ኤፍሬም ማዴቦ (emadebo@gmail.com )
አገራችን ኢትዮጵያ ሥርዓተ መንግስት መስርታ እንደ አገር በኖረችባቸው በሺዎች በሚቆጠሩ አመታት ውስጥ ነገስታት ተፈራርቀውባታል፣ወታደራዊ አምባገነን እና የአንድ ብሔር አምባገነኖች ገዝተዋታል ዛሬም እየገዟት ነው። እስከ 1983ዓም ድረስ የነበሩት የኢትዮጵያ መንግስታት የህዝብን መብት የረገጡ ጨቋኝ መንግስታት ቢሆኑም፣የኢትዮጵያ የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት ከምንም ነገር በላይ የሚገዳቸው መንግስታት ነበሩ። ከደርግ በኋላ አራት ኪሎን የተቆጠጠሩት ህወሓቶችና የዛሬዎቹ ብልፅግናዎች ግን ከኢትዮጵያ የሚያስቀድሙት የራሳቸውን ብሔር ወይም የሥልጣን መሰረታችን ነው ብለው የሚያምኑበትን የራሳቸውን ክልል ነው። የዛሬዋ ኢትዮጵያ በታሪኳ ለመጀመሪያ ግዜ የሥልጣን ዘመኑን ለማራዘም ሲል በየቀኑ የራሱን ዜጎች በሚጨፈጭፍና ከራሱ ህዝብ ጋር በተለያዩ ግንባሮች ጦርነት ውስጥ በገባ መንግስት እየተመራች ነው። ጠሚ አቢይ አህመድ በአንድ በኩል “መደመር” የሚል አብረን እንስራ፣አብረን እንኑር፣አብረን እንደግ የሚልና አብሮነትን የሚያጠነጥን ተከታታይ መጽሐፍ እየጻፈ፣በሌላ በኩል ደግሞ የተዋለደ፣በታሪክ የተሳሰረና ለአመታት አንድ ላይ አብሮ የኖረ ህዝብ እንደ ጠላት እንዲተያይና እርስ በርሱ እንዲዋጋ እያደረገ፣የጥቁር ህዝብ የነጻነት ተምሳሌት የሆነችው ኢትዮጵያን እያፈረሰ ነው።
አገሬን ኢትዮጵያን በደርግና በህወሓት/ኢህአዴግ ዘመን አውቃታለሁ፣ በደርግ ዘመን ቀይሽብርን የመሰለ ዘግናኝ ወንጀል ሲፈጸምና ሱማሌ፣ኤርትራና ትግራይ ውስጥ ጦርነት ሲካሄድ አውቃለሁ፣በተለይ ከህወሓትና ከሻዕቢያ ጋር የተደረገውን ትንቅንቅ በአካባቢው ሆኜ በቅርብ ተከታትያለሁ። በእነዚህ ግዜዎች ሁሉ የኢትዮጵያ አንድነት አደጋ ውስጥ መግባቱ አሳስቦኛል፣አስጨንቆኛልም። ዛሬ በጠሚ አቢይ አህመድ ዘመን የሚያሳስበኝ ግን አንድነታችን አደጋ ውስጥ መግባቱ ብቻ ሳይሆን፣የኢትዮጵያ እንደ አገር መቀጠል እራሱ ትልቅ አደጋ ውስጥ መግባቱ ነው። ጠሚ አቢይ አህመድ የሚከተለው እጅግ በጣም ደካማ የሆነ የእውር ድንብር ዲፕሎማሲ ኢትዮጵያ በአካባቢዋ ባሉ አገሮች ሁሉ እንደ ወራሪ ኃይል እንድትታይ ከማድረጉ ባሻገር፣ሉዓላዊነታችንን እና ትልቅ አገር መሆናችንን ለዘመናት አክብረው የኖሩ ታሪካዊ ጠላቶቻችን በሰሜን፣በምስራቅና በምዕራብ በኩል ጓሯችን ድረስ መጥተው እንዲሰፍሩ መንገድ ከፍቶላቸዋል።
በተለያዩ ሜዲያዎችና በማህበራዊ ትስስር ገጾች ላይ የተለያዩ ፖለቲከኞች ሰለ ጠሚ አቢይ አህመድ ሲናገሩ፣አቢይ አህመድ የኢትዮጵያን ችግሮች የመፍታት ፍላጎት በፍጹም እንደሌለው ሲናገሩ በተከታታይ እሰማለሁ። ይህ አፈር ላይ ጠብ የማይል እውነት ነው፣ግን እውነቱ እሱ ብቻ አይደለም፣ጠሚ አቢይ አህመድ የኢትዮጵያን ችግሮች የመፍታት ፍላጎቱ ብቻ ሳይሆን ችሎታውም በፍጹም የሌለው ሰው ነው። ታዲያ እስከመቼ ነው እኛ ኢትዮጵያዊያን የአገራችንን ችግሮች የመፍታት ፍላጎቱም ችሎታውም የሌለው ችግር ፈጣሪ ሰው እኛንም አገራችንንም ይዞ ገደል ሲገባ እጃችንን አጣጥፈን የምንመለከተው?
