ምንድን ነው የመጀመሪያ ምርጫችን ጦርነት ወይስ የፖለቲካ ስምምነት? በሚል አርዕስት በኦፍሬም ማዴቦ በቦርከና ድር-ገጽ ላይ ለንባብ ለቀረበው የተሰጠ የግንዛቤ መልስ!!
ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)
ጥቅምት 8፣ 2019(October 18, 2026)
Politics is the only profession where you can lie, cheat, and steal, and still be respected. (Mark Twain)
እስካሁን ድረስ በአብዛኛዎቻችን ዘንድ በፍጹም ግንዛቤ ያላገኘውና ለማግኘትም የማይችለው ነገር ፖለቲካ የሚባለው እንደማንኛውም ትምህርት በስልጠና መልክ የሚሰጥና የመጨረሻ መጨረሻ እንደ ሙያ ሊያገለግል የሚችል ነው የሚለው ነገር ነው። ለምሳሌ አንድ የህክምና ትምህርት ለመማር የሚፈልግ ወጣት ልጅ የከፍተኛ ትምህርት የመልቀቂያ ፈተናውን በበጣም ጥሩ የፈተና ውጤት ማለፍ አለበት። ይህ ሲሆን ብቻ ነው አንድ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ለመመዝገብና የህክምና ትምህርቱን ሊከታተል የሚችለው። ዩኒቨርሲቲም ከገባ በኋላ በአጠቃላይ ሲታይ ሰለሰውነት ክፍሎች በሙሉና፣ ሰለበሽታዎች ዐይነት መማር አለበት። ሶሶት ዓመት ከተማረ በኋላ በጣም ከባድ ፈተና ይወስዳል፤ እሱን ካለፈ በኋላ ወደ ከፍተኛው ደረጃ ይተላለፋል። ትምህርቱን በመማር ላይ እያለ በተግባርም የሰውነት ክፍሎችን ያያል። ከስድስት ዓመት የህክምና ትምህርት በኋላና ፈተናውን ካጠናቀቀ በኋላ ወዲያኑ ሀኪም ሆኖ ይሰራል ማለት አይደለም። አንድ ሆስፒታል ውስጥ በመግባት የበለጠ በማየት ልምምድ ያደርጋል። እዚያው ውስጥ ባለበት ወቅት የዶክትሬት ዲግሪውን በመጻፍ ዲፌንድ ካደረገ በኋላ ዶክተር የሚል ርዕስ ይሰጠዋል። በዚህ መልክ አጠቃላይ ሃኪም ይሆናል። ይሁንና ስፔሽያላይዝ ለማድረግ ከፈለገ ለምሳሌ በሆድ ዕቃ ወይም በዐይን፣ ወይም በሌላ የሰውነት ክፍል ተጨማሪና ጠለቅ ያለ ስልጠና መውሰድ አለበት። በተጨማሪም ፈተናውን ካለፈ በኋላ ለምሳሌ የዐይን ሀኪም ሆኖ ይሰራል ማለት ነው። በአጠቃላይ ሲታይ በማንኛውም ዐይነት የህክምና ትምህርት የሰለጠነ ሰው በስራ ላይ በሚሰማራበት ጊዜ ከባድ ኃላፊነት እንዳለበት ጠንቅቆ ማወቅ አለበት። አንድ ሰው ታሞ ሀኪምቤት በሜሄድበት ጊዜ ታማሚው ሰው በተቻለ መጠን ከበሽታዬ አገግማለሁ. የመጨረሻ መጨርሻም እፈወሳለሁ ብሎ በማመን ነው። ይሁንና ይህ ከመሆኑ ቀርቶ በሽታው የባሰ የሚፀናበት ከሆነ የታዘዘለት መድሃኒት ያልተስማማው ሊሆን ይችላል፤ ወይም ደግሞ ታማሚው በሽታው በታም ከጠናበት በኋላ ስለሄደ በቀላሉ በቀላል ህክምና ሊድን አይችልም ማለት ነው። ያም ተባለ ይህ አንድ ሰው በአንድ ሙያ የሰለጠነ ከሆነ ከፍተኛ ህበረተሰብአዊ ኃላፊነት እንዳለበት ማወቅ አለበት። ከዚህም በላይ ከፍተኛ ስነ-ምግባር እንዲኖረው ያስፈልጋል።
