እልም ነው ጭልጥ ነው ውኃ አይላመጥም ፣
ጠላት ወዳጅ ላይሆን አልለማመጥም ፤
በኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 46 (2) ድንጋጌ መሰረት “ክልሎች የሚዋቀሩት በሕዝብ አሰፋፈር ፣ ቁንቋ ፣ ማንነትና እና ፈቃድ ላይ በመመስረት ነው” ይላል ። እነኚህን መስፈርቶች መሰረት አድርጎ በጎሣ ማንነት አስተዳደራዊ አሀዶችን (ክልሎችን ) ማዋቀር የአባርታይድ ስርአት የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች በመሆናቸው በመካከላቸው ምንም አይነት ልዩነት የለም ። እንዲህ አይነቱ ስርአተ መንግሥት በዓለም ላይ የተለመደ ባይሆንም በሀገራችን ኢትዮጽያ ከ1994 ዓም ጀምሮ ተግባራዊ ሆኗል ። ክልሎቹ ሲጀመር 9 ነበሩ አሁን ወደ 12 ከፍ ብለዋል ፤ ወደፊትም ሊጨምሩ ይችላሉ ።
በሀገሪቱ ውስጥ በቋንቋ ፣ በባህል ፣ በአኗኗር ፣ በአሰፋፈር እና በእምነት ልዩነት ያላቸው ነገር ግን ተሰባጥረው እንዱ ከሌላው ጋር በጋብቻ ፣ በማምረት ፣ በምርት በክፍፍልና በልውውጥ ሂደት የጋራ መስተጋብር ፈጥረው ለረጅም ዘመናት አብረው ኑረዋል ።
የጋራ መስተጋብሩ ከላይ በተጠቀሱት ግንኙነቶች የሚያበቃ ሳይሆን የቋንቋ ፣ የባህል ፣ የአኗኗር ዘይቤን መወራረስና በጋቻ የደምና የስጋ ውሁድነትንም ወደ መፍጠር ተደርሷል ። በዚህ የተነሳ ሕዝባችን አሰፋፈሩ ከጫፍ እስከ ጫፍ አብሮ እና ተሰባጥሮ ይኖራል ።
አብሮ ስለሚኖሩ በመካከላቸው ምንም አይነት ልዩነትና ቅራኔ አልነበረም ወይን አይኖርም ማለት አይደለም ። በተለያዩ ምክንያቶች የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን በባህላዊ መንገድ አንተም ተው አንቺም ተዪ በመባባል የኖሩ ቢሆንም ዘላቂ መፍትሄ መስጠት ስለማይቻል ዘመናዊው ስልጣኔ ያመጣው ሁሉንም እኩል ተጠቃሚና ባለቤት የሚያደርግ ዲሞክራሲያዊ የሆነ የመንግሥት ስርአት አስፈላጊ ነው ።
የዚህ አይነት የመንግሥት ስርአቶች ደግሞ የተለያዩ ስያሜና መዋቅራዊ አሀዶች ቢኖራቸውም መሰረታቸው የግለሰቦች መብትና ነጻነትን መሰረት ያደረጉ ናቸው ። የእገራችን የክልል (የጎሣ) ፌደራሊዝም ግን መሰረት የሚያደርገው የቡድን ሁለንተናዊ መብትን ያለምንም ተጠያቂነት በግለሰቦች ላይ የሚጭን በመሆኑ የክልሉ ነባር ባለቤት (indigenous) እኔ ስለሆንኩ ስፈቅድልህ ትኖራለህ ካልፈቅድኩኝ ያሻኝን አደርጋለሁ ብሎ እስከ ዘር ማጥፋት ያደረስ ስርአት ነው። ለዚህ ማስረጃ ፍለጋ የምንኳትን ሳይሆን እስካሁን በዐማራው ሕዝባችን ላይ ካሁን በፊት የተፈጸመውንና አሁንም እየተፈጸመ ያለውን እልቂት መመልከቱ በቂ ነው ።
