ቀሲስ አስተርአየ ጽጌ
nigatuasteraye@gmail.com
ህዳር ፲፯ ቀን ፳፻፲፰ ዓ.ም.
(November 26, 2025)

ለአንባብያን ወገኖቼ ማሳሰቢያ:-
የዚህች ጦማር ዓላማ ሞራላዊ ልዕልናን ለመግለጽ እንጅ ስለ ሃይማኖት ንጽጽር ወይም ስለ ሰው ውድድር ለመናገር አይደለም። የሞራል ልዕልና የመጨረሻ ጽንፍ ቅድስና ነው፡፡ የሞራል ጽንፍ ባለቤትና ምንጭ እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡ በኦርቶዶክስ ክርስትና እምነታችን አምላክ ሰውን ከፍጥረቱ በላይ አክብሮ በአምሳሉ ከፈጠረበት ፍቅሩ ይልቅ ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በነሳው ሰውነት የመጀመሪያ ፍቅሩን ገሐድ ያደረገበት ፍቅሩ የበለጠ አርክቶናል፡፡ ከአይሁድና ከእስልምና ሃይማኖት ከመንለይባቸው ልዩነቶቻችን መሠረታዊውና ዋናው ይህን ነው፡፡ አምላክ ሰውን አክብሮ በአምሳሉ ሲፈጥረው ያሳየውን ፍቅር፣ በአርያው የፈጠረው ሰው ከሰውነቱ ሲወድቅበት ሰው ሆኖ ባዳነበት ፍቅሩ ላይ አምልኮታችንን መስርተን እናመልከዋለን፡፡ ጻድቃን ሰማእታትም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው ሆኖ ሰውን ያዳነበት ፍቅሩ እየጎተተ በክርስቲያኖች አንገት ላይ በተሰነዘረው ሰይፍ እየገቡ አንገታቸውን የሰጡት ሰውን ሲፈጥረው ያሳየውን ፍቅር ሲወድቅበት እንደገና ሰው ሆኖ በማንሳት ያረጋገጠበት ፍቅርን ለመግለጽ ነው፡፡ ከተሰነዘረብት ሰይፍ ሌላውን ለማዳን የራስን አነገት ከመስጠት የበለጠ የሞራል ልዕልና የለም፡፡ የሞራል መለኪያችንም ለሌላ ተላልፎ መሞት ነው፡፡
ቅዱስ ጳውሎስ “ከኃጢአት ጋራ እየተጋደላችሁ ገና ደምን እስከ ማፍሰስ ድረስ አልተቃወማችሁም”(ዕብ 12:4) እንዳለው፣በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ክርስትና የሞራል ልዕልና መለኪያ ሌላውን ከተሰነዘረብት ሰይፍ ለማዳን የራስን አነገት በመስጠት ነው፡፡ በዘመናችን ያለው ቅዱስ ሲኖዶስ ህዝበ ክርስቲያኑን ከተሰነዘረበት ሰይፍ ለማዳን የራሱን አንገት ሊሰጥ ቀርቶ፣ ጥቁር አስለብሶ ሰው አስገደለ እንጅ ሐላፊነቱ የሚመጥነውን ያህል እንደ ተቀዳሚ ሙፍቲ ሀጂ ዑመር ኢድሪስ ዘለቀ “ሰው ሁኑ! ሰው መሆን ይቅድማል!” እንኳን አላለም፡፡ የዚህች ጦማር አላማ በተከበሩ ሐጂ ዑመር የተከሰተውን ሰበነክ ባህርይና በሲኖዶድስ አባላት የተከሰተውን ሰበነክ ባህርይ ለማናጻጸር እንጅ ሰውን ከሰው ሃይማኖትን ከሃይማኖት አበላልጦ ለማሳየት አይደለም፡፡
የጊራራው ንጉሥ አብርሃምን እንደቀደመው፡ የተከበሩት ሐጂ ዑመር ኢድሪስ ዘለቀ ሲኖዶሳችንን ቀደሙት!!!
