ድሮ በልጅነቴ እናቴ ከፍየል ቆዳ የተሰራ ማህደር ያለውን ድጉስ ዳዊት ሰጥታ ቄስ ትምህርት ቤት ዳዊት እንድደግም ልካኝ ነበር፡፡ መምህራችን ሲፀልዩ አስታውሳለሁ፣ እንደ አይሁዶች ጭንቅላታቸው እየወዘወዙ ነበር፡፡ታዲያ የሚነቀላፋ ተማሪ ካገኙ አንተ “ፃረሞዳረሞ” ብለው ይገስጹታል፡፡
የኋላ ኋላ ፃረሞዳረሞ ሰዎች ወደ መንፈሳዊ ቦታ ሊሄዱ ሲሉ እንቅልፍ የሚለቅባቸው ጋኔል መሆኑን አወቅሁ፡፡ ታዲያ እኛ መምህሬ አንድ እኛ ሰፈር የነበሩ እኛ መምሬ አብደላ ብለን የምንጠራቸው አብሿም ፊደል አስቆጣሪ ነበሩ፣ እሳቸውንም ሲገኟቸው “ፃረሞዳረሞ” ብለው ነበር የሚጠሯቸው፡፡ ለእሳቸው ፃረሞዳረሞ ትርጉሙ ሰውን በቁሙ እንዲያንቀላፋ የሚያደርግ፣ መጥፎ ሃሳብ እንዲያስብ የሚያደርግና ሰዎችን ከህይወት መስመር የሚያስወጣ መንፈስ ነው፡፡
እዚህ ካናዳ ከመጣሁ ከአስር አመት በላይ ሆኖኛል፡፡ መቼም ሰሜን አሜሪካ ሲነሳ እስከ -40 ድ.ሴ. የሚደርሰው የክረምቱን ቅዝቃዜና ከ38 ድ.ሴ በላይ የሚሆነውን የበጋውን ሙቀት አንድ ነገር ሳይሉ ማለፍ አይቻልም፡፡ አሁን የለሁበት የካናዳ ክፍለ ሃገር ግን ለአፍሪካውያን ቆዳ ክረምቱም ሆነ በጋው የከፋ አይደለም፡፡ እንደ ስሙ ቆነጆ የሆነ ቢዩቲፉል ብርቲሽ ኮሎምቢያ ነው፡፡
ወደ ብርቲሽ ኮሎምቢያ የመጣሁት ከዘጠኝ አመት በፊት ነው፡፡ ከዚያ በፊት የምኖረው ቶሮነቶ ነበር፡፡ ቶሮነቶ ሳለሁ አስጠግታኝ እኖረ የነበረኩባት ባለውለታዬ ሴት ወደ ብርቲሽ ኮሎምቢያ መሄዴ ነው ስላት፣ ዝናብ ይበዛዋል፣ ደግሞ አየሩ አዘውትሮ ጭጋጋማ ነው አለችኝና የአየር ጠባዩ ደግሞ ሰዎችን ድብርት ውስጥ ከቶ እራሳቸው እንዲያጠፉ ሊገፋፋ ይችላል የሚል ጥናት አለ አለችኝ፡፡
በግዜው ስራ ያልነበረኝና ቤተሰቤን ሃገር ቤት ትቼ የመጣሁ በመሆኔ ብዙ የድብርት ምልክቶች ይታዩብኝ ስለነበር ለእኔ ጤንነት አስባ እንደነገረችኝ አስታውሳለሁ፡፡ እውነት ነው የዚህ ሃገር ዝናብ በሃገራችን እኝኝ ብላ የሚባለውን የነሃሴ ዝናብ ነው የሚመስለው፡፡ በዚያ ላይ ደግሞ ሁሉም ነገር የሚታየው ከግራጫው ድባብ ስር ነው፡፡
በዚሁ ሰሞን አነድ ወዳጄ ልቤ ብሎ የሚጠራኝን ሰአሊና የሚዲያ ግራፊክስ ባለሞያ፣ እዚህ ከመምጣቱ በፊት ማለት ነው፣ ወዳጄ ዮናታን ሞገስን ከግራጫው ድባብ ስር ያለው የህይወት ምስቅልቅሎሽ ገና የአርባዎቹን ጎልማሳነት ሳያጣጥም፣ ሴትዮዬ ለእኔ በፈራችልኝ መንነገድ ሳይሆን አልቀረም? ወይም … ወደ የሚቀጥለው አለም ሳንሰባበት አመለጠኝ፡፡
