ክርስቶሳዊ ያልሆነ ክርስቶሳዊነት! 

October 14, 2023

T.G

 

d7baf760 cc5e 11ed be2e 754a65c11505
ኮሜዲያን እሸቱ መለሰ

ሁልጊዜም እንድማደርገው መደበኛ (traditional) እና ማህበራዊ (social) ሚዲያዎችን ስጎበኝ ኮሜዲያን እሸቱ ወደ ቃታር (ኳታር) ተጉዞ በዚያው ከሚኖሩ ወገኖች ጋር ቤተ ክርስቲያን ስለ ማሠራት መነጋገሩንና ለዚህም የገንዘብ ማሰባሰብ ዘመቻ ለማካሄድ  ፕሮግራም መያዙን ሲያስተዋውቅ ተመለከትኩ ወይም አደመጥኩ።

መቸም በመሠረተ ሃሳቡ አልስማማም የሚል ወይም ጉዳዩን ለማጣጣል የሚሞክር እንኳንስ የኦርቶዶክስ ተከታይ ሌላ ቅን ህሊና ያለው ሰውም የሚኖር አይመስለኝም።

ከባዱ ጥያቄ ግን ለብዙ ዓመታት እንደ የአለንበት የዓለም ክፍልና አገር ፈጣሪን እንደ እየምነታችን እያመሰገን ያልኖርን ይመስል አሁን አገር ቤት ከወረደውና እየወረደ ካለው ለመግለፅ የሚያስቸግር የመከራና የቀውስ ዶፍ አንፃር ሲታይ የቅድሚያ ቅድሚያ ትኩረት ልንሰጠው የሚገባን ጉዳይ ነው ወይ? የሚለው ነው። ወይንስ የቅድሚያ ቅድሚያ ትኩረት የሚባል ነገር በሃይማኖታችን ቦታ የለውም???

ህፃናትን እጅግ ልክ ለሌለው የሶሻል ሚዲያ ንግድ ሲባል ከሚችሉት ወይም ከአቅማቸው በላይ በሆነ ሁኔታ እያነገሩ “ተአምሩን ተመልከቱ”በሚል እልልታና ጭብጨባ ማቅለጥ ልጆችን ያለ አቅማቸው ግራ ከማጋባት አልፎ ፈጣሪንም የቅድሚያ ቅድሚያ ትኩረትን የሳተ አስተሳሰብና አካሄድ ተባባሪ ማድረግ ነው የሚሆነው።

አገር ለማሰብ በሚያስቸግር መከራና ሰቆቃ ውስጥ እየማቀቀች ባለበችበት እና የዚሁ መከራ የመጀመሪያ ተጠቂዎች የሆኑ እጅግ አያሌ ሚሊዮን ህፃናት በሚገኙበት ሰፊና መሪር  እውነታ ውስጥ  በአገር ቤት በሃይማኖት ስም መነገዱ ጋብ ሲል ባህር ማዶ ቤተ ክርስቲያን ተከፈተ ወይም ገዳም ሊሠራ ነው ሲባል እየዞሩ ህፃናትን ሳይቀር የሶሻል ሚዲያ ንግድ (social media business) ማሳለጫ ማድረግን እንኳንስ እውነተኛው አምላክ በእርሱ አምሳል የተፈጠረና ጤናማ ህሊና ያለው ሰውም ፈፅሞ አሜን ብሎ የሚቀበለው አይደለም!!!

