መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ
ይህን ፅሑፍ ለመፃፍ ያነሳሳኝ ፣አብዛኛው የትግራይ ኗሪ ፣ ወያኔ ከጅምሩ ካጠመቀው የጎሣ ና የቋንቋ መንገድ መውጣት አቅቶት ፤ ኢትዮጵያ አገሩ እንደሆነች አሥረስቶት ከአንድ ፋብሪካ እንደተሰራ አሽግ ቁሥ ወጥ የሆነ ባህሪ እንዲያሳይ ማድረጉን ያለማሥተዋሉ ነው ። ( እርግጥ የወያኔ በጭካኔ የተሞላ ተግባር በራሱ ዜጎች ላይ ከበረሃ ጀምሮ የታየ ነውና በፍርሃትትግራይ ያለው ኗሪ ጥቂት የማይበለው አንድ አይነት የኮኮ ጥርሙስ ሆኖ መታየቱ አያሥገርምም ፤ የሌት እና ቀን ፣ ፕሮፖጋንዳውና እሥከ ጎጆው የዘለቀው የአንድ ለአምሥት ጥርነፋ ለ30 ዓመት አደንዝዞታልና ቆም ብሎ ያለማሰቡ በጥፋት ጎዳና ቢያሥጉዘው አይገርመኝም ። ያሥገረመኝ ማሐል አገር የሚኖር ሰውነቱን የረሳ ምሁር ነኝ ባይ በሰው ቁሥል ላይ እጨት ሲሰድ ማሥተዋሌ ነው ። ( ወንድም ወንድሙን በመግደሉ መጨፈር ሰውነት አይደለም። አውሬነት እንጂ !! )
ለመሆኑ ትግራይ የትግራውያን ብቻ ነች እንዴ ? እንዲህ ከሆነማ ፤ የመላው ኢትዮጵያዊያን እናት ና አባቶች የአድዋ ና የማጨው መሰዋትነት ከቱ ነበር ። ያ በአደዋ ና በመቀሌ በፋሺስት ኢጣሊያ ምሽግ ላይ የፈሰሰው ደምና የተከሰከሰው አጥንት በከንቱ ለአፈር ማዳበሪያነት የዋለ ነበር ። ትላንት የወያኔንን ጨካኝ ጭፍጨፋ ለመመከት የወደቀው የኢትዮጵያ ሠራዊት መሰዋትነትም የዕቃ እቃ ጨዋታ ነበራ !
የወያኔ ሎሌዎች ና መሰሎቻቸው በሃሺሽ ጦዞው የሚቀባጥሩት የዘረኝነት ቅሥቀሳ ግቡ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነትን ከኢትዮጵያ ጠላቶች ጋር መቅበር ነውና በባዳነት ተሰልፈው ፣ ታሪካችንን ለመደምሰስ ቢጥሩ አያሥገርምም ።
እንደጨው ዘር በመላው ኢትዮጵያ ተበታትነው ከሌሎች ቋንቋ ተናጋሪ ጋር ተጋብተው የተዋለዱት የትግሪኛ ቋንቋ ተናገሪዎች አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ናቸውና የሎሌውን የጌታቸውን ፕሮፖጋንዳ አጥብቀው ይቃወማሉ ።
የገንጣይ ሥም ባላቸው በህወሓት የትላንትም ሆነ የዛሬ መንገድ ላይ ከቶም አይራመድም ። የአሁኑ አፀያፊ የባንዳ ተግባር የተቀነባበረው ታሪክ ይቅር በማይለው የሐሰት ቅሥቀሣ ነው ።
