አንዱ ዓለም ተፈራ
ሰኞ፣ ሐምሌ ፳፰ ቀን ፳፻፲፯ ዓ. ም.
የመንግሥት ተቋማትና የሃይማኖት ተቋማት፤ ሁለት የተለያዩ አካላት ናቸው። ምንም እንኳን ሁለቱም ለአንድ አገር ሕዝብ የተቋቋሙ ቢሆኑም፤ የሚያገለግሉት ለሁለት የተለያዩ ፍላጎቶች ናቸው። የሃይማኖት መሪዎች ዋና ተልዕኮ፤ የአማኞቻቸውን ሥጋዊ ፍላጎት ለነፍሳቸው አገልጋይ እንዲሆን ማስተማር ነው። ለዚህ ይረዳ ዘንድ፤ ሥጋቸው በምን መንገድ መኖር እንዳለበት የሚያስተምሩ መጻሕፍት አሏቸው። በዚህ እሳቤ፤ ሰዎች በምድር ላይ የሚኖሩት፤ ለሚቀጥለው ዘለዓለማዊ ህይወት፤ በዛሬው፣ በዚህ ዓለም፣ ለመፈተን እና ለመዘጋጀት ነው። እናም የሃይማኖት ተልዕኮ፤ ቢያንስ በማውቀው በክርስትናና በእስልምና፤ አማኞች የሥጋ ፍላጎታቸውን በማገድ፤ ለነፍሳቸው መዳን እንዲገዙ ማዘጋጀት ነው። በአንጻሩ፤ በመንግሥት በኩል ያለው ተልዕኮ፤ ሰዎች በአገራቸው በአንድነት ሲኖሩ፤ ፍትኅና ርትህ በመካከላቸው እንዲሰፍን፣ በመካከላቸው ያለው ግንኙነት በሕግ የሰፈረ፣ አብሮነታቸውን እና የአንድ አገር ሕዝብ መሆናቸውን ማረጋገጥ ነው። በርግጥ በዚህ ክንውኑ፤ በሥልጣን ላይ የሚቀመጥ የመንግሥት አካል፤ የሕዝቡን ደህንነት፣ ሰላም ውሎ መግባት፣ እርሻና ንግድ በትክክል መካሄዱን መከታተል፣ ሕክምና ማግኘት፣ የትምህርት ዕድል መኖር፣ ትክክለኛ ገበያ ኖሮ ልውውጦችን እንዲያካሂዱ ማድረግ፣ እና ሌሎችም አስፈላጊ የኅብረተሰብ ጉዳዮች እንዲጠናቀቁ ያስችላል።
በዚህ ጉዳይ ላይ፤ አንደኛው በሌላው ክንውን ጣልቃ እንዳይገባ፤ ረዘም ላለ ጊዜ የፍልስፍና ሊቃውንት፤ ሲወያዩበት፣ ባለሥልጣናት ደግሞ ሲገፋፉበት፣ ሕግ አውጪዎች የሕግ መሻሻሎችን ሲያደጉበት፣ ቆይተዋል። ቀደም ሲል፤ በሃይማኖት መሪዎችና በአገር አስተዳዳሪዎች መካከል ልዩነት አልነበረም። መሪዎች ሁለቱንም በመሆን ያገለግሉ ነበር። እናም እነሱን እና የነሱን ሃይማኖት ያልተከተለ ከፍተኛ ዋጋ ሲከፍል ነበር። የመጀመሪያዎቹ የክርስትና ተከታዮች የደረሰባቸውን መከራና የከፈሉትን መስዋዕት የሚተርኩ ብዙ መጽሐፍት አሉ። የመጀመሪያዎቹ የእስልምና ተከታዮችም እንዲሁ በደረሰባቸው በደል ወደ ኢትዮጵያ መሰደዳቸውን ታሪክ ይነግረናል። ያ በጊዜና በሂደት እየተስተካከለ፤ የሃይማኖት ጉዳይ እና የመንግሥት ተግባር እየተነጣጠሉ ሄዱ። በተለይም በአሁኑ ሰዓት፤ ላቅ ያለ የአስተዳደር ግንዛቤ ባላቸው አገራት ዘንድ፤ በመንግሥትና በሃይማኖት