የደስታችን ምንጭ ሜዳሊያው ብቻ ሳይሆን አትሌቶቻችን ኢትዮጵያን አሸናፊ ለማድረግ ያሳዩት ትብብርና ህብረት ነው- ሻለቃ አትሌት ኃይሌ

የደስታችን ምንጭ ሜዳሊያው ብቻ ሳይሆን አትሌቶቻችን ኢትዮጵያን አሸናፊ ለማድረግ ያሳዩት ትብብርና ህብረት ነው ሲል ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ ተናገረ።
ኢትዮጵያ በአሜሪካ ኦሪገን በተካሄደው 18ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በሜዳሊያ ብዛት ከዓለም ሁለተኛ ደረጃን ይዛ በድል እንድታጠናቅቅ ያደረገው የአትሌቲክስ ቡድን ወደ ሀገሩ ገብቷል።
የአትሌቲክስ ቡድኑ ዛሬም በአዲስ አበባ ዋና ዋና ጎዳናዎች ላይ እየተዘዋወረ ደማቅ አቀባበል እንዲሁም በብየራዊ ቤተ መንግሥት አቀባበል እየተደረገለት ይገኛል።
ኢትዮጵያ በአትሌቲክስ ታሪክ በዓለም አደባባይ ስሟ በጉልህ እንዲነሳ ሰንደቅ ዓላማዋ ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ ካደረጉ አንጋፋ አትሌቶች አንዱ ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ ነው።
ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ለአትሌቶቹ እየተደረገ ባለው አቀባበል ተገኝቶ ለጋዜጠኞች በሰጠው አስተያየት የአትሌቶቹ ድል ትልቅ ትርጉም እንዳለውና በተገኘው ውጤት ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማው ተናግሯል።
በተለይ ኢትዮጵያ ስሟ በጦርነትና በተለያዩ ችግሮች እየተነሳ ባለበት በዚህ ወቅት የአትሌቲክስ ቡድኑ የተቀዳጀው ድል፤ ኢትዮጵያ በአንድነትና በፅናት ፈተናዎቿን እንደምታሸንፍ ያሳየ ነው ብሏል።
በጥቅሉ ለተገኘው ድል የድሉ ባለቤቶችንም ፈጣሪንም ማመስገን እንደሚገባም አትሌት ኃይሌ ተናግሯል።
አትሌት ኃይሌ መላው ኢትዮጵያዊ በድሉ የተደሰተው ባገኘነው ወርቅ፣ ብርና ነሐስ ብቻ ሳይሆን የአትሌቲክስ ቡድኑ አባላት በዓለም አደባባይ ባሳዩት ኢትዮጵያዊ አንድነትና ሕብረት ነው ይላል።
አትሌቶቹ ያሳዩትን አንድነት፣ ሕብረትና ትብብር በሌሎች ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በመድገም ሁሉም ኢትዮጵያዊ ለእናት ሀገሩ ሰላምና ልማት በአንድነት ሊነሳ እንደሚገባም አስገንዝቧል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
”ይህን ትብብር ወደ ፖለቲካው፣ ወደ ኢኮኖሚውና ለሌሎች በጎ ነገሮች በማዋል ኢትዮጵያ ፍቅርና አንድነት የሰፈነባት ሀገር ማድረግ ይገባል” ብሏል።
ኢትዮጵያ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናው አራት የወርቅ፣ አራት የብርና ሁለት የነሐስ በድምሩ 10 ሜዳሊያዎችን በማግኘት ታሪካዊ ድል አስመዝግባለች።
ዘገባ የዋልታ
ተጨማሪ ያንብቡ:  ከማን.ዩናይትድ ጋር የተያያዙ 10 አነጋጋሪ የወሲብ ቅሌቶች

1 Comment

  1. ልክ ነህ ሃይላችን፣ የምንግዜም ጀግናችን! ግን ሃይላት ከዚያም በላይ አለ። ፕሬዚደንት ሳህለ ወርቅ እንዳሉት ‘የኦሪጎን ድል ከሜዳሊያ እና ሪኮርድ መስበር በላይ ነው”። እውነታውን መጋፈጥ ያስፈልጋል። ኦሪገንን ልዩ የሚያደርገው ከተገኝው አራት ወርቅ ሦስቱ በትግራይ ልጆቻችን/እህቶቻችን መሆኑ ነው። በትግራይ ክልል ካለው ነባራዊ ሁኔታ በመነሳት የብዙዎችን ስሜት አዘበራርቋል። ጥያቄዎችን አጭሯል። ደብረ ጺዮን እና ጌታቸው ረዳም ዝብርቅርቅ ስሜት ሳይሰማቸው ይቀራል ብሎ መገመት ያስቸግራል። በሌላ በኩል ይህ ድል “የአቢይ ድል” መስሎት አፍ አውጥቶ ባይናገርም ቅር የተሰኘም አለ። አትሌቶቻችንን እናመስግናለን፣ አምላካችን ሰላማችንን እና ፍቅራችንን ያብዛልን!

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share