ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)
ጥር 3፣ 2018( February 10, 2026)
በአሜሪካና በተቀሩት የምዕራብ አውሮፓ ካፒታሊስት አገሮች ውስጥ ያለው ትልቁ ችግር የፖለቲካው መድረክና የመንግስት መኪናው በሳይንቲስቶች፣ በፈላስፋዎችና በሶስዮሎጂስቶች አለመያዙ ወይም በእነሱ ቁጥጥር ስር አለማዋሉ ነው። ምንም ዐይነት ዕውቀት የማይፈጠርበት፣ ወይም ለስልጣኔ የሚያመቹ መጻህፍት የማይጻፍባቸውን ኢትዮጵያንና የተቀሩትን የአፍሪቃ አገሮችን ከቁጥር ውስጥ ሳናገባ ወደ አሜሪካና ወደተለያዩ የምዕራብ አውሮፓ ካፒታሊስት አገሮች ስንመጣ ለጭንቅላት መዳበርና የሰውን ልጅ እንደሰው እንዲያስብ የሚያደርጉት ልዩ ልዩ የፖለቲካ መጻህፍት፣ የፍልስፍና፣ የተፈጥሮ ሳይንስ፣ የሶሰዮሎጂና የተለያዩ የኢኮኖሚክስ መጽሀፎች የሚደረሱት ወይም የሚጻፉት እነዚህ ሰለጠን የሚሉት አገሮች ውስጥ ነው። እንዲሁም የልበ-ወለድና ልዩ ልዩ የስነ– ጽሁፍ መጻህት አሜሪካና ምዕራብ አውሮፓ ውስጥ ነው በብዛት የሚጻፉትና የሚታተሙት። ደቡብ ኮሪያ፣ ቻይናና ጃፓንም የማይናቅ ሚና አላቸው። በተጨማሪም ፊልምና ቲአትሮችም ይሰራሉ። ወደ ዕውቀት መፍለቅና መዳበር ከግሪክ ስልጣኔ በኋላ ከ15ኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ ፍልስፍና፣ የተፈጥሮ ሳይንስ፣ ማቲማቲክስ፣ በኋላ ላይ ላይ ደግሞ ካፒታሊዝም እንደስልተምርት እያደገና እየዳበረ ሲመጣ የኢኮኖሚክስና የሶስዮሎጂ ዕውቀቶች በአውሮፓ ምድር ውስጥ ነው መዳበርና መስፋፋት የቻሉት። እነዚህ ሁሉ ዕውቀቶች ሲፈጠሩና ሲስፋፉ ዋናው ዓላማቸው ለዕውቀት ተብለው ብቻ ሳይሆን በዚያው መጠንም የሰውን የማሰብ ኃይል ያዳብራሉ፤ ከተለያዩ አቅጣጫዎችም ማየት ያስችላሉ ከሚል ግምት ነው። እነዚህም ዕውቀቶች በመፈጠራቸው ምክንያት፣ በመደበራቸውና በመስፋፋታቸው ነው የኋላ ኋላ ላይ ሳይንስና ቴክኖሎጂዎች ሊዳብሩ የቻሉት። በሳይንስና በቴክኖሎጂዎች ማደግና መስፋፋት ነው የሰው ልጅ ህይወት ካለፉት አራትና አምስት መቶ ዓመታት የአኗኗር ስልት ጋር ሲነፃፀር ዛሬ በተሻለ ሁኔታ መኖር የቻለው። ይህም ማለት አንድ ሰው ወይም ፖለቲከኛ ነኝ የሚልና የመንግስትን መኪናን የሚቆጣጠር ማኛውንም ህብረተሰቡንና የዓለም አቀፍ ሁኔታን የሚመለከቱ እርምጃዎች በስሜትና እኔ ነኝ የበላይ ነኝ፣ ስለሆነም የፈለግሁትን ነገር ለማድረግ እችላለሁ ከሚለው አስተሳሰብ በመነሳት ሳይሆን ተግባራዊ መሆን ያለባቸው ነገሮችን ከሁሉ አቅጣጫ በመመርመርና በማመዛዘን ብቻ ነው። ማንኛውም ፖለቲከኛ ነኝ የሚል የምንጠቀምባቸው ነገሮች ሁሉ በዛሬው ዓለም እንዴትስ በዚህ መልክ ሊገለጹና ልንጠቀምባቸውስ ቻልን ብሎ ወደ ኋላ ዞር ብሎ መመልከት አለበት። ይህም ማለት አንድ ሰው ፖለቲከኛ ለመሆን ሲያስብና የአንድንም ህብረተሰብ ዕድል ለመወሰን እችላለሁ ብሎ ሲነሳ ጭንቅላቱን በልዩ ልዩ ዕውቀቶች ማነፅ አለበት፤ ወደ ኋላም ዞር ብሎም የመመልከት ኃይልና ችሎታ እንዲኖረው ያስፈልጋል። በሌላ ወገን ግን ሁላችንም እንደምናውቀው በተለይም በምዕራብ አውሮፓ የካፒታሊስት አገሮች ውስጥና በአሜሪካንም ጭምር የህግ-የበላይነት የሚባል ነገር ስላለ አንድ ግለሰብ ፕሬዚደንት ወይም ጠቅላይ ሚኒስተር ስለሆነ ብቻ የፈለገውን መወሰን በፍጹም አይችልም። ይሁንና በተለያዩ የተወሳሰቡ የአሰራር ዘዴዎች ምክንያት የተነሳ የህግ የበላይነት የሚባለው ነገር እየተጣሰ እንደመጣ እንያለን። ይህ ሁኔታ በተለይም በአሁኑ ወቅት በአሜሪካን ምድር ጎልቶ የሚታይ ሀቅ ሊሆን ችሏል። ፕሬዚደንቱ ከማንኛውም ህግ የበላይ በመሆን ማንኛውንም ነገር እየወሰነ ነው። የፓርቲው አባላትም ሆነ ተቃዋሚ ፓርቲ ነኝ የሚለው የዲሞክራቲክ ፓርቲው ፕሬዚደንቱ ዝም ብለው ይመለከቱታል። ይህ ሁኔታ የሚያረጋግጠው ወደ ማዕከለኛው ክፍለ-ዘመን መመለሳችንን ነው። በሌላ አነጋገር፣ ዲስፖታዊ አገዛዞች ይገዙ የነበሩበት ሁኔታ በአሁኑ በ21ኛው የሳይንስና የቴክኖሎጂ ዘመን ተግባራዊ እየሆነ ለመሆኑ እንመለከታለን። የሰው ልጅ ለብዙ ሺህ ዓመታት ስንትና ስንት ጉዞዎችን ከተጓዘና እዚህ ዐይነቱ የተወሳሰበ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ዘመን ደርጃ የደረሰ ቢሆንም፣ በአሁኑ ወቅት የኋሊት ጉዞ የሚያደርግ ይመስላል።
