ዳሂሎን ያሲን
መግብያ
በቅርቡ በዳቮስ የተደረገው የዓለም የኢኮኖሚ ፎረም ስብሰባ ከወትሮው በተለይ መልኩ የዓለምን ትኩረት የሳበ ነበር። ይህ ስብሰባ ዶናልድ ትራምፕ እንደ ዋና ተዋናይ የቀረበበት ብቻ ሳይሆን፣ የዓለምን የወደፊት አቅጣጫ በሚመለከት የደህንነት ስጋት ጎልቶ የታየበት መድረክ ሆኖ አልፋል። በዚህ መድረክ በርካታ ውይይቶችና አስተያየቶች ቢቀርቡም፣ በብዙዎች ዘንድ ታሪካዊ ተብሎ የተመዘገበው እና የትራምፕን ፖሊሲ በግልፅ ቋንቋ የተቃወመው የካናዳ መሪ ንግግር ልዩ ትኩረት አገኘ ማለት ይቻላል ።
ከዚሁ አጠቃላይ አውድ ጋር ተያይዞ በተጨባጭ መልኩ የታየው የደህንነት ስጋት፣ ትራምፕ የዴንማርክ ግዛት በሆነችው ግሪንላንድ ላይ “ይገባኛል” ወይም “ያስፈልገኛል” በሚል መግለጫ ያቀረበው ጥያቄ ነበር። ይህ ጉዳይ የመጨረሻ ብይን ያልተሰጠበት ቢሆንም (the jury is still out)፣ ትንሿ ዴንማርክ ከልዕለ-ኃያል ሀገር ጋር በገጠመችው ሙግት ለጊዜውም ቢሆን በአሸናፊነት ወጣለች ማለት ያስደፍራል። ጉዳዩ እስከ አሁን ዴንማርክ በተለመችው መንገድ እየተስተናገደ ይገኛልና።
በተመሳሳይ ጊዜ የእኛን አከባቢ ያተራመሰው (አከባቢው ትርምስ ያነሰው ይመስል) ሌላ ክስተት ደግሞ ትራምፕ በህዳሴ ግድብ ጉዳይ ላይ ለኢትዮጵያ ያቀረበው “ከግብፅ ጋር ለመደራደር” ትዕዛዝ መሰል ጥሪ ነው። ይህ አጭር መጣጥፍ ዓላማው በዳቮስ ስብሰባ ላይ የታየውን የዓለም የደህንነት ስጋት ለመተንተን ሳይሆን፣ ተዛማጅ የሆነውን የኢትዮጵያ ታላቁ የህዳሴ ግድብ (GERD) ዲፕሎማሲ ፈተና ከዴንማርክ ተሞክሮ አንፃር ለመቃኘት ነው።
የትራምፕ የድርድር ጥሪ እና የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ፈተና
ትራምፕ በቅርቡ በኢትዮጵያ እና ግብፅ መካከል በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ (GERD) ዙሪያ ያለውን ውዝግብ “ለመሽምገል” ያቀረበው ጥሪ ለአዲስ አበባ አዲስ ክስተት አይደለም። ተመሳሳይ ጉዳይ በተለያዩ መልኩ ከዚህ በፊት ተፈትኗልና የተቀሰመ ትምህርት እንዳለ መገመት ይቻላል።
ግብፅ ጥሪውን በፍጥነት መቀበሏ፣ የራሷን ፍላጎቶች ለማስፈፀም እንደ አዲስ እና መልካም እድል መመልከቷ አያስገርምም። የድርድር የጥሪው ገለልተኛ የሆነ የሽምግልና ጥረት ሳይሆን በአንደኛው ወገን ላይ ጫና በማድረግ ሌላኛውን ወገን ለመጠቀም የታለመ መሆኑ ብዙ ምርምር አያሻውም። ከበስተ ጀርባ ያሉትን ገፊ ምክንያቶች ዝርዝር ውስጥ መግባቱ የቱክረታች አቅጣጫ እንዳያስተን ለግዜው እንለፈው።
በ“ሽምግልና” ሽፋን የተከሰተውን የውጭ ግፊት ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ከምትገኝበት የውስጥ ፖለቲካ ምስቅልቅል አንፃር የሚደቅነው ፈተና አቅልሎ ማየት የጉዳዩን ክብደት አለመገንዘብ ብቻ ሳይሆን፣ ሊከተል ለሚችለው አደጋ አስተዋፅኦ ማድረግም ጭምር ይሆናል። ስለዚህ ቁልፉ ጥያቄ፣ ኢትዮጵያ ይህን የተደቀነውን ዲፕሎማሲ ጫና እንዴት መመከት ትችላለች? የሚለው ነው። እንዴት ትወጣው?