እግዚአብሔር “ብዙ ተባዙ ምድርንም ሙሏት ግዟትም የባሕርን ዓሦችና የሰማይ ወፎችን በምድር የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ ግዟቸው”(ዘፍ 1፡26፡ 28)፡፡ ብሎ ሰውን ወዶና ከፍጥረቱ በላይ አክብሮ ፈጠረው፡፡ ዘር እየተካ እስኪሞት ድረስ አርሶ ቆፍሮ የሚመገበውን በማምረት፣ በተኬነዎቱ ከማሕጸነ ምድር ፈልቅቆ በሚያወጣው ማእድን ዓለምን ለኑሮው እንድትመቸው አድርጎ በማበጀት እንዲኖርባት በዚህ ዓለም አሰማራው፡፡
ቅዱስ የሚባለው ፓትርያርክና ብጹዐን የሚባሉት ሊቃነ ጳጳሳት ዘር ከማብዛት፣ ከማረስ፣ ከመቆፈር፣ ከመሸመን፣ ወርቅ፣ ብር፣ ብረት፣ እህል ከማምረት፣ የፈረሰ ድልድይ፣ ቤት አጥር ከመጠገንና ከተዘረዘሩት ተግባራት የተለዩት ናቸው፡፡ ከተዘረዘሩት ተግባራት የተለዩት ከሰውነት በተለየ መንገድ ተፈጥረው አይደለም፡፡ ዘር መተካትም ርኩስ ሆኖ አይደለም፡፡ ሕብረተ ሰቡ ዓለምን ከሚያበጅበት ተግባረዕድ የተለዩትም ተግባራተዕዱ ርኩሳት ሆነው አይደለም፡፡ ከመራባቱና በእደ ጥበብ ዓለምን ከመለወጥ የተለየ ለሕብረተ ሰቦች እነሱ ብቻ የሚያደርጉት ብቸኛ አስተዋጽኦ ስላላቸው ነው፡፡
ለዚህ ብቸኛ አስተዋጽኦ ሁለንተናቸው ከተሰራበት ዓለም ለተቀደሰ ተልእኮ ተለይተው እንዲወጡ ተጠርተዋል፡፡ ለተቀደሰው ተልእኳቸው ወደ ዓለም ተመልሰውም ተልከዋል፡፡ ዐለም የሚባለው ከላይ የተዘረዘሩት መሠረታውያን ነገሮችና የሕብረተ ሰቡ ማህበራዊው ትስስር (የፖለቲካው ውስብስብ) ነው፡፡ ቅዱሳና ብጹዐን የሚባሉት የተቀብኦ ስሞቻቸው እንደሚያመለክቱት ፓትርያርኩ በቅድስናቸው ሊቃነ ጳጳሳቱ በብጽዕናቸው ከኔ ቢጤ ተራው ሰውና በመንግሥት አመራር ካሉት ሁሉ ሊቃነ መናብርት ለክርስቶሳዊው ጥሪያቸው የተለዩ ናቸው፡፡
ለክርስቶሳዊ ጥሪ የተለዩ 80 ብጹዐን ሊቃነ ጳጳሳት ስብስብ ተዋቅሮ በቅዱስ ፓትርያርክ የሚመራ ቅዱስ የሚባል ሲኖዶስ አለን፡፡ ይህ ሲኖዶስ “እነዚህን የሚያህሉ ምስክሮች እንደ ደመና በዙሪያችን ካሉልን፣፤እኛ ደግሞ ሸክምን ሁሉ ቶሎም የሚከበንን ኃጢአት አስወግደን የእምነታችንን ፍጻሜ ኢየሱስ ክርስቶስን ተመልክተን በፊታችን ያለውን ሩጫ እንሩጥ”(12፤1) እያለ የሚከተለው ሕዝብ አለ፡፡ ለሕዝባቸው ተላልፈው የተሰውትን ጻድቃን ሰማታትን እንደደመና በዙሪያቸው እንደከበቧቸው አምነው በህዝቡ ላይ የተጫነውን ሸክም ራሳቸው እየተሸከሙ በጻድቃንና በሰማእታት የተገለጸውን የኢየሱስ ክርስቶስን ሰበነክ ፍቅር አባታችን ለሚለው ሕዝብ በመናገርም በተግባርም ተላልፎ በመሞትም ለማሳየት በሲኖዶሱ የተካተቱት ሊቃነ ጳጳሳት የተሰለፉ ናቸው፡፡
በጻድቃንና በሰማእታት ለሕዝበ ክርስቲያን የተገለጸው የኢየሱስ ክርስቶስ ሰበነክ ፍቅር ከክርስትና እምነት ውጭ ያሉትን አይመለከትም፡፡ ከብሉያቱና ከሐዲሳቱ ይልቅ እጅግ በዝተው ግምጃቤቶቻችንን አጣበው የያዙት ከስንክሳሩ ጀምሮ የጻድቃንንና የሰማእታትን ተልእኮ የሚገልጹ ከኦርስቶዶክሳውያን መንፈሳውያን ውጭ ያሉትን አይጨምርም፡፡ የፊደል ዘር ከለየን በኋላ ንባብ ውርድ ንባብ እንድንማር የምንጠቀምባቸው ከስንክሳሩ ጀምሮ ያሉት ሁሉ መጻሕፍት ጻድቃንንና ሰማእታት ስለሰው እየተላለፉ መሰዋታቸውን የሚገልጹ ናቸው፡፡ አባቶቻችን ይህን ስርአተ ትምህርት የዘረጉልን የማንበብ ችሎታችንን እንድናዳብርባቸው ብቻ ሳይሆን ጻድቃን ሰማእታት በህወታቸው ያሳዩትን ፍቅር በሕሊናችን ለመቅረጽ ጭምር ነበር፡፡
