February 4, 2024
38 mins read

የህልውና ተጋድሎው በዴሞክራሲያዊት አገር እውን መሆን ይጠናቀቅ ዘንድ…

February 5, 2024

ጠገናው ጎሹ

 

በየሃይማኖታዊ እምነትም ሆነ እውነተኛ በሆነ ምድራዊ (ፖለቲካዊ) እምነትና አስተሳሰብ  የጥንብም ጥንብ  ለሆነው የጎሳ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ወለድ ቀውስና ፈተና  ያለንበትን ዘመን በሚመጥን ሁኔታ መፍትሄ ለማግኘትና ለማስገኘት አጥጋቢና ዘላቂ የጋራ ጥረት (ትግል) ለማካሄድ ባለመቻላችን በጊዜ ርዝማኔም ሆነ በአስከፊነት መመዘኛ ሲመዘን እንደ ግለሰብም ሆነ እንደ ማህበረሰብ (እንደ ህዝብ) ተያይዘን የወረድንበት የመከራና የውርደት ቁልቁለት ከቶም ማነፃፀሪያ አይገኝለትም። አዎ! በቀደምት ትውልዶች ፈፅሞ የዋጋ ተመን የማይገኝለት የደምና የአጥንት መስዋእትነት ተሠርቶና ተጠብቆ የተሰጠንን የአገር ባለቤትነት ድንቅ ታሪክ በውጭ ወራሪ ሃይል ሳይሆን በገዛ ራሳችን ደጋግሞ የመውደቅ አስከፊ ደዌ (ልክፍት) ምክንያት በዚህ በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የዓለም ከንፈር መምጠጫ፣ “የታሳስቡናላችሁ” መግለጫ፣ የርሃብና የእርዛት መገለጫ (ምሳሌ)፣ እና በአጠቃላይ የሁለንተናዊ ኋላ ቀርነት ማሳያ ከመሆን አስከፊና አሳፋሪ ምንነትና ማንነት ሰብረን ለመውጣት አልቻልንም።

ይህንን ስል እስካሁን ባለመቻላችን ፣ አሁንም ከፈተናችን ክብደት አንፃር ሲታይ እየቻልን ባለመሆናችን ነገ ወይም ከነገም ወዲያ አይቻለንም ለማለት አይደለም።እንዲህ አይነት ደምሳሳና ተስፋ ቢስ እሳቤ እንኳንስ እጅግ ሰፊና ጥልቅ የሆነውን ዴሞክራሲያዊት አገርን እውን አደርጋለሁ ለሚል  ራዕይና ዓላማ ለየትኛውም አወንታዊ የህይወት ሂደት ፈፅሞ የማይጠቅም መሆኑ አያጠያይቅምና።

ለ17 ዓመታት የፖለቲካ ተልእኳቸውና ግባቸው ማስፈፀሚያ በመሆን ሲያገለግል የነበረውን ህወሃት ሠራሽ የቃል ኪዳን ሰነዳቸውን (ፕሮግራማቸውን) በዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች መከበር ምዕራፎችና አንቀፆች ስም ጀቡነው (ሸፍነው) ወደ ህገ መንግሥትነት በመለወጥ ለሩብ ምእተ ዓመት (እ.ኢ.አ 1983- 2010) በራሱ በህወሃት ፍፁም የበላይነት እና ጠፍጥፎ በሰራቸው የኢህአዴግ ተብየው አባል ድርጅቶች አሽከርነት ሲገዙበትና ሲዘርፉበት የመኖራቸው መሪር ሃቅ ገና ተዘግቦ ያላለቀና ወደ ታሪክ መዘክር ያልገባ የፖለቲካ ብቻ ሳይሆን የአጠቃላይ ውድቀታችን ታሪክ አካል ነው።

ይኸውና አሁን ደግሞ ራሳችንን እጅግ ታይቶና ተሰምቶ በማይታወቅ ሁኔታ ውስጥ ካገኘነው ለስድስት ዓመት ጥቂት ወራት ብቻ ቀርተውታል። ለዚህ ትውልዳዊ ውድቀትና መከራ ከዳረጉን እጅግ አስከፊ ስህተቶቻን (ድክመቶቻችን) መካከል አንዱ ዴሞክራሲያዊ ለውጥን መሠረታዊ ከሆነ የፍኖተ ለውጥ   ራዕይ፣ መርህ፣ ዓላማ፣ አቋምና ቁመና አንሸራተን ለሩብ ምእተ ዓመት በፖለቲካ ወለድ ወንጀል ከበሰበሰና ከከረፋ ሥርዓት ለተገኙና የጎሳ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ሥርዓቱን እንኳንስ ለማመን ለማሰብም በሚከብድ ሁኔታ ላስቀጠሉት ሸፍጠኛ፣ ሴረኛና ጨካኝ ገዥ ቡድኖች አሳልፈን የመስጠታችን መሪር እውነታ ነው።

