የአገራችን የተወሳሰበ ችግር  አንድን መሪ በሌላ በመተካት ብቻ የሚፈታ አይደለም  !!  – ፈቃዱ በቀለ፣ ዶ/ር

ፈቃዱ በቀለ፣ ዶ/ር

ሰኔ 26፣ 2019

መግቢያ

 

በየጊዜው የተለያዩ ጸሀፊዎች አዳዲስ ጽሁፎችን በመጻፍ ለሰፊው ህዝብ ለንባብ ያቀርባሉ። እንደምገምተው ከሆነ በዚህ መልክ የታሪክን አደራ ለመወጣት በማሰብና አገራቸውም እንዳትበታተን ለማሳሰብ ነው። ይሁንና ግን አንደኛ፣ የአብዛኛዎች የአጻጻፍ ስልት ግልጽ አይደለም። ሁለተኛ፣ አብዛኛዎች ጽሁፎች በተወሰነ ሃሳብ ላይ ያተኮሩና በዚያው ላይ የሚሽከረከሩ አይደሉም። በሌላ አነጋገር፣ እንድንወያይበትና እንድንከራከርበት በር የሚከፍቱ አይደሉም። ሁሉም እንደፈለገውና እንደመሰለው የሚጽፍ እንጂ ከተጨባጭ ሁኔታዎችና ከህሊና ሁኔታ በመነሳት ችግራችንን የሚተነትን አይደለም። በሶስተኛ ደረጃ፣ በአንዳንድ ድህረ-ገጾች ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በአንድ ግለሰብ ሃሳብና ርዕይ ላይ ያተኮሩ ሳይሆኑ፣ የግለሰብን ስም የሚያወድፉ ወይም ሞራሉ እንዲወድቅ የሚያደርጉ ናቸው። አሁንም በሌላ አነጋገር፣ ሳይንሳዊ ትንተና መሆናቸው ቀርቶ ተራ እንካ-ስላንቲሃ ወይም ስድብ ናቸው። ስለሆነም የሚያሰተላልፉት መልዕክት ይህንን ያህልም የሚጨበጥና እንድናስፋፋው ወይም ትችታዊ በሆነ መልክ እንድንገመግመው የሚጋብዘን አይደለም።

እንደሚታወቀው አንድን ህብረተሰብ የሚመለከት ጽሁፍ ተጽፎ በሚቀርብበት ጊዜ የራስን ስሜት ለመግለጽ ተብሎ አይደለም። እንደሚገባኝ ከሆነ ለህብረተሰቤ ያገባኛል የሚል፤ ስለዚህም የራሴን አስተዋፅዖ ማበርከት አለብኝ ብሎ ብዕሩን የሚሰነዝር፣ 1ኛ) ስለሚጽፈው ነገር ማውቅ አለበት። 2ኛ) ለምን እንደሚጽፍ መረዳት አለበት። በሌላ አነጋገር ምን መልዕክትና ትምህርት ለማስተላለፍ እንደሚፈልግ ማውጣትና ማውረድ አለበት። 3ኛ) ምን ዐይነት የአሰራር ስልት እንደሚጠቀም መገንዘብ አለበት። ዝም ብሎ በጥሩ አማርኛም ሆነ አንግሊዘኛ አቀነባብሮ ለመጻፍ ብቻ ወይስ ሳይንሳዊ የአሰራር ስልትን በመጠቀም፣ በተለይም ታዳጊውን ትውልድ ለማስተማር እችላለሁ ብሎ የበኩሉን አስተዋፅዖ የሚያበረክት መሆኑን ከመጀመሪያውኑ መረዳት አለበት። ይህም ማለት አንድን ህብረተሰብም ሆነ አንድን ሁኔታ የሚመለከት ነገር ለመጻፍ ስንነሳ የተወሰነ ስልትንና ሳይንሳዊ የአተናተን ዘዴን መከተል አለብን። አንድን የአሰራር ዘዴና ሳይንሳዊ አተናተንን ያልተከተለ አጻጻፍ የሰውን ጭንቅላት ለማደስና ለማስተማር አይችልም። ዕውነተኛውንም የነፃነት መንገድ ይዘን እንድንጓዝ መመሪያ ሊሆነን አይችልም።  ከተጨባጭ ሁኔታዎችና ከአገዛዝ አወቃቀር፣ እንዲሁም ከአጠቃላዩ የህዝብ አስተሳሰብ ተነስቶ የማይጻፍና የችግሮችንም አመጣጥ በተቻለ መጠን ተቀራራቢ በሆነ መንገድ ለማመልክት የማይችል ጽሁፍ የሰውን አስተሳሰብ በታኝ ብቻ ሳይሆን፣ የአንድን ህብረተሰብም ችግር እንዳይፈታ ዕንቅፋት ይሆናል።  በየጊዜው በኢትዮጵያውያን ድህረገጾች ላይ በእንግሊዘኛም ሆነ በአማርኛ የሚወጡትንና ለንባብ የሚቀርቡትን ጽሁፎች ስመለከትና ሳገላብጥ ግራ የሚያጋቡኝ ነገሮች አሉ። ለኢትዮጵያ ህዝብና ለአገራችን ተቆርቋሪ ነን ብለውና አጥብቀው የሚሟገቱትን ሰዎች ጽሁፍ ሳነብ ለምን እንደሚጽፉ፣ ምን ዐይነት ስልትና ሳይንሳዊ ዘዴን እንዲሁም የትኛውን ፍልስፍና መሰረት በማድረግ እንደሚጽፉ ለማወቅ ግራ ከተጋባሁ ዘመናት አልፈዋል። የአገራችንም የተወሳሰበ ችግር እንዴት እንደሚፈታና እንደ ህብረ-ብሄር ወይም እንደ አገር በጠንካራ መሰረት ላይ በየአቅጣጫው እንዴት መገንባት እንዳለባት የሚጠቁም አጻጻፍ አይደለም።

ስለሆነም አገራችንና ህዝባችንን ነፃ እናወጣለን፣ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ባለቤት በማድረግ የተከበረችና የተፈራች አገር እንዲገነባ እናደርጋለን፣  ሺህ በሺህ የሚቆጠሩ ሳይንቲስቶች፣ የቴክኖሎጂ ሰዎች፣ ፈላስፋዎችና የጥበብ ስዎች ለማፍራት የሚያስችል መሰረት መጣል አለብን የምንል ከሆነ ከሳይንሳዊ ጥናትና ትንተና ማለፍ አንችልም። የፍልስፍና መሰረትና ዕምነትም ያስፈልገናል። ማንኛውም ነገር፣ ምግብ እንኳ ሳይቀር ከሳይንስ አኳያ እየታየ የሚተከልና ለምግብም የሚቀርብ ካልሆነ በሽታን ነው የሚያስከትለው። በተጨማሪም ከሳይንስ አንፃር እየታየና እየተመጠነ የማይቀቀል ምግብ የመጨረሻ መጨረሻ ጤንነትን ያቃውሳል። አንድ ጽሁፍም እንዲሁ ከሳይንስ አኳያ የማይጻፍና የተወሰነ የአሰራር ዘዴን የማይከተል ከሆነ የታዳጊን ትውልድ ጭንቅላት ከማደንዘዝ በስተቀር የሚያበረክተው አዎንታዊ አስተዋፅዖ አይኖርም። ጭንቅላቱ እንዲሾልና ተጨባጩን ሁኔታ በደንብ እየተመለከተ ትንተና ለመስጠት የማይችል ወጣት ትውልድ በሚፈለፈልበት ህብረተሰብ ውስጥ ደግሞ ትግል ከስሜታዊነት ሊዘልቅ በፍጹም አይችልም። እንደዚህ ዐይነቱ ትውልድ ደግሞ በራሱ ላይ እንዳይተማመንና ጥቂት ግለሰቦችን እያመለከ እንዲኖር ይገደዳል።  ይህ ዐይነቱ ሁኔታ ደግሞ የግዴታ ወደ ርስበርስ መነታረክና ወደ መጨራረስ እንድናመራ ያስገድደናል። በየካቲቱ አብዮት ወቅት የደረሰው የወንድማማቾች መተላለቅና፣ እስከዛሬም ደርሶ እንዳንግባባ ያደረገን ነገር ከዚህ ከሳይንስና ከፍልስፍና ውጭ የተደረገና የሚደረገ ትግል መመሪያችን በመሆኑን ነው። በመሆኑም  ከሳይንስ፣ ከፍልስፍና፣ ከዲያሌክቲክና ከሶስይሎጂ ውጭ ትግል ማድረግ በመጀመራችን ስንትና ስንት መቶ ሺህ ህዝብ እንዲያልቅ ማድረጋችን ብቻ ሳይሆን፣ ትግሉ ሁለት ትውልድ አልፎ እስከዛሬ ድረስ ሲያፋልመንና  ሲያነታርክን ቆይቷል። በዚህም ከቀጠለ በቀላሉ መቋጠሪያ የሚገኝለት አይመስለኝም። ይህ ጸሀፊ ይህንን ችግር ተረድቶ የአመለካከታችን፣ ሁኔታዎችን የማንበብ ጉዳይና፣ ከዚያ በመነሳት እንዴት ትንተና ማድረግ እንዳለብን ከአስር ዐመት በላይ የፈጀ ትግል ቢያደርግም ተደማጭነት ሊያገኝ አልቻለም።  በዚህም የተነሳ ሀቀኛውን የትግል ዘዴ ከአሳሳቹና የሰውን ጭንቅላት ከሚያበላሸው የትግል ዘዴ ለመለያየት የቱን ያህል አስቸጋሪ እንደሆነ ከተገነዘብኩኝ ዘመናት አለፈዋል።  ይሁንና ግን ደግሞ እጅን አጣጥፎ መቀመጥ እንደተሸናፊነት መቆጠሩ ብቻ ሳይሆን ታሪካዊ ወንጀልም እንደመስራት ይቆጠራል። የድህነቱ ዘመን እንዲራዘምና ህዝባችን ውርደትን ተከናንቦ በውጭ ሃይሎች ዘለዓለሙን እየተናቀ እንዲኖር አስተዋፅዖ እንደማበርከት ይቆጠራል።

ያም ሆነ ይህ እኔም ሆነ ሌሎችም ጻፉ በአጠቃላይ ሲታይ የአስተሳሰብ ለውጥ (mindset) ማድረግ እስካልቻልን ድረስ ምንም ዐይነት ለውጥ ልናመጣ አንችልም።  ዛሬ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ሰፈነባቸው የሚባሉትን የምዕራብ አውሮፓ የካፒታሊስት አገሮችን ሁኔታ ስንመለከትና ስንመረምር በየአገሮች ውስጥ የአስተሳሰብ ለውጥ ሳይደረግ ዝም ብሎ በጭፍን ትግል የተካሄደበት ቦታ የለም። በሌላ ወገን ግን የአስተሳሰብ ለውጥ አንድ ቦታ ላይ በመጫን የሚመጣ  ሳይሆን በየጊዜው ራስን በመጠየቅና የጭንቅላት ጂምናስቲክ በማድረግ የሚመጣ ነው። የታሪክን ሂደት መረዳት የሚቻለውና የአንድን ህብረተሰብ አስቸጋሪ ሁኔታ መገንዘብ የሚቻለው ከሳይንስ አንፃር ትግል ለማድረግ ሲሞከርና ጥረት ሲደረግ ብቻ ነው። በየጊዜው ጥያቄን ማቅረብ ሲቻል ብቻ ነው ተቀራራቢ መልስ ማግኘት የሚቻለው። ከዚህ ስንነሳ  የተወሳሰበውን የአገራችንን የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የባህልና የስነ-ልቦና ችግሮችን ለመረዳት የግዴታ የአዕምሮን መሰረታዊ ወይም ቁልፍ ቦታ መረዳት እጅግ አስፈላጊ ነው ብዬ አምናለሁ። ቆንጆም ሆነ መጥፎን ነገር ማድረግ የምንችለው በአዕምሮአችን እየታገዝን በመሆኑ የአዕምሮን ቁልፍ ሚና መረዳቱ በተለያየ መልክ የሚታየውንና የሚገለጸውን ችግር ለመረዳት ያግዘናል።

 

ዋናው ችግራችን! የአዕምሮን ወይም የመንፈስን ትርጉም ያለመረዳት ነው !

እንደሚታወቀውና ሁላችንም የምንቀበለው ሀቅ ማንኛውም ሰው በግልጽ የምናየውና የምንዳስሰው አካል ብቻ ሳይሆን መንፈስም ሆነ አእምሮ እንዳለው ነው። እኛም ራሳችን አለን። እንደ አስተዳደጋችን፣ እንደ ትምህርት አቀሳሰማችንና ንቃተ-ህሊናችን የማሰብ ኃይላችን፣ አንድን ነገር መረዳትና መተንተን፣ ወይም ያለመረዳትና ለመተንተን ያለመቻል፣  ማውጣትና ማውረድ፣ ግንዛቤን ማሳደር፣ ወይም ግንዛቤ ማሳደር ያለመቻል፣ አርቆ የማሰብ ኃይላችንም ሆነ ያለማሰብ፣ ቁጠኛ መሆንም ሆነ አለመሆን፣ አመጸኛ መሆንም ሆነ፣ አንድን ነገር በሰላምና በውይይትም ሆነ በክርክር መፍታት መቻል ወይም ያለመቻል፣ ስለሰው ልጅ የሚኖረን ግንዛቤም ሆነ ግንዛቤ ያለመኖር፣ ስለ ነፃነትም ሆነ ስለ ዕድገት የሚኖረን ግምትና ግምት ያለመኖር፣ በጠቅላላው ከየት እንደመጣን፣ በዚህች ዓለም ላይ ለምን እንደምንኖርና ምን መስራት እንዳለብንና ወዴትስ እንደምንጓዝ ማወቅና መረዳት የምንችለው በመንፈስና በአዕምሮ ኃይላችን አማካይነት ብቻ ነው። ባጭሩ፣ መጥፎ ነገርም ሆነ ጥሩ ነገርን ማድረግ የምንችለው በአዕምሮአችንና በመንፈሳችን እየተመራን ነው። ለማንኛውም ዐይነት ድርጊታችን ፣ በተለይም ለህብረተሰብ ዕድገት በሚደረገው ትግል የመንፈስ አወቃቀራችና የንቃተ-ህሊናችን ሁኔታ ከፍተኛውን ቦታ ይይዛሉ ማለት ነው። ከመንፈስና ከአዕምሮ እንዲሁም ከንቃተ-ህሊና ውጭ የምናደርገው ምንም ነገር የለም። በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የሚዳሰሰውና በግልጽ የሚታየው አካላችን የመንፈሳችን ተገዢ ወይም በመንፈሳችን የሚመራ ነው። በሌላ ወገን ግን መንፈሳችን የአካላችን ተገዢ በመሆን ድርጊታችንን ወደ ማይሆን አቅጣጫ በመመራት ችግር ፈጣሪዎች እንድንሆንና ህብረተሰብንም እንድናመሰቃቅል ያደረገናል። ይሁንና ግን የማሰብ ኃይላችን የዳበረ፣ የተወሳሰቡ ነገሮችን መረዳት የሚችልና የመተንተንም ኃይል ካለው የምናደርገውን እናውቃለን ማለት ነው። መንፈሳችን የሰውነታችን ወይም የአካላችን ተገዢ መሆኑ ቀርቶ መንፈሳችን የበላይነትን በመቀዳጀት ታሪካዊ ነገሮችን መስራት እንችላለን።

