አክሎግ ቢራራ (ዶ/ር)
ክፍል ሰባት
የችግሩ እምብርት ምንድን ነው?
አሁን ያለንበትን ሀገራዊ ቀውስና ለቀውሱ መውጫ መንገዶችን ከመመልከታችን በፊት፤ ‹‹ኘገርን ከሥሩ፤ ውሃን ከጥሩ›› እንዲሉ፤ የችግሩን መነሻ ወደኋላ ጥቂት ዓመታትን ተመልሰን እንድንመለከት ያስፈልጋል፡፡
ባለፉት 40 ዓመታት በተከታታይ ኢትዮጵያ እጅግ በጣም የሚዘገንን እልቂትና ማህበረሰባዊ ቀውስ የተካሄደባት አገር ሆናለች። የፖለቲካ ሥልጣኑን በኃይል የተጎናጸፉት መሪዎች ሥርዓተ መንግሥታቸውን የመሠረቱት በዜግነት፤ በጋራ ብሄራዊ መለያ፤ ማለትም በኢትዮጵያዊነት ላይ ሳይሆን፤ ግጭትንና የእርስ በእርስ ጦርነትን በሚፈጥር፤ በብሄር ልሂቃን መካከል መረን የለቀቀ (Ethnic political and social elites) የተፈጥሮ ኃብት ሽሚያን የተለመደ በሚያደርግ፤ ለእርቅ፤ ለሰላም፤ ለእርጋታ፤ ለህግ የበላይነት፤ ለአብሮነት፤ ለዘላቂና ፍትሃዊ ልማት መሰናክል በሆነ የፌደራል ስርዓት ነው። ይህ ሕዝብ ድምጽ ሳይሰጥበት የመስረቱት ስርአት ኢትዮጵያን የሲኦል አገር አድርገጓታል። የሲኦል አገር ስል ሰው በሰላም ወጥቶ የማይመለስባት፤ በነጻነት የማይኖርባት፤ ሠርቶ በቂ ገቢ የማያገኝባት፤ ህገ ወጥነት በተለይም መንግሥታዊ ህገወጥነት የነገሰባት፤ የአስተዳደር ብልሹነት የበከላት ወዘተ ማለቴ ነው። በሁሉም ዘርፍ የተባረከች የነበረችዋን አገር፤ በገዥዎቿ ጨካኝነትና አምባገነንት ተበክላለች። ለዚህ ነው የሲዖል አገር የተባለችው፡፡
ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ አሊ ሥልጣን ከያዘበት ወዲህ የአንድ ጎሳ ልሂቃን የበላይነት የአንበሳውን ድርሻ አንዲይዝ ተደርጓል። ይህ የአንድ ጎሳ የበላይነት ስር ነቀል የሆነ ተቋማዊና መዋቅራዊ ለውጥ ፈጥሯል። የኦህዴድ ብልጽግና የኢትዮጵያን ህብረ-ብሄረሰባዊ ስርጭት ኢ-ሚዛናዊ፤ ኢ-ፍትሃዊ እና እ-ዲሞክራሳዊ በሆነ ደረጃ ስላናደው፤ የአንድ ዘውግ ብዝሃታዊነት (Single ethnic group majority) በሁሉም ዘርፎች የበላይነቱን ለዘላለም እንዲይዝ አመቻችቶታል።
ከአሁን በኋላ በኢትዮጵያ የዲሞክራሲ ስርዓት ቦታ እንዳይኖረው መወሰኑን ለመገንዘብ አያስቸግርም። ምርጫ የሚካሄደው ለይስሙላ ይሆናል ማለት ነው። የኦሮሞ ልሂቃን በሥልጣን ቢለያዩም ቅሉ፤ በዚህ የአንድ ጎሳ የበላይነት ላይ ግን ይስማማሉ። የኢትዮጵያ ፖለቲካ የቁጥር ፖለቲካ ሆኗል።