ወደ ሌሎች ሙያ ነክ ነገሮችም ጋ ስንመጣ፣ ለምሳሌ የአርክቴክቸር ትምህርት፣ አንድ ሰው በዚህ ሙያ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ሳይስለጥንና ሳይለማመድም ራሱን አርኪቴክቸር ነኝ ብሎ በፍጹም አይጠራም። ይህ ዐይነቱ አካሄድ በማንኛውም ሙያ ነክ ስልጠና ላይ በተግባር የሚውል ነው። ራሱ የፀጉር አሰራርም ሆነ የዳቦ መጋገር በስልጠና መልክ ከተሰጡ በኋላ ነው አንድ ሰው ተቀጥሮ ሊሰራ የሚችለው። በአንድ ዐይነት ሙያ የሰለጠኑም የስራ መስክ ለማግኘት የሚችሉት ቀጣሪው ኩባንያ ተቀጣሪው ሰራተኛ በተሰማራበት መስክ ላይ ስራውን በጥንቃቄ ያከናውናል በማለት ነው። በተለይም ለሰዎች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በጠቀሜታ ላይ የሚውሉ ማንኛውም የኢንዱስትሪ ውጤቶች በትንቃቄ መመረት አለባቸው። የሰውን ህይወት አደጋ ላይ የሚጥሉ መሆን የለባቸውም። በተለይም ምግብ ነክ ነገሮች በጣም ጥንቃቄ እንዲኖራቸው ያስፈልጋል። የሰውን ህይወት በቀላሉ የሚመርዙ ከሆነና ይህም በግልጽ ከታወቀ ምግቡ ወዲያውኑ ከገበያ እንዲወገድ ይደረጋል። አሰሪው ኩባንያም በምን ምክንያት እንደዚህ ዐይነት ምርት ተመርቶ ለገበያ እንደቀረበ ይጠየቃል። አስፈላጊም ከሆነና ስህተቱ ተደጋጋሚ ከሆነ አምራች ኩባንያው ፈቃዱን ሊነጠቅ ይችላል። በተለይም በካፒታሊስት ስርዓት ውስጥ ከፍተኛ ውድድር ስላለ የኩባንያው ባለቤት ደንበኞችን ላለማጣት ሲል የግዴታ ብቃትነቱን ማስመስከር አለበት። ገበያ ላይ የሚቀርቡና የሚሸጡት ዕቃዎችም ሆነ ምግብ-ነክ ነገሮች የሰውን ጤንነት የሚያቃውሱ ወይም ለአደጋ የሚያጋልጡ መሆን የለባቸውም። ይህንን ጉዳይ ወደ ፖለቲካ እንተርጉመው።
ወደ ፖለቲካ ጋ ስንመጣ አብዛኛዎቻችንን ግራ የሚያጋባው ነገር አንድ ሰው በቂ ዕውቀት ሳይኖረውና ፖለቲካ ማለት ምን ማለት ነው? በፖለቲካስ ምን ነገር ነው መስራት የሚቻለው? የሚሉትን ጥያቄዎች ሳያነሳና ከፍተኛ ምርምር ሳያደርግ ዝም ብሎ ብቻ ፖለቲከኛ ሆናለው በማለት እንደምንም ብሎ ስልጣን ለማግኘት ይሞክራል። በተለይም እንደኛ ባለው አገር ውስጥ አብዛኛዎች ፖለቲከኛ ነን ባዮች በውጭ ኃይሎች ታጭተው ስልጣን