ፋሽስታዊው የኦህዴድ ብልጽግና አገዛዝ እንደዚህ ወቅት፤ ከፍተኛ ውጥረት ደርሶበት አያውቅም። በሁሉም ዘርፎች የከሰረና የወደቀ፤ በአብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ የተጠላና በዓለም ሕዝብም የተናቀ አገዛዝ ነው።
የኦሮሙማን ኩሻይት የግዛት ተስፋፊነት (Cushite restoration and territorial expansionism) መርህና ግብ ተከትሎ የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም ለመታደግ አይቻልም። ይህ ጉዞ ከአድዋ መንፈስ ጋር አብሮ አይሄድም። ይህ አደገኛ የሆነ የከፋፍለህ ግዛውና ከፋፍለህ ብላው አገዛዝ፤ ራሱ ከፈጠረው አጣብቂኝ እንዴት እንደሚወጣ አያውቅም ብል አልሳሳትም። በመሆኑም፤ ይህ ስርዓት መገርሰሱ አይቀርም፤ ደግሞ የውድቀት ጉዞውን ከጀመረው ቆይቷል፡፡ በሰው ህይዎትና በኢኮኖሚው ላይ ከፍተኛ ዋጋ ማስከፈሉ ግን አይቀርም።፡ የአማራ ፋኖ ትግሉን ማፋጠን ያለበት ከዚህም አንጻር ነው የሚል ግንዛቤ አለኝ።
የአማራ ፋኖ ውህደት ለዛሬ እንጂ፤ ለነገ ሊሆን አይችልም!
ብዙ ጉዞ ወደፊት እያለ፤ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን በስልጣን ሆነ በሌላ ምክንያት የገመድ ጉተታ አያለሁ። ይህንን ጉተታ ከጀርባ ሆነው ግፉበት የሚሉ ኃይሎች እንዳሉ አውቃለሁ።፡የአማራ ፋኖ ውህደት የግለሰቦች፤ የመንደር፤ የጎጥና የሥልጣን ግብግብ አይደለም የሚልም እምነት አለኝ። ይህ የእኔ እምነት ብቻ ሳይሆን የብዙሃን አማራውና የአገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያኑ ሁሉ እምነት እንደሆነም አምናለሁ፡፡
የአማራ ፋኖ በሁለት ዓመታት ውስጥ ያሳየውን ጀብዱ ያሳየ ኃይል ፈልጌ ላገኝ አልቻልኩም። ይህ ጀብዱ ብዙ ዋጋ ተከፍሎበታል። ብዙ ጀግኖች መስዋእት ሆነውበታል። ንጿሃን ወገኖቻችን በድሮን፤ በጀት፤ በታንክ፤ በሞርታር ተጨፍጭፈዋል። ግዙፍ መሰረተ ልማት ወድሟል፤ የረሃብተኛው ህዝብ ቁጥርም ጨምሯል። ዐብይ አህመድ አሊ በአማራው ሕዝብ ላይ አስቸኳይ አዋጂ ይፋ ካደረገ ወዲህ ብቻ በአማራው ክልል ላይ 200 የድሮን ጭፍጨፋ አካሂዷል። የዐብይ ጀኔራሎች የአማራውን ሕዝብን ካላምበረከከን በስተቀር ጭፍጨፋውን አናቆምም ብለው ዝተዋል። እንደዚህ ያለ አረመኔነት ታይቶም፤ ተሰምቶም አያውቅም ብል አልሳሳትም።
ዐብይ አህመድ አሊ የሚመራው የኦህዴድ ብልጽግና አገዛዝ፤ የአማራውን ሕዝብ በፖለቲካው፤ በፋይናንሱ፤ በኢኮኖሚው፤ በመሬቱ፤ በባህሉ፤ በእምነቱ፤ በባጀቱ፤ በውጭ ግንኙነቱ ወዘተ ካላመከነው በስተቀር የጀመረውን እልቂት አያቆምም። በቅርቡ በጎጃም ቀጠና የሚንቀሳቀሰው አንድ የሥርዓቱ ጦር አዛዥ (ብርጋር ጄኔራል አዲሱ መሀመድ ይባላል) በአዳራሽ ለተሰበሰው ህዝብ ያስተላለፈውን እዚህ ላይ ማንሳት ይገባኛል፡፡ እብሪተኛው ጄኔራል የአማራን ህዝብ ለመጨረስ ‹‹ዘመናዊ መሣሪያ ታጥቀናል፤ የፈለገውን ያህል ቢፈጅም ሳንጨርሰው እንመለስም›› ነበር ያለው፡፡
