የመቀሌው የደጺ ግሩፕ በተለይ በአዲስ አበባ ያሰማራቸው ኤጀንቶቹ በሁለት ነገሮች ላይ በስኬት እየሠሩ መሆናቸው ተደርሶበታል፡፡
ከነዚህ ሰሞነኛ የሤራ ተግባሮቹ ውስጥ አንዱ ሙስና ሲሆን፣ ሙስናን ከሃያ ሰባቱ ዓመት የጨለማ ዘመን በባሰ ሁኔታና በረቀቀ መንገድ በአገሪቱ እንዲስፋፋ ማድረግ ዓላማው አድርጎ እየሠራበት ነው፡፡ ሌላው ደግሞ የጦር መሣሪያ ማዘዋወር ከባድ ነገር እየሆነ በመምጣቱ ሌሎች መሣሪያ የማይጠይቁ ፀረ ደኅንነት መሰናክሎችን ልክ እንደ ቲማቲም ማሣ ችካል እዚህም አዚያም መቸከል ሌላው ስትራቴጂክ እቅዱ ሆኖ እየተገበረው ነው፡፡ ይህ የደኅንነት ሥጋት ደግሞ በከተማው ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ዝርፊያዎችን መፈፀምና ነዋሪዎችን ማማረር ብሎም ተስፋ ማስቆረጥ ነው፡፡
እስካሁን ድረስ ታዲያ ይህን እኩይ ተግባር ሲፈጽም እንደተለመደው እንደ ርኩስ መንፈስ ከእይታ ውጪ ሆኖ አሻራ ሳያስቀር ወንጀሎችን በታላቅ ጥንቃቄ መከወን ነው፡፡ የኦዴፓ ሰላዮች ዓይኖች ደግሞ እነ እስክንድር ነጋ እንቅስቃሴዎች ላይ ተቸክለው ስለቀሩ የሥውሩን የሕወሐትን እጆች ለማየት ገና አልታደሉም፡፡ ስለዚህም በከተማይቱ ውስጥ የሚታየው የዘረፋ እንቅስቃሴ ከቁጥጥር ውጪ እየሆነ በመምጣት ላይ ይገኛል፡፡ ወያኔ ሕወሐትም ይህ ሤራው የታቀደለትን ግብ እየመታ መሆኑን ወደ መቀሌ የሚላኩት ሪፖርቶች ያመለክታሉ፡፡
የነዚህ የሁለቱም ሤራዎች ዓላማዎች ግልጽ ናቸው፡፡ የመጀመሪያው ‹‹ሙስናው አሁንም አልቀነሰም !!! ጭራሹንም በባሰ ሁኔታ ተጧጡፎ ቀጥሏል!!!›› ስለሚያስብል ለነጌታቸው አሰፋም ሆነ ለሁሉም የሕወሐት አባላት ለጥፋት ማቅለያነት ብቻ ሳይሆን ኦዴፓንና አዴፓን ከደሙ ላለማንጻት ፍቱን መድኃኒቶች ናቸውና የመቀሌው ቡድን በሚገባ ይጠቅማቸዋል፡፡
ልክ እንደዚሁ የደኅንነት ሥጋቱን ማጦዝ ደግሞ፣ የአዲስ አበባ ነዋሪዎችና የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ‹‹ሰው ካልሄደና ካልሞተ አይመሰገንም›› እስኪሉ ድረስ ነዋሪዎቿን በከፍተኛ የሥጋት ቅርቃር ውስጥ አስገብቶ ‹‹እነ ዐቢይ ማስተዳር አልቻሉም›› (ኦሮሞ አገር መምራት አይችልም) የሚለውን ሕወሐታዊ ትርክት ማስረገጥ ላይ የሚያጠነጥን ነው፡፡
በከተማችን በአዲስ አበባ ውስጥ የጦር መሣሪያ ሳያዘዋውርሩ በቀላሉ የሚያከናውናቸው እነዚህ ሁለቱ መስኮች በዚህች ቅጽበት ውስጥ በሰፊው እየተሠሩባቸው ለመሆኑ ማስረጃዎች አሉ፡፡
የዘረፋው ነገር በዚያን ሰሞን ታከለ ኡማ ሞተር ሳይክል በከተማዬ ውስጥ ማየት አልፈልግም ልክ ብሎ እንደ በረሮ በከተማይቱ መንገዶች ላይ ሲርመሰመሱ የነበሩትን ሞተር ሳይክሎችን በድነገት እገዳ ሲጥልባቸው የቀን ዘረፋው በሚያስገርም ደረጃ የቀነሰ ቢመስልም አሁን ደግሞ መልኩን ቀይሮ በአዲስ ስልት መጥቷል፡፡ ተሸከርካሪዎችን መሠወር፣ በተቀነባበረ መንገድ ሰዎችን እያገቱ መዝረፍ የመሳሰሉትን ፕሮፌሽናል በሚያስብል መልኩ አገሬውን ብቻ ሳይሆን፣ እንዲያውም በሚገራርሙ ስልቶች የውጭ ዜጎችን ዒላማ አድርገው እየተካሄዱ ይገኛሉ፡፡
የሚገርመው ነገር ዘረፋዎቹ በተራ ሰዎች አይካሄዱም፡፡ የሚካሄዱትበጣም የዳበረ ዕውቀት ባላቸው ግለሰቦች ነው፡፡ ቻይናዎቹ በጣም ብዙ የሚባሉ ተሸከርካሪዎች ተሠውረውባቸዋል፡፡ አንዳንዴም ካቆሙባቸው ቦታዎች፣ አንዳንዴም እባክህን አሽከርክርልን ብለው በደመወዝ በቀጠሩአቸው ተቀጣሪ አሽከርካሪዎቻቸው አማካኝነት፡፡