ላይ የሚወጡ የሚደረጉ ናቸው። እንደነዚህ ዐይነት ኃይሎችም ቀደም ብለ ክትትል ከደረገባቸውና የህሊና አወቃቀራቸው ከታወቀ በኋላ የእኛን ጥቅም(የውጭ ኃይሎችን ጥቅም) ሊያስጠብቁ ይችላሉ፣ በቀላሉም ሊጠመዘዙ ይችላሉ በማለት በዚህም በዚያም ተብሎ ጠ/ሚኒስተር እንዲሆኑ ይደረጋሉ። ይህም ማለት እንደኛ ባለው አገር ውስጥ ለጠቅላይ ሚኒስተር የሚታጩት እዚያው አገር ውስጥ በምሁራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ በመሳተፍ፣ በተለይም እንደ ኢኮኖሚና የማህበራዊ ጥያቄዎችን በማንሳት የማስተማርና የመከራከር ልምድ ያላቸውና፣ የተሻለ ሃሳብም በማቅረብ ስልጣን ላይ ካለው አገዛዝ ጋር በመጋፈጥ የተፈተኑ ሳይሆን ዝም ብለው በውጭ ኃይል የምንፈልገው እሱን ነው በማለት ስልጣን ላይ እንዲቀመጡ የሚደረጉ ናቸው።
የእኛው፣ በተለይም ይኸኛውን ወይም ያኛውን ኃይል አምላኪና ተከታይ ትልቁ ችግር ፖለቲካ ከሚባለው ነገር ጋር ምንም ዐይነት ግኑኘነት ሳይኖረን ዝም ብለን ብቻ አንድን ሰው በቁመናውና በመልኩ በመማረክ፣ ወይም ሳይንሳዊ ባለሆነው አነጋገሩ በመመሰጥ ዝም ብለን እንከተለዋልን። ይህ ሰው ስልጣን ላይ ከወጣ በኋላ የህብረተሰቡን አንገብጋቢ ጥያቄዎች፣ ለምሳሌ መሰረታዊ ነገሮችን(Basic Needs) ሊፈታና ሊያሟላም ይችላል ብለን ጥያቄ አናነሳም። ፖለቲካ የሚባለው ነገር፣ በተለይም እንደኛ ባለው አገር ውስጥ በብዙ መልኩ ወደ ኋላ በቀረ አገር ውስጥ፣ በተለይም ሰፊውን ህዝብ ሊያገለግሉ የሚችሉ በስነ-ስርዓት የተገነቡ ከተማዎችና መንደሮች በሌሉበት አገር ውስጥ ፖለቲካ የሚባለው ነገር የግዴታ ከአገር ግንባታ ጋር የሚያያዝ መሆን እንዳለበት አንዳችም ግንዛቤ የለንም። ክዚህም በላይ ፖለቲካ የሚባለው ነገር ከስነ-ምግባርና ሞራል፣ እንዲሁም በብዙ ሚሊዮን ህዝቦች ከሚቆጠር ህይወት ጋር በቀጥታ መያያዙንና፣ ጠ/ሚኒስተርም ሆነ ሌሎች ሚኒስተሮችም ሆኑ ባለስልጣናት የሚባሉት በቀጥታ ህዝባዊና አገራዊ ኃላፊነት እንዳለባቸውና የህዝብ አገልጋዮችም እንደሆኑ ምንም ዐይነት ግንዛቤ የለንም። እንደሚታወቀው ጠ/ሚኒስተርም ሆነ ሌሎች ሚኒስተሮች ከህዝብ በሚሰበሰብ ቀረጥ ደሞዝ የሚከፈላቸው እንደመሆኑ ኃላፍጊነታቸውን መወጣት የሚችሉ መሆን አለባቸው። ኃላፊነታቸውን ሊወጡ የማይችሉ ከሆነም የግዴታ ከስራ ቦታቸው መነሳት አለባቸው።
