ሰው በሀገሩ፣ በቀዬው፣ በሰላም መኖር ቅንጦት ሆኖበት፣ ሲሳደድ፣ እየታደነ በጅምላ ሲገደል እያዩ፣ ማዘንና መቆጣት ሲያንስ ነው። ይህ ዓይነቱ ጥቃትና እልቂት ያዘቦት ክስተት እየሆነ መምጣቱ ደግሞ፣ ከአሳዛኝነቱም በላይ ያስቆጣል። ነገር ግን፣ ሰሞኑን በአርሲ የደረሰውን የንጹሐን እልቂትና መሰል ጥቃቶችን ተከትሎ በሲኖዶሱ ላይ የሚሰነዘረው ዘለፋና ማንጎጠጥ ቅጥ አላጣም ወይ? ኢላማውንስ እየሳተ አይደለም ወይ?
እርግጥ ነው፣ ሲኖዶሱ የምእመናንን ሕይወት ለመታደግና ጥቃቱን ለማስቀረት ማድረግ ሲገባውና ሲችል ያላደረጋቸው ብዙ ነገሮች ሊኖሩ ይችላሉ። የጉዳዩን አሳሳቢነት የሚመጥን ሥራ ሳይሠራ ቀርቶም ይሆናል። ከዚህ አንጻር፣ ይህና ያ ይደረግ ብሎ ማሳሰብ፣ ፈርጅ ያለው ሐሳብ ማቅረብ፣ አቅጣጫ ማሳየት፣ ሲኖዶሱ ኃላፊነቱን እንዲወጣ በአግባቡ ግፊት ማድረግ ክፋት የለውም። አስፈላጊም ነው። ችግሩ ይህን አጥር ተሻግሮ የሚደረገው ዘለፋና ውል አልባ ውርጅብኝ ነው።
ከጥቃቶቹ ጋር በተያያዘ በሲኖዶሱ ላይ የሚሰነዘሩት አብዛኞቹ ነቀፋዎች፣ ሲኖዶሱ ማድረግ ሲገባው ባላደረገው፣ ወይም በአግባቡ ባልፈጸመው ተግባር ዙሪያ የሚያጠነጥኑም አይደሉም። ከዚያ ይልቅ፣ ለምን የመንግሥት አዳራሽ ሄዳችሁ፣ ለምን ይህን መረቃችሁ፣ ለምን ያንን ባረካችሁ፣ ለምን ከመንግሥት ጋር ተነካካችሁ የሚል ዘለፋ ነው የሚበዛው። ከዘለፋውና ከውርጅብኙ በስተጀርባ ደግሞ፣ ሲኖዶሱ መንግሥትን በቀጥታ እንዲያወግዝ፣ ከመንግሥት ጋር እሰጥ አገባ ውስጥ እንዲገባ፣ አልፎም አመፅ እንዲያስነሳ ጫና የማድረግ ፍላጎት ይስተዋላል።
ሲኖዶሱ ጥቃቱን አጥብቆ ሊያወግዝና ቀጣይነት ባለው መንገድ ፍትሕ ሊጠይቅ ይገባል። ሆኖም፣ ጳጳሳቱ ከሀገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ ውጭ ሊንቀሳቀሱ አይችሉም። በዚያ ላይ፣ ቤተ ክህነቱን ከመንግሥት ጋር የሚያገናኙት ብዙ የዕለት ተዕለት አስተዳደራዊ ጉዳዮች አሉ። ስለዚህ፣ ከመንግሥት ጋር በቀጥታ እንዲላተሙ መጠበቅ ትክክል አይመስለኝም። ኃላፊነታቸውን ለመወጣት እየጣሩም፣ በተቻለ መጠን ከመንግሥት ጋር ሰላማዊ ግንኙነት ማስቀጠል ይኖርባቸዋል። ሁለቱን አመዛዝነው መራመድ ግድ ይላቸዋል።
ጳጳሳቱ፣ ከመንግሥት ጋር አምባጓሮ ከፍተው ምን ዓይነት መፍትሔ እንዲያመጡ እንደተፈለገም አልገባኝም። ቤተ ክርስቲያኗ፣ የምእመናኗን ደኅንነት ከማስጠበቅ አልፎ፣ በአጠቃላይ መረጋጋትንና ሰላምን በማስፈን ረገድ ልትወጣው የሚጠበቅባት የራሷ ድርሻ አላት። ነገር ግን፣ በመንግሥት ላይ አመፅ መቀስቀስም ሆነ መንግሥትን መቀየር የቤተ ክርስቲያኗ ተልዕኮ አይመስለኝም።
የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስብስብ ነው። አይደለም ቤተ ክርስቲያኗ፣ ፖለቲካን ሙያዬ ብለው የያዙት ሰዎችም፣ ወደ አመፅና ተቃውሞ ከማምራታቸው በፊት፣ እርምጃቸው ሄዶ ሄዶ ማረፊያው ምን ሊሆን እንደሚችል ማሰብ፣ መቋጫውንም ቀድመው ማዘጋጀት ይኖርባቸዋል። ያለዚያ፣ ባልተብላላና ባልተጠና ነገር ውስጥ በስሜት ተገፋፍቶ መግባት፣ በቀውስ ላይ ቀውስ መደረብ ነው ትርፉ።
