ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)
ታህሳስ 5፣ 2018(December 14, 2025)
መግቢያ!
የታሪክ ግዴታ ሆኖ የአንድ አገር ህዝብ ዕድል በመጥፎም ሆነ በጥሩ መልክ ሊወሰን የሚችለው ስልጣንን በጨበጠ ኃይልና፣ በጠቅላላው ሲታይ ኤሊት ነኝ በሚለው ጥቂት ኃይል ነው። ይህ ኃይል ደግሞ በጣም ጥቂቱ ካልሆነ በስተቀር ፈጣሪና አምራች ያልሆነ፣ እንዲሁም አንድን አገር ለመገንባት በሚያስችሉ ሳይንሳዊ ምርምሮች ላይ የማይሳተፍ አገርን አስተዳድራለሁ የሚል ነው። በሌላ ወገን ደግሞ በአንድ አገር ውስጥ የሚኖር ጠቅላላው ህዝብ፣ የፖለቲካ፣ የሚሊተሪ፣ የፀጥታ ኃይል፣ ፖሊሱንም ጨምሮና በየቢሮዎች ውስጥ ተቀምጠው ቢሮክራሲያዊ ስራዎችን የሚሰሩና፣ ሌሎችም በተለያዩ የአገልግሎት መስኮች ውስጥ ተሰማርተው የሚሰሩ ሁሉ ለአንድ አገርና፣ አንድም ህብረተሰብ እንደህብረተሰብ ይያዝ ዘንድ የግዴታ አስፈላጊዎች ናቸው። እንደሚታወቀው አንድ ህብረተሰብ እንደ ህብረተሰብ ሊቆጠር የሚችለው በስራ-ክፍፍል አማካይነት ሲደራጅ ብቻ ነው። የስራ-ክፍፍል በደንብ ባልዳበረበት ህብረተሰብ ውስጥ አንድ ህብረተሰብ ልዩ ልዩ ነገሮችን ሊፈጥር አይችልም። ከዚህ ውስጥ ልዩ ልዩ ነገሮችን የሚያመርቱና የማያመርቱ ክፍሎች አሉ። የማያመርተው ወይም በአጠቃላይ አነጋገር የአገልግሎት መስኩ የሚመካው ልዩ ልዩ ነገሮች በሚመረቱበት ክፍል ብቻ ነው። አንድ ህብረተሰብ እንደህብረተሰብ ሊንቀሳቀስ፣ ሊኖርና ሊያስብም የሚችለው አምራች በሆነው መስክ ልዩ ልዩ ነገሮች ተመርተው ሲቀርቡለት ብቻ ነው። ስለሆነም የግዴታ ለአንድ ህብረተሰብ አምራች የሆነው ክፍል በጣም ወሳኝ ሚናን ይጫውታል። ልዩ ልዩ ሰብሎች፣ ፍራፍሬዎችና አትክልቶች፣ እንዲሁም የምርት መሳሪያንና ልዩ ልዩ የፍጆታ ዕቃዎችን የሚያመርተው የስራ-ክፍፍል አካል የሆነው ቀልጣፋማና ምርታማ እንዲሆን ከተፈለገ በሳይንሳዊ ምርምርና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ መደገፍ አለበት። የ ሲሆን ብቻ ነው በአንድ አገር ውስጥ በቁጥር እየጨመረ የሚሄድን ህዝብ ልዩ ልዩ ፍላጎቶቹን ማሟላት የሚቻለው። የአንድን ህብረተሰብ ፍላጎት ለማሟላትና ለስራ እንዲዘጋጅ ከተፈለገ የግዴታ ለሰው ልጅ አስፈላጊ በሆኑ ነገሮች ላይ ማትኮሩ የህዝቡን የመፍጠር ችሎታ ሊያሻሽለው ይችላል፤ መሰረታዊና ለሰው ልጅ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች ተመርተው ገበያ ላይ ሲቀርቡ እያንዳንዱ ግለሰብ የማሰብ ኃይሉ ክፍ ማለት ብቻ ሳይሆን ማንነቱንም ያውቃል። ሰው መሆኑንም ይገነዘባል። ሰለሆነም በአንድ አገር ውስጥ ያለ የተማረ ኃይልና መንግስት የሚባለው አካል የግዴታ ለሰፊው ህዝብ አስፈላጊ በሆኑ ነገሮች ላይ ከፍተኛ አትኩሮ መስጠት አለባቸው። በሌላ ወገን ግን በአገራችንም ሆነ በተለያዩ የሶስተኛው ዓለም አገሮችን ሁኔታ ስንመለከት መንግስት የሚባለውና በአጠቃላይ ሲታይ ኤሊት የሚባለው ክፍል ንቃተ-ህሊናቸው በጣም ዝቅተኛ ወም ደካማ ስለሆነ አንድ ህዝብ ለህይወቱ አስፈላጊ ነገሮች ተመርተው ይቅረቡለት ወይም አይቅረቡለት ግዴታቸው አይደለም። የአገዛዝ ስልታቸውም በደመ-መንፈስ መመራት ስለሆነ ሳይንሳዊ መሰረት የሌለውንና በደንብ ያልተጠና የኢኮኖሚ ፖሊሲን ተግባራዊ በማድረግ አንድ ህዝብ ተዘርክርኮ እንዲኖር ያደርጋሉ። የመንግስትን መኪና የሚቆጣጠሩና በተለይም የፖለቲካና የኢኮኖሚ ኤሊቱ ከውጭ ኃይሎች ጋር በጥቅም የተያያዙና የእነሱንም ጥቅም አስጠባቂዎች ስለሆኑ በየጊዜው ተግባራዊ በሚያደርጉት የኢኮኖሚ ፖሊሲ ድህነትንና ኋላ-ቀርነትን ያስፋፋሉ። ህብረተሰቡም ርስ በርሱ የጠነከረ ግኑኘነት እንዳይመሰርትና እንዳይደጋገፍም በማድረግ በራሱ ላይ ዕምነት እንዳይኖረው ያደርጋሉ። በቀላሉም የውጭ ኃይሎች ሰለባ በመሆን የዝቀተኝነት ስሜት እንዲያድርበት ያደርጋሉ። ይህ ዐይነቱ በደመ-ነፍስ ላይ የተመሰረተ ወይም ኢ-ሳይንሳዊ የሆእነ የአገዛዝ ስልት የግዴታ ለጎሳና ለሃይማኖት ግጭቶች አመቺ ሁኔታን ይፈጥራል። ስራ-ፈትና ያልነቁ ኃይሎች ከውጭ ኃይሎች ጋር በማበርና ህብረተሰቡን በጎሳና በሃይማኖት በመከፋፈል ርስ በስርሱ እንዲበላላ ያደርጋሉ። አትኩሮው ስራና መፍጠር መሆኑ ቀርቶ ይህንን ኃይል ለህይወት አስፋላጊ ባልሆኑ ነገሮች ላይ በማተኮር እየተፋጠጥጠና እየተጨቀጫቀቀ እንዲኖር ያደርጋሉ። ይህ ዐይነቱ ሁኔታ እንዳይከሰተ ከተፈለገ አንድ ህብረተሰብ ጭንቅላታቸው በበሰለ፣ አርቀው በሚያስቡና ጥልቅ ዕውቀት ባላቸው መመራት አለበት።
ከዚህ ሁኔታ ስንነሳ እያንዳንዱ የህብረተሰብ ክፍል በግሩፕም ሆነ በግለሰብ ደረጃ በሚያበረክተው አስተዋፅዖ ብቻ ነው አንድ አገርና ህብረተሰብ ጤናማ በሆነ መልክ ሊያድጉ የሚችሉት። ከዚህም ባሻገር የመንግስት ሚናና በሳይንሳዊ ፍልስፍና መዋቀሩ ለስራ-ክፍፍል መዳበር በጣም ወሳኝ ነው። በሌላ ወገን አንድ የመንግስት አወቃቀር ከታች ወደ ላይ በስርዓት ካልተዋቀረና ለህዝቡ ልዩ ልዩ ግልጋሎቶች የሚሰጡ ልዩ ልዩ ተቋማት ከሌሉና የመንግስትን መኪና የሚቆጣጠረው በአስተሳሰቡ እጅግ ወደ ኋላ የቀረ ከሆነ የስራ-ክፍፍል ሊዳብር በፍጹም አይችልም፤ የህዝቡም መሰረታዊ ፍላጎቶችም ሊሟሉ አይችልም። በአገራችንም ሆነ በተለያዩ የአፍሪካ አገሮች የምናየው ሁኔታ የመንግስት መኪና ወድ ግል-ሀብትነት የተለወጠና የመጨቆኛ መሳሪያም በመሆን ህዝብን ማስፈራሪያ መሳሪያ፣ እንዲያም ሲል በህዝብ ላይ ጦርነት ማስኬጃ እንደሆነ እንመለከታለን። ከዚህም በላይ የመንግስትን መኪና የሚቆጣጠሩ ኃይሎች ከውጭ ኃይሎች ጋር በመተባበርንባ የእነሱ ታዛዥ በመሆን የመንግስትን መኪና የህብት መዝረፊያ መሳሪያ ያደርጋሉ። በተለይም የመንግስትን ኢ-ሳይንሳዊ ፖሊሲና የመንግስቱንም መኪና ወደ ግል ሀብትነት መለወጡን የሚከታተሉና የሚያጠኑ፣ እንዲሁም የሚዋጉ የነቁ የህብረተሰብ ክፍሎች በሌሉበት አገር ውስጥ አንድ መንግስትና የፖለቲካና የኢኮኖሚ ኤሊት አገርን በማፈራረስ ተግባራቸው ይገፉበታል። ስለሆነም በአንድ አገር ውስጥ የሚኖር ህዝብ የንቃተ-ህሊናው መዳበርና የፖለቲካ አመለካከቱ መብሰል ለሁለ-ገብ የኢኮኖሚ ዕድገትና ለስራ-ክፍፍል መዳበር ወሳኝ ሚናን ይጫውታሉ።