አዎ! ጥንብ የሆነውን የጎሳ አጥንት ስሌት ፖለቲካ እምነት፣ አስተሳሰብ እና አካሄድ እየተጋቱ ያደጉ እና ሥልጣነ መንበሩን በበላይነት ከፈጣሪያቸውና ከአሳዳጊያቸው ህወሃት ላይ ነጥቀው ከተቻላቸው በአብዛኛው ኢትዮጵያዊ የደም ጎርፍና የመከራ ዶፍ ኢትዮጵያን ሰጥ ረጭ አድርገው ለመግዛት፤ ይህ ካልሆነ ግን “ታላቋንና ልዑአላዊት ኦሮሚያን” ወይም ለእኩይ ፖለቲካቸው በሚያመች ሁኔታ በሚተርኩት የኩሽ ነገድ ስም “የምሥራቅ አፍሪካ ኢምፓየርን” ለመመሥረት ያሰቡና የተዘጋጁ ኦህዴዳዊያን/አነጋዊያን/ ኦሮሙማዊያን እጅግ የከፋ የፖለቲካ ሰብእና ብልሽት ብቻ ሳይሆን እጅግ አስከፊ ( deeply miserable) የሆነ የሞራልና የሥነ ምግባር  ቀውስ በተጠናወተ አብይ አህመድ አማካኝነት “ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት” በሚል እጅግ  አማላይ (አዘናጊ) ዲስኩራቸው ጠልፈው ሲጥሉን ተጠልፈን የወደቅንላቸው ጊዜ ነበር  ፈፅሞ ለማሰብ በሚከብድ የመከራና የውርደት አዘቅት ውስጥ ራሳችንን ያገኘነው።

በእጅጉ የሚያሳዝነው ደግሞ የዚህ አይነት እጅግ አስቀያሚ የፖለቲካ ትወና (ጨዋታ) የመጀመሪያው ሰለባ “ከእኔ በላይ ፊደል መቁጠር (መማር) ለአሳር ነው” በሚል ራሱን በከንቱ ውዳሴ የሚያንቆለጳጵሰው (የሚያሞካሸው) የህብረተሰብ ክፍል የመሆኑ መሪር እውነት። እያልኩ ያለሁት መበረታትና መመስገን ያለበት መበረታትና መመስገን አይገባውም አይደለም። እያልኩ ያለሁት እንኳንስ ለሩብ መቶ ክፍለ ዘመን የጎሳ አጥንት ስሌት ፖለቲካ መርዝን ሲጋት ያደገና የጎለመሰ ፖለቲከኛ በአንፃራዊነት “ከዚህ አይነት የፖለቲካ ጨዋታ ነፃ ነኝ” የሚል ግለሰብ ወይም ቡድን መሪ ነኝና ተቀበሉኝ ብሎ ቢመጣ ቢያንስ ማን ነህ /እነማን ናችሁ? ከየት ወደ የት? ከምንስ ወደ ምን? ለምን? ከመቼ ወዲህ? እንዴት? የሚሉ የአንድን ነገር/አካል ለመገንዘብ የሚያስችሉ መሠረታዊ ጥያቄዎችን ጠይቆ ለመረዳት የተሳነው ምሁርነትንና ሊቀ ሊቃውንትነትን ከምር ተፈተሽ (ተጠየቅ) ካላልነው ከአስከፊው የውድቀት አዙሪት አንወጣምና ከምር እንውሰደው ነው ።

ይህንን የምለው አሁንም እንደ ሥርዓት ፈፅሞ የበሰበሰውንና የከረፋውን ሥርዓት በጋራ እና በሁለገብ ተጋድሎ አስወግዶ ለሁሉም ዜጎቿ/ልጆቿ የምትመች ዴሞክራሲያዊት አገርን እውን ለማድረግ የሚደረጉ ተጋድሎዎችን ገንቢነት ባለው ሂሳዊ ሃሳብ እና በሌሎች የድጋፍ አይነቶች ከማበረታታት/ከማጠናከር ይልቅ ፈፅሞ ከእውነት እና ከሰብአዊነት አስተሳሰብ ምህዋር ተንሸራተው ሳይሆን ተምዘግዝገው የወደቁትን እኩያን ገዥ ቡድኖች  “እባካችሁ ስለ ፍትህና ሰብአዊ መብት ብላችሁ በጎ ቀን (ጊዜ)  እንዲመጣ አድርጉልን” የሚል እጅግ የወረደና አዋራጅ የትንታኔ ድሪቶ የሚደርቱ ፊደል ቆጣሪዎች ቁጥር ቀላል ስላልሆነ ነው።

