በዶክተር አክሎግ ቢራራ
ይህ የትንታኔ ባለፈው በቡርኪና ላይ ከወጣሁት የፖለቲካ ኢኮኖሚ ትንታኔ ጋር ግንኙንት አለው።ለየት የሚያደርገው ረሃብተኛነት፤ ድህነት፤ የሰብአዊ መብቶች ሙሉ በሙሉ በሚያስብል ደረጃ መገርሰሳቸውና የዐብይ አህመድ ኦህዴድ ብልጽግና አገዛዝ ለሕዝብ መሰረታዊ ፍላጎቶች ደንታቢስ መሆኑ ታሪካዊያቷን ኢትዮጵያን ሊበታትናት እንደሚችል አለመገንዘቡ ነው።
እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር ሰኔ 1991 ጀምሮ እስከ ጥር 1992 ባሉት ጊዜያት ውስጥ የፍርሰት ሂደቷን ጨርሳ የፈረሰችው ዩጎዝላቪያ፤ ከመበታተኗ በፊት ትከተለው የነበረው ፖለቲካዊ ሥርዓት እና የኢኮኖሚ ግሽፈት አሁን የብልጽግናው ሊቀመንበር ከሚያካሂዱት ጋር ሙሉ በሙሉ በሚያስብል ደረጃ ተመሳሳይ ነበር፡፡ ‹‹ፀጉር ሲመልጥና ነገር ሲያመልጥ አይታወቅም›› እንዲሉ፤ አገርም ሲወድቅ አይታወቅምና፤ ኢትዮጵያ እንደዩጎዝላቪያ ከመሆኗ በፊት ሁሉም ብሔረሰብ በአንድነት ሊመክርና የብልጽግናውን ሥርዓት በጋራ ትግል ሊያስወግደው ይገባል፡፡
በአሁኑ ሰዓት ሥልጣን ላይ ያሉት የብልጽግናው ሊቀመንበርና እሳቸው ያዋቀሩት መንግሥት፤ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ስጋት መሆኑን በተግባር አሳይቷል፡፡ የኢትዮጵያን የቁልቁለት ጉዞም በፍጥነት እያሽከረከረው ይገኛል፡፡ ይህ ሆነ ተብሎ የሚሰራ እቅድ ነው።
ይህንን ሥርዓት መታገልና ከዙፋኑ መንቀል የአማራው ህዝብ ብቻ የቤት ሥራ ሳይሆን፤ የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ግዴታ ነው፡፡ ‹‹ርሃብ ጊዜ አይሰጥም›› የሚለውን አባባል በቴሌቪዥንና በሬዲዮ ሳይሆን፤ በተግባር ሁላችንም የምናውቀው የርሃብ ክፉ ገጠመኝ ነው፡፡ በአሁኑ ሰዓት በኢትዮጵያ የደረሰው የርሃብ አደጋ እና ቀጣይ ያንዣበበውን ስጋት በሚገባ ላጤነ ማንኛውም ጤነኛ አእምሮ ያላው ሰው መእገንዘብ ያለበት፤ የብልጽግናው መንግሥት ድህነትን ብቻ እያበለጸገ ይመስላል፡፡
ድህነት ደግሞ ብሔርና ጾታ፣ ሀይማኖትና ዕድሜ ወዘተ ለይቶ የሚያጠቃ መርጦ የሚተው ሳይሆን፤ ሀገራዊ ስጋትና ህዝባዊ አደጋ ነው፡፡ ይህን አደጋ መቀነስ ሳይሆን ማስወገድ የሚቻለው ደግሞ፤ የድህነትና የሀገር ብተና መሀንዲስ የሆነውን የብልጽግናውን ሥርዓት በማስወገድ ነው።
የኢትዮጵያዊያን የጋራ መግባቢያ እየሆነ የመጣውን የርሃብና የችጋር ምንጭ በጋራ ተነስተን ማስወገድ ካልቻልን፤ የዩጎዝላቪያ እጣ ፋንታ በደጃችን ቆሟል፡፡ ያ ከሆነ ደግሞ እንደ ህዝብ ሁሉም ተጎጂ እንጂ ማንም አትራፊ እንደሌለ መገንዘብ።
ለመሆኑ ይህን ስርዓት ማን ይታገለው? እንዴት እንታገለው? በኢትዮጵያ የሰፈነው የርሃብና የችጋር ስፋትስ እንዴት ይገለጻል? የሚሉትን ዝርዝር ነጥቦች በትንታኔ ጽሁፉ እንመለከታለን፡፡
‹‹ታላላቅ ነገሮች ሁልጊዜ ከውስጥ ይጀምራሉ›› የሚለውን የቡድሂስት አባባል በማስርገጥ ወደ ትንታኔየ እሄዳለሁ።
በሊበራል ዲሞክራሲም ይሁን በአምባገነናዊ መንግስት ጉቦ፤ ሙስና፣ ጎሰኝነት፣ አድሎአዊነት፣ ባጀትን አላግባብ መጠቀምና አድሏዊ በሆነ ደረጃ ማሰራጨት፣ ኃብትና የስራ እድልን ለተመረጡት ጥቂት ግለሰቦችና ስብስቦች መስጠት እና የማንፈልጋቸውን ከዕድል እና ድምጽ ተደራሽነት ማግለል፣ ድህነትን ያባብሳል፡፡
