ታጣቂ ኃይሎቹ የፈጠሩት ትብብር ይፋ የተደረገበት መግለጫ እንደወጣ፣ ቀድሞ ከተሰማው የተለየ አዲስ ነገር ይኖረው እንደሆን በሚል አገላብጬ አነበብኩት። አዲስ የሚባል ነገር የለውም። ሆኖም፣ ከተባለው ነገር ይልቅ፣ ያልተባለው ነገር ይበልጥ ቀልብ የሚስብ ሆኖ አገኘሁት።
መግለጫው፣ አሁን ሥልጣን የተቆጣጠረው አካል በሕዝብ ላይ እያደረሰ ነው የሚለውን ሰቆቃና በሀገሪቱ ላይ እያስከተለ ነው የሚለውን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ኪሳራ በማተት ይጀምራል። ከዚያም፣ ኃይሎቹ በለስ ቀንቷቸው መንግሥትን ከሥልጣን ቢያስወግዱ፣ የሚከፈተውን የሽግግር ምዕራፍ ዋና ዋና ዓላማዎች በሁለት ከፍሎ ያስቀምጣል። ከዚህ ውጭ፣ ትብብሩን የመሠረቱት ኃይሎች በመሠረታዊ የፖለቲካ ጥያቄዎች ላይ የደረሱበትን ተጨባጭ የጋራ አቋም የሚገልጽ ነገር በመግለጫው ውስጥ የለም።
ይህ ግን ያልተጠበቀ ነገር አይመስለኝም። ቀደም ሲል፣ ታጣቂ ኃይሎቹ በቀጥታም ሆነ በደጋፊዎቻቸው በኩል፣ ትብብሩ በመሠረታዊ የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ የተደረሰ መግባባትን መሠረት ያደረገ እንዳልሆነ፣ አሁን ላይ ሙሉ ትኩረታቸው ኃይላቸውን አስተባብረው አገዛዙን ማስወገድ ላይ እንደሆነ፣ ሌሎቹ ጉዳዮች፣ ከመንግሥት ውድቀት በኋላ በሽግግር ሂደቱ እንደሚስተናገዱ፣ በአንድም በሌላም መንገድ ሲገልጹ ቆይተዋል። ሆኖም፣ ምንም እንኳን ትብብሩ የጋራ የተባለ ተጨባጭ አቋም ባያስቀምጥም፣ የመግለጫው ይዘት ስለ ትብብሩ አጠቃላይ የእይታ አቅጣጫ፣ የአስተሳሰብ ዝንባሌ የሚጠቁሙን ነገሮች የሉትም ማለት አይደለም።
በመግለጫው ይዘት ውስጥ፣ ትኩረት የሚስበው ቀዳሚ ነገር ለሀገር አንድነት የተሰጠው ቦታ ነው። መግለጫው፣ በአንድ በኩል፣ አሁን ያለውን አገዛዝ፣ በሀገር ላይ የመፍረስ አደጋ የጋረጠ፣ ከሕዝብ ክብርና ከሀገር ሉዓላዊነት ጋር የተጣላ እያለ ይከሳል። በሌላ በኩል ግን፣ ትብብሩ የተመሠረተበት ምክንያት በተገለጸበት አረፍተ ነገር ውስጥም ሆነ፣ የሽግግር ምዕራፉን ዋና ዓላማዎች በሚዘረዝርበት አንቀጽ ውስጥ፣ ስለ ሀገር ሉዓላዊነትና ስለ ግዛት አንድነት፣ ጥርት ብሎ በቀጥታ የተቀመጠ ነገር አይገኝም። ከዚያ ይልቅ፣ “የሁሉንም ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ሕልውና ማስከበር”፣ “የሕዝቦችን ሕልውናና የሀገርን ደኅንነት መታደግ” እና መሰል ሰፊና አሳቻ ትርጉም ያላቸው ሐረጎችን መጠቀም መርጧል።
