አፋር ውስጥ በየጊዜው እየተምቦገቦገ የሚታዬውና ለቱሪስት መስህብነት ሳይቀር እያገለገለ የሚገኘው ኤርታሌ ትርጉሙ የሲዖል ወይም የጀሃነም በር መግቢያ እንደሆነ በሚዲያ ሲነገር ሰምቻለሁ፡፡ ለዚያ ነው ለዚህች መጣጥፌ ይህን ስያሜ የመረጥኩት፡፡
እንደ እውነቱ ከሆነ ኢትዮጵያ የሲዖል በር ሳትሆን ራሷ ሲዖል ከሆነች ቆዬች፡፡ ያለፉት 50 ዓመታት ብዙ ነገር አሳይተውናል፡፡ ደረጃው ይለያይ እንጂ በተለይ ከ1967 ዓ.ም ወዲህ የሚስተዋለው ሀገራዊ ሁኔታ እጅግ አስገራሚና ለመስማትም የሚሰቀጥጥ ነው፡፡ ያለፉት ሰባተት ዓመታት በተለይ የተለዩ ናቸው፡፡ ያለፈባቸው ያውቃቸዋል – ኅሊና ካለውና ራሱ ባይቸገር የሌሎች ችግር የሚገባው ከሆነ ማለቴ ነው፡፡
ለድርጊቱና ለተፈጥሮው ስም የማጣለት አቢይ አህመድ ሥልጣኑን በማጭበርበርና በአፍ ጂዶ ከተቆጣጠረ ወዲህ ኢትዮጵያ አለች ማለት አንችልም፡፡ በስሟ እየነገዱ በተግባር ግን ኢትዮጵያን ድራሹዋን እያጠፉ የሚገኙት አቢይና መንጋው አማራንና የአማራ ወዝና መዓዛ አለበት የሚሉትን ሁሉ እያወደሙ መጥተው የሚቃዡባትን የኦሮምያ ሪፓብሊክ ለመመሥረት የቀራቸው ጊዜ በጣም አጭር ነው – ያላሰቡት ነገር ካላሰቡት አቅጣጫ መጥቶ ዕቅዳቸውን ካላጨናገፈባቸው በስተቀር አካሄዳቸው ሁሉ አስፈሪ ከመሆኑም ባሻገር ከፈጣሪያቸው ከሊቀ ሣጥናኤል የሚያገኙት እገዛም ቀላል እንዳለመሆኑ ፍላጎታቸው አይሰምርም ብሎ ማመን ወደ ጅልነት የሚያዘነብል አደገኛ አስተሳሰብ ነው፡፡
በእስካሁኑ እሳቤያችን አምላክ ኢትዮጵያን ጥሎ እንደማይጥላትና በመጨረሻው እንደሚያስባት ማመናችን መልካም መሆኑ እንዳለ ሆኖ አንዳንዴም “ጠርጥር ገንፎም አለው ስንጥር” እንዲሉ ነውና የመጥፋት ጠማማ ዕድል ሊያጋጥመን እንደሚችል መገመቱም መጥፎ አይደለም፡፡ ዕድል ሲጠም የመቶ ዓመት ጦርነትና ዕልቂትም ያጋጥማል፡፡ ለዚህ ደመግሞ ብዙ ዋቢዎችን መጥቀስ እንችላለን፡፡
ሦርያውያንን፣ ሰሜን ኮሪያውያንን፣ ባቢሎናውያንን፣ አፍኒስታውያንን፣ ሶማሌያውያንን፣ ሊቢያውያንን፣ ዩጎዝላቪያውያንን፣ ኡክሬናውያንን፣ ራሽያውያንን፣ ሜሶፖታሚያውያንን፣ ኢራቃውያንን፣ ኢራናውያንን፣ የመናውያንን፣ ፍልስጥኤማውያንን፣ እሥራኤላውንን፣ ወዘተ. እግዚአብሔር ነው የፈጠራቸው፡፡ ኅሊናችንን በአግባቡ ተጠቅመን ራሳችንን ማለትም ውስጣችንን ከፈተሸን ኢትዮጵያ ከነዚህ ሀገራትና ሕዝባቸው ለፈጣሪ የተለዬ ቀረቤታ የላትም፡፡ ስለሆነም መጥፋት ከዚህም በላይ አለ ብለን እስካልተጽናናን