ይህ ጨካኝና ነውረኛ ፋሽስታዊ ስርዓት፤ አማራን ህዝብ ለመጨረስ የሚጠቀምባቸው መሳሪያዎች ብዙ ናቸው፡፡ ከቀየው ማባረር፤ በድሮንና ጀት፤ ታንክና ሞርታር መጨፍጨፍ፤ ወጣት ሴቶችንና እናቶችን መድፈር፤ የገበሬውን ማሳ ማውደም፤ ሕዝብ እንዲማረር ማስራብ፤ አማራው እርስ በእርሱ እንዲናከስ፤ በጎጥና ጥቅም መከፋፈል፤ ራሱ እየገደለ የአማራ ፋኖ ገደለህ ብሎ ማመካኘት፤ ለሰላምና እርጋታ ማነቆ የሆነው የአማራ ፋኖ እንጂ እኔ አይደለሁም ማለት፤ የአማራ ፋኖ በውህደት እንዳይደራጅ የተሳሳተ መረጃ አዘውትሮ ማሰራጨት ስልቶቹ ናቸው።
ይህንን ሁሉ ስኬታማ ለማድረግ ዐብይ አህመድ ብዙ መቶ ሚሊየን ዶላር ለፕሮፓጋንዳ ብቻ ፈሰስ ያደርጋል። ይህ ጠቅላላ ሁኔታ የሚያስተምረን ዋና ነገር፤ የአማራ ፋኖ የአማራውን አሰቃቂ ተግዳሮቶች ሊወጣው የሚችለው በውህደት ብቻ መሆኑን ነው።
ጥናቶችና ምርምሮች የሚያስተምሩን እሴቶች፤ ውህደት ስኬታማ እንዲሆን ከተፈለገ የእርስ በእርሥ መተማመን (Mutual Trust) ፤ የዓላማ ግልጽነትና ጽናት( Unity of purpose and dedication to it) ፤ ከግለሶቦች ፍላጎት ላይ ሳይሆን ከህዝቡ ፍላጎትና ምኞት፤ ለጋራ ዓላማ (በጋራ መስራት (Team Work)፤ ደንብና ስነስርዓት ማክበር የሚሉ ይገኙበታል።
ውህደት ስል፤ በአንድ ድምጽ በመናገር፤ ለአንድ ዓላማ በመቆም፤ በፖለቲካው፤ በሚሊተሪው፤ በውጭ ግንኙነቱ፤ በቁሳቁሱ፤ በሚዲያው፤ በኃይል አሰላለፉ ወዘተ እየተናበቡና እየተደጋገፉ በመንቀሳቀስ ማለቴ ነው። ውህደት ስል ምስጢርን መጠበቅ ማለቴ ነው። ውህደት ስል፤ እኔ ከማለት ይልቅ እኛ ማለትን እንምረጥ ማለቴ ነው።
በኔ ግምገማ፤ ውህደት ሊሳካ የሚችለው የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት (አፍሕድ) እና የአማራ ፋኖ ብሄራዊ ኃይል (አፍብኃ) እንደ ድርጅት አንድ ወጥ ዓላማና አንድ ወጥ አደረጃጀት የበላይ አመራር ሲኖራቸው ነው። ድርጅቶቹ ከስመው አዲስ አንድ ወጥ የአማራ ፋኖ ድርጅት ይመሰርታሉ ማለት ነው። ይህ ሲሆን፤ የሥልጣን ሽሚያ ሊኖር አይችልም፤ የገመድ ጉተታ አይከሰትም። ሁልጊዜም ቢሆን፤ በሌሎች አገሮች ትግል የሚታየው ትምህርት፤ የስልጣን ውዝግብ ከተከሰተ ዋናውን የህልውና ዓላማ ይበክለዋል። ይህ ውዝግብ ከተከሰተ ዋጋ ያስከፍላል። ከፍተኛ ዋጋ የሚከፍለው የአማራው ህዝብ ነው።
ተስፋ የማደርገው የአማራ ፋኖ ይህንን ሁኔታ ገምግሞ ችግሩን በብልሃትና በጥበብ ባስቸኳይ እንዲፈታው እመክራለሁ። የሥልጣን ሽሚያ ከሴራ ፖለቲካ ጋር ግንኙነት አለው። የሴራ ፖለቲካ ለአማራ ጠላቶች መሳሪያ ይሆናል። ለኦህዴድ ብልጽግና፤ ለህወሃት፤ ለኦነግ ወዘተ መሳሪያ ይሆናል። ባጭሩ፤ እኔ አደራ የምለው፤ ዋናውን የአማራ ህልውና ትግል ስኬታማ ለማድረግ የምንችለው ‹‹ድር ቢያብር አንበሳ ያስር›› የሚለውን የአባቶቻችን ስልታዊ ምክር ስንተግብረው ብቻ ነው። በርግጥ የዐቢይ አህመድ አሊ ብልጽግና ሥርዓት፤ ‹‹አንበሳ ነው” እያልኩ አይደለም፡፡ ሥርዓቱ፤ የዘመናችን ጨካኝ ጅብ መሆኑን ዘንግቸውም አይለም፡፡
በዚህ አጋጣሚ እኔ የሚገባኝ፤ በሁሉም የአማራ ክፍለ ሃገሮች የተሰማራው የአማራ ፋኖ ሰራዊት የሚፈልገውና የሚጠይቀው፤ ውህደቱ ስኬታማ እንዲሆን ነው። የአማራ ፋኖ መሪዎች ይህ ግዙፍ ኃይል የሚጠይቀውን የተቀደሰ ጥያቄ መተግበር አለባቸው። ይህ ታሪካዊ ግዴታ ነው። በተመሳሳይ፤ የአማራን ህዝብ የህልውና ትግል የምንደግፈው ሁሉ በጥቃቅን ልዩነቶች ላይ የምናደርገውን ትኩረትና ለዚህ ቡድን፤ ለዚያ ቡድን የምናሳየውን አድልዎ የማቆም ግዴታ አለብን።
የአማራው ውህደት የሚያስፈራው ማንን ነው?