ትግራይ ውስጥ ጦርነት ከመጀመሩ ከሁለት አመት በፊት ጀምሮ፣ጠሚ አቢይ አህመድ ማድረግ የሚችለውን ሁሉ አድርጎ ከህወሓት ጋር ያለውን ልዩነት በውይይት/ድርድር እንዲፈታና፣ በሌላ በኩል ደሞ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አገራችን ኢትዮጵያ ከውጭም ከውስጥም የሚገጥማትን ፈተና መወጣት በሚችልበት መልኩ በፍጥነት እንዲደራጅ በተከታታይ ተነግሮታል፣በተለይ የህወሓት ሰዎች አዲስ አበባን ለቅቀው መቀሌ ከገቡበት ግዜ ጀምሮ ለጦርነት እየተዘጋጁ እንደሆነና የጦር መሳሪያም በገፍ እያስገቡ እንደሆነም ተነግሮታል። ይህ የጦርነት ዝግጅት መረጃ በተለያዩ ሰዎች ከተለያየ አቅጣጫ ሲነገረው የጠሚሩ መልስ “ህወሓቶች ከፌዴራል መንግስቱ ጋር ጦርነት ውስጥ መግባትን በፍጹም አያስቧትም” የሚልና ሰውየው እውነትም የለየለት የፖለቲካ ድንክ መሆኑን በግልጽ ያሳየ መልስ ነበር። ይህ የጠሚ አቢይ አህመድ ንዝህላልነትና አርቆ አለማሰብ የትግራይን፣የአፋርንና የአማራን ባጠቃላይ እንደ አገር የኢትዮጵያን ህዝብ እጅግ በጣም ከፍተኛ ዋጋ አስከፍሏል። ለምንድነው እኛ ኢትዮጵያዊያን በግለሰብ ደረጃም በአገር ደረጃም በየቀኑ ከፍተኛ ዋጋ የሚያስከፍለንን መሪ ተሸክመን አመት የምንቆጥረው?
በትግራይ ጦርነት ወቅት ዘግናኝ የጦር ወንጀል ተፈጽሟል፣የአንድ አገር ህዝብ እርስ በርስ ተጋድሏል፣እናቶችና ወጣት ልጃገረዶች ቤተሰቦቻቸው እያዩ ተደፍረዋል፣ንብረት ወድሟል፣መሰረተልማት ፈራርሷል፣የደረሰ እህል ተቃጥሏል፣ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህዝብ ተፈናቅሏል። ባጠቃላይ የትግራይ ጦርነት የረጂም ዘመን ታሪካዊ ትስስር ያላቸውን ህዝቦች እንደ ጠላት እንዲተያዩ ካደረገና አገራችን ኢትዮጵያን እጅግ በጣም ከፍተኛ ዋጋ ካስከፈለ በኋላ በፕሪቶሪያ ስምምነት ተቋጭቷል። የፕሪቶሪያው ስምምነት ዋና አላማ የትግራይ፣የአፋርና የአማራ ህዝብ የሰላም አየር እየተነፈሰ ፊቱን ወደ ልማት እንዲያዞር ማድረግ ነበር። ሆኖም ዕድሜ ለአቢይ አህመድ ዛሬ ስምምነቱ ከተፈረመ ከሦስት አመት በኋላ፣አማራ ክልል የጦርነት አውድማ ሆኗል፣የትግራይና የፌዴራል ኃይሎች እንደገና ጦርነት ውስጥ ለመግባት ቃላት እየተወራወሩ ነው፣ኦሮሚያ ውስጥ መሳሪያ ያነገበ ሁሉ ዜጎችን አፍኖ ገንዘብ ይጠይቃል፣ይዘርፋል፣ይገድላል። ለምንድነው እኛ ኢትዮጵያዊያን በአለም አቀፍ ደረጃ የተደረሰን የሠላም ስምምነት ያፈረሰንና የፖለቲካ ልዩነቶችን ሁሉ በጦርነት ብቻ ለመፍታት የሚሞክርን ዕብድ ሰው ከአናታችን ላይ እሽቀንጥረን የማንጥለው?