ድረስ በበኩሌ አሁን ላይ አልጠፋንም ብዬ መዋሸት አልፈልግም፡፡ በቁምም ቢሆን ጠፍተናል፡፡ 130 ሚሊዮን የሚገመት የተደገመበት በግ በአንድ እዚህ ግባ በማይባል ማይም ፍየል ሲደናበርና ይገባበትን አጥቶ በየቀኑ ሲያልቅ ማየት ዘግናኝ የታሪክ ምፀት ነው፡፡ ደህና ሰው ቢያጠፋኝ እመርጣለሁ – መሞት እንኳን ካለብኝ፡፡ በዚህን የመሰለ የሚያደርገውን ቀርቶ የሚናገረውን በማያውቅ ዕብድ መጨቆኔም ሆነ መገደሌ ያሳዝነኛል፡፡
ያጠፋን ሰው – አቢይ የሚባለው ሰው መሳይ ጭራቅ – የጥፋት ተልእኮን መቶ ከመቶና ከዚያም በበለጠ ከማከናወን አንጻር ተፈጥሮው ልዩና እንደምንንቀው ያህል አለመሆኑን በዚህ አጋጣሚ ባስታውስ ደስ ይለኛል፡ አቢይና ሰይጣን በርህራሄ በፍጹም አይገናኙም፡፡ ሰይጣን ከአቢይ አኳያ ሲታይ ገርና የዋህ፣ ሩህሩህና ቸር ነው፡፡ አቢይ ግን “ሰይጣን” ለመባል ራሱ እጅግ የሚያንስበት፣ ክፋቱና አስመሳይነቱ፣ ጭካኔውና ከሃዲነቱ ከሰይጣን ጋር ፈጽሞ ሊወዳደር የማይችል ዐረመኔ ነው፡፡ ይህን ጭራቅ ለመግለጽ የየትኛውም ሀገር ቋንቋ አይችልም፡፡ አዲስ ቃል መፈጠር አለበት፡፡ እና ሰዎች እየተሳሳቱ ይህንን ሰው “ሰይጣን” ሲሉት ስሰማ ለሰይጣን ለራሱ አዝናለሁ፤ በቋንቋዎች ደካማ ጎን/ውሱንነትም እበሳጫለሁ፡፡ አቢይን በሚገባ የሚያውቀው ሰይጣን ይህን የአቢይ ስም ሲሰማ እንዴት እንደሚናደድ መገመት አይቸግረኝም፡፡
… ኦርቶዶክስን ያጠፏት ራሳቸው ቀሳውስቱና ጳጳሣቱ ናቸው፡፡ ለምን ቢባል እነሱ ራሳቸው ለአጋንንቱ ዓለም አደሩ፡፡ ከዚያም መለኮታዊ ተልእኳቸውን መወጣት ተውና ለብልጭልጩ ዓለም ተገዙ፡፡ ከልዕለ-አጋንንቱ የመንግሥት ቡድን ጋርም በአንድ ማዕድ ቀረቡና ሃይማኖቱንም ሕዝቡንም ካዱ፡፡ “በአርሲ ይህን ያህል ክርስቲያን አለቀ” መባልን ሲሰሙ ልክ እንደወሮ በላው መንግሥታቸው ሲፈልጉ “ፋኖ ፈጃቸው” ሲፈልጉ “ግድያው ፖለቲካዊ አይደለም” ሲፈልጉ “የሞቱት በሃይማኖታቸው ምክንያት አይደለም” ወዘተ. እያሉ በመዘበራረቅ ጳጳሣቱ ራሳቸው ለማተባቸው ሳይሆን ለትዳራቸው – ማነው – ለዓለማዊ ፍላጎታቸው አድረው ለሊቀ ሣጥናኤል ተንበረከኩ፡፡ ሁሉም በወደደው ይቆርባል፤ የወደደውም በመጨረሻው ያጠፋዋል፡፡ እያንዳንድሽ ጠብቂ!! (አንዳች ኃይል በል በል አለኝ ልበል?) አዎ፣ ኦሮሙማንና አሽከሮቹን የሚጨርሳቸው የሰው ኃይል ሳይሆን በሚሊዮኖች ያፋሰሱት ደምና በሚሊዮኖች ያፈናቀሉት ሕዝብ ዕንባና ዋይታ ነው፡፡ ማንም ከፍርድ አያመልጥም፤ ግን ሊዘገይ ይችላል፡፡ ይህኛውንም የሕይወት ክፍል ወይም የጉዞ አቅጣጫ መዘንጋት አይገባም፡፡