መግለጫው፣ አገዛዙ በሕዝብና በሀገር ላይ እያደረሰ ነው የሚለውን ጥፋት ከዘረዘረ በኋላ፣ ትብብሩ እንዲመሠረት አስገዳጅ የሆነውን ሁኔታ እንዲህ ያስቀምጣል፦ “በመሆኑም የኢትዮጵያ ሕዝቦች ሕልውና የሚገደን ሕዝባዊ ኃይሎች ይሄንን አገዛዝ በመገርሰስ የሁሉንም ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ሕልውና የማስከበርና አዲስ ምዕራፍ የመክፈት ታሪካዊ ኃላፊነት ወድቆብናል።” እዚህ ላይ፣ “ኢትዮጵያ” የሚለው ቃል “ሕዝቦች”ን ለመግለጽ ከመጠቀሱ በቀር፣ ስለ ኢትዮጵያ እንደ ሀገር የተባለ ነገር ጨርሶ የለም።
ከዚህ ዝቅ ብሎ፣ “ከአገዛዙ ውድቀት በኋላ የሚከፈተው የሽግግር ምዕራፍ ዋና ዓላማም” በሚል ንዑስ ርዕስ ሥር፣ በተራ ቁጥር አንድ ላይ ከተዘረዘሩት ነገሮች መካከል፣ “የሀገር ደኅንነት” የሚል አገላለጽ “የሕዝቦችን ሕልውና” ተከትሎ ተጠቅሷል። በተራ ቁጥር ሁለት ላይ በተዘረዘሩት ጉዳዮች ውስጥ ደግሞ፣ “ለሀገሪቱ ሰላምና ለሕዝቦች ቀጣይ ሕልውና” የሚል ሐረግ አለ። በተረፈ፣ ስለ ሀገር አንድነትና ሉዓላዊነት፣ ስለ ግዛት አንድነት የተባለ ነገር አይገኝም።
በአጠቃላይ፣ መግለጫው ምንም እንኳን አገዛዙን በሀገር አፍራሽነት ቢከስም፣ ወደ ትብብሩ ዓላማ ሲመጣ ግን፣ የሀገርን ጉዳይ “የሀገር ደኅንነት”፣ “ለሀገሪቱ ሰላም” በሚሉ አሻሚ አገላለጾች በስሱና በገደምዳሚው ማለፍን ነው የመረጠው። በአንጻሩ፣ “የሕዝቦችን ሕልውና”፣ “ለሕዝቦች ቀጣይ ሕልውና” የሚሉት አገላለጾች ጎላ ብለው ወደፊት እንዲወጡ ተደርጓል።
ትብብሩ በጋራ የፖለቲካ አቋም ላይ የተመሠረተ አይደለም ስለተባለ፣ በመግለጫው ይዘት ብቻ በመመርኮዝ፣ በሀገር አንድነት ላይ አቋሙ እንዲህ ነው እንዲያ ነው ለማለት አመች ላይሆን ይችላል። ሆኖም፣ ትብብሩን የፈጠሩት ኃይሎች የተቃኙባቸው የፖለቲካ እሳቤዎች፣ የሚያራምዷቸው አቋሞችና ዓላማቸው አድርገው ወደ ትግል የገቡባቸው የፖለቲካ መስመሮች እንዳሏቸው የታወቀ ነው። ስለዚህ፣ ትብብሩ በሀገር ሉዓላዊነትና በግዛት አንድነት ላይ የያዘውን አቅጣጫ ለመበየን፣ የትብብሩ አባላት በሀገር አንድነት ላይ ያላቸውንና የሚያራምዱትን አቋም መለስ ብለን መቃኘት ይኖርብናል።
ህወሓት፣ ምንም እንኳን በታሪክ ግጥምጥሞሽ ማዕከላዊ ሥልጣንን ተቆጣጥሮ ሀገር መግዛት የቻለ ኃይል ቢሆንም፣ ከጅምሩ ትግራይን የመገንጠል ትልም አንግቦ የተነሳ ድርጅት ነው። ሀገር ገዛሁ ብሎም ትግራይን የመገንጠል ሕልሙን እርግፍ አድርጎ መተው የቻለ ኃይል አይደለም። የህወሓትና የሀገር አንድነት ነገር፣ ያው እንደሚታወቀው፣ “ሲፋጅ በማንኪያ፣ ሲበርድ በእጅ”፤ “ለሥልጣናችን ሲመች ትኑር፣ ሳይመች ትቅር” ሆኖ ነው የዘለቀው።
በቅርቡ እንኳን፣ የህወሓቱ አማኑኤል አሰፋ፣ ከትግራይ ቲቪ ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ፣ ይህንኑ የቆየ የህወሓት ወላዋይ የሀገር አንድነት እሳቤ በሚያንጸባርቅ መልኩ፣ “የኢትዮጵያ ጉዳይ በሚፈሩት መንገድ እንዳይዘጋ፣ በብተና እንዳይቋጭ የሚሰጉ ወገኖች፣ በጥምረቱ ላይ ተስፋ ጥለዋል” ብለው ይጀምሩና፣ ይህን ሐሳብ በቅጡ እንኳን ሳይቋጩት፣ ራሳቸውን አቋርጠው “ማለት ኢትዮጵያ ውስጥ እኮ ሀገር ሊፈጠር ይችላል፤ it doesn’t matter… ግን ሀገሮች ሲፈጠሩ፣ በዩጎዝላቪያ መንገድ ሳይሆን፣ በቼኮዝሎቫኪያ መንገድ…” ብለው ይቀጥላሉ።
