”መገደልም ሆነ መግደል አልፈልግም፤ ከሁለት አንዱን እንድመርጥ ከተገደድኩ ግን ያለጥርጥር ከምገደል፤ አገላለሁ።” (ስሙን የዘነጋሁት አይሁዳዊ ፈላስፋ)። የዘመኑ ገዥዎቻችን ”እንገላችኋላን ! እናጠፋችኋለን” ብለው ተነስተዋ፤ በተግባርም አሳይተውናል፤ እያሳዮንም ነው። ታዲያ የ’ኛ መልስ ምን መሆን አለበት?
በተለይም የአዲስ አበባን ሁኔታ ሳስብ፤ በአሥራ ስምንተኛው ክፍለ ዘመን የነበረው፤ የነባር አሜሪካን ወይም የቀይ ኢንዲያና ‘’የሞድክ’’ ነገድ ባላባት፣ ስለ ወራሪ አውሮፓዊያን የተናገረውን ያስታውሰኛል፤
”አውሮፓዊን ወደ አገራችን ሲመጡ ብዙ ቃል ገብተውልናል፤ ከገቡት ቃል ሁሉ ግን በተለይም አንዱን ፈጽመውታል። ‘መሬታችሁን እንወስደዋለን ” ብለው ነበር፤ አዎ—ቃል እንደገቡት መሬታችን ወሰዱት።” ነበር ያሉት።
ኦነጋዊ – ብልጽግናም የአዲስ አበባን ”ዲሞግራፊ” እንቀይረዋለን ወይም ከጥቅም ውጭ እናደርጋታለን ብለው ቃል በገቡት መሰረት ”ቃላቸውን” አየፈጸሙ ይገኛሉ።
ግን የኢትዮትዮጵያ፣ የአፍሪካ፣ የኦሮሚያና የሸገር ዋና ከተማ ህዝብ እንዲት ይኽን ሊፈቅድ ቻለ?
አዲስ አበቤ ከሌላው አካባቢ በተሻለ ደረጃ የመደራጀት፣ የመናበብ አቅምና መብቱን የማስከበር ችሎታ አለው። የገዥዎቻችን ሰምቶ አዳሪዎችም ሆነ አቀንቃኝ ”ካድሪዎች” የማያታልሉት፤ ከወያኔ ዘመን ጅምሮ የጎሳን ፓለቲካ አደገኛነት የተረዳና አንቅሮ የተፋ ነው። ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያዊነቱም ብዙ መሰዋአትነት የከፈለ ህዝብ ነው።ይሁን እንጂ የፍርሃት ይሁን በኑሮ ውድነት መደንዘዝ ወይም በአንድነትና በኢትዮጵያዊነት ስም በሚነግዱ የፓለቲካ ሆድ-አደሮች በመከዳቱና ከጎሳ ገዥዎቻችን ጋር በማበራቸው ፤ ”የህዳር አህያ” ለመሆን በቅቷል። ግን እስከመቼ?
የአዲስ አበባ ህዝብ የተቀጣጠለውን ትግል ከአሁኑ በመቀላቀል የራሱንም ሆነ የኢትዮጵያዊንን ህልውና ብሎም
ገዥዎቻችን በያቅጣጨው የሚያደርሱት የዘር ፍጅት ከቁጥጥር ውጭ ሳይሆን ከሌሎች ወገኖቹ ጋር በመሆን መታደግ ይችላል።
በብልጽግና ገዥዎቻችን ዘነድ የአዲስ አበባ ህዝብ ‘የአዲስ አበባ ህዝብ አይደለም ፤ መጤ ነው። ኗሪ ነው። ዜግነት የለውም። ማንኛውም የመኖር ሆነ የመስራት መብቱ የሚወሰነው በተረኞቹ የኦነጋዊ -ብልጽግና ገዥዎቻችን በጎ ፈቃድ ብቻ ነው። መጤ መብት የለውም፤ መጤ ማለት ውጣ ሲባል የሚወጣ፣ ግባ ሲባል የሚገባ፤ የገነበው ቤት በላዩ ላይ የሚፈርስበት፣ በላቡ የሰበሰበው ኃብትና ንብረት የሚወረስበትና የሚዘረፍበት ፤ልጆቹ የገዥዎችን ቋንቋ ካልተማሩ (ቋንቋ መማር በግዳጅ ወይም የሌለውን ቋንቋ ለማጥፋት እሰክ ካለሆነ ድረስ ጥቅም እንጅ ጉዳት የለውም።) በቀር ከትምህርት ቤት የሚባረሩበት፤ በአጠቃላይ ከሰው በታች ከሞቱት በላይ ”የአፓርታይድ” አገዛዝ ውስጥ ከወደቀ ዓመታትን አስቆጥሯል።
ግን እንዴት? —-የአዲስ አበባ ህዝብ ለዘመናት ተሳስሮና ተጋምዶ የኖረ፤ በኢትዮጵያ የፓለቲካ ትግል ውስጥ ከአዲስ አበባ ዮኒቨርስቲ ጀምሮ የአምበሳውን ድርሻ የሚይዝ፣ በአንደነት በመታገል ለሌሎች ከተሞችና አካባቢዎች አርያ የነበረው ህዝብ፤ እንዴት ዛሬ ኢትዮጵያዊነቱ ተገፎ፣ ማንነቱ ተዋርዶና ተንቆ፤ ልጆቹን በጅብ ሳይቀር እያስበላ ለመኖር ፈቀደ?