አሁን ባለው የኢትዮጵያ ተጭባጭ ሁኔታ 86 ብሔር ብሔረሰቦች ሲኖሩ ከ76 እስከ 77 ቱ በፌደሬሽን ምከር ቤት እውቅና እንዳላቸው የሚታወቅ ሲሆን እነዚህ ሁሉ ክልል የመመስረት ህገ መንግሥታዊ መብት አላቸው ። ይህ ማለት የሀገሪቱ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ብርኃኑ ጁላ እና የአዲስ አበባ ከንቲባ ወይዜሮ አዳነች አቤቤ ህወኃትን እንዳሉት ባዘጋጁት ህገ መንግሥት አንቀጽ 39 መሰረት 86 ቦታ ሀገሪቷ ተቆራርሳ ሁሉም ሀገር ሆነው ያለ ከልካይ እንዲሰናበቱ እውቅና መስጠት ነው ።
ለዐማራ ሕዝብ የህልውና አደጋ መነሻና መዳረሻው የህወኃትና የኦነግ ስሪት የሆነው ህገ መንግሥት እና ያንን መሰረት አድርጎ የተዋቀረው የጎሣ ፌደራሊዝም የማይነካ ቀይ መስመራቸው መሆኑን ደግመውና ደጋግመው ተናግረዋል ። ይህ በእንዲህ እያለ የዐማራ ፋኖ አይበገሬነቱን በጦር ሜዳ በተግባር ሲያረጋግጥ በማየታቸው ጦር ከፈታው ዎሬ የፈታው እንዲሉ ካድሬዎቻቸውን አስማርተው የፕሮፖጋንዳ ዘመቻ በማካሄድ ፣ በገንዘብና ሹመት በመደለል ፣ ባንዳ አስርጎ በማስገባት ፣ በድርድር ስም በማዘናጋት ፣ ሕዝብን አስተባብሮ አንድ ቀን ሰላማዊ ሕዝብዝዊ ንቅናቄ ያላደረገ የህልውና ትግሉን ለማደናቀፍ አብሮነት በሚል ስብስብ ውስጥ የኦነግና ህወኃት ካድሬዎችን አካቶ ጦርነት ይቁም ሰላም ይሰፈን እያሉ ማደናገር ቀጥለዋል ።
እንዲህ አይነቱን ጎሣን መሰረት ያደረገ ስርአት ዲሞክራሲያዊ ማድረግ በፍጹም አይቻልም ። ምክንያቱም ክልሉ ውስጥ የሚኖረውን ሕዝብ የጎሣ ስብጥር ታሳቢ ያላደረገ ነባር ነው ብለው ያስቡትን ጎሣ ብቻ ህገመንግስታዊ ባለቤት ያደረገ በመሆኑ ሌላው ብዛቱ ምንም ያክል ይሁን ምን እንደ መጤ ተቆጥሮ ስጓዝ እንደመሸበት እንግዳ አድሮ ሲነጋ የሚሰናበት ባዕድ ነው። ዲሞክራሲ የጋራ የሆኑ ነገሮችን እኩል እንዲጠቀሙ የሚያደርግ የአስተዳደር ስርዓት እንጂ የሌላን ንብረት ባለቤት ካልሆነው ግለሰብ ጋር እኩል እንዲጠቀም የሚያደርግ ተምኔታዊ የኮሚንዝም እሳቤ አይደለም ስለሆነም የክልል አወቃቀሩ መጤና ባለቤት ብሎ የነፈገውን መብት ዲሞክራሲያዊ ማድረግ በፍጹም አይቻልም ። የሚቻለው ሁሉም እኩል ባለቤት ሲሆንና ማንኛውም ኃላፊነት “ቀሚሳችን በቁመታችን ልክ ይሰፋልን” በሚል በኮታ መስፈርት ሳይሆን በችሎታና ብቃት ሲያዝ ነው። ሀቁ ይህ ሆኖ እያለ የስርአቱ እርክቴክቶች በህገመንግሥታቸው ድንጋጌ እንቀጽ 39 መሰረት የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መብት እስከ መገንጠል ብለው ያረጋገጡት