ይሁንና ግን በአንድ አገር ውስጥ የሚኖር ህዝብ የቱን ያህል በስራ ክፍፍል እንደሚያምንና፣ አንደኛው ካለሌላው ለመኖር እንደማይችል ይገነዘብ አይገነዘብ እንደሆን ለማወቅ በጣም አስቸጋሪ ነው። በአጠቃላይ ሲታይ ግን በተለያዩ አገሮች ውስጥ ስልጣን ላይ የተቀመጡና ከበስራቸው ያለው የአገዛዝ መዋቅርና፣ በተለይም በፖለቲካ ውስጥ እሳተፋለሁ የሚልና እዚህና እዚያ የሚሯሯጥ በግለሰብም ሆነ በግሩፕ ደረጃ ራሱን ለመግለጽ የሚሞክር ሁሉ እነዚህ በአጠቃላይ አጠራር ኤሊት ተብለው የሚጠሩ ኃይሎች አንድ ህብረተሰብ በስራ-ክፍፍል አማካይነት መገለጽ እንዳለበትና፣ አንድ ህብረተሰብም በመደጋገፍ ላይ ብቻ የተመሰረተ መሆኑን የሚረዱ አይደሉም። ስልጣን ላይ የተቀመጡና የቀረበላቸውን ከመመገብና ሌላው ሰርቶ ያመጣውን ከመጠቀም በስተቀር እነዚህን ሁሉ ነገሮች ማን ሰራቸው ወይም ማን አመረታቸው፣ እንዴትስ ተመረቱ ብለው ሊያወጡና ሊያወርዱ ወይም በቅጡ ለማሰብ የሚችሉ አይደሉም። ዝም ብለው በደመ-ነፍስ የሚመሩና የሚሰሩትንም ነገር ለምን እንደሚሰሩና፣ ለምንስ በዚያ መልክ እንደሚሰሩ ለመጠየቅ የሚችሉ አይደሉም። ከዚህም ባሻገር አንድ ህብረተሰብ እንደ ህብረተሰብ እንዲያያዝና እንዲደጋገፍም ከተፈለገ የግዴታ ሳይንሳዊ የሆነ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ፖሊሲ እንደሚያስፈልገውና፣ ይህም አጠቃላይ የሆነ ህዝባዊ ሀብት መፍጠር እንዳለበትና ጠቅላላውንም ህዝብ ከድህነትና ከኋላ-ቀርነት ሊያወጣው የሚችል እንደሆነ በፍጹም የሚገነዘቡ አይደሉም። ስለሆነም በተለይም በውጭ ኃይሎች እየታዘዙ ተግባራዊ የሚያደርጓቸው ፖሊሲዎችና በደመ-ነፍስ በመመራት የሚወስዱት በጉልበት ወይም በኃይል ላይ የተመሰረተ ፖለቲካ የሚሉት ፈሊጥ የእኛን አገር ብቻ ሳይሆን የተለያዩ አገሮችን ፖለቲካዊና ማህበረሰባዊ ሁኔታ እያዘበራረቀው ይገኛል። ከፍተኛ የባህል ውድቀትም እያስከተለ ነው። በዚህም ምክንያት የተነሳ ታሪክን እንዲሰራና በሰላም እንዲኖር የተፈጠረ ሰፊ ህዝብ ሰይጣናዊ መንፈስ ባላቸው ፖለቲካ ነኝ ባዮችና፣ በአጠቃላይ ሲታይ የፖለቲካ፣ የሚሊተሪ፣ የፀጥታና የሌሎችም ኤሊቶች ሰለባ በመሆን ለዝንተ-ዓለም እየተሰቃየ እንዲኖር ይገደዳል። አንድ አገርም ታሪክ የሚሰራባት መድረክ ከመሆን ይልቅ የማንም ዱርዬዎች ይሁንና ፖለቲካ ነን ባዮች መፈንጫ ትሆናለች ማለት ነው።
በተለይም ባለፉት ሃምሳ ዓመታት በአገራችን ምድር በፖለቲካ ስም የተሰራውን ወንጀል፣ መጠነ-ሰፊ ግድያ፣ ከቀዬ ማፈናቀልና አካባቢውን ጥሎ እንዲጠፋ ማድረግ፣ ከዚህም በላይ ከውጭ ኃይሎች ጋር በመደራደር የባርያ ንግድ የሚመስል ስምምነት በመፈራረም ወጣት ሴቶች አገራቸውን ጥለው ወደ ተለያዩ የአረብ አገሮች እንዲሰደዱና የስቃይን ጽዋ እንዲቀምሱ ማድረግ፣ ይህ ሁሉ የሚካሄደው ሰይጣናዊ መንፈስ ባላቸው ወይም ደግሞ ጭንቅላታቸው ከልጅነታቸው ጀምሮ በጥሩ ዕውቀት ባልተኮተኮተና ራሳቸውም ሰው መሆናቸውን በማይገነዘቡ ጥቂት ኤሊት ነን ባዮች አማካይነት ነው። ይህንን የሰይጣናዊ መንፈስ ማቆጥቆጥና ወደ አገር አፍራሽነት መለወጥ ለመረዳት ነገሩን ጠለቅ ብሎ መረዳት ያስፈልጋል። በመጀመሪያ ደረጃ ግን የሰው ልጅ ለምን ሰው እንደሆነና ከእንስሳም እንዴት እንደሚለይ አንዳንድ ነገሮችን እንመልከት!
የሰውን ልጅ ከእንስሳ የሚለየው ነገር ምንድን ነው?
የሰውን ልጅ ሰው የሚያሰኘው የማሰብ ኃይል ስላለው ነው። የማሰብ ኃይል ስንል ደግሞ በመጥፎ ነገር የሚገለጽ ሳይሆን ቆንጆ ቆንጆ ነገሮችን ማሰብ ማለት ነው። ይህም ማለት ሰውን አለመጉዳት፣ ማመዛዘን፣ ለሌላው መቆርቆ፣ አዛኝ መሆን፣ አንዱ አንድ መጥፎ ነገር ሲያጋጥመው በተቻለ መጠን ለመርዳት መሞከር፣ መረዳዳትና መተባበር፣ ራሱን የህብረተሰብ አካል አድርጎ መቁጠር፣ በሌላው ላይ ለመዘባነን አለመሞከር፣ በተቻለ መጠን ትሁት ለመሆን መሞከር፣ ሀብት አለኝ ወይም የተሻለ ደረጃ አለኝ በማለት ሌላውን ለመናቅ አለመሞክር…ወዘተ. እነዚህ ሁሉ ነገሮች የሰው ልጅ ውስጣዊ ባህርዮች ናቸው። ከዚህም ባሻገር በአንድ ህብረተሰብ ውስጥ ከአንድ የበላይነት ከሚሰማው አካል በኃይል የሚፈጸምን ነገር በጋራ ለመቋቋም መሞከር፣ አንድ አገር የጥቂቶች መፈንጫ መድረክ ሳትሆን በዚያው አገር ውስጥ የሚኖር የጠቅላላው ህዝብ ንብረት መሆኗን በማወቅ ለመንከባከብ ወይም ለመከላከል መሞከር፣ ባጭሩ ዝም ብሎ አለማየት እነዚህ ሁሉ በተለይም አንድ ተማርኩ የሚል ሰው ማድረግ ያለበትና ለሌላውም አርአያ መሆን ያለበት ጉዳይ ነው። ከዚህ ስንነሳ በተለይም አንድን ሰው ሰው የሚያሰኘው በምንም ዐይነት ለጥቅም የማይገዛና፣ ለሌላው በማደር ወይም በማጎብደድ ሌላውን አምሳያው የሆነውን የማያጠቃ ከሆነ በእርግጥም ይህ ሰው ሰው መሆኑን የተገነዘበ ነው ማለት ይቻላል። ከዚህም ባሻገር አንድ ሰው ሰው መሆኑ ጥያቄ ማቅረብ ሲችል፣ በተለይም መደረግና መደረግ በሌለባቸው ነገሮች መሀክል ያለውን ልዩነት የሚገነዘብ ከሆነ ይህ ዐይነቱ ሰው ዕውነትም ሰው ነው ያሰኘዋል። ምክንያቱም ተፈጥሮ የሰጠውን ፀጋ ወይም እግዚአብሄር የለገሰውን የማሰብ ኃይል ተጠቅሟል ማለት ይቻላል። ባጭሩ የሰው ልጅ ራሱን ወደ ውስጥ የመመለክት ኃይል ስላለው ያለውን አዎንታዊ ሁለ-ገብ ባህርይ ከተጠቀመ ዕውነትም ሰው ነው ወይም ደግሞ በእርግጥም በእግዚአብሄር አምሳል የተፈጠረ ነው ማለት ይቻላል።
ከዚህ ወጣ ብለን ወደ ሌሎች ነገሮች ስናመራ አንድን ሰው ሰው የሚያሰኘው የታሪክን ሂደት የተገነዘበ እንደሆንና፣ የአንድ አገርም ታሪክና የህብረተሰብ አወቃቀር በአጉል ትረካ ላይ ተመስርቶ የሚወራ ሳይሆን በጣም የተወሳሰበ መሆኑን የተገነዘበ እንደሆን ብቻ ነው። በሌላ አነጋገር፣ የአንድ አገር ታሪክ በጥቁርና በነጭ በመጻፍ እንደዚህ ነበር ወይም እንደዚህ ተደርጎ ነበር ተብሎ የሚወራ ሳይሆን፣ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የአንድ አገር ታሪክ በተለያየ ጊዜ ወይም የታሪክ ኤፖክ በተፈጠሩ ሰዎች፣ ከዚኸኛው ወይም ከዚያኛው ብሄረሰብ በተውጣጡና በመጋባትና በመዋለድ በተፈጠሩ ሰዎች የሚሰራ መሆኑን የተገነዘበ እንደሆነ ብቻ ነው። ስለሆነም የአንድ አገር ወይም የህብረተሰብ አወቃቀር በቀጥታ(Linear) መንገድ የሚጓዝ ሳይሆን ብዙ ነገሮች በመመሰቃቀልና በውጣ ውረድነት የሚሰራ ብቻ መሆኑን ግንዛቤ ውስጥ ሲገባ በእርግጥም በተለይም አንድን የተማረ ሰው ሰው መሆኑን ያስገነዝባል። እንደሚታወቀው የማንኛውም አገር ታሪክ ወይም ህብረተሰብአዊ አወቃቀር ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፍና፣ የዛሬው ሁኔታ ካለትላንቱ ሊኖር እንደማይችል ግንዛቤ ወስጥ የተገባ እንደሆን ብቻ ነው። በምርምር እንደተደረሰብትና ጥናቶችም እንደሚያረጋግጡት የሰው ልጅ የማሰብ ኃይል እንደየሁኔታዎች እየዳበረ ሰለሚሄድ ከዛሬ ሁኔታ በመነሳት ከሁለት መቶ ዓመት በኋላ የአንድ አገርና ህዝብ ዕጣ፣ እንዲሁም ዕድገቱም ምን ሊመስል እንደሚችል በፍጹም መናገር አይቻልም። በሌላ አነጋገር፣ የአንድን ህብረተሰብ ዕድገትና አወቃቀሩን በተሟላ መልክ ማቀድ በፍጹም አይቻልም። ይሁንና ግን በጣም የጠለቀ የፍልስፍና ዕውቀት ያላቸው ሰዎች ከሆኑ ቀደም ብለው የአንድን ህብረተሰብ ግንባታ መልከ ሊሰጡትና ተከታታዩም ትውልድ በዚያ ላይ ተመርኩዞ እንዲያሻሽለው መሰረት ሊጥሉ ይችላሉ።