አሁን እዚህ በምኖርበት ሃገር ስራ ማግነት ብርቅ እየሆነ መጥቷል፡፡ ሰዎች ስራ ሳያገኙ አመት የሚያልፍበት ሁኔታ እየተፈጠረ ነው፡፡ በእርግጥ በአውሮፓና ሰሜን አሜሪካ መኖር ምን እበላ ይሆን የሚያሰብል ጥያቄ የለም፡፡ ገንዘብ ባይኖር እንኳን ፉድ ባንክ ሄደህ የሚበላ ነገር በዘንቢሎች ተሸክመህ ወደ ቤትህ መሄድ ትችላለህ፡፡ በዚያ ላይ መንግስት የዜጎቹን መሰረታዊ ፍላጎት ለሟሟላት ብዙ የእርዳታ መንገዶችን አመቻችቷል፡፡ እንዲህም ሆኖ ግን መስራት እየቻልክ ስራው ሲጠፋ ድብርት ውስጥ መግባት አይቀርም፡፡
እዚህ ሃገር፣ ሃገር ቤት የተሳካላቸው የነበሩ ሰዎች መጥተው ህይወትን እንደገና ሀ ብለውን ነው የሚጀምሩት፡፡ ሃገር ቤት ማስተርስና ፒኤች.ዲ ድግሪ ያላቸወ ሰዎችን ጽዳት ሲሰሩ ወይንም ስጋ መሸጫ ቤት ስጋ ሲዘለዝሉ ማየት የተለመደ ነው፡፡ ክብር ሃገር ቀረ…
እዚ ሃገር መጥተው የተማሩ ሰዎችም ቢሆኑ ብዙ ውድድር አለባቸው፡፡ በተለይም በአንዳንድ የትምህርት ዘርፎች በመጀመሪያም ሆነ በሁለተኛ ድግሪ የተመረቁ የካናዳ ዜጎች በየማክዶናልዱና ቲም ሆርተን ተቀጥረው ሲያሰተናግዱ ማየት የተለመደ ነው፡፡ እንደነዚህ አይነት ስራዎች ተሰርቶ ደግሞ ገንዘቡ ከቤት ክራይና ከምግብ ፍጆታ ያለፈ ጠብ የሚል ነገር የለውም፡፡
አንድ በጡረታ የተገለለ ወዳጄ አለ፡፡ ሁለት ማስተርስ ድግሪ ከተለያዩ ሁለት የውጭ ሃገራት አሉት፡፡ እዚህ ካናዳ፣ ናቫሰኮሻ ክፍለ ሃገር በአድሚራል ሎው ማሰተርስ ድግሪ አለው፡፡ በተማረበት መስክ ስራ ማግኘት ሳይችል ነው ጡረታ የወጣው፡፡ እኔና እሱ ስንገናኝ የቀለጠችና አታድርገው በኛን ወግ ሳናወጋ አናልፍም፡፡
አንድ ግዜ ነው አሉ ፒያሳ የነበረው በቀለ ስጋ ቤት መሰለኝ አንዱ የራበውና እጁ ያጠረ ሰው ጠጋ ብሎ እባካችሁ ትንሽ ሩብ ኪሎ ስጋ ስጡኝ ይላል፡፡ እሺ ብለው የእርዳታ ያህል የጠየቀውን ያክል ሰጡት፡፡ ትንሽ ቁርጥ ቢጤ ከበላ በኋላ ይጠበስልኝ ብሎ ስጋ ወደ ኩሽና ይልካል፡፡ አሰተናጋጁ ለሰውዬው የሰጠውን ቁጥር ይዞ መጥቶ ቁጥር ሰማኒያ ብሎ ይጣራል፡፡ ይሄን ግዜ የሚበላውን ጥብስ እያሰበ አፉን ምራቅ የሞለው ሰው አቤት እዚህ አለው ይለዋል፣ ይሄን ግዜ አስተናጋጁ ምንም የተጠበሰ ስጋ ይዞ ሳይመጣ ቀለጠች አለው ይባላል፡፡