ህወኃቶች በ27 ዓመት እውን ማድረግ አለመቻላቸውን ተከትሎ ኦነጎች ደግሞ የእተገባበር ችግር እንጂ ከስርአቱ አለመሆኑን እየነገሩን ከርመው መንበረ ስልጣኑን በተቆጣጥሩ 7 ዓመት ውስጥ የነበረውን ሁሉ እንዳልነበረ በማድረግ በኢትዮጵያ መቃብር ላይ ኦሮሚያ የምትባል ሀገር ለማዋለድ ሀገሪቷን የደም ምድር አድርገው ከወደቁ መንግሥታት (failed state) ደረጃ አድርሰዋታል ። እንዲህ አይነቱን ውድቀት ከስህተታቸው በመማር ለማስተካከል ከመጣር ይልቅ ተፈጥሮአዊና ሊታለፍ የማይችል አድርገው በመውሰድ ሌላውን ለማሳመን የብልጽግና ካድሬዎች ይጥራሉ ለዙህ ማስረጃው አምባሳደር ለንጮ ባቲ በሳውዲ አረቢያ ኢትዮጵያውያንን ሰብስበው ባነጋገሩበት ወቅት “አንዲት ሴት ልጅ ስትወልድ እንደሚደማት ሁሉ እኛም አዲስ ሀገር እያዋለድን በመሆኑ ደም መፍሰሱ አይቀሬ ነው” ብለዋል ።
ሕወኃትና ኦነግ የዐማራን ሕዝብ በጠላትነት ፈርጀው ከኢትዮጵያ ምድር ሊያጠፉት ከአምስት አስርተ ዓመታት በላይ ሲዘጋጁ ከርመው ለመንበረ ሥልጣን ከበቁ እነሆ 34 ዓመት ሆኗቸዋል ። ሁለቱ ቡድኖች በጋራም ሆነ ለዬብቻቸው ሕዝቡን በጎጥ ከፋፍለው ህገመንግሥት ቀርጸው መግዛት ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ ጠላት ብለው የፈረጁትን ዐማራ በገሀድ የዘር ማጥፋት ወንጀል ፈጽመውበታል እየፈጸሙበትም ነው ።
መፈናቀልና መገድል የሰለቸው ዐማራ ችሎ መኖርም ሆነ ሸሽቶ ማምለጥ አለመቻሉን ሲያረጋግጥ ነፍጡን አንስቶ ራሱን መከላከል ጀመረ ፣ ሱሪውን ሊያስወልቅ ፈክሮ የመጣን ጠላት ግልገል ሱሪውን ጭምር አስወለቀው ፣ ትጥቅ ሊያስፈታ ከመጣ ጠላት ትጥቅ አስፈትቶ ታጠቀ ፤ ባንዳ ሰርጎ ገብ ላከበት የውኃ ሽታ አደረገው ፤ ሆዳሞችን በያሉበት አሰማራ ሆዳምና ወዶገባ ውሻ የሚጮሄው ለበላበት ስለሆነ መተማመን ጠፋ ፤ ሲያልቅ አያምር ነውና የአስጥሉኝ ጩሄት እና ቴያትር ከውስጥና ከውጭ በመስተጋባት ላይ ይገኛል ።
አገዛዙ ፋኖን ተዋግቶ ማሸነፍ አለመቻሉን ሲያረጋግጥ እንዲያስጥሉት የአገርን ጥቅም ሙሉ በሙሉ ለባዕዳን አሳልፎ በመስጠት በተማጽኖ ላይ ሲገኝ አኩሯፊ መሳይ ኦነጋዊያን ፣ የህወኃት እና የህዳር አህያ የሆኑ የባዴን ካድሬዎች ከፋኖ ፎንቃ (ጥልቅ ፍቅር)እንደያዛቸው በማስመስል ሌት ተቀን „የፍቅር ዜማ” ማዘም ከጀመሩ ሰንበትበት ብሏል ። ለማንኛውም ሙያ በልብ ነውና ቁማር ቆማሪውንም ሆነ የፍቅር ተውኔት ተዋኙን ሁሉንም እንደ አማጣጡ ተቀብሎ ማስተናገዱ የታጋዮቻችን እና ቅን የትግሉ ደጋፊ የሆኑ የዐማራ ተወላጆች ተግባር ነው።