በኦላ በኩል፣ ኦሮሚያን የመገንጠል ትልሙ ብዙም የተሸፋፈነ አልመሰለኝም። አሁንም እዚያው የ“ኢምፓየሯ ኢትዮጵያ” ትርክት ላይ እንደቆመ ነው። ከሰሞኑ መግለጫዎቹና ቃለ መጠይቆቹ አጠቃላይ ይዘት መረዳት የሚቻለው፣ ኦላ ብረት አንስቶ ጫካ የወጣበትን፣ የቆየ አቋሙን እንዳልቀየረ ነው። ኦላ የራሱን የመገንጠል ትልም ከማስረገጥ ባሻገርም፣ የተቀሩት የትብብሩ አባላት ይህንን አቋሙን እያወቁ ወደ ትብብሩ እንደገቡ ጭምር ጠቁሞን ነው ያለፈው።
ወደ አፋብን ስንመጣ፣ የሀገር አንድነት እሳቤው ትንሽ የተወሳሰበና ገባ ብሎ መፈተሽ የሚጠይቅ ይመስለኛል። አፋብን ምንም እንኳን እንደሌሎቹ ሁሉ፣ አንድን ብሔር ማዕከል አድርጎ የተመሠረተ ብሔርተኛ አደረጃጀት ቢሆንም፣ እወክለዋለሁ የሚለው የአማራ ሕዝብ ለኢትዮጵያ አንድነት ካለው ቀናኢነት የተነሳ፣ በኢትዮጵያ አንድነት ላይ ጥያቄ የሚያነሳ ድርጅት እንዳልሆነ በስፋት ይታሰባል።
ባለፈው ዓመት ጥር ወር ላይ የወጣው የአፋብን መመሥረቻ ሰነድም፣ ድርጅቱ የሚመራበት ርዕዮተ ዓለም የአማራ ብሔርተኝነት እንደሆነ ይጠቅስና “የአማራ ብሔርተኝነት በራስ በቅነት ሁለንተናዊ ውስጣዊ አቅምን በመገንባት፣ በሀገራዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት ማዕቀፍ ውስጥ የሕዝባችንን ሕልውና በማረጋገጥ፣ መብትና ጥቅሞቹን በማስጠበቅ፣ የሌሎች ኢትዮጵያውያን የቡድንና የግለሰብ መብቶች የሚከበሩበት ሥርዓት በማንበር፣ በፍትሐዊና ሰላማዊ አብሮነት የሀገር ቀጣይነትን ለማረጋገጥ የሚተጋ ነው።” የሚል ሐሳብ አስፍሯል።
ስለዚህ፣ ጥያቄው ታዲያ፣ አፋብን በስፋት እንደሚታሰበውና በመመሥረቻ ሰነዱ ላይ እንደተጠቆመው፣ በሀገር ቀጣይነት ላይ ጥያቄ የማያነሳ ድርጅት ከሆነ፣ በሌሎች የትብብሩ አባላት በኩል መገንጠልን አስመልክቶ ለሚነሱ ሐሳቦች ለምን ግልጽ ተቃውሞ አላሰማም?
ሲጀመር፣ ህወሓትና ኦላ በሀገር አንድነት ላይ በያዙት አቋም መሠረታዊ የሚባል ለውጥ ባላደረጉበት ሁኔታ፣ ትብብሩን ለመቀላቀል እንዴት ወሰነ? በተለይ ኦላ ከዚህ በላይ የመገንጠል ትልሙን ግልጽ ሊያደርግ የሚችል አይመስለኝም። ታዲያ “የሀገርን ቀጣይነት ለማረጋገጥ እተጋለሁ” የሚል ድርጅት፣ መገንጠልን ቢያንስ እንደ አማራጭ ከሚያስቀምጥ ድርጅት ጋር፣ ለአንድ የፖለቲካ ግብ እንዴት ሊሠራ ይችላል? በዚህ ሁኔታ፣ እውን አፋብን፣ በመመሥረቻ ሰነዱ ላይ እንዳሰፈረውና በስፋት እንደሚታመነው፣ ከሌሎቹ ብሔርተኛ የፖለቲካ ኃይሎች በተለየ፣ በሀገር ሉዓላዊነትና አንድነት ላይ የማያወላውል አቋም አለው ለማለት ያስችላል ወይ?
