በዶክተር ሶስና ታደሰ (የፖለቲካና ስትራቴጂክ ጥናት ክፍል)

መግቢያ፦ የጥፋት ወጀቡ፣ እና «የስንብት የዘር ማጥፋት»
በኢትዮጵያ ዘመናዊ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ላለፉት አምስት አስርተ ዓመታት ብቅ ጥልቅ ሲል የነበረው የሕወሓት የጥፋት ወጀብ፣ በ2013 ዓ.ም ጥቅምት ወር ማብቂያ ላይ የጭካኔውን ጥግ በማሳየት በግልጽ የደም፣ የክህደት እና የህጻናትና እናቶች ሰቆቃ ጮኸት ምዕራፍ የጀመረበት ሆኖ በታሪክ ተመዝግቧል።
ይህ ወቅት፣ መላው ዓለም በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ስጋት ተውጦ በሚናጥበት እና ምዕራባውያን ለክትባት ፈጠራ በሚንደረደሩበት አስጨናቂ ድባብ ውስጥ የነበረ ጊዜ ነበር። ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የሰው ልጅን ሕይወት የታደጉ ሳይንሳዊ ምርምሮች ላይ ሲጠመድ፣ የሀገራችን የቀድሞ የሕወሓት አምባገነን ገዢዎች ግን ራሳቸውን ለጥፋት እና ለመጠፋፋት የጦርነት ድግስ በሴራና በሸፍጥ ሲያዘጋጁ ነበር።
የጥፋት እቅዳቸውም ፍጹም በተቀናጀ መንገድ እንዲህ ተጀመረ፦
- ጥቅምት 22 ቀን 2013 ዓ.ም፦ በምዕራብ ወለጋ ጋዋ ቃንቃ የትምህርት ቤት ግቢ ውስጥ ከ200 በላይ የሚሆኑ ንጹሃን የአማራ ተወላጆች በኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች በግፍ ተጨፈጨፉ፤ መንደሮች በእሳት ተቃጠሉ።
- ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም፦ በአዲግራት፣ በመቀሌ፣ በአጉላእ፣ በሰሮ እና በዳንሻ በተካሄደው የተቀናጀ የሰሜን ዕዝ ክህደት፣ የሕወሓት ልዩ ኃይል በሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ ድንገተኛ ጥቃት በመሰንዘር በሺዎች የሚቆጠሩ የቁርጥ ቀን የኢትዮጵያ ወታደሮችን በዘግናኝ ሁኔታ ገደለ፣ ጨፈጨፈ።
አሁንም የጥፋት ወጀቡ ቀጠለ፤ ላለፉት 50 ዓመታት የተጓዘው የትህነግ የጥፋት መርከብ፣ ቀድሞውንም ታሪካዊ ርስቱ እንዳልሆነ የሚያውቀውን የወልቃይትና የሰሜን ምዕራብ ምድር ከመልቀቁ በፊት የመጨረሻውን “የስንብት የዘር ማጥፋት” (Terminal Genocide) ለመፈጸም የመረጣት መዳረሻ ጥቅምት 30 ቀን 2013 ዓ.ም በታሪካዊቷ የማይካድራ ከተማ ላይ ነበር!