ከአስመሳይ አፍቃሪዎችና ተዋኞች ፊት ፊት እየቀደሙ መንገድ ጠራጊ የፖለቲካ ተንታኝ ነን ባይ አደናጋሪዎች እና አንዳንድ የሚዲያ ሰዎች አንዴ በፖለቲካ ቋሚ ጠላትም ሆነ ወዳጅ የለም የሚለውን ብህል ጊዜና ቦታ የማይሽረው ዘለዓለማዊ የፖለቲካ ስልት አድርገው ሊያስተምሩን ሲሞክሩ ሌላ ጊዜ ዐይናችሁን ጨፍኑና እናሞኛችሁ በሚመስል ጠላት ከማብዛት ወዳጅ ማብዛት ይሻላል ይሉናል ። የወጋ ቢረሳ የተወጋ አይረሳምና መንጋ አሰልጥነው ወገናቻችንን አፈናቅለውና አስጨፍጭፈው አልጸጸትም የታገልኩለት ዓላማ ግቡን መቷል ብለው በድፍረት ድርሰት ሲደርሱብን ፣ የፖለቲካ ቁማር ቆምረን በላናቸው ብለው የሚዘባበቱብንን ፣ ከዐማራ ጋር አትጋቡ የተጋባችሁም ተፋቱ ብለው ትዳር ያፈረሱትን ፣ ካሁን በኋላ በክልላችን ሌላው ቀርቶ ቀና ብሎ ካየን አንገቱን በሜንጫ እንቀላለን የሚሉንን እና በሚቻለው ሁሉ የዐማራን ሕዝብ ቁጥር ቀንሰን ህዳጣን እናረጋቸዋልን ብለው አቅደው የዘመቱብንን ታግለን ህልውናችንን እንዳናስጠብቅ ለማድረግ ያልተነካ ግልግል ያውቃል እንዲሉ ሰላማዊ ትግል እንጅ የትጥቅ ትግል አያስፈልግም ፤ ወዳጅ እንጅ ጠላት ማብዛት ጥሩ አይደለም ፤ ቋሚ ወዳጅም ሆነ ቋሚ ጠላት የለም ፤ ዘላቂ ሰላም እንዲኖር የሚያስፈልገው ድርድር ነው እያሉ ለስር ነቀል ለውጥ የሚደረገውን ትግል ለመጥለፍ በመረባረብ ላይ ይገኛሉ ።
ዐማራ ጠላቶቹ ህወኃትና ኦነግ ከ50 ዓመት በላይ የውሽት ትርክት ፈጥረው ፣ ተከታይ አፍርተው ፣ በጸረ ዐማራነት ተደራጅተውና ታጥቀው ለበትረ ሥልጣን ከበቁ እና በዐማራ ሕዝብ ላይ የዘር ማጥፋት ፣ የዘር ማሳሳትና የዘር ማጽዳት ዘመቻ በገሀድ ከጀመሩ እነሆ ከ34 ዓመት በላይ ተቆጥሯል ።
ትናንትና ወንጀሉ በተሳለጠ መንገድ እንዲፈጸም ባቋቋሙት የሚዲያ አውታር ስቀሰቅሱና ድጋፍ ሲያደርጉ የነበሩ ጽንፈኛ የኦሮሞ ሊህቃን ዛሬ ፋኖ ክንዱን አፈርጥሞ በህልውና ትግሉ የጦር ሜዳ ውሎ ድል በድል መሆኑን ሲያረጋግጡ ህልማችን ቅዥት እንዳይሆን በሚል እሳቤ ዐማራን ሲፈርጁም ሆነ ለማጥፋት ሲያቅዱ ገና በእናቱ ማህጸን ያልተጸነሰውን አብይ አአህመድን ብቸኛው ወንጀለኛ አድርገው በመሳል ለስር ነቀል ለውጥ የሚደረገውን የህልውና ትግል አብይን ከሥልጣን ወደ ማውረድ ተግባር ብቻ ዝቅ ሊያደርጉ ለት ተቀን ይማስናሉ ።
ካሁን ቀደም ሥልጣን ከህወኃት ወደ ኦህደድ እንዲሸጋገር ሲደረግ የህወኃት የእጅስራ የሆኑ ተጋላቢ ብአደኖች የፈጸሙትን ስህተት በመድገም በአንዲት ድንጋይ ሁለቴ የሚደናቀፍ ራሱ ድንጋይ የሆነ ዐማራ ያለ አይመስለኝም ። ለዐማራው የህልውና አደጋ መሰረታዊ መንስዔ የሆኑ “ህገመንግሥት” ተብዬውና በዘር ላይ የተመሰረተው ፌደራሊዝም አይነካም ቀይ መስመራችን