እንደ እውነቱ ቢሆንማ መማር (ምሁርነት) ህዝብ ሊያጋጥመው የሚችለውን ወይም ያጋጠመውን የተፈጥሮም ሆነ ሰው ሠራሽ ቀውስ ለመዋጋት የሚያስችል መሣሪያ (education is the means to fight against catastrophe) ነበር/ነውም። መቸም የገዛ ራሳችንን ግዙፍና መሪር እውነታ በግልፅና በቀጥታ ተጋፍጠን የመማርን ምንነትና እንዴትነት ማሳየት ሲሳነን የሚቀናን በሰንካላ የሰበብ ድሪቶ ውስጥ መሸሸግ  ክፉ ልማድ ሆኖብን ነው እንጅ  አሁንም  መማርን ወይም ትምህርትን  ያለንበትን የውድቀት አዙሪት ሰብሮ ለመውጣት ከመጠቀም ይልቅ ፖለቲካ ወለድ የሆነውን የመከራና የውርደት ዶፍ ያለ በቂ የመፍትሄ ሃሳብ (ያለ ገንቢ ሂሳዊ ፍሬ ሃሳብ) በመጽሐፍ ወይም በሌላ መልክ እያስደጎስን (እያስጠረዝን) ለገበያ ማቅረብን ትልቅ ትውልዳዊ ሃላፊነትን እንደተወጣና ብንሞትም እንደማንሞት አድርገን ራሳችንን እየሸነገልን ቀጥለናል።

ለተጨማሪ የመከራና የሰቆቃ ዘመን እድል የመስጠቱ ክፉ ልማዳችንን አደብ እየገዛን መመርመርና በቅጡ ማድረግ ይኖርብናል። ትናንት ግሩም ድንቅ ስለሆነው መጽሐፉ ወይም መጣጥፉ ወይም ማስታወሻው ሲተርክልን የነበረ ምሁር (ደራሲ- ፀሃፊ) ዛሬ በየሚዲያው ወይም ባገኘው አጋጣሚ እየተሰየመ የህልውና ትግልን ለሁሉም ዜጎቿ የምትመች ዴሞክራሲያዊት  ኢትዮጵያን እውን ከማድረግ ራእይ፣ ዓላማና ግብ ጋር አጣምሮ እየተካሄደ ያለውን እልህ አስጨራሽ ተጋድሎ ግልፅ፣ ቀጥተኛ፣ ቅንና ገንቢ በሆነ ሂሳዊ ይዘትና አቀራረብ ከማገዝ ይልቅ እንኳንስ እንደ እኛ ባለ እጅግ አስከፊ በሆነ ፖለቲካ አውድ ውስጥ የሚገኝ የነፃነትና የፍትህ ትግል ማነኛውም የሚሠራ ሰው ሊያጋጥሙት የሚችሉትን ስህተቶች እና ከግለሰቦች ንግግር የሚከሰቱ እንከኖችን በማግዘፍና የውድቀት ምክንያት በማድረግ የፋኖን እና ዓላማውን ተጋርተው ድርሻቸውን እየተወጡ ያሉ በርካታ ኢትዮጵያንን ጥረት ለማጣጣል ሲሞክር  መታዘብ ባያስደንቅም ያሳዝናል።

እናም ለዘመናት ከመጣንበትና በአሁኑ ወቅ ደግሞ ለመግለፅም በሚያስቸግር ሁኔታ ተዘፍቀን የምንገኝበትን አስቃቂ ፖለቲካ ወለድ እውነታ (tragic political reality) ተጋፍጠን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን ማድረግ ካለብን ከእንዲህ አይነቱ የተንሸዋረረ ወይም በአድርባይነት የተበከለ ወይም ከለየለት ድንቁርና በባሰ ደረጃ በእኔ ምን አገባኝነት ደዌ የተለከፈ የምሁርነት ባህሪን ከምር መታገል (በሃሳብ) ይኖርብናል። 

ይህንን ለመካድ ወይም ለማስተባበል ወይም ለማጣጣል ወይንም ደግሞ በጎ ለውጥ የመጣ ይመስል “በለውጥ ወቅት ሊያጋጥም እንደሚችል ፈታኝ ሁኔታ” አድርጎ የማየትና የማሳየት ሙከራ የሚመነጨው ከለየላቸው የንፁሃን ደም ነጋዴ ገዥ ቡድኖችና ግብረ በላዎቻቸው ወይም የአድርባይነት ልክፍተኞች ከሆኑ የሁለቱም ዓለም (የገሃዱና የሃይማኖታዊው ዓለም)  ምሁራንና ሊቀ ሊቃውንት ነን ባዮች ወይንም መከራንና ውርደትን እንድንለማመድ ከተደረግንበት ድንቁርና (ignorance) ካልሆነ በስተቀር ዘመን ጠገቡን ፖለቲካ ወለድ የህይወት ምስቅልቅል በመስማት ሳይሆን በመኖር ከሚያውቅና ብቸኛው መፍትሄ መሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ለውጥን እውን ማድረግ መሆኑን አምኖ የድርሻውን  ለመወጣት ከሚፈልግና ዝግጁ ከሆነ የአገሬ ሰው ፈፅሞ አይሆንም ።