 እናም አያሌ ሚሊዮን ህፃናትና ታዳጊዎች እጅግ አስከፊ በሆነ አገራዊ መከራና ሰቆቃ ውስጥ በሚገኙበት መሪር እውነታ ወቅት ባህር ማዶ ቤተ ክርስቲያንና ገዳም ለማሠራት ወይም ያለውን ይበልጥ ለማስዋብ “ዶላሮቻችሁን ብትሰጡ የፅድቅ መንገድ ነው” በሚል ዘመቻ ላይ መጠመድ እውነተኛውን ፈጣሪ ጨምሮ የሸፍጥ  ወይም የአታላይነት ንግድ ተባባሪ ማድረግ ነው የሚሆነው።

እደግመዋለሁ! ይህንን አይነት አስቀያሚ ወለፈንዲነት (hypocrisy) ምነው ምን ነካችሁ? ብሎ የሚገስፅ  አዋቂ ወይም ሽማግሌ ማግኘት ብርቅየ የመሆኑ ጉዳይ ደግሞ ቅንና ሚዛናዊ ህሊና ላለው ነፃነትና ፍትህ ፈላጊ የአገሬ ሰው በእጅጉ የስጨንቃል ፤ያስፈራልም። እውነተኛውን አምላክም ያስቀይመዋል እንጅ ከቶ ደስ አያሰኘውም።

እናም የቅድሚያ ትኩረት አጀንዳና ርብርብ አስፈላጊነትን በአፍ ጢሙ የሚደፋን የሃይማኖታዊ ነጋዴነት እምነት (merchant of religious belief) ነውር ነው በማለት የቁማር ጨዋታው  አጫፋሪዎች ከመሆን  መቆጠብ ይኖርብናል ።

ረቂቅ የሆነው የፈጣሪነቱ ሚስጥር እንደተጠበቀ ሆኖ ክርስቶስ ያስተማረንና በመጨረሻም በመስቀሉ ላይ የመጨረሻውን መሪር ፅዋ በደስታ ተቀብሎ ያሳየን የቅድሚያ ቅድሚያ ትኩረት ባደረገበት የሰው ልጆች ነፃነት፣ ፍትህ፣ ርትዕ፣ ሰላም፣ ፍቅርና የተሳካ ህይወት ነው።  አዎ! ክርስቶስ የሰው ልጅን የታደገው በጎ መንፈስ በጎደላቸው ገዥዎች ሥር የመከራና የውርደት ህይወት እንዲገፉ ከተገደዱት ጎስቋሎች ጋር እየኖረና እያስተማረ እንጅ ዛሬ እኛ እንደምናደርገው የመከረኞችን መከራ እየሸሸ ወይም ችላ እያለ “ቤተ ፀሎት ወይም ቤተ እምነት ወይም ቤተ ገዳም ለማሠራት ያላችሁን ካልሰጣችሁ የአባቴን ቤት እቆልፍባችኋለሁ” በሚል የግብዝነት ዘመቻ አልነበረም።

በገዛ አገራቸውና ቀያቸው ተወልደው ሌላው ቢቀር በድህነት ለማደግና ለመኖር ያልተፈቀደላቸው አያሌ ሚሊዮን ህፃናትና ታዳጊ ወጣቶች በሚገኙበት፣ ወላጆች የመከራቸውን እንባ የሚያነቡበትና አምላካቸውን የሚማፀኑበት ቤተ እምነት አጥተው ግራ በተጋቡበት፣ የቤተ እምነት አገልጋዮች ከነቤተሰባቸው (ከነትዳር ጓዶቻቸው) በሚታረዱበት፣ ቤተ እምነቶች እንደጠላት የጦር ሰፈር ተቆጥረው የአስከፊ ጥቃት ሰለባዎች በሆኑበት ፣ ይህ ሁሉ መከራ አልበቃ ብሎ አየሌ ሚሊዮኖች በአስከፊው የርሃብ ጠኔ ክፉኛ በተመቱበት ፣ በእኩያንና ጨካኝ ገዥ ቡድኖች  ምክንያት የጤና ተቋማት እየወደሙ በመሆናቸው መትረፍ የሚችሉ የንፁሃን ነፍሶች  እንደ ቅጠል እየረገፉ ባሉበት ፣ ወዘተ መሪር እውነታ ውስጥ “ባህር መዶ ለሚሠራ ቤተ እምነት እና ሊሠራ ለታሰበ ገዳም የቅድሚያ ቅድሚያ ትኩረት ሰጥታችሁ ዶላር ብትለግሱ የገነት በር ቁልፍ ይሰጣችኋል” ማለት እንዴት አይነት ክርስቶሳዊነት እንደሆነ ለመረዳት ይከብዳል።