ይህ ልምምድ ደግሞ፤ የኢትዮጵያን ግዙፍ የህብረተሰብ ክፍል በተለይም ወጣቶችን የሚጎዳና ከፍተኛ ዋጋ የሚያስክትል መሆኑን በግልጽ አያየን ነው። ይህ ሁኔታ ባስቸኳይ መፍትሄ ካልተገኘለት ኢትዮጵያ የቀድሞዋን ዩጎዝላቭያ መሆኗ የማይቀር ነው።
ሁኔታውን የሚያባብሰው ደግሞ ኢትዮጵያ በዘውግ መከፋፈሏና የኑሮ ውድነት ሕዝቡ ከሚችለው በላይ እየናረ መሂዱ ነው። ዩጎዝላቪያም የመጨረሻዎቹ ዘመኖቿ በዚህ ሂደት እንዳለፈች ልብ ይሏል፡፡
ዐብይ አህመድ በበላይነት እየመራው ባለው የኦህዴድ/ብልጽግና ሥርዓት፤ የሰባት ዓመታት የሥልጣን ዘመን፤ ዘላቂ ልማት መስፈርት ምን ስኬት ይታያል? ብዬ ራሴን ስጠይቅ፤ በማያሻማ ደረጃ፤ የድንጋይ ዘመን የሆነ የገጠር ኢኮኖሚ ይዞ ለመበልጸግ አይቻልም።
በአሁኑ ወቅት፤ 43 በመቶ የሚሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ረሃብተኛ ነው። በሁሉም ዘርፍ ዝቅተኛ ፍላጎቱ አልተሟላም ማለት ነው። ማለትም፤ ምግብ፤ ንጹህ ውሃ፤ የጤና አገልግሎት፤ መጠለያ፤ ንጽህና፤ ትምህርት፤ ኤሌክትሪክ አቅርቦት መስፈርት ሲገመገም 70 በመቶ የሚገመተው የኢትዮጵያ ሕዝብ በድህነት ውስጥ ይኖራል።
ይህንን በመሬት ላይ የሚታይ ሃቅ ከተቀበልን፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ዋናው ትኩረት ከምን ላይ ነው? ብለን የመጠየቅ ግዴታና ሃላፊነት አለብን። አንድ ወዳጄ፤ “ያልተማሩ አባቶቻችን ያስረከቡንን የጀግኖች አገር፤ የተማሩ መሃይሞች እያፈረሷት ነው” አለኝ፡፡ ይህ የማይካድ የፖለቲካ እና የማህበራዊ ምኅዳር፤ ኢትዮጵያን ወደ መበታተን ጫፍ እየገፋት ነው።
የኦህዴድ/ብልጽግና ሥርዓት ወታደራዊ ሃይል፤ በመንደር፣ በከተሞች፣ በእርሻዎች፣ በእንስሳት፣ በመሠረተ ልማት እና በንጹሃን ዜጎች ላይ ያለማቋረጥ የቦንብ ድብደባ እያካሄደ ነው፡፡ ይህ ተግባር ደግሞ የመንግሥትን ሚና ትርጉም የለሽ እና ልማት አምካኝ ያደርገዋል። እሱም የዐቢይ አህመድን ብልጽግና መንግሥት ብለን ከጠራነው ነው፡፡ ገዢ እንጅ መንግሥት አይደለም፤ የሕዝብ አዛዢ እንጅ የሕዝብ አገልጋይና ታዛዢ አይደለም።፡
ምክንያቱም ይህ ሥርዓት ግዙፍ መዋለንዋይን ለጦርነትና ለስለላ፤ ለቁጥጥር ስለሚያውል ነው። ጦርነት ደግሞ ኢኮኖሚን ብቻ ሳይሆን ትውልድን አምካኝ ነው። ጦርነትና ሰላም፤ ጦርነትና እርጋታ፤ ጦርነትና አብሮነት፤ ጦርነትና መልካም ጉርብትና አብረው አይሄዱም። ጦርነት ካለ ጭካኔ አይቀርም። ጦርነት ካለ ፍርሃት አይቀርም፤ ህጻናት በጦርነት ካደጉ ጦርነት የተለመደ ይመስላቸዋል። የእርስ በእርስ ጦርነት ደግሞ በባሰ ደረጃ አምካኝ ነው። ጭካኔው መረን የለቀቀ ነው። የጦር ኃይሉ ግዙፍ ቢሆንም፤ በጭካኔ የሚገዛ መንግሥት ደግሞ እድሜው ረዥም ሊሆን አይችልም።
በዐቢይ አህመድ አገዛዝ፤ በኢትዮጵያ ውስጥ የታፈነው የፖለቲካ፣ ማህበራዊ፤ ኢኮኖሚያዊ እና ባህላዊ ምኅዳር በተጎዱ ቡድኖች መካከል ያለውን የእርስ በርስ መተማመን የሚቀንስ እና፤ ገዥው አካል በርካታ መሰናክሎችን ለመቅረፍ ባለው አቅም ላይ እምነት እንዳይኖር አድርጎታል።
የአመራር ብቃት የሚመነጨው ለሰብአዊነት እና ለሰብአዊ መብቶች ቁርጠኝነት ሲኖር ነው። የመንግስት አመራር ኢሰብአዊ ማለትም፤ ኢ-ልባዊ፣ ጨካኝ፣ ይቅር የማይል፤ ምሕረት የለሽ፣ ርኅራኄ የሌለው ከሆነ፤ መሪው ችግሮችን ለመፍታት የሚጠቀምባቸው መሳሪያዎች እነዚህን ዋና እሴቶቹን ያንጸባርቃሉ። ስለሆነም፤ የሚያደርሰው ጥፋት ሁሉ ጀግንነት ይመስለዋል። የጥፋቱን ድርጊት የሚደግፉ ተከታዮች ስላሉት፤ ጭራሽ ሁኔታውን ያባብሰዋል።