ህውሃት ከጅምሩ ፣ በዘረኝነት ያበደ ጭንቅላት ሥላለው ዛሬም ከዚህ አውዳሚ የፋሺሥት ተግባር አለመላቀቁ አይገርምም ። ይህ ግዝፍ የነሳ የዘረኝነት ና የባንዳነት አሥተሣሠቡም ዛሬ ጎልቶ መውጣቱ ፣ ጨካኝና ግፈኛ ና ዘርፎ በል አሸባሪ ቡድንነቱን በይበልጥ አሳውቆናል ። ጨካኝና ግፈኛና ዘርፎ በል ብቻ ሳይሆን በሰው ደም ፣ በሰው ሞት የናጠጠ ሀብታም በመሆኑ ፣ በዘረፋ ሀብቱን አጥቶ እሥካልደኸየ ድረሥ የጥፋት ተግባሩ እሥከ መሐል አገር መቀጠሉ አይቀሬ ነው ።
በዘረኝነት ያበደ ና በዘረፋ የኖረ ድርጅት ነውና ፣ “ ሠርተህ ብላ “ ብትለው ከቶም በጄ አይልም። እናም የአሁኑ ድንገቴ ፣ የተኩስ አቁም ሥምምነት በውሸት ቅሥቀሣው ግራ የተጋባው የትግራይ ህዝብ ይህንን የዘረፋ አሥተሳሰብ ያለውን አጥፊ ቡድን የበለጠ እንዲረዳው ና እንዲገነዘበው የማሰብያ ጊዜ ይሰጠዋል ።
የጥፋት ኃይሉ ፣ ማለትም አሸባሪው ቡድን በ1983 ዓ/ም ፣ በህዝቡ ጭቆና ፣ እርዛት ፤ በችጋር ና በቸነፈር መጠቃት ሰበብ ወደሥልጣን ቢመጣም ፣ ሥልጣኑንን ለግል ብልፅግናው እንጂ ፣ ሥልጣኑንን የህዝቡን ጥያቄ መለሻ አላደረገውም ። 1.8 ሚሊዮን የትግራይ ህዝብ በእርጥባን ኗሪ ነበር ። በ27 ዓመቱ የወያኔ /ኢህአዴግ የሥልጣን ዘመን ተጠቃሚዎቹ ባለሥልጣናቱ ና የትግራይ ጀነራሎቹ ነበሩ ። ንጉሣዊ ኑሮ የሚኖሩ ባለፎቅና ባለፋብሪካ መሆናቸውን የትግራይ ህዝብ አሣምሮ ያውቃል ። ይህ ምድር ላይ ያለ እውነትን የትግራይ ህዝብ በጊዜ ርዝመት የተሰወረ የድሮ ታሪክ አይደለም ። የዛሬና የአሁን ታሪክ እንጂ !
ታዲያ ለምን ከአሸባሪው በንዳ ጋር ጥቂት የማይባለው የትግራይ ህዝብ ቆመ ? ለምንሥ የመከላከያ ኃይሉን ፤ የኢትዮጵያን ፤ የገዛ አገሩን ሠራዊት ከኋላው ወጋው ? ዛሬም በእርጥባን መኖር ናፍቆት ? ዛሬም ሌሎች በእሱ ጀርባ ተንጠላጥለው እንዲበለፅጉ ፈልጎ ? አይመሥለኝም ።
በእኔም ሆነ በብዙዎች አሥተዋዮች ግምት ፣ አንደኛ ከህዝቡ ከግማሽ በላይ ዕድሜው ከ30 ዓመት በታች በመሆኑ በሥሜት ና በውሸት ለመነዳት በመቻሉ ። ሁለተኛ የሚቀምሰው ና የሚልሰው ያጣ በመብዛቱ ፣ እና የእርዳታ እህሉን ወያኔ በዋሻ በማከማቸቱ ና ሥንቅ ከእኔ ጋር ነው የምታገኙት በማለቱ ።