ነው የምንታገለው ኦሮሚያ የምትባል አገር ልንፈጠር ነው የሚሉ ጽንፈኛ የኦሮሞ ሊህቃን ዐማራን አብረን እንስራ የሚሉት የቱን የጋራ ዓላማ ለማሳካት ፈልገው መሆኑን ቢነግሩን መልካም ነው ፤ በዐማራው ላይ ለተፈጸመው ሁሉ አቀፍ ወንጀል ጠቅልሎ ለአብይ ብቻ ለመስጠት ከመሞከር ይልቅ እያንዳንዱ የድርሻውን ለመቀበል ቢያንስ ቃል ቢገባ የተጎዳውን የዐማራ ሕዝብ አንጀት ባራራው ነበር ።
አሁን የአብይ ተቃዋሚ መስለው በየሚዲያው የሚወራጩ የህወኃትና የኦነግ ቀንደኛ ካድሬዎች አብይ አህመድ እነርሱ የጀመሩትን አዝጋሚ ለውጥ በፍጥነት ከግቡ ለማድረስ ከመጣደፍ ውጭ ሌላ ያደረገው የተለየ ነገር የለም ስለሆነም እነኚህ ግለሰቦች ጭንቀታቸው አብይ ከስልጣን ሲባረር ያቀድነው በሙሉ መና ሆኖ እንዳይቀር አሁኑኑ አደናግረንና አወናብደን አፓርታይዳዊ ስርአቱን እና ህገመንግሥቱን እናትርፍ ብለው ስር ነቀል የሆነ ስርአታዊ ለውጥ እንዳይመጣ ለማደናቀፍ የሚያደርጉት ሸፍጥ መሆኑን የኢትዮጵያ ሕዝብ ተገንዝቦ ከፋኖ ጎን ቆሞ ሊዋጋቸው ይገባል ይህ ሳይሆን ቀርቶ አገር ብትፈርስ የሚጎዳው የዐማራ ሕዝብ ብቻ አለመሆኑንን ሁሉም ልገነዘብ ይገባል ።
ዐማራ ለምን እንደሚታገል አውቆ ወዳጅና ጠላቱን ለይቶ „እልም ነው ጭልጥ ነው ውሃ አይላመጥም ጠላት ወዳጅ ላይሆን አልለማመጥም” ብሎ አይቀሬውን የህልውና ትግል በመጀመሩ ወዳጆቹ አብረውት ናቸው ሊያጠፉት የተነሱ ወድጅ ሊሆኑም ሆነ ሊያፈቅሩት እንደማይችሉ ተገንዝቦ ለስር ነቀል ለውጥ የጀመረውን ትግል ከግቡ ሳያደርስ በሴረኞች ርብርብ አያቆምም ።
ማጠቃለያ ፣
የዐማራን ሕዝብ በጠላትነት ፈርጆ ፣ ራሱን አደራጅቶ እና ታጥቆ ፣ የእኔ የሚለውን ማህበረሰብ አንቅቶ ፣ አስታጥቆ እና አሰማርቶ የዘር ማጽዳትና ማጥፋት ወንጀል የሚፈጽሙበት መሰረታዊው ምክንያት በኢትዮጵያዊነቱ የማይደራደር በመሆኑ እሱን አዳክመን ኢትዮጵያን እናፍርስ ነው ። ይህ ዐማራን አጥፍቶ እና ኢትዮጵያን አፈራርሶ አገር የመሆን እኩይ እቅዳቸው እንዳይሳካ ማድረግ የሚቻለው ከኢትዮጵያዊነት ማማ አልወርድም በማልት ወይንም ለዚህ ያበቃሽኝ አንቺ (ኢትዮጵያ)ስለሆንሽ አይንሽ ለአፈር በማልት ሳይሆን ከፋኖ ጎን ቆሞ በመታግል ስለሆነ ሁሉም ዐማራ የድርሻውን ሊወጣ ይገባል።
