ህይወት እንደ ጅረት ትፈሳለች
“ሰው ራሱ ጅረት ነው”፣እያለች ፡፡
አንዱ ሲሄድ፣አንደኛው ይመጣል ፡፡
መሄድ፣መጓዝ መች ያቆማል??
በማለት፣…
ዘላለማዊ ፍሰቷን
እየመሰከረች ።
መጣመር ፣መዋለድ
ማደግና ማርጀት
ጥንትም ነበረ፣
ዛሬም አልተቀየረም…
አስተውሉ እያለች ፡፡
ሳታቋርጥ ፣ ሳትታክት ፣
ከመጣው ጋር ፣ ትጓዛለች
አንዱን ወደ መቃብር ከታ …
ወዲያው ሌላውን ትተካለች ።
ግና…ወላፈንድ የሆነ ፤
በህይወት፣ጅረት
በወንዞ ፍሰት…
የምንመለከተው…
የምናስተውለው…
ጥቂት ነገር አለ ፡፡
የሚሳዝናችሁ
በየ ዕድራችሁ ፡፡
ደሞ ብዙ አለ
በየሰፈራችሁ
የሚያስደንቃችሁ ፡፤
ተራ ሞች ያልሆነ
በምናብ የገነነ ።
አርቆ አሳቢ …
በዕውቀት ተጠባቢ…
ነገን አመላካች …
ለእውነት ተሞጋች ።
ለእውነት ታሣሪ …
ለእውነት ተወጋሪ …
ለእውነት ተሠቃይ …
ለእውነት ተገዳይ ።
ሃሳቡ የማይሞት
የሚኖር በህይወት
እሥከዘለአለሙ
የሚናኝ በዓለሙ ።
…………………………
ደሞ፣ አለላችሁ…
የዚህ ተቃራኒ
በየእድራችሁ
ድንገት ሣታሥቡት…
በ12 ቁጥር ምሥማር
የሚቸነክራችሁ ..
እዝጊዖ ! …
የሚያሰኛችሁ ፡፡
በጌተ ሰማኒ …
“ኢሎሄ እንዳለው …
( ጌታችን ኢየሱስ )
ላማ ሣብቀተኒ ! ”
እናንተም …
12 ቁጥር ምስማር
በእጃችሁ ተቸንክሮ
በእግራችሁ ተቸንክሮ
( በጅራፉ ብዛት )
በደም አባላ ታጥባችሁ …
በአረመኔ እጅ ላይ ወድቃችሁ …
ፈፅሞ ሳታስቡት
ደባውን ሳትረዱት
ጠላት ወዳጅ መስሎ
ድንገት አጥምዷችሁ …
በሽንገላው ብዛት
ቀልባችሁን ገዝቶ
በአፍዝ አደንግዙ
ህሊናችሁን አግቶ
ገደል ጨምሯችሁ
በአንደበቱ አሥብቶ …
የደንቆሮ መዓት…
በየፊሥ ቡኩ
በየ ዩቲዪቡ
ሥምአኒ የሚያሰኝ
ዓምላክን የሚያሥጠራ
የሤጣንን … ጅራፍ ይዞ
በቀጣፊ አንደበቱ …
መንጋውን አደንዝዞ …
ያ – ለነጭ ሠጋጅ
አሣሪ ተብታቢ ፣
መንጋውን አሣዳጅ ?!
አርማጌዶን… አዋጅ …
ከሤጣን ጋር አባሪ …
ሥንት አለ መሠሪ ?
በሰው ደም ቆማሪ ?…
የዋሃንን ለማጥፋት
በቋንቋ የሚያቧድን …
በኃይማኖት የሚያናቁር …
በድንቁርና ተጠቅሞ
ጥላቻን የሚቸረችር ።
” ሥንት አለ አፈ ቅቤ
ሆኖ ልበ ጩቤ ፡፡ ”
በሠላ አንደበቱ
ውሃ ፤ የሚያረጋችሁ
ድንገት ሳታስቡት
ከህይወት መዝገብ ላይ…
የሚያሰርዛችሁ ፡፡
ሲኦልን ፈጥሮላችሁ
ገነት ናት በማለት…
የሚያሳምናችሁ ፡፡
ሞት ደግሶላችሁ
” ህይወት እኮ እንዲህ ናት !…
አትገረሙ !… ” የሚላችሁ ፡፡
” ይኼ ፣ የትም ያጋጥማል…”
እያለ …
የሚያላግጥባችሁ ። …
አሜሪካ የሌለ !
አውሮፓ የሌለ !
የዘረኝነት እሣት !
የቋንቋ አምላኪነት …
ኢትዮጵያን ሲያጠፋት…
በአይናችሁ ፤ …
በብረቱ እያያችሁ
” አይዞችሁ አትስጉ…
ይኽም ያልፋል ! ” እያለ
የሚያዘናጋችሁ ፡፡ …
ዛሬም ይኽ ሰው ገዝፎ …
በመላ ጦቢያ ላይ
በዳቢሎስ ህሊና – ያሴራል
ኢሢላም ክርስቴን ላይ
የጦስ ዶሮ ይጥላል …
እልቂት ይደግሳል ፡፡
ሰውን ያለ ኃጥያቱ
ሥቀሎ !ሥቀሎ ! ሥቀሎ !
እያለ ይጮኻል ።
የክርሰቲያን እናት
የሙስሊሙ እናት
የለቅሶ ድምፅ
ለአገር ይሰማል ።
” ፀጥታ አሥጠባቂው ፤
ሠላም አሥከባሪው ፤
ይኽንን እየሠማ …
እንዴት ዝም ይላል ? ”
ብለን እንጠይቃለን …
” ጥፋት ሲደጋገም …
እንባ ዝናብ ሲሆን …
የሰው ደም ሲጎርፍ…
መንግሥት ዳተኛ የሆነው
ምንድን ቸግሮት ነው ?
የፍትህን አለንጋ …
ወዴት ሸሽጓት ነው ?… ”
ወይስ …
” መንግስት ሞቷል !?
የገደለውም ፈጣሪው ነው ።
ያ ፣ በዘር እና በቋንቋ የሚያምነው ..
አሥቀድሞ ሥለፈጠረው ?
በህገመንግሥቱ ሥለሚያኖረው ?
በፈጣሪው ሐሣብ ሥለሚኖሮ ይሆንን ?
ሰው ቋንቋ ሆኖ … ሲተራረድ
ዳር ቆሞ የሚያየው ? ”
እንበል ?
ወይስ ?
እንበል 12
እዝጊኦ ! ማሀረነ…
መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ
2014 ዓ/ም
ውድ አዘጋጅ
ዛሬ ደግሞ በግጥም ሃሳቤን ይዤ ብቅ ብያለሁ ፡፡ በፖለቲካዊ ግጥሙም ጭምር የባለቂኔው የክቡር ሎሬት ፀጋዬ አድናቂነኝ ፡፡ የመንግስቱ ለማና የፀጋዬ ግጥሞች ተጽዕኖ በግጥሞቼ ውስጥ ይታያሉ