እንዴት ሃይማኖቱንና አገራዊ የድል ቀኑን ማክበር እንኳን ተከለከል? እንዴት ሰንደቅ ኣላማውን እንኳን በመሰለው መልክ መጠቀም የሚያስገድለው ሆነ? እንዴት ከአገራችን ህዝብ ሁሉ ለዘመናዊነት፡ ለስልጣኔና መብቱን ለማስከበር ቅርብና ችሎታው ያለው በሚልዮን የሚቆጠር ህዝብ ፤ ከሌላ አካባቢ በመጡ ገዥዎች እንደ እቃ እየቆጠሩና እያንቋሸሹ ፤ በኑሮ ውድነት አይጠበሱ ሲገዙት አሜን ብሎ ተቀበለ?
በዚች ሰዓት እንኳን በተለያዩ የአገራችን ከተሞችና መንደሮች ከአገዛዙ ጋር እየተናናነቁ ያሉ የወገኖቹን ትግል እየሰማና እያየ ዝም ብሎ መረገጥንና መጨቆንን መረጠ?
ዛሬ በየቦታው የሚፈጸመው የዘር ፍጅት ነገ ለእሱም የተደገሰ መሆኑን እያወቀ በዝምታና በፍርሃት ቆፈን እንዴት ለመያዝ ቻለ?
መልሱ ብዙ መመራመር የሚያስፈልገው አይመስለኝም ፤ ሶስት ምክንያቶች አሉ፤
1ኛው/ ስለ አልተደራጀ
2ኛው / ስለ አልተደራጀ
3ኛው/ ስለ አልተደራጀ
ታዲያ ዛሬ አዲስ አበቤ በዚህ በሰለጠነ ዘመን ድህነትን አንደ ጫማው -ተጫምቶ፣ ግፍን እንደ ዕለት ጉርሱ -ጎርሶ፣ ዘረኝነትን እንደ ዓመት ልብሱ-ተላብሶ እያስተናገደና በየቀኑ እየሞተ፤ ገዥዎቻችንም የኢትዮጵያዊነትና የአንድነት ተምሳሌት የሆነውን ህዝብ ጎሰኝንትንና መንደርተኝነትን ሲገቱትና በአሸናፊነት ሲመጻደቁበት፤ የግፍ ጽዋው ሞልቶ እየፈሰሰ ዝምታን መምረጡ፤ ከዚህ በፊት የተጠቀምኩት ቢሆንም ፤ ”ዩሊዝ ” የተባለ የቻናዊያን የጥንት ተረት ገላጭ ምሳሌ ነው።—–
”—-በታላቋ ቻይና ቹ የምትባል ግዛት አለች። በዚች ቹ በተባለች ግዛት ውስጥ ዞንግ የተባለ ሰው የብዙ መንጋ ዝንጀሮዎችን ባለቤት ነበር። ዞንግ ሃብት ያካበተውና የሚተዳደረው ዝንጆሮዎቹን ወደ ጫካ በማሰማራት፤ እነሱ ለቃቅመው በሚያቀርቡለት ፍራፍሬና አትክልት ነበር። ስለዚህም በአካባቢው ሰው ” የዝንጆሮዎቹ ጌታ” ለመባል በቃ። በየቀኑ ማለዳ ላይ ዝንጀሮዎቹን ግቢ ውስጥ ይሰበስባቸውና ትዕዛዝ ይሰጣቸዋል። ፈርጣማውንና አለሁ -አለሁ ባዩን ዝንጀሮ መርጦ በሌሎቹ ላይ ስልጣን ይሰጠዋል። ፈርጣማዋ ዝንጀሮ ሌሎቹን በመምራት ወደ ጫካ ሄደው ፍራፍሬና አትክልት ለቅመው እንዲያመጡና እያንዳንዱ ዝንጀሮ ከሰበሰበ ላይ ከአሥር አንዱን እጅ ለጌታ ዞንግ መስጠት እንዳለባቸው ህጉ ያዛል። ህጉም ይፍርጸማል። ህጉን መፈጸም የማይችል ዝንጀሮ ግን አይቀጡ ቅጣት ይቀጣል። ሁሉም ዝንጀሮዎች ኑሯችውን የሚገፋትበገባርነት፣ በስቃይና በግርፋት ነበር። ይሁን እንጅ እንዳቸውም የተቃውሞ ወይም የህግ ይሻሻልልን ድምጽ አሰምተው አያቁም። ሁሉም በፍርሃት ቆፈን የተያዙ ነበሩ።
