ይሄ “እንደሠራ አይገድል” የሚባል አማርኛ አንዳርጋቸው ጽጌን የመሳሰሉ የታሪክ ዝቃጮችንና በሞቀበት ዘፋኞችን ለመግለጽ ምንኛ ክርክም ያለ ውብ ገላጭ መሰላችሁ! ብዙ ነገሮች አጀማመራቸው ቢያምር አጨራረሳቸው አያምርም፡፡ ለዚህም ነው እንዳማሩ መሞት የለም የሚባለው፡፡ ይሄ የፈረደበት አማራ እንዲህ የማንም ሞልፋጣ አፍ መክፈቻና መጫወቻ ሆኖ ይቅር ግን? የዚህን ሰው ብልግና ሰምቼማ ዝም ማለት የለብኝም በሚል ብዕር አነሳሁ፡፡ የፈለገው ይምጣ እንጂ እስከዶቃ ማሰሪያው እነግረዋለሁ፡፡ ባለጌን ባለጌ ካላሉት ደግ የሠራ ይመስለውና ቅርሻት ብስናቱን በስፋት መቀጠሉ አይቀርም፡፡ እንደአማራ የሚያሳዝን አሁን አሁን የለም፡፡ ሁሉም እየተነሳ ያልተገራ መደዴ አፉን በነገር የሚያሟሸው አማራን በመሳደብ ነው፡፡
በቅድሚያ ግን ወደ ደርግ ዘመነ መንግሥት ልውሰዳችሁና ስለመንጌ አንድ ነገር ላጫውታችሁ፡፡ መንጌ አንድ ወቅት ሚኒስትሮቹን ሰብስቦ “ብታምኑም ባታምኑም እናንተ የት እንደምታመሹ፣ ምን እንደምትበሉና እንደምትጠጡ፣ ከማን ጋር እንደምትዝናኑ፣ ምን ምን ሀብትና ንብረት እንዳላችሁ የኢትዮጵያ ሕዝብ በሚገባ ያውቃል!…” አላቸው (ዘመኑ ራቅ በማለቱ በትክክል ባልጠቅስ ይቅርታ)፡፡ ለምን ትዝ አለኝ መሰላችሁ – የኢትዮጵያ ሕዝብ ያኔም ሆነ አሁን የሚጠቅሙትንና የሚጎዱትን፣ የሚያላግጡበትንና ከምር አለሁልህ የሚሉትን፣ ጨዋዎችንና ዋልጌዎችን፣ እውነተኞችንና አስመሳዮችን … ለይቶ በሚገባ ያውቃቸዋል … ለማለት መፈለጌን ለማጠየቅ ነው፡፡ ብዙው ፖለቲከኛ ከአልባሌ ቦታ እየመጣ ፖለቲካን እንደብቸኛ አማራጭ ወስዶ ሕዝብ ጫንቃ ላይ እንደሙጫና እንደመዥገር ስለሚጣበቅ ይሉኝታና ሀፍረት ብሎ ሲያልፍም አይነካው፤ ፖለቲካ እንጀራ እንጂ ሙያ መሆኑ ቀርቷል፡፡ አብዛኛው ፖለቲከኛ አንድም በሌላ ሙያ ቢሰማራ ችሎታ እንደሌለው በማመን ወደ ፖለቲካው ይገባና ያጨመላልቀዋል፡፡ አንድም በሥልጣን አራራ በመናወዝ ወደዚያው የፈረደበት ፖለቲካ ይገባና ዝናንና ታዋቂነትን አትርፎ በዚያ ለመኮፈስ በሀብትም ይበልጥ ለመክበር ይገባል፡፡ የአማራጭ-የለሾች መሰባሰቢያም እንደሆነ ይነገራል፡፡ በዚህም ሳቢያ የኛን ፖለቲከኞች ስናይ ከሙያ አንጻር እንኳን ጥቁር ሠሌዳና ጠመኔ የሰለቻቸው መምህራን ወይም አካፋና ዶማ ያንገላታቸው የቀን ሠራተኞች ወይም የቢሮ ጉዳይ አስፈጻሚ የነበሩ አውደልዳዮች እንጂ በሕዝብ አስተዳደር ዲግሪ ይቅርና ሰርቲፈኬት እንኳን ያላቸውን ለማግኘት እንቸገራለን፡፡ የኛ ሀገር ፖለቲካ ደግሞ በሩ ለማንም ዋልጌና ስድ ክፍት በመሆኑ እንደከተማ አውቶቡስ ማንም ዘው እያለ ከፍ ሲል እንደጠቀስኩት ቅርሻቱን ይለቅብናል፡፡
