በእጅጉ ከቆሸሸ ሥርዓት የቆሻሻ ዑደት እና ውጤት እንጅ የተለየ ነገር አይጠበቅም!!!

February 18, 2024

ጠገናው ጎሹ

ከቆሸሸ ግብአት የቆሸሸ ውጤት (GARBAGE IN, GARBAGE OUT) እንጅ የተለየ ውጤት መጠበቅ ፈፅሞ አይቻልም።

ይበልጥ አስከፊ በሆነ መልኩ ፈፅሞ ሊፀዳ በማይችል መርዘኛ የፖለቲካ ቆሻሻ /ወንጀል ከበበሰበሰና ከከረፋ የፖለቲካ ሥርዓተ ዑደትም ይበልጥ አደገኛ የሆነ መርዘኛ ቆሻሻን እንጅ ሌላ የተለየ ውጤትን መጠበቅ ፈፅሞ አይቻልም ።

ለዚህ ደግሞ በእኩያን የህወሃት የፖለቲካ ኢሊቶች የበላይ ዘዋሪነት (ተቆጣጣሪነት) እና ከአምስት ዓመታት በፊት ጀምሮ በተረኝነት ሥልጣነ መንበር ላይ ተሰይመው የጎሳ አጥንት ስሌት ፖለቲካውን ታይቶና ተሰምቶ በማይታወቅ አስከፊና አስፈሪ ሁኔታ እያስኬዱት ባሉት ገዥ ቡድኖች አሽከርነት (መሣሪያነት) ተፈፃሚ የሆነውና እየሆነ ያለው ህገ መንግሥት (ህገ ጥላቻ፣ ህገ መለያየት ፣ ህገ ጭቆና ፣ ህገ ዝርፊያ ፣ ህገ ሰቆቃ፣ ህገ መከራ፣ ህገ ውርደት፣ ህገ ገዳይ/ አስገዳይ/አገዳዳይ፣ ህገ ምድረ ሲኦል፣ ወዘተ) በመሣሪያነት እየተጠቀሰ ካደረሰውና እያደረሰ ካለው ሁለንተናዊ አገራዊ ሰቆቃ በላይ ግዙፍና መሪር ማስረጃ የለም ፤ አይኖርምም። ለእንዲህ አይነት ምንነት፣ ማንነት፣ እንዴትነት እና ከየት ወደ የትነት የዳረገንን የገዛ ራሳችን ግዙፍና መሪር እውነት በመጋፈጥ ትውልዳዊ የሆነ መሠረታዊ ዴሞክራሲያው ለውጥን እውን ከማድረግ ይልቅ ሰንካላ የሰበብ ድሪቶ መደረቱ ስለሚቀናን መቀበል እያቃተን ነው እንጅ በፖለቲካ ታሪካችን ሂደት እንዲህ አይነት በመርዛማ ቆሻሻ ዑደትና ውጤት የተበከልንበት ፈተና አጋጥሞን አያውቅም።

ይህንን አስተያየቴን የተጋነነ ወይም ለገዥ ቡድኖች ከሚኖር ጭፍን ጥላቻ እንደሆነ አድርገው ለማየትና ለማሳየት የሚሞክሩ ወገኖች እንደሚኖሩ በሚገባ እገነዘባለሁ። እንዲህ አይነቱ አስተሳሰብ የሚመነጨው ግን መሬት ላይ ያለውን ግዙፍና መሪር እውነታ ተረድተው የሚጠበቅባቸውን ድርሻ ለመወጣት ጥረት ከሚያደርጉ ወገኖች ሳይሆን አንድም ቀጥተኛ ከሥርዓቱ ተጠቃሚዎች ወይም በንፁሃን ደምና መከራ ከሚነግዱ ግለሰቦችና ቡድኖች ወይም  የሥርዓቱ ፍርፋሪ ለቃሚዎች ከሆኑ የአድርባይነት ልክፍተኞች ወይንም ደግሞ ከእኩያን ገዥዎች የሚመነጨውን መከራና ውርደት እንደ እጣ ፈንታ እንድንቆጥር ካደረገን ሥር የሰደደ ድንቁርና እንደሚሆን ለማወቅ የተለየ እውቀትን አይጠይቅምና ቢያሳዝነኝም አይገርመኝም።

በተለይም የለየላቸው የሥርዓቱ ባለሥልጣናትና ካድሬዎች ፈጣሪ ራሱ ተገልጦ በአምሳሌ በፈጠርኩት ህዝበ አዳምና ሄዋን ላይ ግዙፍና እጅግ አስከፊ የመከራ ዶፍ እያወረዳችሁ ስለ የትኛው ሰላምና ብልፅግና ነው የምተርኩት ወይም የምትሰብኩት ወይም የድል አድራጊነት ዲስኩር የምትደሰኩሩት”? ብሎ ቢጠይቃቸው ይህ በእግዜር አምሳል የተገለጠ ሰይጣን እንጅ እግዜር ራሱ አይደለም እስከ ማለት የሚደርሱ እጅግ ባለጌዎች፣ ደንቆሮዎች ፣ ሴረኞች፣ ሸፍጠኞችና ጨካኞች መሆናቸውንን መሬት ላይ ተዘርግቶ የሚነበበው ድርጊታቸው ስለሚናገር ብዙ ማለት የሚያስፈልገኝ አይመስለኝም።