ዝርዝሩን እመለስበታለሁ። ለእኔ መልሱ፣ በአጭሩ ግን፣ አፋብን በስፋት እንደሚታሰበው በሀገር ሉዓላዊነትና አንድነት ላይ የማያወላውል አቋም ያለው አደረጃጀት አይደለም የሚል ነው። ይህን ስል፣ አፋብን ራሱን ችሎ የመገንጠል አጀንዳ ያራምዳል ማለቴ አይደለም። ሆኖም ግን፣ የኢትዮጵያ መቀጠል አለመቀጠል ጉዳይ እንቅልፍ የሚነሳው ቡድን ነው የሚል እምነት የለኝም። እንበልና፣ ትብብሩ መንግሥትን መጣል ቢሳካለትና ከድል በኋላ ህወሓትና ኦላ የመገንጠል አጀንዳ ቢገፉ፣ አፋብን “መንገዱን ጨርቅ ያድርግላችሁ” ከማለት የሚገድበው መርሕ አለው ብዬ አላስብም።
ቀደም ብዬ የጠቀስኩት የአፋብን መመሥረቻ ሰነድ፣ “የአማራ ብሔርተኝነት በራስ በቅነት [self-reliance] ሁለንተናዊ ውስጣዊ አቅምን በመገንባት፣ በሀገራዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት ማዕቀፍ ውስጥ…” ይላል። ሆኖም፣ እዚሁ ላይ በአንድ በኩል “ሁለንተናዊ ውስጣዊ አቅም” እና “ራስ በቅነት”፣ በሌላ በኩል ደግሞ “ሀገራዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት” በሚሉት እሳቤዎች መካከል ያለውን ውጥረት ማየት ይቻላል። በተሳሰረ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ አውድ፣ በአንድ ሀገር ውስጥ፣ አንድ ማኅበረሰብ ተነጥሎ “ራስ በቅ” የሚሆነው እንዴት ነው? እርስ በራሱ ታጥሮ ይገበያያል? የብቻው መሠረተ ልማት ይኖረዋል? የራሱ ኢኮኖሚ፣ የራሱ ፖሊስ፣ የራሱ ጦር ይኖረዋል? ይህ አስተሳሰብ ከሀገር አንድነት እሳቤ ጋር የሚጣጣም አይደለም።
ሰነዱ በሌላ ቦታ ደግሞ “የአማራ ሕዝብ ራሱን በመዘንጋት እና ሀገሩን በማስቀደም እየኖረ…” የሚል፣ የአማራን ሕዝብና የኢትዮጵያን ጥቅም፣ አንዱ ቀድሞ ሌላው ሊከተል የሚችል፣ እንደ ሁለት የተለያዩ ጉዳዮች አድርጎ የሚያቀርብ ሐረግ አለው። በአጠቃላይ፣ በሰነዱ ውስጥ አማራና ኢትዮጵያ መሳ ለመሳ የሚጠቀሱባቸው ቦታዎች ቢኖሩም፣ የአፋብን የፖለቲካ መርሕ፣ የአማራን ሕልውናና የሀገርን ቀጣይነት እርስ በርስ የተሳሰሩና አንዱ ከሌላው ሊነጠል የማይችሉ ጉዳዮች አድርጎ ያያል ብሎ ለመናገር አያስደፍርም።
አፋብን በሀገር አንድነት ላይ ያለውን አቋም ጥያቄ ውስጥ የማስገባው ግን፣ የድርጅቱን የፖለቲካ እሳቤና አሁን ከኦላና ከህወሓት ጋር የፈጠረውን ትብብር ተመርኩዤ ብቻ አይደለም። አፋብን የተቃኘበት የአማራ ብሔርተኝነት፣ ከጅምሩ፣ በሙሉ ባይሆንም፣ ለኢትዮጵያ አንድነት ተቆርቋሪነትን ከራሱ ላይ አውርዶ የተነሳ ከመሆኑም አንጻር ነው።
