አንዱ ዓለም ተፈራ
አርብ፣ ኅዳር ፳ ፮ ቀን ፳ ፻ ፲ ፰ ዓ. ም. (12/05/2025)
የኔ ጽሑፍ ነውና፤ ከወዲሁ እኔ ራሴ ምርጫው እንደሚካሄድ፣ መራጮቹም ወደ ምርጫ ቦታዎች እንደሚሄዱ፣ ተወዳዳሪዎችም ተሙነሽነሸው እንደሚቀርቡ፣ እና አቸናፊዎችን ዛሬ እንደማውቅ ልንገራችሁ። ገዢው ፓርቲ ከታች የምዘረዝራቸውን ባያደርግም፤ በከፍተኛ ድምጽ (ምናልባትም ክ90% በላይ እና ከ100% በታች) ያቸንፋል። ነገር ግን፤ አምባገነን ምን ጊዜም በሕዝቡ ስለማይተማመንና ሁሌም ፈሪ ስለሆነ፤ አስቀድሞ ምርጫውን እንዲያቸንፍ፤ በራሱ ሕገ መንግሥት እንኳን ሕገ ወጥ የሆኑ ጉዶችን በተወዳዳሪዎቹ ላይ ያደርጋል። እናም በሚፈልገው መንገድ ያቸንፋል። ደርግ ምርጫዎችን አካሂዷል። የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባር ምርጫዎችን አካሂዷል። ይሄም የተረኛው የአክራሪ ኦሮሞ ገዢ ቡድን ምርጫዎችን አካሂዷል። በሁሎችም ምርጫዎች፤ ውጤታቸው ምርጫዎቹ ከመደረጋቸው በፊት የታወቀ ነበር። ያም ሆኖ፤ ሊወዳደሩ ይችላሉ ተብለው የተፈሩ ታስረዋል፣ ተከሰዋል፣ ተሰደዋል፣ ተገድለዋል። የሚገርመው፤ ኢትዮጵያን በምታክል አገር፣ በሕዝቡ ሰላማዊነት፣ ሃይማኖተኛነት፣ ሕግ አክባሪነት የታወቀ እውነታ፣ እንዴት ነው መሪዎች ከሌላ ቦታ የመጡ ይመስል፣ ፀረ አገር እና ፀረ ሕዝብ የሆኑት?
አገራችን ውስጥ በትክክል ነፃ የምርጫ ውድድር ተደርጎ አያውቅም! ይሄን እንዴት ማለት ትችላለህ? ብሎ የሚጠይቅ ይኖራል። ነገር ግን፤ መቼ ተደረገ? ብዬ ብጠይቅ፤ መረጃ አስደግፎ ነበር ብሎ መልስ የሚሠጠኝ የለም። ከመጀመሪያውም ምርጫዎቹ ለይስሙላና ለውጪ ጌቶቻቸው ማስደሠቻ ስለሆኑ፤ ድንገት እንኳ ተወዳዳሪዎች ሊያቸንፉ ቢቀርቡም፤ ወይንም አንዳንድ ቦታዎች ቢያቸንፉም፤ በነጋታው ተወዳዳሪዎችን በማሰርና ምክንያት አበጅቶ ከምርጫ ውጪ በማድረግ፤ ገዢው ቡድን ያቸንፋል። አሁን ለኔ ጥያቄ የሚሆኑት፤ ከምርጫው ጋር ተያይዞ፣ ስንት ሰዎች ይታሠራሉ? ስንት ሰዎች ይሰደዳሉ? ስንት ሰዎች ንብረታቸውን ያጣሉ? እኒህ እና እኒህን የመሰሉት ናቸው። በቴሌቪዥን እና በሬዲዮ እንዲቀርቡ የሚደረጉት፤ ያለውን ገዢ ቡድን የሚያሞግሱ ብቻ ይሆናል። አዎ! ለይስሙላና ማኳኳያ የሆኑ አይቀርቡም አልልም። ለሆዳቸው ያደሩ በለጠ ሞላንና ብርሃኑ ነጋን የመሰሉ ለሕዝብ ቀርቶ ለራሳቸውም ክብር የሌላቸው ብቻ ሳይሆን፤ ክብር በሚባልበት ቦታ ቀርበው የማያውቁ ይኖራሉ። ያ ግን ለዴሞክራሲያዊ አሠራርና ለትክክለኛ ምርጫ ማሳያ አይሆንም።