ይህ ሁኔታ ዱብ እዳ አይደለም። እዚህ የደረሰበት የራሱ ሂደትና ታሪክ አለው። ሕዝብ በራሱ ፈቃድ በምርጫ ተሳትፎና ድምጽ ሰጥቶ ሳይወክለው ሥልጣን የወሰደው የህወሓት/ኢህአዴግ መንግሥት ከተመሰረተበት 1983 ዓ.ም ወይም እ.አ.አ 1991 ወዲህ፤ በብሄርና በቋንቋ የተዋቀረው ሕገ መንግሥትና የክልል አስተዳደር ዘውግ ተኮር እልቂትን፤ አፈናን፤ መፈናቀልን፤ እስራትን፤ ድህነትን አባብሶታል። ህወሃት መሩ መንግሥትና ህወሃትን የተካው የኦህዴድ/ብልጽግና መንግሥታት፤ በግልጽ ጸረ-ሕዝብንትን፣ ጸረ-አማራነትን፣ ጸረ-ኢትዮጵያዊነትን፣ ጸረ-የዜጎች እኩልነትን፣ ጸረ-ሰብአዊ መብትን፣ ጸረ-የህግ የበላይነትን እና ጸረ-ዴሞክራሳዊ አገዛዝን መመሪያቸው አድርገውታል። የሚከተሉት መርህ ብሄር ተኮር በሚል ካባ የጠባብ ቡድን ጥቅምን ማስጠበቅ ነው። ሁለቱም የሚጋሩት የጋራ ባህሪያቸው ደግሞ ጸረ-አማራነትን ሁለቱም የሥርዓታቸው ዋና ማጠንጠኛ ማድረጋቸው ነው። ይህ ለዲሞክራሲ መሰናክል መሆኑ አያከራክርም። ቁጥርን መዋቅራዊ ለማድረግ የጠላትን ቁጥር መቀነስ ያስፈልጋል።
ለምሳሌ፤ በሰሜኑ ጦርነት ወደ አንድ ሚሊየን የሚገመት የትግራይ ወጣት ደም ፈሷል። ጦርነቱ የተካሄደው በህወሃትና በዐብይ አህመድ ሰራዊት መካከል ነው። ለእልቂቱ ተጠያቂ ማነው? ተብሎ ሲጠየቅ ግን ተከሳሽ ተደርጎ የቀረበው አማራው ነው። በሌለበት፤ ባልሰራው ወንጀል፤ ጭራሽ ‹‹አማራውን ሒሳብ አወራርድበታለሁ›› እየተባለ በተዘመተብት፣ ክልሉን 30 ዓመት ወደኋላ የጎተተ ኪሣራ በደረሰበት፣ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ልጆቹ በተገደሉበት፣ በቆሰሉበትና በተደፈሩበት፤ የሁለቱ ነውረኞችን ሀጢአት ለእሱ (ለአማአራው) ተሰጠው፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብ በጋራ ሰላማዊ ሰልፎች አካሂዶ ጠባብ ብሄርተኛውን ሀወሃትን ከስልጣኑ ሲያስወግደው፤ እድሉን ተጠቅሞ በተለይም በአማራ ህዝብ አንቀልባ ታዝሎ፤ የመንግሥት ሥልጣኑን የተረከበው፤ እውነተኛ የህዝብ ወኪል የሆነ ሀይል ሳይሆን፤ ‹‹አባቴ በአለንጋ ገርፏችኋል፤ እኔ በጊንጥ እገርፋችኋለሁ፡፡ የእኔ ትንሽ እጣት ከአባቴ ወገብ ትወፍራለች›› ብሎ፤ ከህወሓትም የባሰ ነውረኛና ዘረኛ መሆኑን ያሳየው ኦህዴድ/ብልጽግና ነው፡፡
ይህ ቡድን ደጋግመን እንደተናገርነውም ሆነ፤ እስኪበቃን በድርጊቱ እንዳረጋገጠልን፤ ጠባብ ብሄርተኛ ነው። ኦህዴድ/ብልጽግና የብሄር ልዩነቶችን አባብሶ የአንድ ብሄር፤ ማለትም የኦሮሞ ልሂቃን የበላይነትን እመሰርታለሁ ብሎ በህዝቡ ስም እየነገደ የራሱን ጥቅም ለማስጠበቅ ወንጀል የሚሠራ ቡድን ነው። ብሄራዊ ወይም አገራዊ ተቋማትን አፍርሶ፤ የአንድ ጎሳ ተቋማትን ለማጠናከር ብዙ ርቀት ተጉዟል፤ በአንዳንዶቹ ሲሰካለት በቀሪዎቹ ገና ውጤታቸው አልታየም፡፡ በጠባብ ብሔርተኝነት ቅኝት ሥራው ስኬታማ የሆነለት በራሱ አምሳል የቀረጸው የዐብይ መከላከያ ኃይል ነው።