በሦሥተኝነት የሚጠቀሰው ፍራቻ ሲሆን ፤ ከወያኔ ጋር ያለመተባበር ደግሞ የሚያሥከፍለው ዋጋ ህይወትን በአሰቃቂ መንገድ ማጣት በመሆኑ ፤ ከመገደልና ታረዶ ለጅብ ከመሰጠት ሰሳይወድ በግዱ የጥቂት ሤጣናትን ፈቃድ ፈፃሚ ሆኗል ።
በነዚህና በሌሎችም የፍራቻ ና ህይወትን የማሥቀጠል ምክንያቶች ፣ ግፈኛውን አሸባሪ ቡድን የትግራይ ህዝብ ፈርቶታል። ገሚሱም ፣ እንደማይፈታው አውቆ” ጎመን በጤና “ በማለት አድብቷል ። ሰው ፍርሐትን እሥካልገደለ ድረሥ የህይወት ድንክ ሆኖ መኖሩ ደግሞ እርግጥ ነው ። የትግራይ ህዝብ ከፍርሐት ይወጣ ዘንድ ከእውነተኛ ጠላቱ ጋር ማፋጠጡ ተገቢ እርምጃ ነው ።በዲህ አይነት የእውነት ፍለጋ ነው ፣የትግራይ ህዝብ ወያኔ ከ1983 ዓ/ም ሰኔ ወር ጀምሮ የፈፀመውን ሥህተት መገንዘብ የሚቻለው ።
ወያኔ ራሱን ኢህአዴግ የተሰኘ ካባ አልብሶ ፣ ከሽግግር መንግሥቱ ጀምሮ ፣ የብሔርተኝነት ሥሜትን በእጅጉ በማጉላት ከፍተኛ ሥህተት ፈፅሟል ። ለሁሉም ባህሎች ነፃነት መሥጠት ና አክብሮት ማሳየት አንድ ነገር ሲሆን ፣ ሰዎችን በብሔር ና በቋንቋ ፖለቲካ እንዲደራጁ በማድረግ ነበር የአራት ኪሎ ቤተመንግሥትን ሲቆጣጠር ተቀዳሚ ሥራው ያደረገው ። በብሔር ፖለቲካ ላይ የተመሠረተ መደራጀት አደገኛ የሆነ መቃቃርን በህዝቦች መካከል እንደሚፈጥር እያወቀ ይህንን በዓለም መንግሥታት ውሥጥ የሌለ ርዕዮት አብዮታዊ ዴሞክራሲ ካባ ፈጥሯ እውን አደረገው ።
መንግሥታት ግን በሣይንሥ በተረጋገጠ ና በታወቁ ርዕዮት ነው የሚመሩት ። የታወቀ የፖለቲካ መሰመር ባላቸው ሊሂቃንም ነው የሚመሩት ። ሊሂቃኑ በርዕዮት_ ዓለም ፤ በአመለካከት ፤ በመደብ ፣ በይዘት ፣ ወዘተ ። የዳበረ ህሊና ያላቸው ናቸው ። ሰዎችን በብሔር ለመለያየትም ከቶም አይፈልጉም ።ሰዎችን በብሔራቸው መግፋት ጨቆኝነት ነው ።
ወያኔ ግን ፣ ኢትዮጵያውያን ፣ ኢትዮጵያዊያን መሆናቸውን ክደው በብሔራቸው እንዲምሉ ለ27 ዓመት ሠርቷል ። ሰውነትንን እና ዜግነትን እና ፈጣሪን አሥክዷል ።ዜጎች በቋንቋዊ አመራር ነፃነታቸውን አጥተው ፣ በብሔራቸው መታወቂያ እንዲሰጣቸው አድርጎ ነበር ።
በኢትዮጵያዊነት ለመታወቅ የሚፈልጉ ፣ ከሁለት ቋንቋ ተናጋሪ የተወለዱትን ከፖለቲካዊና የቋንቋ ፖለቲካው ከሚያሥገኘው ጥቅም እንዲገለሉ አድርጎ ነበር ። እነዚህ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች የመምረጥ እንጂ የመመረጥ መብት አልነበራቸውም ።
