አርባ ሁለት ሀገራት በኢትዮጵያ በተያዘው አመት ከሚካሄደው ምርጫ ቀደም ብሎ በመሰረታዊ መብቶች ላይ ገደቦች መጣላቸውን በመጥቀስ በሀገሪቱ ያለው የሰብአዊ መብት ሁኔታ እንዳሳሰባቸው ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታወቁ።
ሀገራቱ ባሳለፍነው ባወጡት የጋራ መግለጫ “በኢትዮጵያ ያለው የሰብአዊ መብት ሁኔታ፣ በተለይም ሀሳብን በነፃነት የመናገር፣ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ እና የመደራጀት መብቶች መገደባቸው አሳስቦናል” ሲሉ ገልጸዋል። አክለውም፣ “በቅርቡ በሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች ላይ የተፈጸመውን ማስፈራራት እና እገዳን ጨምሮ የሲቪክ ምህዳር መጥበብ እና መዘጋት አሳሳቢ ነው” ብለዋል። ሀገራቱ በገለልተኛ መገናኛ ብዙኃን እና ጋዜጠኞች ላይ እየደረሰ ያለው ማስፈራራትም ስጋት እንደፈጠረባቸው በመግለጽ፣ ለእነዚህ ክስተቶች ግልጽ የሆነ ምርመራ እንዲካሄድ ጥሪ አቅርበዋል።
ፊርማቸውን ያኖሩት ሀገራቱ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብት ከፍተኛ ኮሚሽነር ጽህፈት ቤት በ2024 ሪፖርቱ ላይ “በመንግስታዊ እና መንግስታዊ ባልሆኑ አካላት ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እና ጥቃቶች መፈጸማቸው መገለጹን” ጠቅሰው ይህም አሳሳቢ መሆኑን አመላክተዋል። በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ በ2025 በህጻናት እና በትጥቅ ግጭቶች ዙሪያ የቀረበን ሪፖርት በመጥቀስ፣ “የህጻናት መገደልና የአካል ጉዳት ማድረስ፣ ወሲባዊ ጥቃት፣ እንዲሁም መታገትን ጨምሮ በህጻናት ላይ የሚፈጸሙ ከባድ ጥሰቶች በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩ” በእጅጉ እንደሚያሳስባቸውም ገልጸዋል።
በተጨማሪም፤ “የኢትዮጵያ መንግስት እና ሌሎች ሁሉም ተዋናዮች በአማራ፣ ኦሮሚያ እና ትግራይን ጨምሮ ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች እየደረሰ ያለውን የሰብአዊ መብት ጥሰት እና በደል ለማስቆም ተጨባጭ እርምጃ እንዲወስዱ እንጠይቃለን” ብሏል መግለጫው። በተለያዩ አካላት እየተፈጸመ ያለውን “ በንጹሃን ሰዎች ላይ ግድያና ጉዳት ማድረስ፣ ማሰቃየት፣ ኢ_ሰብዓዊ አያያዝ፣ በግዳጅ መሰወር፣ የዘፈቀደ እስር እና ማቆየት፣ በንጹሃን ሰዎች መሰረተ ልማት ላይ የሚደረጉ ጥቃቶችን፣ እንዲሁም ከባድ ደረጃ ላይ የደረሰ ወሲባዊ እና ጾታ ላይ የተመሰረተ ጥቃት” በአስቸኳይ እንዲቆም አሳስበዋል።
ሀገራቱ ባለስልጣናት በአገር አቀፍ ደረጃ የሰብአዊ መብቶችን እንዲያከብሩ፣ ፍትህና ተጠያቂነትን እንዲያረጋግጡ ጠይቀዋል።
የጋራ መግለጫው በኢትዮጵያ የሽግግር ፍትህ ሂደት ውስጥ መሻሻል ባለመኖሩም ስጋቱን ገልጿል። ተአማኒነት ያለው የሽግግር ፍትህ እና የተጠያቂነት ማዕቀፍ መተግበር “ለተጎጂዎች እና ከጉዳት ለተረፉት ብቻ ሳይሆን፣ በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላምና እርቅ ለማረጋገጥም ወሳኝ ነው” ሲል አስታውሷል።
ሀገራቱ በተጨማሪም የኢትዮጵያ መንግስት “ከተባበሩት መንግስታት እና ከሌሎች የጥበቃ አካላት ጋር እንዲተባበር እና ገልተኝነታቸውን እንዲያከብር” አሳስበዋል። ሁሉም ወገኖች ተጨማሪ ጥሰቶች ከመፈጸም እንዲታቀቡ እና መረጋጋትን ለመመለስ በሰላማዊ ውይይት እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል።