጠ የጋራ መግለጫ!

January 14, 2025
ኤፍሬም ማዴቦ ([email protected]) ባለፉት ሁለት ወራት አገር ውስጥና በውጭ አገሮች ያሉትን የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ካጨናነቁ ዜናዎች ውስጥ አንዱ ፓርላማው ይህንን ወይም ያንን የህግ ረቂቅ አጸደቀ የሚሉ ዜናዎች ናቸው። የኢትዮጵያ ፓርላማ ምንም ይሁን ምን

የኢትዮጵያ ፓርላማ ሲመረመር

 ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)   ጥር 2፣ 2017(January 10, 2025) መግቢያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ

ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?

ከሃይለገብርኤል   አያሌው የኦቦ ሲራጅና የወይዘሮ ፉንታዬ ልጅ ጃዋር መሃመድ ትላንትን ዛሬንና ነጋችንን ሊያሳይ የሚችል መጽሃፍ አዘጋጅቶልናል:: በእውነቱ መጽሃፉ ሊነበብ በሚችል የሃሳብ ፍሰት ተቀንብቦ በአነጋጋሪነቱ ቀጥሏል:: ጃዋርን እና የቄሮን ትውልድ በቅጡ ለመረዳት መጽሃፉ ማንበብ

የጃዋር የፖለቲካ ጅዋጅዌ! “ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ’’

ጥር 2 ቀን 2017 ዓ/ም   January 10, 2025  በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡ ቤተ ሰብ፡ ወዳጅ ዘመዶቻችሁን ያጣችሁ: ልጆቻችሁን የቀበራችሁ፡ አካልችሁን ያጣችሁ፡ የተሰነዘረውን ብትር በመከላከል ላይ ያላችሁ፡ያለፈቃዳችሁ በመንግሥት ተጽእኖ ወደመግደልና

በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛ ተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡

January 10, 2025
Go toTop