ዐብይ አህመድ ‹‹አይዟችሁ እኔ ኢትዮጵያን አሸጋግራታለሁ›› ብሎ እንደ ተናገረ ታሪክ ይመሰክራል። ሥልጣኑን ካመቻቸ በኋላ ያደረገው ግን ተቃራኒውን ነው፤ ማለትም በአንድ ብሔር የበላይነት የሚያምኑ ልሂቃንን ፍላጎትና የራሱን ሥልጣን መደላድል ነው ያሰፈነው፡፡ ያሻገረውም፤ ኢትዮጵያን ከድህነትና ኋላቀርነት እንዲሁም ከጭቆና ወደ ልማት፣ ሰላምና ዴሞክራሲ ሳይሆን፤ የራሱን የሥልጣን ጥም፤ ከምኞት ወደ እውንነት ነው ያሸጋገረው፡፡ በመንግሥት ደረጃ የጭካኔው ዒላማ ያደረገው ደግሞ አማራውን ነው። ይህንን በተከታታይ ስድስት ትንተናዎቸ በመረጃ አስደግፌ አቅርቤዋለሁ፡፡
ቀደም ሲል እንደገለጽኩት፤ ህውሃትና ኦህዴድ ብልጽግና የሚጋሩት አንድ መሰረታዊ ሃቅ፤ ሁለቱም ጸረ-አማራና ጸረ-ኢትዮጵያዊነት ናቸው። በሌላ አነጋገር ጠባብ ብሄርተኛ የፖለቲካ ድርጅቶች ናቸው። የነጻነት ግንባር ሆኖ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን ለመታደግ አይቻልም። ኢትዮጵያን የመታደግ ፍላጎትና ምኞት ያለው ሀይል፤ ከመጀመሪያውም ጠባብ ብሔርተኛ መሆን አይችልም፡፡ ሥልጣናቸውና ጥቅማቸው እስካልተነካ ድረስ፤ ኢትዮጵያን እንደ ሃገር ይቀበላሉ። ሥልጣናቸው ከተነካ ግን ይህች ረዥም ታሪክ ያላት አገር ብትፈራርስ አያስጨንቃቸውም።
የአገር ውስጥና የውጭ ተመራማሪዎች እና ታዛቢዎች የሚስማሙት፤ የኢትዮጵያ የዘውግ ፌደራል ስርዓት ኢትዮጵያን ወደማትመለስበት የመፈራረስ አደጋ እየወሰዳት በመሆኑ ላይ ነው።
በሰሜን በኩል ከህወሃት ጋር የተካሄደው ጦርነት፤ ከዚያ ወዲህ በአማራውና በኦሮሚያ ክልሎች የሚካሄዱት ጦርነቶች፤ በብሄርና በሀይማኖታቸው ምክንያት ከአራት ሚሊየን በላይ የሚቆጠረው የተፈናቀለው ህዝብ ብዛትና ብሶት፤ በሰላም ወጥቶ መግባት ብርቅ መሆኑ ወዘተ የመንግሥቱን ባህሪይና አገር የማስተዳደር ድክመቶች ያሳያል።
ባጭሩ፤ በአብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ አመለካከት የኦህዴድ/ብልጽግና መንግሥት ቅቡልነት እና አመኔታነት መጨረሻ እርከን ላይ ደርሷል። ይህ መንግሥት ራሱን ገምግሞ የስርአት፤ የተቋምና የመዋቅር ለውጥ ለማድረግ ፈቃደኛ መሆኑ ያጠራጥረኛል። ዐብይ አህመድ “እመኑኝ፤ አሸጋግራችኋለሁ” ካለን በኋላ ወደ የት እንዳሸጋገረን አይተናል። በፍጹም አይታመንም። በርግጥ አስቀድሞም ቢሆን፤ ‹‹የሚፈልጉትን እየተናገርክ፤ ወደምትፈልገው ውሰዳቸው›› ሲል በመጽሀፉ ያሰፈረ የሴራና የተንኮል ሊህቅ ነው፡፡
- የሽግግርመንግሥት ምን ማለት ነው?