እንደ ኢትዮጵያ ባሉ፤ ብዙ ብሔረሰቦች እና እምነት ባለበት ሀገር ውስጥ፤ ተፎካካሪ ፍላጎቶች ባሉበት፣ አዛኝ እና ተቆርቋሪ መሪነት በጣም አስፈላጊ ነው። ኢትዮጵያ ደግሞ እንዳለመታደል ተቆርቋሪ መንግሥት የላትም። በሁሉም ዘርፎች ተተኪነትን የሚያጠናክር አገዛዝ ነው ኢትዮጵያን የበከላት። ተቋማትን ሙሉ በሙሉ በሚያስብል ደረጃ የአንድ ዘውግ አገልጋይ አድርጎታል፡፡ ባንኮችን በሙሉ፤ ፍርድ ቤት፤ መከላከያ፤ ፌደራል ፖሊስ፤ መረጃ፤ ሚዲያ፤ የመሬት ይዞታ ወዘተ የሥርዓቱና የሥርዓቱ መሪ አገልጋይ ተደርገዋል፡፡
በየትኛውም አገር፤ ለሁሉም ዜጎች ሰብአዊ መብት መቆም እና ፍትሃዊ አያያዝ ማሳየት አስፈላጊ ነው። አለያ፤ ሕዝቡንም አገርንም ለባሰ አደጋ ይዳርጋል። አደጋው የሚባባስበት መሰረታዊ ምክንያት፤ ገዥዎቹ ተሸናፊዎችን እና አሸናፊዎችን ስለሚመርጡ ነው።
በኢትዮጵያ ተሸናፊዎቹን በተከታታይ እያሳደደ ያመክኗቸዋል። ንጹሃን ይሞታሉ። ይህ ድህነትን ያባብሰዋል። የድህነት ጥልቀት መጨመር ደግሞ ለኢትዮጵያና ለመላው ሕዝቧ የሕልውና ቀውስ ሆኗል።
ከድሆች እና ምንም አይነት የመንግሥት ትኩረት ካልተደረገላቸው ከ30 ዓመት በታች የሆናቸው ኢትዮጵያውያን ወጣቶች መካከል፤ 65 በመቶ የሚሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ፤ ሌላ አማራጭ ስለሌላቸው ከአደገኛ አካላት ለሚቀርቡ ፈተናዎች ተጋላጭ ናቸው። በነሱ ላይ ልንፈርድ አንችልም። ኑሯቸውና ህይወታቸው አስገዳጅ ስለሆነባቸው እንጂ የሚመርጡት በሃገራቸው ሰርተውና ተከብረው መኖርን ነው።
መፍትሄ አለ፤ ወይስ የለም? ብለን ስንጠይቅ፤ ፍትህ፣ ሰላምና እርጋታ ሲኖር መፍትሄው ቀላል ነው። መንግስት እና የሲቪል ማህበረሰቡ ድህነትን ለማጥፋት ቁርጠኝነት ማሳየት አለበት። የኢትዮጵያ መንግሥት የመጀመሪያው ኃላፊነትም ይኼው ነበር። ግን፤ ድህነትን ከመቅረፍ ይልቅ ድሃን ማጥፋትና ድህነትን ማበልጸግ ቀዳሚ ሥራው አደረገው ይዘውታል። ይህ ብቻ ይህንን ስርዓት ከሌሎች አገሮች ይለየዋል።
በዚህ ዘገባ ላይ እንደሚታየው እያንዳንዱ የሰው ፍጥረት ህይውቱን፤ ኑሮውን ለመደገፍ በዝቅተኛ መመዘኛ፤ ምግብ፣ ውሃ፣ መጠለያ፣ ጤና እና ልብስ ያስፈልገዋል። በተዛማጅ፤ ትምህርት፤ መጓጓዣ፤ የህይዎት ዋስትና ያስፈልገዋል። እነዚህ ዝቅተኛ የሰው ልጅ መሰረታዊ ፍላጎቶች ናቸው። እነዚህ ፍላጎቶቹ ካልተሟሉለት ደግሞ፤ ሕዝብ ሊሰራ አይችልም፤ ሊንቀሳቀስ አይችልም። ሊያመርት አይችልም፡፡ ውሃ ካልጠጣም እንዲሁ። ጤናው ከታወከም እንዲሁ። በገፍ የሚሰደድበት አንዱ መሰረታዊ ምክንያትም ይህ ነው።
ሌላው ጦርነትና ግጭት ነው። ሕዝቡና መንግሥት ተደጋግፈው ቢስሩ የሰዉ ልጆችን መሰረታዊ ፍላጎቶችን በማሟላት በኢትዮጵያ ሰላምን፣ ሰብአዊ ደህንነትን እና መረጋጋትን አወንታዊ እና ዘላቂ ማድረግ ይችላሉ የሚል እምነት አለኝ። ሆድና ጀርባ ከሆኑ ግን አይችሉም። ፍላጎቶች ሲሟሉ፤ ኢትዮጵያውያን በራሳቸው እና በአገራቸው ማመን ይጀምራሉ። በጣም የሚያሳዝነው ግን የአብይ መንግስት ይህንን ግዴታ አያውቀውም። የእድገት እና የልማት አጀንዳው ፍጹም ተቃራኒ ነው።