በብዙ ምርምሮችና ጥናቶች እንደተደረሰበት ለአንድ ሰው የማሰብ ኃይልና ማመዛዘን እንዲሁም በረቀቀ መልክ ማሰብ መቻልና ያለመቻል የተወለደበትና ያደገበት ህብረተሰብ ወሳኝ ሚናን እንደሚጫወት ነው። በሌላ አነጋገር፣ የምርት ኃይሎች ማደግ ወይም አለማደግ፣ የባህል ዕድገት መኖር ወይም አለመኖር፣ የከተማዎች በቆንጆ መልክ መሰራትና ያለመሰራት፣ በገጠር ውስጥ ማደግና ያለማደግ፣ ወዘተ… በአሰተሳሰባችን ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ይኖራቸዋል።  የቤተሰብ ሁኔታ፣ የማሀበረስብ የአኗኗር ስልት፣ እንዲሁም አጠቃላዩ የህብረተሰብ እወቃቀር የአንድን ሰው አስተሳሰብ ይቀርጹታል፤ ድርጊቱንም ይወስናሉ። ለዚህ ነው መጀመሪያ የግሪክ ፈላሳፎች ምርምር ሲጀምሩ ለአዕምሮ ከፍተኛ ቦታ የሰጡት። በነሱ ዕምነትም የማንኛውም የሰው ልጅ ድርጊት በአርቆ የማሰብና ያለማሰብ ኃይሉ የሚወሰን ሲሆን፣ ይህ በአንፃሩ  ደግሞ ሊወሰን የሚችለው በቀሰመው ዕውቀት አማካይነት ብቻ ነው። በተለይም ሶፊስቶችን አጥብቀው ይዋጉ የነበሩት ሶክራተስና ፕላቶ አርቆ የማሰብ ኃይልን ሚና ሲያነሱ ትክክለኛ ዕውቀት ለማሰብ ኃይላችንና ለፈጠራ ስራችን የቱን ያህል ወሳኝ ሚና እንዳለው በማስመር ነው። ለዚህም ነው በሚታዩ ነገሮች ላይ ብቻ ያተኮረውንና በጥቂት ሰዎች ተደንግጎ የሚቀርበውን ህግም ሆነ ዕውቀት እንደመመሪያ አድርገው ማስተማርና መስበክ የጀመሩትና ሶፊስቶችን ወይም የተሙለጨለጨ አስተሳሰብ ያላቸውን ምሁሮች አጥብቀው መዋጋት የጀመሩት። በሶክራተስና በፕላቶም ዕምነት ግሪክ በጊዜው የነበራትን የበላይነትና ኃያልነት ልትነጠቅና የመጨረሻ መጨረሻም ስልጣኔዋ ሊዳከም የቻለው በጊዜው የነበሩት አገዛዞች በሶፍስቲያዊ ዕውቀት በመሰልጠናቸውና፣ ከዚህም በመነሳት በስልጣንና በሀብት በመመካታቸውና በመባለጋቸው ነበር። ሌሎች ስልጣኔዎችና ኃያላን መንግስታትም ሊፈራርሱና ሊወድሙ የቻሉት በጉልበትና በሀብት በመመካት ብቻ በመስፋፋታቸውና የመጨረሻ መጨረሻ ኃይላቸው በመዳከሙ ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን፣ የአዕምሮና የመንፈስ አለመዳበር፣ አርቆ አለማሰብና ባሉት ነገሮች ብቻ ጠግቦ ወይም ተደስቶ መኖርና፣ ይህንን እንደባህል አድርጎ ማስፋፋትና ማስተማር ለዕድገት ከፍተኛ እንቅፋት እንደሚሆን የታወቀ ጉዳይ ነው። ፈላስፋዎች ትችታዊ አመለካከት ወይም እየመላለሱ መጠየቅ የሚሉት ቁም ነገር አለ። ይህም ማለት አንድ የሚነገርን ነገር ዝም ብሎ መቀበል ሳይሆን መመርመርና ትክክል መሆኑና አለመሆኑን በጥያቄ ውስጥ ማስቀመጥ እንደሚያስፈልግ አጥብቀው ያስተምራሉ። ስለሆነም በፕላቶ ዕምነትና መመሪያ አንድን ነገር ዝም ብሎ ከመቀበል በፊት የግዴታ እየመላለሱ መመርመርና ማገናዘብ እንደሚያስፈልግ ያሰተምራል። አንድ ነገር ተቀባይነትን ከማግኘቱ በፊት በዲያሊክቲክና በፍልስፍና መነጽር መመርመርና መታሸት አለበት። በዚህ አማካይነት ብቻ ሀቀኛውን ከአሳሳቹ፣ ለዕውቀትና ለስልጣኔ የሚታገለውን ለስልጣንና ለራሱ ዝና ብቻ ከሚታገለው ነጥሎ ማወቅ ይቻላል። ይህንን ሳያደርግ ዝም ብሎ በጭፍን በትግል ዐለም ውስጥ የገባ የአንድ ሰው ወይም የአንድ ድርጅት ጭራ በመሆን የራሱን ነፃነት ማጣቱ ብቻ ሳይሆን ለዕውነተኛ ህዝባዊ ነፃነት የሚደረገውን ትግል ያደናቅፋል። በየጊዜው ጠብ ጫሪ በመሆን ሀብረተሰብአዊ ስምምነት እንዳይኖር በማድረግ የአንድ ህዝብ ዕድል በውጭ ኃይሎች እንዲወሰን ያደርጋል።

በአጠቃላይ ሲታይ መንፈስ ወይም አዕምሮ በመሰረቱ የቆንጆ ነገሮች ማፍለቂያ ነው። አንድን ነገር በስነ-ስራዓት እንድንሰራ ወይም እንድናደራጅ፣ እንድናቅድ፣ እንድናቀናጅና መልክ እንድንሰጠው የሚመራን ነው። መንፈስ ወይም አዕምሮ የሙዚቃ፣ የሰዕል፣ በአጠቃላይ ሲታይ ደግሞ የዕውቀት ምንጭ ሲሆን፣ በዚህ እየተመራን ቆንጆ ቆንጆ ነገሮችን እንድናስብና ተግባራዊ እንድናደርግ መመሪያ የሚሰጠን ነው፡፡ ለህይወታችን ትርጉም እንድንሰጠው፣ ሰው መሆናችንን የሚያረጋግጥልን ልዩ ነገር ነው። እንደሚባለው መንፈሱ ቆንጆ የሆነና የማሰብ ኃይሉ የዳበረ ሰው ተዓምር ይሰራል። በረሃውን ወደ ገነት መለወጥ ይችላል። ልዩ ዐይነት ቅርጽና ውበት በመስጠት የሰው ልጅ ኑሮ ዝርክርክ እንዳይሆን ያደርጋል። ስለሆነም ቆንጆ መንፈስ የፍቅር፣ የሰላም ፣ የስርዓት፣ የጥበብና የፈጠራ ምንጭ ነው፡፡ በአንፃሩ ደግሞ መንፈሱ የተረበሸ ወይም በልጅነቱ በደንብ ያልተኮተኮተ የተቃራኒውን የሚያደርግ ነው። ከበጎ ነገር ይልቅ ክፉ ነገርን የሚሻ፣ መንፈሱ ለተንኮል ብቻ የተፈጠረ ይመስል ተንኮልን የሚያውጠነጥን፣ ከፍቅር ይልቅ ጦርነትን የሚናፍቅ፣ የሌላውን ሰው ደስታ የማይሻ፣ በሰው ስቃይ የሚደሰት፣ ስለሆነም ሰውን በመጉዳት ወይም ተንኮል በመስራት የተሻለ ነገር የሚያገኝ የሚመስለው፣  በአጠቃላይ ሲታይ የአንድ አካባቢ ህዝብ በሰላምና በደስታ ቢኖር ደስ የማይለው ነው።  ከመሰሉ ጋርም በማበር ዘለዓለማዊ ጦርነት እንዲሰፍን የሚያደርግና የአንድ ሀገር ሀብትና የታሪክ ቅርስ እንዲወድም የሚያደርግ ነው። በመሆኑም በራሱ ስግብግብ ፍላጎት በመመራትና ከውጭ ኃይሎች ጋር በመተባበር አንድ ህዝብ ታሪክ እንዳይሰራ እንቅፋት የሚሆን ነው። እንደዚህ ዐይነቱ ሰው የማሰብ ሃይሉን በሚገባ የማይጠቀም፣ ሰው መሆኑን የዘነጋና ታሪካዊ  ኃለፊነትም እንዳለበት የሚገነዘብ አይደለም። አንድ ቦታ ላይ ቆሞ ድርጊቱን የሚያወጣና የሚያወርድ፣ እንዲሁም የሚያመዛዝን አይደለም። ባጭሩ መንፈሱ የተሰለበና የሚሰራውን የማያውቅ፣ እንዲሁም ለመኖር ብቻ የሚኖር የሚመስለው ነው።

ጭንቅላታችን አርቆ የማሰብ ኃይል ያለውን ያህል፣ ሌሎች የሰው ልጅ ባህርያት ሊገለጹና ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉት በማሰብ ኃይላችንና በቀሰምነው ዕውቀት አማካይነት ብቻ ነው። የመንፈስ ጥንካሬና በፕሪንስፕል መመራት፣ በቀላሉ ያለመታለልና ያለመደለል፣ ለምናምነው ዓላማ መቆምና እሱን በጥሞናና በውይይት ለማሳመን መሞክር፣ ለነፃነት መቆምና ለሌላው ላልተማረው ጠበቃ መሆንና ዕውነተኛውን የነፃነት ፈለግ እንዲከተል መንገዱን ማሳየት፣ የአንድን ህብረተሰብ ሁኔታና ችግር ከብዙ አኳያ ማየትና መገምገም፣ ከዚህም በመነሳት ለስልጣኔ መቆምና እስከመጨረሻው መታገል፣ እነዚህና ሌሎች ነገሮች ሁሉ በጭንቅላታችን ውስጥ የሚውጠነጠኑና የሚገነቡ ናቸው። ለምሳሌ ለምን በተለያዩ ሰዎች ዘንድ የተለያየ አስተሳሰብ ብቻ ሳይሆን፣ ከላይ የዘረዝርኳቸው ነገሮች ሊኖሩ ይችላሉ ብለን? ጥያቄ በምናስቀምጥበት ጊዜ የምናገኘው መልስ ባጭሩ አስተዳደጋችንና የገበየነው ዕውቀት ወሳኝ ሚናን እንደሚጫወቱ እንደሆነ መገንዘብ እንችላለን። በተለይም የአንድ ህብረተሰብ አወቃቀርና የታሪክ ሂደት እንዲሁም የባህል ሁኔታ ባህሪያችንን ይወስኑታል። ስለዚህም ነው ማንኛውም ግለሰብም ሆነ ድርጀት ከሞላ ጎደል የህብረተሰቡ ግልባጭ ወይም ኮፒ ነው የሚባለው።  ከዚህ ስንነሳ አንደኛው ቀጣፊና ውሸታም፣ አድሀሪና ወላዋይ፣ አጎብዳኝና ነገር አቀባይ፣ እራሱን ለሌላው ለመሸጥ የሚዘጋጅ፣ ሰላይና በራሱ ላይ ዕምነት የሌለው፣ እንደየሁኔታው ሃሳቡን የሚቀያየር፣ አለሁ አለሁ ባይነት የሚያጠቃው፣ ስግብግብነትና አገር ለመሸጥ መዘጋጀት፣ ለሀገር ነፃነት ጥብቅና ከመቆም ይልቅ የሌላውን አገር ጥቅም በማስቀደም አገር ማፈራረስ፣ ታሪክን በተጣመመ ሁኔታ ማቅረብና ሌላውን አሳስቶ አንድ ህዝብ ተስማምቶ እንዳይኖር ማድረግ፣ ጠባብ አስተሳሰብ እንዲስፋፋ በማድረግ ግለሰቦችም ሆነ የተለያዩ ዕምነት ተከታዮችም ሆነ ከዚህም ሆነ ከዚያ ብሄረሰብ የተወለዱ በጥላቻ መንፈስ በመጠመድ በመፈራራትና የጎሪጥ እየተያዩ እንዲኖሩ ማድረግ፣ ቀጥሎም ወደ ጦርነት እንዲያመሩ ማድረግ፣ ለውንብድና በመዘጋጀት አንድን አገር የጦር አውድማ በማድረግ ታሪክ እንዳይሰራ ማድረግ፣ እነዚህ ሁሉ በማሰብ ኃይል ድክመትና በተሳሰተ ዕውቀት ምክንያት የሚፈጠሩ ድርጊቶች ናቸው። በተጨማሪም በተንኮል ተጠምዶ ሌላውን ከሱ የላቀን ሰው ለማጥፋት የሆነ ያልሆነ ምክንያት መፈለግና ስም ማጥፋት የጭንቅላት አርቆ አለማሰብ ችግር ነው። በተሳሳተ ዕውቀት በመመራትና በዚህም ምክንያት ጭንቅላት በትክክል ለመገራት ያለመቻሉ የሚገለጽ ችግር ነው። በተጨማሪም ሌላው ደግሞ የአንድን ተንኮለኛ አነጋገር ሰምቶና አምኖ የሚያስተጋባና ለትግል እንቅፋት የሚሆን እንደዚሁ ጭንቅላቱ በደንብ ያልተገራ ወይም ደግሞ የቀጨጨ አስተሳሰብ ስላለው ነው።