ጥናቶችና ልምዶች የሚያስተምሩን የሽግግር መንግሥት አስፈላጊ የሚሆንበት መሰረታዊ ምክንያት፤ ሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት አገሪቱን ለማስተዳደር፤ ሰላምና እርጋታን ለመፍጠርና ስኬታማ ለማድረግ ፍላጎት፤ ብቃትና ችሎታ ሳይኖረው ሲቀር ነው።
በዚህ መርህ ካየነው፤ በኢትዮጵያ ያለው አሁናዊ ሁኔታ ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ነው፡፡ የእርስ በእርስ ጦርነት ተባብሷል። ሰው ከቤቱ ወጥቶ ለመግባት አይችልም። የኑሮ ውድነት ሰው ወደማይችልበት ደረጃ ተሸጋግሯል። ነዳጅ ውድ ስለሆነ ተሽከርካሪዎች በሚያሰጋ ደረጃ መንቀሳቀስ አልቻሉም። አርሶ አደሩ ሊያመርት አልቻለም። ነጋዴው ሊነግድ አልቻለም።
አርሶ አደሩ ማምረት ያልቻለው ደግሞ በሶስት ምክንያት ነው፤ የመጀመሪያው ምክንያት፤ አርሶአ ደሩን የዐቢይ መንግሥት ሚሊሻ አድርጎ እያስገደለው በመሆኑ፤ ሁለተኛ፤ የአርሶ አደሩ ማሳ የውጊያ ቀጠና እንዲሆን በማድረጉ እና በሶስተኛ ደረጃ ደግሞ፤ ውጊያ በማይካሄድበት ቀጠና የሚኖረውም ሆነ ከጦርነት ውጭ ሆነው አርሶ አደር አርሶ እንዳይዘራ፤ የአፈር ማዳበሪያን ሆን ብሎ ስለከለከለው ነው፡፡
በማክሮ እኮኖሚ ፖሊሲው ግራ የተጋባው የዐብይ መንግሥት፤ ማንኛውንም ለህዝብ የሚሰጠው ድጎማ (ድጋፍ) ሁሉ ከራሱ የሥልጣን ህልውና አንጻር እንጂ፤ ከዜጎቹ ኑሮና ህይወት መናጋት አንጻር አይደለም።
የብር የመግዛት ጥቅም 99 በመቶ የወረደበት ምክንያት ምንድን ነው? ብላችሁ ጠይቁ። ነዳጅን በሚመለከት በኢራን ላይ የሚካሄደው ጦርነት በተባባሰበት ወቅት፤ በቀን ከሚሰጠው ከዘጠኝ ሚሊየን ሌትር በአንድ ጊዜ ወደ አራት ነጥብ አምስት ሚሊየን ወረደ? ብላችሁም ጠይቁ። የዐብይ አማካሪዎች የሚያስከትለውን ቀውስ አስቀድመው ለመገምገም ያልፈቀዱበት ምክንያት ምንድን ነው? ወይስ እሱ ራሱ የአማካሪዎቹን ምክር ሊቀበል ስለማይችል ነው?
ትምህርት ለዜጎች ህይወት ወሳኝ መሆኑን መላው ዓለም ከተቀበለው የዐብይ መንግሥት ለምንድን ነው ከ11 ሚሊየን በላይ የሚገመት ወጣት፤ የትምርህት እድሉን የዘጋበት? ብላችሁ ጠይቁ። ይህንን ቁጥር ከኤርትራ ሕዝብ ቁጥር ጋር ብናነጻጽረው የኤርትራ ከሰባት ሚሊየን በታች ነው። የጂቡቲ አንድ ሚሊየን ሁለት መቶ ሽህ ነው። የሁለቱ አገሮች ድምር የትምህርት እድል ከተነፈገው የኢትዮጵያ ወጣት ትውልድ በታች መሆኑ ነው። አስቡት።
የኦህዴ/ብልጽግና አባላት ልጆች ይማራሉ፤ የድሃው ልጅ ግን አይማርም። ይህ የሚዘገንን ታሪክ የሚያወሳው ወንጀል ነው።
ያለ ነዳጅ ዘመናዊ ኢኮኖሚ አይንቀሳቀስም። አል ጀዚራ በApr 26, 2026 ያቀረበው ዘገባ እንዲህ ይላል። “Ethiopia is facing a deepening fuel crisis as the war on Iran and closure of strait of Hormuz drives up global oil prices and disrupts supply chains. In Addis Ababa, drivers queue fordays at petrol stations often only to find no fuel available, leaving taxis and lorries stranded.”