የህልውና አደጋ እና የመከራ ዋናው ምክንያት (root cause of existential threat and painful suffering) የሆነውን የባለጌ ፣ የፈሪና የጨካኝ ገዥ ቡድኖች ሥርዓት በተባበረ ዴሞክራሲያዊ አርበኝነት በማስወገድ  የሁሉም ዜጎች የግልና የቡድን መሠረታዊ መብቶች መከበር ለታላቁ የኢትዮጵያዊነት እሴትና ማንነት ይበልጥ ክብርና ጌጥ የሚሆኑበትን ሥርዓት  እውን ከማድረግ እጅግ ግዙፍና የተቀደሰ ራዕይ፣ መርህ፣ ዓላማ፣ ስትራቴጅ፣ እቅድና ግብ ጋር አቆራኝቶ የማስኬዱ ጉዳይ ለነገ የሚባል ጉዳይ መሆን የለበትም። ህልውናን እንደ ደመ ነፍስ እንስሳት መሠረታዊ የህይወት ማቆያ ግብአቶችን እያገኙ እንደመኖር አድርገን ካላየነውና ካልተቀበልነው በስተቀር።

ለዚህም ነው የአማራ ፋኖን እና ትግሉን በመጋራት የበኩላቸውን ጥረት በማድረግ ላይ የሚገኙትን ወገኖች ገንቢ፣ ወቅታዊ ፣ሁለገብ እና ውጤታማ በሆነ ድጋፍ ማጠናከርና የታለመለትን ዴሞክራሲያዊት አገር እውን የማድረግ ዓላማና ግብ እንዲመታ ማስቻል ፍፁም ሊያመልጠን የማይገባ መልካም እድል ነው  ማለት ትክክለኛ መልእክት የሚሆነው።

በገሃዱ ዓለም ብቻ ሳይሆን በአምላካዊው ዓለምም ፍፁም ትክክለኛና ፍትሃዊ ከሆነ ምክንያት የተነሳውንና ይህንንም በአስገራሚ የሽምቅ ውጊያ ጥበብ፣ አስደማሚ በሆነ የዲሲፕሊን ተገዥነት ፣ አርአያነት ባለው የሥነ ልቦና እና የሥነ ምግባር ማንነት፣ ህልውና ማረጋገጥን እና ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን እውን ማድረግን አቆራኝቶ በያዘ የፖለቲካ እምነትና የተግባር ውሎ ላይ ተመሥርቶ እየተካሄድ ያለው የአማራ ፋኖ ተጋድሎ እንከን አልባ ሊሆን አይችልም። ይህ እንኳንስ ለዘመናት የዘለቀውን እጅግ አስከፊና ውስብስብ የሆነ የፖለቲካ ሥርዓት ለማስወገድ ለሚደረግ ትግል ለማነኛው የለውጥ ሂደት ትግል የሚቻል አይደለምና።

ማድረግ የሚቻለውና መሆን የሚችለው ወሳኝነት ያላቸውን ጥንካሬዎች በገንቢ ሂሳዊ አስተያየትና ሌሎች አስፈላጊ ድጋፎች ይበልጥ የማጠናከሩ ጉዳይ በእጅጉ አስፈላጊ ከሆነበት ጊዜና ሁኔታ ላይ መሆናችንን ከምር ተረድቶ የበኩልን ድርሻ በመወጣት መልካም ምኞትና ራዕይ እውን እንዲሆኑ ማስቻል ነው። መልካም እድልን በአግባቡ ማለትም በእውቀት፣ በጥበብ፣ በቅንነት ፣ በሞራላዊና ሥነ ልቦናዊ ልእልና  እና በወቅቱ መጠቀም ፖለቲካ ወለድ የጋራ መከራንና ውርደትን አሳጥሮ የጋራ ደስታንና ክብርን ሊያጎናፅፍ የሚችለውን ሥርዓተ ማህበረሰብ ለማዋለድ ያለው የወሳኝነት ሚና የሚያጠያይቀን አይመስለኝም።

