በኢትዮጵያ በተለያዩ አከባቢዎች በቀጠሉት ግጭቶች በህይወት የመኖር መሰረታዊ መብት “አሳሳቢ” ደረጃ ላይ መድረሱን ኢሰመኮ አመለከተ
በኢትዮጵያ በተለያዩ አከባቢዎች በቀጠሉት በትጥቅ የታገዙ ግጭቶች ምክንያት በህይወት የመኖር መሰረታዊ መብት “አሳሳቢ” ደረጃ ላይ መድረሱን የሚያሳዩ በርካታ ክስተቶች መስተዋላቸውን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አስታወቀ።
ኮሚሽኑ በአማራ ክልል በአዛኛው አከባቢዎች በመንግስት ሀይሎች እና በታጣቂ ቡድኖች [ፋኖ] መካከል እየተካሄደ ባለው የትጥቅ ግጭት በግጭቱ ላይ ተሳታፊ ያልነበሩ ሰላማዊ ሰዎች ለሞት እና ለአካል ጉዳት መዳረጋቸውን አስታውቋል።
ግጭቶች ሲካሄዱባቸው በነበሩ አከባቢዎች የመንግስት ሀይሎች በሚቆጣጠሩበት ወቅት “ፋኖን ትደግፋላችሁ፤ ትቀልባላችሁ” ያሏቸው ሰዎች ላይ ግድያና መኖሪያ ቤቶችን በእሳት ማቃጠል ጥቃቶች መፈጸማቸውን አመላክቷል።
በሌላ በኩል በክልሉ የሚንቀሳቀሱት ታጣቂዎች [ፋኖ] “ለመከላከያ ሰራዊት መንገድ አሳይታችሗል፤ ሰዎችን ጠቁማችሁ አስይዛችሗል” በሚል እና የመንግሥት ሰራተኞች ወደ ስራ ገበታቸው እንዳይገቡ በማስፈራራት እና በገቡት ላይ ግድያ እንዲሁም በመኖሪያ ቤቶች ላይ ዘረፋ እና ውድመት መፈጸማቸውን በምርመራ መረጋገጡን በሪፖርቱ ተጠቅሷል።
በተመሳሳይ በኦሮሚያ ክልል በመንግስት ሀይሎች እና በኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ታጣቂዎች መካከል በሚደረገው በትጥቅ የታገዘ ግጭት ሳቢያ በሁለቱም አካላት በንጹሃን ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱንም ኢሰመኮ አስታውቋል።”የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ታጣቂዎች በወሰዱት እርምጃ በሰዎች ላይ ሞት፣ የአካል ጉዳት፣ እገታ እና የንብረት ውድመት ደርሷል” ብሏል።
ዜናው የአድስ ስታንዳርድ