ይህም ማለት ምን ማለት ነው? ለአንድ ህዝብ በሰላም መኖር፣ ራሱን መለወጥና ማደግ እንዲሁም ታሪክ መስራት መንፈስ፣ ጭንቅላትና አዕምሮ ከፍተኛ ሚናን የሚጫወቱ ብቻ ሳይሆኑ ወሳኞችም ናቸው። በሌላ ወገን ደግሞ አንድ ሰው የፈለገውን ያህል የተማርኩ ነኝ ቢልምና አስር ጊዜ ካለኔ በስተቀር ታጋይ የለም እያለ ቢምልና ቢገዘትም ጭንቅላቱ ውስጥ የተቀበረውን ወደ መጥፎ ነገርና ተንኮል እንዲያመራ የሚያደርገውን የተወላገደ ባህርይ ማስወገድ እስካልቻለ ድረስ በምንም ዐይነት ለህብረተሰብ ዕድገትና ለነፃነት አስተዋፅዖ ሊያበረክት አይችልም። በአገራችንም ሆነ በልዩ ልዩ አገሮች የደረሱትን ዕልቂቶች፣ የታሪክና የሀብት ውድመቶች፣ የህዝብ መበታተንና በሌላ አገር ባክኖ እንዲኖር ማድረግ፣ በአጠቃላይ ሲታይ ለዕድገት እንቅፋት መሆን ዋናው ምክንያት በትንሽ ዕውቀት እየታገዘ ስልጣን ለመውጣት እታገላለሁ በሚል አጉል ግብዘኛ ምክንያት የተነሳ ነው። በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ባልተማሩ ስዎች ወይም በደሀ ገበሬና ወዝ አደር ጦርነት የተቀሰቀሰበትና አገር የወደመበት ሁኔታ በፍጹም አልታየም፤ አልተመዘገበምም። እስከዛሬ ድረስ ብዙ አገሮች የወደሙትና በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብ እንዲያልቅ የተገደደው ተማርኩ ባሉ ጥቂት ኤሊቶች አማካይነት ነው። የሰውን ልጅ ለመግደልና ለማሰቃየት ተብለው የሚሰሩት የተወሳሰቡ መሳሪያዎች በተማሩ ሰዎች አማካይነት ነው። ትዕዛዝ የሚሰጡትም እንዲሁ በህዝብ ተመርጠናል፣ ውክልናን አግኝተናል ብለው በሚዘባነኑ ፖለቲከኞች አማካይነት ነው።  ዛሬ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለውን ውዝግብ፣ በሃይማኖት አሳቦ ዕልቂት ማስከተል፣ የብዙ ሺህ ዐመታትን ታሪክና ባህል ማውደምና፣ የብዙ ሺህ ስዎችን ህይወት መቅሰፍ ስንመለከት የምንደርስበት መደምደሚያ ይህ ሁሉ አሰቃቂ ግፍ የሚፈጸመው በሀብት በናጠጡና በስልጣን ጥም በሰከሩ ኤሊት ነን በሚሉት አማካይነት ነው። ወይም ደግሞ አንድን መመሪያና ዕውቀት የሚሉትን ራሳቸው በፈለጉት መልክ ስለሚተረጉሙት ብቻ ነው።  የዩሁዲው ማርክሲስትና ምሁር አዶርኖ እንደሚለው ለዚህ ዋናው ምክንያት ገለብ ገለብ ያለ ዕውቀት ነው። በሱ ዕምነት የታሪክን ሂደትና አመጣጥ፣ የአንድን ህብረተሰብ አወቃቀር ውጣ ውረድነት ያለው መሆኑን ያልተገነዘበ ኤሊት በስሜት ብቻ እየተነዳ የሚያካሂደው ፖለቲካ የሚሉት ፈሊጥ የግዴታ ለታሪክ መበላሸት፣ ለህዝቦች ዕልቂትና ለአገር መፈራረስ ዋናው ምክንያት ይሆናል። ሂትለር በስድስት ሚሊዮን ህዝቦች ላይ ያደረገው ዕልቂትና የሌሎችንም አገሮች በመውረር ወደ ሃምሳ ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብ እንዲሞትና አገሮችም እንዲፈራርሱ የተደረገው ይሁዲዎች ለጀርመን ስልጣኔ ያደረጉትን አስተዋፅዖ ለመገንዘብ ባለመቻሉና፣ ወደ ኋላ መለስ ብሎ የታሪክን ሂደት ለማጥናት ባለመቻሉ ብቻ ነው። በዘረኝነት ቲዎሪ በመመራቱና የጀርመንም ህዝብ ከሁሉም ዘር በላይ ይበልጣል ብሎ በማመኑ ነው። ይህም የሚያረጋግጠው፣ የተቆራረሰ ዕውቀት ጭንቅላትን እንደሚጋርድና፣ ሌላውን በመናቅና በማንቋሸሽ ለብዙ ሚሊዮን ህዝቦች መሞትና፣ ለባህልና ለታሪክ መፈራረስ ምክንያት እንደሚሆን ነው። የአገራችንንም የአብዮት ታሪክና የደረሰውን ዕልቂት ስንመረምር ለችግሩ መንስኤ የሆኑ ሰዎች ተማርን የሚሉ ሲሆኑ፣  የታሪክን ውጣ ውረደነት ያልተገነዘቡ፣ በየታሪክ ደረጃዎች ላይ የነበረውን ንቃተ-ህሊና ያላገናዘቡ፣  አንድ ህብረተሰብም ሆነ አገር ለመረጋጋርትና ታሪክን ለመስራትና እንዲሰራበትም ለማድረግ አንድ ህዝብና አገዛዝ ህብረተሰብአዊ መመሰቃቀሎችንና ውህደቶችን ማለፈና ራሳቸውን ለመገንዘብ በብዙ መቶ ዐመታት የሚቆጠር ዕድሜ እንደሚያስፈልግ ባለመረዳታቸው ነው። ፍሪድሪሽ ሽለር የተባለው ታላቅ የድራማ፣ የፍልስፍናና የሳይንስ ምሁር እንደሚያስተምረን፣ የሰው ልጅ ራሱን በራሱ እስኪያገኝ ድረስ ብዙ ውጣ ውረዶችን ማለፍ እንዳለበት ነው። በእሱም ዕምነት የሰው ልጅ አርቆ የማሰብ ኃይሉን ማዳበር ከፈለገ የግዴታ መንፈሱ ከልጅነቱ ጀምሮ በጥሩ ዕውቀትና ጥበብ መኮትኮት አለበት። ጥበባዊ ጭንቅላትን የመኮትኮቻ ትምህርት( The aesthetic education of the human mind) በሚለው መጽሀፉ ውስጥ የሚያመለክተውና የሚያረጋግጠው ይህንን ነው። የሰው ልጅ ጭንቅላት ከልጅነቱ ጀምሮ በጥሩ እውቀት እስካልተኮተኮተ ድረስ ሰብአዊ ባህይ ሊኖረው አይችልም። ቆንጆና የተረጋጋ ማሀበረሰብም ሊገነባ አይችልም። ሜንደልሰን የሚባለውና የጀርመኑ ሶክራተስ እየተባለ የሚጠራው ይሁዳዊው ምሁርም የሚያረጋግጠውም ይህንን ነው። ጭንቅላቱ በሚገባ ያልተኮተኮተና ያልዳበረ እንደ አውሬ እንደሚሆንና፣ ለሌላው እሱን ለሚመስለው ሰው ምንም ዐይነት ርህራሄ እንደማይኖረው ነው። ኢማኑኤል ካንትም በተለይም በሰው አዕምሮ ላይ ከፍተኛ እትኩሮ በመስጠት የሰው ልጅ በአጠቃላይ ሲታይ ወደ ውስጥ ራሱን መመልከት እንዳለበትና ድርጊቱን ሁሉ መቆጣጠር እንዳለበት ያስተምራል። አዌርነስ(Awarness)  በሚለው ሀተታው የሰው ልጅ የግዴታ ለድርጊቱ ሁሉ ተገቢውን ግንዛቤ ማድረግ እንዳለበት ያስተምራል። በመሆኑም የሰውን ልጅ የጭካኔ ባህርይ የተረዱት የአስራ ስምንተኛውና የአስራዘጠነኛው ክፍለ-ዘመን የጀርመን ምሁራን ምርምር ያደርጉ የነበረውና አጥብቀውም ያነሱ የነበረው የሰውን ባህርይ በመኮትኮት ጤናማ አስተሳሰብ እንዲኖረው ማድረግ ነበር። ጠቅላላው የጀርመን ፈላስፋዎች ምርምርም በዚህ ዙሪያ ያተኮረ ሲሆን፣ አንድ ህዝብ ታሪክን ሊሰራ የሚችለው በየጊዜው ራሱን መጠየቅና ጭንቅላቱን መኮትኮት የቻለ እንደሆን ብቻ ነው። የሚያስገርምውና የሚያሳዝነውም በብዙ መቶ የሚቆጠሩ ፈላሳፋዎችና ምሁራን ብቅ ባሉበትና ሳይታክቱ ባስተማሩበት፣ እንዲሁም ትምህርታቸውን ተግባራዊ ባደረጉበት አገር ሂትለርና ፋሺዝም መነሳታቸውና ለብዙ ሚሊዮን ህዝብ መሞት ምክንያት መሆናቸው ነው።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የወያኔ ጥላቻ ፍሬ (ፕ/ር መስፍን ወልደ ማርያም)

ወደ አገራችን ስንመጣም ያለው ችግር ለመንፈስና ለአዕምሮ መዳበር አትኩሮ ያለመስጠትና፣ የመንፈስ መበላሸትም ሆነ በጥሩ ዕውቀት መኮትኮት ያለውን አሉታዊና አዎንታዊ ሚና ያለመገንዘቡ ነው ። ለአንድ አገር ዕድገት፣ አንድ ህዝብ ኋላ ቀር ከሆኑ አመለካከቶች ተላቆ በመተባበር አገር እንዲገነባ ከተፈለገ ትክክለኛ ዕውቀት አስፈላጊና በዚህ ላይ መረባረቡ የሁሉም ነገር ቁልፍ መሆነን ግናዛቤ ያለመደረጉ ነው። በመሆኑም በተለይም ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ የገባው ይህንንም ያህል ለጭንቅላት መዳበር፣ ለአርቆ አሳቢነትና ለፈጠራ ስራ የማያመቸው ትምህርት ህብረተሰብአዊ መዘበራረቅን እንዳስከተለና አቅጣጫ እንዳሳጣን ምርምር ያለመደረጉ በጣም የሚያሳዝንም የሚያስገርምም ነው። ይህ ዐይነቱ ቸልተኝነትና ንቀት ደግሞ የግዴታ በየኤፖኩ የተነሱትን ሁኔታዎች እንደፈለግን ልንተረጉማቸው ተገደናል። ለምሳሌ አብዛኛው ተንታኝ በአብዮቱ ወቅት የተፈጠረውን ትርምስና እጅግ ለጭንቅላት የሚዘገንን ድርጊት ለማያያዝ የሞከረው ዝም ብሎ በደፈናው ከማርክሲዝም ጋር ነው። ፊዩዳሊዝምና እጅግ ተበጣጥሶ የገባው የካፒታሊዝም የፍጆታ አጠቃቀምና አመራረት በህሊና አወቃቀራችንና በመፈሳችን መበላሸት ላይ ያለውን አሉታዊ ተፅዕኖ የተገነዘበ ያለ አይመስለኝም። ስለዚህም አብዛኛው ሰው ወይም ምሁር ነኝ ባይ  በአብዮቱ ጊዜ የደረሰውን ዕልቂትና መተራረድ የተገነዘበው ከውጭ ከመጣው የማርክሲስት-ሌኒንስት ረዕዮተ-ዓለም ጋር በማያያዝ ነው። ለምሳሌ የኢትዮጵያ የጦር ኃይል እንዳለ የሰለጠነው በአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም የጦር ሳይንስ በሚሉት ነው። መሳሪያዎቹም የመጡት ከዚያ ነው። ፖሊሱ ደግሞ በጀርመን ፖሊሶች የሰልጠነ ሲሆን፣ የማሰቃያ መሳሪያዎችም በሙሉ ከዚያ የመጡ ነበሩ። በሌላ አነጋገር የኢትዮጵያ የጦር ኃይልና ፖሊስ በኢምፔሪያሊዝም የጭቆናና የማሰቃያ እንዲሁም ሰውን የመግደያ ስልት ነው የሰለጠነው። ስለሆነም በአብዮት ጊዜ የተካሄድው መተላለቅ ከማርክሲዝምና ከሶሻሊዝም ጋር ምንም የሚያገናኘው ነገር የለም። ማርክሲዝምና ሶሻሊዝም የብዙ መቶ ዐመታትን የደነደነ አስተሳሰብና መንፈስ በተወሰነ ጊዜ ውስጥ የመቀየር ኃይል የላቸውም። የሰው ልጅ የማሰብ ሃይል በክንውንና በሂደት ውስጥ የሚቀረጽ ነው። በተለይም ፍሪድሪሽ ሄግል ይህንን ነው የሚያስተምረን።

ከዚህ ስንነሳ በአጠቃላይ ሲታይ የብዙ የሶስተኛውን ዓለም አገሮች የተዘበራረቀ ሁኔታና የየመንግስታቱን የመጨቆና መሳሪያና አለመደላደልን ስንመለክት ከአገራችን ሁኔታ ጋር ተመሳሳይነት አላቸው። የሚለዩት ግን አብዛኛዎቹ አገሮች እንደኛው በፊይዳል ስርዓት ውስጥ አለማለፈቸው ብቻ ነው። ያም ሆነ ይህ፣ የአንድን ህብረተሰብ ዕድገት ሁለንታዊ ከሆነ ሁኔታ ያላጤኑ መንግስታትና ሁለ-ገብ ዕርምጃ ለመውሰድ ያልሞከሩ አገሮች አንዳች ነገር በሚፈጠርበት ጊዜ ወደ መረጋጋት ከመምጣት ይልቅ ወደ ውዝግብናና መተረማመስ ያመራሉ። በአገራችን በአብዮቱ ዘመን የተያው የመንፈስ መረበሽና ለጭንቅላት የዘገነነ ድርጊት ዋናው መነሾው ጭንቅላትን ለማደስና መንፈስን ለማረጋጋት የሚያስችል ዕውቀት ባለመስፋፋቱ ብቻ ነው ። ዛሬም ያለው ችግርና የህዝብ መፈናቀልና የመንግስትም ቸልተኝነት ዋናው ምክንያት ሰው  መሆናቸንን የሚያረጋግጥልንና ታሪክ ሰሪ መሆናችንን የሚያስጨብጠን ዕውቀት ከጭንቅላታችን ጋር እንዲዋሃድ ባለመደረጉ ነው። ስለሆነም አብዮቱ ከመተባበር ይልቅ ቡድናዊ ስሜትን አጠናከረ። ወደ ጤናማ ፉክክር ሳይሆን ወደ ጦርነት የሚያመራና ደም መፋሰስን ወደሚያስከትል አጉል እልከኝነት ውስጥ ከተተን። ሁሉም በየፊናው በመራወጥ አሸናፊ ሆኖ ለመውጣት ዝግጅት ማድረግ ጀመረ። ሁሉም በየፊናው በቀላሉ ድልን የሚቀዳጅና ስልጣን የሚጨብጥ መስሎ ታየው። ብሄረሰቤን ነፃ አውጣለሁ ብሎ የሚታገለው ደግሞ አገሪቱን ወደ ጦር አውድማነት ለወጣት። አብዛኛው ታጋይ ነኝ ባይና ቢሮክራሲው ሁሉ ሳይቀሩ የኢትዮጵያ ጣላቶች ሆኑ። የስልጣኔና የዕድገት ጠንቅ በመሆን ውስብስብ ሁኔታዎችን ፈጠሩ። በመሰረቱ እነዚህ ሁሉ ኃይሎች ትንሽም ቢሆን ፊደል የቆጠሩና የተማሩም ነበሩ። የተማሩት ትምህርት ግን የማሰብ ኃይላቸውን እንዲጠቀሙ አላገዛቸውም። የመንፈስን የበላይነት በማስቀደም የወንድማማች ደም እንዳይፈስ ጥረት እንዲያደርጉ አላስቻላቸውም። በተንኮልና አገርን በማፈራረስ፣ እንዲሁም ሳይቀድመኝ ልቅደመው በሚል ፈሊጥ በብዙ መቶ ሺህ የሚቆጠሩ ለጋ ወጣቶች ህይወታቸውን እንዲያጡ ሁኔታውን አመቻቹ።

 