ፀሐይ የሞቀውንና የእያንዳንዱን ንፁህ የአገሬ ሰው ህይወት ያመሰቃቀለውን የባለጌና የጨካኝ ገዥ ቡድኖች ፖለቲካዊ ባህሪና ድርጊት እና እነርሱው እያዘጋጁ የሚያድሉንን (የሚሰጡንን) አጀንዳ ደጋግመን ከማመንዠክ (ከማኘክ) ክፉ አባዜ በመላቀቅ ምን መደረግ አለበት? እንዴትስ መደረግ አለበት? የሚሉ እጅግ ቁልፍና ፈታኝ ጥያቄዎችን በአግባቡ፣ የጊዜን ወሳኝነት ግምት ውስጥ ባስገባ ፣ ትርጉም ባለው የጥራትና የመጠን ሚዛን፣ ወደ ተፈለገው መሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ለውጥ በሚወስድ ፍኖተ እሳቤ ፣ ወዘተ ለመመለስ በሚያስችል ሁኔታና አጋጣሚ ላይ ማተኮር ይኖርብናል የሚል እምነት አለኝ። በሌላ አገላለፅ   ብዙውን ጌዜያችንንና ሌሎች ውድ ግብአቶቻችንን እጅግ ግልፅና ግልፅ በሆነውን የህሊና ቢስ ገዥዎች ጭካኔ እና በሚወረውሩልን አቅጣጫና ትኩረት አዘናጊ አጀንዳዎች ዙሪያ የማባከንን አስቀያሚ የፖለቲካ አስተሳሰብ ልማድ በእጅጉ በመቀነስ  ምን መደረግ አለበት?  እንዴትስ መደረግ አለበት? በሚሉ እጅግ ወሳኝ ጥያቂዎች ዙሪያ ማተኮር ግድ ከሚል ጊዜና ሁኔታ ላይ መገኘታችንን ከምር መውሰድ ይኖርብናል።

ይህ ማለት ግን ከአገራችን የረጅም ጊዜና በእጅጉ የተበላሸ የፖለቲካ አስተሳሰብና ባህል አንፃር ነገሮች ሁሉ ቀላል ናቸው ወይም ፋኖ እና ሌሎች የነፃነት የፍትህ አርበኛ ወገኖች አይሳሳቱምና አዎን አዎን ወይም ይሁን ይሁን በሉ ማለት በፍፁም አይደለም። ከነፃነትና ከፍትህ ትግሉ ጎን እንቁም ሲባል ትግሉ በባለጌና በጨካኝ ገዥ ቡድኖች እና በግብረ በላዎቻቸው ጥቃት ብቻ ሳይሆን ከውስጥ በሚፈጠሩ ስህተቶችና ሌሎች ምክንያቶች እንዳይደናቀፍ እና ተመልሰን የመከራና የባርነት ቀንበር ሰለባዎች እንዳንሆን በሚያስችል አቋምና ቁመና ፀንተን የህልውና፣የነፃንትና የፍትህ ተጋድሎውን ለግብ እናብቃው ለማለት ነው።

የምንነጋገረው መሬት ላይ ስለሆነውና እየሆነ ስላለው የገዛ ራሳችን ግልፅና ግልፅ እውነታ ከሆነ ይህ የፋኖ እልህ አስጨራሽ የህልውና፣ የነፃነትና የፍትህ ትግል በአንፃራዊነት (ፍፁምነት አይጠበቅምና) በአገራችን እስካሁን ከታዩት የነፃነትና የፍትህ እንቅስቃሴዎች (ትግሎች) ትምህርት የወሰደና አሁን ላለንበት የፖለቲካ ምስቅልቅልና ቀውስ ዋነኛ ምክንያት (root cause) የሆነውን የእኩያን ገዥ ቡድኖች ሥርዓት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ፍፃሜ እንዲያገኝ እና የነገዋ ዴሞክራሲያዊት የጋራ አገር እውን እንድትሆን የሚያስችል ወርቃማ እድል ነው።

የዚህ ወርቃማ እድል ስኬት ወይም ውድቀት የሚወሰነው አምላክ ከማሰቢያ አእምሮና ከብቁ አካል ጋር የፈጠረን የእርሱን እገዛና በረከት እየጠየቅን እና በሰጠን መልካም ምድር (አገር) ላይ እየሠራንና ይበልጥ እየሰለጠን በደስታና በፍቅር እንድንኖር እንጅ የራሳችን ልክ የሌለውና ተደጋጋሚ ስህተት ጠልፎ በጣለን ቁጥር “እግዚኦ ምን አደረግንህ!” እያልን የእኛን ደጋግሞ የመውደቅ አባዜና ድንቁርና በእርሱ እንድናላክክ በፍፁም አይደለም። እንደዚህ አይነት አምላክም የለም። ተቀበልነውም አልተቀበልነው  እጅግ ከሰብአዊ ፍጡርነት በታች ያወረደን ዘመን ጠገቡ የገዛ ራሳችን ልክ የለሽ ውድቀት እንጅ የፈጣሪ ፈቃድ ባለመሆኑ አይደለም። “እረዳችኋለሁ እርዱኝ” ሲል ከሌላው እንስሳት ለይቶ ከረቂቅ አእምሮና ከብቁ አካል ጋር የፈጠረበትን ዓላማ ለማሳካት ከጣርን  እርሱም እንኳንስ ስንጠራው ሳንጠራውም እንደሚረዳ ሲያስተመርን እንጅ ሌት ተቀን ስሜን በመጥራትና እግዚኦ በማለት ብቻ የተሟላ ህይወት ይኖረናል ለማለት አይመስለኝም። ለዚህም ነው ዘመን ጠገቡን ፖለቲካ ወለድ  የመከራና የውርደት ቀንበር ሰብረን የነፃነትና የፍትህ ዓለምን (ሥርዓትን) እውን ማድረግ ያልተሳካልን። በመንበረ ሥልጣን ላይ የሚፈራረቁ እኩያን ገዥ ቡድኖችም ይህንኑ የአማኝ ህዝብን (የምእመናንን) የሃይማኖታዊ እምነት እውቀት ወይም አረዳድ ድክመት ስለሚያውቁ ነው ከጨካኙ የፖለቲካ ሰይፋቸው በተጨማሪ  በየሃይማኖት ተቋሙ ካሚገኙ ደካማና አድር ባይ ወይም ለሥጋ ድሎት እኖር ባይ መሪዎችና ሰባኪዎች እየተጠቀሙ  የመከራውንና የውርደቱን ዘመን ለማራዘም የቻሉትና እየቻሉ ያሉት።

