March 1, 2016
20 mins read

ለዲ/ን ኒቆዲሞስ፦ በውቀቱ ስዩም፣ ጓደኛው ተመስገንን “ከሚወዳት ልጅ ጋር አንሶላ ሲጋፈፍ ማደር …”  እንዳለበት አልመከረም! ውሸት ነው!

አሊ ጓንጉል

aliguangul@gmail.com

ዲ/ን ኒቆዲሞስ፣ በውቀቱ ጓደኛው ተመስገንን “..ከሚወዳት ልጅ ጋር አንሶላ ሲጋፈፍ ማደር …” እንዳለበት መክሯል የሚሉትን ከየትኛው ገጽ ላይ እንዳገኘኸው አላውቅም። “አንሶላ”፣ “ሲጋፈፍ” እና “ማደር” የሚሉት፣ እንኳን ቃላቶቹ ራሳቸው፣ የግስ እርባታቸውም በምዕራፉ ውስጥ የለም። ለነገሩ ግን “መጽሃፉም” እንኳን ቢሆን፣ “ብዙ ተባዙ” ሲል አንሶላ ሳይጋፈፉ መባዛት የለም። በውቀቱ ያለው “አለምን መቅጨት…” ማለት ደግሞ፣ እንዳለ በጽሁፋዊ (Literal) ትርጉሙ በየትኛው መ/ቃላት “አንሶላ መጋፈፍ..” ማለት እንደሆነ ዲ/ን እና ዲ/ን ኒቆዲሞስ ብቻ መሆን አለበት የሚያውቀው። ስለዚህ ዲያቆኑ ዋሽቷል።

 

ለመሆኑ ፍሮዳይኒዝም  “…የሚያስተምረው ራስን ያለ ልክ መውደድን ነው። ሃይማኖትን አለመከተል፣ እግዚአብሔርን አለመቀበል፣ ባህልን አለመጠበቅ፣ ወሲብን ለእርካታ ብቻ መጠቀም፣ የገዛ እናትን ለወሲብ መመኘት የገዛ ወላጅ አባት እንዲሞት በጥልቅ መሻት የመሳሰሉት እሳቤዎች የፍሮይድ አስተምህሮ የማዕዘን ድንጋይ ናቸው። ለፍሮዳዊያን ወሲብ እንቅልፍ ማምጫ እንጂ ከአብሮ መቆየት፣ ከቅዱስነት፣ ዘርን ከማስቀጠል፣ ሓላፊነት ከመውሰድ ጋር ፈፅሞ አይገናኝም…” ያልከው ከየትኛው መጽሃፍ ላይ ነው ያገኘኸው? ለምን መጽሃፉን ከነገጹ ጠቅሰህ አትነግረንም?  እኔ “ሲግመንድ የሚታወቅባቸው ነገሮች” ብየ ጎግል አድርጌ፣ በጎግል የመጀመሪያ ረድፍ ላይ ያገኘሁት ይኸን ነው፦ “… Freud has been influential in two related, but distinct ways. He simultaneously developed a theory of the human mind and human behavior, and a clinical technique for helping unhappy (i.e. neurotic) people. በግርድፉ እንዲህ ይተረጎማል፦

ሲግመንድ ፍሪውድ በተለያየ መንገድም ቢሆን በሁለት [እርስ በርስ] በተገናኙ ጉዳዩች ለውጥ አምጪ ሆኗል–ደስታ ቢስ የሆኑ ስዎችን መርዳት የሚያስችል የህክምና ቴክኒክ ፈጥሯል፣ የሰው ልጅን ባህርይ (behavior)  እና አይምሮ (mind) በተመለከተም ቲዩሪ ነድፏል።

ሲግመንድ በስራዎቹ ውስጥ ስለወሲብ እና ውስብና መጻፉ እርግጥ ነው። እግዚአብሄርን አለመቀበል ደግሞ ከሶቅራጢስ ጀምሮ ያለ፣ በዚህ ዘመንም ትልቅ ሃይማኖት እየሆነ ነው። ነገር ግን ታላቅ የክ/ዘመኑ ሊቅ ከሆነው ከሲግመንድ ፍሩይድ ታላላቅ ስራዎች ውስጥ “ወሲብ፣ ባህልን አለመጠበቅ፣ ወዘተ…” የመሳሰሉትን ኢምንት የሆኑትን ጉዳዩች ብቻ በመጥቀስ፣ እንዲህ በሙያው የመሰረት ድንጋይ ያስቀመጠውን ሳይንቲስት “ሰይጣን” አድርጎ መቀባት፣ የራስን “ቅዱስነት ለማጉላት” [ምናልባትም ምንም ቅዱስ ነገር ሳይሰሩ] ካልሆነ ምን ይባላል?