አንዳርጋቸው ጽጌም – ይቅርታ ይደረግልኝና – ከነዚህ ልቅ አፎችና መደዴዎች አንዱ ነው፡፡ ይህ ሰው የጭቃ እሾህ መሆኑን ለመረዳት ጊዜ ቢወስድም አሁን ላይ ብዙዎቻችን አወቅነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ውለታቢሶችን በዝምታ ማለፍ ለሌሎች ባለጌዎች በር እንደመክፈት ነውና አካፋን አካፋ ማለት ነውር የለበትም፡፡ አንድ ሰው ከመናገሩ በፊት ደጋግሞ ማሰብ አለበት፤ ዕብሪት የትም አያደርስም፡፡ በወያኔ ዘመን ታስሮ ብዙ ስቃይ ያየበትንና ከልጅነቱ ጀምሮ መከራ የቆጠረበትን የሀገር ነፃነት ትግል በአንዴ በዜሮ የሚያባዛ ንግግሩን ከዚህ በታች እንመልከትለትና ወደተጨማሪ ማብራሪያ እናምራ፡-
የመከላከያን ጭራ እየተከተልክ ያሸነፍክ ሲመስልክ .. ጀግናው ልዩ ሀይላችን ትላለህ ስትቀጠቀጥ ደሞ መከላከያ የታለ ለኔ ወግኖ ሌላ ኢትዮጲያዊን ይውጋ ትላለህ፡፡ በ‹ሆሏ ለድል ሽሚያ መሯሯጥህ አይቀርም officially declare “ወያኔ ከአቅማችን በላይ ነው
ይህ ያላንዳች ለውጥና አርትዖት(editing) በቀጥታ ከምንጩ የተገለበጠ ጽሑፍ የአንዳርጋቸው ጽጌ መሆኑ በአስተማማኝ ማስረጃ ተደግፎ በፌስቡክ ሲዘዋወር የተገኘ ነው፡፡ “ከርሱ እንዲህ ያለ ቅሌት አይወጣም” በሚል በመጠራጠሬም ሁነኛ ሰው ጠየቅሁ፤ ግን እውነት ነው፡፡ ይህ ሰው አብዷል፡፡ ጠበል ውሰዱት፡፡
ይህ ፀረ-አማራ ዝቃጭ ንግግር በ@ardii_africa ላኪ አድራሻ ለ@HabtamuAyalew21 ተቀባይ አድራሻ የተላከ ሲሆን የሚሣለቀው በአማራ ላይ ስለመሆኑ እያንዳንዱ ቃል አፍ አውጥቶ ይናገራል፡፡
አማራን ለመሳደብ አንዳርጋቸው ይህን ያህል መቃተት ለምን እንዳስፈለገው ለመግለጽ ግንቦት ሰባት ድረስ መሄድ አያስፈልግም፡፡ እዚያ ድረስ ቢኬድ ብዙ ገመና ይወጣል፡፡ ምክንያቱም ያ የኢዜማ እርሾ የሆነ የአየር በአየር ቀፋላ ድርጅት ፀረ አማራ መሆኑን በብዙ አቅጣጫዎች ያስመሰከረ በመሆኑ ወደዚያ ገብቶ መዳከር ጊዜ ማባከን ነው፡፡ እንጂ አማራን በገዛ ሀገሩና በገዛ ቀየው “መጤ ነው” ሲል በቅርቡ የተናገረውን የድርጅቱን የዕድሜ ይፍታህ ፕሬዝደንት ካሙዙ ባንዳ ብርሃኑ ነጋን ማውሳት በተቻለ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ግን