በእርግጥ ኢትዮጵያ ልትከተል የሚገባው አማራጭ መንገድ በመንበርከክ ወይም በመጋፈጥ ብቻ የተገደበ አይደለም። ሶስተኛ አማራጭ የሰከነ የተጠና የዲፕሎማሲ ስልት መዘየድ ነው። ዴንማርክ በግሪንላንድ ጉዳይ ከተዘፈቀችበትን አረንቋ በአሸናፊነት ለመውጣት ከተከተለችው ስልት አስፈላጊውን ልምድ በመቅሰም።
የዴንማርክ ግሪንላንድ ተሞክሮ፡ ጫናን ወደ ተቋማዊ ሂደት (institutional process) ማስቀየስ
ዴንማርክ በግሪንላንድ ጉዳይ የተከተለችው አካሄድ ትንሽ ሀገር የልዕለ-ኃያልን ጫና ከመመከት ባለፈ እንዴት የራሳን መሠረታዊ ጥቅም ማስጠበቅ እንደሚቻል የሚያሳይ የዲፕሎማሲ ጥበብ ማሳያ ነው ማለት ይቻላል። ዴንማርክ የተከተለችው የዲፕሎማሲ ስልት ስጠቃለል፣ በልዕለ-ኃያል የሚመጣውን ጫና በትዕግሥትና በብልሃት በመገደብ፣ ውዝግቡን ከፍጥጫ ወደ ሕጋዊና ተቋማዊ ሂደት (institutional process) በማሸጋገር ላይ የተመሠረተ አቀራረብ ነበር።
በዚህ መሠረት ዴንማርክ አጋሮችና መከታዎችን በማሰባሰብ ጉዳዩ ከጊዜያዊ የውዝግብ መድረክ ወደ ተቋማዊ ሂደት ማሸጋገርን አሳካች። ይህም በአንድ ቃል ሲገለጽ፣ የመጫወቻ ሜዳን ለራሷ ጥቅም በሚመች መልኩ የማመቻቸት ብልሃት ነበር።
ዴንማርክ የከተለችው አቀራረብ በአጭሩ በሚከተሉት ዋና ነጥቦች ሊጠቃለል ይችላል፦
- ጉዳዩንበሰላም ለመፍታት ፍላጎት በማሳየት፣ ውዝግቡ ወደ ፍጥጫ እንዳይመራ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ፣ እና ከአሜሪካ ጋር ለመተባበር ዝግጁነቷን መግለጽ ። ለምሳሌ፣ በአርክቲክ የደህንነት ትብብር ላይ ውይይት ለማካሄድ ፍቃደኛ መሆን፣
- ለድርድርየሚቀርቡና የማይቀርቡ ጉዳዮችን በግልፅ መለየት (ቀይ መስመር ማስመር)፣ በተለይ የግሪንላንድ ሉዓላዊነትና ባለቤትነት ለድርድር እንደማይቀርብ በማያሻማ መልኩ ማስረገጥ፣
- ጉዳዩ በጋራ ኮሚሽን አንዲታይ ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ጥረት በማድረግ ውዝግብ ወደ ሂደት ማሽጋገር፣ ይህ አካሄድ ውጥረትን ከማርገቡ በተጨማሪ ጉዳዩ ከፖለቲካ ትዕይንትን ወደ ቴክኒካዊ ድርድር እንድሽጋገር አስችለዋል።
- የNATO እና የአውሮፓ ህብረት(EU) ድጋፍ በማሰባሰብ ከጎኗ ማሰለፍ፣
- የድርድሩንአውድ በማስፋት፣ ጉዳዩ በአሜሪካና በዴንማርክ መካከል ብቻ የሁለትዮሽ ግጭት እንዳይመስል ማድረግ፣ እና ዓለም አቀፋዊ ገፅታ እንዲኖረው ማስቻል፣