የማንኛውም ሰው የማሰብ ኃይል ወይም ሰው መሆኑን ማወቁ በንቃተ-ህሊናው መዳበር የሚወሰን ነው። የንቃተ ህሊና መዳበር ማለትም በመጀመሪያ ደረጃ ራስን ማወቅ ነው። ራስን ማወቅ ማለትም ማለት ሰው መሆኑን መረዳትና በጭንቅላት ውስጥ ያለውን ጤናማ አስተሳሰብ መኮትኮትና ማዳበር ነው። በሌላ ወገን ደግሞ የተማረ ሰው ሁሉ ንቃተ-ህሊናው የዳበረ ሊሆን በፍጹም አይችልም። የተማረ ሁሉ ንቃተ-ህሊናው የዳበረ ቢሆን ኖሮ በዓለም ላይ ይህ ሁሉ ግፍ ባልተሰራ ነበር። የዓለማችንን በተለይም ዘመናዊ አስተሳሰብ ወይም ዘመናዊነት የሚሉት ነገር ከተፈጠረ ጊዜ ጀምሮ የሚካሄዱት ሌላውን ሰውና በአጠቃላይም ሲታይ አንድን ህብረተሰብ የሚጎዱና ታሪካዊ ስራዎችን እንዳይሰራ የሚያደርጉት መጥፎ ነገሮች፣ ለምሳሌ የጅምላ ግድያዎች፣ ጦርነትን በማካሄድ የአንድን አገር ታሪክ ማፈራረስና ህዝብን መግደል፣ በተለይም ደግሞ ዘርና ሃይማኖት ላይ አትኩሮ በማድረግ የሚካሄዱት ጦርነቶችና ግድያዎች በሙሉ የማሰብን ኃይል ለመጠቀም ካለመቻል ወይም አንድ ሰው ወይም ኤሊት ነኝ የሚል ሰው መሆኑን ካለመገንዘቡ የተነሳ የሚካሄዱ ናቸው። አንድን ህዝብ በጎሳና በሃይማኖት በመከፋፈል እንዳይተማመን ማድረግና እንዲያም ሲል ወደ ጦርነት ውስጥ እንዲገባ መገፋፋት እነዚህ ሁሉ ሰይጣናዊ ነገሮች የሚወጠነጠኑትና የሚተገበሩት ተማርን ወይም ዘመናዊ ነን በሚሉ ግለሰቦችና ወይም በፖለቲካ ስም በተደራጁና የውጭ ኃይሎች ተላላኪዎች በሆኑ ኤሊት ነን ባዮች አማካይነት ነው። ለምሳሌ የአለፉትን የሃምሳ ዓመታት ታሪካችን ብቻ ስንመለከት በአገራችን ምድር የተካሄዱትና ዛሬም የሚካሄዱት ጦርነቶችና ታሪክንም ማውደም ተማርን በሚሉ ሰዎች አማካይነት ነው። ከዚህ ስንነሳ የተማረ ሰው ሁሉ ፈጣሪ የሚሆንና ከማንኛውም ዕቡይ ስራዎች የሚርቅ ሊሆን በፍጹም አይችልም። ባጭሩ የዓለም የየአገሮች ታሪክና በኤምፔሪያሊዝም ዘመን በጣም የተወሳሰቡና መርዛማ መሳሪያዎችን እየሰሩ በሚሊዮን የሚቆጠርን ህዝብ መጨረስና አንድን አካባቢ ሰብሎችንና ፍራፍሬዎችን እንዳያበቅል ማድረግ፣ ለምሳሌ የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ቬትናምን ለመውረር ሲል በየሜዳዎች ላይ ይረጭ የነበረው ኤጀንት ኦራንጅ የሚባለው መርዝ፣ እነዚህ ሁሉ የሚውጠነጠኑትና የሚመረቱት ሰይጣናዊ መንፈስ ባላቸው ሰዎች አማካይነት ብቻ ነው። ይህ ዐይነቱ ድርጊት ደግሞ የተፈፀመው ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ያለኝና በህግ የበላይነትም እተዳደራለሁ በሚል ኃያል መንግስት አገዛዝ አማካይነት ነው።
በአጠቃላይ ሲታይና ባለፉት ሁለት መቶ ዓመታት የተደረገውን የሳይንስና የቴክኖሎጂ ምጥቀት ስንመለከትና ዘመናዊነት(Modernization) የሚባለው ነገር ቢስፋፋም ይህ ዐይነቱ ዕድገት በተለይም የፖለቲካና የሚሊተሪ ኢንዱስትሪ ውስብስብ የሆነውን ኤሊት በፍጹም ሰብአዊ አላዳረገውም። እንዲያውም ሰይጣናዊ መንፈሱ የበለጠ በመጠናከር ስልጣኔዎችንና ታሪክን በማውደም፣ በዚያው መጠንም በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን ህይወት ካለምንም ርህራሄ በመቅጠፍ ተዝናንቶ የሚኖር ነው። ባጭሩ ሳይንስና ተኢኮኖሎጂ በተለይም የፖለቲካ ኤሊትን በፍጹም ርህራሄ እንዲኖረው አላደረጉትም። በሌላ ወገን ደግሞ የሳይንስና የቴክኖሎጂን ዕድገት ታሪክ ስንመለከት ተመራማሪዎችና አፍላቂዎች በሙሉ ስለሳይንስና ስለቴክኖሎጂ ሲመራመሩ የሰውን ልጅ ከጨለማ ለማውጣት ብቻ ነው። እንደ አርቺሜዲስ፣ ጋሊሌዬ፣ ሬኔ ዴካ፣ ላይብኒዝና ኒውተን፣ እንዲሁም ጋውስና ሪማን የሚባሉትና ሌሎችም አያሌ የፍልስፍና፣ የሳይንስና የቴክኖሎጂ እንዲሁም የማቲማቲክስ ተመራማሪዎች የፈጠሯቸው ነገሮች በሙሉ የሰውን ልጅ ለመጨረስና ዕረፍትም እንዳይኖረው ለማድረግ አይደለም፤ አላሳቡም። ይሁንና ግን ሰይጣናዊ መንፈስ የተናወጣቸው ወይም መንፈሳቸው በመጥፎ አስተሳሰብ የተዋቀረ የፖለቲካ ኤሊት ነን ባዮች በተለይም በሚሊተሪ-የኢንዱስትሪ ውስብስብና የስለላ ድርጅት በመታገዝ ሳይንስና ቴክኖሎጂን የሰውን ልጅ ህይወት ማቃለያ ከማድረግ ይልቅ የበላይነትን መግለጫና ማስፈራሪ በማድረግ ጦርነትን አለም አቀፋዊ በማድረግ የብዙ የሶስተኛው ዓለም ኢሊቶችንንም ያባልጋሉ፣ ለማባለግም ችለዋል። በየአገሮች ውስጥ ያሉ የፖለቲካ ስልጣንን በአጋጣሚም ሆነ በምርጫ የተቀዳጁ ኃይሎች አገርን በፀና መሰረትና ቆንጆ አድርጎ ከመገንባት ይልቅ ህብረተሰብን ማዋከቢያና ጦርነትን በመፈልፈል የየአገሮች ህዝቦች በሰላም እንዳይኖሩ ለማድረግ ችለዋል። በሌላ አነጋገር፣ የእኛም ሆነ የአብዛኛዎቹ የሶስተኛው ዓለም አገሮች የመንግስት መኪናና የፖለቲካ ኤሊቱ አስተሳሰብና ድርጊቱ በቀጥታ ሰይጣናዊ በሆነ አስተሳሰብ ከታነፀው የአሜሪካ የሚሊተሪ-ኢንዱስትሪ ውስብስብ ኤሊት ጋር የተያያዘና በአሜሪካ የፖለቲካ፣ የሚሊተሪና የስለላ መዋቅር የሚበወዝ በመሆኑ ይኸው እንደምናየው በየአገሮች ውስጥ፣ አገራችንንም ጨምሮ ሰይጣናዊ መንፈስ በተናወጣቸው ኃይሎች ፍዳቸውን እንዲኡያዩ ለመደረግ በቅተዋል። ከዚህ ሁኔታ ስንነሳ በተለይም ባለፉት 80 ዓመታት በዓለም አቀፍ ደረጃ የተዋቀረው መንግስታዊ አወቃቀርና የሚመረተው በአጠቃላይ ሲታይ የፖለቲካና የኢኮኖሚ፣ እንዲሁም ሌላ ኤሊት ፈጣሪና ሰላምን አምጭ አይደለም። የታሪክን ሂደትና የሳይንስንና የቴክኖሎጂን አፈጣጠርና መዳበር ስለማይገነዘብ ያለውን ስልጣን በመጠቀምና የመንግስትን መኪና ወደ መጨቆኛ መሳሪያነት በመለወጥ ህዝብን እያስፈራራ ይኖራል። በአብዛኛው ህዝብ ዘንድም ይህ ዐይነቱ የጥቂት ኢሊቱ ሰፊን ህዝብ ማስፈራራት ከእግዚአብሄር የተሰጠ ፈቃድ እንደሆነ አምኖ በመቀበል ዝም ብሎ እንደ ከብት ይነዳል። ለመጠየቅና ለመጋፈጥ የሚችልም ኃይል ስለሌለ ፍዳውን እያየ ለዝንተ-ዓለም ይኖራል ማለት ነው።
የዘመናዊነት መስፋፋት፣ አተረጓጎሙና ጠንቁ!