ለዚህ ታላቁ ምሳሌወቻችን ከሕብረተ ሰቡ የተገለሉለት “… አንድ ሰው ባንተ አንዳይሰናከል ያለ ሐሜት ኑር፡፡ ሕዝባዊ ለራሱ ያስባል፡፡ አንተ ግን ከባድ ሸክም ተሸክመሐል…(ፍ አ 5፡120) ተብሎ በቀኖና መጽሐፋችን እንደተገለጸው ሕብረተ ሰቡ ሊሠራው የማይችለውን የጎደለውን ለመሥራትና ለመሙላት የተሰማሩት ቅዱስ ፓትርያርክና ብጹዐን ሊቃነ ጳጳሳቱ ነበሩ፡፡
ከህዝቡም ከሕዝባውያን ሊቃነመናብርትም የከበደ ተጠያቂነትን የሚያስከትልበት በፓትርያርኩ በሚመራው ሲኖዶስ ላይ የሐላፊነት ከባድ ሸክም እንደተሸከሙ መጽሐፈ ቀኖናችን ይገልጸዋል፡፡ ሕዝብ እያመረተ ዘር ለማስቀጠል ለትዳሩ ለልጁ ለንብረቱ በሚያደርገው ትኩረት ያንዣበበትን የሕይወት አደጋ አሻግሮ ለማየት አቅም ያንሰዋል፡፡ መጽሐፉ “ሕዝባዊ ለራሱ ያስባል፡፡ አንተ ግን ከባድ ሸክም ተሸክመሐል” እንዳለው፦ ፓትርያርክና ብጹዐኑ ሊቃነ ጳጳስቱ ከማነኛውም የእጅና የጉልበት ሥራና ከማነኛውም ቆሳቁሳ ነክ ከሆኑ ተግባራት የተገለሉበት ዋና ምክንያት ከሕዝባዊ ትኩረት ያመለጠውን፣ ያንዣበበትን መከራና ስቃይ አስቀድሞ በማየት ተላልፎ ለመሞት ነበር፡፡
“ሰው ሁኑ! ሰው መሆን ይቅደም!” እያሉ ብቅ ያሉት ክቡር ሐጂ መፍቲ ዑመር ጻድቃን፣ ሰማእታትን እየጎተተ ለሞት ከዳረጋቸው ክርስቶሳዊ ፍቅር ሩቅ ናቸው። ይህን መግለጽ የሚገባቸው ቅዱስ ፓትርያርክና ብጹዐን ሊቃነ ጳጳሳት ከገዳይ ጋራ ተባበሩ እየተባሉ በሚከሰሱበት ወቅት የተከበሩ ሐጂ “ሰው ሁኑ! ሰው መሆን ይቅደም!” እያሉ ከመስጊዳቸው ብቅ ማለታቸው ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በስንክሳሯ የምትመዘግበው ተአምር ሰሩ፡፡ በክርስትና እምነታችን ክርስቶስ ሰው ሆኖ ያዳነበትን ፍካሬ አድርገው መምጣቸው በዘመናችን ያሉትን ሁሉ ጳጳሳት ምቱራን አድርጓቸዋል፡፡
በቀኖናችን መሠረት ወደ ተልእኮው ስምሪት ገብቶ ተልእኮውን መፈጸም ያልቻለውን ፓትርያርክንም ሆነ ሊቀ ጳጳስን፦ ሰው ሆኖ ተጸንሶ ሞቶ ከተወለደ ውራድ ጋራ በማነጻጸር የቀኖናችን መጽሐፍ ምቱር ብሎ ይገልጸዋል፡፡ ከላይ እንዳልኩት ከሁለቱም ማለትም ከይሁዲውም ከእስልምናውም የምትርቅበት “ወአስተዋህዶተ መለኮቱ ምስለ ሥጋነ ይትነከር ፈድፋደ እምቀዳሚ ኀበ ዘቦቱ ልብ”(ሃ 61፡32)፡ እግዚአብሔር ሰውን በአርያው ከፈጠረበት ፍቅሩ፡ ሰው ሆኖ ያዳነበት ፍቅሩ ይበልጣል” ጻድቃን ሰማዕታትን ላካባቢያቸው ሕዝበ ክርስቲያን እየተጋረዱ እንዲሞቱ በህዝበ ክርስቲያን አንገት ላይ ለተሰነዘረው ሰይፍ አንገታቸውን እየሰጡ የሞቱት ለክርስቶስ ያላቸውን ፍቅር ለመግለጽ ነው፡፡ ይህን የማይገልጽ ፓትርያርክና ሊቀ ጳጳስ ምቱር ነው፡፡