መካከል፤ አንደኛው በሌላው ውስጥ ጣልቃ እንዳይገባ፤ ሕጎች ተደንግገው፤ እየተገበሩ ይገኛሉ። ይሄ ምን ማለት ነው? አሁን አገራችን ባለችበት የፖለቲካ ሀቅስ ምንድን ነው ቦታው? የመንግሥትና የሃይማኖት መለያየትስ ተገቢ ነው ወይ? ለዐማራ የህልውና ትግል፤ የሃይማኖትና የመንግሥት መለያየት ምን ያከናውናል? በዚህ ጽሑፍ ይሄ ይተነተናል።
ለምሑራን፤ በተለይም በምዕራባዊ አገራት ለምንኖር፤ ይሄ የመንግሥትና የሃይማኖት መለያየት፤ ያለ(ለ ይጠብቃል) ነገር (faith accompli) አድርገን እንወስደዋለን። ይሄ ግን፤ በሁሉም ቦታ ያለና፤ በሁሉም ሰዎች ዘንድ ተቀባይነት ያለው ተደርጎ መወሰድ የለበትም። ለኔ፤ በዝርዝር እንድሄድበት የገፋፋኝ ምክንያት አለ። የሃይማኖት እና የመንግሥት ሂደት መለያየት፤ መንግሥት በሃይማኖት ተቋማትም ሆነ አሠራር ጣልቃ እንዳይገባ፤ በአንጻሩም የሃይማኖት ልሂቃን በመንግሥት አሠራር ጣልቃ እንዳይገቡ የሚያደርግ አስተሳሰብና መመሪያ ነው። ለምን? አንድ መንግሥት፤ ስርዓቱን የሚያካሂደው፤ በአገሩ ላለ ሕዝብ ሲሆን፤ በአገሩ ውስጥ ደግሞ፤ የተለያ እምነት ተከታዮች፤ በነፃነት፤ በግለሰብም ሆነ ተቧድነው፣ የፈለጉትን ሃይማኖት እንዲከተሉ፣ መንግሥት ጫና እንዳይፈጥር ታስቦ ነው።
እኔ፤ ይህ መንግሥት በሃይማኖት ጣልቃ እንዳይገባ፤ የሃይማኖት ልሂቃን በመንግሥት አሠራር ጣልቃ እንዳይገቡ የሚያደርገውን አካሄድ፤ በየጥግህ (ይሄ የኔ ገላጭ ቃል ነው)( በእንግሊዝኛ Secularism – ሴኩላሪዝም) ብየዋለሁ። “የቄሳርን ለቄሳር፣ የአምላክን ደግሞ ለአምላክ” ብሎ የማርቆስ ወንጌል ምዕራፍ አስራ ሁለት፣ ቁጥር አስራ ሰባት ላይ እንዳሰፈረው። በየጥግህ፤ የመንግሥትን እና የሃይማኖት ተቋማትን የተለያዬ ሚና በትክክል በመረዳት፤ አንዱ በሌላው ውስጥ ጥልቃ እንዳይገባ የሚናኝ አንድ የአስተሳሰብ ዘርፍ ነው። በተለይም በመንግሥት ኃላፊነትና በእምነት ተቋማት አስተምህሮ መካከል ግልጥ ልዩነት እንዲኖር አስፈላጊ በመሆኑ ነው። በሌላ በኩል፤ “የለም! የኛ እምነት ገዢ መሆን አለበት! መንግሥታችን የኛን ሃይማኖት ብቻ መከተል አለበት!” ባዮች አሉ። በዚህም መንገድ አገራቸውን የአንድ ሃይማኖት ተከታዮች ብቻ መብት ያላቸው አድርገው የሚያስተዳድሩ መንግሥታት አሉ። ይሄ ሌሎችን ከመንግሥት ክንውን የማራቅ ጉዳይ፤ ቀደም ሲል በስፋት ነግሦ ነበር። የሃይማኖት መሪዎችን በመንግሥት ውስጥ ፈላጭ ቆራጭነት ለመቀነስ የተጀመረው ሂደት፤ ለኅብረተሰብ ማዘመን እና ላጠቃላይ እድገት ወሳኝ ነው! የሚል ግንዛቤ ፀነሱ። እናም በአውሮፓ ከሶስት መቶ ዓመታት በፊት ጀምሮ፤ አስተሳሰቡ እያደገ መጣ። በዩናይትድ ስቴትስ ኦቭ አሜሪካ፤ ይሄን አቋም ግንባር ቀድም ሆኖ በማራመድ የሚታወቀው፤ መሥራች አባቶቻችን ከሚሏቸው አንዱ ቶማስ
ጀፈርሰን ነው። በፈረንሳይ ይሄ የበጥግህ ጉዳይ በጥብቅ በተግባር የዋለ ነው። በሕንድ አገር፣ በፊሊፒንስ እና በአውሮፓ፤ በሕገ-መንግሥታቸው ውስጥ፤ በግልጥ የመንግሥትን እና የሃይማኖትን መለያየት ያስቀመጡ አንቀጾች አሏቸው። በሌላ በኩል ደግሞ፤ በእንግሊዝና በዴንማርክ፤ ምንም እንኳን በተግባር በየጥግህን ቢከተሉም፤ የአገር ቤተክርስያን ተብሎ የተያዘ አለ።
አብዛኛውን ጊዜ፤ ለሃይማኖታቸው ቀናዒ የሆኑ የሃይማኖት አባቶች፤ “ይሄ ሕግ ሃይማኖታችንን እንዳንተገብር ያደርገናል!” የሚል ክስ ይሰነዝራሉ። የሕጉ ደጋፊዎች ለዚህ መልስ ብለው የሚያቀርቡት፤ “በአንድ አገር ውስጥ ፍትኅ ያለበትና ትክክለኛ ኅብረተሰብ እንዲኖር፤ ሕጉ አስፈላጊ ነው!” የሚል ነው። እንግዲህ በየጥግህ፤ መንግሥት የራሱ የሆነ ሃይማኖት እንዳይፈጥር፣ አንዱን ሃይማኖት አቅርቦ ሌላውን እንዳያርቅ፣ ሌሎችም አከፋፋይ የሆኑ ተግባራት ላይ እንዳይሄራ ያግደዋል። ዋና መሠረታዊ ዓላማው፤ ግለሰቦች በነፃነት የፈለጉትን ሃይማኖት እንዲከተሉ አለማገድ ነው። ሃይማኖት የግለሰቦች ምርጫ ነው። ግለሰቦች ብዙ ምርጫ አሏቸው። በርግጥ የወላጆቻቸው እምነትና አስተዳደጋቸው ከፍ ያለ ተፅዕኖ እንዳለው አልዘነጋም። ሆኖም ሲያድጉ ያንን ትተው ሌላ ሊከተሉ ወይም ሊተው እንደሚችሉ፤ ለሁላችን ግልጥ ነው።
የበየጥግህ መሠረታዊ መርኅ፤ ግለሰቦች ያለ መንግሥት ጣልቃ ገብነት፣ የፈለጉትን ሃይማኖት፣ በግላቸውም ሆነ ተቧድነው፣ የመከተል መብት እንዲኖራቸው ማድረግ ነው። መርኁ የሚያራምደው፤ መንግሥት አንድን ሃይማኖት ከሌሎች ለይቶ እንዳያራምድ፣ እንዳያገን፣ በቀሪዎቹ ሃይማኖቶች ላይ ጫና እንዳያደርግ ነው። በዩናይትድ ስቴትስ ኦቭ አሜሪካ፤ በአገራቸው ሕገ-መንግሥት፣ በመጀመሪያው እክያ፤ የመንግሥትን እና የሃይማኖትን ጉዳይ አስመልክቶ፤ “ኮንግሬስ ሃይማኖትን በመመሥረትም ሆነ በማበረታታት በኩል ምንም ሕግ ማውጣት የለበትም!” የሚል ሰፍሯል።
አሁን በያዝነው በዐማራ የህልውና ትግል ውስጥ፤ ይሄን ጉዳይ እንዴት እናገናዝበዋለን?