መግቢያየ ላይ እንደጠቀስኩት ዲ/ን ኒቆዲሞስ ያልተባለውን “ተብሏል” ብሏልና ዋሽቷል። “ከአንድ የሃይማኖት ሰባኪ እንደዚህ ያለ ውሸት አይጠበቅም…” እንዳልል፣ በውቀቱ ካሁን ቀደም “…የዲሲ ቄስ በበኩሉ ሙዳየ ምጽዋት አፍሶ፤… የንስሃ ልጁን ጡት ተንተርሶ፤ በቴስታ ተከሳክሶ ይኖራል የሚል ሀሜት አለ…” እንዳለው፣ የአብዛኛውን የሃይማኖት መሪዎችን በሞራል የመዝቀጥ ነገር ሳስበው “በርካታ እውነት የሚናገሩ የሃይማኖት መሪዎች አሉ” የሚል እንድምታ ያስከትልብኛል። እናም በደፈናው ዲ/ን ኒቆዲሞስ እንዲህ ያለተጻፈ ነገር እንደተጻፈ አስመስሎ የመጻፉ ነገር ብዙም አይገርመኝም።

 

እኔ ዲ/ን ኒቆዲሞስን ብሆን ኖሮ፣ ብዕሬን የማነጣጥረው፣ ከዋሽንግቶን ዲሲ እስተ ሎንዶን ከተሞች ሳይቀር የምዕራቡን አለም ከተሞች እስኪቀውጥ ድረስ በኡኡታ አገር ሲያምሱ እና ሲያተራምሱ፤ “በቴስታ ሲከሳከሱ…” የሚውሉትን እና በቅርቤ ያሉትን ሰዎች መተቸት እና መፍትሄ መፈለግ ላይ ነበር የምሰራው። “እሱ ብሎ ቄስ፣ እሱ ብሎ ጳጳስ፣ ዲያቆን ማንትስ ይኼን ያህል ገንዘብ አጎደለ፣ የወያኔ ተላላኪ ነው…ወዘተ…” የሚል ጽሁፍ እና የቪዲዩ ንትርክ ሳናይ ውለን የምናድርበት ቀን አለ እንዴ?

 

አንድ በአገሪቱ የስነ-ጽሁፍ ታሪክ አንቱ የተባለ ያገሬን ሰው “ለኢትዮጵያ ምን ትመኛለህ” ብለው “…ላንድ ሰከንድ የነብይነት ስልጣን ባገኝ፣ ኢትዮጵያዊ እንዳይዋሽ አደርገው ነበር” ያለኝን ሳስታውስ፣ እና እንዲህ ከሃይማኖት መሪዎች የሚታየው ማስመሰል፣ ቅጥፈት እና ሸፍጥ፣ ኢ-ሞራላዊ መሆን…ወዘተ ያመጣብን ይሆን? እላለሁ።

 

ስለ ዲሲ ቄስ “ሙዳየ ምጽዋት ማፈስ”፦ አንዲት በጣም የምግባባት እና በሰዓት $7.00 እያገኘች፣ ተሰኞ እስተ ሰኞ ያለ እረፍት እየሰራች፣ ሜሪላንድ የምትኖር ያገሬ ሴት “… የስለቴን ለቤተስኪያን $1000.00 አገባሁ…” ብትለኝ “አብደሻል እንዴ! አሊቤርጎ የመሰለ ቤት ተከራይቶ ለሚሰብክ አጭበርባሪ ሁላ እንዴት እንዲህ የደከምሽበትን ገንዘብ ትስጫለሽ?” ስላት “…በቃ! ደስ ያለኝን ነገር ስላገኘሁ፣ ደስ ያለኝን ነገር አደረግሁ” ካለችኝ ወዲህ፣ እውነትም የያንዳንዳችን የደስታ ማግኛችን መንገድ የተለያየ ነው። ይቺም እህቴ፣ ደስታ እስተሰጣት ድረስ፣ ገንዘቧን ወንዝ ውስጥ ብትበትነውስ ምን አገባኝ?” ከዚያ ወዲህ አንስቼባት አላውቅም።