አብዛኛዎቻችን በፖለቲካ ውስጥ እንሳተፋለን የምንል ሁሉ የቱን ያህል የዘመናዊነት አስተሳሰብ ከሚለው ፅንሰ-ሃሳብ ጋር የተዋወቅን፣ ወይም በነገሩ ላይ በቂ ምርምር እንዳደረግን ለማወቅ በጣም አስቸጋሪ ነው። በተለይም እንደኛ ባለው ሁሉም ከውጭ የመጣን ነገር ዝም ብለን(uncritical) ከመቀበልና ተግባራዊ ከማድረግ በስተቀር የነገሮችን አፈላለቅ፣ አመጣጥና መስፋፋት ትችታዊ በሆነ መልክ የመመራመር ፍላጎት የሌለን ዝም ብለን ከመጠቀም ወይም ዘመናዊ ለመምሰል በስተቀር ዘመናዊነት ማለት ምን ማለት ነው ብለን የምንጠይቅ እምብዛም ነን። ስንቶቻችን የዛሬውን በሳይንስና በቴክኖሎጂ የሚገለጸውን ዓለም ሁለት መቶና ሶስት መቶ ዓመት ከነበረው ሁኔታ ጋር በማወዳደር ይህ ዐይነቱ ዕድገት እንዴት ሊመጣ ቻለ ብለን የምንጠቅይን ያለን አይመስለኝም። ይህ ዐይነቱ ችግር የእኛ ኢትዮጵያውያን ችግር ብቻ ሳይሆን እዚህ ሰለጠነ የሚባለውም በአውሮፓ ምድርና በአሜሪካ አገር ውስጥ የተስፋፋ ነው። ህሉም የቴክኖሎጂን ውጤት ከመጠቀምና ከመነዳት ይህን ያህልም አይጨነቅም። ወደ አገራችን ስንመጣ በየዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የፍልስፍና፣ የሳይኮሎጂና የሶስዮሎጂ ትምህርቶች ቢሰጡም እነዚህን ነገሮች ባለፉት ሰባና ሰማንያ ዓመታት በአገራችን ምድር ዘመናዊነት የሚባለው ነገር ሰተት ብሎ ከገባ ጀምሮ ያበረከተውን አስተዋፅዖና፣ በታዳጊውና በህዝባችን ላይ ያሳደረውን አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደመመርመሪያ መሳሪያ በመጠቀም በግልጽ የሚታዩ ወንጀሎች፣ መንግስት ነን በሚሉት ላይ በተለይም ፖሊሲ ነክ የሆኑና ይሁንና በአብዛኛው ጎናቸው አገርንና ህብረተሰብን የሚጎዱና የሚያዝረከርኩ፣ ዱርዬነትን የሚያመርቱ፣ የአካባቢ መቆሸሽን የሚያስፋፉና ህብረተሰባችንም እንደማህበረሰብ ሳይሆን ተናጣጥሎ እንዲኖር የሚያደርጉትንና፣ በአጠቃላይ ሲታይ ህዝባዊ ሀብት እንዲመረት ይህን ያህልም አስተዋፅዖ የማያበረክቱትን፣ እንዲያም ሲል ለሳይንስና ለቴክኖሎጂ ዕድገት ዕንቅፋት የሚሆነውን የገዢውን መደብ ፖሊሲን በመተንተንና በመተቸት ዕርማት ሲደረግ በፍጹም አይታይም። ውጭ አገር ያለውና ተማርኩም የሚለው ኢትዮጵያዊም በሳይንስና በቴክኖሎጂ ዓለም ውስጥ ቢኖርም፣ በየአገሮች ውስጥ ክሪቲካል የሆነ የሳይንስ ኮሙኒቲ ቢኖርም ከእነዚህ ጋር በመተዋወቅና በየጊዜው የሚፃፉ መጽሀፎችንና የሚታተሙ ጆርናሎችን በማንበብ ክርቲካል አስተሳሰብ ሲያዳብርና የሁለ-ገብ ዕድገት አንቀሳቃሽ ኃይል ሆኖ ሲታገል በፍጹም አይታይም። ማለት የሚቻለው አብዛኛው ኤሊት ነኝ ባይ በአሜሪካን የፖለቲካ፣ የሚሊተሪና የኢንዱስትሪ ኤሊት አስተሳሰብ ውስጥ በመካተትና፣ የዓለምን ሁኔታ በጥቁርና በነጭ በመሳል የታዛዥነትን መንፈስ ያዳበረ የሚመስል ነው። በሌላ አነጋገር፣ ራሱን ለማግኘትና፣ ራሱን ነፃ በማውጣትና ተራማጅ አስተሳሰብ በማዳበር ለሌላው ምስኪን ህዝብ አርአያ ለመሆን የሚችልና የሚጣደፍም አይደለም። ባጭሩ ባለው ቴክኖክራሲያዊ አስተሳሰብ በመዝናናትና ስልጣን ላይ ለመውጣት በመቋመጥ ሰፊውን ህዝብ የሚጠቅም ሁለ-ገብ ዕድገት ተግባራዊ እንዳይሆን ሳያውቀው የሚስራ ነው ማለት ይቻላል። ከዚህ ሁኔታ ስንነሳ እንደ ሌሎች አገሮች ኤሊቶች ሁሉ ሳያውቀው ሰይጣናዊ መንፈስ በማዳበርና እንደ አጋጣሚ ስልጣን ላይ ቢወጣ የውጭ ኃይልን ዓላማ ተግባራዊ ከማድረግ በስተቀር የሚፈይደው ሌላ ነገር የለም። ከአንዳንድ ከሶስተኛው ዓለም አገሮች ምሁራን፣ ይሁንና ክሪቲካል አመለካከት ካላቸው ጋር ተቀመጬ ሳወራ የማገኘው መልስ ስልጣን ላይ ያሉት አገዛዞችና ምሁራን ነን ባዮችም፣ በጣም ጥቂቱ ካልሆነ በስተቀር አገራቸውንና ህዝቦቻቸውን የሚጎዱ ስራዎች እንደሚሰሩ ነው። ወደ ኢትዮጵያችን ስንመጣ አዲሱን የኦሮሞ ኤሊት ለማስተናገድ የተሰራው ስማርት ከተማ የሚባለው፣ በመሰረቱ ሰይጣናዊ ወይም የመባለጊያ ከተማ፣ ካለምንም የከተማ ዕቅድና ሁሉኑም ነገር ሳያካትቱ በየቦታው የሚሰሩ ህንፃዎችና፣ ተሰርተውም የሚገዛቸውና የሚከራያቸው ጠፍቶ ተንቀዋለው የሚታዩት ህንፃዎች፣ አሁን ደግሞ በብዙ መቶ ጋሻ መሬት ላይ ሊሰራ የታቀደው ወደ አስር ቢሊዮን ዶላር ያወጣል የሚባለው በአፍሪካ ውስጥ ተወዳዳሪነት የማይገኝለት የአውሮፕላን ጣቢያ፣ እነዚህ ሁሉ የሚያረጋግጡት ዘመናዊነት የሚባለው ነገር የቱን ያህል በተሳሳተ መልክ እንደተተረጎመና አገራችንም መንፈሱ ሰይጣናዊ በሆነ ኤሊት እንደምትገዛና የታሪክም ወንጀል እንደሚስራ ነው። ባጭሩ እንደነዚህ ዐይነት በአፍሪካ ውስጥ ተወዳዳሪ የማይገኝለት የአውሮፕላን ጣቢያ ከተሰራና ተግባር ላይ የሚውል ከሆነ የሚጨርሰውን ሀብት ወይም ሪሶርስን መገመቱ ከባድ አይሆንም። በሌላ አነጋገር፣ የአውሮፕላን ጣቢያ በራሱ ምርታማ መስክ ስላልሆነ በእርሻውም መስክ የሚመረቱትን ሰብሎችና ፍራፍሬዎች፣ እንዲሁም በኢንዱስትሪው መስክ የሚመረተውንና በአገልግሎት፣ ለምሳሌ እንደውሃና የመብራት ኃይል የሚቀርበውን በመጠቀምና በመምጠት በህብረተሰባችን ውስጥ፣ በተለይም በአዲስ አበባና በአካባቢው ውስጥ ከፍተኛ መዛባትን እንደሚያስከትል ግልጽ ነው። ባጭሩ ግዙፍ ሆኖ የሚሰራው የአውሮፕላን ጣቢያው ከህዝባችን ዕድገት ጋር የሚጣጣምና ከድህነትም እንዲላቀቅ የሚያደርገው አይደለም ማለት ነው። ይህ ዐይነቱ ግዙፍ የአውሮፕላን ጣቢያ በዚያች ደሃ አገር ውስጥ በሰይጣናዊ መንፈስ የሚመራው የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የሌሎችም ኤሊት ነን ባዮች መገለጫ ብቻ ነው። በሌላ ውገን ግን ቢታሰብበት በአስር ቢሊዮን ዶላር በብዙ ሺሆች የሚቆጠሩ የመጠነኛና የማዕከለኛ ኢንዱስትሪዎችን በመትከልና የእርሻውንም ዘርፍ በማሻሻል አጠቃላይና ሰፊውን ህዝብ የሚጠቅም ሀብት መፍጠር በተቻለ ነበር። በዚያው መጠንም ለብዙ ሚሊዮን የስራ ፈላጊ ህዝብ የስራ ዕድል መክፈት ይቻል ነበር። ባጭሩ ይህ ዐይነቱ ተግባር የሚፈፀመው ባልተገለፀላቸው ወይም ንቃታ-ህሊናቸው ባልዳበረና የዘመናዊነትን አስተሳሰብ በተሳሳተ መልክ በሚተረጉሙ ኤሊት ነን ባዮች አማካይነት ነው።
ዘመናዊነት የሚባለውን አስተሳሰብ አስመልክቶ በጥንቱ ዘመን በግሪክ አገር በእነ ሶክራተስና በእነ ፕሌቶንና እንዲሁም በተቀሩት የግሪክ ፈላስፋዎች ዘመን በመሀከላቸው ስምምነት ነበር። አንድ ህዝብ ካለበት አስቀያሚ ሁኔታ እንዲላቀቅ ከተፈለገ የግዴታ ኑሮው መሻሻል እንዳለበትና ለዚህም የስራ-ክፍፍል መዳበር አስፈላጊ እንደሆነ ግንዛቤ ነበር። በእነዚህ ፈላስፋዎች ዕምነት በአንድ አገር ውስጥ የተሰተካከለና ፍትሃዊነትን የተላበሰ ዕድገት እንዲመጣ ከተፈለገ የአዕምሮ ወይም የመንፈስ ዘመናዊነት ወይም ተሃድሶ መደረግ እንዳለበት፣ በተለይም የፖለቲካ ኤሊቱ መንፈስም ጦርነትን በሚያስቀድም ሳይሆን ስልጣኔን በሚያስቀድም አስተሳሰብ ወይም ሳይንሳዊ ዕውቀት መቀረፅ እንዳለበት ስምምነት ነበረ። ለድዚህ ደግሞ ልጆች የግዴታ ከልጅነታቸው ጀምረው መንፈስን ብሩህና ሰብአዊ ከሚያደርግ፣ እንዲሁም ሀቀኛውን መንገድ ከሚያሲዝ ሳይንሳዊ ዕውቀት ጋር መተዋወቅ አለባቸው፤ ጭንቅላታቸው በሚገባ መኮትኮት አለበት። ስልጣንም ላይ የሚወጡ፡የተመረጡ መሆን አለባቸው። በሌላ አነጋገር፣ በአንድ አገር ውስጥ በልዩ ልዩ ነገሮች የሚገለጽ የኑሮ መሻሻል ተግባራዊ እንዲሆን ከተፈለገ እያንዳንዱ ልጅ ከገረጀፈ በኋላ ሳይሆን ከህፃንነቱ ጀምሮ ሰይጣናዊ በማያደርግ ዕውቀት መንፈሱ መታነፅ አለበት። ለዚህም ነው ፍልስፍና፣ የተፈጥሮ ሳይንስ፣ ማቲማቲክስና ሌሎች ነገሮች በሙሉ ሊፈጠሩ የቻሉት። የፍልስፍና፣ የሳይንስንና የቴክኖሎጂን ዕድገት ስንመለከት እነዚህ ሁሉ ሊፈጠሩ፣ ከተማዎች በአማረ መልክ ሊገነቡ የቻሉት፣ ስዓሊዎች ሊፈጠሩና ቆንጆ ቆንጆ ነገሮች ሊሳሉ የቻሉት፣ እንደ ክላሲካል ሙዚቃ የመሳሰሉት መንፈስን ሊያድሱ የሚችሉ ሙዚቃዎች ሊደረሱ ወይም ሊገጠሙ የቻሉት፣ ድራማና ቲአርት ሊደረሱና ሊሰሩ የቻሉት ቅዱሳዊ መንፈስ ባላቸው ወይም መንፈሳቸው ሰይጣናዊ ባልሆነ መልክ ባልተቀረፀ እግዚአብሄር ከላይ ሆኖ ዱብ አድርጎ እንደጣላቸው በተፈጠሩ ስዎች አማካይነት ነው።