ይህንን ተረድተን እንደ ግለሰብም ሆነ እንደ ማህበረሰብ የየራሳችንን ታሪካዊ ሃላፊነትና ድርሻ መወጣት ካለብን በሥልጣነ መንበር ላይ እየተፈራረቁ ለሁሉም ዜጎቿ ምድረ ገነት ልትሆን የሚገባትና የምትችል ኢትዮጵያን ምድረ ሲኦል ያደረጓትን ባለጌና ጨካኝ የጎሳ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ገዥ ቡድኖችን ከመቸውም ጊዜና ሁኔታ በላቀ የዓላማ ፅዕናትና የሞራል ልእልና መጋፈጥን ግድ ይለናል። ይህንን አድርጎና ሆኖ ለመገኘት ራሳችንን እኩያን ገዥ ቡድኖችን በመቃወምና በመፋለም  የህይወት ዋጋ በከፈሉ፣ የአካልና የአእምሮ ስብራት በደረሰባቸው፣ በተገኙበት የማህበረሰብ ማንነት እና በሃይማኖታዊ እምነታቸው ምንነት ምክንያት  እጅግ አስከፊ የዘር ማጥፋት (ማፅዳት) ወንጀል በተፈፀመባቸው ፣ በየማሰቃያ ማእከላት ሰለባዎች በሆኑ፣ የሃሰት (ፖለቲካ ወለድ) የክስ ድርሰት እየተዘጋጀ በፍትህ ተጠያቂነት ስም በየእስር ቤቱ የቁም ስቃይ በመቀበል ላይ በሚገኙ፣ በፖለቲካ ቀውስ ምክንያት በሰላም አርሰውና አምርተው ለመኖር ባልቻሉና የአንድ ወቅት የዝናብ ጠብታ በተስተጓጎለ ቁጥር የሞትና የቁም ስቃይ ሰለባዎች በሆኑ በብዙ ሚሊዮኖች በሚቆጠሩ ንፁሃን ወገኖች ሁኔታ ውስጥ  እያስገባን ማየት ይኖርብናል።

ይህ መሪርና ጥልቅ ስሜት የሚጎለን ከሆነ ከእለት እለት ከክስተቶች ትኩሳት ጋር በሚወጣና በሚወርድ የፖለቲካ ስሜት እየተርመጠመጥን፣ ከጉንጭ ማልፋት የማያልፍ አጀንዳ እያመነዠክን፣ የመከራና የውርደት ወሬና የወሬ ትንታኔ እያዥጎደጎድን ፣ ያልኖርነውን ህይወት እንደኖርነው አድርገን ራሳችንን እያታለልን እና ይህንኑ ለትውልደ ትውልድ እያወረስን እንቀጥላለን። ይህ እንዳይሆን ከፈለግን  ከወሬው ቀንሰን  ወደ ተግባር የማተኮሩ ጊዜው  አሁንና አሁን ነው። ለዚህ ደግሞ በአማራ ፋኖ እና በዴሞክራሲያዊት አገር በእኩልነትና በፍቅር መኖር እንደሚቻል አምነው በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የትግሉ ባለ ድርሻ በሆኑ ወገኖች እየተካሄደ ያለውን ተጋድሎ ገንቢነት ባለው ሂሳዊ ሃሳብ እና በሌሎች አስፈላጊ ድጋፎች ማገዝ በፍፁም ለነገ የሚባል ጉዳይ መሆን የለበትም።