ሕብረተሰብ እየመገበ ትውልድ ለመተካት የገባበት ውጥረት ትኩረቱን አሟጦ ስለሚወስድበት ከውጭ የሚመጡበትን ረቂቅና ጉሉህ አደጋወች አሻግሮ ለማየት ሰአትና ትኩረት ያጥረዋል፡፡ የሃማኖት ሰወች ከባተሌው ሕዝብ አስቀድመው በማየት ህዝቡ እንዲከላከልና እንዲነቃ የማድረግና ካስፈለገም ራሳቸው ከህዝቡ በፊት ቀድሞ የመሞት ኃላፊነት አለባቸው፡፡
መጽሐፈ ቀኖናችን “ኤጲስ ቆጶሠ ዘነስአ ክህነተ እመግዚአብሔር ከመ ይዕቀብ ሥጋ ወነፍስ እም ኀጉል፡ በከመ ነፍስ ትከብር እምሥጋ፡ ከማሁ ክህነትኒ ትትሌዐል በክብር እመብግሥት፡ ወይእቲ ተአሥሮ ለዘይደልዎ ኩነኔ፡፡ ወትፈትሆ ለዘይደልዎ ፍትሐት፡፡ ለዘይትቃረና ለክህነት ይፈደፍድ እምኩነኔሁ ለዘይትቃረንዎ ለንግሥ”(ፍ አ 9፡289)፡፡ እንዳለውም፦ መሬት ያፈራችውን እኩል ለማስተንተን ከተሰለፉት ከፖለቲከኞችም ይልቅ ለሚመሩት ሕዝበ ክርስቲያን ተላልፎ የመሞት ግዴታ ያለባቸው የሃይማኖት መሪወች ናቸው፡፡ የጊራራው ንጉሥ አብርሃምን እንደቀደመው፡ የተከበሩት ሐጂ ዑመር ሲኖዶሳችንን ቀደሙት፡፡
ካራን በሚባለው አገር ሰው ሁሉ ሰውነቱን ክዶ፡ ወደ አውሬነት ተለውጦ፡ ሰው በጠፋበት ዘመን አብርሃም የካራንን ጣዖት አራግፎ ከዘመዶቹ በአካልም በመንፈስም ተለይቶ በመራቁ ከትድግና ቅድጅት ጋራ ከሰው ሁሉ በላይ ከፍ ብሎ ነበር (ዘፍ 11፡31_12፡1_5) ፡፡ አብርሃም የተቀዳጀውን ትድግና ረሳ፡፡ ሳራንም ለመከራ ዳረጋት፡፡ የጊራራውንም ንጉሥ ዋሽቶ ከስህተት ላይ እንዲወድቅ አደረገው፡፡ ከፍ ካለበት ክብር እራሱን አዋረደ፡፡ አብርሃም እሻላለሁ ብሎ ከሚያስበው ከጊራራው ንጉሥ እግር ሥር ወደቀ፡፡ የጊራራው ንግሥ “ይህን ያደረክብኝ ለምንድነው? ምን ክፉ ሥራ ሠራሁብህ ? ምን አይተህ ነው? ባመጣሀው ኃጢአት የማይገባ ሥራ በኔ ሠራህብኝ? (ዘፍ 20፡9_10) ብሎ አብርሃምን ከሰሰው፡፡
ሰው በጠፋበት ዘመን “ሰው ሁኑ” እያሉ ሰውነት በሌለው ሕብረተሰብ መካከል ስለተከሰቱት ክቡር አባታችን ሐጂ ሙፍቲ ዑመር ልዕልና ስመሰክር ለምሳሌ የምጠቅሳቸው እሳቸው የሚስማሙባቸውን ከክርስትና በፊት የነበሩትን ኖኅን፣አብርሃምንና የጊራራውን ንጉሥ ነው፡፡
“ከኃጢአት ጋራ እየተጋደላችሁ ገና ደምን እስከ ማፍሰስ ድረስ አልተቃወማችሁም”(ዕብ 12_4) የሚለውን ሐዋርያዊ ትውፊት በቃል ማስተማር በተግባርም ማሳየት ግዴታ የነበረባቸው ጳጳሳት ነበሩ፡፡ ዛሬ በዘመናችን በኃጢአት ተጠቅልለው የህዝበ ክርስቲያኑን ደም ከሚያፈሰው ጋራ የተስማሙ ናቸው፡፡ እኛ ኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች ክርስትና ባዘዛቸው መሠረት ጻድቃን ሰማእታት ለሰው ልጅ የገለጹትን ርቆ የሄደውን ክርስቶሳዊ ፍቅር በየእለቱ የምናነበው እስልምናውም ሆነ ይሁዲም አይጋሩንም፡፡ የክቡር ሀጂ ዑመርን ሥነ ሕሊና አተኩሬ ስመለከት፦ ብጹዐን ቅዱሳን ነን ከሚሉት ይልቅ ክቡር ሀጂ ዑመር መጥቀውና ልቀው በመካከላችን ብቅ ብለው ታዩኝ፡፡