ያም ሆነ ይህ በአጠቃላይ ሲታይ የሰው ልጅ ጭንቅላትም ሆነ መንፈስ አንድ ዐይነት ቅርጽ ነው ያላቸው። ይህም ማለት በየትኛውም አገር የተወለደና ያደገ ሰው ሁሉ ሁሉንም የስው ልጅ ባህርዮች ይኖሩታል። ከላይ እንዳልኩት የየግለሰቡ ባህርይና ድርጊት ሊቀረጽና ሊወሰን የሚችለው በአስተዳደጉ፣ በአካባቢው ሁኔታና በአጠቃላይ ሲታይ ደግሞ በጠቅላላው የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊና የባህል ዕድገት ሁኔታ ነው።  ይሁንና ግን አንዳንድ ሰው ሲወለድ ከመጀመሪያውኑ ተቀድሶ የሚወለድና ጭንቅላቱ ወደ ተንኮልና ወደ መጥፎ ነገር የማያመራ አለ። ይህ ባይሆን ኖሮ እንደ ሶክራተስና ፕላቶንን፣ እንዲሁም ታላላቅ የሳይንስና የፍልስፍና ስዎች የመሳሰሉት ብቅ ባላሉ ነበር። እንደዚህ ዐይነት ሰዎች ደግሞ  ወደ እግዚአብሔርም የሚጠጉ ናቸው። ለጥሩ ነገር እንጂ ለመጥፎ ነገር ያልተፈጠሩ፤ ጠቅላላው አስተሳሰባቸው የሰውን ልጅ ታሪክ ሰሪነት ማስታወስና ማስተማር ተልዕኮዋቸው የሆነ ልዩ ዐይነት ፍጡሮች ናቸው። በመሆኑም እንደነዚህ ዐይነት ስዎች ባይፈጠሩ ኖር የሳይንስና የቴክኖሎጂ ባለቤት መሆን ባልቻልን ነበር። ኑሮአችን ሁሉ የጨለመና እየተንከራተትን እንደ እንስሳ የምንኖር ነበርን።  ተግባራችን ሁሉ ጦርነትና መተላለቅ ብቻ በሆነ ነበር።  የዓለምና የሰው ልጅ አስደናቂውና በቅራኒዎች መወጠር የሚያስገርመው  ነገር  እዚህ ላይ ነው። በአንድ በኩል ለቅዱስ ስራ የተፈጠሩና የተካኑ፣ በሌላ ወገን ደግሞ ለተንኮልና ለጥፋት እዚያው በዚያው መኖራቸው የሰው ልጅና የተፈጥሮ ግዴታ ናቸው ማለት ይቻላል። ጨለማና ብርሃን፣ የሚያቃጥልና ቀዝቃዛ ነገሮች እንዳሉ ሁሉ፣ የሰው ልጅ ባህርይም በአጥፊዎችና በተንኮለኞች በአንድ በኩል፣ በሌላ ወገን ደግሞ በፈጣሪዎችና ለተቀደሰ ዓላማ በቆሙ ሰዎች የሚገለጽ ነው።

ከዚህ ስንነሳ የጭንቅላትን ሚና፣ ታሪክ ሰሪነትና አጥፊነትን መረዳቱ የሚታለፍ ነገር አይደለም። እንደገና የፕላቶንን ቁም አባባል ለማስታወስ፣ የሰው ልጅ ችግር አርቆ አለማሰብና በትክክለኛ ዕውቀት አለመኮትኮት ነው። ለመጥፎ ድርጊትና ለችግር መፈጠር እንዲሁም ለጥሩ ስራ ዋናው ተጠያቂው የሰው ልጅ እራሱ እንጂ ከላይ ሆኖ የሚቆጣጠር ኃይል ወይም ደግሞ አንዳች ዐይነት ርዕዮተ-ዓለም በመከተሉ አይደለም። እንደየ አስተዳደጋችን እኛው እራሳችን የአስተሳሰባችንና የድርጊታችን ተጠያቂዎች ነን። ሌላ ሰው የሚያሳስተን ከሆንና የሱን አስተሳሰብ ተከትለን ወደ መጥፎ ነገር የምናመራ ከሆነ ጭንቅላታችን በጥሩ ዕውቀት አልተኮተኮተም ማለት ነው። የማመዛዘንና ጥያቄን የመጠየቅ ልምድ አላካበትንም፤ ከጭንቅላታችንም ጋር አልተዋሃደም ማለት ነው። ዝም ብለን የምንመራ፣ ሌላው ሲጮህ የእሱን የምናስተጋባ ከሆነ ጭንቅላታችን ዕውነተኛ ነፃነትን አልትጎናጸፈም ማለት ነው። ዕውነተኛ ግለሰባዊነትና በራስ ላይ መተማመንን አላዳበርንም ማለት ነው። በጭፍን የምንመራ እንጂ በራሳቸን የማሰብ ኃይል የምንመራ አይደለንም ማለት ነው። እንደዚህ ዐይነት ሰዎች ደግሞ ማንኛውንም መጥፎ ነገር ከመስራት አይቆጠቡም።

ሁለ-ገብ የመንፈስ ተሃድሶ ዘዴ የሰላምና የዕድገት ዋናው ቁልፍ ነው !!

በታሪክ ውስጥ ስልጣኔንና ዕድገት የተካሄደባቸውንና የሰውም ልጅም ዕውነተኛ ግለሰባዊ ነፃነትን የተቀዳጀበትን ሁኔታና ታሪክን ስንመለከት የመንፈስ ተሀድሶ መሰራታዊ የሆነና፣ ከፍተኛውን ሚናም እንደሚጫወት እንገነዘባለን። በታሪክ ውስጥ የመጀመሪያው ሁለ-ገብ የመንፈስ ተሃድሶ ተግባራዊ የሆነው ከክርስቶስ ልደት በፊት በአምስተኛው ክፍለ-ዘመን ሲሆን፣ ይህንንም ተግባራዊ ያደረገው ሶሎን የሚባለው ታላቅ ፈላስፋና የአገር መሪ ነበር። ለሶሎን መነሳትና የተቀደሰ ድርጊት ደግሞ ቀደም ብለው የተካሂዱት በተፈጥሮ ፈላስፋዎች የተደረጉት ምርምሮችና የሆሜር ድርሰት ትልቅ አስተዋፅዖ አበርክተዋል ማለት ይቻላል። በጊዜው የነበረውን የእርስ በእርስ ጦርነትና የገዢ መደቦችን ቅጥ ያጣ ብዝበዛና ግፍ የተመለከተው ከመሳፍንት ዘር የተወለደው ሶሎን በጊዜው የነበረውን አስቀያሚ ሁኔታ ያያዘው ከመንፈስ ወይም ከአዕምሮ መበላሸት ወይም በጥሩ ዕውቀት ካለመታነፅ ጋር ነው። ስለሆነም ስልጣን ሲጨብጥ በአካባቢው ያሉትን በማሳመን ሁለ-ገብ ጥገናዊ ለውጥ በማካሄድ በታሪክ ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ ልዩ ዐይነት በሳይንስ፣ በማቲማቲክስ፣ በፍልስፍና፣ በድራማና በአርክቴክቸር የሚገለጽ የዕውቀት መሰረት ይጥላል።  ለሶክራተስ፣ ለፕላቶን፣ ለአርቺሜዲስና ለአርስቲቶለስና እንዲሁም መጠናቸው ለማይታውቅ ፈላስፋዎቻና የሳይንስ ሰዎች መነሳት ዋናው ምክንያት ይሆናል። ታላቁ አሌክሳንደር ሲነሳ ይህንን መሰረት በማድረግ ስልጣኔውን ማስፋፋት ይጀምራል። በሱ ስም በሚጠራውም የግብጽ ከተማ የመጀመሪያውን መጽሀፍ ቤት ይከፍታል። አስተሳሰቡ ከዚያ በመነሳት በአካባቢውና በዓለም አቀፍ ደረጃ ሳይንስና ጥበብን ማስፋፋት ነበር። ይህ ህልሙ ግን በሮማውያን ወራሪዎች ድምጥማጡ ይጠፋል። ከሰባት መቶ ሺህ በላይ የሚጠጉ መጻህፍቶችም ይቃጠላሉ። የግሪኩና የግብጹ ስልጣኔ መውደም በአውሮፓ ውስጥ የጨለማው ዘመን እየተባለ ለሚጠራው መነሺያ ሲሆን፣ ይህ በራሱ በምዕራብ አውሮፓ ምድር ከሀይማኖት ጋር የተጣመረ ፊዩዳላዊ የጨለማ አገዛዝ እንዲስፋፋ ያደርጋል። የአውሮፓ ህዝብ ዕጣ በሽታ፣ ረሃብና ጦርነነት ይሆናል። የሰፊውን ህዝብ አስተሳሰብ በጭፍን ዕምነት እንዲጋረድ ያደረጉት የካቶሊክ ሃይማኖት መሪዎች የአውሮፓ ህዝብ ታሪክ እንዳይሰራና ዕውነተኛ ነፃነቱን እንዳይቀዳጅ ያደርጉታል። ይህ ሁኔታ ግን ቀስ በቀስ የሚለወጥበት ሁኔታ ይፈጠራል። ዳንቴ የደረሰው የአምላኮች ኮሜዲ ለጭንቅላት ተሃድሶ በሩን ይከፍታል። የሰው ልጅ ከጨለማው ዓለም በመላቀቅ እንዴት አድርጎ ብርሃንን እንደሚጎናጸፍ ዳንቴ በግሩም ድርስቱ ውስጥ ያመለክታል። የዳንቴ ድርሰት ለሬናሳንስ መነሳት መሰረቱን ይጥላል። የእሱን ድርሰት ያነበቡት መልዕክቱን በመረዳት ለአዲስና ለታሪካዊ ስራ ይነሳሳሉ።

በአረቦችና በይሁዲዎች አማካይነት ወደ ምዕራብ አውሮፓ የገባው የግሪኩ ዕውቀት ወደ ላቲን በመተርጎምና የነበረውን ጨለማዊ አገዛዝ በመጋፈጥ በአውሮፓ ምድር ውስጥ፣ በተለይም በጣሊያን ሪናሳንስ የሚባለው ዕውቀትን መልሶ የማግኘት ዘዴ ይስፋፋል። ዛሬ ኢስታንቡል ተብላ ከምትታወቀው በድሮ ስሟ ኮኒስታንቲኖፕል ተብላ ከምትጠራው ከተማ ፈልሰው የመጡ ቀሳውስት የፕላቶንን ሃሳብ በማስፋፋት አዲስ የስልጣኔ ፈለግ ይቀዳሉ።  የንግደና የዕድ-ጥበብ መስፋፋት አዳዲስ ኃይሎችን ሲያፈልቅ፣ የድሮው ጨለማዊ አገዛዝ በድሮ መልኩ የማይቀጥልበት ሁኔታ ይፈጠራል። እነ ኬፕለርና ጋሊሊዮ እንዲሁም ብሩኖ ጋርዲያኖ የመሳሰሉት ጠለቅ ያለ ዕውቀት ያላቸው ምሁራን ያፈለቀትና ያዳበሩት አዲስ ዕውቀት የካቶሊክ ሃማኖት መሪዎችን ጭፍን ትምህርት በመቀናቀን መፈናፈኛ ያሳጣዋል። የእነ ዳቪንቺና  ሚካኤል አንጀሎ ልዩ ሰዕላዊና የአርክቴክቸር ስራዎች ለአወሮፓው ስልጣኔ መነሻ ይሆናሉ። ይሁንና ግን ፊዩዳላዊው ስርዓትና የሃይማኖት ዕምነት ሙሉ በሙሉ ተዳክምው ህዝቡ ግለሰባዊ ነፃነት እስኪቀዳጅ ድረስ ረጅም መንገድ መጓዝ ነበረበት። ለብዙ መቶ ዐመታት የተንስራፋውን አስተሳሰብና የኃይል አሰላለፍ ለማሸነፍ ቀላል አልነበረም። ስለሆነም ሪፎርሜሽን ተብሎ የሚጠራው የካቶሊክን ሃይማኖት የሚቀናቀን ሃይማኖት በማርቲን ሉተርና በተከታዮቹ አማካይነት በመዳበርና በመስፋፋት የካቶሊክን ጭፍን አመለካከት ይጋፈጣል። ይህ እንቅስቃሴ ግለሰብአዊ ስነ-ምግባርን በማዳበር ለካፒታሊዝም ዕድገት ልዩ ዕምርታን ይሰጣል። ይህ አዲሱ ሃይማኖት በተስፋፋባቸው ቦታዎች ሳይንስ፣ ጥበብና ንግድ በመዳበር ለከበርቴው መደብ መነሳት ምክንያት ይሆናል።

ከአስራሰባተኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ የሊበራል አስተሳሰብ ሲስፋፋ ዋና ዓላማውም ኋላ-ቀር አስተሳሰቦችን በማስወገድና በመደምሰስ የሪፓብሊካንን አስተሳሰብና አገዛዝ መትከል ነበር። አንድ ወጥ የሆነውን ዲስፖቲያዊ አመራርና አመለካከት በመጋፈጥ ለሲቪል እንቅስቃሴ በሩን በመክፈት ሳይንስና ጥበብ ዋናው መመሪያ ይሆናሉ። ኢንላይተንሜንት እየተባለ የሚታወቀው ምሁራዊ እንቅስቃሴም ዋናው ትርጉሙና ዓላማው በጭንቅላት ውስጥ ብርሃን ተፈናጥቆ የሰው ልጅ ታሪክን እንዲሰራ ማድረግ ነው። ስለሆነም ኢንላይተንሜንት የሚባለው እንቅስቃሴ የአሪስቶክራሲውንና የፊዩዳሉን አገዛዝና አስተሳሰብ በመደምሰስ የሲቪል ነፃነት ወይም ሊበሪቲን ማወጅ ነበር። ዋናው ዓላማው ይህ ቢሆንም፣ የሊበራል እንቅስቃሴ መሰረታዊውን የፕላቶንና የሶክራተስን  አስተሳሰብ፣ ማለትም ዕውቀት ከጭንቅላት ውስጥ ነው የሚፈልቀው የሚለውን የሚቃውምና ክስተታዊ አመለካከትንና ከዚህም በመነሳት ሁኔታዎችን ማንበብ የዕውቀት መነሻ ዋናው ምክንያት ነው ብሎ የተቀበለና የሚሰብክ ነው።  ይሁንና ከውጭ ወደ ውስጥ የገባው ክስተታዊ አስተሳሰብ በጭንቅላት ውስጥ መብላላትና ወደ ተግባርም መመንዘር እንዳለበት ለኢንላይተንሜንት እንቅስቃሴ ምሁሮች ግልጽ  ነበር።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የታፈነዉ ጠጣር እዉነት ...1 ለህዝቦች አብሮነት! - ታዬ ደንድአ