- በአለምአቀፋዊ ተቋማት አማካኝነት ጉዳዩ ተገቢውን ትኩረት እንዲያገኝ ማድረግ፣ እና ውዝግቡ ወደ ሕጋዊና ተቋማዊ (institutional) ማዕቀፍ እንዲገባ መግፋት።
በአጠቃላይ፣ ዴንማርክ የተከተለችው አቀራረብ ጉዳዩ ወደ ፍጥጫ እንዳይመራ ከፍተኛ ጥንቃቄ ከማድግ ጎን ለጎን ውዝግቡን ወደ ተቋማዊ ሂደት እንዲሸጋገር በማስቻል፣ መሠረታዊ ጥቅሞቿን እንዲጠብቅ ያስቻላት የተጠና የዲፕሎማሲ ስልት ነበር።
የዴንማር ተሞክሮ ለኢትዮጵያ?
ኢትዮጵያ የዴንማርክን ተሞክሮና ስልት በመጠቀም፣ በ“ሽምግልና” ስም በህዳሴ ግድብ (GERD) ዙሪያ የተቀናባበረውን ጫና እንዴት መቋቋም ትችላለች? የሚለው ጥያቄ የዚህ ጽሁፍ እምብርት ነው። ምንም እንኳን ዴንማርክ በ“የግሪንላንድ ይገባኛል” ጥያቄ ምክንያት የተጋፈጠችው ውዝግብ ከኢትዮጵያ በGERD ጉዳይ ላይ ከገጠማት ጫና ጋር በአውድና በውስብስብነት ቢለያይም፣ የዴንማርክ አቀራረብ ጠቃሚነቱ ሊመዘን እና ሊዳሰስ የሚገባ የዲፕሎማሲ ተሞክሮ ነው። በተለይ ጫናን ከፍጥጫ ወደ ተቋማዊ ሂደት በማሸጋገር ላይ ያተኮረው መርህ ለኢትዮጵያ ጠቃሚ ትምህርት ይሰጣል። ኢትዮጵያ ምን ታድርግ?
በGERD ጉዳይ ላይ ኢትዮጵያ ከዴንማርክ ተሞክሮ ትምህርት በመውሰድ ልትከተላቸው የሚገቡ የዲፕሎማሲ አቅጣጫዎች በመሠረቱ በሶስት አንኳር መርሆች ስር ሊጠቃለሉ ይችላሉ፤ እነሱም፦ (1) ለውይይት ዝግጁነት በግልፅ ማሳየት እና ውዝግቡ ወደ ፍጥጫ እንዳይመራ መቆጣጠር፣ (2) ቀይ መስመሮችን በግልፅ ማስቀመጥ፣ (3) የድርድሩን አውድ ማስፋት እና ወደ ተቋማዊ ሂደት ማሸጋገር ናቸው።
1) ለውይይት ዝግጁነት ማሳየት (Diplomacy of readiness)
በ“ሽምግልና” ሽፋን የሚቀርብ ጥሪ ወደ ንትርክ ወይም ፍጥጫ እንዳያመራ ኢትዮጵያ ከፍተኛ ጥንቃቄ መውሰድ ይገባታል። በዚህ ረገድ የሚያዋጣው አቀራረብ፣ ጥሪውን ከወዲሁ ውድቅ ከማድረግ ይልቅ የድርድርን አስፈላጊነት በመርህ ደረጃ መቀበል እና ለሁሉም ወገን ጠቃሚና ዘላቂ መፍትሔ ለማፈላለግ ዝግጁ መሆኗን በግልፅ ማሳየት ነው።
ኢትዮጵያ ከመጀመሪያው ጀምሮ ከግብፅና ሱዳን ጋር ለመወያየት እና በአስፈላጊ ጉዳዮች ላይ ለመደራደር ያሳየችውን ፍላጎት በማስታወስ፣ ለውይይት እና ለድርድር ምን ጊዜም ዝግጁ መሆኗን ማረጋገጥ ተቀዳሚ ተግባር ይሆናል። ይህ አቀራረብ ኢትዮጵያ እምብተኛ ወይም አፈንጋጭ ሳትሆን ችግሩን በሕጋዊ አግባብ ለመፍታት ያላትን ጽኑ አቋም ከማንፀባረቅ በላይ፣ ዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ ድጋፍ ለማሰባሰብ ተግባራዊ መንገድ ነው።