በጣም በርካታ የኮንስትራክሽ መሣሪያዎችም እንዲሁ ተሠውረዋል፡፡ ወዴት ይወሰዳሉ የሚለውን ለጊዜው ባንመልሰውም ከሰሞኑ ግን ለተዘራፊዎችም ለመንግሥትም ግብአት የሚሆኑ ሚስጥሮችን ጀባ እንላቸኋለን፡፡
ለነደጺ የሚያስገኙት ጠቀሜታ ግን ከላይ እንደገለጽነው ፖለቲካዊ ብቻ ሳይሆን ኤኮኖሚያዊም መሆኑ አሌ “አይባልም፡፡ በዚህ ረቂቅ አሠራር ላይ ከሰሞኑ በተሸለና በበለጠ መረጃ ብቅ ለማለት ቃል እንገባለን፡፡
በሙስናው ረቂቅ ሥራ ላይ ግን የደረሱን ተጨባጭ መረጃዎች እንደሚጠቁሙን ከሆነ የታከለ ኡማ የአዲስ አበባ መንግሥት በአዲሱ ዓመት ዕቅድ የያዘላቸውን ፕሮጅክቶችንና የልማት ሥራዎችን ማሰናከል ወይንም መጓተትን የሚፈጥሩ አሻጥሮችን መጫወት ከዒላማዎቹ ውስጥ ዋነኛው ነው፡፡
ከሰሞኑ በአንዱ የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ ፕሮጅክት ላይ የተደረገውን አሻጥር እንደምሣሌ መጥቀስ ይቻላል፡፡
ኤጀንሲው ክረምቱ ሲወጣ በወርሃ መስከረም ላይ እሠራለሁ ብሎ ከያዛቸው ፕሮጅክቶች ውስጥ አንዱ የመንገድ ቅብ (ሮድ ማርኪንግ) ነው፡፡ ፕሮሰሱን የጀመረው ከስድስት ወር በፊት ሲሆን በዓለም አቀፍ ጨረታ ተጫራቾችን አወዳድሮ ሥራውን ለአንድ የዓለም አቀፍና ለአንድ የአገር ውስጥ ኮንትራክተሮች ለመስጠት ዝግጅት በሂደት ላይ ሳለ በውድድር የተሸነፉና በዘመነ ሕወሐት ሥራውን በርስትነት ይዘው ቆይተው የነበሩ ድርጅቶች በግንባር በመሆን ከግዢ ሥርዓቱ በወጣ ሁኔታ በአዲስ አበባ ፋይናንስ ዲፓርትመንት ሥር ለሚገኘው የቅሬታ ሰሚ ክፍል ቅሬታ አለን በሚል በህገወጥ መንገድ ቅሬታቸው እስኪታይ ድረስ የጨረታው ሂደት እንዲቋረጥ ያስደርጋሉ፡፡
አካሄዱን ሕገወጥ የሚያደርገውም በቴክኒክ መመዘኛ የወደቁት እነዚህ ሰዎች በቴክኒክ ውጤቱ ላይ ቅሬታ አቅርበው ኤጀንሲውም ለቅሬታቸው በቂና አጥጋቢ መልስ ከሰጣቸው በኋላ በውሣኔው ባይስማሙ የቅሬታ ቅሬታ ማቅረብ እየቻሉ ያንን ሳያደርጉ ቆይተው ፋይናንስ መመዘኛው ውጤት ከተከፈተ በኋላ ውጤቱ ለተወዳዳሪዎች ተገልጾ አሸናፊዎች ከተለዩና ሂደቱ ከተጠናቀቀ በኋላ ጉዳዩ ለማይመለከተው አካል ጊዜውን ያልጠበቀ ቅሬታ ማቅረባቸው ነው፡፡
በአጭር አገላለጽ የሰዎቹ ፍላጎት ጨረታውን በዚያም በዚህም ብለው (በእጅም በእግርም ብለው) እንዲሠረዝ ማድረግና ፕሮጅክቱን ማጓተት ስለሆነ ከውስጥ ባሉአቸው የነሱ ሰዎችና በገንዘብ ኃይል ሕገወጥ የሆነ ውሣኔ አስወስነው ሥራውን እያጓተቱት ይገኛል፡፡ ውሣኔውን ያልተቀበለው ኤጀንሲም አላስፈላጊ መጓተት ውስጥ ገብቷል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ገላጋዩ ታከለ ኡማ ስለሆነ የኡማ ልጅ ምን እንደሚያደርግ ከሰሞኑ የሚታይ ይሆናል፡፡
ለማጠቃለል፣ ‹‹ ባልበላውም ጭሬ እበትነዋለሁ›› እንዳለችው ዶሮ በእልህ ፖለቲካ ጨርቁን ጥሎ ሊሄድ የደረሰው ሕወሐት የዚህችን አገር ሰላም ማመስ መቀጠሉን ተያይዞታል፡፡ ስለዚህ መንግሥት ለነዚህ ችግሮች አፋጣኝ ምላሽ ሊሰጣቸው ይገባዋል፡፡
ሙስናውንም መከታተል በተለይ ደግሞ በከተማው ውስጥ እየተቀጣጠለ የሚገኘውን የደኅንነት ሥጋት ምንጭ የሆነውን ዘረፋ በውጭ አገር ባለሙያዎች በመታገዝ ባስቸኳይ ለጉዳዩ እልባት ቢያበጅለት ይሻለዋል፡፡ እግረ መንገዱንም የሕወሐትን ሤራ ኦዴፓ ብቻውን ሊቋቋመው እንደማይችል አምኖ መቀበልና ለዚህም ችግር መውጫ ፖለቲካዊ መፍትሔ ቢያፈላግለት ይበጀዋል፡፡
ኢኑሻ አየለ