1. ማይካድራ፦ ከ«ስንብት የዘር ማጥፋት» እስከ ታሪካዊው እውነታ
ማይካድራ ከ1990ዎቹ መግቢያ ጀምሮ የከተማ ቅርጽ የያዘች፣ ከሁመራ 30 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የምትገኝና ወደ ሱዳን ለማምራት ስትራቴጂክ ቦታ የሆነች የነጭ ወርቅ ምድር ነች። ትህነግ በ1995 ዓ.ም በርካታ የትግራይ ተወላጆችን በሰፈራ መልክ ተከዜን አሻግሮ በማስፈር፣ ከሱዳን የተመለሱትን (ላጅኖችን) በመተካት እና ባለርስቶቹን የአማራ ተወላጆች በገፍና በሐይል በማፈናቀልና በመግደል መሬታቸውንና ማንነታቸውን ቀማ።
በወቅቱ ከትግራይ ክልል «ሳምረ» ከተባለ ድንጋያማ አካባቢ የመጡ ሰዎች የሰፈሩበት አካባቢ «ሳምረ ሰፈር» ሲባል፤ በወረራ ከተቀማው መሬት የተፈናቀሉ የአማራ ተወላጆች ደግሞ በ«ግንብ ሰፈር» ተሰባስበው በጉልበት ሥራና በዕለት ስራ ይኖሩ ነበር። መንደሮቹንና ነዋሪዎችን ልብ ብሎ ለተመለከተ አንዳች የሚለያቸው ድባብ አለ፤ ያ ድባብ ለተወላጆቹና ለርስቱ ባለቤቶች ያ ልዩነት የተለየ ስቃይ ይፈጥራል፣ ለአማራዎቹ ለባላባቶቹ ስሜቱ ከቃላት በላይ ነው።
የወልቃይት ጠገዴ አማራ የዘመናት ተጋድሎ ታሪክ «ከማይካድራ በፊት እና በኋላ» በሚል በሁለት ምዕራፍ ይከፈላል፦
- ከማይካድራ በፊት፦ አካባቢው በወረራ የተያዘበት፣ ባለእርሰቱ አማራ የጅምላ እስር፣ ስደት፣ መፈናቀል እና ግድያ አስተናግዶ ህልውናውን ላለማጣት የማያቋርጥ ትግል ሲያደርግ የኖረበት የመጀመሪያው ምዕራፍ ነው።
- ከማይካድራ በኋላ፦ ግን በሳምሪ ሰፈር ልጆች አማካኝነት የትህነግ የጥፋት መርከብ የመጨረሻ ወደብ ሆኖ የታየበት፣ ከ1,600 እስከ 2,000 የሚደርሱ የአማራ ተወላጆችና የቀን ሰራተኞች በ6 ሰዓታት ውስጥ በሜንጫ፣ በገጀራ፣ በቢላዋ፣ በዱላ እና በገመድ ታንቀውና ታርደው በጨካኝ ሁኔታ ያለቁበት የግፍና የጭካኔ ጥግ ነው!
ይህ ጥፋት የሕወሓት የስንብት የዘር ጭፍጨፋ ወንጀል ነው!!
2. የዓይን እማኞች፣ የሰብአዊ መብት ሪፖርቶች እና የአምነስቲ ማስረጃዎች
ጥቅምት 30 ቀን 2013 ዓ.ም ከቀኑ 9:00 ሰዓት ጀምሮ እስከ ምሽቱ 3:00 ሰዓት ድረስ ለተከታታይ 6 ሰዓታት በከተማዋ «ግንብ ሰፈር» በተካሄደው የተቀናጀ የዘር ማጥፋት ጥቃት ከ1,600 እስከ 2,000 የሚደርሱ የአማራ ተወላጆች ተጨፈጨፉ።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) መርማሪ ቡድን አባል የነበረችው ሐይማኖት አሸናፊ ወደ ከተማዋ ስትደርስ የነበረውን አሰቃቂ ድባብ ስታስታውስ፦
“ወደ ከተማዋ ስንደርስ አስፓልቱ በሙሉ በተቃጠሉ ቁሳቁሶች፣ በወደቁ ጫማዎችና ቃሬዛዎች ተሞልቶ ነበር። በከተማዋ ውስጥ የሚረብሽ የአስክሬን ጠረን ይነፍስ ነበር… በአቡነ አረጋዊ ቤተ-ክርስቲያን ግቢ በርካታ የጅምላ መቃብሮች የነበሩ ሲሆን፣ ሟቾችን ለመቅበር ቀናት ፈጅቷል።”
የተረፉት የዓይን እማኞች የሰጧቸው ምስክርነቶች የጥቃቱን ማንነት ተኮርነት ቁልጭ አድርገው ያሳያሉ፦