ከዚህ ምርጫ ውጤት በኋላ በሚቋቋመው መንግሥት ፣ ዜጎች ፣ ለቀያቸው እትብታቸው ለተቀበረባቸው ቦታዎች ሁሉ ባይተዋር እንደማይሆኑ አሥባለሁ ። ከአምሥት ዓመት በኋላ ቋንቋ አወቁም አላወቁም በተወለዱበት እና በኖሩበት አካባቢ ፤ ገጠር ይሁን ከተማ በምርጫ የመወዳደር መብት ይኖራቸዋል ። የሚል እምነትም አለኝ ። ይህ እምነቴ የመነጨው የ21 ኛውን ክ/ዘ በቅጡ ከተረዳው ከብልፅግና ፖርቲ መሪ ከደ/ር አብይ አህመድ በብልሐት ና በጥበብ የተመራ ለውጥ ጉዞ ነው ።
የኢትዮጵያ መንግሥት የአሸባሪውን ጥቂት ቡድን የህወሓትን “እኔ ከሞት ሰርዶ አይብቀል። “ የሚል አካሄድን በመረዳት ፣ “የተኩሥ አቁም “ በተናጥል ማድረጉ ፤ ዓለምን በውሸት ፕሮፖጋንዳ ያጭበረበረውን ፣ የአብዬን ወደ እምዬ “ የማላከክ የአሻጥር ጫወታ የሚጫወተውን ፣ ለአገር እና ለህዝብ ደንታ የሌለውን አሸባሪ ቡድን የሚያጋልጥ በመሆኑ የሚደገፍ ነው።
ከበርቴዎቹ ህወሃትዎች የመንግሥትን እጅ ለመጠምዘዝም ሆነ ፣ እኔ ከሞት ሰርዶ አይብቀል እንዳለችው እንሥሣ አገርን በማያባራ ጦርነት ውሥጥ ለመክተት ያላቸውን ብርና ዶላር በሰፊው መርጨታቸውና ቅጥር ነፍሰ ገዳይ ሽፍቶችንና በየአገሪቱ ማሠማራታቸውን እሥከዕለተ ሞታቸው ለመቀጠል ፍላጎት ያላቸው መሆኑንን ተረድቶ ፣ ለትግራይ ህዝብ ፈረሱም ሜዳውም ይኸውልህ ። የተቀረውን አንተ ጨርሥ ብሎ ከመላው የትግራይ ከተማ ጦሩን ማሶጣቱ ተገቢ እርምጃ ነው።
ሲጀመር ህውሃትዎች በግንባር ቀደምትነት ይህንን እኩይ ተግባራቸውን የሚፈፅምላቸው የእኔ ነው የሚሉት አንድ ቋንቋ ተናጋሪ በፕሮፖጋንዳቸው የሠከረ ና በዕለት ጉርስ እጦት የተቸገረ የሰው ኃይል አላቸው ። በቋንቋው ” ላም አለህ በሰማይ…” ይሉታል ። ነገ ተዋግተን ድል ሥናደርግ የተቀናጣ ኑሮ ትኖራለህ ። በርታ ጀግን ይሉታል ። በአማላይ ቃላት እየሰበኩ ፣ ሰው መሆኑንን ዘንግቶ ፣ በካናቢስ ጦዞ ወንድሙን እንዲያርድ ቢላ ያቀብሉታል ።ከዛ በኋላማ ራሱን እንደ አንድ ” ልእለ ሰብ ” ይቆጥራል ። ፈሪኃ እግዛብሔር የሌለው ፍፁም ዳቢሎስ ይሆናል ። በተግባር ። እንዲህ አይነቱ ዳቢሎስም እንዲበዛ ይፈልጋሉ ። በዳቢሎሶች ተጠቅመውም ህዝብን በሽብርና በፍርሃት በመያዝ ከጎናቸው ያሰልፉታል ። ሰዋዊ ምሽግም ያደርጉታል ። ይህንን በግልፅ የታየ ሁነት ለመቀልበሥ ፣ ለራሱ ለትግራይ ህዝብ የቤት ሥራውን መሥጠት ተገቢ ነው ።