በመጀመሪያ ደረጃ የኦህዴድ ብልጽግናን ነው። በሁለተኛ ደረጃ ህወሃትን ነው። በሶስተኛ ደረጃ በአማራው ስም የሚነግዱትን አማራ ጠል፤ ለሆዳቸው ያደሩትን አማራዎችን ነው። በአራተኛ ደረጃ የአማራውን ሕዝብ ጀግንነት (ደጋግሜ የአድዋ መንፈስ የምለው)፤ ለነጻነቱና ለመብቱ ቆራጥነት ስጋት የሆነባቸው የውጭ መንግሥታትን እንደ ግብጽ፤ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ወዘተ ያሉትን ነው።
የፋኖ ውህደት በዘገየ ቁጥር ትዝ የሚለኝ ትግሉ ቀላል አለመሆኑን ነው፤ ብዙ መሰናክሎች እንዳሉ እገነዘባለሁ። ብልህነት (Wisdom) የሚያስፈልገው ለዚህ ነው። መቻቻል፤ ቅንነት፤ መተሳሰብ፤ መደጋገፍ የነገውን ማሰብ አስፈላጊ ነው። ቅንነት ካለ የሚሰራው ስራ ግዙፍ ስለሆነ ሁሉም ሚና ይኖረዋል። ሁልጊዚ ማሰብ የሚያስፈልገው ዓላማን ስኬታማ ከማድረጉ ላይ ነው።፡
የአማራ ፋኖ መሰናክሉን ሁሉ ሊወጣው የሚችለው፤ ሁል ጊዜም ቢሆን ምሰሶውና ደጀኑ የአማራው ሕዝብ ህልውና የፍትህ ትግል መሆኑን በማጤን ነው። የአማራ ፋኖ በአማራነት የሚታገልበት መሰረታዊ ምክንያት የአማራው ሕዝብ በማንነቱ ተለይቶ በተክታታይ እልቂት ስለደረሰበት ነው። በየትኛውም ኢትዮጵያ ክፍል የሚኖረው አማራ፤ የአማራ ፋኖን ትግል የሚደግፍበትም ምክንያት ይኼው ነው። ስለሆነም፤ ሕዝብ የደገፈው ትግል ሊሸነፍ አይችልም።
የአማራ ፋኖ ከማሸነፍ ውጭ ሌላ አማራጭ የሌለው መሆኑን በተደጋጋሚ ስንገልጸው ቆይተናል፤ አሁንም ማስታወስ እወዳለሁ፡፡ ከማሸነፍ በስተቀር የአማራ ፋኖ ሌላ ምርጫ የለውም። ቢሸነፍ፤ የሚጠብቀው፤ ምንም ርህራሄ የሌለው የኦህዴድ ብልጽግና አገዛዝ በያለበት ይጨፈጭፈዋል። አንድ በአንድ እየለቀመ ይጨርሰዋል፡፡ ለዚህ የኦህዴድ/ብልጽግና የጭካኔ እርምጃ ደግሞ፤ የብአዴን መዋቅር በሚገባ ይጠቅመዋል፡፡
ወርቃማው እድል ቢባክን ማን ተጠያቂ ይሆናል?
ሁላችንም ተጠያቂ እንደምንሆን አሳስባለሁ። ቁም ነገሩ ግን፤ የአማራ ህዝብ የህልውና ትግሉን ከፊት ሆኖ እየመራ ያለው የአማራ ፋኖ እጁ ላይ ወርቃማ እድል ገብቶለታል የሚለው ነው። ይህ በብዙ መስዋእት የተገኘ እድል ከመከነ፤ የአማራው ሕዝብ ባሪያም ሆኖ የሚኖርባት ኢትዮጵያ አትኖርም። የችግሩን ጥልቀትና ክብደት ማመዛዘን ግድ ይላል።
አካባቢንም መቃኘት አስፈላጊ ነው። የአፍሪካ ቀንድ ጂኦ ፖለቲካ በየቀኑ እየተለዋወጠ ነው። የአማራ ፋኖ ለውጡን ለአማራው ሕዝብ ፍትሃዊ ትግል ሊጠቀምበት የሚችልበት እድል እንዳለው ያሳያል። እድሉን ለመጠቀም ግን ውህደቱ ተቀዳሚ ተግባር ነው።
በቀጠናውም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ፤ የአማራ ፋኖ ይህንን እጁ ላይ የገባውን እድል የመጠቀም ግዴታ አለበት። ይህንን ካደረገ በመላው ዓለም ተደማጭነት እንደሚኖረው አልጠራጠርም። የአማራ ፋኖ የሚታገለው መላው ዓለም የናቀውን፤ አብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ የጠላውን አገዛዝዝ ነው። ህዝቡ የተሻለ አማራጭ ይፈልጋል። ስለሆነም፤ ላሰምርበት የምፈልገው ሃሳብ፤ የአማራው ሕዝብ ራሱን በውህደት ተደራጅቶ ከማዳን በስተቀር ማንም የውጭ ኃይል ሊያድነው የማይችል መሆኑን ነው። ለመከበር