… ዛሬ ጧት አንዱ ወደጄ “በአምስት ቀናት ውስጥ ብቻ 3000 ብር ትራፊክ ፖሊስ ቀጣኝ” አለኝ፡፡ የ30 እና 50 ብር ቅጣት አሁን አነሰ ሲባል 1000 እና 1500 ሆኗል – በኦሮምያ ከ10 ሺህ ብርም ያለፈ ቅጣት አለ አሉ፡፡ ይሄ የገንዘብ ፍቅር ያሳበደው “መንግሥት” ማጂራት መቺ ከሆነ ቆዬ፡፡ አንዳንድ ማጅራት መቺ እንዲያውም አዝኖልህ “ከኔ የባሰ ድሃ!” በሚል አዘኔታ የተቀላቀለበት ትችት የተወሰነ ብር ለመሣፈሪያ ይተውልሃል፡፡ የአቢይ መንግሥት ግን የዘመዶችህንና የወዳጆችህን ኪስ ብቻ ሳይሆን ለምነህም እንድትሰጠው ጨርቅ አንጥፈህ እንድትቧግት ያስገድድሃል፡፡ ቀደም ሲል 5000 ብር ለምትከፍልበት ዓመታዊ ግብር አሁን 300 እና 500 ሺህ ብር ሲጠይቅህ ቅንጣት አያፍርም፤ ኦሮሙማ ማለት “ወያኔ ማሪኝ!” የሚያስብል አንዳችም ‹ሼም› የሌለው ማፊያ ቡድን ነው – በአራድኛ አገላለጽ፡፡ “ንግዱ ይቅርብኝ፤ ፈቃዴን ሰርዙልኝ” ብትል እንኳን “የሁለት ዓመቱን የወደፊት ግብር ከፍለህ ነው የሚሰረዝልህ” ትባላለህ፤ ሊያውም በከፍተኛ ማይማዊ የመጀነን ኩራት እየተንጠባረሩ – እንደአቢይ መንጋ በሰው ስቃይ የሚደሰት የትም የለም፡፡ በየቀኑ እየሆነ ያለውን ብትሰሙ ታብዳላችሁ፤ ትቀውሳላችሁ፡፡ በየዕለቱ የሚወጣው ደምብና መመሪያ ዘረፋ ላይ ያተኮረ ነው፡፡ በሀብታምና በሠራተኛ ላይ እያካሄዱት ያለው ዘመቻም የተለዬ ነው፤ ሟቿ ኢትዮጵያ መሥራትና መነገድ ወንጀል የሆነባት ብቸኛዋ ሀገር ናት፡፡ ሰዎቹ ለይቶላቸው አብደዋል፡፡
… የኔ ነገር፡፡ ያዝ ለቀቅ ሆነብኝ፡፡ ያ ጓደኛየ ሰሞኑን የተቀጣበትን ትራፊክ ፖሊሱ የሰጠውን የመቀጫ ወረቀት ገንዘቡን ከከፈለ በኋላ እንደዱሮው መስሎት በንዴት ቀዳዶ ይጥለዋል፡፡ 1500 ብር የከፈለበትን ደረሰኝ አሳይቶ መንጃ ፈቃዱን ሊቀበል ሲሄድ “ቅጣቱን የሚያሳየው ወረቀት የታል?” ተብሎ ይጠየቃል፡፡ እንደማያስፈልገው ቆጥሮ እንደጣለው ይነግራቸዋል፡፡ ከዚያም “እንደጠፋብህ ነግረህ ከፖሊስ ማስረጃ አጽፈህ አምጣ” ይሉታል፡፡ መኪናውን እዛው አካባቢ አቁሞ ወደሚቀርበው ፖሊስ ጣቢያ በታክሲ ይሄዳል፡፡ እንደደረሰም ጉዳዩን ለማስረዳት አንደበቱን ከመክፈቱ “300 ብር ክፈልና ደረሰኙን ይዘህ ሂድ” ይሉታል፡፡ የተጻፈለት ደብዳቤም የለም፤ 300 ብር መዘረፉን ብቻ የሚጠቁመውን ደረሰኝ ይዞ ተመለሰ፡፡ መንጃ ፈቃዱም ተሰጠው፤ ከእሱ የሚፈለገው 300 ብሩ ነበረ፡፡ መኪናው የቆመችበት የሁለት ሰዓት ክፍያ ደግሞ የ80 ብር ካርኒ ተቆረጠለት፡፡ በደጉ ዘመን በሁለት ብር የምናወጣው የቀበሌ መታወቂያም አሁን ሁለት መቶ ብር መሆኑ ተይዞልኝ ቢጠፋብህ ደግሞ ስለመጥፋቱ 300 ብር፣ በድራቦሹ ለካርዱ 200 ብር በድምሩ 500 ብር ታወጣለህ – በትንሹ፡፡ “ጉድ በል ሸዋና ጎንደር!” ማለት አሁን ነው፡፡
አዳሜ እንዲህ እየተዘረፈ ይኖራል – መኖር ተብሎ፡፡ አሁን የቀረን ለምንተነፍሳት አየርና ለምንሞቃት ፀሐይ በቀን ወይ በወር ታስቦ ክፈሉ እንዳንባልና ሚስት ያለን ሰዎች ደግሞ በየሚስቶቻችን ጭኖች ሥር ባልቦላ ገጥመው በዚያች ብቸኛ መተከዣችን ላይ ግብር እንዳይጥሉብን ነው ትልቁ ስጋታችን – አደራችሁን “የረሱትን አስታወስክብን” ብላችሁ እንዳትቀየሙኝ ታዲያ፤ እነሱ እኮ አያደርጉም አይባሉም፡፡ “የዛሬውስ እንትና አርም አያሳራ!” ብሎ ጥንት ያኔ የተናገረውና ወደተረትነት የዞረለት ማን ነበር? አማራ እኮ ለተረት ማንም አያህለውም፡፡ በፋኖዎች ላይስ “ወጣ ወጣና እንደሸምበቆ፤ ተንከባለለ እንደሙቀጫ” ብሎ የዛሬ ስንትና ስንት መቶ ዓመት ተርቶ የለም? ግን ግን በእውነት ፋኖዎች የት ገቡ? “እየመጡ ነው” ወይንስ “እየሄዱ ነው” ? ማንኛውን እንመን? የሰው ዐይን ድንጋይ ይሰብራል እንኳን የተፋፋመ የነፃነት ትግልን፡፡
… ወንድሜ ስማኝ፡፡ ጉራና ትዕቢትን ያላሸነፈ ሰው ዓላማው ምንም ይሁን ምን የትም አይደርስም፡፡ ቢደርስ እንኳን የሚገጥመው አንከላፋና ደንቃራ በጣም ብዙ ነው፡፡ ሀብት ቢኖርህ፣ ገንዘብና ዝና ቢጎርፍልህ፣ ጀግንነትህ በጥይት ወፍ ከሰማይ ቢያወርድ፣ ወጣትነትህ አማላይ ቢሆን …. ትኁት ካልሆንክና ሃይማኖት ከሌለህ እመነኝ ባዶ ነህ፤ በዕብሪትና በጥጋብ የምትታወር ከሆነ ዋጋ የለህም፡፡ ልታይ ልታይ ያሉ መጨረሻቸው አምሮ አያውቅም፡፡ ትዕቢትንና ትምክህትን ያሸነፈ ካሰበው ይደርሳል፡፡ የናቁት ወንድ እንደሚያስረግዝ ተገንዝቦ በውል ያልተጓዘ ሰው – እደግመዋለሁ – መጨረሻው የዜሮ ብዜት ውጤት ነው፡፡ በዚህች በምላት ነገር እንማማርባት፡፡ አበቅቴው ገና ነውና የፋኖ ሁኔታ ጨርሶውን ተስፋ የሚያስቆርጥ አይደለም፡፡ ከፍ ሲል ስለሌሎች ሀገራት የተናገርኩትን አስቀያሚ ተሞክሮም እንዳልረሳሁት ማስታወስ እወዳለሁ፡፡