እንዲህ አይነቱን እጅግ አስከፊና ዘመን ጠገብ አዙሪት ሰብሮ ለመውጣት ከምር የምንፈልግ ከሆነ መሠረታዊ የሆነ ዴሞክራሲያዊ ለውጥን በብሩህ ራዕይ ፣ በፅዕኑ የመርህ፣ የዓላማና የግብ መሠረት ላይ ተመሥርቶ እውን ከማድረግ ይልቅ እገሌ የሚባለው/ዋ ካድሬ ወይም አድርባይ ተሽሮ/ራ እገሌ የሚባል/ትባል ተሾመ/ች ወይም  በሽግሽግ ወደ ሌላ ሥልጣን ተዛወረ/ች ወይም “በክብር” ተሰናበተ/ች ወይም የተቃውሞ ዲስኩር ደስኩሮ/ራ ተሰደደ/ች ወይም በካድሬነቱ/ቷ ወቅት ንፁሃንን ሲያሳስርበት /ስታሳስርበት ወደ ነበረው ከርቸሌተወረወረ/ች  ወዘተ የሚለውን የመርዘኛ ቆሻሻ ዑደት (garbage in, garbage out) ከማመንዠክ ክፉ ልማድ አሁንኑ ሰብረን በመውጣት ለዜጎች ሁሉ የምትመች አገርን እውን ማድረግን ግድ ይለናል። ዘመናትን ያስቆጠረው የሸፍጥ፣ የሴራ እና የጭካኔ ፖለቲካ ባህሪያቸውና ተግባራቸው ግልፅና ግልፅ የሆነውን የጎሳ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ቁማርተኞች የቆሻሻ ግባ እና የቆሻሻ ውጣ (garbage in, garbage out) የፖለቲካ ጨዋታ እንደ ሰላማዊ የሥልጣን መተካካት ፣ እንደ ጤናማ የሥልጣን ሽግሽግ እና በአጠቃላይ እንደ አወንታዊ የለውጥ ሂደት እየቆጠርን ራሳችንን ከደመ ነፍስ እንስሳት በማይሻል ሁኔታ ውስጥ የማግኘታችንን መሪር እውነታ በቅጡ (ከምር) ካልተረዳነውና ካልተፀየፍነው የመረረ የነፃነትና የፍትህ ተጋድሎ ለማካሄድና የምንመኘውን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን ለማድረግ ፈፅሞ አይቻለንም።

የፖለቲካ ብቻ ሳይሆን የሞራልና የሥነ ምግባር ሰብዕና ቀውስ የተጠናወተው የአሁኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ተብየ አብይ አህመድ ከዛሬ ስድስት ዓመታት በፊት የህወሃቱን መለስ ዜናዊ የሙት መንፈስ ተላብሶ (የራሱን የፖለቲካ ብቻ ሳይሆን የሞራል ሰብዕና ለሟች አለቃው በቀፎነት አሳልፎ ሰጥቶ) በጠቅላይ ሚኒስትርነት ሥልጣነ መንበር ላይ የቆየውን ሃይለማርያም ደሳለኝን  ሲተካው እና ታሪካዊ የሆነ ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር (መተካካት) በሚል በመከረኛው ህዝብ ላይ ሲሳለቁበት ከምር በመቆጨት፣ በመፀፀትና በመቆጣት እምቢ ለመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለውጥ ብሎ ለመነሳትና ለማነሳሳት ያለመቻላችን አስከፊና አሳፋሪ ውድቀት ያስከተለብንና እያስከተለብን ያለው ታይቶና ተሰምቶ የማይታወቅ የመከራና የውርደት ዶፍ አሁንም መሪር ተሞክሮ ካልሆነን ምን አይነት መከራና ውርደት ትምህርት ሆኖ ሊያነሳሳን እንደሚችል ከባድ እእቆቅልሽ ነው።

በዚህ ረገድ ቀዳሚው ከፈተና ወዳቂ በአብዛኛው ተማርኩ ብቻ ሳይሆን “ሊቅነት ከእኔ ወዲያ ላሳር ነው” በሚል የሚኮፈሰው የህብረተሰብ ክፍል ነበር። አሁንም ነው። ዘመን ጠገብ የሆነውንና በእጅጉ የተበላሸውን የአገሩን ፖለቲካ በመስማት ሳይሆን በመኖር የሚያውቀው ይህ የህብረተሰብ ክፍል መከረኛው ህዝብ የሸፍጠኞችንና የሴረኞችን “የተሃድሶ ገድል” አክሽፎ የእውነተኛ ለውጥ ባለቤት ይሆን ዘንድ ማነሳሳቱ (እምቢ ለቆሻሻ ግባ እና ቆሻሻ ውጣ ፖለቲካ  ጨዋታ እንዲል) ማስቻሉ ቢቀር እንኳ ለምን? እንዴት? እና ከየት ወደ የት? የሚሉ ጥያቄዎችን ለመጠየቅ ጊዜ ሳይወስድ የአዙሪቱ ሰለባ የሆነ እለት ነበር የመከራውና የውርደቱ ፖለቲካ በአስከፊ ሁኔታ ሊቀጥል እንደሚችል ግልፅና ግልፅ የሆነው።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የእስክንድር ነጋ መልዕክት ከቃሊቲ እስር ቤት - "ለህዝባዊ እምቢተኝነት ሁኔታዎች ተመቻችተዋል"