ራስን ማክበርና ማስከበር መሰረት ነው። በዚህ መስፈርት፤ የአማራ ፋኖ የሞራል ልእልና (Moral and ethical superiority) ከፍተኛ ነው። መሻሻል ያለበቸው ጉዳዮች እንዳሉ ይገባኛል። ለምሳኤ በአመራር ዴሞክራሲያዊ ባህርይ ለማሳየት ፍትሃዊና ሚዛናዊ መሆን ያስፈልጋል። እኔ ብልጫ ይኑረኝ ብሎ ግትር መሆን አያዋጣም፤ ይህ ከሆነ ከኦህዴድ ብልጽግና ሊለይ አይችልም። በሁሉም መስፈርት ራስን ከጨካኙና ነውረኛው ስርዓት መለየት ያስፈልጋል።
በተጻራሪው የኦህዴድ ብልጽግና አመራር በሁሉም ዘርፎች የሞራል ውድቀት (moral decay or degeneration) ያሳያል። ዲሞክራሲያዊ ሊሆን አይችልም። ሰብአዊ ፍጥረትን ይንቃል፤ ይለያል።
የኦህዴድ ብልጽግና አገዛዝ የአማራ ፋኖን ዓላማ በማዛባት “እነዚህ ጽንፈኞች የሚታገሉት አማራው ተመልሶ የበላይነቱን እንዲይዝ ነው” በሚል ትርክት ነው። እስከማውቀው ድረስ የአማራው ህዝብ የሚታገለው ‹‹እንደ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በእኩልነት ልኑር፤ መብቴ ይከበር፤ የፈጠራ ትርክት እየለፈፋችሁ በአማራው ላይ እልቂት አታካሂዱ፤ በፍትህና በሰላም ልኑር›› በሚል መርህ መሆኑን ነው። የአማራው ሕዝብ እኔ ብቻ ልግዛ፤ እኔ ብቻ ልብላ ያለበት ጊዜ የለም።
በተተኪነት ቅዠት ዓለም ውስጥ የሚንቀሳቀሰው የኦሮሙማ አጀንዳን ስኬታማ ለማድረግ የሚታገለው የዐብብይ አህመድ ኦህዴድ ብልጽግና ቡድን ግን፤ ይህንን ሃቅ ሊቀበለው ፈቃደኛ አድይደለም። ዓላማው ፍጹም የሆነ የአንድ ዘውግ የበላይነት ነው። ባንኩንም፤ በጀቱንም፤ ታንኩንም፤ መሬቱንም፣ ሚዲያውንም ወዘተ ማጠቃለል የእቅዱ አካል ነው።
ሌላው የሃሰት ትርትክት የአማራ ፋኖ የኢትዮጵያን የባህር በር ጥያቄ አያስተናግድም፤ አያስተጋባም የሚል ሃሰት ነው። እንደ አማራው ሕዝብ ለኢትዮጵያ ግዛታዊ አንድነት፤ ሉዐላዊነት፤ የባህር በር ተጠቃሚነት መብት የታገለ ኃይል አለ ወይ? ተብለው ቢጠየቁ፤ የሚክዱት ይመስለኛል። ኤርትራን ወደ እናት አገሯ ወደ ኢትዮጵያ እንድትቀላቀል ያመቻቹት የአማራ መሪዎች ናቸው።
በአሁኑ ወቅት፤ ኢትዮጵያ እንደ ሃገር የራሷን ብሄራዊ ጥቅም እንዳታስከብር የእርስ በእርስ ጦርነት እያካሄደ ለውጭ ኃያላን በር የከፈተላቸው የዐብይ አህመድ ኦህዴድ ብልጽግና መሆኑን መጠቆም እፈልጋለሁ።
የኢትዮጵያ ዘላቂ ጥቅም ሊከበር የሚችለው መላው ሕዝቧ በእኩልነት፤ በሰላም፤ መብቱ ተክብሮ ለመኖር ሲችል ብቻ ነው። የአማራ ፋኖ ስኬታማ ሲሆን የኢትዮጵያ ዘላቂ ጥቅም የሚከበርበት ሁኔታ እንደሚፈጠርና እንደሚመቻች አምናለሁ።
የአማራ ፋኖ ውህደት ለኢትዮጵያ ዘላቂ ውህደት (Ethiopia’s unity) መሰረት ነው። የአማራውን ሕዝብ ከተገንጣዮች የሚለየው፤ ኢትዮጵያዊነቱ ነው። ይህ የዜግነት መለያ አንዱን ብሄር ወይንም እምነት ከሌላው አይለይም። የአማራው ሕዝብ በኢትዮጵያዊያን ብሄራዊ አንድነነት ያምናል።ስለሆነም ሌሎች በኢትዮጵያ ዘላቂነትና በኢትዮጵያዊነት የሚያምኑ ሁሉ የአማራ ፋኖን ያምኑታል፤ ይከተሉታል። የደቡብ ፋኖ እንቅስቃሴ ምሳሌ ነው። የኦሮሙማ አጀንዳ እንደሚውጣቸውና እንደሚያጠፋቸው ያውቃሉ። ለጋራ የአማራ ህዝብና የኢትዮጵያ የህልውና ዓላማ የጋራ ትግል ይኑረን የምለው ለዚህ ነው።