ባጭሩ ፖለቲካ እንደንማንኛውም ሳይንስ ነክ ዕውቀት ሁሉ ከፍተኛ ዕውቀትንና ጥንቃቄ ያለው መሆኑን ስለማንረዳ ስለፖለቲካ ያለን ግንዛቤ አልቦ ነው ማለት ይቻላል። እንዲያውም አንድ ሰው አገር ሲያፈራርስና የአገርን ሀብት ሲሸጥ፣ አገርን ወደ ብልግና መድረክ በግልጽ ሲለውጥ ይህ ዐይነቱን ድርጊት ከፖለቲካ ጋር በማያያዝ አገር አፍራሽ የሆነውን ፖለቲከኛ ባይ እንዲያውም እናጨበጭብለታለን። ስለሆነም አንድ ፖለቲከኛ ነኝ የሚል ሰው በመመረጥ የስልጣን ዕድል ካገኘ ህዝብ የጣለበትን አደራ በስነ-ስርዓትና ህዝብን በማይጎዳ መልክ ተግባራዊ ከማድረግ ይልቅ ህዝብ የጣለበትን አደራ በመዘንጋት ራሱን ወደ ጨቋኝነት ሲለውጥ ዝም ብለን እንመለከታለን። በተለይም ምሁራዊና የተደራጀ ኃይል በሌለበት እንደኛ ባለበት አገር ውስጥ ማንም ተራ ዱርዬ እየተነሳና ከውጭ ኃይሎች ጋር በመተባበር አንድን ባህላዊና ታሪካዊ አገር ሲያፈራርስ እንዲያውም እንደዚህ ዐይነት ወንጀላዊ ድርጊቱን ዘመናዊ ነው በለን እንጠራዋለን። ከዚህም ሆነ ከዚያኛው ኃያል መንግስት ነኝ ከሚልና የዓለምን ፖለቲካ እንደፈለገው ከሚበውዝና በሚሊዮን የሚቆጠሩ ህዝቦችን ከሚያፈናቅልና፣ እንዲያም ሲል በምስኪን ህዝቦች ላካ በማን-አለኝበት ጦርነትን የሚከፍት ስነ-ልቦና ሞራል ምን እንደሆኑ ከማያውቅ ጋር በመተባበርና ትዕዛዝም በመቀበል አገርን አደጋ ላይ ሊጥል የሚችልና ብሄራዊ ነፃነትንም የሚያስደፍር ውል በመፈራረም ህዝቡን ከፍተኛ አደጋ ውስጥ ሲጥል ይህንንም የውጭ ፖለቲካ ብለን እንጠራዋለን።
ከዚህም በላይ የህዝቡን መሰረታዊ ፍላጎቶች(Basic Needs) ሊፈታ የማይችል ኢ-ሳይንሳዊ የሆነ የኢኮኖሚ ፖሊሲ የሚሉትን ነገር ተግባራዊ በማድረግ የባሰውኑ ሰፊውን ህዝብ ለድህነትና ለኋላ-ቀርነት ሲዳርገው ዝም ብለን አፋችንን በመክፈት እንመለከታለን። በአጠቃላይ ሲታይም አገሩን በዕዳ እንድትቀፈደድ በማድረግ በየዓመቱ የዕዳ ከፋይ በመሆን ኢኮኖሚው በአስተማማኝ ሁኔታ እንዳያድግ ሲያደርግ ማንም የሚከራከረው የለም። በዚህም ምክንያት የተነሳና የውስጥ ገበያም የማደግ ዕድሉ በጣም ዝቅ ስለሚል አገዛዙ ከቀረጥ የሚያገኘው ገቢ በጣም ዝቅ ይላል ማለት ነው። እንደሚታወቀው የአንድ አገር አገዛዝ ወም የመንግስት የቀረጥ መሰረት(Tax Base) ሊሰፋ የሚችለው አንድ አገር ሰፋ ያለ ልዩ ልዩ ምርቶችን የሚያመርት የኢንዱስትሪ መስክ ሲኖራት ብቻ ነው። አንድ አገር ሰፋ ያለ የማኑፋክቸሪንግ መሰረት ካላት ተቀጥሮ የሚሰራውም የህዝብ ቁጥር ክፍ ይላል ማለት ነው። ስለሆነም የሰራተኛው ገቢ በተከታታይ ስለሚያድግ በዚያው መጠንም የመንግስት የገቢ ቀረጥና ሌሎች ተዘዋዋሪ ቀረጦች ከፍ ይላሉ ማለት ነው። በዚህም ምክንያት የተነሳ የመንግስት በጀት ከፍ ስለሚል ለሰፊው ህዝብ የሚያገለግሉ ልዩ ልዩ የመገለገያ መስኮችን ሊያሰፋቸውና በየጊዜው ሊጠግናቸው ይችላል ማለት ነው። ከዚህ መሰረታዊ ሁኔታ ስንነሳ እንደኛ አገር ያሉ ፖለቲከኞች የፖለቲካን ትርጉም የመረዳት ኃይላቸው በጣም ዝቅተኛ ስለሆነ የህዝብ አለኝታ ከመሆን ተስፋ አስቆራጭ ይሆናሉ ማለት ነው። ይህንን ዐይነቱን ሁኔታ በአገራችን ምድር ባለፉት 50 ዓመታት የምንገነዘበው ሀቅ ነው። ፖለቲከኛ ነን የሚሉ በሙሉ ችግር ፈቺዎች ከመሆን ይልቅ ምስቅልቅል ሁኔታዎችን በመፍጠር አንድ ቀን ተገፍተው በመጣል የታሪክ ትዝታ ሆነው ያልፋሉ ማለት ነው። የዚህ ሁሉ ችግር አብዛኛዎቻችን ፖለቲካ የሚለውን ፅነሰ-ሃሳብና ከፍተኛ ሳይንሳዊ ትርጉም ያለውን እንደተራ ነገር ስለምንቆጥር ነው። በአብዛኛዎቻችን ዘንድ ፖለቲካ ራሱን የቻለ ሳይንስና ከብዙ ነገሮች ጋር እንደሚያያዝ በፍጽም ግንዛቤ የለንም።
ፈላስፋዎች፣ በተለይም እነ ፕሌቶ እንደሚያስተምሩን አንድ ሰው ፖለቲከኛ ለመሆን የሚችለው የግዴታ ከልጅነቱ ጀምሮ መንፈሱ በሚገባ የተኮተኮተ እንደሆነ ብቻ ነው። በተጨማሪም ስነ-ምግባርና ሞራል ምን ማለት እንደሆኑ የተገነዘበ እንደዚህ ዐይነት ሰው አገርንና ህዝብን የመምራትና፣ ታሪካዊም ስራ የመስራት ኃይሉ ከፍ ያለ ነው ማለት ይቻላል። በችግር ፈተናም መፈተን አለበት። ሰው መሆኑንንም መገንዘብ አለበት። ፖለቲካ ከአንድ ህዝብና ከአንድ አገር ጋር የሚያያዝ እንደመሆኑ መጠንና፣ እንደዚሁም አንድ አገር ተከታታይነት እንዲኖረው ከተፈለገ የግዴታ በፖለቲካ ዓለም ውስጥ የሚሰማሩ ሰዎች መንፈሳቸው የረጋ፣ ጥበበኞችና፣ ሚዛናዊ አመለካከት ያላቸው መሆን አለባቸው። ወደ ዘመኑ ሁኔታ ስንመጣ ደግሞ በተለይም ከ17ኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ ዕውቀት የሚባለው ነገር በተለያዩ አቅጣጫዎች የተስፋፋ በመሆኑ ከሞላ ጎደል አንድ ፖለቲከኛ ለመሆን የሚፈልግ ሰው፣ በተለይም ከህብረተሰብ ሳይንስ፣ ማለትም ከፖለቲካ ኢኮኖሚ፣ ከሶስዮሎጂና ከሳይኮሎጂ ጋር መተዋወቅና በየቀኑም ማንበብ አለበት። እንደሚታወቀው አንድ አገር በአንድ ግለሰብ ብቻ የሚተዳደር ስላልሆነ በተለያየ ሙያዎች የሰለጠኑ ሰዎች ስልጣንን በመያዝና በመመካከር አንድን አገር በተሟላ መልክ የመገንባት ችሎታ እንዲኖራቸው ያስፈልጋል። አስቸጋሪው ነገር በተለይም በዓለም አቀፍ ደረጃ ካፒታሊዝም ስለተስፋፋና ብዙ ነገሮችም ለምሳሌ እንደ ኢኮኖሚክስ የመሳሰሉት ትምህርቶች በተሳሳተ መልክና ከሳይንስ ውጭ ተነድፈው ስለሚቀርቡ በኢኮኖሚክስ ሙያ የሚሰለጥን ሰው በመሰረቱ በጣም ጥራዝ ነጠቅ አመለካከት