የህዝብን ሥሥ ስሜት ተጠቅመው በአቋራጭ ለመቶጀር (ቱጃር ለመሆን) የሚቅበዘበዙ የዚህ ትውልድ አባላት አደብ ግዙ ሊባሉ ይገባል!

August 13, 2023

T.G

የሩሲያው ደራሲ ዶስቶቭስኪ ይነሰም ወይም ይብዛ ስኬታማነት ከወንጀል (ከሃጢአት) ንክኪ ፍፁም እንዳልሆነ  “በየአንዳንዱ ስኬታማነት ጀርባ ወንጀል ይኖራል ወይም አለ (There is crime behind every success) ሲል  Crime and Punishment በተሰኘው ልብ ወለድ መፅሃፉ ይገልፀዋል።

የአገራችንን “የባለፀጋነት” ባህሪና አካሄድ ከምር ልብ ለሚልና መሪሩን እውነት ለመጋፈጥ ዝግጁ ለሆነ ሰው ይህ የዶስቶቭስኪ አገላለፅ ግልፅ የማይሆንለት አይመስለኝም።

አገር እንደ አገር ወይም ህዝብ እንደ ህዝብ ዘመኑን በሚመጥን የእድገት አኗኗር ለመኖር ተስኖት እና መሠረታዊ ፍላጎቶቹን የማሟላት ጉዳይ የሰማይን ያህል ርቆበት ከደመ ነፍስ እንሳሳት በታች በሆነ ሁኔታ ላይ ከሚገኝባቸው ዋነኛ ምክንያቶች አንዱ ቀጥታ ባይዘርፉም ወደ መንበረ ሥልጣን ከመጣው ጨካኝና ዘራፊ ገዥ  ቡድን ጋር የሚሞዳመዱ እና ሃይማኖታዊ እምነትን  ጨምሮ የህዝብን እጅግ ሥሥ የሆኑ ስሜቶች የሚኮረኩሩ ጉዳዮችን “የተውኔተ ብልፅግና” መጫወቻ ሜዳቸው የሚያደርጉ  የዚህ ትውልድ አባላት ባህሪና ተግባር ነው።

አዎ! በርካሽ ህዝበኝነት (cheap popularity) በአቋራጭ ባለፀጋ የመሆን ክፉ ባህሪ የተጠናወታቸውን ወገኖች በአንፃራዊነት ንፁሃን (እውነተኛ) ከሆኑት ለመለየትይችል ዘንድ  ለምንና እንዴት? ብሎ ለመጠየቅ የተሳነው ትውልድ በቀጥታም ይሁን ስልታዊ በሆነ መንገድ “በልፅገን አበልፅገንሃል ወይም ወይም እያበለፀግንህ ነው” በሚል የሚመፃደቁበት (የሚሳለቁበት) ወስላታ ወገኖች እና ተባባሪ ዘራፊ ገዥ ቡድኖች ሰለባ ቢሆን ከቶ አይገርምም።

ለዘመናት የመጣንበትና አሁንም ለማሰብ በሚከብድ አኳኋን የቀጠለው የአገራችን እጅግ አስከፊና አስፈሪ እውነታ ይኸው ነውና ከዚህ የመውጫ መንገዱን በጋራና ወደ ኋላ በማይመለስ የጋራ ትግል ከመክፈትና ከማስከፈት በስተቀር ከቶ ሌላ አማራጭ የለም!

በሌላ አባባል በጎሳ አጥንት ስሌት የፖለቲካ አስተሳሰብና አካሄድ ላይ ተቸክለው አብሮና ተከባብሮ ለመኖር ያልቸገረውን መከረኛ ህዝብ የማያቋርጥ የመከራና የውርደት ናዳ (ዶፍ) ያወረዱበትንና እያወረዱበት የሚገኙትን ባለጌ፣ ፈሪና ጨካኝ ገዥ ቡድኖች በወንጀል ከበከተው ዙፋናቸው ላይ እንዲወርዱ እና ከቻሉ ንስሃ ገብተው የመፍትሄ አካል እንዲሆኑ ፣ ካልሆነ ግን እንዲወገዱ በማድረግ እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን እውን ማድረግ ብቻ ነው!

ተጨማሪ ያንብቡ:  በወለጋ ትናንት ምሽት የአካባቢው ተወላጅ ያልሆኑ ዜጎች ቤት ሲቃጠል አመሸ፤ ህጻናትም ተቃጥለዋል ተባለ

አዎ! እውነተኛ ነፃነትና ፍትህ የሰፈነባትና የጋራ ብልፅግና የተርጋገጠባት አገር እውን ማድረግ ካለብን ብቸኛው መፍትሄ (መውጫ መንገድ) ይኸው ነው!

እናም በየትኛውም ማህበረሰብ የሚነነሳ የነፃነት፣ የፍትህና የእኩልነት ትግልም መታየትና መደገፍ ያለበት ከዚሁ እጅግ መሠረታዊ ጉዳይ አኳያ ነው።

ለዚህም ነው በተረኛ ኢህአዴጋዊያን (ኦሮሙማዊያን) አሽከርነታቸው (አገልጋይነታቸው)  በመቀጠል ተገኘንበት በሚሉት ማህበረሰብ ላይ ለማመን ቀርቶ ለማሰብም የሚከብድ የመከራና የውርደት ናዳ (ዶፍ)  እንዲወርድበት ያደረጉትንና በማድረግ ላይ የሚገኙትን ብአዴን ተብየዎች  በመጠራረግ ለዜጎቿ ሁሉ የምትመች ዴሞክራሲያዊት አገር እውን ማድረግን መዳረሻው ያደረገው የአማራው ማህበረሰብና የእውነተኛ አጋሮቹ እልህ አስጨራሽ ተጋድሎን መደገፍ  ትክክል የሚሆነው።

ያለዚያ ግን እጅግ በገነገውና አስከፊ በሆነው የመከራና የውርደት አዙሪት ውስጥ እየጓጎጡ መኖር ነው  የሚሆነው (መኖር ከተባለ) ።

ስለሆነም ልብ ያለው ልብ ይበል!!!

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share