የሕዝባችን የህልውና ትግል ራስን የመከላከል ፍትሀዊ ተጋድሎ በመሆኑ ድል ማድረጉ አይቀሬ ነው ። ይህንን ከድል በመለስ ገቺ ኃይል የለለውን ተጋድሎ በአነስተኛ መስዋዕትነትና በአጭር ጊዜ መፈጸም ሲቻል በአንድነት እጦት ብዙ ዋጋ ማስከፈሉ አግባብ ስላልሆነ ፋኖዎቻችን የተሰው ጓዶቻቸው ደም እና ታሪክም እንዳይፋረዳቸው በፍጥነት ወደ አንድነት መጥተው ለድል እንዲያበቁን እያልኩ ለአንድነቱ እንቅፋት የሚሆኑ የውስጥ አርበኞች ሊኖሩ ስለምችሉ ወደ ውስጣቸው ሊመለከቱ እና ሊያስተካክሉ ይገባል ፤ ከሁሉም በላይ ወሳኙን የጋራ ሕዝብዝዊ ዓላማና ግብ ዘንግቶ ያለ ቦታውና ያለ ጊዜው በራስ ወዳድነት (በኢጎ) ለስልጣን የሚደረግ የርስ በርስ ሽኩቻ በተግባር ውሎ ሳያድር በውይይት ሊፈታ ይገባል።መስማት የምንፈልገውን እየተናገሩ እንደ ብልጽግናው ውሸታም መሪ አብይ አህመድ ተቃራኒውን ማድረግ መቆም አለበት። ፖለቲካ የማስተዳደር ጥበብ እንጂ በጓዶቹ ደም ቆምሮ እና ዋሽቶ ለስልጣን ማብቂያ መሰላል አይደለምና ነው።
በዐማራ ሕዝብ ላይ የተፈጸመው ወንጀል ሂትለር በአይሁዶች ላይ ከፈጸመው ቢበልጥ እንጂ የሚያንስ አይደለም ይህ ከስብዕና ወጭ የሆነውን ግፍ የፈጸሙበት ኢትዮጵያን አላስነካም በማለቱ (በፓትሪኦትነቱ) ነው ። ይህንን ሀቅ ማንኛውም ዐማራ ያውቃል ነገር ግን ለዐማራ መጨፍጨፍ ኢትዮጵያ ምክንያት ሆነች እንጂ ጠላቱ አይደለችም ። ስለሆነም አይንሽን ለአፈር ማለት ለጠላት ዱላ እንደማቀበል ወይንም ለትኋን ብሎ ቤትን እንደማቃጠል ስለሚቆጠር ምንም እንኳ ድርጊቱ ቢያበሳጨንም ዐይናችንን በጋራ ከኳሱ ላይ ማድረጉ ስለሚጠቅም ለሀገር አፍራሾች መሰሪያ ከመሆን ብንታረም መልካም ነው ። ከዚህ ተለይቶ የማይታየው ሌላው የጅል አመለካከት ደግሞ እንዴት አባተን ሁኜ ነው ከኢትዮጵያዊነት ሰገነት ዎርጄ በጎጥ የምደራጀው በሚል ዐማራነትን ተጸይፎ ሳይደራጅና የሚጠበቅበትን ለማበርከት ሳይችል ተመልካች የሆነ የዐማራ ተወላጅ ወገኑን ለጠላት አሳልፎ እንደሰጠ ይቆጠራልና ቢያንስ ከታሪክ ተወቃሽነት ለመዳን ኑ ተደራጁ የድርሻችሁን ተወጡ ማልት እወዳለሁ ።
በሀገር ውስጥም ሆነ በዲያስፖራ የምንገኝ የዐማራ ተወላጆች ውዷ እህታችን መምህርትና የሰብአዊ መብት ተሟጋች መስከረም አበራ እንዳለችው ፋኖ (ዐማራ) በህልውና ትግሉ ያለው አማራጭ ማሸነፍ ብቻ ነው ያ ሳይሆን ቀርቶ ከተሸነፈ በኢትዮጵያ ምድር ባሪያ ሆኖ ለመኖር እንኳን አይፈቀድለትም ። ስለሆነም በበሬ ወለደ ምክንያት ታጋዮችን (ፋኖዎችን) የሚያሳፍኑና የሚያስገድሉ ጥቂት ማን አለብኝ ባዮች ትግሉን እንዳያስጠልፉ መሽኮርመሙ ቀርቶ በግላጭ ተው ሊባሉም ይገባል ።
ከሁሉም በላይ የዐማራውን አንድነት የሚሸረሽረው ፣ ለጠላት መግቢያ ቀዳዳ የሚሆነው እና ትግሉን የሚጎዳው በማወቅም የሁን ባለማወቅ ወደ ጎጥ የመሰባሰብ አዝማሚያዎች ስላሉ በፍጥነት መታረምና ሁላችንም በዐማራነታችን የተከፈተብንን አደጋ ለመመከት አንድ ላይ መሆን ግዴታ እንጅ አማራጭ አለመሆኑን ልንረዳ ይገባል ።
መልካም ንባብ
ንጉሤ አሊ