ከንጉሤ አሊ
ከላይ ባስቀመጥኩት ሎጎ ስር ሀሳቤን እንድገልጽ ያስገደደኝ ካሁን ቀደም ተወክለው የዐማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት (አፋሕድ) የዲያስፖራ አስተባባሪ ሆነው ሲያገለግሉ የነበሩ ነገር ግን በድርጅቱ ውሳኔ አዲስ ተወካዮችን ከቀድሞ አመራሮችም የተወሰኑት ተጨምሮ መሰየሙን ያልተቀበሉ ግለሰቦች አንድነት በሚል መጠሪያ ድርጅት መመስረታቸውን ተከትሎ የተሰማኝን ስሜት ለመግለጽ ነው።
ዐማራ ካሁን ቀደም በክፍለ ሀገሩ በአንዳንድ ቦታዎችና ከክፍለሀገሩ ውጭ በሚኖሩ ወገኖቹ ላይ ይካሄድበት የነበረው የዘር ማጽዳት ፣ ማሳሳትና የዘር ማጥፋት ወንጀል በኦህደድ ብልጽግና አገዛዝ ዘመን ከልለው በሰጡት ስፍራ ድረስ ዘልቀው በመግባት ጦርነት አውጀው እየፈጁት ይገኛሉ ። ሮጦ ማምለጥ አለመቻሉን የተረዳው ዐማራ በሚኖርበት አካባቢ የጎበዝ ሀለቃውን እየመረጠ የአልሞት ባይ ተጋዳይነት ተጋድሎውን በሚያስደንቅ ጀግንነት በማካሄድ ላይ ይገኛል ።
የዐማራ ሕዝብ የህልውና ተጋድሎ ስኬታማ ሲሆን ነጻ የሚያወጣው በክልሉ የሚኖረውን ዐማራ ብቻ ሳይሆን ከክልሉም ወጭ የሚኖረውን ዐማራና የዘር ፖለቲካው ሰለባ የሆኑትን ኢትዮጵያንንም ጭምር ነው ። ስለ ሆነም የድል ጊዜውን በማፍጠን መስዋዕትነትን ለመቀነስ ጉዳዩ የሚመለከተው ሁሉ ተባብሮ በመነሳት ከፋኖ ጎን መቆም ይኖርበታል ። በነባራዊ ሁኔታዎች አስገዳጅነት የተነሳ የፋኖዎች ወደ አንድ እዝ መምጣት ቢዘገይም የህልውና አደጋውን አስወግዶ ለመኖር አንድ መሆን አማራጭ ሳይሆን የግድ ይላል ።
የህልውና ትግሉ ውጤት በዘገዬ ቀጥር የመስዋዕትነት መጠኑ ይጨምራል ፤ የታጋዩ የውጊያ ሞራል ይቀንሳል ፤ ምሽግና ስንቁ የሆነው ሕዝብ አቅሙ ውስን ይሆናል ይሰላቻልም ። ይህንን ታሳቢ በማድረግ አርበኞቻችን አንድ እንዲሆኑ ከወስጥና ከውጭ ጫና በሚደረግበት ወቅት በዲያስፖራ የምንገኝ የዐማራ ተወላጆች እንዳለ መታደል ሆኖ በረባ ባረባ ምክንያቶች ልዩነት እየፈጠርን የድርጅት ረሀብና ጥም ያለብን ይመስል ሁለትና ሶስት እየሆንን የተለያዬ መጠሪያ በመስጠት እንደ ዶሮ ጫጩት ድርጅት እንቀፈቅፋለን ።