የአማራ ብሔርተኝነት እንዲቀሰቀስ ብዙ ሁኔታዎች ግብዓት ሆነው ይሆናሉ። ሆኖም፣ ለዓመታት ሲራመድ የኖረው፣ አማራን ኢላማ ያደረገ “የጨቋኝና ተጨቋኝ” ትርክት፣ “ትምክህተኛ”፣ “ነፍጠኛ” ወዘተ በሚሉ ተለጣፊ ስያሜዎች በተለይ በአዲሱ የአማራ ትውልድ ላይ የፈጠረው ሥነ-ልቦናዊ ጫናና የማንነት ውዝግብ፣ ለብሔርተኝነቱ መቀስቀስ የተጫወተው ሚና ቀላል አይደለም። ይህ የአማራ ብሔርተኝነትን ውልደትና ዕድገት በትኩረት ሲከታተል ለነበረ ሁሉ የተደበቀ ነገር አይመስለኝም።
የአማራ ብሔርተኝነት ማቆጥቆጥ በጀመረባቸው የመጀመሪያ ዓመታት፣ በእንቅስቃሴው ውስጥ ጉልህ ተሳትፎ ያደርግ የነበረ አንድ ወጣት በማኅበራዊ ሚዲያ ገጹ ላይ አሜሪካ ውስጥ በአንድ 7-Eleven መደብር ካገኘው የኦሮሞ ወጣት ጋር የነበረውን ገጠመኝ አጋርቶ ማንበቤን አስታውሳለሁ። የማስታውሰውን ያህል፣ ይዘቱ ይህን ይመስላል።
ልጁ ወደ 7-Eleven ሲገባ፣ አንድ የኦሮሞ ልጅ በመደብሩ ውስጥ ሲሠራ እንዳገኘ በመግለጽ ይጀምራል። እሱም “ከየት ነህ?” ብሎ ሲጠይቀው፣ “ከኦሮሚያ” የሚል መልስ ያገኛል። በተራው የኦሮሞው ልጅ “አንተስ ከየት ነህ?” ብሎ እንደጠየቀው ይገልጻል። የኦሮሞው ልጅ ከእሱ የጠበቀው መልስ፣ ያው እንደተለመደው፣ “ከኢትዮጵያ” የሚል ነበር ይልና፣ እሱ ግን “ከአማራ ነኝ” ብሎ እንደመለሰለት ይገልጻል። ከዚያም ተጨዋውተው በሰላም እንደተሰነባበቱ ከገለጸ በኋላ፣ “ወገኖች፣ እያጋጨን እያስጠቃን ያለው፣ ይህ ‘ኢትዮጵያዊነት’ ላይ ሙጭጭ የምንለው ነገር ነው” በሚል መልዕክቱን ይቋጫል።
ይህን የማኅበራዊ ሚዲያ መልዕክት ያመጣሁት፣ በወቅቱ፣ በተለይ በዲያስፖራ፣ በአማራ ብሔርተኝነት አቀንቃኞች መካከል ሲንጸባረቅ የነበረውን፦ “ካልፈለጉን አንፈልጋቸውም፣ ከሄዱ እንሄዳለን፣ ከተገነጠሉ እንገነጠላለን፤ ኢትዮጵያ የእኛ ዕዳ አይደለችም፤ እንደ ቀደመው የአማራ ትውልድ፣ ኢትዮጵያ መጣች ቀረች ሆዳችን አይባባም” የሚል ስሜት ቁልጭ አድርጎ ስለሚያሳይ ነው።
ይህን ስል፣ ኢትዮጵያዊነትን ሽሽት ሳይሆን፣ የኢትዮጵያ ፖለቲካ በብሔር እንደመዋቀሩ፣ አማራም በብሔር ካልተደራጀ ይንሳፈፋል፤ እንደ አማራ መደራጀት በአማራ ሕዝብ ላይ የደረሰውን ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጫና ለመታገል ያለው ብቸኛ አማራጭ ነው በሚል ስሌት ወደ አማራ ብሔርተኝነት የገቡ የሉም ማለቴ አይደለም። የአማራ ብሔርተኝነት መልክ ይህ ብቻ ነው ማለቴም አይደለም።
ነገር ግን፣ የአማራ ብሔርተኝነት፣ በከፊልም ቢሆን፣ ላለፉት ሦስት አስርት ዓመታትና ከዚያም በላይ የኢትዮጵያን ፖለቲካ ሲቃኝ የኖረው “የጨቋኝና ተጨቋኝ” ትርክት ለፈጠረው ሥነ-ልቦናዊ ጫና ግብረ መልስ ሆኖ መቀስቀሱ የሚያከራክር አይመስለኝም። ከዚህ አንጻር፣ የአማራ ሕዝብ ለኢትዮጵያ ቀናኢ ስለሆነ ለሕዝቡ ቆመናል የሚሉ የአማራ ብሔርተኛ ፖለቲካ አራማጆችም፣ ከሕዝቡ ትይዩ፣ ለሀገር አንድነት ተቆርቋሪ ይሆናሉ የሚለው ስሌት የተወሰነ እውነታ ቢኖረውም፣ የአማራ ብሔርተኝነትን ሙሉ ገጽታ አያሳይም።