ለማስመር ያህል፤ ፖለቲካ፤ ሰዎች በአንድ አገር ውስጥ አብረው ለመኖር፤ እርስ በርሳቸው የሚኖራቸውን ግንኙነት፣ የአስተዳደር ጉዳይ፣ ባጠቃላይም የአብሮ መሄዱን ቅንብር አስመልክቶ የሚኖራቸውን ግንዛቤ የሚገዛው መስክ እንደሆነ ካላይ ሰፍሯል። ይሄ ሙሉ በሙሉ የሥጋ ጉዳይ ነው። በሃይማኖት በኩል ደግሞ፤ ሰዎች በምድር ላይ ለምን እንዳሉ በመመራመር፣ ለምን እንደተፈጠሩ፣ ወደፊት ከሞት በኋላ ስለሚከተለው አጠቃላይ የሥጋ ሳይሆን፤ በውስጣቸው አለ ብለው ስለሚያምኑት ነፍስ፤ ሁሉንም ገዢ በሆነው ፈጣሪያቸው ዘንድ መመሪያ ያደረጉበት፤ ሥራቸውን ለነፍሳቸው አገልጋይ እንድትሆን የሚያዘጋጁበት መሪ እምነታቸው ነው። ለሃይማኖቱ ቅድሚያ የሚሠጥ ግለሰብ፤ በሥጋው ላይ የሚካሄደውን ሁሉ፤ ለነፍሱ አገልጋይ እንዲሆንና ስቃይን እና መከራን ለመቀበል ዝግጁ እንጂ፤ ለኔ እንዲህ ይሁንልኝ! ብሎ የሚነሳ አይደለም። እኒህ ሁለቱ በምንም መንገድ አይገናኙም። ፖለቲካውን ሥጋ ሲገዛ፤ ሃይማኖቱን ነፍስ ይመራዋል። በሃይማኖት፤ ዋናው ጉዳይ ለነገና ለነፍስ ማስብና መጨነቅ ሲሆን፤ በፖለቲካ ለዛሬና ለሥጋችን የምንጨነቅበት ሀቅ ነው። እንግዲህ ይሄ በትክክል በሃይማኖት መጽሐፍት የሰፈሩትን ማስረጃ በማድረግ ነው። በቆሮንጦስ ምዕራፍ አስራ አራት፣ ቁጥር ሰላሳ ሶስት እንዲህ የሚል አለ። “እግዚአብሄር የሠላም አምላክ እንጂ የሁከት አምላክ አይደለም”። እናም እኔ ሳድግ የተነገረኝ፤ የክርስትና እምነት፤ ቀኝ ፊትህን ቢመታህ፤ ግራህን እንዲደግመው አቅርብለት! ተብዬ ነው። ታዲያ ለዐማራ ህልውና ታጋይ ይሄ ምን ማለት ነው? ሃይማኖታችንን ለየግላችን፣ በየመሰለን እየተረጎምን፤ በጋራ ለመኖር ተሰባስበን የሚወረወርብንን መመከትና ጠላቶቻችንን ማጥፋት ነው።
በማቲዎስ ወንጌል፤ ምዕራፍ ስድስት፤ ቁጥር ሃያ አራት ላይ፤ “ማንም ሁለት ገዢዎችን ሊያገለግል አይችልም። አንድም አንዱን ጠልቶ ሌለናውን ይወዳል፤ አለያ ደግሞ፤ ለአንደኛው ሙሉ አገልጋይ በመሆን ሌለኛውን ያስቀይማል። እግዚአብሔርን እና ገንዘብን ማገልገል አትችልም።” ሲል አስፈሯል። ምናልባት ቃል በቃል አስታውሼ አላሰፈርኩት ይሆናል። መንፈሱ ግን ይህ ነው። እና ለነፍሱ የሚጨነቅ፤ ለሥጋው ሲል ከሌላ፤ በአምላክ ምስያ ከተፈጠረ ሰው ጋር ጦር አይማዘዝም።