… ዛሬ ጧት አንድ ነገር አየሁ፡፡ አማራ ጄኖሳይድ ከታወጀበት 51ኛ ዓመቱን ሊያጠናቅቅ እንደሆነም ተረዳሁ፡፡ ለ50 ዓመታት ሲሞትና ሲጋዝ የነበረን ሕዝብ ነፃ ለማውጣት ነው እንግዲህ አዳሜ ከ50 ቦታ ተበታትኖና ለሀብትና ለሥጋዊ ፍላጎት ተንበርክኮ ወጣት ፋኖን በሞርታርና በድሮን እያስጨረሰ ያለው፡፡ ሊኖርና ሊበላ! ለሆድ አድሮ ሺህ ዓመት ከየደንገጡሩ ሲዳራና ሲበሻቀጥ ሊኖር!! ከብልጼ ጋር ተሞዳምዶ ኢትዮጵያንም ባወጣች ሸጦ በፋኖ ስም አራት ኪሎን ሊጋራ! አቢይን በማመን ለሀብትና ለሥልጣን ቋምጦ ሕዝብን የሚከዳን ሰው “የሞት ተራህን የምትጠባበቅ ጅል፣ ጅላጅልና ጅላንፎ ነህ” በለው በጌታው አማርኛ፡፡ ቀደም ሲል በደርግ ዘመን በኪሎ ሦስት ብር ይሸጥ የነበረን ታጥቦ የተቀሸረ ቡና “ብሩ ያልተገባ ዋጋ ተሰጥቶት ስለነበረ (ሲሉ ሰምቶ “overvalued” ሲል እንደገለጸው) አሁን ከ1600 ብር በላይ መሸጡን እየሰማ ለአንድ ዝቅተኛ ደሞዝ ተከፋይ የመንግሥት ሠራተኛ 6000 ብር በመነሻነት የሚከፍል ዕብድ ጠ/ሚኒስትር ያላት ኢትዮጵያ ብቻ ናት፡፡ የመንገድም፣ የኢንዱስትሪም፣ የፋብሪካም፣ የትምህርትም፣ … ልማት ቆሞ ለአንድ ወፈፌ ሰውዬ ወንበር ሲባል ሁሉም ነገር ወደ ጦርነት በሆነባት ሀገር አድሮ መገኘት ራሱ ከባድ ሸክም ሆኗል፡፡ ኑሮው ከጦርነቱ ከፍቶ፣ ብልሹውና ሙሰኛው አስተዳደር በእጅ ካልሆነ በእግር ተሄዶ አንድም ጉዳይ የማይፈጸምበት ሀገራዊ ድባብ ተፈጥሮ፣ በአማራና በትግሬ ሆነ ተብሎ ትምህርት እንዳይኖር የትምህርት ተቋማት በድሮን እንዲወድሙ ተደርገው… በዚህ አገዛዝ እንዴት እንደሚኖር እግዜር ያሳያችሁ፡፡ በዚህ ጨለማ ውስጥ የሚኖር ሕዝብ ፀጥ ረጭ ማለቱም ሌላው የህመምና የጭንቀት መንስኤ ነው፡፡ ይሄ ተራ አጭበርባሪ ማይም ምን እንዳዞረብን ጊዜው ሲደርስ መጠናት ይኖርበታል፤ ለቀልድ አይደለም የምለው፡፡
… እናልህ በ67 ዓ.ም 60 ሰዎች እንደተገደሉ ተነግሮ ሳለ እውነቱ ግን 83 እንደነበሩ አንዱ ውስጥ አውቂ አጋለጠ፡፡ ከነዚህ ብዙዎቹ ደግሞ እንደአጋጣሚ ሆኖ አማሮች ነበሩ፡፡ እና የተገነዘብኩት ነገር ከደርግ ባለሥልጣናት ውስጥ በሥውርም በግልጽም ፀረ አማራ የነበሩ ተንከሲስ ዘረኛ ዜጎች መኖራቸውን ነው፡፡ እንዲያውም ሟች ጋዜጠኛ ዜናነህ መኮንን እንደተናገረው “ኦሮሞ ነህ እንዴ? አማራ መስለኸኝ እኮ ላስገድልህ ነበር” ብሎ ለአንድ የቅርብ ባለሥልጣን ጓደኛው እንደተናገረው በሚዲያ ሲገልጽ ሰምቻለሁ፡፡ ይህ የዘረኝነት ልክፍት ዱሮም ነበር ለማለት ነው፡፡ እንደኔ በዓለማችን ትልቁ ደዌ ዘረኝነት ነው፡፡ ወደን ባልገባንበት ልዩነት መፋጀት ትልቅ ሥነ ሕይወታዊ በሽታና ቀውስ ነው፡፡