ሁሉም ዝንጀሮዎች ኑሮ ምሯቸው የሚያደርጉት በጠፋባቸው ሰዓት አንድ ቀነ ከሁሉም ያነሰው ትንሹ ዝንጀሮ፤ ለመሆኑ ፍራፍሬዎችንና አትክልቶቹን የተከለው ጌታ ዞንግ ነውን? ” በማለት ሁሉም ዝንጀሮዎች በተሰበሰቡበት ጠየቃቸው ።
”ዞንግ አልተከላቸውም ፤ በተፈጥሮ የበቀሉና ያደጉ ናቸው።” አሉት።
”ካለ ዞንግ ፈቃድ ፍራፍሬዊችንና አትክልቶችን መውሰድ እንችልምን?” ሲል በድጋሜ ትንሹ ዝንጀሮ ጠየቃቸው።
ሁሉም ዝንጀሮዎች ተያዩና ” አዎ !—- እንችላለን።” በማለት መለሱለት።
ትንሹ ዝንጀሮ ግን ጥያቄውን በመቀጠል ”ታዲያ ለምንድነው በጌታ ዞንግ እጅ ላይ የወደቅነውና እሱን የምናገለግልው፤ ብሎም የሚያሰቃየን—-?” በማለት ንግግሩን ሊቀጥል ሲል ሁሉም ዝንጀሮዎች ሚስጢሩ ተገለጸላቸው፤ ከተኙበት የዘመናት እንቅልፍ ባነኑ።
‘በዕለቱ ማታ ዝንጀሮዎቹ ተመካከሩ ፤ ስለሚወስዱት እርምጃም እቅድ አወጡ። እናም በእቅዳቸው መሰረት ጌታ ዞንግ እንቅልፍ ሲወስደው የታጎሩበትን በረት ሰባበሩ። ግቢውንም በሙሉ አፈራረሱ። የጌታ ዞንግ ንብረት የነበረውንና ለዘመናት ያከማቸውን፤ በእነሱ የሰበሰቡትን ፍራፍሬና አትክልት በሙሉ ጠራርገው በመውሰድ የሚችሉትን ያህል በመያዝ ወደ ገደላቸው ሄደው ገቡ። ከዚያም በኋላ አልተመለሱም፤ እነሱም በሰላምና በደስታ መኖር ጀምሩ። ጌታ ዞንግም በድህነት ኖሮ-በድህነት ሞተ።’–‘
የዘመኑ ገዥዎች የአዲስ እበባን ሃብት፣ የአዲስ አበባ መሬት ፤ በአጠቃላይ ሳርቅጠሉ ሳይቀር ”ፊንፊኔ ኬኛ ” አሉት ። ዞንግ ለዝንጀሮዎእቹ የፈቀደላቸውን ”ከአስር እንድ እጅ” እንኳን አልተፈቀደላቸውም። ህዝብም እንደ ዞንግ ዝንጀሮዎች ”የአፓርታይደን” ኑሮ ተቀብሎና ሃብትና ንብርቱን እያሰረከበ ፤ በፍርሃትና በሞት ጥላ ውስጥ ግዜውን ይገፋል።
የራሱ ሃብትና ንብረት እየዘረፋ በህዝብ መሃከል ቅራኔና ጥላቻ ለመስፋፋት ”ከዘመናት በፊት ለተበደለው ወገንናቸው” አከፋፈሉት ፤ ተከፋፈሉት። በአሁን ሰዓት በመቶ ሺዎች የሚቆጥሩ ዜጎች ቤት አልባ መሆናቸው ስላለበቃ፤ የሚያሰጠጋቸውም እንድይኖር ተረኞቹ ህግ-አውጥተዋል። ህዝብ የመንቀል ተግባሩም ወደፊትም እንደሚቀጥል ሳይታለም የተፈታ ነው። ”። የአዲስ አበባ ህዝብ ከ’ርስቱ እንዲነቀልና የመከራ ኑሮ እንዲገፋ ወንጀል ሆኖ የተቆጠረበት ደግሞ ኢትዮጵያዊነቱ ነው። ገጣሚው እንዳለው፤
”በሕልም ተበድለው ፣ በውን ተበቀሉ
ግራር ይተክላሉ ሰው እየነቀሉ።—”