በየዋህ አማኝነትም ይሁን ወይም እናውቃለን በሚል አጉል ግብዝነት ይመስለኛል አንዳንድ ወገኖች “ለእግዚአብሔር ከሆነ ሌላው ነገር (ጉዳይ) ሁሉ ቀርቶ  ቤተ እምነት ወይም ገዳም ለምን በወርቅ አይሠራም” ሲሉ እንሰማለን። አዎ! ይህንን የሚያሰኝ የአኗኗር (የሁለንተናዊ ነፃነትና ድሎት) ኖሮን ቢያንስ የፈጣሪን ፍቅር ለመግለፅ ብንናገረው ሸጋ በሆነ ነበር።

ለዘመናት የመጣንበትንና አሁንም ለማሰብ እጅግ በሚከብድ ሁኔታ የቀጠለውን ፖለቲካ ወለድ መከራና ውርደት አሸንፈን ለመውጣት ባለመቻላችን የአገራችን ህዝብ በአጠቃላይ እና በተለይም ህፃናት፣ አርጋዊያን፣ እናቶች፧ አቅመ ደካሞች፣ ንፁሃን ሠርቶ (ለፍቶ) አዳሪዎች ፣ ነፃነትና ፍትህ ፈላጊዎች ፣ ወዘተ ከሰብአዊ ፍጡራን በታች እንዲሆኑ በተገደዱበትና እየተገደዱ ባሉበት መሪር እውነት ውስጥ “ቤተ ክርስቲያን ወይም ገዳም በወርቅ ቢሠራስ?” የሚለውን ቃለ ነቢባችንን በደስታ የሚቀበል አምላክ ፈፅሞ የለም!  አለ እንጅ ካልን እውነተኛውን አምላክ ጨምሮ የወንጀል ተባባሪ ማድረግ ነው የሚሆንብን።

እናም ክርስቶሳዊ ባልሆነ ክርስቶሳዊነት ውስጥ ከተጠመድንበት ክፉ አባዜ ሰብረን በመውጣት  ዘመን ጠገቡንና እያደር እጅግ እየከፋ በመሄድ ላይ ያለውን ፖለቲካ ወለድ መከራና ውርደት ከፈጣሪ እርዳታ ጋር ፍፃሜ እንዲኖረው በማደረግ የእውነተኛ ነፃነት፣ ፍትህ፣ ርትዕ፣ ሰላም ፣ እድገት/ልማት ፣ ወዘተ ሥርዓትን እውን ለማድረግ ሁሉን አቀፍ የሆነ፣ በፅዕኑ መርህና ዓላማ ላይ የተመሠረተ፣ የተጠና እና የታቀደ ፣ የተደራጀና የተቀነባበረ ፣ በአንፃራዊነት ከራስ ወዳድነት ደዌ የፀዳ፣ በፅዕኑ የአርበኝነት ስሜትና ውሎ የታጀበ ፣ ወዘተ ትግል ላይ ራሳችንን እናግኘው!!!

 

 

5 Comments

  1. በመልካም ጀምረህ አለሳልሰህ ክፉ መልእክትህን አስነበብከን ። እሸቱ ግለሰብ ነው ሊተገበር የሚገባውን ጥያቄ አድሬስ ማድረግ የነበረብህ ለጠሚኒስቴሩና ለምክትሎቹ ሽመልስ አብዲሳና አዳነች አቤቤ መሆን በተገባው ነበር። እሸቱ መልካም ሰው ነው ሰው እረዱም አይልም መቅሱድ ነስሮ የሚባለው ልጅ እሱ ፕሮግራም ለይ ቀርቦ ያደረገለትን መልካም ተግባርና ለልጁ ከእኛ በላይ የሚቀርበው የለም ያሉት ኡስታዞች ያደረጉለትን አመዛዝነው። እነሱ ልጁን ተጠቅመው ስሙኒ ሲሰበስቡበት እሸቱ ግን የቤተ ሰቡን ህይወት ነው የለወጠው። የቻሪቲና የስቴትን ተግባር መለየት ያስፈልጋል። የምትወረውሩት ክፉ ሀሳብ መልካም ሰዎች እንዲሳቀቁብን ያደርጋል። መልካም ባያደርግ ምን ትጽፍ ነበር።