የእርስ በእርስ ጦርነት ዛሬ የተጀመረ አይደለም። ዛሬ የበለጸጉ አገሮች የምንላቸው እንደ ጀርመን፣ እንግሊዝ፣ ጣሊያን፣ ቻይና ወዘተ ብዙ የእርስ በእርስ ጦርነት የተካሄደባቸው፤ በደም የተበከሉ አገሮች ናቸው። በአፍሪካ ሩዋንዳና ናይጀሪያም በተመሳሳይ፤ በንጹሃን ዜጎች ላይ የተፈጸመው እልቂት ላወቀበት ብዙ ያስተምራል። ጀርመኖችና ጣልያኖች የሚናገሩት ተመሳሳይ ቋንቋ ነው። ብሄራቸው አንድ ነው። የአፍሪካ አገሮችን የሚለየው ሩዋንዳም ሆነ ናይጀሪያ ልዩ ልዩ ብሄረሰቦች የሚኖሩባቸው አገሮች መሆናቸው ነው።
የብሄር ልዩነቶቻቸውን በጥበብ አያስተናገዱት ይታያሉ። ቁም ነገሩ፤ የሃገርና የሃገረ መንግሥት ግንባታ ሽርሽር አይደለም። ላወቀበት፤ ከላይ ከተጠቀሱት የተለያዩ አገሮች ልምዶች ትምህርት ወስዶ የሕዝቡን መሰረታዊ ፍላጎት ማሟላት ነው። ይህን ግን የዐቢይ አህመድ ብልጽግና ትምህርት ሊወስድበት አይችልም፡፡ ትምህርት ይወስድበታል ከተባለም፤ እልቂቱን እንዴት ከእነዚህ አገራት በላቀ መጠን ማሳደግ እችላለሁ ብሎ ነው የሚስበውና የሚሰራው። ፡ይህ ዝንባሌ ጤናማ አይደለም።፡
ድህነት ለሰላም፤ ለእርጋታ፤ ለአብሮነት፤ ለእድገትና ለልማት፤ ለሃገረ መንግሥት ግንባታ፤ ለመልካም ጉርብትና ጸር ነው። መሰናክል ነው። ያባባሰው የዘውግ የበላይነንትና ተተኪነት ነው። በረሃብ ለሚሰቃይ ድሃ ሕዝብ ምርጫና ዲሞክራሳዊ ፋይዳ የለውም። በረሃብ የሚሰቃይ ሕዝብ የመጀመሪያ ፍላጎቱ ፍትህ ነው። የፍትህ መሰረቱ ደግሞ ፍላጎቱን ማሟላት ነው። ይህ የሕዝቡ ሰብአዊ መብት ነው። “ላም አለኝ በሰማይ” ፍትህ አይደለም። ብልጭልጭ ፕሮጀክትም የተራበውን ሊመግብ አይችልም።
መሰረታዊ መብቱ ካልተከበሩ ሕዝቡ እንዴት ስለ ዲሞክራሲ፣ ስለ ምርጫ፣ ወዘተ ሊያስብ ይችላል? አይችልም። የመሰረታዊ ፍላጎት መጠኑን በሚገባ ካልተገነዘብነው መፍትሄ ለመፈለግ አይቻልም።
በ2025 43 በመቶ የሚሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ በፍጹም ድህነት (Extreme Poverty) እርከን ውስጥ የሚኖር ነው፡፡
ከ50–60 በመቶ የኢትዮጵያ ሕዝብ የምግብ ዋስትና የለውም፤ በከተሞች ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው 90 በመቶ ረሃብተኛ ናቸው፡፡ በሌላ አነጋገር ምስኪን ናቸው ማለት ነው፡፡
60 በመቶ ማለትም 70 ሚሊየን የኢትዮጵያ ሕዝብ ንጹህ ውሃ የለውም፤ አያገኝም፤ ይህ ለበሽታ ያጋልጠዋል፡፡
86 በመቶ የሚሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ የንጽህና አገልግሎት ወይም መጸዳጃ የለውም፤ ይህ በሽታን ያባብሳል።
85 በመቶ የሚሆነው የኢትዮጵያ የገጠር ሕዝብ ምንም አይነት የጤና አገልግሎት የለውም።
Habitat for Humanity በሰጠው ዘገባ 70 በመቶ የሚገመተው የኢትዮጵያ ህዝብ፤ አግባብ ያለው መኖሪያ የለውም፤ ልክ እኔ በተወለድኩበት ዘመን የነበረው ሁኔታ አሁንም አለ ማለት ነው፡፡
ከ50 በመቶ በላይ የሚገመተው የኢትዮጵያ ህዝብ የኤሌክትሪክ አገልግሎት አያገኝም።
የዓለም የምግብ ፕሮግራም የ2025 ዘገባ የሚያሳየው ረሃብና የወጣት ልጆች የምግብ እጥረት እየጨመረ መሄዱን ነው።
በኢትዮጵያ ይህንን ሁኔታ ያባባሰው ተከታታይ ጦርነት፤ የእርስ በእርስ ግጭት፤ የአየር ጠባይ ለውጥ፤ የዜጎች መፈናቀል፤ የኢኮኖሚና የፋይናንስ ቀውስ እና የአካባቢው አለመረጋጋት መሆኑን ዘገባው ቢጠቁምም፤ በቀዳሚነት የሚነሳው ምክንያት ግን፤ የብልጽግናው መንግሥት የሚከተለው የጦርነት ፖሊሲ እና የማክሮ ኢኮኖሚ ዝንፋት ነው፡፡ .