አፋብንም፣ በአማራ ብሔርተኝነት የተቃኘ የፖለቲካ ኃይል እንደመሆኑ፣ ስለ ሀገር አንድነት ያለው እሳቤ፣ በብሔርተኝነቱ የውልደት ሂደት ውስጥ ከተንጸባረቀው “የኢትዮጵያ ባለ እዳ አይደለንም”፣ “ካልፈለጉን አንፈልጋቸውም”፣ “ከሄዱ እንሄዳለን” ከሚሉ አስተሳሰቦች ተጽዕኖ ውጭ ይሆናል ብሎ ማሰብ ይከብዳል። የዚህን አስተሳሰብ ውልደት ለመረዳት ደግሞ፣ ወደ ኋላ ተመልሰን፣ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ፣ ለአማራ ብሔርተኝነት መነሳት መንስኤ የሆኑትን የትግራይና የኦሮሞ ብሔርተኝነቶች መሠረታዊ የፖለቲካ እሳቤ በአጭሩ ማስታወስ ጠቃሚ ይመስለኛል።
ህወሓት መራሹ የትግራይ ብሔርተኝነትም ሆነ ኦነግ መራሹ የኦሮሞ ብሔርተኝነት፣ የትግራይንና የኦሮሞን ሕዝብ “ነፃ” እናወጣለን የሚል ትልም ይዘው እንደተነሱ ብዙም ማብራሪያ የሚያስፈልገው ነገር አይደለም። ስማቸው ላይ በግልጽ ተከትቧል።
ይህ ማለት፣ በህወሓትና በኦነግ በተቀነቀነው የነፃ አውጪ ፖለቲካ ውስጥ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ዘመናትን በተሻገረ የማኅበረሰቦችና የመንግሥታት መስተጋብር የተበወዘ፣ የተከላለሰና የተወራረሰ፣ የትናንት ታሪኩ የተሳሰረ፣ የነገ ዕጣ ፈንታው ላይፈታ የተጋመደ፣ ብዙ መልክ ያለው የአንድ ሀገር ሕዝብ ሳይሆን፣ ብቻ ብቻቸውን ዕድል ፈንታቸው የሚወሰንላቸው፣ ያልተቀላቀሉ፣ ያልተወራረሱ፣ በገዢዎች ፍላጎት ብቻ አብረው ተጠፍረው የኖሩ፣ የብሔረሰቦች ደሴት ጥርቅም ነው።
ይህ እሳቤ፣ ሄዶ ሄዶ፣ “የራስን ዕድል በራስ መወሰን፣ እስከ መገንጠል” የሚል፣ ተደጋግሞ እንደተባለው፦ “ራስ” የሚባለው ማን ነው? ግዛቱስ የት ድረስ ነው? ድንበሩንስ ማን ይወስናል? በዚያ ግዛት ውስጥ የሚኖር ሌላ ሕዝብስ የራሱን ዕድል በራሱ እንዴት ይወስናል? የሚሉትን ጥያቄዎች በቅጡ ያልመለሰ፤ እንግዲያውስ ሀገሪቱ እንዲህ ተበጣጥሳና ተፈረካክሳ እንድታልቅ ከተፈረደባት፣ ሁሉም ማኅበረሰብ በስፋት ተቀላቅሎ የሚኖርባቸው አካባቢዎችና ከተሞች ዕጣ ፈንታስ ምንድን ነው? ቅይጥ የብሔረሰብ ማንነት ያላቸው ስፍር ቁጥር የሌላቸው ኢትዮጵያውያንስ መውደቂያቸው የት ነው? የሚሉ መሠረታዊ ጉዳዮችን እንኳን ያልተነተነ፣ ያላብራራ፣ መያዣ መጨበጫ የሌለው ነገር ሕግ ተብሎ በኢትዮጵያ ላይ እንዲጫን አድርጓል።