ፈረሱም ይኸውልህ ። ሜዳውም ያንተው ነው ። ከጭቆና እና ከግፍ አገዛዝ ለመላቀቅ በወጉ ፣ በሥርዓት ና በህግ አግባብ በሜዳው ላይ ለመጋለብ የሚችል ። አቀበትና ቁልቁለቱን ከደሃው ህዝብ ጋር በመጎዝ ወደ ብልፅግና የሚወሥድ መሪ የመምረጥ ፣ ዳቢሎሶችን የማወገዝና የማሶገድ ሥራ ያንተ ነው ። በዚህ ዕድል መጠቀም የአንተ ነው ። ብሎ ለአፍታ ዞር ማለት የተወናበደው ህዝብ ቀልቡን እንዲገዛ ያደርገዋል ።
ይህንን ዳቢሎሥ ከህዝብ ለመነጠል የግድ ቆም ብሎ የትግራይ ህዝብ ማሰብ አለበት ። በሰው ደም የሚነገግዱ የሤጣን ደቀመዝሙሮችን ከእንግዲህ በቃችሁ ማለት መቻሉንም በተግባር ማሳየት የሚችልበት ጊዜ አሁን ነው ።
ዛሬ እና አሁን በመላው ኢትዮጵያ የምንኖር ዜጎች ፣ ከትግራይ ወገናችን ጎን መቆም ይኖርብናል ። የጥፋት ኃይሉን ወይም በአሸባሪነት የተፈረጀውን ህውሃትን ፣ በፍርሃት ፣ በእጦቱ ምክንያት ምርጫ በማጣት እንዲሁም ተገዶ አብሮት የተሰለፈውን ከዳቢሎሥ ሠራዊት ለይተን ማየት ይኖርብናል ። ።
ማጠቃለያ
ትላንት በተቀነባበረ የውጪ ኃይሎች ሴራ በዘመነ ደርግ በኤርትራም ሆነ በትግራይ በረሃ ያለቁት ኢትዮጵያውያን ናቸው ። ያለቁበት መሣሪያም ከምዕራቡና ከምሥራቁ ( ከቀኙ ና ከግራው ) የተሸመተ እና ሻጮቹን አትራፊ ያደረገ ነው ። ዛሬም በሰው ደም ለማትረፍ ሁሌም የሚያሴሩ የሞት ነጋዴዎች በሥውር እጃቸው ኢትዮጵያ የምትታረድበትን ቢላዋ እያቀበሉ ነው ።
ኢትዮጵያዊያን በእነዚህ የውጪ ኃይሎች ሴራ እየሞትን ነው ። በሤረኞቹ ቢላዋ እየተራረድን ነው ። አማራጭ አጥቶ ከአሸባሪው ቡድን ጋር ተሰልፎ የሚሞተውም ሆነ ፣ የኢትዮጵያን ዳር ድንበር እና የህዝቡን ሠላም ለማሥከበር ሲል የሚሰዋው ኢትዮጵያዊ ነው ።የወያኔን ቱጃሮች ጥቅም የሚሰዋው ዓላማ ቢስ ነው ። ሞቱም የውሻ ሞት ነው ። የኢትዮጵያ ሠራዊት ግን ለዘላለም የሁለቱምየሚታወስ የሀገር ውድ ጀግና ልጅ ነው ።ከቤተሰቡ ከዘመድ አዝማዱ ጎን መንግሥትና የኢትዮጵያ ህዝብ ሁሉ ይቆማል ። የደግፋል ።
የዜጎች ሞት ሁሉ ለኢትዮጵያ ጉዳት ነው ። ለኢትዮጵያ ሐዘን ነው ። ልጅ ልጅ ነውና የሁለቱም ሞት ያሳዝናታል ። ምንም እንኳን አንዱ ዓላማ ቢስ እና አሣፋሪ የባንዳነት ተግባር ላይ ተሠማርቶ መሞቱ ቢያበሣጫትም ?!
