ይኄይስ አእምሮ
የሀገራችንን ወቅታዊ ሁኔታ ለመግለጽ ብዛታቸው ከሰባት ሺህ ለሚያልፉት የዓለማችን ቋንቋዎችም አስቸጋሪ ነው፡፡ “ለቤት ቀጋ ለውጭ አልጋ” የሆነው ከጥልቁ የጨለማው ዓለም የተላከብን አቢይ አህመድ የተፈቀደለት የቅጣት ዘመን እስኪጠናቀቅ ድረስ የማናየውና የማንሰማው ጉድ እንዳይኖር ተፈርዶብናል፡፡ በተለይ ከትምህርቱም፣ ከዕውቀቱና ጥበቡም፣ ከማስተዋሉም የተነጠለው ይህ ወፈፌ አቢይ አህመድ ወደ ሥልጣን ከመጣበት ከ2010 ወዲህ አንዲት የነበረችው ኢትዮጵያ ሁለት ሆናብን የተቸገርን እጅግ ብዙ ነን፡፡ የማንና የማን ኢትዮጵያ እንደምላትም ይቸግረኛል፡፡ በዘር እንዳልመድባት የሁሉም ዘሮች ማለትም ነገዶች አባላት በሁለቱም ኢትዮጵያዎች ውስጥ ይገኛሉ፤ ቁጥራቸው ቢለያይም፡፡ በሃይማኖትም ሆነ በቋንቋ እንዳልመድባትም እንደዛው፡፡
እኔ የምገኝባት ኢትዮጵያ ዜጎቿ ሰማይና ምድር ተደፍቶባቸው ውለው ማደራቸውም ሆነ አድረው መዋላቸው እንደተዓምር የሚቆጠርባት በማንኛውም የስቃይና የመከራ ዶፍ ሲዖልን የምታስንቅ ናት – ለአብነት ሲዖል ውስጥ ቢያንስ በሣምንት አንድ ቀን ዕረፍት እንዳላቸው በቀልድም ቢሆን ይነገራል፤ እኛ ግን በሣምንት ቀርቶ በአሥራዎች ዓመታትም የደቂቃ እንኳን ዕረፍት የለንም፡፡ በዚህ ጎራ ውስጥ ለሚገኙ ዜጎች ራበኝ ጠማኝ በረደኝ ታረዝኩ ብሎ መናገር ራሱ እንደቅንጦት ይቆጠራል፡፡ እነዚህ ወገኖች እንደዜጋ ሣይሆን የኦሮሙማው መንግሥት የጥይት ተኩስ ዒላማ መለማመጃነት ወይም አንገታቸውን በሜንጫ በመቅላት የማረድ ልምምድን መማሪያነት እስከሚጠቀምባቸው ድረስ ከቀሪው የእንስሳት ዓለም ሳይቀር የወረዱ ከንቱ ፍጡራን ናቸው፤ ነን፡፡ በዚህ ምድብ አማሮች ቁጥር አንድ ሰለባ መሆናቸው ደግሞ ግልጽ ነው፡፡ ለነገሩ ኦሮሞ ሆነህም ሰው ልሁን ብለህ የጤናማ አስተሳሰብ ባለቤት ልሁን ካልክ አንተም አይቀርልህም፤ እንደለዘብተኛ የሩዋንዳ ሁቱ በክብር ትገደላለህ፡፡ በዚህ አጋጣሚ የክብር ሞትና የውርደት ሞት መኖሩንም ተረዱልኝ፡፡ አማራን ገድለው ሬሣውን ይጫወቱበታል – እነአባ ሜንጫ፡፡ ሥራቸው የግፍ ግፍ ነው፡፡