ኢንተርናሺናል ረስኪው ኮሚቴ የተባለው የታወቀ ሰብአዊ ድጋፍ ለጋሺ ድርጅት በ2025 ከፍተኛ ቀውስ ከተከሰተባቸው አስር አገሮች ማካከል ኢትዮጵያን በርከን አራት መድቯታል። እንዲህ ብሏል፤ Ethiopia: Risk of major conflict grows as global flashpoints intensify.” ለተባሰው እንዲሉ፤ “የአገር ውስጥና የአካባቤው ዳይናሚኮች (ንትርኮች) ሁኔታውን እያባባሱት ነው። ይህ ሁኔታ፤ የኢትዮጵያን አለመረጋጋት አጠናክሮታል። ከድጋፍ አንጻር ሱታይ፤ የአሜሪካ መንግሥት ሰብአዊ ድጋሩን በ$ $387 ሚሊየን መቀነሱ ድጋፍ በሚያስፈልጋቸው እንደሚጎዱ ያሳያል። በትግራይ ክልል ብቻ 800,000 ከቀያቸው የተፈናቀሉ የክልሉ ተወላጆች አሰቃቂ በሆነ ደረጃ እንደሚኖሩ አሳስቧል። በመካከለኛው ኦሮምያ በፌደራሉ መንግሥትና ተቃማዎች መካከል በሚካሄደው ግጭት ምክንያት፤ከ 288,000 በላይ ተፈናቅለዋል። ይህ ግጭት የንጹህ ዜጎችን ህይውዎት እየቀጸፈ፤ ህጻናት በረሃብ እንዲሰቃዩ፤ ህይዎት እንዲናጋ እያደረግ መሆኑን ያበስርል። ቤተሰቦች ቤታቸውንና ንብረታቸውን እየተው የሚሰደኡ መሆናቸውን አስምሮበታል።
የአሜሪካ እርዳታ በከፍተኛ ደረጃ መቀነሱ የሚኖረው ፋይዳ ምንድን ነው? ብየ ራሴን ስጠይቅ፤ 600፣000 ህጻናትና እናቶች የመኖር አለመኖር ሁኔታ እንደሚገጥማቸው ተገንዝቢያለሁ። ይህ እጆግ በጣም አሳሳቢ ነው። ይህንን ክራይሲስ የዐብይ አህመድ መንግሥት እንዴት እንደሚወጣው ለሕዝቡ የመግለጽ ግዴታ አለበት።
ይህ ብቻ አይደለም። የአሜሪካ መንግሥት የውጭ ድጋፍ መቀነሱ ደግሞ፤ አራት ነጥብ አራት ሚሊየን በሚሆኑ ህጻናትና ነፍሰ ጡር ሴቶች ህይወት ላይ፤ ከፍተኛ ተጽኖ እንደሚያስከትል ይነገራል። ችግሩ የተባባሰባቸውን ክልሎች ሲጠቁም—በሶማሌ፤ አፋር፤ ኦሮምያና ትግራይ የተባባሠ ሁኔታ እንደተከሰተ ይናገራል። የአማራውን ክልልና ጋምቤላን ከእነዚህ ጋር እመድባቸዋለሁ። ይህ ሁኔታ የረሃብን መጠን ከፍ እንደሚያደርገው አምናለሁ፡፡
ይህ የድህነት እርከን ዝቅ ካላለ መሰረታዊ ፍላጎቶችን ለማሟለት የማያስችል ተግዳሮት እንደሚፈጥር እገምታለሁ።
አሜሪካዊው የስነ-ልቦና ተመራማሪ እና ሳይንቲስት አብርሃም ማስሎው “የሰው ተነሳሽነት ንድፈ ሃሳብ” በተሰኘው መጽሃፉ፤ ከዋናው ስራው የምጠቅሰው የሰው መስወረታዊ ፍላጎትን (Basic needs) የሚመለከት ሲሆን፤ የሰው ልጅ የሚያነሳሳውን እንድንመረምር ያስገድደናል፡
እኔ ስለ በከፍተኛው ደረጃ እንወያይ አልልምም። ራስን እውን ማድረግ፤ ለራስ ክብር መስጠት እና ፍቅር እና እዚህ ጋር መሆን እነዚህ እንደኔ ላሉት በድሎት ለምንኖር ሰዎች ከፍ ያሉ እና ተፈላጊ ማበረታቻዎች ናቸው።
የኢትዮጵያ ሕዝብ አሁናዊ ፍላጎቱ የድሎት ኑሮ አይደለም። ቢያንስ ማስሎው የጠቆሟቸው ዝቅተኛ ፍላጎቶቹ እንዲሟሉለት ነው። ምግብ፤ ንጹህ የሚጠጣ ንጹህ ውሃ፤ ንጽህና፤ መጠለያ፤ የጤና አገልግሎት ወዘተ ማግኘት ሰብአዊ መብት ነው።
ማንም ሰው በያለበት ኑሮውን ለመደገፍ ይጥራል። ጥረቱ ፍሬ የሚኖረው ሰላምና እርጋታ ሲኖር ነው። የሰው ደህንነትና ፍላጎትን ማሟላት ግንኙነት አላቸው። ምንም አይነት ሁከት ባለበት አገር፤ መንግስት ንፁሀን ዜጎችን ከገደለ፤ ጠለፋ፤ እስራትና ሌላ ሁከት ከፈጠረ፤ ፍላጎትን ስኬታማ ለማድረግ አስቸጋሪ ይሆናል።