ስታዘበው በእጅጉ ያባልጋል፡፡ እዚያ ላይ ሲወጡ አፋቸውን ምን እንደሚበላቸው አይገባኝም – ማን አይዟችሁ እንደሚላቸውም እንደዚሁ፡፡ የዕብሪትና ጥጋባቸው መንስዔ የሀብት ብዛት ይሁን፣ የዝነኝነት ብዛት የሚያስከትለው ሥነ ልቦናዊ ልክፍት ይሁን፣ የዕውቀት ብዛት ይሁን፣ የአስተዳደግ ጉድለት ይሁን … ምሥጢሩ ምን እንደሆነ ሳይገባኝ አንዳንድ ሰዎች አንደበታቸውን መግራት እየተሳናቸው በተደጋጋሚ ሲቀሉ አስተውላለሁ፡፡ ደግነቱ “እባብ ልቡን አይቶ እግሩን ነሳው” እንደሚባለው ይህን መሰሉን ቅምድምድነታቸውን እያዬ ይመስላል ፈጣሪም እዛው ባሉበት ድውይ አድርጎ ያስቀራቸዋል፤ ሊጨብጡት የሚፈልጉትን ነገር በማየት ብቻ ያረጃሉ፤ይሞታሉም፡፡ ላይ ወጡ የሚባሉትም መጨረሻቸው ሳያምር አንድም ለሞት አንድም ለስደት ይዳረጋሉ፡፡ አዎ፣ “እንደሠራ አይገድል” ብሎ ብሂሉ አስቀድሞ አስቀምጦታላ፡፡ ትኅትና ማንን ገደለ? ኢትዮጵያዊ ጨዋነትን ምን በላው? ይሉኝታ ወዴት ሸፈተ? የመማርና የማወቅ ትርጉሙስ ምንድን ነው?
አንዳርጋቸው ጥጌ ልክ እንደአለምነህ መኮንን አማራን ለመዘርጠጥ ይህን ያህል የደፈረው ማንን ለማስደሰት እንደሆነ በመሠረቱ ግልጽ ነው፡፡ እንደመረገም ሆኖብን ካለፉት 30 ዓመታት ወዲህ የኢትዮጵያን ፖለቲካ እንዳሻው የሚጋልበው በመለስ ዜናዊ ተቀርፆ ከ1983 ወዲህ ሥራ ላይ የዋለው አማራ ጠሉ የጎሣ ፖለቲካ ዘይቤ ነው፡፡ መለስ ቢሞትም ተረካቢው ግራኝ አህመድ ማነው አቢይ አህመድ የዘር ፖለቲካውን በሚገባ አጠናክሮ እያስቀጠለው ነው – “ካለበት የተጋባበት” ይባላል ዱሮውንም፡፡ በዚህ ፖለቲካ አንዳች ጥቅምና ሥልጣን ለማግኘት የሚቋምጥ ደጅ ጠኚ ሁሉ ታዲያ አማራን ካላንጓጠጠና ካልተሳደበ በባለጊዜዎቹ ተረኛ ዘረኞች ዘንድ የሚወደድ ስለማይመስለው ቀጭን ሰበብ እየፈለገ ሁሉም የሥልጣን ተስፈኛ አማራ ላይ ሲለፋደድ ይታያል፡፡ በሥልጣን ዙሪያ ይሉኝታ እንደሌለ ደግሞ ግልጽ ነው፡፡ ዛሬ የምትለው ነገር ከትናንቱ መቃረኑ አያሳስብህም፡፡ ጭንቀትህ ተረኛውን ኃይል ማባበልና ማስደሰት በመሆኑ ትኩረትህ ሁሉ ገዢው የሚጠላውን ወገን በስድብ ለመሞለጭ ቀን ከሌት የስድብ ክምችትህን ማደስና በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ የፈረደበት ባለተራ ተሰዳቢ ላይ መትፋት ነው፡፡ አንዳርጋቸውና ብርሃኑም ከነቢጤዎቻቸው እያደረጉት ያለው ይህንኑ ነው፡፡ ዕድሜ እማያለዝበው ትምክህት!