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሒዶ ቤተክርስትያንን በጥንቃቄ ለሚከታተል፤ በጦርነት አልተስፋፋችም! ሌሎችን በመግደል አታምንም። ራስን ዝቅ ማድረግን እንጂ፤ የበላይ ለመሆን ሌሎችን ተዋጋ! ብላ አላስተማረችም። “ሰዎች ነንና መኖር አለብን! ለመኖር ደግሞ’ በሌሎች ህይወት ላይ መፍረድ አለብን፤ እነሱ አድርገውታልና!” የሚል አስተምህሮ የላትም። ይህ የሥጋ አስተሳሰብ ነው።
እንግዲህ ወደኛ የህልውና ትግል ስናቀና፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ አብሮ የሚኖረው፤ የተለያየ ሃይማኖት ያላቸውና ሃይማኖት የማይቀበሉ ሁሉ በአንድ ላይ ነው። በክርስትና እምነትም ሆነ በእስልምና እምነት፤ የተለያዩ ዘርፎችን የሚከተሉ ሁሉ በአንድ ላይ በአገራችን እንኖራለን። እኒህ ሁሉ ታዲያ፤ አንድ አገራችን ብለን በምንኖርባት ኢትዮጵያ የምንጋራው፤ የአገሪቱን ኢኮኖሚ፣
ባህል፣ ፖለቲካ ነው። ሃይማኖት የየግላችን ነው። በዚህ የፖለቲካ ቅኝት፤ በአስተሳሰብ ላይ ብቻ የተመረኮዘ ስብስብ እንዲፈጥሩና እንዲሰባሰቡ ያደርጋቸዋል። ዐማራ አገሬ ብሎ በኢትዮጵያ ሲኖር፤ ይሄን ሀቅ ተቀብሎና አምኖበት ነው። መገንዘብ ያለብን፤ ዐማራ፤ የጁዲይዝም፣ የክርስትና፣ የእስልምና ሃይማኖትን ተቀባዮች ከሆኑት ግንባር ቀደም ሕዝቦች አንዱ መሆኑን ነው።
የዐማራ የህልውና ትግል፤ መነሻው በዐማራነት የደረሰና እየደረሰ ያለው በደል ነው። ይሄ የሃይማኖት ጉዳይ አይደለም። ይሄ የዐማራነት ጉዳይ ነው። የክርስትና እምነት ተከታዮችም ሆኑ የእስልምና እምነት ተከታዮች፤ ሁሉም በደሉ ደርሶባቸዋል፤ እየደረሰባቸውም ነው። የሃይማኖቱ ሊቆች በየተቋማቸው ግፍ ተፈጽሞባቸዋል። አረመኔ የሚለው ቃል እንኳ በትክክል በማይገልጠው ግፍና በደል ተገድለዋል። የትኛው የበለጠ ተጎዳ የሚለው አይረዳም። በሁሉም በኩል ዐማራ መጨፍጨፉን ነው መገንዘብ ያለብን። በተጨማሪም፤ የኒህ ሁለቱ ሃይማኖቶች ተቋማት እንዲፈርሱ ተደርገዋል። ያንን መካድ አይቻልም። ለአንድ ዐማራ ደግሞ፤ መጀመሪያ ልኑር ብሎ መነሳቱ፤ የተፈጥሮ ግዴታ ነው። ይህ ነው ዐማራ አምሮ እንዲነሳ ያደረገው።