የኢትዮጵያ ህዝብ፣የአፍሪካ ህብረትና የተባበሩት መንግስታት ድርጀት የፕሪቶሪያው ስምምነት ሲፈረም ደስ ያላቸው ኢትዮጵያ የሰላም አየር መተንፈስ ትጀምራለች የሚል ዕምነት ስለነበራቸው ነው፣ነገር ግን ሰሜን ኢትዮጵያ ውስጥ የጥይት ድምጽ ትንሽም ቢሆን ፋታ ያገኘው የፕሪቶሪያው ስምምነት ከተፈረመበት ከጥቅምት 23 2015 ዓ.ም. እስከ ሐምሌ ወር ድረስ ባሉት ሰባት ወራት ውስጥ ብቻ ነው። ሐምሌ አጋማሽ ላይ አቢይ አህመድ በዕብደት ተነሳስቶ ፋኖን በ15 ቀን ትጥቁን አስፈትቼና አደብ አስገዝቼ እመለሳለሁ ብሎ የጀመረው ፍጹም ትርጉም የለሽ የሆነ አገር አውዳሚ ጦርነት ዛሬ ሁለተኛ አመቱን ጨርሶ ሦስተኛውን ተያይዞታል። ለምንድነው የጠሚ አቢይ አህመድ መንግስት ትግራይ፣አማራና ኦሮሚያ ውስጥ ምርጫው ጦርነት ብቻ የሆነው? በህዝብ ብዛትም በቆዳ ስፋትም ከግማሽ በላይ በሆነው የኢትዮጵያ ግዛቶች ውስጥ አመታት ያስቆጠረ የርስበርስ ጦርነት እየተካሄደ ኢትዮጵያ እንዴት ነው እንደ አገር መቀጠል የምትችለው?
ዛሬ አማራ ክልል ውስጥ የፌዴራል ኃይሎች በተሸነፉና ጥቃት በደረሰባቸው ቁጥር በጦርነቱ ውስጥ ምንም አይነት ተሳትፎ የሌላቸውን ወጣቶችና አረጋዊያን በያገኙበት ይረሽናሉ፣ወጣት ሴቶችን ደፍረው ጡታቸውን ቆርጠው ይገድሏቸዋል፣እናቶችን ልጆቻቸውና ባሎቻቸው ፊት ይደፍራሉ፣የማንም ይሁን የማን ያዩትን ንብረት ሁሉ ይዘርፋሉ፣ትህምህርት ቤቶችንና የጤና ተቋሞችን በድሮን ያፈርሳሉ። ባጠቃላይ ፋሺስት ጣሊያን በአምስቱ የወረራ አመታት ያልፈጸመውን ግፍና በደል፣ የፌዴራል ኃይሎች አማራ ክልል ውስጥ በየቀኑ ይፈጽማሉ። በነገራችን ላይ አማራው ግፉና መከራው የሚደርስበት በሚኖርበት ክልል ውስጥ ብቻ አይደለም፣ ኢትዮጵያ ውስጥ በሚኖርባቸው አካባቢዎች ሁሉ ይሳደዳል፣ይታሰራል፣ይገደላል። አርሲ በአማራ ደም የረጠበ ምድር ነው፣ወለጋ አማራው በነጋ በጠባ እየታደነ የሚገደልበት ቦታ ነው፣ቤንሻንጉል ጉሙዝም አማራው በስለት የሚታረድበት ቦታ ነው። አዲስ አበባ ውስጥ አማራው ቤቱ እላዩ ላይ ይፈርሳል፣ታፍኖ ደብዛው ይጠፋል፣ይደበደባል፣ይሳደዳል። ዛሬ አማራው ከአማራ ክልል በህዝብ ማመላለሻ አውቶቡስ አባቶቹ ወደ ቆረቆሯትና ወደገነቧት ከተማ ወደ አዲስ አበባ ከመግባት በእግሩ ናይሮቢ መሄድ ይቀለዋል። ለምንድነው የጠሚ አቢይ አህመድ መንግስት አማራው፣ባህሉና ሃይማኖቱ አንድ ላይ እንዲጠፉ የሚፈልገው? ሌላው ኢትዮጵያዊስ ለምንድነው ይህንን መንግስታዊ ጥቃት አፉን ዘግቶ የሚመለከተው? ነገ የጥቃት ሰለባው እሱ ሲሆን ማን ሊደርስለት ነው? ስብሰባ ተጠርቶ ነብሰ ገዳዩ አቢይ በተናገረ ቁጥር የሚያጨበጭበው የኢትዮጵያ ምሁርስ መቼ ነው ምሁር በአንድ አገር ውስጥ መጫወት የሚገባውን ሚና የሚጫወትው? መቼ ነው ምሁር ተብዬዎቻችን እንደ ዳኛቸው አሰፋ የአጎብጋቢነት ሳይሆን ምሁራዊ ሚና የሚጫወቱትና አገርን ከአደጋ የሚያድኑት? የኢትዮጵያ ወጣትስ ግፍና መከራን እየሸሸ በየባህሩ ከሚሞት፣ለምንድነው እዚሁ አገሩ ውስጥ ከነብሰ ገዳዮች ጋር ተናንቆ ሳይፈራ፣ሳይሸበርና ምን እሆናለሁ የሚል ስጋት ሳይኖርበት እየሰራ በሠላም መኖር የሚችልባትን ኢትዮጵያ የማይፈጥረው?