በአዎንታዊ መልኩ ሳቀርበው፤ የሰዎች ደህንነት፤ ድህነትን በመቅረፍ መሰረታዊ ፍላጎቶችን ስኬታማ የማድረግ ጉዞ ግንኙነት ያላቸውና ተደጋጋፊ መሆናቸውን ላሰምርበት እፈልጋለሁ።
የመንግሥት ባጀትና የግል ወይንም የውጭ እርዳታና ሌላ ድጎማ ፈሰሥ ድህነትን ለመቅረፍ ተከታታይ፤ ተቋማዊና አስተማማኝ ሲሆን ፍላጎቶች የሚሟሉበት መሰረት እና እድል ስር እየሰደደ ይሄዳል። ባንግላዴሽ፤ ሕንድ፤ ቻይና፤ ሩዋንዳ፤ ኢንዶኔዢያ ወዘተ ፍላጎቶችን አሟልተዋል። ከእነዚህ አገሮች ልምድ ለመውሰድ ይቻላል። ትርጉም ያለው ልማትና እድገት የዜጎችን መሰረታዊ ፍላጎቶች ሲያሟላ የማምረትና ተዛማጅ የልማት መሰረቶችንና ምሰሶዎች ለመፍጠር የሚቻልበት ሁኔታ ይፈጠራል።
ልማት ውሎ አድሮ የዜጎች የህይዎትና ኑሮ ደህንነት ነው ብዬ እከራከራለሁ። ይህ ዕድሜ፣ ጾታ፣ ዘር ወይም እምነት አይለይም። ምንም ይሁን ምን ሰዎች ሁሉ ምግብ፣ ውሃ፣ ጤና፤ መጠለያ፣ ልብስ፣ መጓጓዣ፣ ንፅህና ያስፈልጋቸዋል እና ይገባቸዋል። ይህ የመንግሥት ግዴታ ነው። ይህ የሕዝብ መብት ነው።
ሁሉም ልጆች ትምህርት ያስፈልጋቸዋል እና ይገባቸዋል። ይህ ሰብአዊ መብት ነው። ያልተማረ ትውልድ ረሃብተኛና ስደተኛ ይሆናል። አድሏዊነት ሁኔታውን የፖለቲካ ያደርገዋል።
አድሏዊ ትምህርት የሚያስከትለው አደጋ አፍራሽ እንደሚሆን አልጠጣጠርም። የተገለሉት ወጣቶች የበከላቸውን አገዛዝ ሲረግሙት መኖራቸው አይቀርም። መርገም ብቻ ሳይሆን ይታገሉትል። መታገልም ይገባቸዋል፡፡ ልጅ የወለደ ባልሥልጣን እንዴት ሌሎች ልጆች እንዳይማሩ ያደርጋል?
በዚህ ክፍለ ዘመን መሰረታዊ ፍላጎቶችን ማሟላት የሰብአዊ መብት ጉዳይ ነው ብዬ አምናለሁ። አንድ መንግሥት እነዚህን ፍላጎቶች ካላሟላ፣ የማስተዳደር ቅቡልነት ያጣል። በአንድ ወቅት፤ የብራዚል ፕሬዝደንት ሉላ ዳሲልቫ፤ ‹‹ርሃብ አጣዳፊ እና ሁሉንም የሚጎዳ ነው፡፡ ሁሉንም የእድገትና የስኬት መንገዶችን የሚያጠፋ፤ ተስፋንም የሚገድል ነው፡፡ ሁላችንም ይህን የጋራ ህመማችንን ልንታገለውና ልንዋጋው ይገባናል›› ብለው ነበር፡፡
‹‹የተራበ ሕዝብ መንግሥቱን ይበላል›› የሚለው ብሂል ቀልድ አይደለም። ድህነት፤ ረሃብተኛነት፤ ስራ አጥነት፤ የሰብአዊ መብት አለመኖር ክፍተት ወዘተ ላለመረጋጋት ግብዓት ናቸው። ይህ ለሽርብተኛ ገዥዎች ሰርግ ሆኗል። ይህ በረሃብ አለንጋ መገረፍ ሁኔታ የኢትዮጵያን ወቅታዊ ችግር ይገልጸዋል። የዐቢይ መንግሥት ለወንበሩ መጥበቅ ድህነትን በዋና መሣሪያነት የሚጠቀመውም ለዚህ ነው፡፡
ለኔ የሕዝቡን መሰረታዊ ፍላጎቶች መሟላት ወይንም አለመሟላት መስፈርት ስገመግመው መንግሥትን የሚቆጣጠረው ግለሰብ ወይንም ፓርቲ ምንም ለውጥ አያመጣም። መለስ ዜናዊ ግራ ዘመም ህወሓት ነበሩ። ኢትዮጵያ በእርሳቸው ዘመን በመሰረተ ልማት አስደናቂ እድገትና ልማት አስመዝግባለች። መለስ ፍጹም ነበሩ ወይ? ካልን መልሱ ቀላል ነው፤ አልነበሩም፡፡ ነገር ግን አፄ ኃይለ ሥላሴ እንዳደረጉት ሁሉ እሳቸውም የቻሉትን አድርገዋል፡፡ የሕዳሴ ግድብን አጼ ኃይለ ሥላሴ እንዲዘጋጅ አደረጉ፤ መለስ ወደ ተግባር ቀየሩት፡፡