 

ስለ ዲሲ ቄስ “የንስሃ ልጁን ጡት ተንተርሶ ማደር”፦ በውቀቱ “ ሃሜት አለ…” ነው ያለው። እኔ ደግሞ በእርግጥ የሆነውን እና የግለሰቧን ማንነት ማውጣት ባይሆንብኝ ኖሮ፣ ለንስሃ አባቷ ሃጥያቷን ልትናዘዝ የሄደች ሴት እንዴት በአባቷ ልትደፈር እንደነበር ከነቤተስኪያኑ እና ከነቄሱ እዚህ በተናገርኩ ነበር። ምን ላተርፍ? የጉዳዩ ባለቤት የሆነችውን ሴት ራሷን፣ ዛሬም እየሄደች የአባቷን ስብከት እንደምትሰማ ስትነግረኝ “እኔ አንቺን ብሆን ኖሮ አንደኛ አጋልጠው ነበር፣ ሁለተኛ እሱ ያለበት ቦታ ድርሽ አልልም ነበር…” ስላት “… እሳቸውን ለመስማት ብዬ ብቻ አይደለም የምሄደው፣ ለቦታው ነው…” ታለችኝ ወዲህ፣ እንዲህ ያለ ክርክር አቆምሁ። እኔ የማውቀው፣ ሲጀምር ቦታውን (መስበኪያውን ቦታ/ቤተስኪያኑን) ያቆሙት እሳቸው (አባቷ) እና አባቷን መሰሎቹ ተጥራርተው ነው። እዚሃር/ሚካየል ራሱ ወርዶ ጎልላት ሲሰቅል አላየሁም።

 

አሁን አሁንማ በየፈረንጅ አገሩ ያለ ያበሻ ቄስ ሁላ “እልል በቅምጤ[1]” ሆኖለታል። የፈረንጅ ቸርች ሁላ ምእመን እያጣ እየተዘጋ ነው። ያበሻ ቄስ እና ደብተራው ሁላ እየተጠራራ ይገዛዋል። አንድ ወቅት፣ እንዲያው ለቤተሰብ ብዬ (እድሜ ለ66ቱ አብዩት፣ እኔም ተሃይማኖት ተተፋታሁ 35 ዓመት አለፈኝ) አንድ አዲስ የተከፈተ ቤተስኪያን “ግራንድ ኦፐኒንግ” (በውቀቱ “ሙዳየ መጽዋቱን እያፈሰ” አለ? ቀላል ቢዝነስ ነው እንዴ!) ላይ ተገኝቼ ነበር። ጸሎተ ቡራኬ ተሰጥቶ እንዲያው ታ’ቀረቀርኩበት ቀና ተ’ማለቴ ቀድሞ ያላየሁት አንድ ፈረንጅ ታ’ጠገቤ ቆሟል። መቸም ኢትዬጵያ የኖረ፣ ቅባ ቅዱስ አግኝቶ፣ ከርስትና የተነሳ፣ የተጠመቀም ይሆናል … እያልኩ ሳስብ፣ ራሱ ወሬ ጀመረኝ–በሹክሹክታ፦

 

“…ኢትዮጵያዊ ነህ፣ አይደል?”

“አዎን”

“አይ ኖው”

“ኧረ! እንዴት አወቅህ በል?”

“ዌል…ይኼ ቤተስኪያን የኛ ነበር፣ የሸጥነው ለኢትዮጵያዊያን ነው እና…”

ጆሮዬ ቆመ። “እናንት እነማን ናችሁ? ማለቴ የማን ቤተስኪያን?”