መጓጓዢያ ከሌለ ኢኮኖሚው ህይወት አይኖረውም። አል ጀዚሪያ እንዲህ ይላል። “Transport shortages have pushed up food prices by nearly 40 percent, with markets struggling to explain daily increases to customers. Export-dependent businesses report shipping costs have more than doubled, threatening their viability. Ethiopia imports nearly all its fuel from the Gulf region, making it acutely vulnerable to the economic shockwaves of distant conflict.”
የምግብ ዋጋ አርባ በመቶ ከፍ ሲል ማን ይጎዳል? ብላችሁ ጠይቁ። ብልጽግናዎች በልተው ያድራሉ። አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ በምግብ እጥረት ይሰቃያል።
ጥናቶችና ምርምሮች የሚነግሩን የነዳጅ አቅርቦት ቀውስ በቀላሉ የሚፈታ አይደለም። እንኳን ድሃዋ ኢትዮጵያ ይቅርና፤ የአሜሪካ ህዝብም እየተማረረ ነው። የነዳጅ ዋጋ መናር ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለመላው ዓለም አሰቃቂ ሁኔታ ፈጥሯል። የሚዋጣው አማራጭ በመካከለኛው ምስራቅ የሚካሄደውን ጦርነት ለሁሉም አገራት በሚጠቅም ሁኔታ መፍታት ብቻ ነው።
የኢትዮጵያው “ከእንቅርት ላይ ጀሮ ድግፍ” እንዲሉ፤ የዐብይ ኦህዴድ ብልጽግና መንግሥት ደግሞ፤ ችግር ፈጣሪ እንጂ መፍትሄ ፈላጊ መንግሥት አለመሆኑን ያሳያል። የሚከተለው ፖሊሲ የዳበሳ ጉዞ ሆኗል። ይኼ ብቻ አይደለም፤ እኔን ቀን ከሌት የሚያሳስበኝ የኦህዴድ/ብልጽግና መንግሥት ለወጣቱ ትውልድ የስራ እድል ለመፍጠር የሚቻልበትን ሁኔታ ለመፍጠር አለመቻሉ ነው። በኔ ግምገማ ይህን ለማድረግ የዐቢይ መንግሥት፤ ችሎታም ሆነ ፈቃደኝነትም የለውም። አብዛኛው ወጣት ትውልድ በኢትዮጵያ የወደፊት ሁኔታ ተስፋ ቆርጧል።
ከጥቂት የሥርዓቱ ተጠቃሚ የኦሮሞ ተወላጆች በስተቀር፤ አብዛኛውን የኦሮሞ ህዝብ ጨምሮ፤ መላው የኢትዮጵያ ህዝብም በዐብይ መንግሥት ላይ ተስፋ ቆርጧል። በአማራው ላይ የሚካሄደው ግፍና በደል በራሱም ላይ እየደረሰበት መሆኑን ተገንዝቧል። የደቡቡብ ሕዝብ፤ ጌዴኦው፣ ሲዳማው፣ ጉራጌው፤ ወላይታው፤ ጋሞው፤ አኝኩና ሌላውም ብሔረሰብ በማያሻማ ደረጃ፤ በአንድ ዘውግ እንደሚዋጥ ተገንዝቦታል።