ከእንግዲህ የኢትዮጵያ ሐዘን ማብቃት አለበት ። የትግራይ ህዝብ የአሸባሪውን ቡድን የጥፋት ተልኮ ” ይበቃል ! ” በማለት የኢትዮጵያን እንባ ለማበሥ ቆም ብሎ ማሰብ አለበት ። ልጆቹ የካናቢስ ሰለባ በመሆን ፣ ህሊናቸውን አጥተው የደቢሎስ ደቀመዝሙር ሲሆኑ ዝም ብሎ መመልከት የለበትም ። ነገ በእነዚህ የሃሺሽ ሰለባዎች እጅግ ዘግናኝ ሥቃይ ላይ ሊወድቅ እንደሚችል ና መፈጠሩን የሚረግምበት ቀን እንደሚመጣም ከወዲሁ መገንዘብ አለበት ።
በበኩሌ የኢትዮጵያ መንግሥት የትግራይ ህዝብ በሰቆቃ እንዳይኖር ፣ የትግራይ ክልላዊ መንግሥት ያቀረበውን የተኩስ አቁም ጥሪ ፣ በአወንታዊነት መቀበሉን አደንቃለሁ ። የሰላም ጥሪ ፣ ወይም የተኩሥ ሥምምነት በማድረግ ና የምህረት አዋጅ በማወጅ ተደናግረው ና የዕለት ጉርስ አጥተው ፣ ወደበረሃ የገቡትን ዜጎች በሰላም እጅ ሰጥተው ሰላማዊ ኑሮን እንዲኖሩም መደገፍ ያለበት የክልሉ መንግሥት ነው ። ይህንን አሸባሪው ህውሐት አልቀበልም ካለ ና ህዝቡም ካልተቃወመው እጣ ፈንታው ጥርሥ ማፋጨት ነው ። ከእንግዲህ ወዲያ ለጨካኞቹ በሃሺሽሽ ለሚቅበዘበዙት ለዳቢሎሶቹ መንግሥት ና የኢትዮጵያ ህዝብ እሣት እንጂ ውሃ አያቀርቡላቸውም ።
ልብ በሉ ከተጨባጭ ነበራዊ እውነት አንፃር ፣ በትግራይ ክልል በሚቀጥሉት ሁለት ወራት ገበሬው ጥይት ሳይጮኽበት የግብርና ሥራውን እንዲሰራ ለማሥቻል ፣ መንግሥት ተኩሥ ማቆምን አትዘንጉ ። ገበሬው ነፃ ማዳበሪያ ና ዘር ሊፈልግ ይችላልና ለዚህም ከወዲሁ መዘጋጀት ያሥፈልጋል ።
የመንግሥትንም ቀናነትን በአወንታዊነት መመልከቱ ተገቢ ነው ። ኢትዮጵያዊው ዜጋ ፣ የትግራይ ሰው በማያሳምኑ ፣ በሥሜት በተሞሉ በሐሰት ትርክት በደለበ ፕሮፖጋንዳ ምክንያትነት ከጥፋት ኃይሉ ጋር ሊተባበር ና መሣሪያ አንግቦ ሊሰለፍ ችሎል ። ይህ ሁኔታ ግን ለኢትዮጵያን ወዳዱ የትግራይ ህዝብ የሚመጥን እንዳይደለ ተገንዝቦ የመንግሥትን የሠላም ፍላጎት ፣ በቅንነት ተገንዝቦ ፣ ንሥሐ ሊገባ ና ያባንዳነት ተልዕኮውን ለመወጣት በሃሺሽ ናውዞ ኢትዮጵያን የሚያደማና የሚያቆሥለውን ማውጎዝ ይጠበቅበታል ።
በዚህና በዛም የሚሥተጋቡ ገድሎ የመፎከር አባዜ ሊቆሙ ይገባዋል በዚህ በበኩል የኢትዮጵያ መንግሥት እጅግ የሚመሰገን ነው ። ገበሬ ና የምሥኪን የከተማ ኗሪ ልጅ በከንቱ አልፎ የሚፎክሩ የግል ሚዲያዎች ከዚህ ሤጣናዊ ድርጊት ሊቆጠቡ ይገባቸዋል ። ቀዳዳው እና ባንዳው ጌታቸው ረዳ ግን መበጥረቁን ይቀጥል ።( እኔ ለእንደዚህ ዓይነቱ ምግባረ ብልሹ በሰው አምሳል ለሚንቀሳቀሥ ሤጣን ክብር የለኝም ። )