ዛሬ አንድ ከድርጅቱ የተባረረ ግለሰብ እጁን ሲሠጥ፤ ስምምነት ከነበረበት ድርጅት ጋር አደረግሁ ብሎ፤ ባደባባይና የውጪ ተቋማት በተገኙበት ዓይኖቻችሁን ጨፍኑ ላሞኛችሁ ያለ ገዢ ቡድን፣ ዛሬ የገዛ ሕዝቡን በቦንብ የሚደበድብ ገዢ ቡድን፣ ዛሬ ኦሮሞ ካልሆንክ ኢትዮጵያዊ አይደለህም የሚል ገዢ ቡድን፣ እንዴት አድርጎ ነው ምርጫ ያካሂዳል! ተብሎ የሚታሰበው? ምርጫ! አዎ፤ ተካሄደ ሊባል ይችላል። የዴሞክራሲያዊ አሠራር መሠረቱ፤ ሕዝቡ ወዶ መሪዎቹን መምረጡ ነው። ያ ግን ቅድመ ሁኔታ የሚያደርገው፤ ሕዝቡ ለመምረጥ ፍላጎትና መብቱ አለው! የሚለውን ነው። ሕዝቡ ትክክለኛ ገበያ በአገሬ አለ! ብሎ ሲያምን ነው። ሕዝቡ ነገ እንዲህ አደርጋለሁ! ብሎ ነገ መምጣቱን ተማምኖ ሲያቅድ ነው። ሕዝቡ በአገሬ በኢትዮጵያ የትም መኖር እችላለሁ ብሎ ሲያምን ነው። የትም ቦታ መምረጥና መመረጥ እችላለሁ ብሎ ሲያምን ነው። ሕዝቡ ከኑሮ ውድነት ጋር በየዕለቱ መጋጨቱ ሲቀርለት ነው። ሕዝቡ ከጉቦ፣ ከሙስና፣ ከአድልዖ ሲገላገል ነው። ሕዝቡ ያለጦርነት መግዛት የማይችል ገዢ ሲኖረው ነው። ረሃብና የሥራ ማጣት፣ መራቆትና ተስፋ መቁረጥ በነገሠበት አገር፣ ምርጫ ቅንጦት ነው። ሕዝቡ በዓለም ተበትኖና አገሩ ውስጥ ያለው፤ መውጫውን የየዕለቱ ሕልሙ እያደረገ፤ በአገር ውስጥ ትክክለኛ ምርጫ ይደረጋል ብሎ ማሰብ፤ እውነታን ሽምጥጦ መካድ ነው፤ ወይንም ዓይኖቻችሁን ጨፍኑ ላሞኛችሁ ነው። አዎ! የገዢው ቡድን አባላትና እግር አጣቢዎቻቸው ይመርጣሉ። አዎ! ተገዶ የሚመርጥም ይኖራል። እውነት ይሄን መርጫ ብለን እንጠራለን? አዎ! ይካሄዳል። አዎ! ብልፅግና ከዘጠና በመቶ በላይ በየቦታው ያቸንፋል።
ብልፅግና ምርጫውን ያካሂዳል። ሕዝቡ በልቶ ስለሚያድረው ይጨነቃል። ራሱን በሥልጣን ኮርቻ መሰላሉ ላይ ወደላይ ለመውጣት የሚሯሯጠው፤ ይዋሻል፣ ጉራውን ይነዛል፣ ሰዎችን ያሳስራል፣ ያስገድላል፣ የአብይን ፎቶግራፍ ግንባሩ ላይ ለጥፎ ይዞራል፣ ምርጫው ይካሄዳል። ብልፅግናም ያቸንፋል። የኑሮ ውድነት ይከፋል። አይ ኤም ኤፍም ጫናውን ያደርጋል። የዓለም ባንክም እንዲሁ። ገዢው ቡድን ራሱን እያሳበጠ፤ ደሞዝ መክፈል የማይችላቸው አካላት ይበዛሉ። ሳልከፍላችሁ ሥሩ ብሎ ጥይት ይተኩስባቸዋል። ያስራቸዋል። ወደ ጦርነት የሚማግደው ወጣት እስኪያጣ ድረስ ያጋብሳል። ማጋበስ ሲያቅተው፤ የሰረቀውን ገንዘብ ይዞ፣ በውጪ እንዲማሩ የላካቸውን ዘመዶቹን ቦታ አዘጋጁልኝ ብሎ፣ መንግሥቱ ኃይለማርያም ዚምባብዌ እንደገባው ሁሉ፤ እምነታቸውን ወይንም የፖለቲካ አመለካከታቸውን ከሚጋራቸው ወይንም እስካሁ አሽከር ሆኖ ወደ አገለገላቸው አገር በመሄድ ቀሪ ቀኖቹን ይጨርሳል። ቀሪው የሱ አገልጋይ የነበረ ሁሉ፤ ተጋልጦ በውርደትና በመሸማቀቅ ይኖራል። ህይወቱ ከተረፈችለት!