የአገር ውስጥ ቀውሱን ከቀጠናው ጋር የማያያዝ ግዴታ አለብን። የአፍሪካ ቀንድ የጆኦፖለቲካ ሁኔታ በየለቱ በመቀየር ላይ ነው። ይህ እድልም አለው፤ ስጋትም አለው። የኔ ዋና ትኩረት በእድሉ ላይ ነው። ኢትዮጵያ ከጎረቤት አገሮች ጋር በመቻቻል፤ በጋራ ጥቅም፤ በሰጥቶ መቀበል ላይ የተመስረተ መርህ መከተል አለባት። ከሱዳን የእርስ በእርስ ጦርነት መማር አለባት። የራሷን ብሄራዊ ጥቅም መሰረት አድርጋ የጎረቤት አገሮችንም ጥቅም የማክበር ግዴታ አለባት። ይህ የሚሳካው በጦርነት አይደለም። በዲፕሎማሲ፤ በፖለቲካ ውይይትና ድርድር ነው።
እኔ ተስፋ የማደርገው በዘላቂነት ለኢትዮጵያና ለኤርትራ ሕዝብ የሚያዋጣቸው መቀላቀል ወይንም አንድነት ነው። በፌደሬሽን ሆነ በውህደት ሕዝቡ ሊወስን ይችላል።
በኔ እምነት የአማራ ፋኖ፤ ኤርትራን ጨምሮ፤ ከቀጠናው ሀይሎች ጋር በኢትዮጵያና በአማራ ሕዝብ ዘላቂ ጥቅም ላይ መሠረት ያደረገ ትብብር እንዲያደርግ እመክራለሁ።
ይህን ለማድረግ የሚችለው ግን በአማራ ፋኖ መሪዎች መካከል የሚታዩት አራት ክስተቶች ሲፈቱ ነው፤
አንደኛ፤ የሥልጣን፤ የጥቅም፤ የመንደርተኛነት ገመድ ጉተታ ሙሉ በሙሉ ሲቆም ነው። በተለይ በጎንደር። የጎንደር ፋኖ በብልጽግናና በሌሎች ኃይሎች ተጠልፏል የሚል እምነት አለኝ። ይህ ለጎንደሬው ልሂቃን አሳፋሪ ብቻ ሳይሆን፤ ጎንደርን ዳርፉር ሊያደርጋት ይችላል።
ሁለተኛ፤ አፋብን ጥራት፤ ግልጽነት፤ ቅቡልነትና ከሌላው ኃይል የሚለየውን የፖለቲካ ፍኖተ ካርታ ቀርጾ ለሕዝብ ሲያቀርብ ነው። ይኼ ለነገ የሚባል ጉዳይ አይደለም።
ሶስተኛ፤ አፋብን በተናጥል ኢትዮጵያን ለመታደግና ለማደስ የማይችል መሆኑን መቀበል አለበት።
መጀመሪያ መቀመጫየን እንዳለችው ዝንጀሮ፤ በድሬደዋ፤ በሃረር፤ በአዲስ አበባ፤ በወለጋ ወዘተ ከሚኖረው የአማራ ብሶተኛና ታጋይ ጋር በረቀቀና ጥንቃቄ ባለበት ደረጃ ግንኙነት መመስረት አለበት። በተጨማሪ፤ በደቡብ፤ በአፋር፤ በሶማሌ፤ በቤኒ ሻንጉል ጉሙዝ፤ በጋምቤላ፤ በወላይታ ወዘተ ከሚገኙ የፋኖን አላማ ከሚጋሩት ጋር የውስጥ ግንኙነት መመስረት አለበት። ስልጠናም የሚሰጥበት እድል አለው።
ሕዝባዉ እምቢተኛነት እንዲቀቀስ ለሚደረገው ዘመቻ ትኩረት መሰጠት አለበት።
አምስተኛ፤ የኦህዴድ ብልጽግና አገዛዝ መፍረሱ የማይቀር መሆኑን መገንዘብ አለበት።
ለሚፈርስ መንግሥት የሽግግር መንግሥት ዝግጅት ወሳኝ ነው። አፋብን ግዙፍ የሆነ ሚና ሊጫዎት ይችላል። አማራው በተደጋጋሚ እንዳይሸወድ ቅድመ ዝግጅት ያስፈልጋል።
እነንዚህንና ተዛማጅ ስራዎችን ለመስራት አፋብን ራሱን መገምገም አለበት።