ወደ ኋላ ዞር ብለን የታሪክን ማህደር ስናገላብጥ በግሪክ ስልጣኔ ዘመንም ሆነ በተለይም ከ17ኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ የሰውን ልጅ፣ በተለይም በፖለቲካ አካባቢ የተሰበሰቡትን በሚመለከት የተለያዩ ፍልስፍናዊ አስተሳሰቦች ይንፀባረቁ ነበር። በተለይም በእነሶክራተስና በፕሌቶ የሚመራው ክንፍ የጭንቅላትን የበላይነት ሲያሰምር፣ ማንኛውም የሚወሰዱ እርምጃዎች በሙሉ ከእራስ አንፃር ብቻ በመነሳትና የራስን ጥቅም በማስቀደም ሌላውን ለመጉዳት መሆን የለባቸውም የሚል ነው። ስለሆነም ማንኛውም ሰው በሞራልና በስነ-ምግባር መገዛትና ራሱንም መቆጣጠር አለብት ይላል። ይህ ሲሆን ብቻ ለስልጣንና ለሀብት መስገብገብ ቦታ አይኖራቸውም የሚል ነው። በሌላ ወገን ደግሞ ይህንን የሚፃረር ሶፊስታዊ አመለካከት ሲኖር፣ ማንኛውም ሰው የራሱን ጥቅም ማስቀደም አለበት የሚል ነው። የመንፍሱ፣ ወይም የሞራል ተገዢ ሳይሆን እንደየሁኔታው የሚዋልልና የራሱን ጥቅም በማስቀደም ከሁኔታዎች ጋር ተመሳስሎ ለመኖር የሚፈልግ መሆን አለበት። የግሪክ ፍልስፍና ከፈለቀ ጀምሮ በእነዚህ ሁለት ተፃራሪ አስተሳሰቦች ወይም አመለካከቶች መሀከል ትግል ሲካሄድ፣ የመጨረሻ መጨረሻ ላይ በአሸናፊንት ሊወጣ የቻለው የሶፊስቶቹ ጦርነትንና ስግብግብነትን የሚያስቀድመው ስነ-ምግባርና ሞራል አልባ የሆነው አስተሳሰብ ነው። ይህ ዐይነቱ አስተሳሰብም በአሸናፊነት በመውጣቱና ሳይንሳዊ ዕውቀት እንደመመሪያ ለመወሰድ ባለመቻሉ በማዕከለኛው ክፍለ-ዘመን በአውሮፓ ምድር ውስጥ እጅግ እልክ አስጨራሽና በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ህዝቦችን የጨረሱ ጦርነቶች ለመካሄድ በቅተዋል። አብዛኛውን ጊዜም የፖለቲካ መድረኩ ፓትሪያሪካላዊ ወይም በኃይል አስተሳሰብ በሚያምኑ ግለሰቦች ወይም ቡድኖች ስለሚያዝና አብዛኛው ህዝብም ከዕውቀትና ከፖለቲካዊ እንቅስቃሴ የተገለለ በመሆኑ እጣው ሁሉ ለጦርነት መማገድና ህይወቱን ማጣት ነበር። በተለይም ከአስራአምስተኛው ክፍ-ዘመን ጀምሮ የመንፈስ ተሃድሶ ቢካሄድምና ከዚያም በኋላ የተፈጥሮ ሳይንስ እየዳበረ ቢመጣም ሳይንሳዊና ፍልስፍናዊ አስተሳሰቦች የፖለቲካ መድረኩ ውስጥ ሰርገው በመግባት ስልጣንን የያዙ ሰዎችን መንፈስ መቆጣጠርና መግታት በፍጽም አልቻሉም። በተለይም ከአስራሰባተኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ ቀስ በቀስ ተቀባይነትን እያገኘ የመጣው የቶማስ ሆበስ አስተሳሰብ የፖለቲካ መድረኩን ለመቆጣጠር ቻለ። በፈላስፋው በቶማስ ሆበስ ዕምነት ማንኛውም ግለሰብ እንደ ቀበሮ የሚታ ሲሆን፣ አንዱ ሌላውን እየፈራና እየተፈራሩ የሚኖርበት ዓለም ነው። ስለሆነም ሁሉንም አንቀጥቅጦ የሚገዛ አስፈሪ አገዛዝ መመስረት፣ ወይም መኖር አለበት ይላል። ይህ የቶማስ ሆበስ አስተሳሰብ በጓደኞቹ በእነ ሁምና ሎክ ተቀባይነት አልነበረውም። በሁምና በሎክ ዕምነት አንድ ሰው አንድ አደገኛ ነገር ሲያጋጥመው ሌላው ዝም ብሎ አያልፈውም፤ የማገዝ ወይም የመርዳት ስሜት ስላለው የሰውን ልጅ ንጹህ በንጹህ ለራሱ ጥቅም ብቻ ነው የሚያስበው ብሎ መቀበልና ይህንን መስበክ ትክክል አይደለም የሚል ነው። በእነሶክራተስና በፕሌቶ እንዲሁም በሌሎች ኋላ ላይ በተነሱት ፈላስፋዎች ዕምነት የሰው ልጅ ጭንቅላት በቅራኔዎች የተያዘ ሲሆን፣ በተቻለ መጠን ጥሩ የሆነውን ጎኑን በየጊዜው መኮትኮትና ማበልፀግ አስፈላጊ ነው። ይህ ሲሆን ብቻና፣ በተለይም ልጆች ከልጅነታቸው ጀምረው መንፈሳቸው በደንብ እየተኮተኮተ ከመጣ በአስተሳሰባቸው የጠሩና ለሌላውም የሚያስቡ ይሆናሉ። ለስግብግብነትና ሌላውን ለመጉዳት ቦታ አይሰጧቸውም የሚል ነው። በትክክል የፍልስፍናና፣ የኋላ ላይ የተፈጥሮ ሳይንስና የማቲማቲክስን መፈጠርና መዳበር ስንመለከት ከልጅነታቸው ጀምረው ከጥሩ ዕውቀት ጋር የተዋወቁና ጭንቅላታቸውም በጥሩ አስተሳሰብ በተዋቀረ ግለሰቦች አማካይነት ነው ለቴክኖሊጂ መሰረት የሆኑት የተፈጥሮ ሳይንስና የማቲማቲክስ ዕውቀቶች መዳበርና የኋላ ኋላ ላይ ለሳይንስና ለቴክኖሎጂ መዳበር መሰረት መጣል የቻሉት።