ሌላውና እጅግ አንገብጋቢው ጥያቄ ድንቅ በሆነ ሁለንተናዊ ዲሲፕሊን እየተካሄደ ያለው ወታደራዊው የትግል ክንፍ በሳልነትን የተላበሰ፣ ጥልቀትና ስፋትን ግምት ውስጥ ያስገባ፣  የአሳታፊነትንና የግልፅነትን ባህሪ የተጎናፀፈ ፣ የግል ኢጎ ሰለባነትን የሚቆጣጠር፣ የኋላ ቀርነት ፖለቲካ ባህላችን ነፀብራቅ የሆነው የጎጥ ልጅነት የሥልጣን ሽሚያ ከቁጥጥር ውጭ እንዳይሆን የሚያደርግ ፣ እና የመጨረሻ ግቡ ዴሞክራሲያዊት የሆነች የጋራ አገርን እውን የማድረግ ፍኖተ ካርታ (ፍኖተ ግብ) ያለው የፖለቲካ ክንፍ አምጦ የመውለዱ ጉዳይ ነው።

ለዚህ የተቀደሰ ተግባር ስኬታማነት አገር ውስጥም ሆነ በየትኛውም የዓለም ክፍል በሚገኙ እና ይህ ተጋድሎ የታለመለትን ግብ እንዲመታ ከምር በሚገዳቸው ምሁራን አማካኝነት በሚደረግ የማስተባበር ጥረት ተዘጋጅቶ የሚቀርብን የሃሳብ ግብአት ይጠይቃል። ይህ በተራው በየሚዲያውና በየአጋጣሚው እየቀረቡ ፋኖ ይሳካለታል ወይስ አያሳካለትም? የሚል የምፀት አይነት ትንታኔ ከመተንተን ባለፈ የእውነተኛ የምሁርነትን አስተዋፅኦ ተገቢና ገንቢ በሆነ ይዘትና አቀራረብ ለማቅረብ እድል ይከፍታልና ከምር መውሰድ ያለበት ጉዳይ ነው የሚል ፅዕኑ እምነት አለኝ።

የህልውና ተጋድሎው ከአንደኛው የትግል ምዕራፍ ወደ የሚቀጥለው በድል (በአሸናፊነት) ለመሸጋገር ይችል ዘንድ  ምን ማድረግ አለብን /ምን መደረግ አለበት (what should we do/what is to be done?) እና እንዴትስ ነው መደረግ ያለበት (how it should be done?) የሚሉ ጥያቄዎችን በአግባቡና በአጥጋቢ ደረጃ መመለስ ይኖርብናል። እነዚህን ቁልፍ/ወሳኝ ጥያቄዎች መሬት ላይ ያለውን ግዙፍ፣ ዘመን ጠገብና መሪር እውነታ በሚመጥንና ትክክለኛ መፍትሄን በሚያስገኝ ደረጃ ለመመለስ ካልቻልን እና ትክክለኛና ዘላቂ መፍትሄ አምጠን ለመውለድ ከተሳነን አገረ ኢትዮጵያን አገረ ነፃነት፣ አገረ ፍትህ፣ አገረ እኩልነት፣ አገረ ሰላም፣ አገረ ሥልጣኔ፣ አገረ እድገትና ልማት፣ አገረ ኩራት ፣ እና በአጠቃላይ አገረ ዴሞክራሲ ለማድረግ ፈፅሞ አይቻለንም።

ለዘመናት ከመጣንበትና ከአምስት ዓመታት (ስድስተኛውን ተያይዘነዋል) ወዲህ ደግሞ ታይቶና ተሰምቶ በማይታወቅ ሁኔታ አገርን ምድረ ሲኦል እያደረጉ የቀጠሉትን ተረኛ የጎሳ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ሥርዓት ዘዋሪዎች  (ኦነጋዊያን/ኦሮሙማዊያን) እና ምንደኛ ብአዴን /የአማራ ብልፅግና ተብየዎችን ትርጉም ባለው የመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለውጥ ከተቻለ አደብ አስገዝተን ከአፍራሽነት ወደ ገንቢነት ሚና ተጫዋችነት ፣ ካልሆነ ግን ከፅልመተ ሞት የፖለቲካ ጨዋታቸው ገለል እንዲሉ በማስገደድ ለሁሉም ዜጋ የምትመች  ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ፈፅሞ አንችልም። እስከ አሁንም ያልተሳካልን አለመታደል ወይም የፈጣሪ ቁጣ ሆኖብን ሳይሆን ለችግሮቻችን/ለፈታኝ ሁኔታዎቻችን መፍቻ ቁልፍ የሆኑ ጥያቄዎችን በተለይም ምን መደረግ አለበት እና እንዴትስ መደረግ አለበት (what is to be done and how it should be done?)  የሚሉ ጥያቄዎችን በአግባቡ፣ በትኩረት፣ ፅዕኑ በሆነ እምነትና አቋም ፣ ፅዕኑ መርህ ፣ግብን እውን ለማድረግ በሚያችል ሁኔታ ለመመለስ   ያለመቻላችን መሪር እውነት ነው።..