“የግሪክ…” አለና ፈገግ ብሎ ቀጠለ “…የማስተዳደሪያ ገንዘብ (በሙዳየ ምጽዋት የሚገኘው) መግባት አቆመ፣ ምዕመኑ ተመናመነ። ሳር ማሳጨጃ እና ማጽጃ ባጀት ሁሉ ጠፋ። እናም ተዘጋ፤ ይኼው እናንተ ገዛችሁት” አለኝ።

 

ለነገሩ የዲ/ን ኒቆዲሞስ ትኩረት በመሰረቱ፣ በንግስት ሣባ ርዕሰ ጉዳይ አስታኮ፣ የበውቀቱን በአደባባይ “ከሃይማኖት ጋር መፋታት…” (ኢ-አማኒነት) ለማጋለጥ እና ኢ-አማኒነትን ለመዋጋት ያደረገው ይመስለኛል። ኢ-ሃይማኖተኛነት እየገነነ/እየገዘፈ የመጣ “ሃይማኖት” እንደሆነ ዲ/ን ኒቆዲሞስ ሳያውቁ ቀርተው አይመስለኝም። ያ ብቻ’ማይደል፣  እንዲህ “ኩላሊት እያወጡ ይወስዳሉ፤ አሳ ነባሪ በላቸው፣ አይሲስ አረዳቸው…” እየተባልን ሁሉ እንዲህ አይናችንን እየጨፈንን የምንመጣበት የምዕራባዊያኑ አገር፣ ስለ እዝጌሩም ሆነ ሰይጣኑ፣ ስለ ሳባም ሆነ ሰለሞን፣ ስለ ወሲብም ሆነ “አንሶላ መጋፈፍ” ወዘተ… በነጻነት ለመወያየት፣ ለመጻፍ፣ ለመናገር ወዘተ የሚያስችል ዲሞክራሲያዊ መብት ያላቸው በመሆኑ ያቆሙት እና እንዲህ ያደረጁት/ያለሙት አገር መሆኑን ዲ/ን ረስቶት አይመስለኝም። የእሱም የንጀራ  ነገር ቢሆንበት ይመስለኛል።

 

የምዕራባዊያኑ በነጻነት የመሰብሰብ፣ ሃሳብን የመናገር፣ የመጻፍ ወዘተ ሲፈቅድ፣ ኢ-አማኒያኑንም የሚሞግት ነጻነትንም ያካተተ ነውና፣ ዲ/ን ኒሞዲቆስ መከራከር መብቱ ነው። ግንሳ መዋሸት ባልተገባ ነበር። ደሞ’ስ የደራሲ በውቀቱ ጽሁፍ መጥፎ መሆኑን የታየውን ያህል፣ እንዲያውም መጽሃፉ ውስጥ የሌለውን እና “… እግረ ሙቅ ለሚጠብቀው ወዳጁ እንደ መልካም ወዳጅ በደጁ ከሚጠብቀው መከራ…  ያንዣበበበትን የመከራ መርግ ለጊዜውም “…አንሶላ ሲጋፈፍ ማደር…” ብሎ ስለመምከሩ በምናብም ቢሆን የታየውን ያህል፤ የተመስገን ደሳለኝ መልካም ሰብዕና፣ እና “… እንደምታሰር …ሰምቻለሁ… ልጆቹን ይዤ የመጣሁት ለዛ ነው። ከምሳ በኋላ እነሱን ሳዝናና ለመዋል አስቤያለሁ። የዛሬው ቀን የነሱ ነው…” (ገጽ 78)፣ የማለቱ እና ተመስገን ያለችውን ግማሽ ቀን፣ በጉዲፈቻ የሚያሳድጋቸው ልጆቹን ለማዝናናት የማሰቡ እና የማድረጉ መልካም ሰብዕና ለምን አልታየህም? ምነው የበውቀቱ አጉል/መጥፎ ሰብእና ብቻ ታየህ? የሌላውን ሰው መጥፎ ስራ (አንዳንዴ የሌለ ጥፋትን በመፍጠር፣  እና ምንም አይነት መልካም ስራ ሳንሰራ) አጎልቶ በማውጣት፣ የራስን መልካምነት ለማሳየት ከመሞከር የምንወጣው መቼ ነው?