ካለፈ ስህተትና ውድቀት ተምረን የተሻለ ዛሬንና በጣም የሚሻል ነገን እውን ለማድረግ በሚያስችል ሁኔታ ላይ ብንሆንና ይህንን ግዙፍና መሪር የሆነ የውድቀት ድግግሞሽ በዚህ አይነት የምሬት ስሜት ባልገልፀው ደስ ባለኝ ነበር።

አሁንም ወርቃማ የሆነውን የህልውና ማስከበር እና የመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለውጥን በቆሻሻ ግባ እና በቆሻ ውጣ (garbage in, garbage out)  የፖለቲካ ሥርዓት መቃብር ላይ ስለ መመሥረትና ስለ መገንባት ሳይሆን ከቆሻሻ  የፖለቲካ ዑደት አንዳች መልካም ነገር (ወጤት) ከመጠበቅ ክፉ አባዜ አልተላቀቅንምና ወደድንም ጠላንም የውድቀታችን እንቆቅልሽ እስኪፈታ ድረስ በግልፅና በቀጥታ መነጋገራችን የግድ ነው።

በሙሲያዊው አብይ አህመድ መሪነትና በካምፓኒው (በኦህዴድ/ኦነግ ብልፅግና) መዋቅራዊ አስፈፃሚነት የተካሄደውና እየተካሄደ ያለው ፖለቲካ ወለድ ወንጀል በመርዘኛ የሥልጣን መተካካት ቆሻሻ የጨቀየ መሆኑን ግልፅ ካላደረገልን እውነትም አቻ የማይገኝለት ድንቁርና ፣ የትኛውንም ምድራዊ መከራና ውርደት የመለማመድ አስከፊ ልክፍት ፣ ጨርሶ አቻ የማይገኝለት የአድርባይነት ደዌ ፣ ወደ ተግባር ሊተረጎም የማይችል ተስፈኝነት ፣ ወዘተ አባዜ  በእጅጉ ተጠናውቶናልና ከምር ሊያሳስበን ይገባል።

የተፈጠርንበትን በነፃነት ጥሮና ግሮ የመኖር ዓላማ ከፈጣሪ ድጋፍ ጋር እውን እያደረግን እንደ መልካም ዜጋ እና እንደ ሰው ሰው ሆነን የምንኖርበትን ሥርዓተ ፖለቲካ አምጦ ከመውለድና ከማጎልበት ይልቅ የመርዘኛ ቆሻሻ ፖለቲካ ዑደትንና ውጤትን (መሾምና መሻርን ወይም የጉልቾች መቀያየርን /garbage in, garbage out) እንደ አበረታች (አወንታዊ) የለውጥ አካል የመቁጠራችንን እጅግ ወራዳና አዋራጅ ሁኔታ ከምር ለሚረዳ የአገሬ ሰው ምን ያህል ህሊናውን እንደሚፈታተነው ለመገመት አያስቸግርም።

እውነት ነው በሥራ ሂደት ውስጥ በአቅም ማነስ ወይንም በጊዜያዊ የፍላጎትና የጥቅም ግጭት ምክንያት የመቆሸሽ እንከን ሊያጋጥመው እንደሚችል አካል በመንበረ ሥልጣን ላይ የተቀመጡ ወይም የሚቀመጡ ፖለቲከኞችም የመቆሸሽ ፈተና ሊገጥማቸው እንደሚችል ለመረዳት አያስቸግርም።የማይጠበቅም አይደለም። የእኛ ግን ከዚህ አይነት ሊጠበቅ ከሚችል የመቆሸሽ እውነታ ፈፅሞ ሊታይና ሊነፃፀር የሚችል ጉዳይ አይደለም። ሊጠበቅ ይችላል የምንለው የመቆሸሽ ፈተና ወይም ችግር ቅንነትንና አስተዋይነትን በተላበሰ አስተሳሰብና የተግባር ውሎ መስተካከል (መፅዳት) የሚቼል ሲሆን ለሩብ ምዕተ ዓመት የዘለቀውና ከስድስት ዓመታት ወዲህ ደግሞ የመከራውንና የውርደቱን አገዛዝ እንኳን ለመገመት ለማሰብም በእጅጉ በሚዘገንን ፖለቲካ ወለድ ወንጀል እያስኬደ ያለው ብልፅግና ተብየ ግን ያለ መሠረታዊ የለውጥ ህክምና (ተጋድሎ) በፍፁም የሚስተካከል ወይም የሚፈወስ አይደለም።

እናም ለዘመናት በሥልጣነ መንበር ላይ በመፈራረቅ ወይም ቆሻሻን አስገብቶ ቆሻሻን በመተካት (garbage in, garbage out) የፖለቲካ ጨዋታ በህዝብ ላይ እጅግ አሰቃቂ የመከራና የውርደት ዶፍ ማውረድ በትክክለኛው ሃይማኖታዊም ሆነ ዓለማዊ አስተሳሰብና እምነት እንኳንስ ተቀባይነት ታጋሽነትም ፈፅሞ ሊቸረው የሚገባው ጉዳይ አይደለምና ልብ ያለው ልብ ይበል ።

ለመሆኑ፦

Ø  የአገርን ልዑላዊነት በግልፅ አሳልፎ እየሰጠ (ከሱዳን እና ከደቡብ ሱዳን ጋር በምንዋሰንባቸው አካባቢዎች የሆነውንና እየሆነ ያለውን ልብ ይሏል) የልዑላዊነት  ሥልጣን (ወደ ሥልጣን የማውጣትና ከሥልጣን የማውረድ ሃይል) አለው የሚባለውን የገዛ አገሩን  ህዝብ ለፖለቲካ መንበሩ ያሰጋል በሚል ከውጭ ጠላት በባሰ ጭፍጨፋ  ዝም ጭጭ ያስደርግለት  ዘንድ በቆሻሻ ግባ እና ቆሻሻ ውጣ የፖለቲካ ዑደት (the political cycle of garbage in, garbage out) መርህና አሠራር መሠረት  ለሾመው  ብርሃኑ ጁላ በዓለም ወታደራዊ የሥልጣን እርከን በቀላሉ የማይገኘውን የፊልድ ማርሻልነት ማዕረግ ከማሸከም የከፋ ምን አይነት የህዝብ (የአገር) ንቀት ይኖራል? ምንስ አይነት መርዘኛ የሆነ የቆሻሻ ግባና የቆሻሻ ውጣ የፖለቲካ አዙሪት ይኖራል?

Ø  ሲሆን የፖለቲካው አውድ በየመስኩ ለሚደረጉ ሙያዊ ጥረቶችና ውጤቶች  (professional engagements and products) የሚበጅ እንዲሆን የመልካም ዜግነት ድርሻን በመወጣት ፣ ያ ካልሆነ ደግሞ በሙያቸው የሚችሉትን አስተዋፅኦ በማድረግ የሚጠበቅባቸውን ተልእኮ መወጣት የነበረባቸውንና ያለባቸውን ባለሙያዎች የመርዘኛ ቆሻሻ ግባ እና ቆሻሻ ውጣ ፖለቲካ ጨዋታ ተዋንያን ማድረግ በእጅጉ አስከፊና አስፈሪ  የሆነ ውድቀታችንን ካልነገረን ሌላ ምን ሊነግረን የሚችል ነገር ይኖራል?

 

Ø  በዚህ ደረጃ በበከተና በከረፋ የፖለቲካ ሥርዓት ውስጥ የሚተካኩ ሹማምንቶችና ካድሬዎች (የቆሻሻ ግባ እና የቆሻሻ ውጣ ፖለቲካ እድምተኞች) ንፁሃን ዜጎች እንደ የውጭ ጠላት በምድር እና በአየር ላይ ጦር ለምን የጨፈጨፋሉ? ከእለት ጉርስና ከመጠለያነት የማያልፈው ንብረታቸውስ ለምን ይወድማል?  ሲባሉ “ህግ የማስከበር ጉዳይ ነው” ፣ በፖለቲካ ወለድ ወንጀል ምክንያት ሚሊዮኖች የአሰቃቂ ርሃብ ሰለባዎች ሆነዋል እኮ ሲባሉ “ገፅታችን ለማበላሸት ሲባል እየተጋነነ ነው እንጅ ከቁጥጥራችን አልወጣም/ሰው በርሃብ አልሞተም” ፣ እጅግ አያሌ ቁጥር ያላቸው ዜጎች በሚፈበረክ  የወንጀል ክስ በየማሰቃያው ማእከል እየተሰቃዩ አይደለም ወይ? ተብለው ሲጠየቁ “በፖለቲካ ምክንያት የታሰረ የለም፤ለማነኛውም በህግ እየታየ ያለ ጉዳይ ነው” ፣ አያሌ ንፁሃን በማንነታቸው ሲገደሉና ሚሊዮኖች ደግሞ እጅግ ኢሰብአዊ ለሆነ መፈናቀል ሲዳረጉ ማየት አያስጨንቅም ወይ? ሃላፊነቱስ በዋናነት የመንግሥታችሁ አይደለም ወይ? የሚል መሪር ጥያቄ ሲቀርብባቸው “በለውጥ ሂደት የሚያጋጥም እንጅ እንደሚወራው አይደለምና የሚጣራ ካለም  ይጣራል፤ ተፈናቃዮችንም ወደ አካባቢያቸው ለመመለስ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ነው” ፣ ወዘተ እያሉ በሚጣልላቸው (በሚከፈላቸው) ምንዳእ (ደመወዝና ልዩ ጥቅም) ከርሳቸውን ሞልተው  መኖራቸውን እንደ  የህይወት ስኬት የመቁጠራቸው መሪር እውነት ለማይታጠፍ የነፃነትና የፍትህ ተጋድሎ የማያነሳሳው ትውልድ ምን አይነት ነፃነትንና ፍትህን እንደሚናፍቅና መቸ እውን እንደሚያደርገው ለመረዳት አይከብድም እንዴ?