  2. በሃይማኖት ተቋማት ስም የሚደረግ ግለሰቦቾ የሚበለፅጉበት አትራፊ ኢንበስትመንት ከሆነ ቆይቷል ። አሁን ደግሞ ከአገር ውጭ የወቅቱ ያልተባነነበት ቢዝነስ መሆኑ ነው የሰው ልጅ በዚህ ልክ የሞራል ዝቅጠት ያሳስባል በርግጥ አርቲስቱ ከዃላው የሚዘውረውን ሃይል ለመቋቋም ስክነትና እውቀት ይኖረዋል ብየ አልገምትም

  3. ይድረስ ለአቶ ሰንደቅ በውጭ ሀገር ኑረህ አንተ ላንተና ለወገኖችህ ማድረግ ያቃተህን እሱ ከሀገር ቤት ማድረጉ የሚያስወቅሰው አይሆንም። ያልተባነነበት ዘረፋ ላልከው በመረጃና በአሀዝ ብታስቀምጥልን መልካም ነበር። በጀርባ መዘወር እዚህ ላይ ምን እንዳመጣው ግልጽ አይደለም ውስብስብ የረቀቀ ጉዳይም አልመሰለኝም። ጣትን ወደ ኪቦርድ ከመጫን በፊት ሊያመጣ የሚችለውን ማሰብ ጠቃሚ ይሆናል።

  4. ሃሳቤን ከተረዳሽ/ከተረዳህ እኔ አርትስቱን በዋነኝነት አልወቀስኩም ። በቤተ -ዕምነት ውስጥ የግል ጥቅማቸውን የሚያባርሩ የሉም ብለህ የምታስብ ከሆነ የሚያስከትለውን የዕምነት ተቋማት ተቀባይነት ማጣት እንደመተባበር ይቆጠሪል።

  5. ሰንደቅ እኔ እስራኤል ዳንሳን፤አቶ ዮናታን አክሊሉን፤አቶ ግርማ ዘውዴን፤እነ እዩ ጩፋ የመሳሰሉትን እያየሁ ያልከውን አልክድም በመልስህ። ግን ጸሃፊው የወረፈው እሸቱን ነው እሸቱ ኮሜዲያን እንጅ የሃይማኖት ሰው አይደለም በውጭ ሃገር ገዳማት ለማሰራት ማሰባሰቡ ክፋት የለውም። ይህንኑ ስራውን ቆጥረው ጋብዘውታል መቼም የኛ የመመልስ ነገር አጠራጣሪ በመሆኑ እኛ ለእኛ ሳናስብ እሸቱ ቢያስብልን ክፋት የለውም። እንደምታውቀው እሸቱ በመልካም ስራዎች ይሳተፋል በዚህ ጉዳይ ነገር ባላካርርም በአንድ ወቅት “ሃይ ሊባሉ የሚገባቸው ወገኖች” በሚል ር እስ ስለ ዮናታን አክሊሉ ተጽፎ አንብቢያለሁ እዚሁ ገጽ ላይ። ያሰፈርከው ጽሁፍ ለዛ አርቲክል ቢሆን መልካም ነበር ለማንኛውም ሰላም ይስጠን።

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Previous Story

ተሳጥናኤል ጋራ ሽምግልና ሲሉ!

91530 1 1
Next Story

ጥናት አልባ የላቲን ፊደል የማፋፋት ዘመቻ – ፓስተር ዲጎኔ ሞረቴው 

Go toTop