በመጨረሻ በሃሺሽ ለደነዘዙት ሤጣናት የውሸት አባቶች የማሥተላልፈው መልዕክት አለኝ ። “ መቼም እናንተ በጭካኔ እና በውሸት የሚወዳደራችው የለምና ፣ ‘ እኛ ድል ሥላደረግን እና በሺ የሚቆጠሩ ምርኮኞች ሥለያዝን መንግሥት ተኩስ እናቁም ሲል ፣ በትግራይ ክልልላዊ መንግሥት በኩል ጠየቀን ። …’ በማለት ለድርድር የማይሆን ጥያቄ ማቅረባችሁ አይቀርም ፤ ሆኖም መንግሥት ያላችሁ ፣ ‘ ለአርሶ አደሩ በማሰብ አምርቶ እንደሚገብ እናሥብለት ፣ ለከተማ ኗሪውም እንዘንለት እና የጥፋት ኃይሉ ሰዋዊ ጋሻ ከመሆን ይልቅ ፣ እርሱን ለብቻው ትተነው ወደ ሠላም ጓዳና በመምጣት የጥፋት ኃይሉን እርቃኑንን በማሥቀረት ለፍርድ እናቅርበው ‘ እንጂ ፣ ነፍሰ በላና አራጁ የጥፋት ኃይል ፣ በደም ከተጨማለቀ እጁ ጋር ከሠላማዊው ሰው ጋር ተቀላቅሎ በሰላም ይኑር እንደልሆነ ከወዲሂ በትረዱት መልካም ነው ። “ በማለት ትሁት ምክሬን እለግሳችኋለሁ ። ይህንን የሠላም ጥሪ ችላ በማለት ዛሬም ሰው መሆናችሁን ክዳችው በተግባር ዳቢሎስ መሆኑንን ካረጋገጠው ቡድን ጋር ከተሰለፋችሁ የተራዘመ ሰቆቃ ውሥጥ የምትኖሩት ራሳችሁ መሆናችሁን እወቁት ። በተአምር ህውሐት ወደ ኢትዮጵያ ፖለቲካ ተመልሶ አይመጣም ።
የትግራይ ህዝብ ሰው ሰራሽ የጦር መሣሪያ አለመሆኑን እና የፈጣሪ ፍጡር ሰው መሆኑንን በዚህ በጥሞና ጊዜ ይረዳል ብዬ አሥባለሁ ።
በዚህ በጥሞና ጊዜ ፣ የትግራይ አጎራባች ክልሎች ሁሉ ግን ከሽብርተኛው ቡድን ሤጣናዊ ተግባር እንደተማሩ ና እጃቸውን አጣምረው ለመታረድ ዝግጁ ሆነው እንደማይቀመጡ በሥሜት የሚነዳው የትግራይ ወጣት ቢገነዘብ መልካም ነው ። ሽብርተኛው ቡድን ምሽግ እንዳደረገውም ቢረዳ መልካም ነው። ጀግና ና ፈሪ ህዝብ ብሎ ነገር እንደሌለ ይገንዘብ ። ማንም ሰው በቢላዋ ቀልድ የለም ማለቱ የተረጋገጠ ነው ። ደግሞም ፤ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ለአገሩ ለመሞት ወደኋላ አይልም ። ትላንትም አደዋ ሄዶ የሞተው ትግራይ ሀገሬ ህዝቡም ወንድምና እህቴ ነው ብሎ ነው ። ዛሬ በብዝበዛው በአጥንቱ ያሥቀረውን ወዶ ያጎረሰውን የሚነክሥ በአጠቃላይ እንደ ህዝብ አለ ብዬ ለማመን ይቸግረኛል ። እናም ህዝቡ እናቱን ኢትዮጵያን ወንድምና እህቶቹን ኢትዮጵያዊያንን አክብሮ የአሸባሪውን እጅ ይዞ ለኢትዮጵያ መንግሥት በመሥጠት ፣ ጳጉሜ አምሥት 2013 ዓ/ም በዴሞክራሲያዊ መንገድ አሥተዳዳሪዎቹን እንደሚመርጥ ተሥፋ አደርጋለሁ ።