በአጠቃላይ ሲታይ ዘመናዊነትን አስመልክቶ በእነ ፕሌቶ ዘመንም በፕሌቶና በተከታዮቹ በአንድ በኩልና የገዢዎችን መደብ የበላይነት በሚያስተጋቡ ሶፊስቶች በሚባሉ ሙልጭልጭ አስተሳሰብ ባላቸው መሀከል የጦፈ ክርክር ነበር። በኋላም ላይ የኤፒኩረያንን መስመር፣ በተለይም የራስን ጥቅም ማስቀደም ወይም ስግብግነትን በሚያስቀድመውና ጭንቅላትን በመጥፎ አስተሳሰብ በሚቀርፀውና፣ በሞራልና በስነ-ምግባር ላይ ባተኮረው ስቶይኮች ተብሎ በሚታወቀው ጭንቅላትን በጥሩ አስተሳሰብ በሚቀርፀው ፍልስፍናዊ አስተሳሰብ መሀከል የጦፈ ክርክር ተካሂዷል ማለት ይቻላል።፡ ይህም የሚያመለክተው ከግሪክ ፍልስፋናና ስልጣኔ አንስቶ የመንፈስን በመጥፎና በጥሩ መልክ መቀረጽ ከፍተኛ ክርክር ይካሂድ ነበር። ይህ ዐይነቱ አስተሳሰብ በካቶሊክ ሃይማኖት የበላይነት በማዕከለኛው ክፍለ-ዘመን ቢዳፈንም የመንፈስ ተሃድሶ የሚባለው እንቅስቃሴ ከተቀጣጠለ ክ15ኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ የሰውን ልጅ፣ በተለይም የገዢ መደቦችን መንፈስ በቀና ወይም በጥሩ መልክ ለመቅረጽ ከፍተኛ ትግል ተካሂዷል። ስለሆነም ነው ከ15ኛው ክፈለ-ዘመን ጀምሮ የሰብአዊነት ትምህርትቤቶች በመስፋፋት አዳዲስ ፈላስፋዎችን ማፍለቅ የተቻለው። ስለሆነም ነው ከ15ኛው ክፈለ-ዘመን ጀምሮ እስከ 19ኛው ክፍለ-ዘመን ድረስ ጭንቅላትን ሊገነቡ የሚችሉ ሳይንሳዊ ዕውቀቶችና ፍልስፍና፣ እንዲሁም ልዩ ልዩ ዕውቀቶች ሊዳብሩ የቻሉት። ይሁንና ግን ካፒታሊዝም እያሸነፈ ሲመጣ የሰብአዊነት አስተሳሰብ እየተደመሰሰና የጦርነትን መንፈስ የሚያጎለምስና ስግብግብነትን የሚያስቀድም መንፈስ በመስፋፋት በአውሮፓ ምድር ውስጥ በቀላሉ መቋጫ ሊያገኙ የማይችሉ ጦርነቶች ሊከሰቱ ቻሉ። የባርያ ንግድና የቅኝ-ግዛት አስተዳደር ወይም ሌላ መልክ ያላቸውን ህዝቦችን እንደ ዝቅተኛና እንደ ተበዝባዥ አድርጎ የመቁጠር መንፈስ፣ እንዲሁም የአንደኛውና የሁለተኛው ዓለም ጦርነቶች የሰይጣናዊ መንፈስ በኃያልነት መውጣት መገለጫዎችና ማረጋገጫዎች ናቸው። ፋሺዝምም ራሱ የሰይጣናዊ መንፈስ መዳበርና በአሸናፊነት መውጣት መገለጫ ነው ማለት ይቻላል። በሌላ አነጋገር፣ በተለይም ካፒታሊዝም ቴክኖሎጂያዊ ምጥቅተን ለማምጣት አመቺ ሁኔታዎችን ቢፈጥርም በዚያው መጠንም፣ በተለይም የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም የበላይነትን ከተቀዳጀ ከ1945 ዓ.ም ጀምሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሰይጣናዊና ጦርነትን የሚያስቀድም መንፈስ በማስፋፋት የገዢ መደቦችም በዚህ ዐይነቱ ሰይጣናዊ አስተሳሰብ በመጠመድ ሰይጣናዊ አስተሳሰብ የፖለቲካ፣ የሚሊተሪና የስለላ ድርጅቶች፣ እንዲሁም በኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚክስ የሰለጠኑ ቴክኖክራቶችና ቢሮክራቶች መገለጫ በመሆን በየአገሮች ውስጥ የተስተካከለና ሰፊውን ህዝብ ለመጥቀም የሚችል ህብረተስብአዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት እንዳይተገበር መሰናክል መፍጠር ተቻለ። በተለይም በከተማ ግንባታ፣ በኢኮኖሚክስ ትምህርትና በሚሊተሪና በስለላ ውስጥ ያለውን የትምህርት አስጣጥ ለተከታተለ የኢኮኖሚክስ ሳይንስ የሚባለው፣ ሌሎች የኢኮኖሚክስ ዕውቀቶችን እየረገጠ በአንድ መልክ ብቻ የሚሰጠው አስተሳሰብ በሙሉ በአገሮች ውስጥ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተና ረጋ ባለ መልክ ህብረተሰቦችን ሁለ-ገብና ጥበባዊ በሆነ መልክ ለማሳደግ እንዳይቻል ለማድረግ ተብሎ የረቀቀና የታዳጊውን ትውልድ ጭንቅላት ያጨለመና ትዕቢተኛ ያደረገው ነው። ከዚህ ሁኔታ ስንነሳ ከ1945 ዓ.ም በኋላ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተስፋፋውን የትምህርት አሰጣጥ፣ የሚሊተሪና የስለላ አሰለጣጠን፣ የቴክኖክራቶችና የቢሮክራቶች እንደ አሸን መፍለቅ…ወዘተ. እነዚህ ሁሉ ከየአገሩ ዕድገትና ከጠቅላላው ህዝብ አንፃር ታስበውና ታቅደው የተነደፉ ሳይሆኑ በቀጥታ ከአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም የተኮረጁና የእሱንም ጥቅም የሚያስቀድሙ ናቸው።
ስለሆነም ባለፉት ሃምሳ ዓመታት በአገራችን ምድር የተፈጠረውን ሁኔታ፣ ለምሳሌ ያልተስተካከለ ዕድገት፣ የተትረፈረፈ የጥሬ-ሀብት እያለ የድሀነት መስፋፋት፣ የከተማዎች በተዝረከረከ መልክ መገንባት፣ በደሃና በሀብታም መሀከል ያለው ልዩነት መስፋት፣ የትዕቢተኝነት መንፈስ ማየልና ሰፊውን ህዝብ መናቅ፣ እንዲያም ሲል የነጭ አሽከር ለመሆን ሽር ጉድ የሚባለውን ሁኔታ ስንመለከት እነዚህ ሁሉ መንፈስን ከሚያድሱና የሰውን ልጅ እንደሰው እንዲያስብ ከማድረግ ጋር የተያያዙ ሳይሆኑ በተለይም የኤሊቱ መንፈስ በሰይጣናዊ መንፈስ እንዲቀረጽና አገርንም ወደ ጦርነት አውድማነት እንዲለውጠው ከዳባረው ሰይጣናዊ አስተሳሰብ ጋር የሚያያዝ ነው። በአብዮቱ ወቅትም የተፈጠረውን ዘግናኝ ሁኔታ ስንመለከት ድርጊቱ ሊያያዝ የሚችለው ከአሜሪካን የዘመናዊነት፣ ይሁንና ሰይጣናዊ አስተሳሰብን ከሚያስፋፋው የተኮላሸ የዘመናዊነት አስተሳሰብ ጋር በቀጥታ የሚያያዝ ነው። በተለይም እንደኛ ባለው አገር ውስጥ ከልጅነት ጀምሮ ጭንቅላትን በጥሩ መልክ ሊቀርጹ የማይችሉ ነገሮች ወይም የትምህርት ዐይነቶች ባልተስፋፉበት አገር ውስጥ ኋላ ላይ የተመለክትነውና እስካሁንም ድረስ አልላቀቀንም ያለው የጨለመ ወይም እልህ የተሞላበት አስተሳሰብ ከሰይጣናዊ መንፈስ መዳበርና መስፋፋት ጋር የሚያያዝ ነው። ይህም ጉዳይ በቀጥታ ግራም በለው ቀኝ ኤሊት ነኝ ከሚለው ጋር የሚያያዝ ነው። ይህም ማለት በአገራችን ምድር የተፈጠሩትና የሚፈጠሩት አስቀያሚ ስራዎችና ጦርነቶች በሙሉ በአጠቃላይ ሲታይ ኤሊት ነኝ የሚለው ኃይል ሳያወጣ ሳያወርድ በደመ-ነፍስ በመመራት ተግባራዊ ያደረገውና የሚያደርገው ነው። በተለይም ወያኔ ስልጣን ከያዘ ጀምሮና ካለፉት ስምንት ዓመታ ጀምሮም በፋሺሽቱ የአቢይ አህመድ የአገዛዝ ዘመን ሰይጣናዊ አስተሳሰብ በከፍተኛ ደረጃ በመስፋፋት ህዝባችንን፣ በተለይም አማራውን ወገናችንን ፍዳውን እያሳየው ነው። ከዚህም በላይ የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ መሆን ከጀመረ ከዛሬ ሰላሳ ሶስት ዓመት ጀምሮ ሰይጣናዊ መነፈስ በከፍተኛ ደረጃ መስፋፋት ችሏል። ይህ ፖሊሲ የአገዛዙ ዶክትሪን በመሆን ጥቂቶችን ማደለቢያና ማባለጊያ በመሆን፤ በዚያውም መጠንም ሰፊውን ህዝብ የሚያደኸይና አገርንም የሚያፈራርስ ለመሆን የበቃ ነው። የሌሎች አገሮችንም ሁኔታ ስንመለከት፣ የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ ያደረጉ አገሮች በሙሉ ቺሌ፣ አርጀቲናና ብራዚል፣ እንዲሁም ሌሎች የደቡብና የማዕከለኛው አሜሪካ አገሮች ወደ ባሰ አረመኔያዊነት ለመለወጥና ሀብት ዘራፊና አዘራፊ ለመሆን የበቁት ይህንን ፖሊሲ የመንግስቶቻቸው ዋናው መመሪያ አድርገው መያዛቸው ነው። ይህ ዐይነቱ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ከአሜሪካ ረቆ የመጣ ሲሆን በቀጥታ የፋይናንስ ኦሊጋርኪውን መደብ ጥቅም የሚያስጠብቅና ሀብትም በቀጥታ ከእነዚህ አገሮች ወደ ታላቁ አሜሪካ በተለያዩ መሳሪያዎች እንዲሸሽ የሚያድርግ ነው። ስለሆነም በየአገሮች ውስጥ የተፈጥሮንና የህብረተሰብን ህግ የሚፃረሩ ነገሮች በመፈጠር የፖለቲካ ኤሊቱ ይህን ድርጊት እንደጥሩ ነገር መስሎት ተዝናንቶ የሚኖርበትን ሁኔታ እንመለከታለን።
ለአገራችን የዛሬው ምስቅልቅል ሁኔታ የግራ ፖለቲካ በመስፋፋቱ ሳይሆን ከአሜሪካን አገር የመጣው የዘመናዊነት ፖሊሲ ተግባራዊ በመደረጉ ነው!!