ቀደም ሲል በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች በሚኖሩ አማሮች ላይ ኦሮሙማውና እነሱን የፈጠራቸው ሕወሓት በርካታውን አማራ ገድለውታል፤ አፈናቅለውታል፤ ሀብት ንብረቱንም ቀምተውና አውድመው በሕይወት ያለውንም ባዶውን አስቀርተውታል፡፡ አሁን ደግሞ ወያኔው ሰፍሮና ለክቶ በሰጣቸው አማራ በሚባለው ክልል ውስጥ በዐርባና ሃምሣ ዙር የሰለጠነው የኦሮሙማ ኮማንዶ ወደቀያቸው ሄዶ በየደጃፋቸው እየረፈረፋቸው ነው፡፡ ግድያውና ውድመቱ በሰዎቹ ብቻም ላይ አልተወሰነም፡፡ መንግሥታዊ ታኅታይና ላዕላይ መዋቅሮቻቸው፣ የጤናና የትምህርት እንዲሁም ፖሊስ ጣቢያንና ፍርድ ቤትን የመሰሉ የፀጥታ ተቋሞቻቸው፣ የእህል ክምራቸው፣ የዐውድማ ሰብላቸው፣ የጎተራና የጉድጓድ እህላቸው፣ ማሣ ላይ የሚገኝ የእህል ቡቃያቸው፣ የቤት እንስሳታቸው፣ ዛፎችና ተክሎቻቸው በሙሉ ከምድረ ገጽ እንዲጠፉ ተፈርዶባቸዋል፡፡ በዚህ ደረጃ አንድ ሕዝብ ላይ የዘመተ ዘረኛ መንግሥት በዓለማችን ታሪክ መቼም ታይቶ አያውቅም፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፡፡
ይሄ የሞት ምድብ ጦርነት በሌለባቸው አካባቢዎች ቢኖር እንኳን ችግሩ መልኩን ቀይሮ ዜጎች በቁም እንዲቀጡ ኦሮሙማው ሌት ተቀን የማያንቀላፉ የሲዖል ትሎችን እየላከ ቁምስቅላቸውን ያሳያቸዋል፡፡ ደምብ አስከባሪ የሚባሉ ዘራፊዎችንና በአብዛኛው ከኦሮምያና ከደቡብ የተመለመሉ ምግባረ ብልሹ ሰገጤ ፖሊሶችን ሕዝብ መሀል በማዝመት በተለያዩና ቁጥር ሥፍር በሌላቸው ደምቦችና ህጎች ሕዝቡን መፈጠሩን እስኪጠላ ማሰቃየት የኦሮሙማ ትልቁ መገለጫ ነው፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ አንድ ሰው በገዛ ሰውነቱ ሳይቀር መብት የለውም፡፡ እንዴት መራመድ፣ እንዴት መተንፈስ፣ እንዴት መቆምና መቀመጥ፣ ምን ዓይነት ቀለም ያለው ልብስ መልበስ ሳይቀር የሚደነግግ ደምብና መመሪያ በቅርብ ሳይወጣ አይቀርም፡፡ የልብሱ እንኳን ዱሮውንም ለምደነዋል፡፡ ለምሣሌ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ቀለሞችን መልበስ እንደየቦታው ሁኔታ እስከማስገደል ለሚደርስ አደጋ ያጋልጣል፡፡ የፊጂንና የማልታን ባንዴራ ብትለብስ ቀና ብሎ የሚያይህ ፖሊስም ሆነ ደህንነት የለም፡፡ በኢትዮጵያ ጥላቻ ያበዱ እነዚህ ኦሮሙማዎች ግን ፈጣሪ በቶሎ ይድረስላቸውና ከዕብደታቸው ይታደጋቸው እንጂ በዚህች አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ባንዴራ ለይቶላቸው አብደው ሰክረዋል፡ የተላኩብን ማይማን ደናቁርት ቀላል አይደሉም፡፡ ጆሮም፣ ዐይንም፣ አንደበትም፣ ሰብኣዊ ስሜትም… እንዳይኖራቸው ሮቦት ሆነው ነው በጌቶቻቸው በአቢይና በሽመልስ አብዲሣ የተቀረጹት፡፡ ስለሆነም ከነሱ ጋር ተነጋግሮ ችግርን እፈታለሁ ማለት ዘበት ነው፤ የባሰ መከራንም መጋበዝ ነው፡፡ በተለይ ከአማራ ጋር ሲገጣጠሙ የሚቀናቸው አነጣጥሮ ግንባርን መበርቆስ ነው፡፡ ከዚያ ጠያቂም የለም፤ ተቆጪም የለም፡፡ እንዲያውም ይህን ማድረግ ያሸልማል፡፡ ለአብነት ያህል ሰሞኑን ፈይሣ ሌሊሣ የሚባል ታዋቂ አትሌት ሁለት ሰው ገጭቶ ከነዚያም አንዷን ገድሎ ሌላኛዋን ክፉኛ አቁስሎ ለመዝናናት ወደወጭ እንዲሄድ እንጂ ዝምቡን እሽ ያለው የለም፡፡ (የምትገርም ሀገር!! አደራውን ፈጣሪ መጨረሻቸውን ሳያሳይ አይግደለኝ) – ኦቦ ፈይሤም ያለው “በገዛ መኪናየ አማራ ገጨሁ እንጂ መች ሰው ገጨሁ” ነው – አሉ፡፡ አማራን መግደል፣ አማራን ማሰቃየት በመንግሥት የሚያሾም የሚያሸልምበት አስገራሚ ዘመን ላይ እንገኛለን፡፡ አማራ ግን ይሄን መሰሉ ስቃይና መከራ የተመቸው ይመስላል፡፡ በጫካም በከተማም ያለው አማራ ላለመስማማትና ላለመግባባት ተስማምቶና ተግባብቶ የአቢይን የዕልቂት ዐዋጅ ለማስተናገድ ቆርጧል፡፡ እንጂ ይሄ ሁሉ አማራ በቁጥርም በዕውቀትም፣ በተኩስ ችሎታም … ከማንም ሳያንስ የጥቂት አሰለጥ ዘረኞች የጥቃት ሰለባ ሆኖ መቅረቱ የክፍለ ዘመኑ ታላቅ ዕንቆቅልሽ ነው፡፡ ራስ ወዳድነትና በሌሎች መስዋዕትነት ነፃነትን መሻት እየረገበ ካልመጣ አማራ ገና ብዙ ፍዳ ያገኘዋል፡፡ ዛሬ ምቹ ሥፍራ ላይ የሚገኝ አማራ ነገ ተራው የርሱ መሆኑን ካለፉ ገጠመኞች ካልተማረ ጤንነቱ ያጠራጥራል፡፡ የዐማራ ዕልቂት ከባሌና ከአርሲ፣ ከሐረርጌና ከወለጋ፣ ከሻሸመኔና ከሌሎችም የኦሮሞ አካባቢዎች ተጀምሮ አሁን በሀገሪቱ ባጀትና በሀገሪቱ መንግሥት ተደግፎ በሙሉ ኃይሉ በመላዋ ኢትዮጵያ ተፋፍሟል፡፡ አማራ ግን ፀጥ!