በአጠቃላይ ሲታይ በግሪክ ስልጣኔ ዘመንም ሆነ በኋላ ላይ በአውሮፓ ምድር ከሬናሳንስ ጀምሮ፣ በተለይም ከ17ኛው ክፍለ–ዘመን ጀምሮ የፖለቲካው መድረክና የመንግስት መኪና ጭንቅላታቸው በደንብ በጥሩ ዕውቀት በተዋቀሩ ሰዎችና የህግን የበላይነት የሚቀበሉና የህዝብም አለኝታ ለመሆን በሚችሉ ሰዎች እንዲያዝ ትግል ቢደረግም እንደምንም ብሎ ስልጣን ላይ የሚወጣና የመንግትስትን መኪና ለራሱ በሚስማማ መልክ የሚያዋቅረው ክሳይንስና ከፍልስፍና የራቀ ኃይል ነው። ሳይንሳዊ ዕውቀትን እንደመመሪያ የሚወስድና ፖለቲካ ማለትም ሳይንስ መሆኑን የተገነዘበ ሳይሆን ከሳይንሳዊ ዕውቀት በብዙ ሚሊዮን ማይሎች ርቆ የሚገኝ ኃይል ነው። ሳይንሳዊ ዕውቀትን የሚያስቀድምና አንድን ፖሊሲ ከሳይንስ አንፃር በመመርመር ተግባራዊ የሚያደርግ ሰው ሳይሆን የፖለቲካ ስልጣንን የሚቀዳጀው ከተወሰነ የህብረተሰብ አንፃር በመነሳት የተወሰነን የህብረተሰብ ጥቅም ብቻ ተግባራዊ የሚያደርገው ነው ስልጣንን ሊይዝ የሚችለው። በተለይም ካፒታሊዝም እየተወሳሰበ ከመጣ ጀምሮና የፋይናንስ ካፒታል የበላይነትን ከቀዳጀበት ጊዜ ጀምሮ ይህ ከሚሊተሪው የኢንዱስትሪ ውስብስብ ጋር(Military-Industrial Complex) በመመሰጣጠርና ራሱን የቻለ የውስጥ መንግስት በመመስረት የፖለቲካ መድረኩን በሚቆጣጠረውና ከሳይንሳዊ ዕውቀት በራቀው ኃይል ላይ ተፅዕኖ በማድረግ ለእሱ የሚስማማውን ማንኛውንም ፖሊሲ ተግባራዊ ማድረግ ቻለ። ህግ አውጭዎችና አፅዳቂዎች የሚባሉትና በህዝብ በመመረጥ የህዝብ ተጠሪዎች ነን የሚሉት በዚህ የሚሊተሪ ውስብስብ ውስጣው አገዛዝ በመገዛትና በሙስና በመተብተብ ዋናው ተግባራቸው የመረጣቸውን ህዝብ ጥቅም ማስቀደም ሳይሆን ከ5% በመቶ በታች የሆነውን በሀብት የናጠጠውን የህብረተሰብ ክፍል ብቻ ነው። ይህ ዐይነቱ ስልጣንና ከሳይንስ የራቀ ፖለቲካ በአሜሪካን ምድር በግልጽ የሚታይና 90% የሚሆነውን ህዝብ ከፖለቲካ መድረኩ ያገለለ ነው። ይህም ሰፋ ያል ህዘብ በየአራት ዓመቱ ምርጫ በሚካሄድብት ጊዜ እንደመሰለው ከመምረጥ በስተቀር በስተቀር በዕውቀት አማካይነት በማውጣትና በማውረድ አይደለም። ስለሆነም ህዝባዊ ንቃተ-ህሊና ባልዳበረበት አገር ውስጥ የፖለቲካ ስልጣንን የሚይዘው ኃይል የጠቅላላውን ህብረተሰብ ጥቅም የሚያስቀድም ሳይሆን በሀብት የናጣጠውንና የምርት ኃይሎችን የሚቆጣጠረውን የህብረተሰብ ኃይል ብቻ ነው። የፖለቲካና የኢኮኖሚ ፖሊሲውም የሚነደፈውና ተግባራዊ የሚሆነው ከዚህ በፖለቲካውና በመንግስት መኪናው ላይ ተፅዕኖ ለማሳደር ከሚችለው የህብረተሰብ ክፍል በመነሳት ነው። ወደ ውጭ ፖሊሲም ስንመጣ በተለይም የተለያዩ የአሜሪካን አገዛዞች የተለያዩ ሰበቦችን በመፈለግ አገሮችን የሚወሩትና የመንግስት ግልበጣ፤ እንዲያም ሲል የሃይማኖትና የብሄረሰብ ግጭት እንዲፈጠር የሚያደርጉት ከአገራቸውና ከህዝባቸው ጥቅም አንፃር በመነሳት ሳይሆን ከዚህ እፍኝ ከማይሞላ የህብረተሰብ ክፍል አንፃር ብቻ በመነሳት ነው። ይህ ዐይነቱ ከሳይንስና ከማንኛውም ዕውቀት የራቀ ፖለቲካ ራሱን አሜሪካንንም በከፍተኛ ደረጃ እየጎዳው ነው። ወደፊት ከፍተኛ በጎሳና በሃይማኖት ላይ የተመሰረተና፣ እንዲያም ሲል በዘር ላይ የተመሰረተ የእርስ በርስ ጦርነት በመነሳት አሜሪካንን እንድ አንድ አገዛዝና አገር እንደሚያወድመው ይህን ያህልም በፖለቲካ ሳይንስ ትንታኔ መብሰል አያስፈልግም። ሁኔታዎች አፍጠው አግጠው የሚታዩ ስለሆነ በቅርቡ የሚፈነዳ ይሆናል።
