መስቀሉ አየለ
የትግራዩ ገዥ ጉጅሌ ላለፉት አራት አስርተ አመታት የተጓዘባቸው “የብሄር ብሄረሰቦች ጭቆና” ወዘተ የሚለው የፖለቲካ ድሪቶ ሞቶ የተቀበረ መሆኑን በራሱ የውስጥ ግምገማ ተማምኗል። ከዚህ ቦሃላ የኢትዮጵያን ህዝብ የሰናፍጭ ቅንጣት ታክል እምነት አግኝቶ አንዲት ስንዝር የሚያራምደው የፖለቲካ አጀንዳ እንደሌለ እርግጠኛ ሆኗል። በመሆኑም ከደደቢት ጽንሰቱ ጀምሮ እስካሁኗ ደቂቃ ድረስ የተጏዘባቸውን መንገዶች አሁን ከተፈጠረበት ህዝባዊ ማእበል አንጻር እንዴት መደምደም እንዳለበት ቁጭ ብሎ በሶስት ደረጃ አስልቶ በመጨረስ ወደ ስራ የገባ መሆኑን ህዝቡ ከልብ እንዲያስተውልና ለቀጣዩ ትንቅንቅ እንዲዘጋጅ ያስፈልጋል።
ስቴጅ ፩
እንደ ህወሃት ግምት ይኽ አሁን ድርጅቱ ያለበትን ሁኔታ የዲተረንስ ስቴጅ ብሎታል። በዚህ ቀለበት ውስጥ አልፎ ነገሮችን ለመፍታት እንደ ግብአት እየወሰደ ያለው በተቻለ መጠን ስጋት አይሆኑብኝም የሚላቸውን እስረኞች በመፍታት አንድም ለብሄራዊ እርቅ የተዘጋጀ በመስለል በአንድ በኩል የተፈጠረበትን የዲፕሎማቲክ ጫና በማርገብ በዋናነት ግን የህዝቡን ቁጣ በመባረድ እኛን ከትግል እያዘናጋ ግዜ የመግዛት ሁኔታን መፍጠር ነው።ቢሆንም ግን በዚህ ደረጃ ህወሃት እራሱ ከገመተው በላይ እንደተጏዘ ነገር ግን በዚህ ቀለበት ውስጥ ይገኛል የተባለው አንጻራዊ መረጋጋት እንዳልተገኘ ይልቁንም ይበልጥ ቀኑ በገፋ ቁጥር ሂደቱ ይበልጥ ውስብስብ እየሆነ መሄዱን ነው የተረዳው። በመሆኑም ወደ ሁለተኛው ቀለበት ወይንም ስቴጅ ፪ በመሸጋገር ላይ ነው።
ስቴጅ ፪
በራሱ የግዜ ስሌት ውስጥ ሄዶ የአስቸኳይ ግዜ አዋጁን ያወጀው የህወሃት የኮብራ ግሩፕ የመጀመሪያውን ቀለበት ሙሉ ለሙሉ እያሟጠጠና ወደ ሁለተኛው ዙር ቀለበት ውስጥ ለመግባት የምጥ መጀመሪያ ላይ የቆመ ሲሆን አለም በአይኑ ብሌን እየተመለከተውም ከሚንስትሮች ምክርቤት እስከ ፓርላማ ያለው መዋቅር ሳያስፈልገው በቁራጭ ወረቀት በቀጥታ ለሚዲያ በወረደ ትእዛዝ የአስቸኩዋይ ግዜ አዋጁን መጫኑ ወደ ሁለተኛው ዙር ቀለበት ውስጥ ለመግባት ያስችለኛል ያለውን ጭምብል በህግ ሽፋን ለማጥለቅ እየተጏዘበት ያለው ሂደት መሆኑ ሊታወቅ ይገባል።