ይህ ምድብ – የሲዖሏ ኢትዮጵያ ጎራ – በጥይት ብቻ ሣይሆን በኑሮ ውድነትም የሚቃጠል ምድብ ነው፡፡ የ3000 እና 4000 ደሞዝ እየተከፈለህ 5 ሊትር ዘይት በ2200፣ አንድ ኪሎ ስኳር በ200፣ ሁለት ሜትር በሦስት ሜትር ለሆነች ደሳሳ ክፍል በአማካይ 5000 የቤት ኪራይ፣ ለሩብ ኩንታል ጤፍ 4000፣ ለአንድ ኪሎ ቡና 1600፣ ለአንድ ኪሎ ምሥር ክክ 300፣ ለአንድ ኪሎ በርበሬ ድልህ 1600፣ ለአንድ ኪሎ ሽሮ 600፣ ለአንድ ኪሎ ገብስ ቆሎ በአማካይ 500፣ ለአንድ ኪሎ ሙዝ 80፣ ለአንድ ኪሎ አቮካዶ በአማካይ 180፣ ለአንድ ኪሎ ኮረሪማ 2800… ስንቱን ብዬህ … እንድታወጣ ይጠበቅብሃል፡፡ ለልጆችህ ትምህርት፣ ለትራንስፖርት፣ ለህክምና፣ ለቁጠባ፣ ለመዝነኛ፣ ለልዩ ልዩ ወጪ … አታስበው ወይንም ስትተኛ በህልምህ አስበው፡፡ የአቢ የቅዠት ኢትዮጵያ እንዲህ እያኖረን ነው፡፡ በዚያ ላይ የውኃው፣ የስልኩና የመብራቱ፣ የአገልግሎቱ ክፍያ አይነሳ፡፡ ቀደም ሲል መታወቂያህ ስለመጥፋቱ ከፖሊስ ብጫቂ ወረቀት ለመውሰድ – ሊያውም ያም ሂደት ራሱ አላስፈላጊ መሆኑ በታሳቢነት ተይዞልኝ – አሥር ብር ትከፍል የነበረው አሁን 300 ሆኗል፡፡ ጠያቂ የለም፤ ተጠያቂም የለም፡፡ ኳስ አበደች ዓይነት የጨረባ ተዝካር ውስጥ እንንጠራወዛለን – አሉ ተብለን፡፡
መብራትን እንውሰድ፡፡ አሁን ያለው የኤሌክትሪክ ክፍያ ብዙዎቻችንን ወገብ ዛላችንን ብሎን መክፈል አቅቶናል፡፡ ይህ አልበቃቸው ብሎ በመጪው ወር ሊጨምሩ እንደሆነ እየሰማን ነው፡፡ በሁሉም ነገር ላይ በየወሩ መጨመር ነው፡፡ በገንዘብ ፍቅር ያበዱ፣ ስለገንዘብ ሚስትና ልጆቻቸውን ሳይቀር የሚሸጡ፣ በሙስና ገንዘብ ከአውሮፓውያኑ ሀብታሞችም ሳይቀር ራሳቸውን በአዱኛ ያገዘፉ፣ የኛ ድህነት የማይገባቸው፣ የሀገር መበታተን ደንታቸው ያልሆነ መሪዎች ገጥመውን ምድራዊ ገሃነም ውስጥ እንገኛለን፡፡ ሁሉም በሆዱ ያለቅሳል፤ እንዳይናገር በስናይፐር ግምባሩ እንዳይበጠስ ይፈራል፡፡ ተከታታይ ማይማንና ጨካኝ መንግሥታት ገጥመውን በሱሪያችን ላይ ሳይቀር የምንስት ፈሪዎች አደረጉን፡፡ በዚህም ሳቢያ 130 ሚሊዮን የሚገመተው ሕዝብ ልክ እንደ አንድ ንፍጣም ሕጻን ተቆጥሮ ማንም ይጋልበን ገባ፡፡ ለነገሩ ይህም ሲያንሰን ነው፡፡ ይበለን፡፡ በዘርና በቋንቋ፣ በሃይማኖትና በሠጥ በሰርጥ የተከፋለ ሕዝብ ለዚህ ዓይነቱ የጭቆና ኑሮ መጋለጡ የሚጠበቅ ነው፡፡ በዚያ ላይ ማይምነቱ የጣለብን የድንቁርና ዳመናና ጭጋግ መቼም የሚገፍልን አይመስልም፡፡ በብዙ ዱላ ተመትተናል፡፡