ለማንኛውም በአጠቃላይ ሲታይ ዕውቀት ሲዳብር የሰውን ልጅ አስተሳሰብ በቀና መልክ ለመቅረጽ ነው። የሰይጣናዊ አስተሳሰብን መዳበር ወደ ጎን በመተው የሰውን ልጅ ሁለ-ገብነት ለማሳየትና ከተለያዩ አቅጣጫዎች በመመልከት ሚዛናዊ ስራዎችን እንዲሰራ ነው። ፖለቲከኞች የሚባሉትም የየህብረተሰቦቻቸው አካሎች እንደመሆናቸው መጠን የተለያዩ መጻህፍቶችን በማንበብና፣ በሙዚቃ፣ በቲአትርና በፊልም መንፈሳቸውን በማረቅ ፖለቲካ የሚባለውን ነገር ከሁሉም አቅጣጫ በማንበብ ተግባራዊ እንዲያደርጉ ነው። በአጭሩ በስሜት እንዳይነዱ ነው። ይሁንና የዓለምን የፓለቲካ ሁኔታ ስናጠናና፣ በተለይም የካፒታሊዝምን ዕድገት ጠጋ ብለን ስንመለከት ፖለቲካ የሚባለው ነገር በአርቆ-አሳቢነት ላይ የተመሰረተና የሌሎችን አገሮች ታሪካዊ ዕድገትና ባህል እሳቤ ውስጥ ያስገባ ሳይሆን፣ ፓለቲካ የሚባለው ነገር ከተለያዩ ዕውቀቶች በመነጠል ማንም እየተነሳ ስልጣን በመያዝ ህዝብንና የዓለምን ሁኔታ ማወዛገቢያ፣ እንዲያም ሲል የጦር መቀስቀሻ መሳሪያ ለመሆን የበቃበትን ሁኔታ ተመልክተናል። አንድ ምሳሌ ለመጥቀስ ያህል ከግሪክ ስልጣኔ መዳከም በኋላ ከ17ኛው ክፍለ–ዘመን ጀምሮ የፍልስፍናና የሳይንስ ዕውቀት ከእንግሊዝ ቀጥሎ በከፍተኛ ደረጃ ጀርመን ምድር ነው የዳበረው። እነ ላይብኒዝ፣ ካንት፣ ሄገል፣ ጎተና ሺለር፣ ማርክስና ኤንገልስ እንዲሁም አያሌ የሳይንስና የማቲማቲክስ ሰዎች ጀርመን ምድር ነው የፈለቁት። ሁሉም ፈላስፋዎችና ሳይንቲስቶች ስለዘረኝነት በፍጹም አልጻፉም፤ ስለጦርነትም በፍጹም አልሰበኩም። አጻጻፋቸው በሙሉ በጭንቅላት አማካይነት በከፍተኛ ደረጃ በማሰብ ኃይል የሰውን ልጅ ከጨለማ ሁኔታ በማላቀቅ የሰለጠነ ኑሮ እንዲኖር ለማድረግ ነው። ቴክኖሎጂዎችም ሲፈጠሩና ሲዳብሩ የተወሳሰቡ የጦር መሳሪያዎችን በመስራት መገዳደያ ለማድረግ ሳይሆን በቴክኖሎጂ አማካይነት ልዩ ልዩ ምርቶችን በማምረት የሰው ልጅ እንዲጠቀምባቸው ለማድረግና ይስልጣኔን ብርሃን እንዲያይ ለማድረግ ነው። ይሁንና ጊዜው የፈጠራቸው እንደ ሂትለር የመሳሰሉ መሪዎች ነን በሚሉ የተወሰነውን ቴክኖሎጂ በመጠቀምና የጥፋት መሳሪያ በመስራትና በአውሮፓ ምድር ትልቁን ጦርነት በማካሄድ ወደ 50 ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብ ህይወቱ እንዲጠፋ ተደርጓል። ወደ 6 ሚሊዮን የሚጠጉ አይሁዲዎች በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድለዋል። ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ ብቅ ያለው ኃያል መንግስት ነኝ የሚለው አሜሪካም ማንም አገር ጦርነት ሳይከፍትበት ከሂሮሺማና ናጋሳኪ፣ እስከ ቬትናምና አፍጋኒስታንና ሌሎችም አገሮች ላይ ጦርነት በማወጅና በመክፈት የብዙ ሚሊዮን ህዝቦችን ህይወት እንዲጠፋ ማድረጉ ብቻ ሳይሆን የታሪክና የባህል ውድመቶችንም አድርሷል። ከሞት የተረፈው የእነዚህ አገሮች ህዝቦች በየቦታው ተበታትኖ ወድቋል። ልጆች ከአባቶቻቸዋና ከተቀረው ዘመዶቻቸው በመነጠልና በየቦታው በመሰደድ በተለይም ሽማግሌዎችን የሚጦር ወጣት ኃይል ሊጠፋ ችሏል። ማንም ሊከሰኝ የሚችል ኃይል የለም እያለ በእየአገሮች ውስጥ ጣልቃ በመግባት ጦርነት የሚያካሂደው ታላቁ አሜሪካ እንደዚህ ዐይነቱን የታሪክ ወንጀል ሰርቷል፤ እየሰራም ነው። ታዲያ ይህ ሰይጣናዊ ኃይል አሁንም ቢሆን እየተፈራና በተለይም በአገራችን የፖለቲካ ኤሊት በአገር ቤት ውስጥም ሆነ በውጭው ዓለም ተበታትኖ በሚኖረው ኢትዮጵያዊ ነኝ በሚለው ምሁር ዘንድ ሲወደስንና ሲኮራበትም ይሰማል። ይሁንና ይህ የሚኮራበትና የሚወደሰው ታላቁ አሜሪካ ሰሞኑን ከሶስት ሚሊዮን በላይ በሚቆጠር ለንባብ ክፍት በሆነ የኤፕስታይን አስቀያሚ ስራ ሊጋለጥ ችሏል። ይህንንም የሚያቀነባብሩት የስለላ ድርጅቶች ሲሆኑ፣ ፖለቲከኞችን በመቆጣጠር እንደ ፈለጓቸው እያሽከረከሯቸው ነው ማለት ይቻላል። ከዚህ ዐይነቱ እጅግ ለጭንቅላት ከሚዘገንን ሁኔታ ስንነሳ እስካሁን ድረስ የምንኮራበትን የካፒታሊዝምን ዲሞክራሲያዊ ስርዓት እንዴት ነው የምንመለከተው? ለዚህስ የሚሆን ምሁራዊ ብቃት አለን ወይ? ብለን እራሳችንን መጠየቅ አለብን።
ያም ተባለ ይህ ይህ ሁሉ የሚያረጋግጠው ምንድን ነው? ፖለቲካ የሚባለው ሳይንሳዊ መሳሪያ ንጹህ በንጹህ ወደ አመፅነትና ወደ ሴራ መስሪያ መሳሪያነት በመቀየር ደካማ አገሮችን ማስፈራሪያ ሊሆንም በቅቷል። ከዚህም ባሻገር የህግ የበላይነት የሚለው የአገዛዝ ስልት ከጥቅም ውጭ በመሆን በተለይም ኤክስኪዩቱቡ ከጦር መሳሪያ አምራች ኩባንያዎችና ከተለያዩ በሀብት በናጠጡ ኩባንያዎች ጋር በመቆላለፍ አሻጥርና ጦርነት የሚፈለፈልበት መሳሪያ ለመሆን በቅቷል። በተለይም የስለላ ድርጅቶች ልዩ ሚና በመወሰድና በዓለም አቀፍ ደረጃ የከፋፍለህ ግዛው ፖለቲካን እንዲካሄድ በማድረግ፣ በተለይም እንደኛ የመሳሰለውን በሳይንሳዊ ዕውቀት እጅግ ደካማ የሆነውንና የተቀሩትን የአፍሪካ አገሮች ወደ ጦር አውድማነት ለውጠዋቸዋል። በተለይም ከ1950 ዓመታት በኋላ የበላይነቱን እያጠነከረ የመጣው የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ዓለምን የሚቆጣጠርበትን ዘዴ በመፍጠር በዓለም አቀፍ ደረጃ ጭንቅላትን የሚከፍት ፍልስፍናዊና ሳይንሳዊ ዕውቀት እንደኛ በመሳሰለው አገር እንዳይስፋፋና እንዳይዳብር ቀስ በቀስ የመንግስታትን መኪና መቆጣጠር ቻለ። ማስልጠን የጀመረውንም የሚሊተሪና የስለላ ኃይልና ተቋም በመጠቀም ስልጣንን የያዙ ኃይሎች የመንግስትን መኪና በመጠቀም ድህነትንና ኋላ-ቀርነት ቀራፊዎችና አስወጋጆች ከማድረግ ይልቅ በአብዛኛው ጎናቸው ጨቋኝና አስፈሪ ለመሆን ቻሉ። ተግባራዊ የሆነውን የኢኮኖሚ ፖሊሲም ህዝባዊ ሀብትን የሚፈጥር ባለመሆኑና ስርዓት ላለው የሳይንና የቴክኖሎጂ ዕድገት የሚያመች ስላልነበር እዚያው በዚያው ዘመናዊነት የሚባለው ነገርና ድህነት ጎን ለጎን የሚጓዙበት ሁኔታ መፈጠር ቻለ። ስለሆነም ላይ ላዩን የሚጋልብ የህብረተሰብ ኃይል መፈጠር በመቻሉ ህብረተሰቡን ማዘብራረቅ ቻለ። ዕውነተኛ ብሄራዊ ባህርይና የአገርና የሰው ወዳድነት ስሜት ከማዳበር ይልቅ በአሜሪካን የበላይነት የሚያምንና ለእሱ የሚታዘዝ ለመሆን በቃ። በዚህም ምክንያት የተነሳ ለሁለ-ገብ ዕድገት የሚያመችና ሰፊውን ህዝብ የሚያካትት ምሁራዊ እንቅስቃሴ እንዳይዳብርና ሳይንሳዊ የሆነ የኢኮኖሚ ፖሊሲም ተግባራዊ እንዳይሆን ተደረገ።
በተለይም መንግስታት በተለያዩ ምክር እንሰጣለን ከሚባሉ ኩባንያዎች ጋር በመቆላለፍና ከሳይንስና ከፍልስፍና፣ እንዲሁም ከሶስዮሎጂ ውጭ የሆነ ፖለቲካ የሚሉትን ነገር በማካሄድ የዓለምን ፖለቲካ እየበወዙት ነው። ከ1989 ዓ.ም በኋላ የተፈጠረው አዲሱ የዓለም ሁኔታም ለአሜሪካንና ለተቀሩት የካፒታሊስት አገሮች አመቺ ሁኔታ የፈጠረላቸው ስለመሰላቸው በየአገሮች ውስጥ የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምንና የተቀሩት የካፒታሊስት አገሮችን ተላላኪ የሆኑ ግለሰቦችን ስልጣን ላይ በማውጣት አገሮችን እያመሱ ነው። ባህሎች እየወደሙና በተለይም የወጣቱን መንፈስ የሚረብሹና ዕውነተኛ እሴት እንዳይኖረው የሚያደርግን የድረግና የግብረ-ሰዶማዊነት ባህል በማስፋፋት ምሁራዊ እንቅስቃሴ እንዳይዳብር ለማድረግ በቅተዋል። እንደኛ ያሉ በአስተሳሰብ እጅግ ወደ ኋላ የቀሩ አገዛዞች የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲን፣ በመሰረቱ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ያልሆነውን የዓለም አቀፍ ስምን በተከናነቡ እንደ ዓለም የገንዘብ ድርጅትና(IMF) በዓለም ባንክ በመመከር ድህነትን እያስፋፉና ሰፊውን ህዝብ አቅመ-ቢስ እያደረጉት ነው። በእነዚህ ዐይነቱ አማካሪ ነን በሚሉ ድርጅቶችና የዓለም አቀፍን ስም በተከናነቡ በዓለም የገንዘብ ድርጅትና በዓለም ባንክ አማካይነት በየአገሮች የሚተገበረው ኢ-ሳይንሳዊ የሆነ የኢኮኖሚ ፖሊሲ በየአገሮች ውስጥ፣ አገራችንም ጭምር ከ90% በላይ የሚሆነውን ህዝብ አቅመ–ቢስ አድርጎታል።በገንዘብ የተገዛው ምሁር ነኝ ባይም የእነዚህ ድርጅቶች ተላላኪ በመሆን ከፍተኛ የሆነ የታሪክ፣ የባህልና የህብረተሰብ ውድመት እያደረሰ ነው። ለተከታታዩ ትውልድ የሚበቃ የጥሬ ሀብት እየየተዘረፈና እየወደመ እናያለን። በተለያዩ ከተማዎችም፣ አዲስ አበባንም ጨምሮ የሚሰሩት ህንፃዎች ከሳይንስ አንፃር በመመርመርና በማቀድ እንዲሁም ለሰፊው ህዝብ በሚመች መልክ ጥበባዊ በሆነና ክረዥም ጊዜ አንፃር የሚሰሩ ባለመሆናቸው የከተማዎችን ውበት እያበላሹት ነው። በእነዚህ በቆሙ ትላልቅ ህንፃዎች ፊለፊትም በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብ አቅመ-ቢስ ለመሆን በቅቷል።