 

‹‹… ወዳጄ እንግዲህ የፈራኸው የመከራ ቀን ኮተተት እያለ እየመጣ እንደሆነ ሳይገለጽልህ እንዳልቀረ እገምታለኹ እናም አብዮተኛው ወንድሜ …” የሚል ጽሁፍ ያለው የትኛው ገጽ ላይ ነው? መጀመሪያ ነገር እያንዳንዱን በመጽሃፉ ውስጥ ተጻፈ ያልከውን ነገር አንድም ቦታ ላይ ገጽ በመጥቀስ ያሳየኸው ነገር የለም። ሲመስለኝ እንዲሁ አድበስብሶ እና አስመስሎ ደራሲውን ለማስጠቆር የተጻፈ ነው የሚመስል።

 

“… በጠራራ ፀሐይ ወሲብ እንደ ሸቀጥ በሚቸረቸርባት በአሜሪካዋ በላስቬጋስ ከተማ ቆይታው በኋላ ይህችን ከተማ ‹‹አትጠገብም፣ ትጣፍጣለች›› በሚሉ ውብ ቃላት ነው ሊገልጽልን የሞከረው። እንዲህ ዓይነቱ ከሃይማኖታችን፣ ከኢትዮጵያዊ ባህላችንና ትውፊታችን ያፈነገጠ የበዕውቀቱ ለወሲብ ያለው ይሄ አፈንጋጭ አመለካከቱ እንዴት በልቡ ሊሰርጽ እንደቻለም እንዲህ ሲል ያወጋናል…” በሚልም በዕውቀቱን ሊተቸው ይሞክራል። ለመሆኑ የትኛው ባህላችን? ይኼ የ10 እና 11 አመት ህጻናት በቦሌ እና መርካቶ፣ በሃገሪቱ ትላልቅና ትናንሽ ከተሞች… በየአደባባዩ ተኮልኩለው፣ ይበሉ ይቀምሱት አጥተው እያየን፣ ት/ቤት በመሄጃ እድሜያቸው ገላቸውን ሸጠው የሚኖሩ ህጻናት የፈሉበትን ኢትዮጵያዊ ባህላችንን፣ ትውፊታችንን እና ሃይማኖታችንን ነው?

 

ባንድ ወቅት አገር-ቤት ሆኜ፣ ለኤች አይ ቪ ኤድስ መከላከያ ፕሮጄክት ለመስራት፣ እየዞርኩ ቃለ መጠይቅ አደርግ ነበር። መርካቶ ውስጥ፣ በጎዳና/ሴትኛ አዳሪነት የምታድር አንዲት የ13 አመት ልጅ “…ኮንዶም ትጠቀሚያለሽ?” ስል ጠየቅኋት። “…እሞክራለሁ። ካልፈለጉ ግን አላስገድዳቸውም” አለችኝ። “…ኮንዶም አለመጠቀም፣  ለኤድስ እና አባለዘር በሽታ ያጋልጣል…” ከማለቴ “ተወኝ ባክህ! ኤድስም፣ አባለዘርም በሽታ ነው። ቀን ይሰጣል። አንተ ምግብ ሳትበላ ስንት ቀን መቆየት ትችላለህ? በሽተኛ እናቴ እና ሁለት ታናናሽ ውንድሞቼ የሚጠብቁት የኔን እጅ ነው። ጊዜ የለኝም..” ብላ፣ እዚያው ትታኝ፣ የመርካቶ ጽልመት ውስጥ ገባች።

 

እኔ እስከማውቀው ድረስ፣ ጠቅላላ አሜሪካ፣ ቬጋስም ሆነ ሎስ አንጀለስ፣ 18 አመት ያልሞላቸው ልጆች፣ ለወሲብ ባደባባይ የማይታዩበት እና በዚህ እድሜ ክልል ካሉ ልጆች ጋር ወሲብ መፈጸም፣ በህግም ሆነ በሞራል የሚያስጠይቅበት አገር መሆኑን ነው! ሃያ አንድ አመት ያልሞላው ሰው መጠጥ ገዝቶ የማይጠጣበት፣ ሲጠጣ ቢገኝ፣ ሻጩም ጭምር የሚቀጣበት ህግ እና የሞራል መሰረት ያለው አገር እና ህዝብ መሆኑን ነው የማውቀው።

[1] “እልል በቅምጤ”= ደስታ በ“እልል”ታ ይገለጻል። ዋናው ደስታ ግን እንዲያው ተነስተህ ቆመህ፣ ጉልበትህ እየተንቀጠቀጠ አይደለም። ተሆነ አይቀር በ“ቅምጥህ እልል” ያልክ እንደሆን የደስታ ሁሉ ደስታ ሆነ ማለት ነው።

 

Go toTop