የጊራራው ንጉሥ “የሚባርኩህን እባርካለሁ የሚረግሙህን እረግማለሁ የምድር ነገዶች ሁሉ ባንተ ይባረካሉ” (ዘፍ 12፡3) ተብሎ በእግዚአብሔር ለአብርሃም የተገባለት የትድግና ቃል አልነበረውም፡፡ አብርሃም ይህን አምላካዊ የትድግና ቃል ኪዳን ረስቶ፦ ራሱን ከሞት ለማትረፍ ሲል የሣራን ሚስትነት ክዶ “በገባንበት አገር ሁሉ ወንድሜ ነው እያልሽ በመናገር ወሮታ ዋይልኝ” ብሎ መልሶ በማይከፍላት ውለታ ከፍኖ ራሱ ሊገባበት በፈራው መቃብር ቀበራት፡፡ አብርሃም ለሳራ የነበረውን ሐላፊነት ክዶ ሳራን አሳልፎ ለመከራ ዳርጎ እንደቀበራት፦ የአዲስ አበባው ሲኖዶስ ለሕዝበ ክርስቲያን ተላልፎ መሞት ያለበትን ክርስቶሳዊ ግዴታና ሀላፊነት ሸሽቶ በራሱ ጥቁር ቀሚስ ክፍኖ ሕዝበ ክርስቲያኑን ቀበረው፡፡ አብርሃም ራሱን ለማዳን ሲል ከሣራ ጋራ በናት ባይገናኙም ባባቱ በኩል የነበራትን እህትነት ብቻ በመጠቀም ሚስትነቷን እንደካዳት በፓትርያርኩ የሚመራው የትግራይ ሲኖዶስ ከትግራይ ውጭ ያለው ሕዝብ በቋንቋና በገጸምድር ባይገናኝም በዜግነት በሥጋና በደም የነበረውን ትስስር ካደው፡፡ የትግራይን ሕዝበ ክርስቲያን ከመላ አካሉ ከኢትዮጵያ ህዝበ ክርስቲያን በክልል ከፈን ጠቅልሎ ቀበረው፡፡
በኦርቶዶክስ ገዳማዊ ስርአተጸሎት “ወበከመ ዐቀብከነ እምነግህ እስከ ሰርክ፤ ወእምሰርክ እስከ ነግህ” ብለን ጸሎት እንጀምራለን፡፡ ይህም ማለት፦ አገር ሰላም ሆኖ፡ ክፉ ነገር ሳንሰማ ሌሊቱን በሰላምና በጤና ተኝተን ጧት ከእንቅልፋችን ስንነቃ፡ ሌሊቱን በሰላም ጠብቀህ እንዳሳደርከን፡ ቀኑንም በሰላምና በጤና ጠብቀህ አውለን” ማለት ነው፡፡ ይህ ስርአተ ጸሎት ትኩረታችን ከህብረተሰብ እንዳያፈነግጥና አቅማችን የፈቀደልንን ሐላፊነት መወጣት እንዳያመልጠን የሚያሳየን ነው፡፡ እኛ ፖለቲካው ውስጥ ላለመግባት ስለ አገር፣ ስለ ሕዝብ መስማት አንፈልግም የሚሉ አንዳንድ ሰወች ገጥመውኛል፡፡ ይህን የሚሉ ወገኖች፦ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “በመሸ ጊዜ ሰማዩ ቀልቷልና ብራ ይሆናል ትላላችሁ፡፡ማለዳም ሰማዩ ደመና ሆኗል ትላላችሁና ዛሬ ይዘንባል ትላላችሁ፡፡ የሰማዩን ፊትማ መለየት ታውቃላችሁ፡፡ የዘመኑንስ ምልክት መለየት አትችሉምን?”(ማቴ 16፡2) ብሎ ጸሐፍት ፈሪሳውያንን ከጠየቃቸው በኋላ ክፉና አመንዝራ ትውልድ ብሎ የሰነዘረባቸውን ተግሳጽ የተገነዘቡ አይመስለኝም፡፡ ከነሱ የከፉም ተስለክላኪ እባቦች በቤተክርስቲያናችን አሉ፡፡ እባብ ከሚሰነዘርበት ብትር ራሱን ጠብቆ በፈራረሱ ካቦች መካከል እየተስለከለከ መርዙን ይረጫል፡፡ ሰው መሳይ ተስልከላኪ እባቦች ባንድ ወቅት በኢትዮጵያና በአሜሪካ፣ በሌላ ወቅት በመንግሥትንና ሲኖዶሱ መካከል እየተስለከለኩ ከሁለቱም ብትር ራሳቸውን ጠብቀው በህብረተሰቡ ሥነ ልቡና ላይ አደንዛዥ መርዛቸውን የሚረጩ አሉ፡፡
እነዚህንና የመሳሰሉትን እየታዘብኩ ባደኩበት ገዳማዊ ስርአተጸሎት ልማድ፡ በኢትዮጵያ ህዝብ በተለይም በቤተ ክርስቲያን ላይ ምን ተፈጽሞ ይሆን በማለት ታላላቅ ሚድያወችን ሳልቃኝ ወደ ጸሎት አልሄድም፡፡ ምንም እንኳ በክርስቲያኖች ላይ የሚካሄደው ግድያ የቆመበት ቀንና ወር ባይኖርም፦ በዚህ ሳምንት አርሲ በሚኖሩት ሰወች ላይ የተፈጸመውን ጭፍጨፋ ከተለያዩ መገናኛወች ሰማሁ፡፡ ለዚህ ሁሉ ተጠያቂው መንግሥት ቢሆንም፡ የክርስትና እምነታችን እንደሚያዝዘው ከፓትርያርኩ ጀምሮ ሊቃነ ጳጳሳቱ ለክርስቶስ ያላቸውን ታዛዥነትና ፍቅር የሚገልጹት በሕዝበ ክርስቲያኑ ላይ የመጣውን ሞት እነሱ ቀድመው በመሞት ብቻ ነው፡፡ ሕዝበ ክርስቲያኑ በዚህ ግንዛቤ በሚደርስበት መከራና ሥቃይ ከመንግሥት በፊት ተጠያቂወች የሚያደርገው ፓትርያርኩንና እሳቸው የሚመሩትን ሲኖዶሱን ነው፡፡ እኔ ገደልኩ የሚል ባይኖርም ከመንግሥትም ሆነ ከግል ሚድያወች በየሰአቱ የምንሰማው የኢትዮጵያ ሕዝብ በተለይም የኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖችን መጨፍጨፍና በህይወት የተረፈው ሕዝብ በሞተው ሬሳ እየተደናቀፈ ወደቀ ሲባል ነው፡፡
ፓትርያርኩ ምለው በትረ ክህነቱን ሲጨብጡ ከራሳቸው እስከ ጥፍራቸው የተቀዳጁት በደስታ ጊዜ የሕዝቡን ይባቤ ለማንጸባረቅ፣ ይህን በመሰለ ጊዜ ደግሞ በህዝብ ላይ የመጣውን ሞት ሞተው ተክፍነው ሊቀበሩበት ነበር፡፡ ለህዝብና ለክርስቶስ ያላቸውን ፍቅር በሞታቸው ሊገልጹት ይቅርና የተነጠፈላቸው የቅንጦት ሥጋጃ ፓትርያርኩን ጠልፎ እንደጣላቸው በመገናኛ ተነገረን፡፡ ምነው ባይናገሩት ምን ያስተምራል ብለው ተናገሩት? እያልኩ በተናጋሪወች እያዘንኩ ሳለሁ፦የቤተ ክህነቱ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ የነበሩት ብጹዕ አቡነ አብርሃም በውጭም በውስጥም ባለው ህዝበ ክርስቲያን ቁስል ላይ እንጨት ሰደዱበት፡፡
በዚህ እድሜ ያሉት ፓትርያርኩ መውደቅ የተጠበቀ ነው፡፡ የሳቸው መውደቅ በዙርያቸው ያሉትን ምንደኛነት ያጋለጠ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ከተወለዱባት መንደር ጀምሮ በመላ ኢትዮጵያ ያለው ሕዝብ ሬሳ እያደናቀፈው በመውደቅ ላይ ሳለ፦ አንድ ቀን በሕዝብ መካከል ተግኝተው ሰው አጽናኑ ሳይባል የቆሙበት የክብር ሥጋጃ አድናቅፏቸው ወደቁ የሚለውን መስማት አሳፋሪ ሲሆን፦ መውደቃቸውን በመጠቀም ደባ ለመስራት የተሰለፉ ሰወች ነበሩ የሚለውን መስማት ደሞ እጅግ የሚዘገንን ነው፡፡
ራሳቸው አቡነ አብርሃም የቤተ ክህነቱ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ አቡነ ጴጥሮስ የሲኖዶሱ ጸሐፊ ሆነው የቤተ ክርስቲያኗን ቁልፍ ከፓትርያርኩ ሲረከቡ ከመንበረ ፓትርያርኩ ላይ ቆመው ሁለቱም ሞት እንጅ ማንም አይለያየንም ለቤተ ክርስቲያናችን ለህዝባችን እንሞታለን ብለው ቃል በመግባት ከፓትርያርኩ እግር ሥር ወድቀው ተነስተው በሙሉ ልብ ተናግረው ነበር፡፡ ሁለቱም የገቡትን ቃል ካዱ፡፡ ሞት ሳይሆን በራስ ወዳድነት ተልያዩ፡፡ አቡነ ጴጥሮስ ከውጭ ሆነው እኛ ስንናገረው የነበረውን መልሰው መናገር ጀመሩ፡፡ አቡነ አብርሃም ደግሞ ከውስጥ ሆነው እኛን በሚከሱበት ክስ አቡነ ጴጥሮስንም ደርበው በመክሰስ ኑና ሙቱልን እያሉ መሳለቅ ጀመሩ፡፡