ይህ ሁሉ የሚያረጋግጠው በታሪክ ውስጥ የጭንቅላት ተሃድሶ ባልተካሄደባቸው አገሮች ውስጥ ታሪክን መስራትና ከውስጥ ደግሞ የተረጋጋ ህብረተሰብ መገንባት እንዳማይቻል ነው። በማንኛውም መልክ የሚገለጽ ጭቆና ዋናው ምክንያትም ጭንቅላት በአዲስ ዕውቀት መታደስ አለመቻሉ ነው። ከአንድ ህብረተሰብ-ውስጥም ጭቆናን ማስወገድ የሚቻለው አንዱ ሃይል ተወግዶ በሌላ ስለተተካ ሳይሆን፣ ጭንቅላትን የሚያድስ ምሁራዊ  እንቅስቃሴና አዱስ ዕውቀት ሲዳብርና ሲስፋፋ ብቻ ነው። በሌሎች አገሮችም ሆነ በአገራችን እንዳየነውና መገንዘብ እንደቻልነው አንድ ጨቋኝማ ፀረ-ዕድገት አገዛዝ ስለተወገደ ብቻ የግዴታ ህብረተሰብአዊ ለውጥ ይመጣል፤  የፈጠራ ስራ ይዳብራል፣ ቴክኖሎጂና ሳይንስ ይስፋፋሉ፣ እንዲያም ሲል ሁለ-ገብ የሆነ ማህበረሰባዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ይመጣል ማለት አይደለም። ባጭሩ የድሮ አገዛዝ ከተባረረና አዲስ ኃይል ስልጣን ከያዘ ጭንቅላትን የሚያድስ ሁሉ-ገብ ዕውቀት እስካልተስፋፋ ድረስ አንድ ህዝብ ነፃነቱን በምንም ዐይነት እንደማይጎናፀፍ  የብዙ አገሮችና የአገራችንም ታሪክ ያረጋግጣል። አንድ አገርም ብሄራዊ ነፃነቷን በማስከበር ህዝቡ ተዝናንቶና ነፃነቱን ተጎናጽፎ ሊኖርባት የሚችል አገር መመስረት አይቻልም። የአንድን ህዝብ ነፃነት፣ ታሪክን መስራት መቻልና አለመቻል፣ ከዚህ አጠቃላይና ሁለ-ገብ ሁኔታ ተነስቶ መመርመር የሚያስፈልግ ይመስለኛል።  በዛሬው ወቅት በአገራችን ምድር የተከሰተውን አስቸጋሪ ሁኔታና የአገዛዙንም መደናበርና ወደ ሌላ የጭቆና አገዛዝ ማምራት ከላይ ከተተነተነው ሁኔታ መመልከቱ አስፈላጊ ይመስለኛል። የአገራችን የተወሳሰበ ሁኔታና የህዝብ መፈናቀልና የፅንፈኝነት መስፋፋት በመደመርና በፍቅር ያሸንፋል መፈክር ብቻ እንደማይፈታ የአንድ ዐመቱ የአዲሱ አገዛዝ ሁኔታ ያረጋግጣል።  የለውጥ ኃይል እየተባለ የሚወደሰው አገዛዝ በእርግጥም የለውጥ ኃይል እንዳይደለ እያረጋገጠልን ነው። ከድሮው የወረሰውን የጭቆና መሳሪያ በማንቀሳቀስ ለማያልቅ ጦርነትና ለህዝቦች የእርስ በእርስ መተላለቅ ሁኔታውን የሚያመቻች ይመስላል።

              አስቸጋሪው ጉዳይ ! የአገራችንን ሁኔታና፣ የአገዛዙን መንፈስና ተልዕኮ መረዳት  !!

በሁላችንም ዘንድ አንድ የተለመደ አነጋገርና የምንዝናናበት ነገር አለ። ይኸውም ኢትዮጵያ የጥንት ታሪክ ያላትና የስልጣኔ አገርም እንደሆነች ነው። የሰውም ልጅ ዘርም ከዚያ የፈለቀ መሆኑ ሁላችንንም ያኮራናል። ይህ ትክክል የሆነውን ያህል፣ እስከዚህም ድረስ የሚያዝናናን አይደለም። የተፈጥሮ ሳይንስ ተመራማሪና ከኒውተን በተጨማሪ የካልኩለስ አፍላቂ የሆነው ጀርመናዊው ላይብኒዝ እንደሚያሰተምረን ማንኛውም አዲስ ትውልድ በድሮ ዝና መደሰትና መዝናናት ያለበት ሳይሆን ዛሬ የሚታየውን ችግር በመረዳት ለመፍታት ታጥቆ መነሳት እንዳለበትና ለሚቀጥለውም ትውልድ የስልጣኔ መሰረት ጥሎ ማለፍ እንዳለበት ያሳስብል። ተከታታዩ ትውልድ መነሻ የሚሆነው የስልጣኔ መሰረት እስከሌለው ድረስ የግዴታ ህብረተሰብአዊ ትርምስ መፈጠሩ የማይቀር ግዴታ እንደሆነም ማረጋገጥ ይቻላል።

ስለሆነም እኛም በጥንቱ ታሪካችን ይህንን ያህልም የሚያዝናናን ነገር የለም።  የጥንት አባቶቻችንና እናቶቻችን ብቻ ሳይሆኑ በታሪክ ውስጥ የተለያዩ አገሮች ስልጣኔን በመስራት ለምዕራብ አውሮፓ ስልጣኔና ለካፒታሊዝም ዕድገት መሰረት ጥለው አልፈዋል። በተለያዩ ምክንያቶች የተነሳም በስልጣኔያቸው ሊገፉበት አልቻሉም። የግብጽ ስልጣኔ፣ የባቢሎን፣ የኢራክና የሶርያ ስልጣኔዎች ከፍተኛ ደረጃ የደረሱበት ሁኔታ እንደነበር ይታወቃል። በታሪክም የተረጋገጠ ነው። ይሁንና ግን ሁኔታው ስላልፈቀደ ወይም የበሰለ ሳላልነበር በነዚህ አገሮች ውስጥ የካፒታሊዝም ስርዓት ብቅ ሊል አልቻለም። የእነዚህ ስልጣኔዎች ተጠቃሚ የሆነው ምዕራብ አውሮፓ ነው። ከላይ ለማሳየት እንደሞከርኩት፣ የተለያዩ አጋጣሚዎች በመገጣጠም በአውሮፓ ምድር ውስጥ በተለያየ ጊዜና ቦታ ካፒታሊዝም ብቅ ሊልና ሲስፋፋ፣ ዛሬ ደግሞ ዓለምን ሊቆጣጠር ችሏል። እዚህ ላይ ግን መቋጠር ያለበት ነገር፣ 1ኛ፟) ካፒታሊዝም ተፈልጎና ታቅዶ የመጣ ስርዓት ሳይሆን ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ በአሽናፊነት የወጣ ስርዓት ነው። 2ኛ) ካፒታሊዝም በራሱ ችግር ፈቺ ስርዓት ሳይሆን፣ በትግል አማካይነት እንደሁኔታው የኃይል አሰላለፍ ሲቀየርና የጭንቅላት ብስለት ሲዳብር ለግለሰባዊ ድርጊት በሩን የከፈተ ነው። በዚህም ምክንያት ስርዓቱ በውስጡ ባለው ውስጠ-ኃይል የተነሳ ለሚከሰቱ ችግሮች መፍትሄ ለመስጠት ያስቻለ ነው። የቴክኖሎጂ ዕድገትና ለብዙ ችግሮች መሰረታዊ መፍትሄ መሆን ከካፒታሊዝም ውስጠ-ኃይል ጋር የሚያያዝ ነው። ስለዚህም ካፒታሊዝም በአንድ አካባቢ ብቅ ያለ፣ ያደገና የተስፋፋ ሲሆን ሁሉም አገሮች በዚህ ውስጥ ማለፍ አለባቸው ወይም ስርዓቱን እንዳለ መቅዳት አለባቸው የሚል በተፈጥሮ የተደነገገ ህግ የለም፤ አይቻልምም። ይሁንና ግን ለፈጠራና ለዕድገት ያመቻሉ፣ አስፈላጊም ናቸው የምንላቸውን ነገሮች መኮረጅና ከአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ጋር በማጣመር ችግር ፈቺ እንዲሆን ለማድረግ መሞከር የማይታለፍ ጉዳይ ነው።  ከዚህ ስንነሳና ወደኛ አገር ስንመጣ ታሪክን ለመስራትና አዲስ ህበረተሰብን ለመገንባት ያልቻልንበትን ምክንያት በመጠኑም ቢሆን ማየት ያፈልጋል። እዚህ ላይ ግን በሰፊው አልሄድበትም።

ለዛሬው አፍጦ አግጦ ለሚታየው የተወሳሰበ ችግራችን ዋናው ምክንያት የሰሜኑ የፊይዳል አገዛዝና ሃይማኖታዊ ዕምነት በአዲስና ጭንቅላትን በሚከፍት አዲስ አስተሳሰብ መጋፈጥ ባለመቻላቸው ነው። ይህ ሁኔታ ለብዙ መቶ ዐመታት ተንሰራፎት በመቆየቱ ለዕድገትና ለህብረተሰብአዊ ለውጥ ማነቆ እንደሆነ የማይካድ ሀቅ ነው። እንደ አውሮፓው ሁኔታ የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ከፍልስፍና ጋር የመጣመርና የመፈተሽ ዕድል ስላላጋጠመው የበላይነትን በመጎናጸፍ አንድ ወጥ አመለካከት በመስፈን ለአዳዲስ አስተሳሰብ መፍለቅ ዕንቅፋት ሊሆን ችሏል። በዚህ ላይ የንግድ እንቅስቃሴና የዕደ-ጥበብ ሙያ ያልተስፋፋ ስለነበር የሰው የእርስ በእርስ ግኑኝነት ከክልል አልፎ የሚሄድ አልነበረም፡፡ ይህ ዐይነቱ የተገደበ አኗኗርና የአብዛኛው ህዝብ ኑሮ ከመሬት ጋር የተያያዘና በእርሻ ላይ የሚመካ ስለነበር አዳዲስ አስተሳሰቦች መፍለቅ አልቻሉም፤ የፈጠራ ስራም ሊዳብር አልቻለም። በብዙ ጥናቶችና በምርምር እንደተደረሰበት በንግድ ልውውጥ አማካይነትና በዕደ- ጥበብ ሙያ መስፋፋት የተነሳ ጭንቅላት ብቻ ሳይሆን ቋንቋ ራሱ ውስጣዊ-ኃይል በማግኘት ስነ-ጽሁፍ እንዲዳብር አስተዋፅዖ ሲያደርግ፣ የሰው ልጅ  ጭንቅላትም የበለጠ አርቆ አሳቢና ፈጣሪ እንደሚሆን ነው።  ከዚህ ስንነሳ የፊዩዳሉ ስርዓትና ሃይማኖት የሰውን የማሰብ ሃይል በማፈን የመንፈስ ልዩ ልዩ ባህርዮች እንዳይዳብሩና ዕውነተኛ ግለሰብአዊ ነፃነት እንዳይጎለምስና፣ ገበሬውም በራሱ ላይ የሚመካ እንዳይሆንና የምርትን እንቅስቃሴ እንዳያሳድግ አስተሳሰቡን ገድቦበታል ማለት ይቻላል። የምርት መሳሪያዎችም ውስን ባህርይ ስለነበራቸው የገበሬው የማረስ ኃይል መዳበር አለመቻሉ ብቻ ሳይሆን፣ የተለያዩ የሰብል ዐይነቶችን፣ ፍራፍሬዎችንና አትክልቶችን በመትከል የተፈጥሮን ምንነት በመረዳት ኑሮውን ሊያሻሽል በፍጹም አልቻለም።  በዚህ መልክ ከስምንት መቶ ዐመታት በላይ የተንሰራፋው ፊዩዳላዊ አገዛዝና ዕምነት ለፈጠራ ስራና ህብረተሰብአዊ እንቅስቃሴ እንቅፋት በመሆን ህብረተሰብአዊ መተሳሰር እንዳይኖር አገደ። በዚህም ምክንያት በሰሜኑም ሆነ በዛሬው መልክ በተዋቀረችው የኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ በከተማዎች የሚገለጽ ዕድገትና፣ የከበርቴ መደብና ፈጣሪ የህብረተሰብ ክፍል ብቅ ሊልና፣ በሌላ ወገን ደግሞ ከሌላ ጋር በንግድ አማካይነት በመገናኘት ህብረተሰብአዊ መተሳሰርና በጋብቻ የሚገለጽ ግኑኝነት እንዲዳብር ማድረግ አልተቻለም። ስለሆነም የህዝቡ አስተሳሰብ ውስን ከመሆኑ የተነሳ ለረሃብ፣ ለድህነትና ለጦርነት እንዲዳረግ ሆነ። ህብረተሰብአዊ ኃይል እንዳይሆንና በአንድነት ተነሳስቶ አገር እንዳይገነባ ታገደ።  በሌላ አነጋገር፣ ለጭቆና መስፋፋትና ለዕድገት ዋናው እንቅፋት የጭንቅላት ተሃድሶ አለመኖርና አዲስ የሪፓብሊካን አስተሳሰብ ያለው ህብረተሰብአዊ ኃይል ብቅ ማለት ያለመቻሉ ነው። ከላይ አንድ ቦታ ላይ ለማሳየት እንደሞከርኩት ሬናሳንስ፣ ሬፎርሜሽንና ኢንላይተሜንት የቱን ያህል ለአውሮፓው ህብረተሰብ የአዕምሮና የመንፈስ ዕድገት አስተዋጽዖ እንዳበረከቱ ነው። ስለሆነም ይህ ዐይነቱ ምሁራዊ እንቅስቃሴ ለህብረተሰብአዊ ለውጥና ለካፒታሊዝም ዕድገት በሩን መክፍት ችሏል ማለት ይቻላል። በዚህም አማካይነት ነው ሳይንስና ቴክኖሎጂ ሊዳብሩና ህብረተሰቡን ሊያስተሳስሩና የዕድገትም መግለጫ ሊሆኑ የበቁት። በሌላ ወገን ደግሞ የኢንላይተንሜንት እንቅስቃሴ ባልተደረገባቸው እንደኛ ባሉ አገሮች መሰረታዊና ስር-ነቀል ሀብረተሰብአዊ ለውጥ ለማምጣት ያለመቻል ዋናው ምክንያት ይህ ዐይነቱ ጭንቅላትን የሚከፍትና ለሁለ-ገብ ዕድገት፣ እንዲሁም ለሳይንስና ለቴክኖሎጂ ምጥቀት የሚያመች የአዕምሮ ወይም የመንፈስ ተሃድሶ መካሄድ አለመቻል ነው።