“አማራ ምን አድርጓችሁ ነው በተስኪያን እንደገባች ውሻ እንዲህ ጠምዳችሁ የያዛችሁት?” ተብለው ቢጠየቁ አንድም መልስ የላቸውም፡፡ “ያው የምታሸንፈውን ምታ ቢሉት ወደሚስቱ ሮጠ” እንደሚባለው ዓይነት ነው፡፡ ተጠሪ ያላቸውን ነገዶች ቢሳደቡ የሚደርስባቸውን ያውቁታል፡፡ እግዜር አይበለው እንጂ ሌሎችን ለመሳደብ አፋቸውን ቢያሞጠሙጡ ሥጋቸው በአንድ ኩርቱ ፌስታል፣ አጥንታቸው በአንድ ሌላ ኩርቱ ፌስታል ተጠቅሎ በየደጃፋቸው እንደሚጣል እነሱም ሸኔዎችም እኛም እናውቃለን፡፡ እርግጥ አማራ ለጊዜው ወኪል የለውም፤ ቢኖረውም ወደ ውራጅ የብቀላ አዙሪት እንደማይገባ ተሳዳቢዎች ሳይቀሩ ይረዳሉ፡፡ ለዚህም ነው ሁሉም በዚህ ሕዝብ ስድብ የሚለማመደው፡፡ አሁንና ዛሬ ደግሞ በገዛ ሀገሩም በየማዕዘናቱ ተወጥሮ የሚገኝ ሕዝብ ሆኗል፡፡ እንደፍቅር እስከመቃብሩ ጀግና እንደአበጀ በለው የራሱን የጎበዝ አለቃ እየመረጠ በየአካባቢው ካልተደራጀና ጠላቶቹን በጋራ ካልተጋፈጠ አማራን ካላጠፉ ሰላም የሚያገኙ የማይመስላቸው አንዳርጋቸዎች አያኖሩትም፡፡
ከፍ ሲል የተቀመጠውን የአንዳርጋቸውን መልእክት ትንሽ ልተቸው፡፡ በምሣሌም ላሳይ፡-
አንድ ሰው ታስረው የተቀመጡ ዕብድ ውሾች አሉት እንበል፡፡ እነዚያን ውሾች ፈትቶ ቢለቃቸውና ጎረቤቶቹን ቢነክሱ ተጠያቂው ማን ነው? ተጠያቂው አርፈው የተቀመጡ ውሾችን ፈትቶ ጃዝ ብሎ የለቀቃቸው ወገን ነው፡፡ ስለዚህ ለ30 ዓመታት ለጦርነትና በጦርነት የተዘጋጁ ዕብድ ወያኔዎችን አውዳሚ የጦር መሣሪያዎችን ከነሙሉ ስንቅና ትጥቅ ሰጥቶ በአማራ ገበሬ ላይ መልቀቅ ፍትኃዊም ሞራላዊም አይደለምና “ወያኔን አልቻልነውምና መንግሥት ይድረስልን” የሚል ዐዋጅ የሚያስነግር ጉዳይ አይደለም፤መሆን ያልነበረበት በመሆኑ፡፡ ከሃዲው አንዳርጋቸው ይህን ሊያውቅ ይገባል፤ ለነገሩ ልቦና ካለው ይህን እውነት አያጣውም፡፡ ለጦርነት ያልተዘጋጀውና በወያኔና በቀጣዩ የአቢይ መንግሥትም ከበፊቱ የከፋ ግፍና በደል እየደረሰበት የሚገኘው የአማራ ሕዝብ በፌዴራሉ ሁለንተናዊ እገዛ ትህነግ እንዲወረው መንግሥትን አልጠየቀም፡፡
ትህነግ ላይ ጦርነት ያወጀው የፌዴራል ተብዬው መንግሥት እንጂ የአማራ ክልል አለመሆኑ ደግሞ ይታወቃል፡፡ አማራ ያደረገው ብቸኛ ነገር የተቀማ ርስቱን ጊዜው ሲፈቅድ በደሙ ማስመለሱ ነው፡፡ አዲስ ነገር አይደለም – በጉልበት የወሰዱት በጉልበት ተመለሰ፡፡ ለአብነት ቦርሣህን ቀምቶ የሚሮጥን ቀማኛ ሌባ ስታሳድድ ቆይተህ ሌባው ድንገት ወለም ቢለውና አንድ ቦታ ቆም ቢል ዕቃህን ነጥቀህ መመለስ እንጂ በህግና በሥርዓት ያልወሰደውን ንብረትህን በህግና