 

ተጨማሪ ያንብቡ:  የሃገራችን ወቅታዊ ሁኔታና ዲፕሎማሲ ከውስጥም እንመልከት! - መላኩ ከአትላንታ

Ø  ከክልሎች ሁሉ በተለየ የአማራ ክልል እነ ገዱ አንዳርጋቸውን፣ ተመስገን ጥሩነህን፣ ይልቃል ከፍያለን፣ እና የአሁኑን አረጋ ከበደን የመርዘኛ ቆሻሻ ግባ እና ቆሻሻ ውጣ የፖለቲካ ጨዋታ አሻንጉሊቶች (የሰው አምሳል ያላቸው እቃዎች) በማድረግ በህዝብ ላይ  የመከራና የውርደት ዶፍ ባወረደውና እያወረደ ባለው ኦህዴድ/ኦነግ መራሽ ብልፅግና ተብየ የበላይነት ሥር በሚካሄድ ንግግርና ድርድር  ከዘመን ጠገቡ ክፉ የፖለቲካ አስተሳሰብና አካሄድ ተላቀን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን እናዋልዳለን ብሎ ከማሰብ የባሰ የፖለቲካ አስተሳሰብ ድንቁርና እና የሞራል ድህነት ይኖር ይሆን?

 

Ø  ዘመን ጠገብ የሆነውን የጉልቾች የመተካካት (ቆሻሻን አስገብቶ ቆሻሻ የማስወጣት) የፖለቲካ ዑደት አራጊና ፈጣሪ እኩያን ገዥ ቡድኖች ጥሩ ሲሠሩ እያመሰገንና ሲሳሳቱ እየወቀስን ካልያዝናቸው አገር ይፈርሳል የሚሉት እጅግ ደምሳሳና የወረደ የፖለቲካ ማስፈራሪያ የቦቅቧቆች ወይም በቁም እየሞቱ አለን የሚሉ ፖለቲከኞች (cowardly and dead alive politicians) ማስፈራሪያ ካልሆነ ሌላ ምን ሊሆን ይችላል?  የገዛ ራስን መሪር እውነት ከምር በሆነ ፀፀትና ቁጭት ተረድቶ ከዚህ አይነቱ ልክ የሌለው የመከራና የውርደት አዙሪት ሰብሮ በመውጣት ህልውና የሚረጋገጥባት እና ለዜጎቿ ሁሉ የምትመች ዴሞክራሲያዊት አገርን እውን ለማድረግ የበኩሉን ድርሻ የማይወጣ ነፃነትና ፍትህ ፈላጊ ነኝ ባይ ምን አይነት ነፃነትና ፍትህ ነው የሚፈልገው?

 

Ø  ከዛሬ ሰላሳ ዓመታት በፊት ህወሃት በአምሳሉ ጠፍጥፎ በሠራቸው አሽከሮቹ (የሚናገሩ አጋሰሶች) እየተመራ ወደ መሃል አገር ሲገሰግስ ለአሽከርነት ምልመላ ዒላማዎቹ ካደረጋቸው ተቋማት መካከል የትምህርት ተቋማት ዋነኛዎቹ ነበሩ ። የዚህ እኩይ ዒላማው ለመሆን በሙሉ ፈቃደኝነት ይጠባበቁ ከነበሩት ደናቁርትና ትውልድ ገዳይ ፊደል ቆጣሪዎች (አስተማሪዎች) መካከል ደመቀ መኮንን አንዱ ነበር። ለዚህም ነበር በቡሬ (ጎጃም) በባዮሎጅ አስተማሪነት ላይ እያለ በጉጉት ሲጠባበቅ የነበረውን የፍፁም ታማኝነት ካድሬነቱን ተልእኮ በደስታ ተቀብሎ መፈፀምና ማስፈፀም የጀመረው። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የተለያዩ የኢህአዴግ ስምሪቶችን እየተቀበለ (የእኩይ ፖለቲካ መልእክቶችንና ዓላማዎችን የሚጫንና የሚያስተላልፍ አጋሰስ እየሆነ) ለሰላሳ ዓመታት ካገለገለ በኋላ ከሰሞኑ “በል በቃህ ጥቅማጥቅምህን ይዘህ ዘወር በል” ሲሉት ውርደቱን እንደ ክብር ቆጥሮ ፣ በአጠቃላይ በመላው ህዝብ እና በተለይ ደግሞ ተገኘሁበት በሚለው ማህበረሰብ ላይ የፈፀመውንና ያስፈፀመውን ግፍ  እንደ  መልካም ውለታ ቆጥሮ፣ አጋሰስ ካድሬነቱን (መሣሪያነቱን) ትጉህና ቅን መሪ አስመስሎ ፣ ከራሱ አልፎ የቤተሰቦቹ ማፈሪያ የመሆኑን መሪር እውነታ የኩራት ተምሳሌት አድርጎ ፣ ወዘተ ሊያሳምነን (ሊያቄለን) ሲሞክር መስማትና ማየት ቅንና ሚዛናዊ ህሊና ባለው የአገሬ ሰው ላይ የሚያሳድረውን ህመም ስንቶቻችን ነን ከምር የምንጋራው? ታዲያ መቸና እንዴት ነው ከዚህ አይነቱ የእኩያን ፖለቲከኞች የጉልቾች መተካካት (ቆሻሻ ግባ እና ቆሻሻ  ውጣ) አዙሪት ሰብሮ በመውጣት እውነተኛ ዴሞክራሲያዊት አገርን እውን ማድረግ የሚቻለው?