2) ቀይ መስመር ማስመር (Defining non-negotiables)
መሠረታዊ የሆኑ ጥቅሞች ለድርድር እንደማይቀርቡ በግልፅ ማስቀመጥ ሌላኛው መሠረታዊ ጉዳይ ነው። ስለዚህም ኢትዮጵያ ለድርድር ሊቀርቡ የሚችሉ እና የማይቀርቡ ጉዳዮችን በግልፅ መለየት አለባት። ይህም በአጭሩ “ቀይ መስመር ማስመር” ማለት ነው።
የዓባይ ውሃ አጠቃቀም ቴክኒካል ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ታሪካዊና ፖሎቲካዊ መሆናቸውን ማመልከቱ አስፈላጊ ይሆናል። በዘመናት ላይ የተገነባው ያልተመጣጠነ ፍትሃዊ ወይም ሕጋዊ መሠረት የሌለው የውሃ ድልድልን ይመለከታል። በተለይ ወደ ቅኝ ዘመን የውሃ ድልድል ስምምነቶች መመለስ ወይም ኢትዮጵያን ያገለሉ ዓይነት የ1959 የግብፅ–ሱዳን ስምምነት መንፈስ ያለውን አቀራረብ ጊዜ ያለፈበት ብቻ ሳይሆን፣ በማንኛውም መስፈርት ተቀባይነት የሌለው መሆኑን በማያሻማ መልኩ መግለጽ ያስፈልጋል። በዚህ ውስጥ ሌሎችም ሉዓላዊነትን የሚጻረሩ እና ለድርድር የማይቀርቡ ቴክኒካዊ ጉዳዮችን ሊካተቱ ይችላሉ።
3) የድርድር መድረኩን ማስፋት እና ወደ ተቋማዊ ሂደት ማሸጋገር (Forum shifting & institutionalization)
በመቀጠለም፣ ጉዳዩ በሁለት ሀገራት መካከል ገለልተኛ ባልሆነ ልዕለ-ኃያል አማካይነት የሚጫን “ድርድር” ሳይሆን፣ ዓለም አቀፍና አህጉራዊ የውሃ አጠቃቀም ስምምነቶችንና መርሆችን መሠረት ያደረገ ፍትሃዊ እና ዘላቂ ድርድር እንዲሆን መግፋት ይገባል። ይህንንም እውን ለማድረግ ውይይቱ ከጊዜያዊ ጫና መድረክ ወደ ፍትሃዊና ተቋማዊ ሂደት እንዲሸጋገር ያልለሰለሰ ጥረት ማድረግን ይጠይቃል።
ይህን ጥረት እንዲሳካ የአፍሪካ ሕብረትን በአጠቃላይ እና የናይል ተፋሰስ ሀገራትን በተለይ ከጎን ማሰለፍ የማይታለፍ አማራጭ ነው። በቅርቡ በብዙ የአባይ ተፋሰስ ሀገራት የተፈረሙና ሥራ ላይ የዋሉት የእንቴቤ (2024) የአባይ ሽለቆ ትብብር መሠረታዊ ስምምነት (Nile Basin Cooperative Framework Agreement (CFA) እና ይህን ለማጠናከር የሚያገለግለው የአባይ ወንዝ ሽለቆ ኮሚሽን (NRBC) በዚህ ሂደት ውስጥ ዋና መሠረትና ተቋማዊ መሣሪያ ናቸው። ይህን ፈለግ በመከተል ጉዳዩ የሁለት ሀገራት ውዝግብ ሳይሆን፣ የአባይ ተፋሰስ ሀገራት ጉዳይ ብሎም የአፍሪካ ጉዳይ እንዲሆን ማድረግ ይቻላል።