የአቡነ አብርሃም ስላቅ ለብልጽግናው ፖለቲካ ሊስማማ ቢችልም፤ ከኦርቶዶካስዊት ቀኖና ጋራ ግን በከፍተኛ ደረጃ ተጋጭቷል፡፡ አቶ ሲሳይ አጌና አቡነ አብርሃም ከቀኖናው ጋራ መጋጨታቸውን ሳይመለከት በሰሞኑ ንግግራቸው ተደንቆ አቡነ ጴጥሮስን ዝቅ አቡነ አብርሃምን ከፍ በሚያደርግ ንጽጽር ያቀረበበትን ፈሊጥ አየሁት፡፡ በበኩሌ ሁለቱም የፖለቲካውንና የቀኖናውን ሂደትና ይዘት የተረዱ አይደሉም፡፡ አቶ ሲሳይ እንዳለው ሁለቱም የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት የሚጥሩ አይደሉም፡፡ ሁለቱም ያላቅማቸው የተሰለፉ ግራ የገባቸውና ራሳቸውን ብቻ ለማዳን የሚቃትቱ ናቸው፡፡ ለሁለቱም ልናዝንላቸው ይገባል እንጅ በሁለቱም አቋም የኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ኩለንተና መለኪያ ማድረግ ፍጹም መሳሳት ነው፡፡
አቶ ሲሳይ እንዳለው፦ “በሐምሌ ወር 2017 ቀርበው ችግሩን እንዲነግሩን እድል ሰጥቻቸው አልቀረቡም፡፡ ታዲያ በየትኛው ሞራላቸው ብቃታቸው እና መንፈሳው ልዕልናቸው ነው አሁን አፋቸውን የሚከፍቱት? “ የሚለው አቡነ ጴጥሮስን የሚመለከት ይመስለኛል፡፡ “በመንፈሳዊ ልምድም በእውቀት ክምችትም ልቀውና ርቀው የሄዱትን በመንበሩ ያሉትን መውቀስ የሚችሉትስ እነ ማናቸው?” በማለት የተጋረፈው እኔንና ከቀኖናው ጋራ ተጋጭታችኋል የሚሉትን የሚመለከት መሰለኝ፡፡
አቶ ሲሳይ በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ተጠምቆ ያደገ ቢሆንም፡ ቀኖናችን “ኢይጸአሉነ ሕዝብ ነኪራን እለ ውጹአን እምኔነ”(ሥ/ ቅ ) ከሚላቸው አንዱ ነው፡፡ አቶ ሲሳይ የሚያወቀው ፖለቲካውን ነው፡፡ አቡነ አብርሃምን ከፍ፣ አቡነ ጴጥሮስን ዝቅ አድርጎ እንዲናገር የዳረጉት የአበኑ አብርሃምና የአቡነ ጴጥሮስ መካካድ ነው፡፡ ሁላችንንም እንዲገርፈን ጅራፉን ያቀበለው የአቡነ ጴጥሮስና የአቡነ አብርሃም መካካድ ነው፡፡ ከፓትርያርኩ ቡራኬ ተቀበልን ብለው ላለመካካድና ለህዝብ ተላልፈው ለመሞት መወሰናቸውን ክደው በቦታም በሀሳብም ተራርቀው እርስ በርሳቸው መቃረናቸው ሁላችንንም እንዲገርፈን ለአቶ ሲሳይ አመቻችተውለታል፡፡ የኢትዮጵያን ህዝብ በመካዳቸው እርስ በርስ በመክካዳቸው አቶ ሲሳይንም በማሳሳታቸውና እኛንም በማስገረፋቸው አቡነ ጴጥሮስና አቡነ አብርሃም እጽፍ ድርብ ኃጢአት ሰርተዋል፡፡
አቶ ሲሳይ አጌና ባወቀውና በተረዳው በመናገሩ አልፈርድበትም፡፡ ሆኖም ግን ቤተ ክርስቲያናችን ሁለቱንም አቡነ ጴጥሮስንም አቡነ አብርሃምን የምትተረጉማቸው እኩል ነውና የአቶ ሲሳይ ከፍና ዝቅ አርጎ ማቅረብ ከቀኖናችን ጋራ ተጋጨ፡፡ ሁሉም ከሀዲወች ናቸው፡፡ ሁሉም ውሸታሞች ናቸው፡፡ ሁሉም ወደ ጵጵስናው የመጡት ክብሩን ሞገሱን ገንዘቡን ቅንጦቱ ፍለጋ እንጅ የጵጵስና ተልእኮ የሚጠይቀውን ከሕዝበክርስቲያኑ በፊት መሞታቸውን ተረድተው አይደለም፡፡ በዚህ መንገድ ወደ ጵጵስናው የሚገቡት ሁሉ መስዋዕትነት ሊከፍሉ ቀርቶ እነሱ ሊሰሩት ይገባቸው የነበረውን ለመስራት የሚጥሩትን ክርስቲያኖች ለማስገደል እንደሚጥሩ ቀኖናችን “… ይቀጽብ ሰብአ ላእሌሆሙ ወያሥተናሰ ወየሀሥሥ ሞቶሙ…” (ፍ አ 10፡ 385) ብሎ እነሱንና የመሳሰሉትን ገልጿቸዋል፡፡ እንደነዚህ ያሉት አባቶች ከነሱ በሞራልና በእውቀት ተሽለው የተገኙትን ከገዳይ ጋራ በመተባበር እየጠቆሙ ያስገድላሉ፡፡ አቡነ ጴጥሮስም የሸሹት አቡነ አብርሃም ጠቁመው እንደሚያሳስሯቸው በመረዳታቸው ይመስላል፡፡ በዚህ ሁኔታ ሁሉም የሚጠበቅባቸውን ሆነው አልተገኙም፡፡ በራሱ ሕሊና ተመዝኖ የወደቀውን የቀድሞውን አብርሃምን መሰሉ፡፡