 

Ø  የደመቀ ድርብ የታማኝ ካድሬነት ሥልጣን የተቸራቸው ሁለት ግለሰቦች ናቸው። አንደኛውና በአብይ አህመድ መልካም ፈቃድ የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ሹመተ ቅብአት የተቀባው በግልፅ የባለጌዎች፣ የሸፍጠኞች፣ የሴረኞች ፣ የፈሪዎችና የጨካኞች ስብስብና እጅግ አስከፊ የኢህአዴግ ውላጅ የሆነው የብልፅግና አባል የሆነው እና ሰብዕናውን ለእኩያን ገዥዎች ሶፍት ዌር ማስቀመጫነት (as a hardware) አሳልፎ የሰጠ መሆኑን ባህሪውና ድርጊቱ የሚመሰክርበት ተመስገን ጥሩነህ ነው። ለጌቶቹ፣ ለቢጤዎቹ፧ ለፍርፋሪ ለቃሚ አድርባዮች ካልሆነ በስተቀር የዚህ ሰው ምንነት፣ ማንነት ፣ ለምንነት፣ እንዴትነት፣ እና ከየት ወደ የትነት ግልፅና ግልፅ ስለሆነ ብዙ ማለት የሚያስፈልገኝ አይመስለኝም።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የኤፍሬም ማዴቦ ሸፍጥ፤ ያይጥ ምስክሯ ድንቢጥ (ክፍል 2) - መስፍን አረጋ

 

Ø  ሌላኛው ደግሞ “አባል አይደለሁም” በሚል ሽፋን በሥልጣነ መንበር ላይ ለሚፈራረቁ እኩያን ገዥ ቡድኖች ሁሉ ከለየላቸው ካድሬዎቻቸው በባሰ ሁኔታ በፍፁም ታማኝነት ለረዥም ጊዜ ያገለገለው (የራሱ የሆነና ሥር የሰደደ ወይም አብሮት ያደገና የጎለመሰ የአድርባይነት ፍልስፍና እና ባህሪ የተጠናወተው) እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ሹመተ ቅብአትን የተቀባው ታየ አፅቀ ሥላሴ ነው።  ለሦስት ዓሥርተ ዓመታትና በተለይም ከስድስት ዓመታት ወዲህ አገረ ኢትዮጵያን የንፁሃን ዜጎች (ልጆቿ) ምድረ ሲኦል ያደረጓትንና እያደረጓት ያሉትን እጅግ ባለጌና ጨካኝ ገዥ ቡድኖች መመሪያና ትእዛዝ እየተቀበሉ ንፁሃንን እንደ ወንጀለኛ እና  በሌላ በኩል ግን ጨካኝ የፖለቲካ ሰይፋቸውን  እንደ ህግና ሰላም አስከባሪ በማድረግ በዲፕሎማሲ ስም ርካሽና አደገኛ የፖለቲካ ፕሮፓጋንዳ  ያካሄዱትንና አሁንም እያካሄዱ ያሉትን ወገኖች አካፋን አካፋን ለማለት በሚያስችል አቋምና ቁመና ቢያንስ ነውር ነው ማለት የግድ አይለንም ወይ?

እንደ ታየ አይነት እጅግ አሳሳችና አደገኛ ግለሰቦችን ጎምቱ ዲፕሎማት፣ በታላቁ ግድብ ጉዳይ ዙሪያ ግብፅን ያንቀጠቀጡ፣ ህወሃትና ብልፅግና ባካሄዱት ጦርነት ብልፅግናን ወክለውና ሸንጣቸውን ገትረው የተከራከሩ ፣ ለአብይ አህመድ የኖቬል እና የፋኦ ሽልማት መብቃት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደረጉ ፣ የአብይ አህመድን የመናፈሻ፣ የችግኝ ተከላ፣ የመንገድ ጥረጋ፣ ወዘተ ዘመቻ በዓለም አድናቆትን እንዲያተርፍ ያደረጉና እያደረጉ ያሉ በሚል መከረኛውን ህዝብ ጨምሮ የርካሽ ፕሮፓጋንዳ ሰለባ የማድረጋቸው መሪር እውነት የሚነግረን የዲፕሎማሲን እውነተኛ ምንነትና ለምንነት (የህዝብ/የብሔራዊ ጥቅም ማራመጃና ማስከበሪያነት) ለባለጌና ጨካኝ ገዥ ቡድኖች ርካሽ የፖለቲካ አጀንዳ ማስፈፃሚነት እንዲውል የማድረጋችንና በማድረግ ላይ የመሆናችንን መሪር እውነታ ነው።ታዲያ ለዚህ ሁሉ አስከፊ ሁኔታ መቀጠል ዋነኛው ምክንያት ሴረኛ፣ ሸፍጠኛና ጨካኝ የጎሳ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ሥርዓት ዘዋሪዎች (አራጊና ፈጣሪዎች) የሚያካሂዱትን የጉልቻ መቀያየር (የቆሻሻ ግባ እና ቆሻሻ ውጣ) ፖለቲካ እንደ የተሃድሶ ለውጥ እና  የሰላማና የልማት ዋስትና እያደረጉ ሲሳለቁብን ለዚሁ በሚመጥን የጋራ ትግል አደባባይ ላይ ለመሰባሰብ አለመቻላችን ነውና አሁንም ተጨማሪ ጊዜ እና ሌላም ውድ ነገር ሳናባክን ህልውና ለሚረጋገጠባትና ነፃነትና ፍትህ (ዴሞክራሲ) ለሚሰፍንባት አገረ ኢትዮጵያ እልህ አስጨራሽ ተጋድሎ በማካሄድ ላይ ከሚገኙ ወገኖች ጋር ከምርና ጨርሶ ወደ ኋላ በማይመለስ አቋምና ቁመና መተባበርን የማይቀበል ነፃነትና ፍትህ ፈላጊ ይኖርህ ይሆን?