ልጨርስ ነው፡፡ በ67 ዓ.ም የሞቱት ባለሥልጣናትና መሣፍንት መኳንንት ያኔ ዕድሜያቸው በአማካይ 50 ነው እንበል፡፡ ባይገደሉ ኖሮ አሁን ላይ በአማካይ 101 ዓመት ይሆናቸዋል – ይህ ዕድሜ ደግሞ በበሽታና በአደጋ ይቅርና በተፈጥሮ ለመሞት ከበቂ በላይ ነውና ያኔ ተገደሉም አልተገደሉም ከሞላ ጎደል ሁሉም አሁን የሉም፡፡ በሌላም በኩል ገዳዮቹ በአማካይ ዕድሜያቸው 40 ነበር እንበል፡፡ እነሱም አሁን በአማካይ 91 መሆናቸውን ልብ ይሏል፡፡ በጣም አርጅተው ቤት ውለዋል፤ ወይም ሞተዋል፡፡ እንደአካሄድ አንድ ሰው ከ80 እና 90 በላይ ብዙም ዓለማዊ ተፈላጊነት አለው ተብሎ አይታመንም፡፡ “ከአፈር እንደመጣህ ወዳፈር ትመለሳለህ” የሚለውን ህግ የሚጠባበቅ ሽማግሌ ነው፡፡
አያችሁልኝ የኛን ሞኝነት? ስንት ዓመት ለመኖር ነው እንዲህ አቅላችንን ስተን የምንገዳደለው? የት ለመድረስ? በዚያኛው ዓለም ምን ለመውረስ? ምን አሳወረን? በአደጋ ወይም በበሽታ በየትኛውም የዕድሜ ክልል ጥለናት ለምንሄዳት ይህች ቆሻሻ ዓለም ስንል ለምን በከንቱ እንጨራረሳለን? ሃይማኖትም በሉት ዘርና ቋንቋ ሰበብ እንጂ ዋና የምንፋጅበት ነገር ማይምነትን መሠረት ያደረገ የጥቅምና የሥልጣን ፍላጎት መሆኑ ግልጽ ነው – አዳመጥከኝ አይተ ሓጎስ? ሰማኸኝ ኦቦ ፈይሣ? ልብ አልክልኝ አቶ ስንሻው? ዶክተር ዘበርጋስ ይህን ሃሳቤን እንዴት አየኸው? በህጋዊ መንገድና በብቃት ማግኘት ያቃተንን ነገር ወደጎሣችንና ሃይማኖታችን እንወሸቅና በስሜት የሚነዳ መንጋን በመታከክ የልባችንን የግል መሻት በሌሎች መስዋዕትነትና ፍጂት እውን እናደርጋለን፤ ሲሳካልን የኛን ኑሮ ወርቅና አልማዝ አድርገን ሥልጣን ላይ ያወጡንን ድሆች እርስ በርስ እናፋጃለን፤ በድህነትና በበሽታ እንቆላቸዋለን፡፡ መቶ ለማትሞላ ዕድሜ!! ሞት ነገ ለኛም አይቀርልንም፡፡ በሽታን ብንከላከል፣ ከአደጋ ብንጠበቅ እርጅና ጊዜውን ጠብቆ ከች ማለቱ አይቀርም፡፡ በዚያ ላይ በድግምትና በጥንቆላ ልጅ በአባት፣ ሚስት በባል …. ሳይቀር የምንተላለቀው ሞኝነት ነው፤ ወንጀልም ነው፤ ኃጢኣትም ነው፡፡ … ጎበዝ ወደየኅሊናችን እንመለስ – ሊያውም ጊዜ ካለን፡፡ ባለቀ ሰዓት መገኘት እንዴት ያለ ዕዳ ነው በል፡፡ አገር ምድሩ የዐውሬው ታዛዥ ሆነና፣ በክፋትና በሃኬት በሰው ስቃይም የሚደሰተው በዛና፣ ዕለተ ምፅዓቱም ተጓተተና ተጨነቅን፡፡….