- ወ/ሮ ትርፋይ ግርማይ (የትግራይ ተወላጅ)፦ የ12 ዓመት አባወራ ባለቤታቸው በአይናቸው ፊት ሲታረድ፤ “ባለቤቴ ምንም የሚያስገድል ወንጀል አልሰራም፤ የተገደለው አማራ በመሆኑ ነው” ሲሉ መስክረዋል።
- ወ/ሮ የሺ ላቀም፦ የ«ሳምሪ» ወጣቶች ባለቤቷን አየነው ሙላትንና የባሏን ወንድም ሲወስዱ “ተውልኝ” ብትላቸው፤ “ዛሬ የምፈልገው ወንዶችን ነው” በማለት በልጆቿ ፊት አርደውታል።
- አቶ ጥላሁን አታላይ እና አቶ ገብረ መስቀል መንግሥቱ፦ ጥቃቱ አስቀድሞ መታወቂያ በመፈተሽ፣ በትራክተርና በቡድን በመደራጀት፣ እና የቀን ሰራተኞችን ከአንድ ቤት እስከ 20 ሬሳ በሚደርስ ሁኔታ በጅምላ በመጨረስ መፈጸሙን አረጋግጠዋል።
ይህንን አሰቃቂ ወንጀል አምነስቲ ኢንተርናሽናል በሳተላይት ምስሎችና በቃሬዛ ክምሮች ያረጋገጠው ሲሆን፣ የUN OHCHR እና ኢሰመኮ ሪፖርቶች በሲቪሎች ላይ የተፈጸመ «የሰብአዊነት መብት ጥሰትና የጦር ወንጀል» (War Crime/Crimes against Humanity) ሲሉ ፈርጅተውታል።
3. ከማይካድራ እስከ ሱዳን፦ የ«ሳምሪ» (Army 70) የውክልና ቅጥረኝነት ዝግመተ-ለወጥ
ከማይካድራ የዘር ማጥፋት በኋላ ወደ ሱዳን ሸሽቶ የሄደው የ«ሳምሪ» ቡድን ታሪክ በዚያ አላበቃም። ይህ ቡድን የአማራ ተወላጆችን ጨፍጭፎ ወደ ሱዳን ከተሰደደ በኋላ በቀጠናው ኃይሎችና በሱዳን ጦር (በአል-ቡርሃን ክንፍ) ድጋፍ በመቀበል፣ በስደተኞች ካምፕ ውስጥ ወታደራዊ ስልጠና በመውሰድ “Army 70” በሚል ስያሜ አዲስ የውክልና ወታደራዊ ክንፍ (Proxy Force) ሆኖ ተደራጅቷል።
ይኸው የ«ሳምሪ/Army 70» ስብስብ ባለፈው የክረምት ወቅት በሸረሪ በኩል የኢትዮጵያን ድንበር ጥሶ ጥቃት ለመሰንዘር ሞክሮ ከፍተኛ ሽንፈት የተከናነበ ሲሆን፤ ይህ ክስተት በፖለቲካ ሳይንስ ስሌት ሁለት መዋቅራዊ እውነታዎችን ያረጋግጣል፦
- የሕወሓት ታጣቂ ኃይል ለአማራ ህዝብ ዘላለማዊ ህልውናዊ ጠላት መሆኑን፦ ቡድኑ የትም ቦታና በየትኛውም ሽፋን ስር ይደራጅ፣ አላማው የአማራን ህዝብ መጨፍጨፍና ማጥፋት እንደሆነ ያሳያል።
- የቀጠናው ቅጥረኝነት (Proxy Mercenarism)፦ የቀጠናው ኃይሎች አማራንና ኢትዮጵያን ለማዳከም የ«ሳምሪ»ን አራጆች (የዘር ማጥፋት ወንጀለኞችን) እንደ ሦስተኛ ደረጃ ተወናይ (Third-tier proxy) እየተጠቀሙባቸው መሆኑን ያረጋገጠ ነው።
4. የ«ፊሽ» እና የዘመነ ካሴ ጥምረት፦ የ«ራስ-ጠልነት» (Self-hatred) እና የሞራል ውድቀት ጥግ
የማይካድራው የዘር ማጥፋት ወንጀል በዋናነት የተደራጀውና የጭፍጨፋ ትዕዛዙ የተሰጠው በጀኔራል ፍስሃ ኪዳኑ (በቅፅል ስሙ «ፍስሃ ማንጁስ») አሰልጣኝነትና መሪነት እንደነበር የታሪክ ማስረጃዎች ያረጋግጣሉ።
በቅርቡ በሶሻል ሚዲያ ሲዘዋወር በሰማነው የድምፅ ቅጅ ላይ፣ የ«ፅምዶ» (ትብብር ለህልውና ብሎ ራሱን የሚጠራው የወንጀለኞች ስብስብ) ሰብሳቢው ዘመነ ካሴ የማይካድራውን ዋና አራጅ ፍስሃ ኪዳኑን «ፊሽ» በሚል የቁልምጫ አጠራር በተደጋጋሚ ሲጠራው ሰምተናል፤ ይህ የማይካድራ የጭፍጨፋ ወንጀል መሪ የፅምዶ/ትብብር ወታደራዊ ኃላፊ መሆኑ ይታወቃል!