በመለስ ዘመን የኢትዮጵያ የድህነት ደረጃ ዝቅተኛ ነበር፤ በአብይ አህመድ ዘመን ግን እጅግ የላቀ ነው። በዚህ መስፈርት ወደኋላ ሄድን ማለት ነው። የኦህዴድ ብልጽግና መሪዎች ይህንን ሃቅ አይቀበሉም። እነሱና ደጋፊዎቻቸው ተጠቃሚዎች ስለሆኑ ነው።
ድህነት ሲጨምር የፍላጎቶች አለመሟላትም አብሮ ይጨምራል። ስለዚህ “አብይ አህመድ የኢትዮጵያን ህዝብ መሰረታዊ የሰው ልጅ ፍላጎቶች ማሟላት አቅቶታል ወይ?” ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው። የእኔ ግምገማ አዎ ነው። አብይ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ነገሮች የተለያዩ ናቸው። የሚያደርገውን ተመልከታችሁ የሚናገረውን ችላ እንድትሉት እመክራለሁ። ግንኙነት የላቸውም። እርግማን ይሁን ሌላ አላውቅም።
የድሮ ናፋቂ ምሁር አይደለሁም። ግን፤ ማነጻጸር አስፈላጊ ሲሆን፤ ምሳሌ መጥቀስ ተገቢ ነው። በአጼ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት፤ ለከፍተኛ ትምህርት ወደ ውጭ አገር ስንላክ፤ ትምህርታችንን እንደ ጨርስን፤ ‹‹ዲፕሎማችን ላኩልን›› እያልን ወደ ሃገራችን የምንመለስ ነበርን። ፍላጎታችን በሞያችን አገራችንን ማገልገልና በኢኮኖሚዋ ማዘመን ስለነበር፤ ስደት ነውር ነበር። በደርግ ዘመነ መንግሥት፤ የተማረውም፤ ያልተማረውም በሁከት ተበክሎ በገፍ መሰደድ ጀመረ። ያ ዝንባሌ ቀጥሎ አሁን ተባብሷል።
ድሃው ሕዝብ ያስተማራቸው ሃኪሞችና ሌሎች ባለሞያዎች በገፍ ከአገር ይሰደዳሉ። ከሃገር እንዴት ልውጣ እንጂ፤ በአገሬ እየኖርኩ ሕዝቤን ላገልግል፤ አገሬን እንዴት ላዘምን የሚለው ክፍል እየቀነሰ ሂዷል። ለዚህ ዋናው ምክንያት የስርዓቱ ከፋፋይነት፤ አድሏዊንት፤ ጎሰኛነት፤ ተተኪነት፤ ሙሰኛነት፤ አፋኝነት፣ ጦረኛነትና አገር አምካኝነት ነው።
እርግማን ይሁን ሌላ፤ እኛ ኢትዮጵያዊያን አገር ዘመናዊ የማድረግ ሂደትን አላወቅንበትም። ከላይ የጠቀስኩትን ልድገመው። ‹‹ያልተማሩት አባቶቻችን በአደራ የሰጡንን ታሪካዊና በነጻነቷ የምትታወቅ አገር፤ የተማሩ ማህይማን እያፈረሷት እያየን ድምጽ እንኳን አናሰማም››” ይህ የሚመስጥ ብሂል ነው። ‹‹ምሁር እንዴት ይፈራል? እንዴት አድርባይ ይሆናል?›› ማለታቸው ነው። መልሱን ለናንተ ልተወው።
አብይ ስልጣኑን ለማቆየት ምን አይነት መሳሪያ ይጠቀማል?
ብንቀበልም፤ ባንቀበልም፤ ድህነት እየጨመረ ነው። የዜጎች ፍላጎት አልተሟላም። ድሃ ሆኖ የተወለደ ህጻን ድሃ ሆኖ የመኖር እድሉ ከፍተኛ ነው። የዐብይ አህመድ አሊ ዋና ትኩረት ድህነትን መቅረፍ አይደለም። እንዲያውም ድሃ የሆነን ህዝብ በቀላል ለመግዛት ይቻላል የሚል ግንዛቤ እንዳለው አምናለሁ። ግዙፍ ገንዘብ ለግለሰቦችና ለስብስቦች ይለግሳል። ዐብይ አህመድ ከሚጠቅማቸው መሳሪያዎቹ መካከል፤ ‹‹ህግ እና ስርዓትን ለማስከበር›› በሚል ሽፋን፤ በመላው አገሪቱ በሚያስብል ደረጃ የከፈተው ጦርነት፤ ለሥልጣኑ የሚጠቀመው ዋና ስልት ነው፡፡
በኢትዮጵያ የድህነትን ሥር ማጥፋት ከፈለግን፤ መንገዱ በሁሉም ዘርፍ ያለውን እምቅ አቅም ችሎታ መልቀቅ ወይንም ማናቆዎችን ማስወገድ አስፈላጊ ነው።
ምን ይደረግ?