የሚኖረውና ድህነትን የሚያስፋፋ ነው የሚሆነው። የአገራችንም ሁኔታና የብዙ አፍሪካ አገሮችም ሁኔታ ይህንን ነው የሚያረጋግጠው። በተለይም እነ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅትና(IMF) የዓለም ባንክ የመሳሰሉት የዓለም የፋይናንስ ካፒታል ተጠሪዎች የሚያረቁትን ፖሊሲ ብለው የሚጠሩትን ነገር ነው እንደ አገራችን የመሳሰሉ መሪዎች ተግባራዊ በማድረግ ህዝባችንን የባሰ ደሃና አቅመ-ቢስ ለማድረግ የበቁትና የሚበቁት።
ኤፍሬም ማዴቦ ቦርከና በሚባለው ድህረ-ገጽ ላይ እንዲለጠፍ ባደረገው መጣጥፉ፣ “ምንድን ነው የመጀመሪያ ምርጫችን ጦርነት ወይም የፖለቲካ ስምምነት? የሚለው አርዕስቱ ጋ ስንመጣ በአገራችን ምድር ያለው ትልቁ ችግር በፖለቲካ ስም የሚነግዱትና የብሄረሰቤን መብት አስጠብቃለሁ፣ እንዲያም ሲል ነፃ እናወጣዋለን የሚሉት ሁሉ ፖለቲካ የሚባለውን ፅንሰ-ሃሳብ ወይም የዕውቀት ዘርፍ ከብዙ ነገሮች ጋር የሚያያዝና ከሰውም ህይወት ጋር በጥብቅ የሚገናኝ መሆኑን ሳይረዱ ነው የነፃ አውጭ ድርጅት የሚሉትን የአሸባሪና የገዳይ ድርጅት የሚመሰርቱት። በተለይም የጦርነት ትግል ሲያካሂዱም በመሀከላቸው ምንም ዐይነት ጥናትና ውይይት አይካሄድም። ይህም ማለት ጭንቅላታቸው ሙሉ በሙሉ በጦርነትና በአመፀኝነት መንፈስ ስለሚቀረጽ መንፈሳቸው ለሌላ ገንቢ ሃሳብ፣ ለውይይትና ለክርክር በፍጹም ክፍት አይደለም። ሳይንሳዊና ሎጂካዊ በሆነ መልክም ማሳመንም በፍጹም አይቻልም። ውጤቱም እንደታየውና እንደሚያረጋግጠው ህወሃት የሚባለው የወንበዴዎችና የዘራፊዎች ስብስብ በአገራችን ላይ ጦረነት ከፍቶ እወክለዋለሁ የሚለውንም ብሄረሰቡን ከፍተኛና በቀላሉ ሊወጣ የማይችለው ወጥመድ ውስጥ ከትቶታል። በተጨማሪም መንፈሱ በአሸናፊነትና በበላይነት ስልተቀረፀ ህወሃት የሚፈልገው እንደገና ስልጣን ላይ በመውጣት አገርን ለማተረማመስ ነው እንጂ የተሻለ ነገር ለመስራት አይደለም:፡ 27 ዓመት ያህል ስልጣን ላይ በነበረበት ጊዜ ማንነቱን አረጋግጧል። በጎሳ ፌዴራሊዝም አሳቦ የከፋፍለህ ግዛው ፖለቲካ በመከተል ብሄራዊ አንድነታችን እንዲደመሰስ አድርጓል። የውጭ ኃይሎች ታዛዥም በመሆን ብሄራዊ-ክብራችን እንዲደፈረ አድርጓል። በእሱ የአገዛዝ ዘመንም ነው የብልግና ኢንዱስትሪ ሊስፋፋ የቻለው። ኤርትራም ነፃ ወጣች ከተባለ ከሰላሳ ዓመት በላይ አገሪቱ አንዳችም የሚንቀሳቀስና ለህዝቡ የስራ መስክ የሚከፍት የኢኮኖሚ ተቋም የላትም። መጠናቸው የማይታወቁ ወጣቶች አገራቸውን ጥለው በመውጣት እዚህ አውሮፓ ውስጥ ለሁለት በመከፈል በአንዳንድ ስብሰባዎች ላይ ርስ በርሳቸው ይከሳከሳሉ። በከፍተኛ ደረጃም በህሊና በሽታ የሚሰቃዩ ኤርትራውያን ቁጥራቸው ከፍ ያለ ነው።