ጠሚ አቢይ አህመድና የሰው ልጅ ስብዕና አብሯቸው ያልተፈጠረ በክልልና በፌዴራል ደረጃ የሚገኙ የአማራ ባለሥልጣኖች ሜዲያ ላይ በቀረቡ ቁጥር “የፋኖ ኃይሎች ሠላም የሚፈልጉ ከሆነና ትጥቃቸውን ፈትተው ከመጡ፣በራችን ለድርድር ክፍት ነው” የሚል መልዕክት በተከታታይ ሲናገሩ ይደመጣሉ፣ነገር ግን በአንድ ራስ ሁለት ምላስ የሆነው ጠሚ አቢይ አህመድ፣ ትጥቃቸውን ሳይፈቱ ሁለቴ ከኢትዮጵያ ውጭ ሄደው ከፌዴራሉ መንግስት ጋር እንዲደራደሩ ለኦነግ ሸኔ ኃይሎች የሰጠውን ዕድል ለፋኖ ኃይሎች አንዴም አልሰጠም። ለምን?
የጠሚ አቢይ አህመድ መንግስት ኢትዮጵያን እያወደመ ያለው በፖለቲካው መስክ ብቻ አይደለም፣በኤኮኖሚው ዘርፍም ኢትዮጵያን ምርት የማይመረትባት፣እህል ተዘርቶ የማይታጨድባት፣ገንዘብ ዕቃ መግዛት የማይችልባት፣የውጭ አገር ኢንቬስተሮች የማይመጡባት፣የአገር ውስጥ እንቨስተር ካፒታሉን የሚያሸሽባት፣በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ አንደኛና ሁለተኛ ድግሪ ያላቸው ወጣቶች ስራ አጥተው ጎዳና ለጎዳና የሚመላለሱባት፣የገጠርና የከተማ ስራ አጥነት የሰፈነባት፣በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች በልተው የማያድሩባት አገር አድርጓታል።
ተናግሮ የማያባራ አፍ እንጂ የሚሰማ ጆሮ የሌለውና እራሱን በሁሉም ነገር እንደ አዋቂ አድርጎ የሚወስደው አቢይ አህመድ፣አገር ውስጥ ፕሮፌሰር አለማየሁ ገዳና በቅርቡ ከዚህ አለም በሞት የተለዩት ፕሮፌሰር በፈቃዱ ደግፌን የመሳሰሉ በኢትዮጵያ ኤኮኖሚ ላይ ለረጂም ግዜ የጥናትና ምርምር ስራ የሰሩ አንቱ የሚባሉ ምሁራን፣ በውጭ አገር ደሞ በአለም ባንክ ውስጥ የሰሩና በታዋቂ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ አስተማሪ የሆኑ እንደ ዶር ዮናስ ብሩና ዶር ተሾመ አበበን የመሳሰሉ ብዙ የኤኮኖሚክስ ጠበብቶች፣የIMF ፖሊሲ እንደ ኢትዮጵያ አይነት ታዳጊ አገር እንዳለ የሚቀበለው ፖሊሲ አይደለም፣እባካችሁ ይቅርባችሁ፣አያዋጣም፣አገር ታበላሻላችሁ እያሉ በተደጋጋሚ ሲነግሩት፣ከራሱ ውጭ ማንንም የማይሰማው አቢይ አህመድ ከአለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም ጋር ተስማምቶ ተግባራዊ ያደረጋቸው ፖሊሲዎች፣ድሃው ኢትዮጵያዊ ሆዱን ቆጥሮ የቆጠበው ገንዘብ በአንድ ጀምበር እንዲሟሟ ከማድረጉ ባሻገር፣ለወትሮው ደህና ገቢ ኖሯቸው ሌሎችን ይረዱ የነበሩ ኢትዮጵያዊያን የሰው እጅ እንዲመለከቱ አድርጓቸዋል። ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚታየው የኤኮኖሚ ችግር የሰው ልጅ መሸከም ከሚችለው በላይ ሆኗል። ጎረቤታችን የሱዳን ህዝብ የዳቦ ዋጋ ተወደደ ብሎ አልበሽርን አሽቀንጥሮ ሲጥል ትናንት በአይናችን አይተናል፣ኢትዮጵያ ውስጥ የሸቀጥና አገልግሎት ዋጋ በየቀኑ ነው የሚያድገው። ኢትዮጵያ ውስጥ ዋጋው የማይጨምር ወይም በየቀኑ ዋጋው እየቀነሰ የሚሄደው የሰው ህይወት ብቻ ነው። ጎረቤት ኬንያ ውስጥ ፕሬዚደንት ሩቶ ከIMF ጋር ተስማምቶ ተግባራዊ ሊያደርግ የነበረውን ፖሊሲ፣የኬንያ ህዝብ በነቂስ ወጥቶ ተቃውሞ ሲያሰማና መንግስትን ወጥሮ ሲይዝ፣ ሩቶ ኬንያውያን በፍጹም አንቀበልም ያሉትን የIMF ፖሊሲዎች ተግባራዊ እንዳይሆኑ አድርጓል። እኛ ኢትዮጵያዊያን በምዕራብ በኩል ለሠላሳ አመታት ሱዳንን አንቀጥቅጦ የገዛ አምባገነን በህዝባዊ እምቢተኝነት ከሥልጣን ተወግዶ እስር ቤት ሲገባ አይተናል፣ኬንያውያን እኛ አፋችንን ዘግተን የተቀበልነውን የIMF ፖሊስ አንቀበልም ብለው በህዝባዊ እምቢተኝነት ተነሳስተው እንዲሻር ሲያደርጉ ተመልክተናል። እኛ የዳቦ ዋጋ ብቻ ሳይሆን የሁሉም ሸቀጥና አገልግሎት ዋጋ እንደ ህፃን ልጅ በየቀኑ እያደገ ህይወት ፈተና ሲሆንብን ለምንድነው ጎዳና ወጥተን መንግስትን ወጥረን የማንይዘውና የፈረመውን ፖሊሲ እንዲሽር የማናደርገው? ለምንድነው ከጎረቤቶቻችን በተለየ መልኩ ጭቆናን፣የኑሮ ውድነትን፣ስራ አጥነትንና በነጋ በጠባ መታፈንና መታሰርን አሜን ብለን ተሸክመን የምንኖረው?
የአቢይ አህመድ መንግስት ስለቴክኖሎጂ በተለይ ሰለ AI በተደጋጋሚ ሲናገር ይሰማል፣አንዴማ ጭራሽ ኢትዮጵያ ውስጥ አርተፊሻል ኢንተሊጀንስ በቅርብ ግዜ በእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ቤት ሊኖር እንደሚችል ተናግሯል። ሆኖም ዛሬ በግልጽ የምናየው የአርተፊሻል ኢንተሊጀንስና የድሮን ቴክኖሎጂ ኢትዮጵያ ውስጥ ለጥፋት እንጂ ለልማት ውሎ አያውቅም። የረቀቀ የአርተፊሻል ኢንተሊጀንስና በየመንገዱና በየሰፈሩ ላይ የሚተከል የስለላ (surveillance) ቴክኖሎጂ፣ የተረጋጋ አምባገነናዊ ሥርዓት የመፍጠር አቅም እንዳላቸውና፣ለተደራጅ ህዝባዊ ትግል እንቅፋት ሊሆኑ እንደሚችሉ የጥናትና ምርምር ስራዎች ያሳያሉ። ይህንን የተረዳው ጠሚ አቢይ አህመድም፣የሥልጣን ዘመኑን የሚያሳጥር ህዝባዊ አመጽ እንዳይጀመር ከተጀመረም ወዲያው ደብዛው እንዲጠፋ ለማድረግ ለእነዚህ ቴክኖሎጂዎች ከፍተኛ በጀት መድቦ እየተንቀሳቀሰ ነው። ከዚህ በተጨማሪ ጠሚ አቢይ አህመድና የሜዲያ ሠራዊቱ፣ ብልፅግና መራሹ ሥርዓት ከዚህ በፊት ከነበሩት ሥርዓቶች ሁሉ የተሻለ ሥርዓት እንደሆነ፣በብልፅግና ዘመን ኢትዮጵያ በከፍተኛ ፍጥነት እያደገች እንደሆነና በቅርብ ግዜ የኢትዮጵያ ኤኮኖሚ የአፍሪካ ትልቁ ኤኮኖሚ እንደሚሆን ዜጎችን ለማሳመን ሰፊ የፕሮፓጋንዳና አእምሮን የመቆጣጠር ስራ እየሰሩ ነው፣የዘመኑ ቴክኖሎጂ ደሞ እንደዚህ አይነት ስራዎችን ለመስራት አመቺ ነው። ጠሚ አቢይ አህመድ ዘመኑ የፈጠረውን ቴክኖሎጂ ተጥቅሞ፣አገር ውስጥም ውጭ አገርም የሚኖሩ ለሆዳቸው ያደሩ ከሃዲዎችን በመሰብሰብ ዲጅታል ሠራዊት የሚባል ቡድን ፈጥሮ ህዝብን የማደናገርና የማሳሳት ስራ በየደቂቃው ሲሰራ በአይናችን እያየን ነው።