የውጭ ኃይሎች ይህንን መስመር ቢቀበሉም፤ ባይቀበሉም፤ የአማራውን የህልውና ትግል ማጠናከር ያለብን ከዚህም አንጻር ነው። የኦህዲድ ብልጽግናን አምባገነንና ፋሺስታዊ ሥርዓተ መቃወምና ማፍረስ አለብን የምለው ለንጹሃን ህይዎትና ለሃገር ቀጣይነት ስጋት ስለሆነ፤ ድህነት ፈጣሪ ስለሆነ፤ ኢ-ስብአዊና ኢ-ዲሞክራሲያዊ ስለሆነ፤ በረሀብተኛነት በማፈናቀል የሚያምን ስለሆነ፤ በሌብነትና ሙሰኛነት የሚያምን ስለሆነ፤ ፋሺስታዊ ስርዓት ስለሆነ ነው። በድሮን ንጹሃንን መግደል ፋሺስታዊ ነው፤ ልጃገረዶችንና እናቶችን መድፈር ፋሺስታዊ ነው። ልጆች እንዳይማሩ ማድረግ ፋሺስታዊ ነው። ዜጎች በርሃብ እንዲሞቱ ማመቻቸት ፋሺስታዊ ነው። ድህነትን መፍጠርና ለድህነት ማመቻቸት የብልጽግና ተጻራሪ ነው።አስቡት ወገኖቸ፤ ድህነት ብሎ ብልጽግና ምን ይባላል?
ዓለም ባንክ በዐብይ አህመድ ዘመነ መንግሥት የኢትዮጵያ የድህነት ደረጃ ወደ 43 በመቶ ተሸጋግሯል ሲል፤ የኦህዴድ ብልጽግና አገዛዝ ድህነትንና ረሃብተኛነትን እንደ መሳሪያ ይጠቀማል ማለት ነው ትርጉሙ። የሕዝቡ ብዛት ነው የሚለውን አልቀበልም። የሕዝቡ የብሄር ስርጭትም ነው የሚለውን አልቀበልም። ሕዝብ ከሕዝብ ጋር የሚያናክሰው ዐብይ አህመድና ፓርቲው ነው። ሕዝብን በድሮን የሚጨፈጭፈው የኦህዴድ ብልጽግና አገዛዝ ነው።
ለምሳሌ፤ በ2025 የናይጀሪያ ሕዝብ ቁጥር 240 ሚሊየን ደርሷል፤ የኢትዮጵያ 135 ሚሊየን ነው። በመግዛት አቅም (Purchasing power parity) ሲገመገም፤ የናይጀሪያ ጠቅላላ የአገር ገቢ $2.6 ትሪሊየን ደርሷል፤ የኢትዮጵያ $620 ቢሊየን ብቻ ነው። ለዚያውም ይህንንም ጠቅላላ ገቢ ዓለም ባንክ የተጋነነ ነው ይለዋል። በመሬት ላይ ያለውን የገቢና የኑሮ ሁኔታ ገምግሞ ይህ ገቢ 54 በመቶ ተጋኗል ይላል፤ በዚህ የዓለም ባንክ ገለጻ እኔ እስማማለሁ።
በናይጀሪያ ህብረ ብሄራዊነት ለእድገትና ለልማት ማነቆ አለመሆኑን እናያለን። ናይጀሪያ ከቢያፍራው ጦርነት ተምራለች፤ ኢትዮጵያ ግን አልተማረችም። ማለቴ ኢትዮጵያን የሚመሯት እንደ ዐቢይ አህመድ ያሉት ገዥዎች፤ ከትናንቱ ስህተት አልተማሩም፤ ወደፊትም የሚማሩ አይደሉም፡፡
በኢትዮጵያ የብሄር ብሄረሰቦች እኩልነት የተከለከለ፤ ቢያንስ የተበከለና ለይስሙላ ብቻ ስለሆነ፤ የእርስ በእርስ ጦርነት የተለመደ ሆኗል። ቅሚያ፤ ዘረፋ፤ ሌብነት፤ ሙሰኛነት፤ ማፈናቀል፤ የመሬት ነጠቃ የተለመደ ሆኗል። በሁሉም መስፈርቶች ስገመግመው፤ ዐብይ አህመድ ባለፉት ሰባት ዓመታት ኢትዮጵያን ከድጡ ወደ ማጡ አሸጋግሯታል። ካሸጋገራት ለመምራት አይችልም ማለት ነው። ሌላ ምርጫ ተካሂዶ ዐብይ መሪ ቢሆን ምን ሊከሰት እንደሚች አስቀድሞ ለማስብ ይቻላል። በአማራው ህዝብ ላይ ጫካኔው ይባባሳል እንጂ አይሻሻልም።
በተጨማሪ፤ ይህ ሁኔታ ድህነትን ያባብሰዋል፤ የነፍስ ወከፍ ገቢን ይቀንሰዋል። ስራ አጥነት የተለመደ ይሆናል። በጥቅሉ ሲገመገም፤ ኢትዮጵያን እንደ ሃገር ይበክላታል። ሊያፈርሳትም ይችላል። ለዚህ ሁኔታ ተጠያቂው ማነው? ብንል፤ የሚያስተዳድራት የኦህዴድ ብልጽግና አገዛዝ ነው። የውጭ ኃሎችን ልንወቅስ አንችልም።
ትኩረቴ ከውህደቱ ወሳኝነት ላይ ስለሆነ በዝርዝር ላቅርበው፤
- የአማራ ፋኖ የሚፋለማቸው ኃይሎች እነማን ናቸው?
በመጀመሪያ ደረጃ ሁሉን ተቋማት የሚቆጣጠረው የኦህዴድ ብልጽግና አገዛዝ ነው። በተመሳሳይ ኢትዮጵያ በዘውግና በቋንቋ እንድትከፋፈል ያደረገውና የአማራውን ሕዝብ በጠላትነት የመደበው ህወሃት ነው።ይህ ካንሰር ስር ሰዷል፤ ሌሎችንም ብሄሮች እንዲበከሉ አድርጓል፤ የትግራይ ህዝብ በድህነት እንዲሰቃይ አድርጓል።
የአማራውንና የትግራዩን ህዝብ የሚያዋጣው መንገድ በወዳጅነት፤ በወንድማማችነት፤ እህትማማችነት ያሉትን ልዩነቶች ወደ ጎን ትቶ፤ በአብሮነት መኖርና ድህነትን በጋራ ለመቅረፍ ቆርጦ ሲነሳ ነው። ያለፈ የፈጠራ ትርክት ምርኮኛ መሆን አያዋጣም።
ኦህዴድ ብልጽግና የአማራውን ህዝብ የሚያሰቃየው ብቻውን ሆኖ አይደለም። በአማራው ሕዝብ ስም በአማራው ክልል ፊት ለፊት ሆነው ስርዓቱን የሚያገልሉ አማራዎች ወገንተኛነታቸው ለአማራው ህዝብ ሳይሆን ደመወዝ ለሚከፍላቸውና ሥልጣን ለሰጣቸው ለኦህዴድ ብልጽግና አገዛዝ ነው። የክልሉን መሪ ማነው የሚሰይመው? ብለን ራሳችን እንጠይቅ፤ የአማራው ህዝብ ሆኖ አያውቅም። ሰያሚው ዐብይ አህመድ ነው። የአማራውን ክልል በበላይነት የሚገዛው አማራው ሳይሆን የኦህዴድ ብልጽግና ነው። ከላይ ሆኖ ድጋፉን ሊያገኝ የቻለበት አንዱ ምክንያት በድህነት የሚሰቃየውን አማራ ድጎማ በመስጠት ነው። ይህ ሁኔታ አማራውን አይመጥንም።
የአማራ ፋኖ መላውን ኢትዮጵያን ከስርዓቱ መንጋጋ ከማስወጣቱ በፊት፤ በአማራው ክልል ለአማራው ፍትሃዊ ትግል መሰናክል የሆኑትን ሁሉ የማጽዳት ግዴታ አለበት። በፈቃደኛነት ትግሉን እንዲቀላቀሉ የሚያድርገውን ጥረት ደግሞ እደግፋለሁ።
- ፋኖ ያለው ያልተቋረጠ የአማራ ህዝብ ድጋፍ፡
የአማራው ፋኖ የትጥቅ ትግል የሚደረገው በድሃው የአማራ ሕዝብ ድጋፍ ላይ ነው። ሕዝቡ የሚለውን ማዳመጥ ወሳኝ ነው። የአማራው ሕዝብ ተዓምር ይመኛል፤ መብቱ፤ ህልውናው፤ ነጻነቱ እንዲከበርለት። ይህ ምኞት ሌላውን በበላይነት ለመግዛት ሳይሆን፤ በእኩልነት እንኑር ከሚል መርህ ነው። በእኩልነት መኖር ደግሞ ለሁሉም ክብር ነው።
ባንድ በኩል ሲታይ የአማራው ሕዝብ ያልተቆጠበ ድጋፍ፤ ለህዝቡ ከፍተኛ ሸክምና ፈተና ሆኗል። በድህነት ዓለም ውስጥ ለሚኖረው የአማራ ገበሬ፤ ይህ ሸክም ተዓምራዊ በሆነ ፍጥነት ውጤታማ እንዲሆንና በድህነትና በኋላቀርነት የሚሰቃየው የአማራ ህዝብ ኑሮው እንዲሻሻልነትና ልጆቹ እንዲማሩለት ይፈልጋልል። ውህደቱ እንዲፋጠን የምመክረውም ይህንን አጣብቂኝ በመገንዘብ ነው። ጦርነቱ እየረዘመ ሲሄድ መሰለቻቸት የማይቀር መሆኑ ስላሰጋኝ ነው።
የአማራው ህዝብ ቁጥር ሃምሳ ሚሊዮን ይሁን ከዚያ በላይ፤ የኢኮኖሚ አቅሙ የዘላለም ጦርነት (Permanent war) ሊደግፍ አይችልም። ማንኛውም ድሃ አገር አይችልም። በተመሳሳይ፤ የዐብይ አህመድ ኢህዴዳዊ ጦር ሰራዊት ወጣቱን ትውልድ እያሰለጠነ ወደ ጦር ሜዳ ሲልከው የሚሞተውና የሚቆስለው ወጣት ግዙፍ ስለሆነ፤ ወላጆች ጥያቄ ማንሳታቸው አይቀርም። እየደቀቀ የሄደው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚም የጦርነቱን መራዘም ሊደግፈው አይችልም።