በእኛ በእትዮጵያውያን ዘንድ ያለው ትልቁ ችግር የህብረተሰባችንን ውስጣዊ ህግና የተወሳሰበ ችግር በቅጡ ያለመረዳት ነው። እኔ እስከማውቀው ድረስ የኢትዮጵያን ህብረተሰብ አወቃቀር ደረጃ በደረጃ ለማጥናትና ለመተንተን እስከዛሬ ድረስ ሙከራ ያደረገ የለም። ከታሪክ አንፃር የሚጻፉት ሀተታዎች በሙሉ ገለጻዊ( Discriptive) ባህርይ ያላቸው እንጂ፣ በዲያሌክቲክ መነፅር እየታዩ ተተንትነው የቀረቡና የሚቀርቡ ሀተታዎች አይደሉም። በመሆኑም ተከታታዩ ትውልድ የህብረተሰብአችንን አወቃቀርና ታሪክ ትችታዊ በሆነ መልክ እንዳይረዳው ተደርጓል ማለት ይቻላል። በተማሬው እንቅስቃሴ ጊዜ እስከተወሰነ ደረጃ ድረስ ሙከራ ቢደረግም፣ ይህም መሰረት ያደረገው ታሪካዊ ማቴሪያሊዝምን (Historical Materialismm )፣ በተለይም በስታሊን በዶግማ መልክ የቀረበውን የህብረተሰብ ታሪክ ከአንድ ደረጃ ወደ ሌላ እንዴት እንደሚሸጋገር ያሳየውን፣ ግን ደግሞ እጅግ አሳሳች የሆነውን ትንተና ዘዴ በመውሰድ ነው። ይህ ዐይነቱ አቀራረብ ደግሞ የህብረተሰብአችንን አወቃቀርና ለዕድገት ማነቆ የሆኑትን ምክንያቶች በደንብ እንዳናጠና አግዶናል ማለት ይቻላል። በተማሪው እንቅስቃሴ ውስጥ በቀጥታ ያልተካፈለው ምሁር ደግሞ የአገራችንን ችግር ሊረዳ የሚችልበት የትንተና መሳሪያ ሊያዳብር በፍጹም አልቻለም። ሌላው ከተማሪው እንቅስቃሴ እየተስፈናጠረ የወጣው ደግሞ የአገራችንን ችግር ከብሄረሰብ ችግርና ጭቆና መኖር አንፃር ብቻ በመመልክቱ አቀራረቡ ከስሜታዊነት ያላለፈና ለተከታታይ ጥናትና ትንተና የሚያመች አይደለም። ያም ሆነ ይህ ፊዩዳሊዝምና ሃይማኖት አንድ ላይ በመጣመር ለዕድገት እንቅፋት ለምን እንደሆኑና፣ ለምንስ ለአዲስ ለተገለጸለት የህብረተሰብ ኃይል መነሳት መፈናፈኛ መስጠት እንዳልቻሉ በሚሉት መስረታዊ ጥያቄዎች ላይ ሰፋ ያለ ጥናት ብናካሄድ ኖር ከብዙ ንትርክና ውጣ ውረድ በዳን ነበር። ለምንስ አንድ ስርዓት ለለውጥ የሚያመቹ ሁኔታዎችን ማዘጋጅት እንደተሳነውና፣ ለምንስ የምርት ኃይሎች ማደግ አልቻሉም?  በሚለው መሰረታዊ ሃሳብ ላይ ጠለቅ ያለ ጥናት ብናካሄድ ኖሮ ለብሄረሰብ ችግር ሁሉ መልስ መስጠት በተቻለ ነበር።  የአገራችንን ችግር በመደብ ትግልና በብሄረሰብ ጭቆና መኖር ብቻ ባልገደብነው ነበር። በሳይንስና በአንዳች ስልት የሚመራም ምሁር ዋና ተግባር በቁንጹል ሃሳብ ላይ በመመርኮዝ እሱን እንደ ቀኖናዊ አስተሳሰብ በመያዝ ለመከራከር መጣር ሳይሆን ከዚያ አልፎ በመሄድ የአንድን ህብረተሰብ ችግር በዲያሌክቲክ መነጽር መመርመር ነው። በዚህ መልክና የሃሳብን የበላይነት ስናውቅና በጥሞና ለመወያየትና ለመከራከር ዝግጁ ስንሆን ለአገራችን የተወሳሰበ ችግር ተቀራራቢ መፍትሄ  ማግኘት እንችላለን።

ከዚህ ስንነሳ የተማሪውን እንቅስቃሴና ዕድገት ውስን ባህርይና ተልዕኮውን መረዳቱ ከባድ አይሆንም። የተማሪው እንቅስቃሴ ተራማጅ መፈክር ይዞ ቢነሳም እንደ አውሮፓው ዐይነት ምህራዊ እንቅስቃሴ በምሁራዊ ውይይትና ሂደት ውስጥ ያለፈ ስላልነበር ነገሮችን በውስን መልክ ብቻ ነበር ይመለከት የነበረው። ይህ ዐይነቱ አመለካከት ደግሞ በአገራችን ብቻ ሳይሆን በስድሳኛውና በሰባኛው ዓ.ም የጦር ትግልና ሰላማዊ ሰልፍ እንቅስቃሴ በሚካሄድባቸው የሶስተኛው ዓለም አገሮችና፣ እዚህ ራሱ የካፒታሊስት አገሮችም የነበረ ችግር ነው። ስለዚህም የአገራችንን የተማሪ እንስቃሴ ብቻ መወንጀሉ የችግሩን ምንነት ለመረዳት ብዙም አያግዘንም። መነሳት ያለበት ጥያቄ፣ የተማሪው እንቅስቃሴ በተለይም ከዚህ የወጡት የማርክሲስት ሌኒንስት ድርጀቶች አብዮቱ ከሸፈ ከተባለበት ጊዜ ጀምሮ ምን አዲስ ሃሳብ አፈለቁ? ዛሬስ መመሪያቸውና ፍልስፍናቸው ምንድነው? አንዳንዶች አንደሚያደርጉት፣ ስም በመለወጥና፣ የመደብለ-ፓርቲና የህግ የበላይነት መኖር አለበት ስለተባለ ብቻ ውስብስቡና ውጥንቅጡ የወጣው የአገራችን ችግር በዚህ መልክ ሊፈታ ይችላል ወይ?  በአንድ ወቅት ሲምሉበትና ሲገዘቱበት፣ እንደመጽሀፍ ቅዱስም ያነቡ የነበረውን ማርክሲዝም ለምንስ እርግፍ አድርገው ጣሉት? ብለን እንድንጠይቃቸው እንገደዳለን።

በመሆኑም፣ አንዳንድ የተማሪውን እንቅስቃሴ መጽሄቶች ስናገላብጥ የምንረዳው በተለይም በየኤፖኩ የተከሰቱትን የህብረተሰብአችንን አወቃቀር፣ የተለያዩ የህብረተሰብ ኃይሎችን የህሊና አወቃቀርና የመንግስት መኪናን አገነባብና፣ መንግስት የሚባለው ፍጡር የምርት ኃሎችን ዕድገት አጋዥ ከመሆን ይልቅ ለምንስ ዕንቅፋት ለመሆን በቃ?  በሚሉት መሰረታዊ ጥያቄዎች ላይ በቂ ጥናት እንዳልተካሄደ መገንዝብ እንችላለን። በእኔ ዕምነት ይህ ባለመሆኑና፣ በተለይም መንግስትና የመንግስት ቢሮክራሲው ከኢምፔሪያሊስት ኃይሎች ጋር ያላቸውን ትስስርና መቆላለፍ በሚገባ ካለመገንዘብ የተነሳ አብዮቱ መክሸፉ ብቻ ሳይሆን በቀላሉ ተተኪ የማይገኝላቸው የአንድ ትውልድ ምሁራንና አገር ወዳዶች ተሟጥጠው እንዲያልቁ ለማድረግ ተበቃ።  በተጨማሪም ይህም የሚያመለክተው የተማሪው እንቅስቃሴ የከበደ አስተሳሰብና ኢትዮጵያን ታላቅ አገር ለማድረግ ያለው ራዕይ እጅግ የጠበበና ትግሉን ከራሱ ባሻገር ለማየት ያልቻለ መሆኑን ነው። ትግሉ የኢትዮጵያ ህዝብ እንደመሆኑ መጠን ለመከፋፈል እንዳያመችና ትግልን በማስተባበር ወደፊት በመራመድ አንድ ታላቅ አገር ለመገንባት ስፊ ጥናትን ተዕግስት እንደሚጠይቅና፣  ሀብረተሰብአዊና ብሄራዊ ፕሮጀክትን ተግባራዊ ለማድረግ የግዴታ መቻቻልንና፣ አንዳንድ የጎለመሰ አስተሳሰብ ያላቸውን ግለሰቦችም ሆነ ድርጅቶችን ሚና የግዴታ መቀበልና ማክበር እንደሚያስፈልግ የተገነዘበ አልነበረም። መናናቅና አንዱ በሌላው ላይ ማሾፍ ወይም ስም ማጥፋት አንደኛው የተማሪውም መልዮ እንደነበርና፣ ይህም ለአብዮቱ መክሸፍና ለአንድ ትውልድ መተላለቅ ምክንያት መሆኑ የማይካድ ሀቅ ነው።

ያም ሆነ ይህ ራሱን ከፊዩዳላዊ ግትር አስተሳሰብ ማላቀቅ ያልቻለውና፣ ጭንቅላቱ ያልበሰለና ያልጸዳ የተወሰነው የተማሪው እንቅስቃሴ አመራር ራሱ ባነሳው ጥያቄ ላይ በእልክነት ጦር አወጀ። ከመቻቻልና ከመደማመጥ ይልቅ „ጩኸቴን ቀሙብኝ“ በማለት አጠቃላይ ጦርነት ከፈተ። በጋራ ለመስራት የሚያስችሉ ሁኔታዎችን ከመጠቀምና የታወጁትን የጥገና ለውጦችን ተግባራዊ ለማድረግ ከመሞከር ይልቅ ሁሉም በየፊናው በአገራችን ላይ  ጦርነት አወጀ። ለዲሞክራሲያዊ ለውጥ እታገለለሁ ብሎ የተነሳውና ከጭቆናም እላቀቃለሁ ብሎ እዚህና እዚያ ይሯራጥ የነበረው ሁኔታውን በጥሞና ከማንበብና ከመተንተን ይልቅ እልክ ውስጥ በመግባት ችግሩን ውስብስና ድርብርብ በማድረግ ዛሬ የምንገኝበት ደረጃ ላይ እንድንወድቅ የበኩሉን አስተዋፅዖ አደረገ። የአብዮቱን የብሄራዊ ባህርይና ለውጥ አምጭነት ያለተረዳው ቢዩሮክራሲያዊ ኃይል ደግሞ ውስጥ ለውስጥ ተንኮል በመስራትና ከውጭው ኃይል ጋር በማበር ለወጣቱ ማለቅ የበኩሉን አስተዋፅዖ አደረገ።  ከዚህ ስንነሳ መገንዘብ የምንችለው ነገር በተለይም ጣሊያን ከአገራችን ከተባረርና ነፃነታችንን ከተቀዳጀን በኋላ የተከሰተው አዲስ ህብረተስብአዊ ኃይል የበሰለ አስተሳሰብ ማዳበር ያልቻለና መንፈሱን ለለውጥ ያላዘጋጀ መሆኑን ነው። በትንሽ ነገር ተደስቶ እንደሚኖርና ታላቅ አገርና ብሄራዊ ኩራት በሳይንስና በቴክኖሎጂ ምጥቀተና በከተማዎችና በመንደሮች ዕድገት የሚገለጽና ለዚህም በታታሪነት መስራት እንደሚያስፈልግ መንፈሱን ያላዘጋጀና የነገሮችንንም ሂደት በደንብ የተገነዘበ ህብረተሰብአዊ ኃይል እንዳልነበር በሳይኮሎጂና በሶስይሎጂ ዕውቀት ማረጋገጥ ይችላል። መናናቅና ሌላውን ዝቅ አድርጎ ማየት፣ እንዲያም ሲል ወደ ዘረኝነት ማድላትና ለኢምፔሪያሊዝም ማጎብደድ በተለይም ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት  በኋላ ሰተት ብሎ ከገባው የፍጆታ አጠቃቀም፣ ብዙም ሳይሰሩ ሀብታም ከመሆን ጋር በጥብቅ የተያያዘ ነው።

ነገሩን ለማሳጠር፣ ዛሬም በመሀከላችን ያለው ትልቁ ችግር ራሳችንን ማግኘትና ማወቅ አለመቻላችን ነው። የመንፈስን የበላይነት በመረዳት የመንፈስ ተሃድሶ ለማድረግ ዝግጁ አለመሆናቸን ስያነታርከን ይኖራል። በመሆኑም ሁሉም በየፊናው ሀቀኛ ታጋይና ለኢትዮጵያ አሳቢ ካለሱ ብቻ  ያለ አይመስለውም። እንዲያውም አንዳንድ ድርጅቶች የሚያስቡት የኢትዮጵያ ጉዳይ የጋራ ጉዳያችንና ሁላችንንም የሚያገባን ሳይሆን ለጥቂቶች ብቻ በሞኖፖሊ የተሰጠ በማስመስል በቁም ነገር ላይ እንዳንወያይና መፍትሄም እንዳንፈልግ በሩን ሁሉ ዘግተዋል። በአንዳንድ አካባቢዎች ደግሞ ጉዳዩን ወደ ተራ ሴሌብሪቲ እየለወጡት ይገኛሉ። ጠቅላላው ለአገራችን የሚደረገው ትግል በተገለጸለት ምሁራዊ እንቅስቃሴ፣ በሳይንስና በፍልስፍና ላይ ከመመርኮዝ ከመታገል ይልቅ የግለሰቦችን ሚና አጉልቶ በማሳየትና ፐርሰናሊቲ ከልት እንዲዳብር በማድረግ ትግሉን ፊዩዳላዊ ለማድረግ በቅተዋል። ይህ ዐይነቱ ትግል ደግሞ ሳንወድ በግድ የዛሬውን „አዲስ አገዛዝ“ እያጠናከረውና የአገራችንን ችግር እየተወሳሰበ እንዲሄድ መንገዱን ሁሉ ያመቻችለታል። ከምሁራዊ ውይይትና ክርክር በማምለጥ በስራችን በመዝናናት በድሮ ዓለም የምንኖር፣ እንዲሁም ደግሞ ሰፋ ያለ ምሁራዊ ውይይትን የምንንቅና ሌላውን የምናጥላላና የምንንቅ ብዙዎች ነን። ስብሰባ በሚዘጋጅባቸው ቦታዎች ሁሉ የሚደረገውን ሽር-ጉድ ስመለከት የቱን ያህል ወደ ኋላ የምንጓዝ መሆናችንን ነው። ለውጥን መፈልግና  የኋሊት ጉዞ አንድ ላይ ሊሄዱ የሚችሉ ነገሮች አይደሉም።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ይድረስ ለአቶ ገብረ መድህን አርአያ ሊላክ ያልተፈለገ ግልጽ ደብዳቤ