በአማራ ብሔርተኝነት ወደተቃኘው አፋብን ስንመለስ፣ ህወሓትና ኦነግ የተጠቀሙትን “ነፃነት” የሚል ቃል አናገኝም። ስለ መገንጠልም አያነሳም። በምትኩ የምናገኘው፣ ቀደም ብዬ እንዳነሳሁት፣ “የአማራን ሕልውና ማስጠበቅ”፣ “የአማራ ራስ በቅነት [self-reliance]” እና መሰል አገላለጾችን ነው። ይህ “አማራን ራሱን እናስችላለን” እሳቤ፣ ያው ህወሓትና ኦነግ ካራመዱት፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ልዩ ልዩ ብሔረሰቦች ከሀገር ሕልውና የተለየ የየራሳቸው የሆነ ሕልውና አላቸው፤ ዕድል ፈንታቸውንም ብቻ ብቻቸውን መወሰን ይችላሉ ከሚለው እሳቤ የሚመዘዝ ነው። የአቀራረብ እንጂ ብዙም የይዘት ልዩነት የለውም። አልሸሹም፤ ዞር አሉ ነው።
እዚህ ላይ፣ የኢትዮጵያ ፖለቲካ የተቃኘበት “የጨቋኝና ተጨቋኝ” ትርክት፣ ከ1983 ዓ.ም. በኋላ በተገነባው የፖለቲካ ሥርዓት ውስጥ ተቋማዊ መልክ አግኝቶ በአማራ ማኅበረሰብ ላይ ላደረሰው ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጫና፣ ግንባር ቀደም ተጠያቂው ህወሓትና ኦነግ የተከተሉት የፖለቲካ መስመር መሆኑ እርግጥ ነው። ይህ ሆኖ ሳለ፣ የአማራን ማኅበረሰብ የሕልውና አደጋ እመክታለሁ ብሎ የተደራጀው አፋብን፣ ዛሬ ላይ ተነስቶ “ህወሓትንና ኦላን በቀኝና በግራ ታቅፌ አራት ኪሎ ካልመለስኩ” የማለቱ እንቆቅልሽም ከላይ ካነሳሁት ሐሳብ ጋር የተያያዘ ይመስለኛል።
የአማራ ብሔርተኝነት ምንም እንኳን ለአማራ ሕዝብ ተቆርቋሪ ሆኖ ቢነሳም፣ ሀገር የሚለውን እሳቤ ከሚረዳበት መነጽር ጀምሮ አጠቃላይ የፖለቲካ ቅኝቱ፣ ቀደም ሲል ህወሓትና ኦነግ ባራመዱት የፖለቲካ እሳቤ ተጽዕኖ ሥር የወደቀ ነው። የብሔርተኛ እንቅስቃሴዎቹ አጀማመር የተለያየ ታሪካዊ ዳራ ሊኖረው፣ የታሪክ አረዳዳቸውም ሊለያይ ይችላል። በየትም በኩል ዞረው ይድረሱበት፣ መሠረታዊ የፖለቲካ እሳቤያቸው ግን፣ ከሞላ ጎደል በአንድ መስመር ነው የሚፈሰው።
ገፈቱን ትተን፣ ጠለቅ ብለን ካየነው፣ የአማራ ብሔርተኝነት የፖለቲካ እሳቤ፣ የቀደሙትን የብሔርተኛ ፖለቲካ መስመሮች በመሠረታዊ መርሕ ደረጃ የመቃረን አካሄድ አይደለም። ይልቁንም፣ በተዘረጋው መስመር ገብቶ ሌላ አንድ ተገዳዳሪ ኃይል የመሆን፣ ከእነሱ አንዱ የመሆን አካሄድ ነው። ከዚህ አንጻር፣ ዞረው ዞረው አንድ ላይ መገጣጠማቸው እምብዛም ላያስገርም ይችላል።
ወደ ተነሳሁበት የሀገር አንድነት ጉዳይ ስመለስ፣ ቀደም ብዬ እንዳስቀመጥኩት፣ ትብብሩን የመሠረቱት ታጣቂ ኃይሎች የኢትዮጵያን ሕዝብ እንደ አንድ የተሳሰረ ማንነትና የጋራ ሕልውና ያለው አንድ ሕዝብ የማይረዱት ከሆነ፣ “የኢትዮጵያን ሕዝብ ሕልውና ያስጠብቃሉ” ተብሎ ተስፋ የሚጣልባቸው እንዴት ነው? መሰባሰባቸውና መተባበራቸው፣ የሁሉም ነገር ማጠንጠኛ የሆነውን የሀገር አንድነት የሳተ ከሆነ፣ ቀንቷቸው ማዕከላዊውን መንግሥት ቢያስወግዱ፣ ሀገር ወደ መቀራመት ላለማምራታቸው ምን ዋስትና አለ?