እንደ ህወሃት ኮብራ ግሩፕ እስትራቴጅ ሂደቱ ወደዚህ ቀለበት ውስጥ ሙሉ ለሙሉ ሲገባ ተከታታይነት ያለው ከፍተኛ የሆነ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት (ሄቪ ኢንተርቬንሽን) ይጠበቃል። አገሪቱ ውስጥ አስፈላጊ በሆነው ቦታ ሁሉ የራሱ የቁርጥ ቀኔ የሚላቸውን የወታደር ክፍል ከመጠቀም ጀምሮ በመላ አገሪቱ የሚገኙትን የወታደራዊ ተቋማት ሳይቀር በቀጣይ ለሚፈጸሙ የጅምላ እስር እያዘጋጀ በሂደት ለሚፈጠሩ ተጋትሮዎች በታንክ ጭምር የተደገፈ የከተማ ውስጥ ወረራ በማድረግ “ድምጽ በራማ ተሰማ ያልወልዱ ጡቶች ያላጠቡ ማህጸኖች ብጽአን ናቸው” ተብሎ የተነገረለትን የሄሮድስን ጌሎቲን ሰይፍ በመምዘዝ ቀይ ሽብርን ተረት በሚያደርግ ፋሽዝም ወደ ለየለት የጅምላ ጭፍጨፋ ለመሄድ ዝግጅቱን በማጧጧፍ ላይ መሆኑን ኢትዮጵያውያን በአንክሮ ሊያውቁት ይገባል። ዛሬ ታማኝ የተባሉትን ቅልብ ጦር እስከ አፍንጫው እያስታጠቀ ከሰሜን ግምባር ወደ መሃል አገር መግባት መጀመሩ የዚሁ የሁለተኛ ቀለበት እቅድ ቅድመ ዝግጅት አካል መሆኑ ነው።
ስቴጅ ፫
እንደ ህወሃት ግምገማ ከህዝቡ የሚጠብቀው ትንቅንቅ ሁለተኛውን ቀለበት አልፎ መውጣት ከቻለ ወደ መጨረሻውና ሶስተኛው ቀለበት ለመሄድ ይገደዳል ማለት ነው። በዚህም እስከዛሬ ድረስ ለይስሙላም ቢሆን የነበረውን የሲቪል የሚመስል አስተዳደር ሙሉ በሙሉ በማውረድ በታንክ አጅቦ የወታደሩን መንግስት በአራት ኪሎ ላይ ያቆማል ማለት ነው።
ለዚኽም ስኬት እስከዛሬ እርስ በርሳቸው እጆቻቸውን ቃታ ላይ አኑረው በይነ ቁራኛ ሲጠባበቁ የነበሩት የሳሞራና የጌታቸው አሰፋ ክንፎች በእነርሱ እምነት ሁለቱንም ጠርጎ ሊወስዳቸው የመጣውን ህዝባዊ ሱናሜ ለመቋቋም ሲባል ጊዜያዊ የመቻቻል ስምምነት ላይ የደርሱ ሲሆን ገለልተኛ በሆነ ሶስተኛ ቦታ እየተገናኙም መረጃዎችን በማቀላጠፍና እቅድ በማውጣት ላይ ተጠመደዋል። ያም ሆኖ ግን ሁኔታዎች ሲያመቹዋቸው ደግሞ አንዳቸው አንዳቸውን ከመብላት እንደማይመለሱ ሁለቱም ያውቁታል።
ውድ ኢትዮጵያውያን ምናልባት ተጽእኖ የማድረግ አቅም ያላቸው የውጭ መንግስታት ይኽ እኩይ ስርአት ሊሄድበት ያለውን የመንገድ እርቀት አስቀድመው ተረድተውና በዚያው ልክ ያላቸውን ሌቬረጅ ሁሉ ተጠቅመው ከዚህ ድርጊቱ እንዲቆጠብ ካልገፉት ወይንም ከተራው ወታደር በሚፈጠር ማፈንገጥና ከህዝብ በሚመጣ መቀናጀት ሂደቱ ሌላ መልክ ካልያዘ በስተቀር ይኽ ህወሃት የተባለ መሰሪ ቡድን እቅዱን ሁሉ ደረጃውን ጠብቆ ተግባራዊ ከማድረግ እንደማይመለስ በእርግጠኝነት ሊታወቅ ይገባል።