ያም ተባል ይህ፣ በአገራችን ምድር መሰረታዊና ሁለንታዊ ለውጥ መምጣት አለበት ብለን የምናምን ከሆነ ከመንፈስ ተሃድሶ ውጭ ልናመልጥ አንችልም። ለመንፈስ ተሃድሶ ደግሞ ራስን መጠየቅ ዋናው መሰረታዊ ጉዳይ ነው። ከዚህ በፊት ያደረግነውን አዎንታዊና አሉታዊ ድርጊቶችን ማውጣትና ማውረድ አለብን። ስህተት ወይም ደግሞ ህብረተሰብአዊ ወንጀል ሰርተን እንደሆን ወደ ውጭ አውጥተን መናገር መቻል አለብን። ስህተታችንን ስናውቅና ከስህተታችን ለመታረም ስንሞክር ብቻ ነው ለመሰረታዊና ለሁለንታዊ ለውጥ አስተዋፅዖ ማበርከት የምንችለው። ለዚህ ደግሞ የግዴታ የምንመራበት ትክክለኛ ፍልስፍናና ሳይንሳዊ የአሰራስር ዘዴ መኖር አለበት። በአንድ ትክክል ነው ብለን በምናመነው ሳይንስና ፍልስፍና እየተመራን የምንጽፍና የምናስተምር ከሆነ የየበኩላችንን አስተዋፅዖ ለማበርከት እንችላለን። በሌላ ወገን ግን ስመለከትወና በጥብቅም ስመረምር አብዛኛዎቻችን ይህንንም ያህል ራሳችንን ለመጠየቅና የመንፈስ ተሃድሶ ለማድረግ ዝግጁ አይደለንም። ስህተት መሆኑ እየታወቀ ድሮ የሰራነው ስራ ትክክል ነው ብለን ድርቅ ብለን የምንከራከር አለን። እኛ ሳንሆን ሌላው ነው ጥፋተኛ እያልን አሁንም እንምላለን፣ አንገዘታለን። አንዳንዶቻችን ደግሞ ከተንኮል ጋር የተወለድን ይመስል ግለሰቦችን እናሳድዳልን። በዚህም ለኢትዮጵያ ህዝብ ነፃነት የሚደረገውን ትግል እናጨናግፋለን። ሌሎቻችን ደግሞ የድርጅትና የግለሰብ ፍቅር እያንገበገበን ዕውነተኛ ውይይትና ክርክር እንዳይደረግ መንገዱን ሁሉ ለመዝጋት እንሞክራለን። በዚህም አንዳንድ ድርጅቶችና እንቅስቃሴዎች የሚያካሂዱትን ትግል ትክክል መሆኑንና አለመሆኑን ሳንመረምርና ሳንጠይቅ ወደ ኩርፊያ እናመራለን።  በእርግጥ ከተንኮል ጋር የተወለደን ማዳን አይቻለም።  በቀና መንፈስ እንታገላለን ብለው እዚህና እዚያ የሚሉትን ግን ወደ አንድ ውሳኔ ላይ ከመድረሳቸው በፊት ሰፊ ጥናትና ምርምር ማድረግና እንዲሁም በቂ ግንዛቤ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ልናሳስባቸው እንወዳለን። እንደምናየው የዓለም ሁኔታ እየተወሳሰበና አስቸጋሪ እየሆነ የመጣ ነው። ስለሆነም ትክክለኛ ወይም ሳይንሳዊ አመለካከትን ለማዳበርና አገራችንን ካለችበት ችግር ለማላቀቅ የምንፈልግ ከሆነ ካለንበት ሁኔታ ባሻገር መመልከት ይኖርብናል። አስተሳሰባችንን ለመለወጥ ዝግጁ መሆን ይኖርብናል። አንድን ሃሳብ ከመቀበላችንና እንደ ዕምነት ከመውሰዳችን በፊት ትክክል መሆኑንና አለመሆኑን መመርመር መቻል አለብን። የተለያዩ ሃሳቦችንና ቲዎሪዎችን ማወዳደር አለብን።  ችግር ፈጣሪዎች ሳንሆን ችግርን ፈቺ ለመሆን ከፈለግን የሚያዋጣው መንገድ ሳይንሳዊ መንገድ ብቻ ነው። ይህንን ካልኩኝ በኋላ የወያኔንም ሆነ ዛሬ ደግሞ በዶ/ር አቢይ አህመድ የሚመራውን አገዛዝ የሃሳብ ችግርና ግትርነትን ምንጭ ወይም ምክንያት መረዳቱ አስፈላጊ ይመስለኛል።

በአገራችን ታሪክ ውስጥ ከየብሄረሰቡ የተውጣጡ ምሁራን ነን ባዮች የየብሄረሰቦቻቸውን የአስተሳሰብ ችግርና የማቴሪያል ዕድገት ኋላ-ቀርነት በማንሳት ሰፊ ጥናት ለማድረግ አልሞከሩም። ሁሉም ነገር ከብሄረሰብ ጭቆና አንፃር በመታየቱ ከሀብረተሰብ የባህል ታሪክ ዕድገትና(Socio-cultural studies) ከማወዳደር አንፃር(Comparative Studies) ጥናት ስላተደረገ የበሽታችንን ዋና ምክንያት ወይም መነሾ ለማወቅ አልተቻለም። ስለሆነም አንዳንድ ሙከራ በሚደረግበት ጊዜ ፈላስፋ ነኝ፣ ማንም የሚወዳደረኝ የለም የሚለው የፕሮፌሰርነት ማዕረግ የያዘው ሁሉ መሳደብና መደንፋት ይጀምራል። የአገዛዙንና የመሪዎችን የአስተሳሰብ ችግር ሲነግሩት ብሄረሰቡን እንዳለ ለመስደብ ወይም ለማንቋሸሽ የሚደደረግ አካሄድ ይመስለዋል። በዚህ መልክ ሳይንሳዊ ጥናትና ውይይት ከማድረግ ይልቅ ችግሩ በይደር እንዲታለፍና፣ በላዩ ላይ ሌላ ችግር እንዲደረብበት ይደረጋል። ለነጻነት በሚደረገው ትግል ውስጥ ከማንኛውም ወገናዊነት መላቀቅ የመጀመሪያው ተግባር መሆኑ ብዙዎቻችን የተረዳን አይመስለኝም። በተጨማሪም አብዛኛዎቻችን  የአንድን ብሄረሰብ ችግርና የህሊና አወቃቀር ለመረዳት የምናድረግው ጥረት ይህንን ያህልም አይደለም። ለመሰረታዊ ለውጥ እንታገላለን የምንል ከሆነ  ካለንበት ሁኔታ ባሻገር ማየት መቻል አለብን።  መለኪያችን የብሄረሰብና የሃይማኖት ጭቆና ሳይሆኑ፣ ሳይንስና ፍልስፍና ብቻ መሆን አለባቸው።  ማንኛውም ህብረተሰብ ችግሩን የሚፈታውና የሰለጠነ ህብረተሰብ ለመመስረት የሚችለው በሳይንስ አማካይነት እንጂ፣ የብሄረሰብና የሃይማኖች ጭቆናን አጉልቶ በማሳየቱ አይደለም። ማናኛውም ብሄረሰብም ሆነ፣ ይኸኛው ወይም ያኛው የሃይማኖት ተከታይ የሆነ በመጀመሪያ ደረጃ መሰረታዊ ፍላጎቱ መሟላት አለበት። መብላትና መጠጣት እንዲሁም ተጠልሎ መኖር አለበት። ህክምናና ትምህርትም ማግኘት መቻል አለበት። የአንድን ህዝብ መሰረታዊ ችግርና ጥያቄዎች በብሄረሰብና በሃይማኖት መፍታት አይቻልም። የብሄረሰብና የሃይማኖት ጥያቄዎችን አጉልቶ ማሳየትና በእነዚህ ዙሪያ አስተሳሰባችን እንዲሽከረከር ማድረግ ያለብንን ኋላ-ቀርነት ያጠናክረዋል። ችግራችንን ያባብሰዋል። እንደማህብረሰብ እንዳንኖር ያግደናል። የብሄረሰብ ጥያቄን በሳይንስ አማካይነት ብቻ መፍታት የሚቻል ሲሆን፣ የሃይማኖት ጥያቄ ግን ግላዊ ነው። ሃይማኖትን  የህብረተሰብ ጥያቄ አድርጎ ማንሳትና፣ የተወሰነው የህብረተሰብ ክፍልም ጭንቅላቱ በዚህ እንዲጠመድ ማድረግ መሞከር ልንወጣው የማንችለው ችግር ውስጥ ይከተናል። ሃይማኖት ዕምነት ነው። በሳይንስ የሚረጋገጥ አይደለም። በሌላ ወገን ግን ማንኛውም ሃይማኖት መከበር ያለበት ነው።  ያም ሆነ ይህ ሰው መሆናችንና አንደኛው ከሌላው እንደማይበልጥ የምንረዳው ሳይንስንና ፍልስፍናን እንዲሁም ዲያሌክቲክን መሰረት አድርገን ከታገልን ብቻ ነው። ይህንን ካልኩኝ በኋላ ወደ ዋናው ፍሬ ነገር ላይ ላምራ።

የቀድሞው የወያኔም ሆነ የዛሬው አገዛዝ የሃሳብ ግትርነት ዋና ምክንያት ምንድነው? ለምንድ ነው አገዛዞቹ እንደዚህ አምረው በጥፋታቸው እንዲቀጥሉ የተገደዱት? በአዕምሮ ጉድለትና በሃሳብ አለመዳበር የተነሳ?  ወይስ አንዳች ከውጭ ሆኖ የሚቆጣጠረቸውና የሚገፋፋቸው ኃይል ስላለ ነው ወይ እንደዚህ አምረው የሚገፉበ? ብለን መጠየቅና ተቀራራቢ መልስ ለመስጠት መሞከር አለብን።

የኢትዮጵያን ህብረተሰብ ታሪክ በደንብ ለተከታተለ የፊዩዳሊዝም ጥንስስ የተጣለው ትግሬ ውስጥ ወይም አክሱም ግዛት ነው። ይህ ግዛት በዘመኑ ታላቅ ስልጣኔዎች ከሚባሉት ውስጥ ቢጠቃለልም፣ ወደ ውስጥ ሲታይ ግን ህብረተሰቡ በስራ-ክፍፍል የዳበረና ሃሳብ የሚንሸራሸርበት አልነበረም። የአገዛዙም ገቢ ከውጭ ንግድ በሚገኝ ገቢና በግብር(Tributary) ላይ የተመሰረተ ስለነበር ወደ ውስጥ ቢያንስ እንደ ቻይናው ስልጣኔ የስራ-ክፍፍልን በማዳበርና ቢሮክራሲያዊ አሰራርን በማጎልመስ የሚታማ አልነበረም። በዚህም የተነሳ የሰው ኑሮና የአሰራር ዘዴ ተደጋጋሚና አሰልቺ ስለነበር ለመንፈስ ተሃድሶው የሚያግዘው አንዳችም ነገር አልነበረም። የስራ ክፍፍሉም ውስን ስለነበረና በግብራና ላይም የተመካ ስለነበር በተፈጥሮ ላይ ከፍተኛ ዘመቻ ሲያካሂድ ቆይቷል። ትግሬ ውስጥ በተደጋጋሚ ይከሰት ለነበረው ድርቅና ረሃብ ዋናው ምክንያት ከብዙ መቶ ዐመታት ጀምሮ ሲሰራበት የነበረው የአስተራረስ ዘዴ ነው። ተከታታይነት(sustainable) ያለውና የተፈጥሮን ምንነት በመረዳት እንክብካቤ የሚደረግለት የአስተራረስ ዘዴና የአኗኗር ስልት ስላለነበር ለም የነበረው  የትግሬ መሬት ቀስ በቀስ ወደ በረሃነት እንዲለወጥ ተገደደ። በዚህም ምክንያትና ከሌላው ህብረተሰብ ጋር በንግድና በስራ-ክፍፍል አማካይነት መገናኘት ያልቻለው ህዝብ በአስተሳሰሰቡ ውስንና ተጠራጣሪ ሆነ።  በራሱ ብቻ ተገልሎ እንዲኖር የተገደደው ህዝብ በአጠቃላይ ሲታይ አገሪቱ ካሳየችው በጣም ደካማ ዕድገት ጋር ተያይዞ ወደ ፊት መራመድና የሃሳብ ለውጥ ማድረግ አልቻለም። ይህ ጉዳይና የሃሳብ ውስንነትና የፈጠራ ችሎታ አለመዳበር በአብዛኛዎቹ የአገራችን የሰሜኑ ክፍልም በጉልህ ይታያል።