ለማንኛውም ማንም ሰው ማወቅና መገንዘብም ያለበት ነገር የአንድ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ዋና ዓላማ አንድን አገር በተሟላ መልክ በመገንባት ሰፊውን ህዝብ ከኋላ-ቀርነትና ከድህነት በማላቀቅ እንደሰው ተከብሮ እንዲኖር ማድረግ ነው። ህብረተሰቡን በደሀና በሀብታም በመከፋፈል ተፋጠው እንዲኖሩ ለማድረግ ሳይሆን ተሳስበው እንዲኖሩ ለማድረግ ነው። በአጭሩ ሁሉም ዜጋ የአገሩ ዜጋና የህብረተሰቡ አካል እንደሆነ እንዲሰማው ለማድረግ ነው። በዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅትና በተለያዩ የአማካሪ ኩባንያዎች የሚመከሩት የየአገራችን መንግስታት ለሰፊው ህዝብ የሚጠቅምና ምርታማነትን በሁሉም አቅጣጫ ሊያሳድግ በሚችል የትናንሽና የማዕከለኛ እንዱስትሪዎች ላይ ከማተኮር ይልቅ በአለ አምስት ኮከብ ሆቴል ቤቶችንና የገበያ አዳራሾችን በመስራት በከፍተኛ ደረጃ የብልግናን ኢንዱስትሪ እያስፋፉ ነው። እነዚህ መንፈሰ አልባ የሆኑ መሪዎችና የጭንቅላታቸው ብሎን የወላለቀመሬዎች ነን የሚሉ ከዓለም አቀፍ ተዋናይና ከኢምፔሪያሊስታዊ ኃይል ጋር በመቆላለፍ ከፍተኛ የሆነ የባህልና የታሪክ ወንጀል እየሰሩ ለመሆናቸው ለእነሱም ሆነ ለእኛ ምሁራን ነን ለምንልና በጥሩ ብዕር ለምንጽፍ የተገለፀልን አይመስልም። ዝምብለን ብቻ እንደ ከብት እየተነዳን ታላቁ አሜሪካ ድረስልን እያልን እንጮሃለን። በመሰረቱ ትምህርት ቤት የተላክነውንና የተማርነው፣ አንዳንዶቻችንም በተለያዩ ሙያዎች “በመሰልጠን” ዲግሪ የተከናነብነው ክሪቲካል በሆነ መልክ እንድናስብና ለእኔ ብጤ ደካማ ለሆነው ሰው ጠበቃ ለመሆንና ለመከላከል ነው። ይህ ከመሆን ይልቅ በአስተሳሰባችን በጣም ደካማ ከመሆናችን የተነሳ በአገራችን ምድር ምስቅልቅል ሁኔታዎችን በመፍጠርና በህዝባችን ላይ ጦርነትም በማወጅ የታሪክ ወንጀል እየሰራን ነው። በዚህ ወንጀላችን በምድር ላይ የሚጠይቀን ባይኖር እንኳ ከሞት በኋላ አስፈላጊውን ቅጣት ማግኘታችን አይቀርም።
በአጭሩ የዓለምን ፖለቲካ የሚባለውን ነገር ጠጋ ብለን ስንመለከት ሰለጠንኩኝ የሚለው በአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም የሚመራው የካፒታሊስቱ ስርዓት የሰለጠነ ፖለቲካ ሳይሆን የሚያካሂደው በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ አገሮችን ማከረባበት ነው። በተለይም የአፍሪካ አገሮች ለሁለ-ገብ ዕድገት በሚያመቻቸው ቴክኖሎጂዎች ላይ አትኩሮ እንዳያደርጉ በማድረግ በተለያዩ መሳሪያዎች በመተብተብ ሀብታቸውን አባክነው እንዲቀሩ ተገደዋል።
ቀደም ብዬ ለማሳየት እንደሞከርኩት በምዕራብ አውሮፓ ውስጥ የአገዛዞችን መንፈስ የሚያርቅ ፍስልፍና፣ የተፈጥሮ ሳይንስና እንደሶስዮሎጂ የመሳሰሉት ጽሁፎች ቢፈጠሩምና ቢስፋፉም የፖለቲካ ኤሊቱ ከዚህ ዐይነቱ ሳይንሳዊ ዕውቀት የራቀ ነው። ስለሆነም የሚከተላቸው የውጭ ፖለቲካ የራሱንም አገር አደገኛ ሁኔታ ውስጥ እየከተተው መጥቷል። ሌሎች አገሮች ውስጥ ጦርነት እንዲከፈት ሲያደርግና የመንግስት ግልበጣም ሲያካሄድ በየአገሩ ውስጥ መኖር የማይችለው የግዴታ እየተሰደደ ወደ አሜሪካና ወደ ምዕራብ አውሮፓ በመምጣት የዲሞግራፊንና የጎሳን ሁኔታን እየቀየረው ነው። በተለይም አሜሪካን አገር በአንዳንድ ከተማዎች ውስጥ ከነጩ ኗሪ ህዝብ የስፓኒሽ ቋንቋ የሚናገሩ በቁጥር እየጨመሩ መጥተዋል። አንዳንድ የምዕራብ አውሮፓ አገሮች ከተማዎች ውስጥም በአንዳንድ ቀበሌዎች ከአገሩ ዜጋ ይልቅ መጤው ኗሪ በቁጥር እየጨመረ በመምጣት ላይ ይገኛል። ይህ ሁሉ ነገር የሚያረጋግጠው የአሜሪካንና የተቀረው የምዕራብ አውሮፓ የፖለቲካ ኤሊት ጭንቅላቱ እንደታወረ ነው። በሌላ አነጋገር፣ ሌሎች አገሮችን አከረባብታለሁ ሲል፣ የራሱንም መቃብር እየቆፈረ እንደሆነ በፍጹም የተረዳ አይመስልም። በሁሉም አገሮች ውስጥ የበላይነቴን ማስፈን አለብኝ በማለት የሚያካሄደው ከአርቆ አሳቢነት ውጭ የሆነ ፖለቲካው የራሱንም አገር ሊያወድምበት እንደሚችል በፍጹም የተገነዘበ አይመስልም። በአብዛኛው የፖለቲካ፣ የሚሊተሪና፣ የስለላና የኢኮኖሚ ኤሊት ውስጥ የተቀረፀ አደገኛ መንፈስ ስላለና ሁሉም በጥቅም የተሳሰሩ ስለሆነ ነገሮችን በሁሉም አቅጣጫ የማየት ኃይላቸው በጣም የደከመ ነው ማለት ይቻላል። አሁን ያለው ፍርሃት አሜሪካና የተቀረው የካፒታሊስት አገሮች በሚያካሂዱት የፍጥጫ ፖለቲካ የሶስተኛው ዓለም ጦርነት ሊቀሰቀስ ይችላል የሚል ነው።