 

Ø  እስኪ ለመሆኑ የትኛ ው/ዋ የቅንና የሚዛናዊ ህሊና ባለቤት የአገሬ ሰው ነው/ናት  ንፁሃን በገፍና በግፍ ቢገደሉም፣ ለማይተካ የአካል ጉዳት ቢዳረጉም፣ ለሰቆቃዊ መፈናቀል ቢጋለጡም ፣ በየማሰቃያ ማእከሉ የከባድ ሰቆቃ ሰለባዎቸ ቢሆኑም ፣ ህፃናት ከወላጆቻቸው አስከሬን ሥር ተቀምጠው በእንቅልፍ ቢንገላቱም ፣ እናት ከማህፀኗ ተተርትሮ እንዲወጣ ከተደረገው ልጇ ጋር ህይወቷ ቢያልፍም፣ ቤተ እምነቶች ከአገልጋዮቻቸውና አማኞቻቸው ጋር በእሳት ቢጋዩም፣ እጅግ አያሌ ቁጥር ያላቸውን ህፃናትንና አረጋዊያንን ጨምሮ በአያሌ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ንፁሃን ወገኖች በአስከፊ የርሃብ ቸነፈር ቢመቱም ፣ ወዘተ “ታሪካዊ”  ግድብ ወይም መንገድ ወይም መታሰቢያ ወይም መናፈሻ ፣ ወዘተ ከተሠራልኝ ለደስታዬ ወሰን የለውም የሚል (የምትል)?

Ø  የትኛው እውነተኛ ሃይማኖታዊ እምነት ነው በፈጣሪ አምሳል የተፈጠረው ሰብአዊ ፍጡር (ሰብአዊ ህንፃ) በባለጌና በጨካኝ ገዥዎች ለማመን በሚከብድ አኳኋን ቢወድምም ቁሳዊ ፕሮጀክቶች እዚህና እዚያ እስከ ተገነቡ ድረስ ደስ ይበላችሁ የሚል???

Ø  የትኛው ትክክለኛ ዓለማዊ አስተሳሰብና ፍልስፍና ነው በነፃነት፣ በፍትህና በተገቢው አያያዝ ቢያድጉ ፣ ቢማሩና ቢመራመሩ አገራቸውን በአጭር ጊዜ ውስጥ ምድረ ገነት በሚያደርጉ የእድገትና የልማት አውታሮችና መረቦች ሊያጎናፅፉ የሚችሉ ህፃናትና ታዳጊ ወጣቶች ህይወት በእኩያን ገዥ ቡድኖች ጨካኝ ሰይፍ ቢሰየፉም የእነ አብይ/የእነ ብልፅግና ፕሮጀክቶችን በአድናቆትና በምሥጋና መቀበልና መደገፍ ተገቢ ነውና ተቀበሉና ደግፉ  የሚለው? ሁለገብ እውነትን በውስጣቸው የተሸከሙ ንፁሃን ወገኖችን መገደል እውነትን ራሱን መግደል አይደለም እንዴ???

 

የአሁኖቹ ተረኛ ገዥ ቡድኖች ለሩብ ምእተ ዓመት የዘለቀውን ቆሻሻን አስገብቶ በቆሻሻ የመተካት እጅግ መሪር የፖለቲካ ሥርዓት ዑደትን እንደ ዴሞክራሲያዊ ፣ ሰላማዊና የሥልጡኖች ፖለቲካ እያስመሰሉ የፖለቲካ ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ የሰብእና ቀውስ ልክፍተኛ በሆነው አብይ አህመድ አማካኝነት ሊያሳምኑን የመሞከራቸው ድፍረት የሚነግረን እንደ አገር (እንደ ህዝብ) እየወረድን ያለንበትን አስከፊና አስፈሪ ሁኔታ ነውና በስሜታዊነትና በክስተቶች ፈረስ ከመጋለብ ተቆጥበን የየራሳችንን ህሊና መጠየቅ ግድ ከሚለን ጊዜና ሁኔታ ላይ ነው የምንገኘውና ልብ ያለው ልብ ይበል።

 

 

1 Comment

  1. ውድ ወንድሜ ጠገናው፦
    እርር ድብን ያልህበትን የትዮጵያን ፖለቲካ ” ቆሻሻ ግባ ፣ ቆሻሻ ውጣ” በማለት መግለጥህ የሚጠበቅ ነው። ግን ምን ይደረገ በሚለው ላይ ምክር አልሰጠህም ? ፖለቲካችን ከሰውነት ወደ አውሬነት እንደተጓዘማ ሁሉም ያውቃል። ሰው ገድሎ፣ ቆራርጦ ከተማ መሀል ዝቅዝቅ የሚሰቅል ሕብረተሰብ ሌላም ያደርጋል። ችግራችን እንዴት ወደ ሰውነትና ወደምትከበር ኢትዮጵያ እንሸጋገር የሚለው ነው። ከሆዳምነትና ከቡድን አሠራር ወደ አገራዊ ዓላማና የጋራ ዕድገት እንዴት እንሸጋገር ለሚለው ተማርሁ፣ ሊቅ ነኝ እያለ በባዶ የሚኮፈሰው ሁሉ ሊጠበብበት ይገባል። በዚህም ሆነ በሌላ አምድ ላይ መሰዳደቡ፣ እርር ድብን ማለቱ፣የመንግሥትን ደካማነት መደርደሩ፣ የሥርዓቱን ቆሻሽ ማጋለጡ የትም አያደርሰንም። የሚሻለን እንዴት ከቆሻሻና ከውርደት እንውጣ በሚለው ላይ አውቃለሁ የሚለው ሁሉ መረባረብ አለበት ። ቆሻሻው በፖለቲካው፣ በሥነ ምግባሩ፣ በትምሕርቱ፣ በኢኮኖሚው፣ በምሁሩ፣ ወዘተ ተስፋፍቷል። እንዴት ቆሻሻውን ጠራርገን ኢትዮጵያን የጋራችን የምታድግ የሰው አገር እናድርጋት ላይ እንረባረብ።