የአማራ ፋኖ በሁለቱም በኩል የሚከሰተውን አደጋና እድል የመጠቀም ግዴታ አለበት። መጀመሪያ፤ በአማራው ህዝብ ላይ ያለውን ጫና አለመርሳት፤ በሁለተኛ ደረጃ የዐብይ አህመድን ደካማ ጎን መጠቀምና ማጋለጥ። ሕዝብ ጨካኝነቱን እንዲያውቀውና እንዲጠላው ያልተቆጠበ ጥረት ማድረግ።
ለወታደርነት በገፍ የሚሰማራውን ወጣት ትውልድ በጦርነቱ እንዳይሳተፍ ማስተማርና ሌሎች እንዳይቀላቀሉ ጥሪ ማድረግ ይጠቅማል የሚል እምነት አለኝ። ህዝቡ የዐብይን ዘረኛነትና ጭካኔ በሚገባ ከተረዳው፤ ድጋፉን እየቀነሰ እንደሚሄድ አልጠራጠርም። ስለሆነም ህዝቡን ሳያቋርጡ በተከታታይ ማስተማር ወሳኝ ነው። ዲያስፖራው ለዐቢይ አህመድ የሚልከውን ሃዋላ (Remittances in the billions of dollars) እንዲቀንስ፤ ሌሎች ዘዴዎች እየተጠቀመ ወገኑን እንዲደግፍ ጥሪ ማድረግ ያስፈልጋል። ለአማራ ፋኖ የሚለገስ የህዝብ ድጋፍና የዐብይን መንግሥት በውጭ ምንዛሬ መደጎም አብረው ሊሄዱ አይችሉም።
የአማራ ፋኖ የራሱን የፖርፖጋንዳ ስራዎች በቅልጥፍና መተግበር አለበት። የአማራ ሚዲያዎችም መልእክቱን ያለመስለቸት ለመላው የኢትዮጵያና የዓለም ሕዝብ ማስተላለፍ አለባቸው። የህልውናው ጦርነት የመሳሪያ ብቻ ሳይሆን፤ የአስተሳሰብ ለውጥንም ማስተጋባት አለበት፤ ይህን ማድረግ ደግሞ ይቻላል።
- የአማራ ፋኖ የሠራዊት አቅም፡-
የአማራ ፋኖ የሰራዊት ኃይሉና አቅሙ መሰረት ሕዝቡ ነው፤ እድሜ፤ እምነት፤ ጾታ፤ ሃብትና ሌላ የማይለየው ግዙፍ የአማራ ህዝብ ድጋፍ። የአማራ ፋኖ እንቅስቃሴ አስደናቂና ተዓምራዊ ለውጥ በማካሄድ ላይ የሚታየው ምንም መሳሪያ ሳይኖረው በብልሃት የኦህዴድ ብልጽፍናን ሰራዊት መሳሪያ እየነጠቀ መታጠቁ ነው።
ይህ ሰራዊት ጠንካራና የማይበገር የሆነበት ዋና ምክንያት፤ የቆመበት ዓላማ የተቀደሰ መሆኑ ነው። ለዓላማ የቆመና በሕዝብ የተደገፈ ኃይል አሸናፊ እንጂ ተሸናፊ ሊሆን አይችልም ለማለት የምችለውም ለዚህ ነው።
ይህ እንዳለ ሆኖ፤ ትግሉ የተወሳሰበ ስለሆነ፤ የድርጂት ጥንካሬና የድርጂት አመራር ያስፈልገዋል። ድርጂት ስል አንድ የአማራ ፋኖ ድርጂት ማለቴ ነው። አመራር ወይንም መሪ ሲባል ብቃት ያለው፤ ለመስዋእትነት የተዘጋጀ፤ የሕዝብ ተአመኔታ ያለው፤ መሪነት ሸክምና ሃላፊነት መሆኑን የሚያውቅ ማለቴ ነው።
ከሩቅ ሆኜ ስመለከተው፤ የአማራ ፋኖ ሰራዊት በአብዛኛው ወጣት መሆኑ፤ ሁሉን አሳታፊ መሆኑ፤ በራሱ የሚተማመን መሆኑ፤ በእርግጠኝነት ታሪክ ሊሰራ እንደሚችል ያሳያል። ልዩ ልዩ ባለሙያዎች፤ ምሁራን፤ መሃንዲሶች፤ አስተማሪዎች፤ ወታደሮ ፤ መኮንኖች፤ ሽማግሌዎች፤ ሴቶች፤ ክርስቲያንና ሙስለሞች የሚሳተፉበት መሆኑ ከሌሎች ታጣቂ ኃይሎች ይለየዋል። የአማራ ፋኖ ውህደቱን ስኬታማ ቢያደርግ ተዓምር ሊሰራ ይችላል የምለው ለዚህ ነው።
- የአፍሪካ ቀንድ እና የቀይ ባህር ጂኦፖለቲካ–እድል ወይንስ ስጋት?