በአጠቃላይ ሲታይ በአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም የፖለቲካ፣ የሚሊተሪ፣ የኢኮኖሚና የሃይ ቴክ ኤሊትና በምዕራብ አውሮፓ የፖለቲካ ኤሊት ዘንድ ነገሮችን በጥቁርና በነጭ ወይም በጠላትና በወዳጅ መሀከል የመሳል አደገኛ አካሄድ አለ። እኛ የምንለውን የማይሰማ፣ ወይም የእኛን አቋም የማያንፀባርቅ፣ ወይም ደግሞ አልታዘዝም የሚል ጠላታችን ነው የሚል ዕምነት አለ። እኛ የምናደርገውን፣ የምናመርተውንና የምንጠቀምበትን ሌላው ማመረትና መጠቀም አይችልም፤ መብትም የለውም። ይህንን በይፋም ባይናገሩም የተለያዩ አሻጥሮችን በመፍጠር የየአገሮች አገዛዞች ወደ ውስጥ እንዳያተኩሩና ለለሰፊው ህዝብ የሚጠቅም ነገር እንዳይሰሩ ለማገድ ችለዋል፤ እያገዱም ነው። ለምሳሌ የአቶም ቴክኖሎጂን ከእኛ ውጭ ሌላው ማምረት አይችልም። ለዓለም ህዝብ አደገኛ ስለሆነና ሌላው እንደኛ አርቆ ማሰብ ስለማይችል በፍጹም ለአቶም ቦምብ መስሪያ የሚያገለግሉ እንደ ዩራኒዩም የመሳሰሉትን ከሚፈለገው በላይ አንድ አገር ማምረት አይችልም የሚል የበላይነትና የዘረኝነት ስሜት በግልጽ ይካሄዳል። በሌላ ወገን ደግሞ ሌሎች እንደ ኢራን የመሳሰሉት አገሮች አቶም ቦምብን መሰራት አይፈቀድላቸውም፣ በጣምም አደገኛ ናቸው የምትለው አሜሪካ በመጀመሪያ ጊዜ ሂሮሺማና ናጋሲኪ ላይ አቶም ቦምብን በማፈንዳት ከ70 ሺህ በላይ የሚበልጥ ህዝብ በራዲዮ አክቲቭ ጨረር በአሰቃቂ ሁኔታ ያቀጠለውና የገደለው አርቆ ማሰብ እችላለሁ የሚለው የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ነው። እንደ ኢራን የመሳሰሉ አገሮችን አቶም ቦምብ መስራት አይፈቀድላችሁም እያለ የሚዝተው አሜሪካ እስራኤል፣ ፓኪስታንና ህንድ አቶም ቦምብ ሲሰሩ ዝም ብሎ ተመልክቷል። በእነ ዕምነት ታላቅ ኃይል ነኝ የሚል መንግስትም ሆነ ሌሎች መንግስታት እንደ አቶም ቦምብ የመሳሰሉትን የሰውን ልጅ ዘር የሚያወድሙትንና ለብዙ ሺህ ዓመታት አካባቢንና አየርን በከልው የሚያስቀሩትን እጅግ አሰቃቂ መሳሪያዎች መሰራት የለባቸውም። ይህ ብቻ ሳይሆን፣ ማንኛውም የሰውን ህይወት ሊያጠፉ የሚችሉ የኬሚካል፣ የባዮሎጂካልና ሌሎችም የተወሳሰቡ መሳሪያዎች በመሰራት የዓለምን ህዝብ ማስፈራሪያ መሆን የለባቸውም። የተወሳሰቡ የጦር መሳሪያዎችንም መስራት የስልጣኔ ምልክት አይደለም። ማንኛውንም ችግር በውይይትና በሰለጠነ ፖለቲካ መፍታት ይቻላል። አሁን ባለው ቴክኖሎጂም በተፈጥሮ ውስጥ ያለውን የጥሬ-ሀብት በመጠቀም ሰላማዊ ኑሮ መኖር ይቻላል። ብዙ ነገሮችን እያግበሰበሱና በብዛት ከሚፈለገው በላይ እየበሉ መኖር ጤንነትን ያቃውሳል። በብዛት ማምረትና መጠቀም የሰውን ጤንነት ከማቃወሳቸውም በላይ አካባቢን በከፍተኛ ደረጃ እየበከሉና ሚዛናዊነቱን እያቃወሱት ነው። በዚያው መጠንም አብዛኛው በዚህች ምድር ላይ የሚኖር ህዝብ መንፈስ አልባ እየሆነ ለመምጣት ችሏል። ለምን እንደሚኖርና የኑሮን ትርጉምና ዓላማውስ ምን እንደሆን እንዳይረዳ ለመደረግ በቅቷል። የካፒታሊስቱ ዓለም በተለይም የአሜሪካን ኢምፔሪያሊም በሚሰብከው ወይም በሚያስፋፋው ፀረ-ሳይንሳዊና ፀረ-ፍልፍናዊ ሰበካ የሰው ልጅ እንደ ወንድማማችና እንደ እህትማማችነት የሚታይ ሳይሆን እንደ ጠላት የሚታይ ለመሆን በቅቷል። በተለይም የየአገሩ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የሚለተሪና የስለላ ኤሊቶች አደገኛ ባህርይ በማዳበርና ትዕቢተኞች በመሆን በየአገሩ ውስጥ ተራውና አቅመ-ቢስ የሆነው ዜጋ ሰላማዊ ኑሮ እንዳይኖር እየተደረገ ነው። ስለሆነም በአብዛኛዎቹ የሶስተኛው