አፄ ኃይለስላሴ ከእንግሊዝ አገር ከስደት ከተመለሱ በኋላ፣ በተለይም ከ1950ዎቹ መጀመሪያ ጀምሮ ተግባራዊ የሆነውን የኢኮኖሚ ፖሊሲ ጋር ስንቶቻችን የተዋወቅን እንደሆን ለማወቅ አስቸጋሪ ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን በተለይም ከ1960ዎቹ መጀመሪያ ጀምሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ፣ በተለይም የታወቁ የሶስተኛው ዓለም አገሮች ምሁራንና አንዳንድ የአውሮፓና የአሜሪካን ምሁራን ስለ ኢኮኖሚ ዕድገት፣ በተለይም በሶስተኛው ዓለም አገሮች ውስጥ ባልተስተካከለ መልክ(Unequal Development) ከሚገለፀው የኢኮኖሚ ሁኔታ ጋር የተዋወቅን መሆናችንን ለማወቅ በጣም አስቸጋሪ ነው። ማለት የሚቻለው አብዛኛዎቻችን በዓለም አቀፍ ደረጃ በተስፋፋው የኒዎ-ክላሲካል ወይም የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚክስ አስተሳሰብ የሰለጠን ስለሆንና፣ ስለ ሁለ-ገብ ዕድገትና በአንድ አገር ውስጥ የሚኖርን ሰፊ ህዝብ ከድህነት በምን መልክ ማውጣት ይቻላል? በሚለው ላይ ያልሰለጠንና የማናውቅም ስለሆን አመለካክታችን ውስንና በተለይም ከአገራችን ሁኔታ ብቻ ስንነሳ አስተሳሰባችን ብሄራዊ ሳይሆን የአሜሪካንን ኢምፔሪያሊዝምን ጥቅም የሚያስተጋባ ነው ማለት ይቻላል። በተለይም አብዛኛው ኢኮኖሚስት ነኝ ባይ በኒዎ-ክላሲካል የኢኮኖሚክስ ትምህርት የሰለጠነ በመሆኑ በአውሮፓ ምድር ውስጥ ከአስራ-ስድስተኛው፣ በተለይም የእነ አዳም ስሚዝ የክላሲካል ኢኮኖሚክስ ጽሁፍ(The Wealth of Nations) መስፋፋትና፣ በጊዜው ኋላ-ቀር ከሆኑ እንደ ጀርመን ከመሳሰሉ አገሮች ምሁራን የፈለቀውን የተሟላና በማኑፋክቸሪንግ ላይ የተመሰረተ ሁለ-ገብ ዕድገትን አስመልክቶ የተዋወቀ ኢትዮጵያዊ የኢኮኖሚክስ ምሁር ስለሌለ ከ1950ዎቹ ዓመታት መጀመሪያ ጀምሮ በአገራችን ምድርና በሌሎችም የሶስተኛው ዓለም አገሮች የተስፋፋውን የተዛባና በአንድ ወይም በሁለት ወደ ውጭ በሚላኩ የኤክስፖርት ምርቶች ላይ ጥገኛ ሆኖ እንዲቀር የሚያደርገውን የኢኮኖሚ ፖሊሲና መዘዙን ሊከታተል የቻለ የለም፤ በፍጹም ፍላጎትም ያለው በጣት የሚቆጠር ማለት ይቻላል። ለማለት የምፈልገው የኢኮኖሚ ዕድገትን አስመልክቶ ከ1950ዎቹ ዓመታት መጀመሪያ ጀምሮ ተግባራዊ የሆነውንና በትምህርት ደረጃ በተዛባ፣ ወይም ጭንቅላትን በሚገባ ከማይቀርጸው ጋር በመተዋወቃችንና ይህንን አሜን ብለን በመቀበላችንና በማምለካችን የግዴታ ጭንቅላታችንን ለሌሎች አማራጭ ለሆኑና፣ ይሁንና ደግሞ የተስተካከለና ጤናማ ዕድገትን ለማምጣት ለሚችለው ከሳይንስና ከቴክኖሎጂ ዕውቀት ጋር ከሚጣመረው ሁለ-ገብ የሆነ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍት ለማድረግ አልቻልንም። እንዲያውም ሌሎችና አንድን ሰፊ ህዝብ ከድህነት ሊያላቅቅ የሚችለውን ሁለ-ገብ የኢኮኖሚክስ ትምህርት የሙጥኝ አድርገን በመያዝና በማስፋፋት ሳናውቀው ፀረ-ስልጣኔ ስራ እየሰራን ነው። ስለሆነም አብዛኛዎቻችን ሶፊስትያዊ አስተሳሰብን በማደበርና በማስፋፋት በአንድ አገር ውስጥ የሚኖር ህዝብ ከድህነትና ከኋላ-ቀርነት እንዳይወጣ አድረገናል፤ እያደረግንም ነው። ይህ በራሱ የሰይጣናዊ መንፈስ መገለጫና አንድ ህዝብ በዘለዓለማዊ ውዝግብ እንዲኖር የሚያደርግ አደገኛ አካሄድ ነው።
ነገሩን የበለጠ ግልጽ ለማድረግ በአገራችን ምድር በተለይም አብዮቱ ፈነዳ ከተባለበት እ.እ.አ ከ1966 ዓ.ም ጀምሮ የተፈጠረው ምስቅልቅል ሁኔታ፣ ቀደም ብሎ የተፈጠረው የተማሪው እንቅስቃሴና፣ እንዲያም ሲል በጥቂት መፈክሮች ዙሪያ ብቻ በመሰለፍና ይህንን ማስተጋባት፣ የብሄረሰብ እንቅስቃሴዎች የሚባሉትም መፈጠርና መስፋፋት፣ እንዲሁም መደማመጥና ሎጂካዊ በሆነ መልክ ለመወያየት አለመቻል፣ በተጨማሪም ከህብረተሰብ አገነባብ ታሪክ ጋር በመተዋወቅ በዚህ ዙሪያ የረጋ ውይይትና ክርክር አለማድረግ ሊሳበብ የሚችለው የግራ አስተሳሰብ ስለተስፋፋ ሳይሆን ቀደም ብሎ ከ1950ዎቹ መጀመሪያ ጀምሮ ከተስፋፋው የመሰረተ-ትምህርት፣ የመለስተኛና የከፍተኛ ትምህርትና፣ ዩኒቨርሲቲ ውስጥም ይሰጥ ከነበረው ትምህርት ጋር በቀጥታ የሚያያዝ ነው። ሳይኮሎጂስቶችና የኮግኒቲቭ ሳይንስ ተመራማሪዎች የሚስማሙበት አንድ ነገር አለ። ይኸውም የአያንዳንዱ ሰው ጭንቅላት መንፈስ ከልጅነቱ ጀምሮ፣ ከቤተሰብ የአኗኗርና የአስተሳሰብ፣ ከአካባቢና፣ ከኪንደር ጋርተንና በየትምህርት ቤቶች ከሚሰጡት ትምህርቶች ጋር በቀጥታ የሚያያዝ ስለሆነ በአንድ ወቅት በሚከሰት ሁኔታ ያ እየዳበረ የመጣ ጭንቅላት ሊለወጥ በፍጹም አይችልም። ይሁንና ይህ ዐይነቱ በመጥፎ የትምህርት አስተሳሰብና አስተዳደግ የዳበረ ጭንቅላት አደገኛ ለሆነ አስተሳሰቦች በቀላሉ ክፍት ሊሆን ይችላል። ይህንን ጉዳይ በሂትለር የአገዛዝ ዘመን በጀርመን ምድርና፣ አሁን ደግሞ በአሜሪካ ምድር የምንመለከተው ሀቅ ነው። በጣም ጥቂቱ ካልሆነ በስተቀር ረጋ ብሎ የነገሮችን ሁኔታ የሚያጤንና የለሰለሰ አካሄድ የሚከተል በጣም ጥቂቱ ብቻ ነው ማለት ይቻላል። ከዚህም ባሻገር የአስተማሪዎች አስተሳሰብና ከተማሪዎቻቸ አግር ያላቸው ግኑኝነት በሚያድጉ ህፃናት ላይ በመጥፎም ሆነ በጥሩ መልክ ሊቀረጹ ይችላል። ይህም ማለት የቅዱሳዊና የሰይጣናዊ መንፈስ መዳበር የሚጀምረው ከልጅነት ጀምሮ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ነው። በተለይም ስለፋሺዝም በጥልቀት ምርምር ያደረጉ የሚነግሩን በጀርመን ምድር ፋሺዥም ስሊስፋፋ የቻለው በአንድ ዕብድ ሰው አማካይነት ብቻ ሳይሆነ ይህንን የሚቀበልና የሚያስተጋባ በፕረሽያ ዘመን የተዋቀረ በጣም ጨቋኝ የነበረ ፓትሪያሪካል የሆነ የወታደርና የስለላ አወቃቀር ቀደም ብሎ በመዘርጋቱ ነው። ይህ ሁኔታና በራሱ የሂትለር አስተዳደግና በተከታዮችም ዘንድ የነበረው ሰይጣናዊ ወይም ይሁዲዎችን የመጥላት መንፈስ ተደምሮበት በጀርመን ምድር በቀላሉ ፋሺዝም ሊስፋፋና በህዝብም ዘንድ ተቀባይነትን ሊያገኝ ቻለ። በሌላ ወገን ደግሞ በጀርመን ምድር ከ16ኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ ጭንቅላትን የሚያዳብር ፍልስፍናዊና ሳይንሳዊ አስተሳሰብ ሊስፋፋ እንደቻለ የሚታወቅ ነገር ነው። ሰብአዊነትን የሚሰብኩና የሚያስተምሩ ትምህርት ቤቶችም በየቦታው ተዘርግተው ነበር። ስለሆነም ነው እንደነ ላይብኒዝ፣ ካንትና ሄግል፣ ኒቸና እንዲሁም ማርክስና ኤንገልስ ሊፈጠሩ የቻሉትና ያንን የመሰለ ዕውቀት ሊፈጥሩና ሊያስፋፉ የቻሉት። ይሁንና የካፒታሊዝም አፀናነስና አስተዳደግ ጤናማ በሆነ መልክ ባለመሆኑ የእነ ካንትንና የእነ ሄገልን ቅዱሳዊ አስተሳበ ለማስፋፋትና የመንግስቱም ዶክትሪን ለማድረግ አልተቻለም። ይህም ማለት የፍልስፍና አስተሳሰብ መዳበር፣ የኢንዱስትሪ አብዮት መካሄድና የከተማዎች ግንባታ የግዴታ ሰብአዊነትንና መቻቻልን ለማደበር ባለመቻሉ ለጀርመን ዕድገት ከፈተኛ አስተዋፅዖ ያበረከቱ እንደ ጠላት እየታደኑ በአሰቃቂ ሁኔታ ሊገደሉ ችለዋል።