በኦሮሞኛ እንድ አባባል አለ፤ ” ዳገቱን መውጣት ካቃተህ በቁልቁለቱ ተንደርደር።” ይላል። የጠ/ ሚ አብይ አህመድ አገዛዝ የሁላችንም መዳኛ የሆነውንና ይሰብክው የነበረው ኢትዮጵያዊነት ዳገት ሆኖበት፤ ቁልቁለቱን እየተደረደር ነው። ከዳገት ወድቆ በቁልቁለት የሚንደረደር ድግሞ ያገኘውን ሁሉ ማፈረርሱና ማውደሙ ግልጽ ነው። ለዚህ ደግሞ በትግራይ የተካሄደው እልቂት አልበቃ ብሎ፤ ዛሬ በተለይም በጎንደር፣ በጎጃም፣ በወሎና በሸዋ የዘር ፍጅቱን አጠናክሮ ቀጥሎበታል።
እንግዲህ የአዲስ አበባ ብሎም የኢትዮጵያ ህዝብ–ከዚህ የበለጠ ስቃይና መከራ አለወይ? ብሎ መጠየቁ ተገቢ ነው። እንደ ቹ ግዛት ዝንጀሮዎች’፤”ለመሆኑ አዲስ አበባ የማናት? ብለን ራሳችን እንጠይቅ። አሁን የተያዘው ፍርሃትም እንበለው ዝምታ ደግሞ ውርደትንና ውድቀትን እንጅ ነጻነትንና መከበረን አያወጣም። ኢትዮጵያን አይታደግም።
”ፈሪዎች ሳይሞቱ፣ ሲሞቱ ሲኖሩ መልሰው መላልሰው
ጀግና ግን፣ የሞቱን የሞተለታ ነው ጣዕሙን የሚቀምሰው። (ሼክስፒር/ ትርጉም ተገኘ በቀለ) የተባለ ያለ ምክንያት አይደልም።
በቅሶና በዋይታ ወይም የፊስ ቡክና የዩቲዮብ ጫጫታ ቤታችን ካላያችን ላይ ከመፍረስ፤ ልጆቻንና አዛውቶች መጥጊያ ከማጣት፣ እምቦቀቅላ በጅብ ከመበላም ሆነ የዘር-ፍጅት ከመፈጸም አላዳነም። ዛሬ የኢትዮጵያዊነት ትግሉ አንድ ምዕርፍ ወደፊት ሄዶ ጀግኖች በየቀኑ መሰዋትነት እየከፈሉና ንጹሃን ወግኖቻችን በ”ድሮውን” እሳት እየነደዱ ነው።
ትላንትም ሆነ ዛሬ፡ ነገም ያለው እውነታ ፤ በየቦታው እንደ አቅማችንና እንደ ችሎታችን ተደራጅተን፣ መሪና ተመሪ በመሆን፤ ታግለን በመታገልና የሚያስፈልገውን መሰዋአትነት ከከፈል ብቻ ነው፤ አዲስ አበባን እስከ ማንነትቷ ልንታደግታና መብታችን ልናስከብር የምንችለው።
ከዘመኑ የጎሰኝነትና የመንደርተኝነት የነቀርሳ በሽታ ራሳችን አጽድተን፤ ተደራጅተንና አደራጅተን ከታገልን፤
የሁላችን አዲስ አበባ፣ ሁሉም ዜጎቿ ልዕልነዋ በተከበረ ኢትዮጵያ፣ በፍትህ፣ በእኩልነትና በባለቤትነት የምንኖርበት የ’ጋራችን ሀገር፣ በጋራ ኃላፊነት እንገነባለን። ምክንያቱም እውነትና ኢትዮጵያዊነት ከኛ ጋር ነውና። ምክንያቱም የኋላ-ኋላ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት አሸናፊ ነውና።
ስለዚህም ትግሉን በማፋፋም፤ የብልጽግናን አገዛዝ በማስወገድ ለሑላችንም የሚበጅ ሥርዓት ለመገንባት የድርሻችን እንወጣ። ይህ አገዛዝ በቆየ ቁጥር የአገርና የህዝብ ህልውና የበለጠ አደጋ ላይ ይጥላልና፤ የጎንዮሽ መናቆር አቁመን በጋራ እንታገል። ለዚህ ደግሞ የአዲስ አበባ ህዝብ ወሳኝነትና ጉልህ ሚና አለው።
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኖራለች!!
——–//——-ፊልጶስ