በሥርዓት ካላስመለስኩ ብለህ ከርሱ ጋር እንድትጓተት – እንድትጃጃል ማለትም ይቻላል – የሚመክርና የሚፈልግም ወገን ካለ መቼም የሌባው ተባባሪ መሆን አለበት፡፡ እውነቱን እያወቁ እንዲህ ባይ ፍርደ ገምድል ወገኖች አስቂኝ የአማራ ጠላቶች ናቸው፡፡ ፌዴራሉ እንደተባለው የጥሞና ጊዜ ለመስጠትና የእርሻ ወቅትን እንዲጠቀሙበትም ይሁን በሌላ ምክንያት የተኩስ አቁም ከወሰነ መከላከያው ከትግራይ ክልል ወጥቶ በትግራይ ድንበሮች መሥፈርና ሌሎች ክልሎችን ከወያኔ ጥቃት መከላከል ነበረበት እንጂ በሽሽት ሽምጥ ሊጋልብ ባልተገባው ነበር – ለዚያውም ከባድ የቡድንና የተናጠል ሜካናይዝድ የጦር መሣሪያዎችን እየተወ፡፡ መከላከያው በተናጠል ተኩስ አቁም ሰበብ ትግራይን በመልቀቅ ሌሎች ክልሎችን ለወያኔ ጥቃት ዳርጎ ከሸሸ እነአንዳርጋቸው የሚያውቁት ሌላ ጉዳይ አለ ማለት ነው እንጂ አንዱ የጀመረውን ጦርነት ሌላው እንዲቀጥል የሚደረግበት አግባብ የለም፡፡ ጦርነት በውርስ የሚተላለፍ የሰንበቴ ጽዋ ማኅበር አይደለም፡፡ ለማንኛውም አቶ አንዳርጋቸውም ሆነ ግብረ አበሮቹ የኢዜማ አንዳንድ ሰዎች ይህን ምሥኪን አማራ ለቀቅ አድርጉት፡፡ ጥላቻችሁንም ገደብ አብጁለት፡፡ ነገ እንዳንተዛዘብና ቡና እንኳን መጠራራት እንዳይከብደን ይህ ጨለማ እንደሚያልፍ ቆም ብላችሁ አስቡና አደብ ግዙ፡፡ መረጋገሙ ዋጋ እንደሌለው ከመረዳት አኳያ ሆን ብለን ተውነው እንጂ አማራን የምትጠሉና ገዢዎችንም ሆነ የስንኩል ተፈጥሯችሁን የተንሻፈፈ ሥነ ልቦና ለማስደሰት ስትሉ ዘወትር አማራን የምትሳደቡ ወገኖች “ልጅ አይውጣላችሁ፤ ጥቁር ውሻም ውለዱ!” ብለን መራገም አቅቶን አይደለም፡፡ አንድን ግለሰብ መሳደብ ተገቢ ባይሆንምና ባይመከርም መሳደብ ግን ይቻላል፡፡ አንድን ማኅበረሰብ ካላበሳው መወረፍ ግን ነውር ብቻ ሣይሆን ወንጀልም ሃይማኖት ካላችሁ ደግሞ ኃጢኣትም ነው፡፡ አማራን ከወደቀ ግን ጋር አመሳስላችሁት ከሆነ ደግሞ ተሳስታችኋልና በቶሎ ታረሙ፡፡ የአቢይ ኦሮሙማ እንደሆነ አማራን መሳደብ ቀርቶ ብትገድሉለትም እንደውለታ አይዝላችሁም፤ ከፍላጎቱ አንዳች ነገር ብታፋልሱ – እናንተም ታውቁታላችሁ – ተራችሁን ጠብቆ ገቢ ያደርጋችኋል፡፡ ለማንም የሚራራ አንጀት ኢንቀብዱ፡፡ ለሰላማዊው ታጋይ ለእስክንድርና ጓደኞቹ ያልተመለሰ ብዔልዘቡል ለእናንተም የሚመለስ አይደለም፡፡ የጎንደርንና የወሎን አማራ በጅምላ አጥፍታችሁ ለሽልማት ብትቀርቡ በሸኔው ይቆላችኋል፡፡ አማራንና አማርኛን ብትጠሉትም በተረት እንደጀመርኩ በተረት ልጨርስ – “አገባሻለሁ ያለ ላያገባሽ ከባልሽ ሆድ አትባባሽ፡፡” ተግባባን?