ፖለቲከኞች ነን፣ የኢትዮጵያም ነገር ያገባናል የሚሉት ግለሰቦችና ድርጅቶች ጋ ስንመጣም በዩቱቭ ቻናል ተጋብዘው ከመለፍለፍ በስተቀር ለአንድ አገር የሚያስፈልጉ መሰረታዊ ጉዳዮችን በማንሳት፣ ለምሳሌ የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊና በአጠቃላይ ሲታይ የአገር ግንባታ፣ የመንግስት መኪና አወቃቀርና ፖለቲካ በሚለው ጽንሰ ሃሳብ ላይ ጥናት በማቅረብ ወጣቱን ሲያተምሩ በፍጹም አይታዩም። አንዳንዶችም የአሜሪካንን ኢምፔሪያሊዝም በመማፀን ስልጣን ላይ ለመውጣት የሚፈልጉ የሚያስመስላቸው እንጂ የአቢይ አህመድ አገዛዝ ከአሜሪካኖችና ከፋይናንስ ካፒታል ጋር በጥብቅ የተሳሰረና የእነሱን ጥቅም ተግባራዊ በማድረግ አገራችንን እንደሚያፈራርስ በፍጹም ግንዛቤ የላቸውም። ከዚህ ሁኔታ ስነሳ በምን በምን ነጥቦች ላይ ነው የምወያየው? የፖለቲካ ርዕያችንስ ምንድን ነው? የምንመራበትስ ደንብ አለን ወይ? በምን ዐይነት ስልትና ቲዎሪ ነው የአገራችንን ሁኔታ ለማጥናትና ለመተንተን የምንችለው? በሚለው ላይ ምንም ዐይነት አመለካከት የለንም። በሁላችንም ዘንድ ሁላችንንም የሚያሰባስብ የጋራ ርዕይና ዋና አጀንዳ በፍጹም የለንም። አንድ አገርም በተበታተነ ሃሳብ በፍጹም እንደማህበረሰብ ሊገነባ አይችልም። ስለሆነም እኔ ፖለቲከኛ ነኝ እያሉ እዚህና እዚያ መዝለሉ የትም አያደርሰንም። ሌላው በመሀከላችን ያለው ትልቁ ችግር በፖለቲካ ፊሎሶፊ ፖለቲካል ሞደርናይዜሽን የሚባል ነገር አለ። ይህ ዐይነቱ አስተሳሰብ ከሁለት ሺህ ዓመት ተኩል በፊት የተነሳና በኋላ ላይ በአውሮፓ ምድር ከ17ኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ ጠለቅ ያለ ጥናትና ውይይት የተካሄደበት መሰረተ ሃሳብ ነው። ፖለቲካ ሞደርናይዜሽንም የሚጀምረው ከጭንቅላት ተሃድሶ በመነሳት ነው። ታላቁ ፈላስፋ ፕሌቶ እንደሚለው የሰው ልጅ ዋናው ትልዩ ችግር የዕውቀት ችግር ነው እንደሚለው በጭንቅላት ላይ በከፍተኛ ደረጃ ካልተሰራ የሰው ልጅ እጣ ጦርነት፣ ድህነትና መሰደድ ይሆናሉ። በዚህ ዐይነቱ መሰረተ-ሃሳብ ላይ ከአንዳችንም ዘንድ በቂ ጥናት አልተካሄደም፤ ትንተናም አልተሰጠም። ታዲያ በምን በምን ነጥቦች ላይ ነው የምንወያየው? ዝም ብሎ በጭፍንና ካለመመሪያ የሚካሄድ ፖለቲካ የሚሉት ነገር ህዝባችንን ከድህነትና ከኋላ-ቀርነት በፍጹም አያላቅቀውም። አገርንም ከመበታተን