ለዐማራ፤ እርሷ ወይንም እርሱ ከሚያምነው ሌላ የሚያምን ዐማራ፤ እህትና ወንድማቸው ናቸው። አሁን ሁላችንም በያለንበት የምናውቀውን እና የሰማነውን በማጤን፤ ቀሳውስት ስለተገደሉ፤ በእምነታቸው ነው። የእስልምና ተከታዮች ሲገደሉ በእምነታቸው ነው። እንላለን። ይሄ ግን ዋናውን ጠላትና ዓላማውን መሳት ይሆናል። አንዳንድ ሰዎች፤ ሌሎች ዐማራ ያልሆኑ ክርስትያኖች ተገድለዋልና፤ ዘመቻው በክርስትያናት ላይ ነው! የሚል አመለካከት አላቸው። በእስልምና ተከታዮችም ዘንድ እንዲሁ። እናም በሃይማኖታችን ከዐማራ ውጪ ያሉትን ሁሉ በማሰባሰብ መታገል አለብን! የሚል መደምደሚያ ላይ ይደርሳሉ። ይህ፤ ለዐማራ ብሔርተኝነት ዋና ጠላት ነው። ትግሉን የሚያዳክም መንገድ ነው። ትግሉ ዘርፈ ብዙ ነው። ጠላት በወታደራዊ ሰልፉ የትም መድረስ ስላልቻለ፤ ይልቁንም እየተቸነፈ ስለሄደ፤ ፋኖዎቻችንን በመከፋፈል ላይ ተሰማርቷል። የሳይቨር ሠራዊት አስማርቶ፤ በጣም ቁሻሻ በሆነ መንገድ፤ የተቃዋሚ ስብሰባዎችን ማደናቀፍ ይዟል። በመካከላችን ክፍፍልን ለመፍጠር የማይጠቀምበት መንገድ የለም። ራሱን የሚቃወም እየመሰልም በመካከላችን ለመግባት ይሞክራል። ለዚህ ሁሉ ማርከሻው፤ አንድነትና የዐማራ ብሔርተኝነትን ዋና የትግል ማዕከላችን ማድረግ ብቻ ነው። ማሰብ ያለብን፤ ሃይማኖትን መስበክና ሌሎችን ግለሰቡ ወደሚከተለው ሃይማኖት የመሳብ ሂደቱ የሚተገበረው፤ ዐማራው መጀመሪያ በህይወት ሲገኝ ነው።
ለማስመር፤ ኦርቶዶክስና ቤተክርስትያኗ ተጠቁ ለሚሉት፤ የእስልምና ተከታዮችና መስጂዶቻቸው ተጠቁ ለሚሉት፤ የዐማራ የእምነት ተቋማት ናቸው የተጠቁት! ዐማሮች በእምነታቸውና በመኖሪያ ቦታቸው ሲጠቁ፤ በዐማራነታቸው ነው። ጥቃቱ የሃይማኖት ሳይሆን፤ የዐማራነት ነው። ምክንያቱም ማንኛውም ዐማራ፣ የፈለገውን ሃይማኖት ቢከተልም፤ ከጥቃቱ አላመለጠም። “ወላሂ ካሁን በኋላ ዐማራ አልሆንም!” ያለችው ሕፃን፤ ከያንዳንዳችን ዐማራ የሆን ሁሉ፣ ምን ጊዜም፤ አባባሏ ሊርቀን አይገባም። እስልምና ተከታይ መሆኗ አላዳናትም።
እያንዳንዳችን ለምናምንበትና ለምንከተለው ሃይማኖት ቀናዒ መሆን እንችላለን። የሃይማኖት የፖለቲካ ድርጅት ግን፤ በመሠረቱ ሊኖር አይችልም፤ ተቃርኖም ነው። በርግጥ የአክራሪ አማኞች ብዛት ያላቸው አገሮች፤ ቀኖናቸውን መመሪያ በማድረግ አገር ሲገዙ አይተናል። ያ ግን የሰው ልጅን መብት የሚረግጥና ጥቂት የሃይማኖቱ መሪዎች በአገሪቱ ላይ በሃይማኖቱ ስም የፈለጉትን የሚያደርጉበት ስርዓት ነው።