ታዲያ ወዳጄ ቤት ለቅሶ ገጥሞት ላስተዛዝን ሄጄ፣ ወዳጄ ማሰተርስ ድግሪ ሲይዝ የተነሳውን ግድግዳ ላይ የተሰቀለ ፎቶ አየሁና በጣም ወጣት ቢሆንብኝ ያ ማን ነው ብዬ ጠየቅኩት፡፡ መልሱ አጭር ነበር፣ ቀለጠች አለኝ፡፡
የካናዳን ኢኮኖሚያዊ ህይወት ሁለት ሞገዶች አናውጠውታል፡፡ የመጀመሪው ኮቪድ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የሩሲያ- ዩክሬን ጦርነት ነው፡፡ የቤት ክራይ መቶ ፐርሰንት በሚባል ሁኔታ ጨምሯል፣ መሰረታዊ የሚባሉት የምግብ አይነቶችም ላይ ጭማሪ ተደርጎባቸዋል፡፡ አሁን አሁን እኔ በምኖርበት አካባቢ ነጭ ቤት አልባ የጎዳና ተዳዳሪዎችን ማየት እየጨመረ መጥቷል፡፡
ታዲያ እኔና ይህ ወደጄ አዳዲስ ቤት አልባ ሰዎችን ስናይ የወለዬዋን አባባል ደጋግመን እንለዋለን፡፡ በኋይለ ስላሴ ዘመን ነው አሉ፣ አንደት ባለበዙ ዘመድንና ሃብታም ቤተሰብ የነበራት የገጠር ነዋሪ የነበረች ነካ ያደረጋት ወለዬ ዘመዶቿ በበቅሎ ጭነው ወደ ፀበል ይወስዷታል፡፡ ይህን ግዜ የእሷ ቢጤ የሆነች ግን ዘመድ የሌለት ሰው እመንገድ ላይ ያአቆረ ውሃ በጫት እንጨት እያማሰለች ታያለች፡፡ እበቅሎዋ ላይ እንዳለች፣ እየተግለበለበች ደግሞ ይህች ምንድን ነች ብላ ጠየቀች፡፡ በአንድ ድምጽ እብድ አሏት፡፡ ይህን ግዜ፣ መገን አተድረገው በኛ ብላ አለፈች አሉ፡፡
አብዛኛው ስደተኛ የሶስት ወር ደሞዙ ቢቆም ሁሉም የጎዳና ተዳዳሪ የሚሆን ይመስለኛል፡፡ እንዲህም ሆኖ ግን የእንግሊዘኛ የመናገር ችሎታውን እያሻሻለ የዱሮ ማንነቱን ረስቶ አዲሱ ማንነቱን ተቀብሎ እራስን ከሁኔታዎች መቀያር ጋር አስማምቶ ለሚኖር ሰው፣ ካናዳም ሆነ አሜሪካ ብዙ እድለኞችን የሚፈጥሩ ሃገራት ናቸው፡፡
ካልሆነ ግን ነገሮች ቀስ በቀስ ድብርት ውስጥ ይከቱናል፡፡ ከዚያም የአልኮል፣ዕጽ…ተጠቂዎች እንሆናለን፡፡ ከዚይም በፍቃደኝነትም ይሁን …ጉዞ ወደሚቀጥለው አለም ይሆናል፡፡ ወዳጄ ልቤ ሰኣሊ ነው ብዬም አልነበር፣ ሁለታችን ስንገናን እንዲህ እንል ነበር፡፡ “የስነ ጥበብ ሰው ካገሩ ከወጣ ከባህር እንደወጣ አሳ ማለት ነው፡፡”