ወደ ኢትዮጵያችን ስንመጣ የዘመናዊ ትምህርት ወደ አገራችን ሲገባ ዝም ብሎ ገባ እንጅ በምን መልክ የታዳጊውን መንፈስና አስተሳስብ ሊቀርጽ ይችላል? ተብሎ ሰፊ ጥናት በማድረግና በመከራከር አልነበረም። ዝም ብሎ ብቻ ዘመናዊነት የሚባለው አስተሳሰብ እንደ ስልት ከመወሰዱ በስተቀር በአጠቃላይ ሲታይ የሰፊውን ህዝብ መንፈስ ከማደስና ሁለ-ገብ ዕድገትን ሊያመጣ ይችላል ብሎ በማውጣትና በማውረድ አልነበረም ተግባራዊ ለመሆን የቻለው። ስለሆነም ይህ ዐይነቱ የዘመናዊነት ፖሊሲ ነው በአገራችን ምድር ያልተስተካከለ ዕድገትን ሊፈጥር የቻለው። ይህን ዐይነቱን የተዛባ የዘመናዊነት የኢኮኖሚና የትምህርት ፖሊሲ በሚገባ ለማጥናት ያልቻለው የተማሪው እንቅስቃሴ የአገራችንን ሁኔታ ወደ ጥቂት መፈክሮች በመለወጥ የግብግብ ሁኔታን ለመፍጠር ቻለ። በኋላ ላይ የዶክትሬት ስራዬን ስጽፍና ምርምር ሳደርግ በተማሪው እንቅስቃሴ የሚወጡ መጽሄቶችን ሳገላብጥ በተለይም የህብረተሰብ አወቃወርና የፖለቲካ ኢኮኖሚክስን ጉዳይ ላይ ምንም ዐይነት ጥናት እንዳልተካሄደ ነው ለማወቅ የቻልኩት። የተማሪው እንቅስቃሴም እየዳበረ ሊመጣ የቻለው በጀርመን ምድርና በአንዳንድ የአውሮፓ አገሮች፣ በፈረንሳይ ምድር በጊዜው የማርክሲዝምና የሌኒዝም መጽሀፎች፣ እንዲያም ሲል የህብረተሰብን ዕድገትን ከሌላ አንፃር የተረጎሙና አዳዲስ የህብረተሰብ ኃይሎችን ሁኔታ ጠጋ ብለው የተመራመሩ እነ ማክስቬበርና ዱርክሃይም ከመሳሰሉ የሶስዮሎጂ ዕውቀቶች በተስፋፉበት ዘመን ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን ጠለቅ ያለ ምርምር ያደረጉ ምሁራን አንዳንድ የአውሮፓ አገሮች ከፊዩዳሊዝም ወደ ካፒታሊዝም እንዴት ለመሸጋገር ቻሉ? እየተባለ በሚጠናበትና ክርክር በሚደረግበት ዘመን ነው። ስለሆነም ከእነዚህና በአጠቃላይ ሲታይ ከግሪክ ስልጣኔ ጋር ለመተዋወቅ ያልቻለው የተማሪው እንቅስቃሴና፣ ከማንኛውም ዕውቀት የራቀው የብሄረሰብ እንቅስቃሴ ጭንቅላታቸውን ለማዳበርና የህብረተሰብን ዕድገት ህግ በስርዓትና ረጋ ባለ መልክ ለማጥናት አልቻሉም። ጭንቅላታቸውን ለማንኛውም ቅዱሳዊ ዕውቀት ዝግ በማድረጋቸው ከሎጂካዊ ክርክር ይልቅ አመጽንና ግድያን ለማስቀደም ቻሉ። ይህ ዐይነቱ ሁኔታ የግዴታ ሰይጣናዊ መንፈስ እንዲስፋፋና አገራችንም የጦር አውድማ እንድትሆን አስቻለ። እዚህ ላይ እንዲታወቅልኝ የምፈልገው ነገር በተማሪው እንቅስቃሴ ከተሳተፉት ውስጥ በአመራር ደራጃ የነበሩ አርቆ የማሰብ ኃይል እንደነበራቸውና በዕውቀትም እንደሚያምኑ ነው። ችግሩ ግን ሁል ጊዜ ጥሩ አስተሳሰብ ያለው ሳይሆን ቸኳይ የሆነና ሰይጣናዊ አስተሳሰብ ያለው በአሸናፊነት ስለሚወጣ አንድ ጥሩ አስተሳሰብ-ለምሳሌ የሶሻሊስት አስተሳሰብ- በመጥፎ ነገር ይተረጎማል። የተደረገውን ድርጊት መሪ ነን ከሚሉትና ከአስተዳደጋቸው ጋር ከማያያዝ ይልቅ አንድን ሳይንሳዊ አስተሳሰብ እንዳለ በመኮነን ይህን ሁሉ ጉድ ያመጣብን ይህ ዐይነቱ አስተሳሰብ በመስፋፋቱ ነው በማለት በጭፍን ይፈረጃል።
የመንግስቱም አወቃቀር፣ ማለትም ወታደሩ፣ የስለላና የፖሊስ አወቃቀርና የመጨቆኛ መሳሪያው ከውጭ የመጡ ስለሆነ ይህንን በስነ-ስርዓት ማስተናገድ ያልቻለው በተለይም የደርግ አገዛዝ ወደ መጨፍጨፊያ መሳሪያነት ለወጠው። ወታደሩ በአጠቃላይ ሲታይ በአሜሪካን የሚሊተሪ ርዕዮተ-ዓለም የለጠነና ኋላ-ቀር ከሆነው ህብረተሰብም የፈለቀ በመሆኑ ጭንቅላቱ ለሎጂካዊ አስተሳሰብና ለክርክር ክፍት አልነበረም። በአጭሩ ትቅበላለህ ወይም አትቀበልም በሚለው አስተሳሰብ የሰለጠነ በመሆኑ ማንኛውንም ነገር በኃይል ብቻ ነው መመለስ የሚቻል የሚመስለው። ከዚህ ሁኔታ ስንነሳ በተለይም በፀረ-ሶሻሊዝምና በፀረ-ኮሙኒዝም አስተሳሰብ መንፈሳቸው የተሳከሩ ኃይሎች በአገራችን ምድር የተፈጠረውን ሁኔታ ያሳብቡ የነበረው የግራ አስተሳሰብ ወይም የማርክሲስዝም የሌኒንዝም አስተሳብ በመስፋፋቱ ነው እያሉ የውሸት ወይም ኢ-ሳይንሳዊ የሆነ ቅስቀሳ በማካሄድ ነው። ይሁንና ደርግ ከተወገደ በኋላ ስልጣን ላይ የወጣው የህወሃት አገዛዝና የዛሬው የፋሺስቱ የአቢይ አህመድ አገዛዝ በምን ዐይነት ርዕዮተ-ዓለም እየተጋዙ ነው መጠነ ሰፊ ግድያና የሀብት ዘረፋ የሚያካሂዱት? ለሚለው ጥያቄ የሚሰጡት መልስ የለም። ስለሆነም በማርክሲዝም ፍልስፍናና ክሪቲካል ቲዎሪ ላይ የሚወራው የተሳሳተ ትረካ የአገራችንን ሁኔታ በትክክል የሚያንፀባርቅ አልነበረም፤ አይደለምም። ትላንትም ሆነ በዛሬው ወቅት በአገራችን ምድር የሚካሄደው ግድያ፣ ህዝብን ማፈናቀልና የሀብት ዘረፋ ጭንቅላት በሚገባ ካለመኮትኮቱና ለመዳበር ካለመቻሉ ጋር የሚያያዝ ነው። ጭንቅላታችን ወደ ግራና ቀኝ፣ እንዲያም ሲል ወደ ውስጥ የመመልከትና የመመራመር፣ እንዲሁም የማገናዘብ ኃይል ስለሌው በደመ-ነፍስ በመመራት የሚካሄደው ፖለቲካ የሚባለው ነገር ህዝባችንን እያሰቃየው ነው። በቀላሉ ሊወጣ የማይችለው ውስብስብ ሁኔታ ውስጥ ከቶታል፤ እየከተተውም ነው። ራሳቸው የገዢ መደቦች የሚባሉትም የድንቁርናቸው ሰለባ በመሆንና ከውጭ የሚመጣን ፖሊሲ ተግባራዊ በማድረግ በችግር ላይ ችግር እየፈጠሩ ነው። ራሳቸውን ለመጠየቅና ተግባራዊ የሚያደርጉትንም ፖሊሲ ለመረዳት ጭንቅላታቸው የተዘጋጀ አይደለም። ሁሉን ነገር ቨጭፍንና በአወቅሁኝ፡ባይነት በማድረግ አንድን ትውልድ ብቻ ሳይሆን ተከታታዩንም ትውልድ በቀላሉ ሊፈታው የማይችለው ችግር ውስጥ ከትተውታል።
ከዚህ ሁኔታ ስንነሳ ካለፉት ሰባት ዓመታት፣ በተለይም ካለፉት ሶስት ዓመታት ጀምሮ የፋሺስቱ የአቢይ አህመድ አገዛዝ በተለይም የአማራው ወገናችን ላይ የሚያካሄደው ጦርነት ጭንቅላቱ ጨቅላ ከመሆን ጋር የተያያዘ ነው። አቢይ አህመድና ግብረ-አበሮቹ የኦሮሞን ህዝብ ጥቅም የሚያስጠብቁ ሳይሆኑ የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምን፣ የእነ ጆርጅ ሶሮና በአጠቃላይ ሲታይ የፋይናንስ ኦሊጋርኪውንና የተባበሩት የአረብ ኢሚራትን ጥቅም የሚያስጠብቁ ናቸው። ጦርነቱም የውክልና ጦርነት የሆነና አገራችንን ለመሽንሸንና ሀብቷን ከመዝረፍ ጋር የተያያዘ ነው። የአቢይ አህመድ ጭንቅላት በቅራኔዎች የተዋጠ ነው። በአንድ በኩል የኢቫንጄሊካል ክርስቲያን አማኝ ነኝ ይላል፤ እዚያው በዚያው ደግሞ የተባበሩት የአረብ ኢሚራት ተወካይና ጥቅም አስጠባቂ በመሆን በክርስቲያኑ ህዝባችን ላይ፣ በተለይም በአርሲ ክፍለ-ሀገር መጠነ ሰፊ ጭፍጨፋ እያካሄደ ነው። በሌላ ወገን ደግሞ አሜሪካን አገር የኢቫንጄሊካል ክርስቲያን አማኞችና የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች እንደ ጠላት የሚተያዩ ናቸው። ለዚህም ነው በ1990ዎቹ መጀመሪያ ላይ ወደ ፊት የሚደረገው ትግል በእስልምና ሃይማኖትና በክርስቲያን ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ ነው ብሎ ሳሙኤል ኸንቲግተን መጽሀፍ የጻፈው። ከዚህች አጭር ሀተታ ስንነሳ አቢይ አህመድ ምንም ዐይነት ዕምነት የሌለውና ስልጣን ላይ ለመቆየት ስሊ ብቻ እያጭበረበረ የሚኖር ነው።