የኢትዮጵያ ሕዝብ የተጋመደ፣ የተዛመደ ብቻ አይደለም። ሀገር በጋራ ያቀና፣ ያጸና፣ የጠበቀ ሕዝብ ነው። ደምና አጥንት የተከፈለላት ሀገር ነው ያለን። የተፈጥሮ ሀብታችን ተመጋጋቢ፣ የጋራ ሀብት ነው። ከተሞች፣ መንገዶች፣ መሠረተ ልማቶች፣ የንግድና የገበያ ትስስሮች፣ የመንግሥትና የሕዝብ ተቋማት፤ ሁሉም በጋራ ሀብት፣ በጋራ እውቀትና ጉልበት፣ በትውልድ ቅብብሎሽ የተገነቡ ናቸው። ይህን ሕዝብ “ድንበርህ እዚህ ድረስ ብቻ ነው፣ ድርሻህ ይሄ ብቻ ነው፤ ራስ ራስህን ቻል” ማለት ታሪካዊም፣ ፍትሐዊም፣ ሞራላዊም መሠረት የለውም። የሚሆንም ነገር አይደለም።
አሁን፣ አንድ ላይ ሆነን ያሉን አለመግባባቶች በፖለቲካ ውክልና፣ በቋንቋ፣ በአስተዳደር ድንበር፣ በመልካም አስተዳደርና በኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ወዘተ ዙሪያ የሚያጠነጥኑ ሊሆኑ ይችላሉ። ኢትዮጵያን ለመነጣጠል የተሞከረ ቀን ግን፣ ወደለየለት የመሬት፣ የንብረት፣ የተፈጥሮ ሀብት፣ የቅርስና የታሪክ ሳይቀር ሽሚያ፣ ማለቂያ ወደሌለው ግጭት፣ ብሎም ወደ ሀገር መፍረስ እናመራለን።
የሀገር መፍረስ የሚያስከትለውን የማያባራ ጦርነት፣ ሞትና ዕልቂት፣ መፈናቀልና ስደት፣ ጥፋትና ውድመት መገመት አያዳግትም። በዘመናት አብሮ የተሰፋ ማኅበረሰብን ለመተርተር፣ ለመነጣጠል መሞከር፣ ምናልባት አሁን ልናስባቸው ከምንችላቸውም በላይ አዳዲስ ፈተናዎችንና አደጋዎችን ይፈለፍላል እንጂ፣ በምንም መልኩ የችግሮቻችን መፍትሔ ሊሆን አይችልም።
ኢትዮጵያ የኢትዮጵያ ሕዝብ የሕልውና መሠረት ናት። የኢትዮጵያ ሕዝብ ሕልውና ከሀገሩ ሕልውና ሊነጣጠል አይችልም። የሀገር አንድነት ሳይጠበቅ፣ የሚጠበቅ የሕዝብ ሕልውና የለም። የኢትዮጵያ ሕዝብ ሕልውናን አረጋግጣለሁ የሚል አካል፣ በኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና በግዛት አንድነት ላይ የማያወላውል፣ የማይዋዥቅ፣ ወጥ አቋም መያዝ ግድ ይለዋል። ወዲህ ወዲያ የለውም። ሌላ ሌላውን ትተን፣ የሀገር አንድነትን በሚያክል ወሳኝ ጉዳይ ላይ እንኳን ቁርጥና ጥርት ያለ አቋም መያዝ የተሳነው ስብስብ፣ ሕዝብን ሊታደግ አይችልም።
አረረም መረረም፣ አሁን የኢትዮጵያ ሕዝብ ሀገር አለው። ጦርነት የሚያስከፍለው ዋጋ እጅግ ከባድ ነው፤ መዘዙም ብዙ ነው። ያ ሁሉ ዋጋ ተከፍሎ፣ ነገ የተሻለ ሀገር፣ የተሻለ መንግሥት፣ የተሻለ ኑሮ ይመጣል የሚል ተስፋ ቢኖር፣ አንድ ነገር ነው። አሁን ትብብሩ እየሄደበት ያለው መንገድ ግን፣ እንደሆነችውም ሆና፣ ያለችውን ሀገር የማሳጣት አደጋን የሚጋብዝ ነው።