“በዚህ ስፍራ እግዚአብሔርን መፍራት በእውነት እንደሌለ ለሚስቴ ሲሉ እንደሚገሉኝ ስላሰብኩ ነው”(ዘፍ 20፡11)፡፡ ብሎ በተናገረው አብርሃም ሲመዘን ከራሱ ሕሊና ሁለት ጊዜ ወደቀ፡፡ የፈጣሪውን ትድግና ረሳ ሣራንም ለራሱ ሕይወት ቤዛ አድርጎ አሳልፎ ሰጣት፡፡ እንደ አብርሃም የሚደገፍበት መለኮታዊ ቃል ኪዳን ያልነበረው የጊራራውን ንጉሥ “ይህን ያደረክብን ለምንድነው? ምን ክፉ ሥራ ሠራሁብህ ? በኔና በመንግሥቴ ላይ ባመጣሀው ኃጢአት የማይገባ ሥራ በኔ ሠራህብኝ? ምን አይተህ ነው? (ዘፍ 20፡9_10) ብሎ ከአብርሃም ተሽሎ አብርሃምን እንደወቀሰው፦ ክቡር ሀጂ ዑመር ከወያኔወች ጋራ ተባብራችሁ በአማራና በኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ስብራት ያመጣችሁባቸው ምን በደሏችሁ? እያሉ እነአቡነ ማትያስን በመውቀስ ላይ ናቸው፡፡
ከአብርሃም ተሽሎ እንደተገኘው እንደ ጊራራው ንጉሥ ለመሳሰሉ እንደ ሙፍቲው ላሉት ታላላቅ ሰወች የቤተ ክርስቲያናችን ቀኖና ትልቁን ክብር ይሰጣቸዋል፡፡ በመካራ በጭንቅ ጊዜ በህዝብ ላይ ካንዣበበው ሞት በነገረተጥባብ በማምለጥ ራሳቸውን ያሻገሩ ጳጳሳት፤ መከራው አልፎ የመረጋጋት ዘመን ሲመጣ፡ ጳጳሳት ነበርን፡፡ አሁንም ነን ብለው እጃቸውን በመጫን የእግዚአብሔር ረድኤተጸጋ በሰጣቸው ቆራጥ ውሳኔ የተቀዳጇትን ጽድቅ እንደ ሙፍቲ ዑመርና አቶ ታዴወስ ታንቱ ላይ እጃቸውን በመጫን እንዳያረክሷት ቀኖናችን “ኢያንብሩ ላዕሌሁ እደ ለመልእክተ ዲቁና ወቅስና እስመ ሎቱ ክብረ ቅስና በተአምኖ ዘስምዕ” (ፍ አ 9፡ 278) ሲል ያስጠነቅቃል፡፡
ይህም ማለት ክርስቲያኖች ሲታረዱ በተባበሩና ዝም ባሉት ጳጳሳት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እንዳትለካ እንጅ አንድ ሰው ከኦሪቱ በፊት አብርሃም በእምነቱ ያስቆጥራትን ክርስቶስ በጥምቀት ያወጃትን ጽድቅ በጥምቀት መተባበሩን ሳይመሰክር ይቀድስ፣ ያጥምቅ፣ ያቁርብ ማለት አይደለም፡፡ ያም ሆነ ይህ የተከበሩ ሙፍትው በመከራ ዘመን የሚያስከፍለውን ተግዳሮት ፈርተው ሕዝቡን ቆመው በማስገደል ላይ ካሉት ከዘመናችን ሊቃነ ጳጳሳት ተሸለው የተገኙ ብጹዕ መባል የሚገባቸው ናቸው፡፡ “ኢያንብሩ ላዕሌሁ እደ ለመልእክተ ዲቁና ወቅስና እስመ ሎቱ ክብረ ቅስና በተአምኖ ዘስምዕ” (ፍ አ 9፡ 278) ብሎ ቀኖናችን በሚፈቀደው መሰረት በሕይወት ቢኖሩ ይጠመቁና ያለ እነ አቡነ አብራሃም አንብሮተዕድ “ሰው ሁኑ! ሰው መሆን ይቀድማል!” የሚለውን ምስክርነት እንዲቀጥሉ በመንበሩ ላይ ይቀመጡልን በማለት እግራቸው ላይ ወድቀን እንለምናቸው ነበር፡፡
እግዚአብሔር ይህን የመከራ ዘመን አሳጥሮ የሙፍቲውን ታሪክ በስንክሳራችን ለሚመዘግቡ “ኃያላን ይጽሕፉ ጽድቀ” ለተባሉት እውነት መዝጋቢወች የተረጋጋ ዘመን ያምጣ፡፡