የምግብ ምርትን ማሳደግ፣ የንፁህ ውሃ መጠጥ አቅርቦትን ማቀናጀት እና ዘመናዊ ማድረግ፣ የጤና፣ የትምህርት አገልግሎትን ስርጭት ማመቻቸትና ሚዛናዊ ማድረግ፣ የገጠሩ ሕዝብ የመብራት አቅርቦት ተጠቃሚ እንዲሆን ግፊት ማድረግ ግድ ይላል።
ሕዳሴን ገድቦ ለሕዝብ አገልግሎት ካልዋለ፤ በኩራዝ ለሚኖረው ሕዝብ ካልደረሰ እኔም፤ ሌሎችም ድጋፍ የሰጠነው ለምን ይሆን? ብለን መጠየቃችን አይቀርም። እነዚህን ስኬቶች ለማግኘት ደግሞ በብልጽግና እና በዐቢይ አህመድ የሥልጣን ዘመን የሚሳኩ አይደሉም፡፡ መፍትሔው የችግሩን አረም መንቀል ነው፡፡
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ አብዛኛው የገጠር ሕዝብ ኢኮኖሚ መሆኑን ሁልጊዜ ማስተጋባት ያስፈልጋል። የገጠሩ ህዝብ መሰረታዊ ፍላጎቶችን ማሟላት ከፍተኛ ትርፍ ያስገኛል። ፋላጎቶች ካልተሟሉ ሰላምና እርጋታ ሊኖር አይችልም።
ይህ ወደዚህ ትችት ፍሬ ነገር፤ ማለትም፤ ወደ ኤሊት ኢኮኖሚ ይዞታ ይወስደኛል። እንዲህ ዓይነቱ ቀረጻ ብዙውን ጊዜ ከመደብ ጋር የተያያዘ ነው። በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ ቅይጥ ሆኗል፤ የብሄር ልሂቃንና መደብ ተያይዘዋል።
በኢትዮጵያ የሀብት እና የፖለቲካ ስልጣን በጥቂት እጆች ማሰባሰብን አምካኝና ጎጅ የሚያደርገው ብሄርንና መደብን መሰረት ያደረገ ኢኮኖሚያዊ፣ፖለቲካዊ፣ማህበራዊ እና ባህላዊ ቅኝቶችና ትሥስሮች ያሉት የአንድ ዘውግ የበላይነት ሁኔታ መከሰቱ ነው። ይህ ክስተት አገር አፍራሽ ስለሆነ አደገኛ ነው። ብዙ ሚሊዮኖችን ይጎዳል። አገርን አተራምሶ እንድትበታተን ግብዓት ይሆናል። ብትበታተን ሁሉም ይጎዳል። አሸናፊ ሊኖር አይችልም።
ወደ ኋላ ተመልሰን ማስሎው የሰጡትን የመሰረታዊ ፍላጎቶች ሞዴል ብናጤን፣ የብዙሃኑ የኢትዮጵያ ሕዝብ መሠረታዊ ፍላጎቶች አልተሟላም። ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ ካለው የሀብት ክምችትና የሀብት አያያዝ አንጻር ስገመግመው ደግሞ እጂግ የሚያሰጋ ኢ-ፍትሃዊ እና ኢ-ሚዛናዊ መሆኑ በግልጽ ይታያል።
እኔን ለትችት የጋበዘኝ ሥርዓቱ ድህነትን እንደ መሳሪያ እየተጠቀመበት መሆኑ ነው። ይህ-ኢ-ፍትሃዊነት የጋራ ማህበረሰባዊ ትሥስሮችንና ጥቅሞችን ይቀንሳል። ብሔራዊ ማንነትን ያመክነዋል። አሉታዊው ውጤቱ ምንድን ነው? ብለን ብንጠይቅ፤ ሁሉም ለራሱ ወይንም ለግሉ መሆኑ ነው። ቢበዛ ለራሱ ብሄር ነው። ሀገሪቱ በጥርጣሬ ውስጥ ገብታ ትፍረከረካለች ወይንም ወደ ሁከት ትሸጋገራለች ማለት ነው።
ኢ-ፍትሃዊነትን መርህ ያደረገ ሥርዓት ደግሞ፤ ዘርፈ ብዙ ሁከት በኦሮሙማ እና በኦሮሞ ልሂቃን የበላይነት ርዕዮተ ዓለም ስኬታማና መዋቅራዊ ለውጥ እንዲሆን እየተደረገ ነው። ይህ የበላይነት መሬትን የማጠቃለል ይዘት አለው፤ እስከ ኤርትራ እና ኬንያ ድረስ ይዘልቃል።
ይህ ሁኔታ ለመላው ቀጠና አደጋ ፈጥሯል። በጣም የሚገርመው ይህ የተጠላለፈ ወይም የተዋሃደ እና ተቋማዊ አሰራር ላይ ላዩን ብቻ ካየነው አደጋ ያዘለ ሆኖ አይታይም። የማይታይበት ሁለት ምክንያቶች አሉት፤ አንድ፤ የውጭ ሚዲያ እንደ ልብ ተንቀሳቅሶ በመሬት ያለውን ሁኔታ ለማቅረብ ባለመቻሉና፤ ሁለት ሕዝቡ በፍርሃት ውስጥ ስለሚኖር ነው። በውጭ የሚኖረው የፍርሃቱ አካል ነው።
መፍትሔው አንድና አንድ ነው፤ እሱም፤ ይህን የሁሉም ኢትዮጵያዊያን የጋራ ስጋትና የሀገር መፍረስ መሀንዲስ የሆነውን ሥርዓት በጋራ ታግሎ መጣል ብቻ ነው፡፡ ይህን ማድረግ ካልቻልን ግን፤ የዩጎዝላቪያዊያን እጣ ፋንታ በደጃችን ቆሞ ያንኳኳል፡፡
December 18, 2025