ወደ ተነሳሁበት ርዕስ ለመግባት ከላይ አርማቸውን ያስቀመጥኩት አዲስ ድርጅት መስርተናል እወቁልን መጠሪያውንም “አንድነት ለአማራ ኅልውና “ ብለነዋል ብለው በመግለጫና በአካል በሚዲያ ቀርበው የምስራች ይመስል “አብስረውናል” ሀቁ ግን አርድተውናል ነው ። ምክንያቱም በዚህ በጣም ወሳኝ በሆነ የሞት ሽረት ታጋድሎ ወቅት ለአንድነት ግምባር ቀደም ሆነው ያስተባብሩናል ብለን እምነት ያሳደርንባቸው ግለሰቦች ተሳትፎ የምስራች (“አንድነት ለአማራ ኅልውና”) ብለው በክልልና ከክልል ውጭ የሚኖር ዐማራ የሚል ውሻል ሰንቅረው መርዶ ማርዳታቸው እጅግ በጣም አሳዝኖኛል ።
ዐማራ የዘር ማጥፋት ዘመቻ እየተካሄደበት ያለው የትውልድ ወይንም የመኖሪያ አካባቢው ተለይቶ አይደለም ፤ የሚያልቀው በዐማራነቱ ነው ፤ እኔን ጨምሮ እንደ ግጦሽ ሳር የሰው ልጅ በክልል ከመከለሉ በፊት ወላጆቻችን ኢትዮጵያ በምትባል እናት ሀገራችን ከጫፍ ጫፍ ተዘዋውረው በሚኖሩበት ወቅት ከክፍለ ሀገሩ ውጭ የተወለድን ዐማራዎች አለን ፤ የምንገደለው እና የተገደሉትም ዐማራ በመሆናቸው ነው ። ስለሆነም ህልውናችንን የምናስጠብቀው በዐማራነት አንድ ሆንን እንጂ በጎጥ ወይንም በትውልድ ስፍራ በመከፋፈል አይደለም ።
እኔ ዐማራነቴ ከዐማራ ቤተሰቦቼ በመወልደ ያገኘሁት የማንነት ጸጋ እንጂ ከትውልድ ቀዬ ወይንም በችሮታ ከሌላ አካል ያገኘሁት ማንነቴ አይደለም ፤ ስለ ሆነም በዐማራ ማንነቴ እየሞትኩ ወደ ንኡስ ማንነት (ሸዌ ፣ ዎሎዬ ፣ ጎንደሬ ወይንም ጎጃሜ) አልፎ ተርፎ በክልልና ከክልል ውጭ ወደሚል ክፍልፋይ የምወርድበት አመክኒዮ የለም ፤ ከላይ በጠቀስኳቸው አካባቢዎች ከተወለዱ ወንድም እህቶቼ ጋር በዐማራነቴ ተደራጅቼ የድርሻዬን ከማበርከት ያገደኝ ነገር ባለመኖሩ በእውነት የዐማራው የህልውና ጉዳይ የሚያሳስባችሁ ከሆነ እባካችሁን በአንድነት ስም እየከፋፈላችሁንና ለጠላት በር እየከፈታችሁ መሆኑን ተገንዝባችሁ ያላችሁን እውቀት ፣ ተሞክሮና እምቅ ይዛችሁ በአቅራቢያችሁ ያሉ የዐማራ ማህበራትን በመቀላቀል አጠናክሩ ፤ የፋኖን ለፋኖ ትተን እኛ የሚጠበቅብንን ሥራ እንስራ ፤ እልህ መጋባትና መጓተት ውጤቱ ሽንፈት መሆኑን ተገንዝባችሁ የያዛችሁት መንገድ እናንተን የሚመጥን ስላልሆነ በጥሞና አጥናችሁ የምትመሰርቱት ድርጅት የዐማራን አንድነት የሚያመጣ ሳይሆን በአንድነት ስም ልዩነትን የሚፈጥረ መሆኑን ተገንዝባችሁ አቁሙት ፤ መልካም ስምና ተግባራችሁን የሚያጎድፍ ስለሆነ ከስሜትና እልህ ወጥታችሁ ከአፋሕድ አመራሮች ጋር የተፈጠረውን ልዩነት በውይይት ፈታችሁ በተግባር የአንድነት ተምሳሌት ሁኑ ።
ፈጣሪ አምላክ ማስተዋልን ሰጥቶ ሀሳባችሁን ያስቀይር ዘንድ ምኞቴ ነው ።