ትናንት ከባህር ዳር 40 ወይም 35 ኪ.ሜ ርቀት ላይ በምትገኘው መራዊ ከተማ ያካሄዱት ነፃ እርምጃ /ጨፍጨፋ/ርሸና ሰለባ የሆኑ ንፁሃን ደም ገና ሳይደርቅ በየመንገዱና በየመንደሩ ፈስሶ ወደ ፈጣሪ እየጮኸ ባለበት ወቅት “የሰላም መልእክተኞች” ሆነው ወደ አማራ ክልል በመዝለቅ  እጅግ ልብ የሚሰብርና የትዕሥትን ልክ የሚፈታተን ጭፍጨፋ ያካሄደውን ሠራዊታቸውን “ሊመሰገን ይገባል” በሚል ሲሳለቁበት  “ይህንን ቆሜ ከመስማት ሞት ይሻላል”  የማይል አማራ ብቻ ሳይሆን ባለ ጤናማ ህሊና የአገሬ ሰው ይኖር ይሆን?

ታዲያ አይነቱ ለስድስት ዓመታት ያለማቋረጥ የተፈፀመና እየተፈፀመ ያለ እጅግ መራር የሆነ ፖለቲካ ወለድ ወንጀል ነፃነት ወይም ሞት! ብለን እንድንነሳ ካላደረገን ሌላ ምን አይነት ምድራዊ መከራና ሰቆቃ ነው የምንጠብቀው?  የፋኖን ተጋድሎስ ይህ አይነት ፖለቲካ ወለድ  የመከራ ዶፍ አይደለም እንዴ የወለደው? ታዲያ ለዚህ አይነት ተጋድሎ በሂሳዊ ምክረ ሃሳብና በሌሎች አስፈላጊ ግብአቶች መድጋፍ (እገዛ) ማድረግ እና ማበረታት ለምን አወዛጋቢ ይሆንብናል?  መልሱን ለአማራ ብቻ ሳይሆን ጤናማ ህሊና ላለው የአገሬ ሰው ሁሉ እተወዋለሁ።

 

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Latest from Blog

መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ ¹⁵ የምድርም ነገሥታትና መኳንንት ሻለቃዎችም ባለ ጠጋዎችም ኃይለኛዎችም ባሪያዎችም ጌቶችም ሁሉ በዋሾችና በተራራዎች ዓለቶች ተሰወሩ ፥ ¹⁶ ተራራዎችንና   በላያችን ውደቁ በዙፋንም ከተቀመጠው ፊት ከበጉም ቍጣ ሰውሩን ፤ ¹⁷ ታላቁ የቁጣው ቀን  መጥቶአልና ፥ ማንስ ሊቆም ይችላል ? አሉአቸው ። ራእይ 6 ፤  15_17 ይኽ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ። የኢየሱስን ልደት ሰናከብር የየሐንስ ራእይን ማንበብ ጠቃሚ ይመስለኛል ። ምክንያቱም በመጨረሻው ዘመን

ከኢየሱስ የፍርድ ቀን በፊት በህሊናችን ውስጥ ፍቅርን ለማንገስ እንጣር 

የምጣኔ ሀብታዊ ፍጥ፣ የፖለቲካ፣ የእውነትና የሰብአዊ መብት ታጋይ፣ የአመኑበትን ነገር ለመናገር እንደ ፖለቲከኛ በቃላት ሳያሽሞነሙኑ ቀጥታ የሚናገሩት የሀገሬ ኢትዮጵያ ታላቅ ሰው ነበሩ “ዘር ቆጠራውን ተዉት፤ የአባቶቻችሁን ሀገር ኢትዮጵያን አክብሩ!”  አቶ ቡልቻ ደመቅሳ

ሀገር ወዳዱ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ከዚህ አለም በሞት ተለዩ

January 6, 2025
ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ? ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ? ዛሬ፣ 2025 ዓ/ም ላይ ብንገኝም በዝንጋታ ገመድ ወደ ሞት እየተጎተትን እንደሆነ አናውቅም። (ሁል ጊዜ የሚሞተው የገነዝነው ይመስለናል። ) “ገብርዬ ነበረ

ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ?

January 3, 2025
መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ ዛሬ እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር ጥር 1ቀን 2025 ዓ/ም ነው ። አውሮፓውያኑ አዲስ ዓመትን “ሀ” ብለው ጀምረዋል ። አዲሱን ዓመት ሲጀምሩም ከልክ ባለፈ ፈንጠዚያ ነው ። ርቺቱ ፣ ምጉቡና መጠጡ

ዛሬ፣ 2025 ዓ/ም ላይ ብንገኝም በዝንጋታ ገመድ ወደ ሞት እየተጎተትን እንደሆነ አናውቅም። (ሁል ጊዜ የሚሞተው የገነዝነው ይመስለናል። )

Go toTop