በሌላኛይቱ ኢትዮጵያ የሚኖረው ሁለተኛው ጎራ በአጭሩ ይህን ይመስላል፡፡ የነገድ ማንነቱ ከማንኛውም ወገን ሊሆን ይችላል፡፡ አንድ የሚያደርገው ግን ገዢው ሆዱ መሆኑ ነው፡፡ ገንዘብን ያመልካል፡፡ ለገንዘብ የማያደርገው የለም፡፡ የ666 አባል ሁን ብትለው ዐይኑን አያሽም፡፡ አማራ ሆኖ ሳለ አማራን ግደልና ይህን ያህል ልስጥህ ብትለው አያቅማማም፡፡ ታንክና ፈንጅ አሲዘው ጎንደርንና ጎጃምን አጥፋልን ብለው ኦሮሙማዎች ቢልኩት ስንት እንደሚከፍሉት ከመደራደር ውጪ ኅሊናውን ተጠቅሞ ለምን ብሎ ራሱንም ሆነ ፀረ አማራዎቹን ኦሮሙማዎች አይጠይቅም፡፡ ይህ ዓይነቱ የተበላሸ ስብዕና ሀገራችን በብዛት ወርሯት ይታያል፡፡ በየከተማው በምቹ ኑሮ የሚንደላቀቀው፣ በዘመናዊ ሊሞዚን የሚንፈላሰሰው፣ በትላልቅ ሆቴሎች የሚዝናናው፣ በየልጁና በየሚስት ውሽማው በሚገዛው መኪና ከተሞችን የሚያጨናንቀው ይህን መሰሉ በሰው አምሳል የተፈጠረ የአጋንንቱ ዓለም ጭፍራ አገር ምድሩን ሞልቶታል፡፡ ይህን መሰል ሰዎች – ሰዎች ማለት ከቻልኩ ነው ታዲያ – ይህን መሰል ሰዎች ሀገር ብትጠበስ ብታርር፣ ብትሸጥ ብትለወጥ፣ ብትበተን ብትገነጣጠል ጉዳያቸው አይደለም፡፡ የነሱ ችግር የሆዳቸው መጉደል ነው፡፡ የነሱ ትኩረት የብልጭልጩን ዓለም ቁሣዊ ሀብትና ንብረት መቆጣጠር ነው – የወዲያኛው ዓለም ለነሱ ደንታቸው አይደለም፡፡ አዲስ አበባ ደግሞ የተጥለቀለቀችው በነዚህን ዓይነት ውሉዳነ አጋንንት ነው፡፡ እናም የሀገራችን ችግር ዘርፈ ብዙ መሆኑን ከዚህ መረዳት እንችላለን፡፡ ሰው የሰውነት መለኪያውን ሲስት የአሁኒቷን ኢትዮጵያ የመሰለ ሀገር ይፈጥራል፡፡
“የሕጻን ልጅ እናት ውሸታም ናት” የሚባል አባባል አለ፡፡ ሕጻኑ እቤት ውስጥ በልቅሶ እየተነሳ ይፈርጣል፡፡ ልጄ ታመመብኝ ብላ እናት እየከነፈች ወደሀኪም ትሄዳለች፡፡ ለሀኪሙ ስታሳየው ልጁ ይቦርቃል፡፡ የእናትን ብሶት የሰማው ሀኪሙም ሕጻኑ ስለመታመሙ ይጠራጠራል፤ እናት ደግሞ የልጇን ልቅሶና ዋይታ ስለምታስታውስ በሀፍረት ትሸማቀቃለች፡፡ የኔም ነገር ማለቴ የኛ ነገርም ልክ እንደዚሁ ነው፡፡ አዲስ አበቤን በቀን ሲተረማመስና ሲስቅ ሲጫወት ለሚያይ፣ አውሮፓ ውስጥ እንኳን ብዙም በማይታዩ በአዳዲስ ሞዴል መኪኖች የመንገዶችን መጨናነቅ ለሚያስተውል “ይሄ ሰውዬ የሚያወራው ስለየትኛው ሕዝብና ስለየትኛዋ ኢትዮጵያ ነው” ብሎ ግር መሰኘቱ አይቀርም፡፡ በዚያ ላይ የከተሞች መብለጭለጭ በተለይ ለውጪው ዓለም የሚሰጠው የተዛባ ምስል የአቢይን ተፈጥሯዊ የሥነ አእምሮና የሥነ ልቦና ህመም በመሸፈን ረገድ የራሱን አስተዋፅዖ ያበረክታል፡፡ እንጂ በኮሪደር፣ በተክሎችና ሣሮች ግርጌ የሚያልቀው ሕዝብ፣ ራሱን የሚያጠፋው ሕዝብ፣ አይግባኙን የሚሰደደው ሕዝብ፣ በየቤት ፈረሳው ለልመና የሚዳረገው ሕዝብ፣ ጨርቁን ጥሎ የሚያብደው ሕዝብ ቀን ሲወጣ መረጃውን የምናየው ይሆናል፡፡ ስንቱ ተፅፎ ግን ይዘለቃል?