የዲጂታል ቴክኖሎጂ ዕድገትና መስፋፋት አምባገነን መንግስታት ህዝብን አፍነው እንዲገዙ ብቻ ሳይሆን፣ህዝብ አፈናውን በቃ ብሎ እንዳይነሳ ለማድረግም ይጠቀሙበታል። ሆኖም ድጂታል ቴክኖሎጂ አምባገነኖች እንዳሰኛቸው የሚቆጣጠሩት ወይም እነሱ ብቻ ያላቸው ቴክኖሎጂ አይደለም። በደርግ ዘመን ትግል ሲካሄድ ደርግ ሜዲያውን ሙሉ ለሙሉ ተቆጣጥሮ የራሱ የፕሮፓጋንዳ መሳሪያ ስላደረገው፣ህዝብ መረጃ የሚያገኝበትና የደርግን ክፋትና ጭካኔ ለአለምአቀፉ ማህበረሰብ በፍጥነት ማድረስ የሚቻልበት መንገድ አልነበረም። በደርግ ግዜ ደቡብ ኢትዮጵያ አርባምንጭ ውስጥ መንግስት ግልጽ የሆነ ወንጀል በአደባባይ ሲፈጽም፣ አዲስ አበባ ውስጥ ያለው ሰው እስኪሰማው ብዙ ግዜ ይወስድ ነበር። ዛሬ ዕድሜ ለቴክኖሎጂ የአምባገነኖች የሜዲያ ሞኖፖሊ ተሰብሮ፣ኢትዮጵያ ውስጥ በትናንሽ ከተማዎችና ወረዳዎች ውስጥ ኮሽ ያለ ነገር ዋሺንግተን ዲሲና አውሮፓ የሚሰማው ኩነቱ በተፈጸመ በሴኮንዶች ውስጥ ነው። ለዚያውም በቪዲዮ ማስረጃ ተደግፎ!!! ስለዚህ እኛ ኢትዮጵያዊያን እሾክን በእሾክ አንደሚባለው እኛም ዘመኑ የቸረንን ቴክኖሎጂ በመጠቀም የተደራጀ፣ የተቀነባበረና ጠንካራ አመራርና ዲሲፒሊን ያለው የህዝባዊ እምቢተኝነት ትግል መጀመር አለብን።
የተቀነባበረ የህዝባዊ እምቢተኝነት ትግል አንዳንዴ በአርተፊሻል ኢንቴሊጀንስና በተወሳሰበ የስለላ መረብ ሊገታ የሚችል ቢሆንም፣በቅርቡ ኔፓል፣ማዳጋስካር፣ፔሩና ሞሮኮ ውስጥ እንደታየው አምባገነኖች ከምንም በላይ የሚፈሩት ህዝባዊ ማዕበል ነው። እኛ ኢትዮጵያዊያን ከላይ ከተጠቀሱት አገሮችና እኛ እራሳችንም በ1966 እና በ2010 ዓም ካደረግነው ትግል ተምረንና የዘመኑን ቴክኖሎጂ ተጠቀመን አገራችን ኢትዮጵያን የህልውና አደጋ ውስጥ ይዞ የገባውን አገዛዝ ማንበርከክ አለብን። እንዲህ ሲባል ግን የአገሪቱን ኃብት ከሚጠቀም መንግስት ጋር የቴክኖሎጂ ውድድር ውስጥ እንግባ ማለት ሳይሆን፣የኛ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ትኩርት ቅልጥፍና ላይና መንግስትን መረበሽና መንግስት የጀመራቸውን አንዳንድ ስራዎች አቋርጦ ቦታውን ለቅቆ እንዲሄድ ማድረግ ላይ መሆን አለበት።
የህዝባዊ እምቢተኝነት ትግል ስትራቲጂንና የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን በተመለከተ ለሚከተሉት አስር ነጥቦት ትልቅ ትኩረት ልንሰጥ ይገባል-
ህዝባዊ እምቢተኝነትን በተመለከተ-
- የህዝባዊ እምቢተኝነት ትግላችን በአንድ መሪ የሚመራ ወይም በግልጽ የሚታይ ከላይ ታች ተዋረድ ያለው አደረጃጀት ሳይሆን፣ለክትትልና ለጥቃት በማያመች መልኩ ያልተማከለ አመራር እንዲኖረው ማድረግ እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው
- የህዝባዊ እምቢተኝነት ትግላችን ከጎዳና ላይ ተቃዉሞዎች ባለፈ ብዙ አይነት ዘዴዎችን መጠቀም አለበት። ለምሳሌ፣የስራ ማቆም አድማ፣የቤት ውስጥ አድማ፣ ቦይኮት ማድረግ፣ ስራ ላይ አለመገኘት ወይም የመንግስት የስራ እንቅስቃሴ እንዲያዘግም ማድረግ፣ምልክቶችንና አጫጭር የትግል ዜማዎችን መጠቀም፣ተመሳሳይ ቀስቃሽ ጽሁፎች ያሉበት ቲሸርት ለብሶ መውጣት፣ትራፊክ መዝጋት ወዘተ የመሳስሉ የትግል እስትራቲጂዎችን እየቀያየርን ብንጠቀም፣አንደኛ በመንግስት ላይ ከፍተኛ ጫና እንፈጥራለን፣ሁለተኛ በመንግስት የአፈና ኃይሎች መጋለጥን እናስወግዳለን
- የህዝባዊ እምቢተኝነት እንቅስቃሴው ሲደራጅ፣አደረጃጀቱ ወይም የአደረጃጀት ሂደቱ መንግስት በቀላሉ በሚቆጣጠራቸው የዲጂታል መረቦች ላይ ሳይሆን፣በቀጥታ ሰው ለሰው በኮሚኒቲ ደረጃ የሚደረግ አደረጃጀት ቢሆን ይመረጣል፣ በተለይ ኢትዮጵያ ውስጥ የስልክ፣የቴሌግራም፣የዋትአፕ፣ የፌስቡክና የኢንስታግራም ግኑኝነቶች መንግስት ሙሉ በሙሉ በሚቆጣጠረው መረብ ውስጥ ስለሚያልፉ ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል
- የህዝባዊ እምቢተኝነት እንቅስቃሴያችን፣ በአንድ በኩል ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ነጻ ሜዲያዎችንና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችን እንዲረድና እንዲደግፍ በተከታታ መማጸን አለበት፣በሌላ በኩል ደሞ አለምአቀፉ ማህበረሰብ ኢትዮጵያ ውስጥ ባለው ጨቋኝ ሥርዓት ላይ የኤኮኖሚ ማዕቀብና ዲፕሎማሲያዊ ጫና እንዲያደርግ ተከታታይ ስራ መስራት አለብን
ቴክኖሎጂን በተመለከተ-
- የህዝባዊ እምቢተኝነት እንቅስቃሴው ሲደራጅና ከመንግስት ጋር ግባ ውጣ ውስጥ ሲገባ፣ ከላይ ታችና ከጎን ወደጎን የሚደረጉ ግኑኝነቶች ሁሉ ከጫፍ ጫፍ ደህንነታቸው በተጠበቀ የግንኙነት መተግበሪያዎች( end-to-end encryption apps) መጠቀም የህዝባዊ እምቢተኝነት ትግሉንከመንግስትክትትልለመጠበቅ በጣም አስፈላጊ ነው
- እኛ ኢትዮጵያዊያን አገር ውስጥም በውጭ አገሮችም ከፍተኛ የፈጠራ ችሎታ ያላቸው የመረጃ ቴክኖሎጂ ሰዎች ስላሉን፣እነዚህ ሰዎች የመንግስት የደህንነት ሰዎች የት እንዳሉ፣የት አካባቢ መንገዶች እንደተዘጉና ባጠቃላይ የህዝባዊ እምቢተንነት እንቅስቃሴ ለማድረግ ለግዜው ከፍተኛ ስጋት ያለባቸው ቦታዎች የት አካባቢ እንዳሉ ለእንቅስቃሴው መሪዎች መረጃ የሚሰጡ የሞባይል ካርታ ስራ መተግበሪያዎችን እንዲፈጠሩና በስራ ላይ እንዲውሉ ማድረግ አለብን።
- የመንግስትን የስለላ መረብ ለመስበር በተለይ የግለሰቦችን ፊት መዝግበው ማንነትን የሚገልጹ ስርዓቶችን ለማደናቀፍ፣ ማስክ መልበስ፣ ካሜራዎች ላይ ሌዘር ማብራት፣ ዣንጥላዎችን መጠቀምና ባጠቃላይ የግለሰቦች ማንነት እንዳይታወቅ ማድረግ አስፈላጊ ነው
- የህዝባዊ እምቢተኝነት እንቅስቃሴው የመንግስትን ፕሮፓጋንዳ ለማክሸፍና በተጨባጭ ትረካዎች ላይ እምነት ለመፍጠር በአርተፊሻል ኢንቴሊጀንስ የታገዘ የእውነት መፈተሽ ስራዎችን በመስራት ህዝብ የቱ እውነት የቱ ውሸት እንደሆነ ለይቶ እንዲያውቅ ማድረግ አለበት