    ባደረግሁት መጠነኛ ንባብ፣ የግራ ዘመሞች ስሜታዊ ተማሪዎች አቢዮቶች አልሠሩም። እንዳየነው፣ ልጅ ያቦካው ለእራት አልበቃም። በምዕራባውያን መንደር በፈረንሳይና በአሜሪካ የተደረጉት አብዮት፟-አከል ትርምሶች ውጤት አስገኝተዋል። በደቡብ አፍሪቃም በኔልሰን ማንዴላ የተመራው ለውጥ በመጠኑ ተሳክቷል። እneዚህ ሁሉ አንድ የጋራ ባሕርይ አላቸው፣ ሁሉም አገራዊ ዓላማ ያላቸው መሪዎች ነበሯቸው። ከእነዚህም ይበልጥ ያደንቅሁት የጃፓንን የ1860 ዎች አብዮት ወይም ለውጥ ነው። ለውጡ የተነሳው በወቅቱ የነበረው አምባ ገነን አገዛዝ ለምዕራባውያን ጫና መንበርከኩ ነበር። ይህ ውርደት የቆጫቸው መሣፍንትና መኳንንት ተሰባስበው ዘምተው አምባ ገንኑን አስወግደው የMeiji ን ንጉሣዊ ሥርዓት እንደገና መልሰው፣ ከመካከላቸው አንዱን መስፍን መሪ አድርገው፣ በሶስት ጥሬ ዕቃዎች የውጭ ንግድ ድጋፍ፣ በ30 ዓመት ውስጥ ጃፓንን የሩቅ ምሥራቅ ኃያል አገር አደርጓት ። እዚህ ላይ፣ ቁም ነገሩ መሪዎች መሣፍንትና መኳንንት መሆናቸውና ንጉሣዊ ሥርዓትም መመለሱ ሳይሆን፣ የለውጥ መሪዎች ደላሎች፣ በቀለኞች፣ ሀብት አሳዳጆች ወይም የቡድን ጥቅም አራማጆች ሳይሆኑ፣ አገር ወዳዶች መሆናቸው ነው። እኛ እስካሁን አገር ወዳዶች ወይም አርበኞች አገር የመሩበት ለውጥ አልገጠመንም። የ1960ዎቹ ተማሪዎች ያልበሰሉ ተማሪዎች ነበሩ፣ ደርግ በበቀልና በጥቅም የተነሳሳ ነበር፣ ሕወሀት መራሹ ኢሕአዴግ በበቀልና በቡድን ጥቅም የተነሳሳ ነበር፣ ብልፅግናም የኢሕአዴግ ውላጅ ነው። ስለዚህ፣ ኢትዮጵያ ተረስታ፣ ሁሉም እንዴት እንደሚገዛንና ለቡድኑ እንደሚያተርፍ ሲቸገር የኖረ ነበር። ለውጥ መሪዎችና ፈላጊዎች፣ የ1960ዎች ተማሪዎች ጭምር፣ ከልብ ለኢትዮጵያ አንድነት፣ ሉዓላዊነትና የጋራ ዕድገት የቆሙ አልነበሩም። ውጤቱ ሰፊ ለም መሬት፣ አያሌ ወንዞች፣ በሚሊዮን የሚቆጠር ሥራ ፈት ወጣና ሰፊ የማዕድን ሀብት ባላት ለሁሉም በምትተርፍ አገራችን ትርምስ፣ ጦርነት፣ ድህነት፣ ስደት፣ ውርደትና የቁልቁለት ጉዞ አመጣን። የሚበጀን፣ አገር ወዳድ ለውጥ መሪዎች፣ በባዶ የማይኮፈሱና አገር ወዳድ “ሊቃውንት” የሁሉም መነሻና መሪ ሆነው ሁሉን ኢትዮጵያውያን ያቀፈና ሁላችንንም እኩል የሚያይና የሚያከበር፣ ለጋራ እኩል ዕድገት የተቀረጸ መንግሥታዊ ሥርዓት መመሥረት ነው። ዛሬ ያለው ሕገ መንግሥት በ9 ክልሎች 9 ጎሣ አንግሶ፣ 74 ጎሣዎችን ለዘጠኙ ጎሣዎች ጥገኛ ያደረገ፣ ፍጹም ኢዲሞክራሲያዊ የሆነ፣ ለዚያውም ባረቀቁትም ሹማምንት እንኳ፣ ቅጣት ስለሌለባቸው፣ የማይከበር የማስመሰያ፣ ከፋፋይና የተምታታ ድርሰት ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share