የዓባይ ግድብ በመሬት ላይ ያለ እውኔታ (fait accompli) በመሆኑ ይህን ተጨባጭ ሁኔታ በአግባቡ መጠቀም ሌላው የድርድር ስልትና አግባብ ነው። በተያያዘ፣ በህዳሴ ግድብም ሆነ በአጠቃላይ በአባይ ወንዝ ውሃ አጠቃቀም ዙሪያ ለሚካሄደው ድርድር ሰፋ ያለ መሠረታዊ ግንዛቤ ለመጨበጥ፣ አሜሪካ ከሜክሲኮ ጋር በኮሎራዶ ወንዝ ላይ ያደረገችውን ስምምነት ተሞክሮ፣ እንዲሁም ቱርክ ከኢራቅና ከሶሪያ ጋር በኤፍራጥስ ወንዝ አጠቃቀም ላይ በተለያዩ ጊዜያት ያደረገችው ውሎችን ማጥናት ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። እነዚህ ተሞክሮዎች እንደ ኢትዮጵያ ሁሉ ራስጌ ተፋሰስ (upstream) ሀገራት ከግርጌ ተፋሰስ (downstream) ሀገራት ጋር የገቡባቸውን የስምምነት ሂደቶች ስለሚያሳዩ፣ ለኢትዮጵያ በGERD እና በአባይ ሽለቆ ውይይት ላይ ተጨማሪ እይታ እና ማጣቀሻ ማዕቀፍ ለመፍጠር ሊያግዙ ይችላሉ።
ማጠቃልያ
ኢትዮጵያ በGERD ጉዳይ የገጠማት ፈተና ዴንማርክ በግሪንላንድ ጉዳይ ከተጋፈጠችው ውዝግብ በብዙ መልኩ የሚለይ መሆኑ ግልፅ ነው። ሁለቱ ሃገራት የገጠማቸው ፈተና ከአንድ ምንጭ ከመሆኑ ባሻገር ከዚህ በላይ እንደተመለከትነው ኢትዮጵያ ከዴንማርክ መቅስም የሚገባት ጠቃሚ ተሞክሮዎች እንዳሉ ተስተውሏል።
ትምህርቱም በዋናነት፣ ኢትዮጵያ በ“ሽምግልና” ሽፋን የሚቀርብ ጫናን ትዕግሥት በተሞላ ዲፕሎማሲ (diplomacy of patience) እና በብልሃት በመገደብ፣ ውዝግቡን ለእርሷ ወደሚመች ፍትሃዊና ተቋማዊ ሂደት (institutional process) የማሸጋገር ዕድል እንዳለ ነው።
በመጨረሻም ኢትዮጵያ በዓባይ ግድብ ላይ ያላትን መሠረታዊና ዘላቂ ጥቅሞቿን ለማስከበር መወሰድ የሚገባቸው አማራጮች ትራምፕ ያነጣጠረበትን የኖብል ሽልማት አሳልፎ መስጠትን ወይም ማስረከብን ሊያጠቃልል ይችላል ይሆን? የሚለውን ጥያቄ ልነሳ ይችላል። አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ አንድ መሪ የሃገሩን ዘላቂ ጥቅም ከማስበር አኳያ መክፈል ያለበት አነስተኛ መስዋዕትነት ነውና። የቨንዙለዋ ማርያ ማቻዶ ተሞክሮን ይመለከታል።