ነገሩን ለመቋጠር በአገራችንና በአብዛኛው የአፍሪካ አገሮች ውስጥ ያለው ትልቁ ችግር ሰፋ ያለ ምሁራዊ ውይይት ለመካሄድ ባለመቻሉ ነው። ወደ አገራችን ላይ ብቻ ሳተኩር አብዛኛው ምሁር ነኝ ባይ ጭንቅላቱን ለአዳዲስ ዕውቀቶችና ውይይቶች ክፍት ለማድረግ የሚፈልግ አይደለም። በሳይንሳዊ ዕውቀትና ኢ-ሳይንሳዊ ዕውቀት መሀከል ያለውን ልዩነት ለመገንዘብ በፍጹም የሚችል አይደለም። የነገሮችን አመጣጥና አስተዳደግ በተናጠል የሚያይ እንጂ እንዴት እንደተያያዙና እንደሚደጋገፉ በፍጹም ለማየትና ለመተንተን አይፈልግም። በሌላ አነጋገር፣ የአገራችን ሁኔታ በእነ አቢይ አህመድ የሚደነገግ ሳይሆነ በውጭ ኃይሎች መሆኑን በፍጹም ሊቀበል አይችልም። በተለይም በአገራችን ምድር ባለፉት ሰላሳሶስት ዓመታት በዓለም የገንዘብ ድርጅት(IMF) ተረቆ የመጣውንና የሚተገበረውን በአገዛዙ የፖሊሲ አውጭዎች ተደረጎ ነው የሚወሰደው። ስለ ፖለቲካ ያገባኛል የሚለው ኤሊት ብቻ ሳይሆን የዩትቭ ቻናል ከፍተው የሚያደነቁሩን ጋዜጠኛ ነን ባዮችም ሁሉ በዚህ ዐይነት የተሳሳተ አስተሳሰብ ጭንቅላታቸው የተቀረፀ ስለሆነ የነገሮችን አመጣጥና ዕድገት በፍጹም ሊገነዘቡ አይችሉም። ሰይጣናዊ አስተሳሰብን ያዳበሩ ይመስል ያንኑ እየደጋገሙ በማውራት በአገራችን ምድር የተገለፀለትና ዲሞክራሲያዊ ስርዓት እንዳይመጣ እንቅፋት ሆነዋል ማለት ይቻላል። በሌላ ወገን ግን ነገሩን በሚገባ ለተመለከተና ጥልቀት ያለው ምርምር ላደረገ የኢትዮጵያ ህዝብና የአገራችን ጠላቶች በግልጽ የሚታዩና በግልጽ የማይታዩ ናቸው። በግልጽ የሚታየው ቀደም ብሎ የህወሃት አግዛዝ፣ ከሰባት ዓመት ጀምሮ ደግሞ የፋሺስቱ የአቢይ አሀመድ አገዛዝና አዛዦቹ የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምና ግብረ አበሮቹ ሲሆኑ፣ በግልጽ የማይታየው ጠላት ደግሞ በምሁርነት የሚያወናብደውና አገር ወዳድ በመምሰል ይሁንና የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምን አጀንዳ በሌላ መልክ ለማስቀጠል የሚታገለው ነው። ባጭሩ የኢትዮጵያን ህዝብ የሚፈታተኑና ታሪክም እንዳይሰራ የሚያደርጉት ጠላቶች ውስብስብና የሚሙለጨለጩ ናቸው። የሀዋሃትና የአቢይ አህመድ አገዛዝ ድርጊታቸው በገሃድ የሚታይ ነው። ፖሊሲያቸውንም በአንዳች ርዕዮተ-ዓለም፣ በሌላ አነጋር በግራና በቀኝ ብሎ ለመግለጽ በፍጹም አይቻልም። እንደዚሁም በምሁር ስምም የሚያወናብደውን ርዕዮተ-ዓለሙን በግልጽ እንደዚህ ነው ብሎ መናገር አይቻልም። ባጭሩ ማለት የሚቻለው ትግሉ በሰይጣናዊ መንፈስ በሚመሩና ቅዱሳዊውን መንገድ በሚከተሉ መሀከል ያለ ነው። በዓለም አቀፍ ደርጃም ያለው ትግል ይህንን ነው የሚመስለው። ዘመኑም በሰይጣናዊ መንፈስ የሚመሩና ይህንን አስተሳሰብ በሚያራምዱ የሚመራ ነው። ባጭሩ ያለው ሀቅ ይህ ሲሆን፣ ትግሉ በካፒታሊዝምና በሶሻሊዝም መሀከል ያለ አይደለም። ከእኛ የሚጠበቀውም ነገር የነገሩን ውስብስብነት በመረዳት ጭንቅላትን ክፍት በማድረግ ለውይይት መዘጋጀት። ሌሎችና አማራጭ አስተሳስቦችን ለማፈን መሞከር የጨለማውን ዘመን እንደማራዘም ይቆጠራል። መልካም ግንዛቤ!!
www.fekadubekele.com
fekadubekele@gmx.de
https://www.youtube.com/watch?v=9id-MwXEQis
https://www.youtube.com/watch?v=gAV0bkTHui8
https://www.youtube.com/watch?v=YfLj1pHGfT4
https://www.youtube.com/watch?v=IvGdu1vAtgc
ማሳሰቢያ፤ ይህ ጸሀፊ ለአገር ዕድገት በሚጠቅሙ ነገሮች ላይ ትምህርታዊ ሰሚናር በዌቢናር ወይም በቪዲዮ ኮንፍረስ መልክ ለመስጠት ይፈልጋል። አትኩሮም የሚሰጣቸው ትምህርቶች 1ኛ) አንድ ህብረተሰብ እንዴት ይገነባል? ምን ምን ነገሮች ናቸው አንድን ህብረተሰብ እንደ ህብረተሰብ የሚያይዙት? 2ኛ) መንግስት ማለት ምን ማለት ነው? ተግባሩስ ምንድን ነው? ፖለቲካ ማለት ምን ማለት ነው? 3ኛ) የኢኮኖሚ ዕድገት ማለት ምን ማለት ነው? 4ኛ) በታሪክ ውስጥ የተነሱ የኢኮኖሚ ዕድገት አስተሳሰቦች ምን ይመስላሉ? 5ኛ) የስራ–ክፍፍልና የህዝባዊ ወይም የብሄራዊ ሀብት ፈጠራ፣ 6ኛ) ገንዘብ ማለት ምን ማለት ነው? እንዴትስ ተፈጠረ? ተግባሩስ ምንድን ነው? 7ኛ) በታሪክ ውስጥ የተነሱ የተለያዩ የኢኮኖሚ ቲዎሪዎች አስተሳሰቦች ምን ይመስላሉ? 7ኛ) በካፒታሊዝምና በተራ የገበያ ኢኮኖሚ መሀከል ያለው ልዩነት ምን ይመስላል? 8ኛ) ካፒታሊዝም እንዴት በአውሮፓ ምድር ብቻ ብቅ ማለት ቻለ? ምክንያቶቹስ ምንድን ናቸው? 9ኛ) የሳይንስና የቴክኖሎጂ ሚና በካፒታሊዝም ውስጥ ምን ይመስላል? ካፒታሊዝም ካለሳይንስና ካለቴክኖሎጂ ሊዳብር ይችላል ወይ? 9ኛ) የዓለም የገንዘብ ድርጅት(IMF) ፓሊሲ እንደ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ሊቆጠር ይችላል ወይ? የኢኮኖሚ ፖሊሲ ዋናው ተግባሩስ ምንድን ነው? አንድን አገር ማዘበራረቅ ወስም ስርዓት ባለው መልከ መገንባትና አንድን ህዝብ ከድህነት ማውጣት? 10ኛ) የዓለም የገንዘብ ድርጅት የፖሊሲ መሳሪያዎች ሳይንሳዊ ባህርይ ለምን የላቸውም? ለምንድነው ዝም ብለን ያንኑ እየደጋገምን ተግባራዊ የምናደርገው? እነዚህንና መጠነ ሰፊ የሆኑ ጥያቄዎችን በማንሳት በትምህርት መልክ መስጠት ይቻላል። በእኔ ዕምነት ከእዚህ ዐይነት አርዕስቶች ውጭ የሚደረጉ ገለፃዎችና ውይይቶች ለአገራችን ህዝብና ለዕድገቱ የሚጠቅሙ አይደሉም። ሰሚናሩን ለማዘጋጀት ቢያንስ 20 ሰዎች ዝግጁ መሆን አለባቸው። ከዚያም በላይ ሊሳተፉ ይችላሉ። በተረፈ በተከታታይ ሳይንሳዊ ጽሁፎችን ለማውጣት ድጋፍ ያስፈልጋል። ድረ-ገጼን በመመልከት አስፈላጊውን ነገር ማድረግ ይቻላል። በጥናትና በምርምር ላይ የተመሰረተ አካሄድ ብቻ ነው አገራችንን ነፃ የሚያውጣውና ህዝባችንንም በአስተማማኝ ሁኔታ ለማኖር የሚቻለው።