ዓለም ታላላቅ ከተማዎች ውስጥ ውንብድናና አደገኛ የሆነ የዕፅ አጠቃቀም ተስፋፍቷል። ለአቅመ-አዳም ያልደረሱ ወጣት ሴቶች እየታፈኑና እየተደፈሩ ለመሆናቸው በብዛት የሚሰማ ዜና ነው። ባጭሩ የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምና ግብረአበሮቹ በሚያካሂዱት ከሳይንስና ከፍልስፍና ውጭ በሆነና አመፅን በሚያስቀድም ፖለቲካ ብዙ ህብረተሰቦች እየተናጉ ነው። የየአገሮችም ፖለቲከኛ ነን ባዮች የተወሳሰቡ የጦር መሳሪያዎችን በመስራትና አንደኛው ከሌላው በመኮረጅ የፍጥጫ ፖለቲካ በማካሄድ ላይ ናቸው። ይህ ዐይነቱ የጦር መሳሪያ ምርትና የተወሳሰቡ የጦር መሳሪያዎችን መሰራት በቀጥታ ከግሎባል ካፒታሊዝም ከመጠን በላይ መስፋፋትና የጥሬ-ሀብት ዘረፋ ጋር የሚያያዝ ነው። በዓለም አቀፍ ደረጃ አንድ የወጥ የሆነ አስተሳስብም በመስፋፋቱ በየአገሮች ውስጥ ክሪቲካል አስተሳሰብ እንዳይዳብርና ክርክርም እንዳይደረግ መንገዱ ሁሉ ተዘግቷል። ይህ ዐይነቱ ሁኔታም ለአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምና ለግብረ-አበሮቹ የሚያመች ነው። ሁሉም ነገርና አስተሳሰብ እነሱ በፈለጉት መንገድ መጓዝ አለበት። ሁሉም ነገር ከእነሱ ቁጥጥር ውጭ መሆን የለበትም። ስለሆነም ክሪቲካል አስተሳስብ በማይዳብርበትና ጥያቄም ለመጠየቅ በማይቻልበት ዓለም ውስጥ የዓለም ህዝብ እየተወዛገበና ፍዳውን እያየ ይኖራል ማለት ነው። ይህ ዐይነቱ አካሄድና አስተሳሰብ አንድ ወጥ ሃይማኖት የሰፈነበትን የማዕከለኛውን ዘመን የምዕራብ አውሮፓ ሁኔታ ያስታውሰናል።
ከዚህ ሁኔት ስነነሳ የአሜሪካን ኤምፔሪያሊዝምና ግብረ-አበሮቹ ነጭ ስለሆንና ሌላ ሌላ ቀለም ካለው ጋር ስንወዳደር የምንበልጥና በእግዚአብሄርም የተመረጥን ነን ብለው ስለሚያምኑ በምንም ዐይነት የሌላውን አገር ህዝብ በሰላም የመኖር ፍላጎት አይመኙም። ራሱ ጦርነትን ማካሄድና ውስብስብ ሁኔታዎችን መፍጠር የኢምፔሪያሊስቶች ባህርይ ስለሆነ ከእዚህ የብጥበጣና አገሮችን የማከረባበት ፖለቲካ ሊገቱ በፍጹም አይችሉም። ለብዙ መቶ ዓመታት በመንፈሳቸው ውስጥ የቀረጹት አደገኛ አስተሳሰብ ስላለ ከዚህ ዐይነቱ ጭንቅላት ውስጥ ከተቀረፀ ሰይጣናዊ አስተሳሰብ በፍጹም ሊላቀቁ አይችሉም። በሌላ ወግን ግን ይህ ዐይነቱ ስይጣናዊ አስተሳሰብ በእነ ኩዛኑስ፣ በእነ ላይብኒዝ፣ ካንትና ሄገል እንዲሁም አያሌ የፍልስፍናና የሳይንስ አዋቂዎች የተፈጠረውን ሳይንሳዊና ፍልስፍናዊ አስተሳሰብ የሚፃረር ነው። የመንፈስን ወይም የማሰብ ኃይልን የበላይነት የሚፃረር የአመጽ ፖለቲካ ነው የትላንትም ሆነ የዛሬዎቹ ኢምፔሪያሊስት ኃይሎች፣ የሚሊተሪና የስለላ ድርጅቶች የሚያካሂዱት። የእኛም አገር መሪዎችና የፖለቲካ ተዋንያን ነን የሚሉት በዚህ ዐይነቱ ሰይጣናዊ አስተሳሰብ በመጠመድና የአገዛዝ ፍልስፍናቸው በማድረግ ነው ገነቲቱን አገራችንን ወደ ሲዖልነት ልቀይሯት የቻሉት። አምላክ ሆይ ፀሎታችንን ስማና ቶሎ ብለህ ድረስልንና አድነን ከማለት በስተቀር ባለን በጣም ደካማ አቅም ምንም ማድረግ አንችልም። መልካም ግንዛቤ!!
fekadubekele@gmx.de
www.fekadubekele.com
ማሳሰቢያ:– የዓለም ፖለቲካ በዝቅተኛና ኢ-ሳይንሳዊ በሆነ አስተሳሰብ ባላቸው ፖለቲከኛ ነን በማለት ለሚዘባኑኑ ክፍት መሆን የለበትም። ጊዜው ሳይንሳዊ ጥናትን የሚፈልግና ሰው መሆናችንን የምናረጋግጥበት ዘመን መሆን አለበት። አንድን አገር ታላቅና የተከበረች ማድረግ የሚቻለው በተንኮልና በዝቅተኛ አስተሳሰብ ሳይሆን በፍልስፍናና በሳይንስዊ ዕውቀት ብቻ በመመራት ነው። ስለሆነም ድረ-ገጼን በመመልክት አንዳንድ ግንዛቤ ማግኘት ይቻላል። መተቸትና በተሻለ መልክ ማቅረብም የተፈቀደ ነው። የአንድ ሰው ትንተና በሌላው ተነቦና ተመዛዝኖ ሲቀርብ ሊዳብርና ለመጭውም ትውልድ መማሪያ ሊሆን ይችላል። ከዚህም በላይ የተለያዩ አርዕስቶችን በመምረጥ ስለአገራችንም ሆነ ስለዓለም የፖለቲካ ሁኔታ ዘመናዊና ሳይንሳዊ በሆነ መልክ በቪዲዮ ኮንፈረነስ መልክ ማቅረብና መወያይት ይቻላል፤ የዩቱቭ ቻናልም በመክፈት ማስተማርና መማር ይቻላል።