በፍጹም ሊያድናት አይችልም። አንድ አገር ከመበታተን ሊድን የሚችለው ጠለቅ ያለ ዕውቀት ያለውና በደንብ የተደራጀ ኃይል ህዝቡን ለመሰብሰብ የሚችል ከሆነ ብቻ ነው። በሌላ ወገን በአገራችን ምድር ምንም ዕውቀት ሳይኖራቸው፣ ሰው ማለት ምን ማለት ነው? ህብረተስብ ማለት ምን ማለት ነው? እንድስ ማህበረሰብ በምን መልክና በምን ቲዎሪና ፖሊስ ሊገንባ የሚችለው? የሚሉትን መሰረታዊ ጥያቄዎች ሳያነሱ ጠብመንጃ በማንገት ለነፃነታችን እንታገላለን እያሉ የሚያወናብዱ ናቸው። ምንም ዐይነት ሳይንሳዊ ግንዛቤ ከሌለው ሰው ወይም ድርጅት ጋር ተቀምጦ በጥሞና መወያየትና መግባባትም በፍጹም አይቻሉም። እንዲያውም አብዛኛዎቹ የውጭ ኃይሎች መሳሪያ ስለሆኑ በእነሱ ድጋፍ ስልጣን ላይ በመውጣት አገርን ለማተረማመስና ለማዘረፍ ብቻ ነው የሚፈልጉት። ከዚህ የተመሰቃቀለ ሁኔታ ስንነሳ አገራችን ከገባችበት ወጥመድ ውስጥ በቀላሉ ማላቀቅ አይቻልም። ማንኛውም ኃይል ህሊናውን በማስገደድና ራሱን በመጠየቅ ወደ ቀናው መንገድ ለመመለስ በፍጹም አይችልም። አብዛኛዎቹም ዕድሜያቸው በጣም የገፋ ስልሆነ መንፈሳቸው ወይም ጭንቅላታቸው ውስጥ ከተቀረፀው መጥፎ አስተሳሰብ በፍጹም ማላቀቅ አይቻልም።
ሌላውና በጣም ትልቁ ችግር በተደራጀ መልክ በተለያዩ አርዕስቶች ላይ ሰፋ ያለ ትንተና በመስጠት ታዳጊውን ወጣት ለማስተማር አለመቻል ነው። በተለይም በአጠቃላይ ሲታይ ሁለ-ገብ ዕድገትን በሚመለከት፣ በተለያዩ ኤፖኮች የፈለቁትንና የሚያከራክሩትን የኢኮኖሚክስ ቲዎሪና እንዲሁም የኢኮኖሚክስ ፖሊሲዎች፣ ስርዓት ስላለው የህብረተሰብ አገነባብ፣ በተለይም ደግሞ የከተማና የመንደሮች ዕቅዶችን በሚመለከት፣ ለሰፊው ህዝብ የሚሆን የቤት ግንባታና የመገበያያ ቦታዎች፣ ስለ ሰፊው ህዝብ መንቃትና መደራጀት፣ እንዲያም ሲል በፖለቲካ ሂደት ውስጥ ስለመሳተፉ ጉዳይ፣ ስለትምህርት ፖሊሲና፣ በህዝብ ህይወትና በማሰብ ላይ ስላለው ተፅዕኖ…ወዘተ…ወዘተ. እያነሳን ለመወያየት ፍላጎት ስለሌንና ዕውቀትም ስለሌን ፖለቲካን የምንመለከተው እንደ አሻጥር መስሪያ ነው። በዚህም ምክንያት የተነሳ ፖለቲካ የሚለው ፅንሰ-ሃሳብ የወንበዴዎችና፣ በተለይም ደግሞ በውጭ ኃይሎች በሚደጎሙና ለሚያወናብዱ ሰዎች መሳሪያ በመሆን ህዝባችን ግራ እንዲጋባና ርስ በራሱም እንዳይተማመንም ለመሆን በቅቷል። ስለሆነም ፖለቲካ የሚለው ሃሳብ አገርን መገንቢያና ታሪክ መስሪያ መሳሪያ መሆኑ ቀርቶ ወደ አገር አፍራሺነት መሳሪያ ለመለወጥ ተችሏል። መልከም ግንዛቤ!!
fekadubekele@gmx.de
www.fekadubekele.com