ሳላነሳው መቅረት የሌለብኝ ጉዳይ አለ፡፡ ለቃሉ ይቅርታ ይደረግልኝና ሰሜኖች ደደቦች ናቸው፡፡ በእልህና በግትርነት እርስ በርስ ከመጠፋፋት ቆም ብለው ቢያስቡና ራሳቸውንም ሆነ ሀገራቸውን በቅድሚያ ቢታደጓት በተሻለ ነበር፡፡ ነገሩ ሁሉ የጅል ነገር ሆነና በሁለቱም ላይ ሥልታዊ ጄኖሣይድ ታውጆባቸው ሳለ አንዴ ያደቆነ ሰይጣን ካላቀሰሰ አይለቅም እንዲሉ ሆኖ በተለይ ትግሬዎች በድርቅና ሲንገታገቱ ትግራይን ከነጭርሱ እንዳያስጠፏት ያሰጋል – በዱሮ በሬ ያረሰ የለም፡፡ አንጎል የተፈጠረው ለማሰብ ነው፤ አንገትም የተፈጠረው ዞሮ ለማየት ነው፡፡ ከዝንጀሮ በልጦ አለመገኘት በተለይ በዚህ በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ከእንስሳነትም እጅግ ማነስ ነው፤ ነውረኝነትም ጭምር፡፡ ዝንጀሮ እንኳን በእሾህ ተወርራ ሲያገኟትና ቀድመው የትኛውን ሊነቅሉላት እንደምትፈልግ ሲጠይቋት “የመቀመጫየን” ነው ያለችው – ሌላውን ከተቀመጠች በኋላ ትደርስበታለችና፡፡ የሰሜኖችን ድድብናና ድንቁርና ከዚህ ነጥብ አኳያ ነው የማየው፡፡ ከዚህች ፍጡር አንሶ መገኘት ሰው ሆኖ መፈጠርን እስከመጠራጠር ያደርሳል፡፡ ትልቁን የኅልውና ችግር ወደጎን አስቀምጦ በኩርማን መሬት “የኔ ነው፤ የኔ ነው” መባባል ቦታ የለውም እንጂ ቢኖረው አማኑኤል ሆስፒታል የሚያስገባ ትልቅ የአእምሮ ችግር ነው፡፡ በዚያ ላይ በአማራና ትግሬ ጥላቻ ያበዱት አቢይና ሽመልስም እንደኤሊትና እንደጤናማ ሰዎችም ተቆጥረው እነዚህን ሁለት ሴማውያን እርስ በርስ ሲያጠፋፉ ሳይ መፈጠሬን እጠላለሁ፡፡ ከስህተቱ የማይማር ሰው በእናቱ ማሕጸን ውስጥ እያለ ቢጨነግፍ ይሻለዋል፡፡ ወጥቶም ለማንም አይጠቅምምና፡፡
ለማንኛውም ብናርም ብንበግንም ትዕዛዙ ከላይ ነው፡፡ ከታዘዘ አይቀርም፡፡ የታዘዘን ደግሞ በጸሎት ማለዘብ እንጂ ማስቀረት አይቻልም፡፡ በሰውና በፈጣሪ መሀል ያለውን የተዘጋ የሚመስል ድልድይ ወይንም በር ለማስከፈት ሁላችንም እንጣር፡፡ ትንቢት ቢዘገይም መፈጸሙ አይቀርምና ለዚያ እንትጋ፡፡ ሰላም ለኢትዮጵያ፡፡ መንጋቱ አይቀርም፤ ሁሉም በሠፈረው ቁና መሠፈሩም እንደዚሁ፡፡