በዜጎች ላይ በተደጋጋሚ የሚፈጸመው ጥቃት የሚፈጥረው ሰብአዊ ሐዘንና ተገቢ ቁጣ እንዳለ ሆኖ፣ በሲኖዶሱ ላይ የሚደረገው ወከባ ግን፣ ቤተ ክርስቲያኗን ጎትቶ ውሉ ላልታወቀ ፀረ አገዛዝ ትግል ለመጥለፍ የሚደረግ ሙከራ እንዳልተቀላቀለበት እርግጠኛ መሆን የሚቻልም አይመስለኝም። ያም ሆነ ይህ፣ ባሕር ማዶ ሆኖ፣ አገዛዙን ፊት ለፊት ካልተጋፈጣችሁ ብሎ በቤተ ክርስቲያኗ አባቶች ላይ የሚሰነዘረው ለከት ያጣ ማብጠልጠልና ማንጎጠጥ፣ ጠቃሚም ተገቢም አይደለም።
በቀድሞው ኢሕአዴግ አገዛዝ ዘመን፣ በዕውቀቱ ስዩም ለትምህርት ይሁን ለሥራ ወደ አሜሪካ በመጣበት አንድ ወቅት፣ አንዳንድ ቃላቱን በትክክል ላላስታውስ ብችልም፣ በጥቅሉ ግን “ሰሞኑን መንግሥትን እንዳይሸጥ እንዳይለወጥ አድርጌ ስዘረጥጠው ብታዩኝ እንዳይገርማችሁ፣ መንግሥት የማይደርስበት ቦታ ስለሄድኩ ነው” የምትል፣ ዲያስፖራውን የምትነቁር አጭር መልዕክት በፌስቡክ ገጹ ላይ አጋርቶ ነበር።
ምን ለማለት ፈልጌ ነው፦ ያለ ከልካይ፣ ያለ ገደብ፣ ባሕር ማዶ ተቀምጦ አገዛዙ ላይ እንዳሻ መደንፋት መቻልን እንደ ጀብዱ ቆጥሮ፣ ሀገር ቤት፣ መሬት ላይ ያለን አካል ምን ዓይነት መሥዋዕትነት መክፈል እንዳለበት መበየን፣ እንዲህ አደረጉ፣ እንዲህ አላደረጉም እያለ ማሸማቀቅና ማንጎጠጥ ያስተዛዝባል።
አስቀድሜ እንዳልኩት፣ ሲኖዶሱ ጥቃቱን ለመከላከል የሚቻለውን ሁሉ እንዲያደርግ ማሳሰብ፣ አቅጣጫ ማሳየትና ግፊት ማድረግ ተገቢ ነው። ሆኖም፣ ሁሉም በልኩና በሥርዓት ሊሆን ይገባል። አቅሙ ካለም፣ ከነቀፌታው፣ ማገዝ፣ ሲኖዶሱ ያጎደለውን መሙላት ነው የሚሻለው። በተለይም የዲያስፖራው ወገን፣ በሲኖዶሱ ላይ ውርጅብኝ ከማውረድ ይልቅ፣ ያለውን ነጻነት ተጠቅሞ እልቂቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ትኩረት እንዲያገኝ የራሱን ሥራ ቢሠራ፣ ጥቃቱ እንዲቆምና ገዳዮቹ ለፍርድ እንዲቀርቡ መንግሥት ላይ ጫና ቢፈጥር የተሻለ ይሆናል።
ጥቃቱን ማንም አደረሰው ማንም፣ ዞሮ ዞሮ ተጠያቂው፣ የዜጎችን ደኅንነት የመጠበቅ ኃላፊነት ያለበት፣ አቅሙም ያለው መንግሥት ነው። ጫና መደረግ ካለበት፣ ጫናው ይህ ሁሉ ሰው ነጋ ጠባ በገፍ እያለቀ፣ ዕቃ የጠፋው እንኳን አልመስልህ ያለው መንግሥት ላይ ነው። ከዚያ አልፎ፣ በሲኖዶሱ ላይ የሚወርደው ውርጅብኝ ኢላማውን የሳተ ነው።
በንጹሐን ዜጎች፣ በምእመናን ላይ የሚደርስን ጥቃት ተገን አድርጎ፣ ሲኖዶሱን አዋክቦ፣ ቤተ ክርስቲያኗን የአመፅ መሣሪያ፣ ለራስ የፖለቲካ ግብ ማስፈጸሚያ ለማድረግ ከሆነም የተፈለገው፣ ይህ በቤተ ክርስቲያኗ ላይ ጥቃት ከመሰንዘር ተለይቶ ሊታይ አይችልም። የቤተ ክርስቲያኗ ጉዳይ ያገባኛል የሚል ሁሉ ልብ ሊለው ይገባል።