- መንግስት በተደጋጋሚ በዜጎች ላይ የሚፈጽመውን ግፍና በደል ከተቻለ በቪዲዮ በተደገፈ መረጃ ካልተቻለ በጽሁፍ ማስቀመጥ፣ህዝባዊ መንግስት ሲመሰረት ህዝብን የረገጡና በህዝብ ላይ ሰቆቃ የፈጸሙ ኃይሎች ለፍርድ ሲቀርቡ እንደ ማስረጃ ሆኖ ያገለግላል
- የህዝባዊ እምቢተኝነት ትግል ሲካሄድ ብዙ የምንወስዳቸው እርምጃዎች ቢኖሩም፣እነዚህን እርምጃዎች ስንወስድ አርተፊሻል ኢንተሊጀንስና መንግስት የሚዘረጋቸው የስለላ መረቦች ሊተነብዩት እንዳይችሉ ለማድረግ፣ የተለያዩ እርምጃዎችን ስንወስድ እርምጃዎቹን ተከታታይ ባልሆነ መልኩ መውሰድ አለብን( non-sequential)
በቅርቡ በሚገባደደው የፈረንጆቹ አመት 2025 ዓም ብቻ ኔፓል፣ኢንዶኔዥያ፣ሞሮኮ፣ፔሩና ማዳጋስካር ውስጥ ህዝባዊ እምቢተኝነት አንዳንድ አገር ውስጥ መንግስታት ከሥልጣን እንዲወርዱ ሌላው አገር ውስጥ ደሞ ማህበረሰቡ ያልተቀበላቸው ህጎች እንዲሻሩ አድርጓል። በብዙዎቹ አገሮች ውስጥ የህዝባዊ እምቢተኝነት እንቅስቃሴው የተቀነባበረውና የተመራው “ጄኔሬሺን ዚ/Gen Z” በሚባለው የማህበረሰብ ክፍል ነው። “ጄኔሬሺን ዚ” የሚባለው ትውልድ በ1990 እና በ2005 ዓም መካከል የተወለዱና ብዙ የሚያመሳስል ባህሪይ ያላቸውን ሰዎች ያቀፈ ትውልድ ነው። የአጠቃቀም ብዛትና ጥልቀቱ እንደየአገሩ ቢለያይም፣“ጄኔሬሺን ዚ” ዲጂታል ቴክኖሎጂ ሲስፋፋ ተወልዶ ያደገ ትውልድ ስለሆነ፣የኮምፒውተር፣የስማርት ስልክና የማህበራዊ ሜዲያ አጠቃቀሙ ከሱ ቀድሞ ከተወለደው የማህበረሰብ ክፍል የበለጠ ነው። ይህ ትውልድ በማህበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ የሚያደርገው ክትትልና ተሳትፎም ከፍተኛ እንደሆነ ይነገርለታል። አገራችን ኢትዮጵያ ውስጥ የ“ጄኔሬሺን ዚ” ትውልድ በቁጥር እስከ 40ሚሊዮን እንደሚደርስ ይገመታል። ስለዚህ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች፣ሲቪክ ማህበራት፣ምሁራን፣የሰብዓዊ መብት ድርጅቶችና የሴቶች ማህበራት ይህንን ትውልድ ማደራጀትና ቀሪ ህይወቱን ስራ እየሰራ፣ቤተሰብ መስርቶ ትርጉም ያለው ኑሮ መኖር የሚችልባትን ኢትዮጵያን እንዲፈጥር ማዘጋጀት አለባቸው። ኢትዮጵያ ውስጥ ጭቆናና አምባገነንነት እስካልተወገደ ድረስ አፈና፣እስር፣ሞትና ስደት በተከታታይ የሚደርስበት ይሄው የ“ጄኔሬሺን ዚ” ትውልድ ነውና፣ተደራጅቶና ታግሎ አምባገነንትን በማንበርከክ ከማንም በላይ የሚጠቀመውም ይሄው ትውልድ ነው። ስለዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ በአንዳንድ አካባቢዎች ተገድደው የህልውና ትግል ለማድረግ በየጫካው የገቡ ኃይሎች የሚያደርጉት የትጥቅ ትግል እንዳለ ሆነ፣ከሱ በተጨማሪ የህዝባዊ እምቢተኝነት ትግልም በየቦታው ቢስፋፋ የኢትዮጵያን ትንሳኤ ያፋጥናልና፣አገር ቤትም በውጭ አገሮችም የሚገኘው ኢትዮጵያዊ ኢትዮጵያ ውስጥ የህዝባዊ እምቢተኝነት እንቅስቃሴ እንዲጀመር የራሱን አስተዋጽኦ ማድረግ አለበት!!!