ከዚህ ዐይነቱ ህብረተሰብ የፈለቀውና የፔሪፈሪ ካፒታሊዝም ዕውቀት ጭንቅላቱን የገረፈው የትግሬ ኤሊት የትግሬን ክፍለ-ሀገር ወደ ኋላ መቅረት የተረጎመው ካጠቃላዩ ከአገሪቱ ሁኔታና ከአገዛዙ ባህርይ ጋር ከማያያዝ ይልቅ፣  የአማራው ኤሊት የትግሬን ዕድገትና የህዝቡን የኑሮ መሻሻል እንደማይፈልግ አድርጎ ነው። ይህ አመለካከቱና አተረጓገሙ ደግሞ በሳይንስ የሚደገፍ አይደለም። ምክንያቱም ከአርባኛው ዓ.ም መጨረሻ ጀምሮ በአገሪቱ ውስጥ በአዲስ አበባና በአካባቢው የተተከሉት ኢንዱስትሪዎች የማደግና የማባዛት እንዲሁም የፈጠራን ችሎታ የማዳበር ባህርይ አልነበራቸውም። አዲስ አበባ ላይ በአማራ የሚታማ አገዛዝ ስለተቀመጠ የአማራው ክፍለ-ሀገራትም ተጠቃሚ አልነበረም። ከደቡቡ የኢትዮጵያ ክፍለ-ግዛት በስተቀር ጠቅላላው የአማራው ግዛትና ትግሬም ጭምርም በአገዛዙ አትኩሮ ያልተሰጣቸውና ዘመናዊ ኢንስቲቱሽን ያለነበራቸው ነበሩ። ስለሆነም በአዲሱ የኢንዱስትሪ ተከላ ፖሊሲ አማካይነት ጠቅላላው የኢትዮጵያ ህዝብ ሳይሆን ተጠቃሚው 5% የማይበልጥ የህብረተስብ ኃይል ብቻ ነበር። ስለሆነም ሌላው የኢትዮጵያ ግዛት ሲያድግ ትግሬ ብቻ ወደ ኋላ ቀረ የሚለው ኢ-ሳይንሳዊ፣ በህብረተሰብ ሳይንስና በኢኮኖሚ ቲዎሪ ያልተደገፈ አባባል የትም ሊያደርሰን አይችልም። ይሁንና ግን ከአማራው ኤሊት ጋር ዕልክ የተጋባውና የአማራን ኤሊት የበላይነት መስበር አለብኝ ብሎ የተነሳው የተወሰነው የትግሬ ኤሊት ነኝ ባይ በጠባብ አስተሳሰብ በመደገፍ በዚያው በማምራት ጦርነት አወጀ። ይህንን ህልሙን ተግባራዊ ለማድረግ ሲል ውስጥ ለውስጥ ከውጭ ኃይሎች ጋር በመስራት ሁኔታዎችን አመቻቸ። የቀድሞው የወያኔ አገዛዝ በጦርነት ዘመኑ ቀና አመለካከትና ብሄራዊ ባህርይ ያላቸውን እየመነጠረ ለድል የበቃ ኃይል ነበር።  የሚያሳዝነውና የሚያስገርመው ግን ይህ ተገንጣይና ከፋፋይ ኃይል በማርክሲዝም ስም መማሉና ለሶሻሊዝም ራዕይ እታገላለሁ ብሎ መነሳቱና ብዙውን የትግሬ ወጣት ማሳሳቱ ነው።  ለወያኔ ማደግና ወደ ድል ማብቃት ሻቢያ የማይናቅ አስተዋፅዖ ማድረግ ችሏል ማለት ይቻላል። ሁለቱም ኃይሎች በመተባበር አገራችንን እጅግ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ከተዋት እንደነበር ይታወቃል።  ሻቢያም በበኩሉ ከ400 በላይ የሚበልጡ በኢትዮጵያዊነታቸው የሚያምኑና ተራማጅ አስተሳሰብ የነበራቸውን ኤርትራውያን እንደጨፈጨፈ ይታወቃል። ይህም ማለት ሁለቱም ሃይሎች በወንድሞቻቸው ደም የታጠቡ ናቸው። ርህራሄ የሌላቸው፣ የሰው ነፍስ የቅንጣትም ያህል የማያሳሳቸው ፍጡሮች ናቸው። ስለሆነም ወያኔ በወንድሞቹ ሞት የሚደሰትና ይህንንም እንደ ድል የሚቆጥርና ጭንቅላቱ የደነደነ ነበር። ጦርነት ማካሄድና ሰውን መግደል እንደሙያና ባህል የወሰደና ከደሙ ጋር ያዋሃደ ነበር። የሌላው ሰው መሞት ምንም ስሜት የማይሰጠው ከአውሬ በታች ያለ ፈጡር ነው ማለት ይቻላል። አዋቂዎች እንደሚሉት መንፈሱ የተሰለበና ራሱም ሰው መሆኑን የተረዳ አልነበረም። የሰው ልጅ ባህርዮችና ስሜቶች ሁሉ ተሟጠው ያለቁበትና ሰውነቱ ብቻ የሚንቀሳቀስ ነበር ማለት ይቻላል። ሰውን ከማሰቃየት በስተቀር ለምን እንደሚኖር የተገነዘበ አይደለም። ፍቅር፣ ስሜት፣ ፀፀት፣ ርህራሄ፣ መቧቧት፣ ለህፃናት ማዘንንና እንክብካቤ ማድረግ፣ ሽማግሌዎችን ማክበርና ተፈጥሮን መንከባከብ የሚሉት በሙሉ በጭንቅላቱ ውስጥ የሌሉ ናቸው። በአፈጣጠሩ የሰው ልጅና የተፈጥሮ ጠላት ይመስል የሚወስዳቸው እርምጃውች ሁሉ የሚያስገርሙም የሚያሳዝኑም ናቸው። ሎጂክልንና የህበረተሰብን ህግ ያለተከተሉ፣ አገራችንን ለከፍተኛ አደጋ የጣሉ ድርጊቶች ነበሩ። ባለፉት 28 ዐመታት ተግባራዊ የሆኑትት ፕሮጀክቶች የአገዛዙን የመንፈስ መቀጨጭ የሚያረጋግጡ ናቸው። በአገሪቱ ውስጥ የተከናወኑትንና የሚካሄዱትን ፕሮጀክቶች ስንመለከት የዚህ ዐይነቱ በስነ-ስራዓት ያለተገራና ጥበብና ሳይንስን ውስጣዊ ያላደረገ የጭንቅላት ውጤቶች መሆናቸውን እንገነዘባለን። በእልክና በአወቅኹኝ ባይነት የሚሰሩ፣  ብዙ ሀብትና የሰው ጉልበት የፈሰሰባቸው ናቸው። ህብረተስብአዊ ሀብትን መፍጠር የማይችሉና ለፈጠራ ስራ የማያመቹ ፕሮጀክቶች ናቸው። ባጭሩ ቀደም ብሎም ሆነ ዛሬ በአገራችን የሚታየው የተዘበራረቀና ቆሻሻ ሁኔታ የወያኔና ግብረ-አበሮቹ ጭንቅላት መበላሸት ውጤቶች ናቸው። ከላይ በተጠቀሰው ሂደት ውስጥ የመጣ ኃይል ደግሞ ከጥፋት ሌላ፣  ታሪካዊና የተቀደሰ እንዲሁም አንድን ህዝብ እንደ ኃይል የሚያሰነሳ ፕሮጀክት ከቶም ሊኖረው አይችልም። ስለሆነም ይህ ዐይነቱ ኃይል ራሱን ስልጣን ላይ ለማቆየት ሲል ከውጭ ኢምፔሪያሊስት ኃይሎች ጋር በመተባበርና ትዕዛዝ ተቀባይ በመሆን አገራችን በችግር ተጠምዳ ዘለዓለሟን ፍዳዋን እያየች እንድትኖር የማያደርገው ጥረት አልነበረም። በዶ/ር አቢይ አህመድ የሚመራው አገዛዝም ከወያኔው  የአገዛዝ ስልት የተላቀቀ የሚመስል አይደለም። የአገራችን ተጨባጩ ሁኔታ እንደሚያረጋግጠው አገዛዙ አገራችንን ወደየት አቅጣጫ እንደሚወስዳት ግልጽ የሆነለት አይመስልም። በሌላ አነጋገር፣ ህዝባችን እየተፈራራ የሚኖርባትና እንዲያም ሲል ወደ መተላለቅ በማምራት የውጭ ኃይሎች አገሪቱን እንዲወሩ ሁኔታውን እያመቻቸ እንደሆነ በፍጹም የተገነዘበ አይደለም።

ባጭሩ ፊዩዳላዊ ባህርይ ከውስን ካፒታሊዝም ሂደት ጋር በመዋሃድ የቀድሞውንም ሆነ የዛሬውን አገዛዝ ጭንቅላት ሊያደነድንና ጥያቄ እንዳይጠይቅና ለተለየ ሃሳብ ጭንቅላቱን ክፍት እንዳያደርግ አግዶታል ማለት ይቻላል። ስልጣን መያዝና በሀብት መደለብ ደግሞ የወያኔን አገዛዝ የባሰ ሃሳቡን እንዳጭለመበት ግልጽ ነበር። ሰብአዊ ባህርዩን እንዳለ ገፎታል። ሰውን በጅምላ መግደል፣  የሚታየውንና የሚዳሰሰውን ነገር መካድ፣ ዕድገት ሳይኖር ዕድገት አለ ብሎ ድርቅ ማለት፣ ከፋፍሎ መግዛት፣ የሃይማኖት መሪዎችን በጥቅም በመግዛት መከፋፈልና ግጭት እንዲፈጠር ማድረግ፣ አንድን ብሄረሰብ ለሁለትና ለሶስት በመከፋፈል በመሀከላቸው ግጭት እንዲፈጠር ማድረግ፣ እኔ ብቻ ነኝ ሁሉንም ነገር መስራት አለብኝ በማለት ለግል መዋዕለ-ነዋይ መንገዱን መዝጋት፣ ማንኛውም ነገር ከሱ ቁጥጥር ውጭ እንዳይሆን ማድረግና፣ በአጠቃላይ ሲታይ አገራችን ዘለዓለሟን በትርምስ ዓለም ውስጥ እንድትኖር የማይሸርበው ተንኮል አልነበረም። እንዲዚህ ዐይነቱ ባህርይና የሃሳብ መቀጨጭ በማንኛውም የህብረተሰብ ታሪክ ውስጥ ያልታየና ያልተለመደ ነው። ሂትለርና ተከታዮቹ እንኳ እንደዚህ ዐይነት የሃሳብ መቀጨጭ አልታየባቸውም። የተከተለው ርዕዮተ-ዓለምና በይሁዲዎች ላይ ያደረሰው ድርጊትና ያወጀው ጦርነት የሚኮነን ቢሆንም፣ የሂትለር አገዛዝ ጀርመንን ለማጥፋትና የህዝቡን ቅስም ለመስበር የተነሳ አልነበረም። ከዚህ ስንነሳ የአገዛዙን ርዕዮተ-ዓለምና የሚመራበትን ፖሊሲ በቀላሉ መተንተንና መረዳት ያስቸግራል። በአንድ በኩል በዝቅተኛ ስሜት የተወጠረ፣ በሌላ ወገን ደግሞ እኔው ብቻ ነኝ የሰለጠንኩትና የማውቀው ብሎ በመዝናናት የበላይነቱን ለማሳየት የሚጥር አገዛዝ ነበር። ስለሆነም ለትግል የሚያስቸግር ነው። በጊዜው በምን ዐይነት የትግል ዘዴ መጣልና ዲሞክራሲያዊ ኢትዮጵያን ለመገንባት እንደሚቻል ግራ ያጋባ አገዛዝ ነበር። ሌላው አስቸጋሪው ነገር ደግሞ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ከውጭ ኃይሎች ጋር የገባውና የተዋዋለው ስምምነት የአገራችንን ሁኔታ ውስብስብ ማድረጉ ነው።

በዶ/ር አቢይ አህመድ የሚመራው አዲሱ አገዛዝም ወያኔ ይከተል ከነበረው ኢ-ሳይንሳዊና ኢ-ህብረተሰብአዊ ፖለቲካ ትምህርት የቀሰመ አይመስልም። ወያኔ 28 ዐመት ኢትዮጵያን እረግጦ ሲገዛ ያደረሰውን ባህላዊና ማህበራዊ ውድቀት፣ እንዲሁም ብሄራዊ ውርደት የተገነዘበ አይመስልም። በተለይም ጊዜው የኛ ነው፣ ይህንን ዕድል ካልተጠቀምንበት መቼ ነው የምንጠቀመው እያሉ የሚያወሩ አንዳንድ የኦሮሞ ኢሊቶችና መሪዎች ከፍተኛ የታሪክ ወንጀል እየሰሩ ለመሆናቸው የተገለጸላቸው አይመስልም። ዝም ብለው በስሜት እየተገፉ የሚወስዷቸው ፖሊሲዎችና ህዝብን መጤ እያሉ ማፈናቀል የተቀረውን ህዝብ ብቻ ሳይሆን እንወክለዋለን የሚሉትን ብሄረሰባቸውንም ወደ ኋላ እንዲጓዝ እያደረጉት ለመሆናቸው በፍጹም የተገነዘቡ አይመስልም። ካላቸው አስተሳሰብና ከሚያካሄዱትም ፖለቲካ የምንረዳው ነገር አዲሶቹ መሪዎች ስለኢኮኖሚና ስለህብረተሰብ ዕድገት ይህን ያህልም ግንዛቤ ያላቸው አይመስልም። የፖለቲካ ስልታቸው በሙሉ የፈጠራ ስራንና አጠቃላይ የሆነን የስራ-ክፍፍልን የሚጻረር ነው። ህዝባችን ለዝንተ-ዓለሙ በድህነት ዓለም ውስጥ እየማቀቀ እንዲኖር የሚያደርግ ነው። በአጠቃላይ ሲታይ የፍልስፍናን፣ የሳይንስን፣ የባህልን፣ አርክቴክቸርንና ለአንድ ማህበረሰብ ዕድገት የሚያስፈልጉ ዕውቀቶችን በሙሉ የሚቀናቀን ነው። ተግባራቸው በሙሉ ለውጭ ኃይሎች የሚሰሩ ነው የሚያስመስላቸው። ስለሆነም ከዚህ ዐይነቱ እጅግ አደገኛ ከሆነ አመለካከትና አገርን በታኝ ፖለቲካ መላቀቅ አለባቸው። ዛሬ እጅግ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ከሚገኙት እነ ኢራክ፣ ሲሪያና ሊቢያ ከመሳሰሉት አገሮች ውድቀት ትምህርት መቅሰም አለባቸው። ሌሎችም እንደክልል መታወቅ አለብን የሚሉ አንዳንድ ብሄረሰቦች የይጎዝላቪያን እጣ ማየትና ከዚያ ትምህርት መቅሰም አለባቸው። በመበታተንና አትድረሱብኝ በማላት ሳይሆን አንድ ክልልም ሆነ አገር ሁለ-ገብ በሆነ መልክ ሊገነቡ የሚችሉት በመተባበርና ሃሳብ ለሃሳብ በመለዋወጥና በመመካከር ብቻ ነው። በመሆኑም ለመጭው ትውልድ ጥሩና ቋሚ ነገር ጥለንለት ለማለፍ የምንፈልግ ከሆነ የሃሳብ ተሃድሶ ማድረግ አለብን። ከግትርነት፣ ከእልከኝነት፣ ከአወቅኹኝ ባይነትና ከጠባብ አስተሳሰብ መላቀቅ አለብን። መልካም ንባብ !!

fekadubekele@gmx.de  

  

 

 

4 Comments

 1. ዶክተር ፈቃዱ መጣጣፎን አነበብኩ።ለአስተማሪነቱ፣ለአዲስ ሃሳብ ጫሪነት፣መጣጣፎ ሁሌም ስለ ጥልቅነቱ አመሰግናለሁ።ዛሬ ዛሬ አረፍተ ነገሮቹ አጠር አጠር ማለታቸው፣ሃሳቦ ለብዙሃን አንባቢዎች በቀላሉ እንዲረዱት ለማድረግ መሞከሮ የሚመሰገን ነው።ሆኖም ግን በአንድና በሁለት ቃላት መልዕክት ሲቀባበል ለሚውል ትውልድ መጣጣፎ መርዘም ብቻ ሳይሆን ቅዱስን መጣፍ ያክላል ነው የተባልኩት።

  ዶክተር ፈቃዱ ሁሌም የምመኘው ምን መሰሎት፣እስከ ዛሬ በአማሪኛ ያቀረቧቸውን መጣጣፎች ቀለል ቀለል ተደረገው፣ቅደም ተከተላቸው ተስትካክሎ ባንድ ላይ ቢታተሙ ደስ ባለኝ።

 2. “በመሆኑም ለመጭው ትውልድ ጥሩና ቋሚ ነገር ጥለንለት ለማለፍ የምንፈልግ ከሆነ የሃሳብ ተሃድሶ ማድረግ አለብን። ከግትርነት፣ ከእልከኝነት፣ ከአወቅኹኝ ባይነትና ከጠባብ አስተሳሰብ መላቀቅ አለብን።”
  AMEN, AMEN!!!!!!!
  However, the very last paragraph indicates that you are not what you preach – shear hypocrisy!

 3. አቶ ክዲር ሰተቴ ዕውንተኛው ስምህ በይ… ይጀምራል። በቅርብ ጊዜ የልደት በዓልህን አክብረሃል። የፃፍከው አስተያየት ሳይሆን ዝም ብሎ የስም ማጥፋት ነው። በሰባ ዓመትህም አትማርም። በጣም ታሳዝናለህ። ለማንኛውም የፃፍከው እኔን የሚመለከት አይደለም። ጊዜ ባታባክን ይሻላል። አገራችንን ድምጥማጧን ለማጥፋት ባትሯሯጥ ይሻላል።

  መልካም ጊዜ

  ፈቃዱ በቀለ

  • Dr., askeyemku ende? Yikrta! However, I still stand by my statement – the very last paragraph negates ALL what you have written above it.
   You are even sure about the starting letter of my name, my age and even that I celebrated my birth day? Believe me someone is being mistakenly blamed here for something he has no idea about. First of all, no need of knowing the person’s identity. Second, you got it ALL wrong! Please the person you characterized has nothing to do with this – be’tiritare endaytalut biye new.

   “አገራችንን ድምጥማጧን ለማጥፋት ባትሯሯጥ ይሻላል።” I think you are unnecessarily judgmental here. I won’t succeed even if I want to, or anyone wants to for that matter. I assure you Ethiopia shall prevail, no matter what! Yes there are setbacks here and there but it will come to pass – Inshallah!

   መልካም ጊዜ to you too!

Comments are closed.

Share