እኔን የሳበኝ የቅርብ ክስተት፤ አፋብን ከህዝቡ ጋር የሚያደርገው ውይይት ነው። አመራሩ ከሕዝቡ ብዙ ሊማር ይችላል። ህዝቡ የሚሰጠውን ምክር ይተግብር። በቅንነት ያገልግል፤ ታዛዢ ይሁን። ትግሉን ከአማራው ክልል መጥቆ ያውጣው። በኃይል አሰላለፍ በኩል አፋብን ጠላቱንና ወዳጁን ይለይ።
ዋናው መርህ የአማራውን ህዝብ ሰቆቃ መገንዘብና ከዚህ አሰቃቂ ሁኔታ እንዲላቀቅ ቀን ከሌት መስራት ነው።
ለሽግግር መንግሥት ምስረታ አግባብ የሚኖረው መርህ፤ “ነጻ አውጭ ግንባሮች” ማኒፌስቶቻቸውን በማስተካከል በዜግነት መብት ላይ ትኩረት ሲያደርጉና የዜግነት መርህን ሲቀበሉ ነው። ይህ ግፌት ይጠይቃል።
አፋብን ይህንን አቋሙን ግልጽ ማድረግ አለበት። የአማራ ብሄርተኛነት ለአደራጃጀት እንጅ የፖለቲካ መርህ ሊሆን አይችልም። የአፋብን መርህ ከነጻ አውጭ ብሄርተኛነት የሚለይበት ምክንያት ግልጽ መሆን አለበት። በመላው ኢትዮጵያ የሚኖረው አማራ በኢትዮጵያዊነቱ የሚያምን ሕዝብ ነው። ከኦህዴድ ብልጽግናና ከሌላው ጠባብ ብሄርተኛ የሚለየውም በዚህ መስፈርት ነው።
ኢትዮጵያዊነቱ አማራውን ለአደጋ እንዳጋለጠው አውቃለሁ። በዘላቂነት ስመለከተው ይህ እሴት በኢትዮጵያ ዘላቂነት ለሚያምኑ ሁሉ መሰረት ነው። አለያ አንድ አገር ሊኖረን አይችልም። አንድ አገር አለን ካልን የሚለየን የዜግነት መለያችን ኢትዮጵያዊነት ብቻ ነው። አማራዊነት አይደለም፤ ትግራዊነት አይደለም፤ የኦሮሞ “ብዝሃታዊነት” ወዘተ አይደለም።
ነጻ አውጭ ግንባሮች “ነጻ” የሚወጡት ከራሳቸው የውስጥ አፋኞች፤ ሌቦች፤ ሙሰኞች፤ ጠባብ ብሄርተኞችና አምባገነኖች እንጂ ከአማራው ሕዝብ አለመሆኑን መቀበል አለባቸው። በተመሳሳይ፤ የአማራ ፋኖ የአማራውን ህልውና ከመታደጉ በተጨማሪ ለሁሉም ዜጎች መብት፤ እኩልነትና ፍትህ የቆመ መሆኑን በተደጋጋሚ ለመለው የኢትዮጵያ ህዝብ ማስረዳት አለበት።
ከዚህ ላይ ላሰምርበት የምፈልገው መርህ፤ የአማራ ፋኖ ከነጻ አውጭ ግንባሮች የሚለይበት ዋና ምክንያት፤ ነጻ አውጭ ግንባር አለመሆኑን ነው። የሚመሰርተው የአማራ መንግሥት አይደለም። የሚታገለው ለፍትህ፤ ለእኩልነት፤ ለዜግነት መብት፤ ለአብሮነት ወይንም ኢትዮጵያዊነት እና ለእውነተኛ የዴሞክራሲ ስርዓት ነው።
ይህንን መርህ የሚያጠናክር ምሳሌ ላቅርብ፤ በደቡብ የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ራሳቸውን “ፋኖ” ብለው የሚጠሩት አማራ ስለሆኑ ሳይሆን፤ የአማራ ፋኖን መርህ ስለሚጋሩት ነው። እኔ ይህንን እንቅስቃሴ እደግፋለሁ።
የሽግግር መንግሥትን ለመመስረት ቅድመ ዝግጅት መደረግ አለበት። በእሴቶችና በመርሆዎች ላይ ስምምነት ያስፈልጋል።
ይቀጥላል
May 8, 2026