ሀገር ቤት መድረኩ አለ፡፡ ጋራ ሸንተረሩ፣ እጣኑ፣ ኩበቱ…ከልጅነታችን ጀምሮ እይታችንን የቀረጹት ነገሮች እዚያው ጥለናቸው ነው የመጣንው፡፡ የስነ ጥበብ እትብታችን እዚያ ነው የተቀበረው፡፡ እዚህ በስደት አለም ከእትብት ገመዳችን የተባጠስን ያህል ሆኖ ነው የሚሰማን፡፡ ይህን ተከትሎም፣
ተመኘ ቢጨንቀው፣ የሚነባው እንባ
ጎርፍ ሆኖ እንዲወስደው፣ ካለመኖር አንባ፡፡
የሚለውን የፕ/ር ደበበ ሰይፉን ግጥም ውስጣችን ሁሌ በገደል ማሚቱ አስተጋብቶ ነው የሚያሰማን፡፡
በስደት ዓለም ደግሞ ሁለት ስራ ሰርተንም ቢሆን የእለት ወጪያችንን ከሸፈን በኋላ ግዜ አግኝተን
ጽሑፍ ብንጽፍ፣ ስዕል ብንስል…እንኳን ለስራችን አይኑና ጆረውን የሚሰጠን ሰው ማግኘት አስቸጋሪ ነው፡፡
አንዳንዱ ጆሮህን ሰጥተህ ካዳመጥከው እንደዛ ፈሪሳዊ ፀሎት አምላኩን ማመሳገኛ ሲያደርግህ ትሰማዋለህ፡፡ እንደዚህ ተምሮ መና ያላደረከኝ አምላክ ተመስገን፡፡ እኔም እሱም የምንሰራው ስራ የታችኛው የኑሮ ደረጃ የሚኖሩት ሰዎች ስራ ነው ይላል፡፡ የሚሉትን ሁሉ ተቋቁመህ ስትፍጨረጨር ካየህ ደግሞ፣ የትም አይደርስም፣ ያ እዚያ፣ዩቢሲ.. ዩንቨርስቲ ተምሮ ዶክትሬት የተመረቀው አሁንም እዚያው ሮና ስቶር እቃ ሲያመላልስና ጣውላ ሲሸከም ነው የሚውለው ብሎ በቀጥታ ወይንም በገደምዳሜ ይነግርሃል፡፡
ቀስ በቀስ ውስጥህ ሲሞት ይሰማሃል፡፡ ከዚያም እራስህንም በነዚያኞቹ ልክ መከርከም ትጀምራለህ፡፡ እምቢ ካልክ ደግሞ ፈረንጅ ሃገር ያለው ፃረሞዳረሞ ጋኔል አረቄና ዕጹን ያቀብልሃል፡፡ ይኸው መሰለኝ ኮመዲያን ልመንህ ታደሰና ድምጻዊ ቴውድሮስ ታደሰ ከህይወት መስመር ያስወጣብን፡፡
መቼም ጥቂት የማይባለው ሃበሻ ተንደርደሮ መፍረድን ባህሉ ያደረገ ስለሆነ ነገሮችን በአንተ አይን እንዲያይልህ መሞከር ከንቱ ልፋት ነው፡፡ እንደው ዝም ብለው ስም እየሰጡህና ስምህን እያጠፉ የኑሮ ቀንበሩን ያከብዱብሃል፡፡ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ከመጠን በላይ ዕጽ ተጠቅመው ሲሞቱ፣ እራሳቸውን ሲያጠፉ ደግሞ፣ እራሳቸው ገፋፍተው ገደል ጫፍ ላይ ካደረሱህ በኋላ የማይሆን ህይወት ውስጥ ገብተህ መውጫው ቁልቁል ወደ እንጦሮጦስ መግባት ነው ብለህ ህይወትህ ላይ ስትፈርድ ደግሞ የቤት ክርስቲያኑ ነጠላ ለባሽ ጋኔል እርኩስ መንፈስ ነው እንደዚህ ያሰደረገው ብሎ ይበይናል፡፡ እዚህ ጋር ፃረሞዳረሞው ማን ነው?