የአማራ ሕዝብና የአማራ ፋኖ ኢትዮጵያ በሁሉም አቅጣጫ የተከበበች አገር መሆኗን መዘንጋት የለባቸውም። በጎንደር ዙሪያ ሱዳን ግዙፍ መሬት የኔ ነው ትላለች። በጋምቤላ የውጭ ኃይሎች ግዙፍ መሬት ነጥቀዋል። በሰሜን በኩል የቀይ ባህር፤ ገና ያልተፈታው የአሰብ ጥያቄ፤ የሶማሊላንድ ሁኔታ ለኢትዮጵያ ከፍተኛ ስጋት ሆኗል።
የአረብ አገሮችና ግብጽ በኢትዮጵያ ላይ የሚያካሂዱት የውክልና ጦርነት ባጭር ጊዜ የሚቆም አይደለም። ግብጽ አሁንም የዓባይን ወንዝ የመቆጣጠር ህልሟን አልሳበችም። የተባበሩት አረብ ኤምሬቶችና ሌሎች የገልፍ አገሮች፤ የምግብ ፍላጎታቸውን ስኬትማ ለማድረግ፤ የኢትዮጵያን ለም መሬት በተለያዬ መንገድ ለመቆጣጠር ይፈልጋሉ። ዐብይ አህመድ ከኤምሬቶች ጋር የፈጠረውን ግንኙነት አደጋ የማየው ከኢትዮጵያ ዘላቂ ጥቅም አንጻር ነው።
በማንኛውም መስፈርት ስመለከተው የጎረቤት አገሮች ለአማራና ለኢትዮጵያ ስጋት ናቸው። የሱዳን ጦርነት በአማራ ህዝብ ላይ ያስከተለውን መጠነ ሰፊ ችግር መገንዘብ አስፈላጊ ነው፡፡ የአማራ ፋኖ የቀጠናውን አሳሳቢ የጂኦፖለቲካ ሁኔታ መተንተንና ለአማራው ሕዝብ የትጥቅ ትግል የሚረዳ ስልት መቀየስ አለበት። ጠላትን ከወዳጅ መለየት አንዱ ሂደት ነው። ይህን ማድረግ የሚችለው ደግሞ የአማራ ፋኖ አመራር በጥበብ ሲመክርና (Statesmanship) የውስጥ አንድነቱን ሲፈጥር ነው፡፡
- የአማራ ጠላቶች እርስ በርሳቸው መከፋፈላቸው–ብልጽግናና ህወሃት
ህወሃት ማኒፌስቶውን አልቀየረም፤ የአማራውን ህዝብ ጠላት ነው የሚለውን ጸረ-አማራ መርህ አልሳበውም። የኦህዴድ ብልጽግና ፓርቲም የሚከተለው መርህ ተመሳሳይ ነው። ይህ አንዳለ ሆኖ፤ በህወሃትና በኦህዴድ ብልጽግና መካከል የተፈጠረው ልዩነት፤ ለአማራ ፋኖ እድል ይሰጣል።
የአማራ ፋኖ በነዚህ አጥፊ ኃይሎች መካከል ያለው ልዩነት ለትግራይ፤ ለኦሮሞ፤ ለአማራውና ሌላው ሕዝብ ሁሉ ስጋት መሆኑን፤ የአማራ ፋኖ ሊያስተጋባው ይችላል። በምንም መስፈርት ሁለቱ ሊተማመኑ አይችሉም በሚል ዘገባ።
ህወሃት የአማራ ሕዝብ መሰሪ ጠላት እንጂ፤ ወዳጅ ሊሆን አይችልም። ስለሆነም፤ የአማራ ፋኖ ጥንቃቄ ማድረግ ያለበት ራሱን አሳልፎ ለህወሃት የበላይነት እጁን እንዳይሰጥ ነው። የአማራ ፋኖ በህወሃት ከተጠለፈ የአማራው ህዝብ የህልውና ትግል በማይመለስበት ደረጃ ሊመክን ይችላል።
ለማጠቃለል፤ የአማራ ፋኖን አመራር የምመክረው ውህደቱን ባስቸኳይ እንዲተገብረው ነው። የአማራ ፋኖ ውህደት ለአማራው ህልውና ትግል መሰረት መሆኑን አያሰመርኩበት፤ አደራ የምለው የአማራ ፋኖ ከአሁን በኋላ በውህደት የሚሰራ መሆኑንና የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጂትና የአማራ ፋኖ ብሄራዊ ኃይል ከስመው አንድ የአማራ ፋኖ ድርጂት የመመስረቱን ተዓምር ዜና ለመላው የኢትዮጵያና የዓለም ሕዝብ ከኢትዮጵያ የክርስትና በዓል በፊት ይፋ እንዲያደርግ ነው።
December 31, 2025