ይህ አሰላለፍ በፖለቲካ ሳይንስና በህዝብ ስነ-ልቦና መነጽር ሲፈተሽ፦
- የፍትህን የመንፈግ ሴራ፦ የማይካድራ ሰማዕታት ደም ሳይደርቅ እና የ1,600+ ንጹሃን አጽም ፍትህ ሳያገኝ፣ ከቀንደኛው የዘር አጥፊ ወንጀለኛ ከ«ፊሽ» እና ከሕወሓቱ ደብረጽዮን ጋር መወገን የአማራው የሕልውና ትግል እና የሰማዕታትን ደም አሳልፎ ለገበያ ማቅረብ ነው።
- «የራስ-ጠልነት» (Self-hatred) እና የባርነት ስነ-ልቦና፦ በገዛ ወገኑና በመርህ አበጋዞች ላይ የትዕቢትና የማሳደድ ዘመቻ የሚከፍተው ስብስብ፤ ለአማራ ህዝብ ቀንደኛ ጨፍጫፊዎች (ለፍስሃ ማንጁስ እና ለደብረጽዮን) ተንበርክኮ ቅቡልነት ለማግኘት መሯሯጡ የመጨረሻው የሞራል ክስረትና የራስ-ጠልነት ማሳያ ሆኖ በታሪክ ተመዝግቧል።
5. የፖለቲካ ሳይንስ ምክረ ሀሳብና እና የቀጣይ ህጋዊ አቅጣጫ
የማይካድራ የዘር ጭፍጨፋ በዓለም አቀፍ ህግ መነጽር በሰብአዊነት ላይ የተፈጸመ ወንጀል (Crimes against Humanity) እና የዘር ማጥፋት (Genocide) ሆኖ ተመዝግቦ የተቀመጠ ነው። የወልቃይት፣ ጠገዴ፣ ጠለምትና ራያ ህዝብ ለ35 ዓመታት ያሳለፈውን የመከራ ታሪክ ለመካስና ፍትህን ለማረጋገጥ የሚከተሉት ስትራቴጂካዊ እርምጃዎች መወሰድ አለባቸው፦
- የወንጀለኞች ዓለም አቀፍ ህጋዊ ተጠያቂነት፦ በሱዳን በወታደራዊ ካምፕ ውስጥ ተሸሸገው የሚገኙት የ«ሳምሪ/Army 70» አባላት፣ አሰልጣኛቸው ጀኔራል ፍስሃ ኪዳኑ እና የሕወሓት አዛዦች በዓለም አቀፍ የጦር ወንጀለኞች መዝገብ ስር ውለው በህግ ፊት እንዲቀርቡ ማድረግ።
- የካሳ እና የይቅርታ ጥያቄ፦ ላለፉት አምስት አስርተ ዓመታት በአማራ ህዝብ ላይ ለተፈጸመው የዘር ማጥፋት ወንጀል የህግ ባለሙያዎችን በማሳተፍ በዓለም አቀፍ ደረጃ ህጋዊ የካሳ ጥያቄ ማቅረብ።
- የ«ፅምዶ»ን የክህደት መስመር በይፋ ማፍረስና መታገል፦ የመሬት ላይ ታጋዩና መላው የአማራ ህዝብ የማይካድራን ደም ለስልጣን ቁማር አሳልፈው የሸጡትን የ«ፅምዶ» ደላሎች በይፋ አውግዞ፣ በራሱ ጽኑ አማራዊ መርህ ላይ የተመሰረተውን እውነተኛ የህልውና ትግል ማስቀጠል።
ማጠቃለያ
በሰው ልጅ ላይ የሚፈጸሙ ዘር ተኮር ጥቃቶች ለጊዜው በፖለቲካ ቁማርና በደላሎች ስብከት ሊሸፋፈኑ ይችላሉ፤ ፍትህ ግን መቼም ቢሆን አትቀበርም! የማይካድራ ሰማዕታት ደም አይባክንም፤ የትህነግ የጥፋት መርከብ ያረፈችበት የማይካድራ፣ ከገዳዮች ጋር የ«ፅምዶ» ወጥመድ የሸረቡ የአሳፋሪ ፖለቲከኞችም የፖለቲካ ማክተሚያ መቃብር ትሆናለች!
ታሪክና እውነት እጃችን ላይ ነውና አሸናፊው እውነተኛው የአማራ ህዝብ ይሆናል!
ፍትሕ ለማይካድራ ሰማዕታት!
ፍትሕ በማንነታቸው ለሚገደሉ ለአማራ እና ለኦርቶዶክስ ሰማዕታት!