እኖራለሁ ብለህ ጠብቀህ የመጣህው ህይወትና በገሃድ እየኖረከው ህይወት መካከል የውቂያኖስ ትልቅነቱን ያህለ ክፍተት መኖሩን ስትገነዘብ አምላክህን ለመለማመጥና ለመለመን እንደየ እምነተህ ወደ ሐይማኖት ተቋማት ብቅ ማለትህ አይቀርም፡፡
እዚያ ደግሞ ሌላ እራስምታት ነው የማገጥምህ፡፡ ቄስ ወይንም ፓስተር እገሌ አዲስ ቤ/ክርስቲያን ከፍተው ከመንግስት የሚሰጠውን ማቋቋሚያ ገንዘብ እንክት አድረገው ነጩት ይሉሃል፡፡ ወይንም ደግሞ አባ እገሌ የእንትናን ሚስት ሲያባለጉ ተያዙ፡፡ ሁል ግዜ የቡድን ጸብ የማይጠፋባት ቤ/ክርስቲያን፣ በሁለት ቄሶች ወይም ፓስተሮች መካከል ለሚነሳ ፉክቻ ለአባልነት ሲመለምሉህ ታገኛቸዋለህ፡፡
በቃ ነገሮች ሁሉ ወደ የነፍስ ጸልመተ ሌሊትህ ያጣድፉሃል፡፡ የሐይማኖት ተቋማት የህብረተሰቡን ችግር ለይተው ለዛ መፍተሄ መስጠት ሲገባቸው የማይገባ ቦታ ተዘፍቀው ነው የምታገኛቸው፡፡ አዲስ መጤው ምን አይነት ተግዳሮት እንደሚያገጥመው ከማስተማር ይልቅ በረጀሙ የታሰረ ዶሮ አድርገው ነው የሚያዩህ፤ የት አባቱ ይደርሳል አይነት ነገር፡፡
ክርስቶስን እየሰበኩ ገንዘብ ሲሰሩ ነው የሚገኙት፡፡ የኮሚኒቲ ሴንተሩም ቢሆን ፖለቲካና ዘርን ተጫምቶ ሲመላለስ ነው የምታየው፡፡ እንግዲህ ለወጣቱና ጎልማሳው ማን ይድረስለት? እኛም በዛገ አይናችን ይህን መከራና በላ እንድንታዘብ ተፈርዶብናል፣ የመረገም ያህለ ውስጣች እያለቀሰ እዚህ አለን፡፡
እዚህ በምዕራቡ አለም ሁሉም ነገር የምግብ ጠረጴዛው ላይ አሉልህ፡፡ መጽሐፍት እንደሚነግሩን፣ “አነብር እም ቅድሜከ ማይ ወእሳት ፣ ዴእ እዴከ በዘፈቀድከ” ነው ነገሩ፡፡ ውሃና እሳት በፊት ለፊትህ አስቀምጬልሃለው፣ እጅህን ወደ ፈቀድከው ጨምር ነው ነገሩ፡፡
ነፍስ ይማር፣ ነገሩ ግን ደበበ ሰይፉ እንደገጠመልን፣
ለምን ሞተ ቢሉ
ንገሩ ለሁሉ
ሳትደብቁ ከቶ!
“ከዘመን ተኳርፎ
ከዘመን ተጣልቶ፡፡” ነው ፡፡
አስቻለው ከበደ አበበ
ሜትሮ ቫንኩቨር፣ ካናዳ