በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በተፈጸመው ሰውን የማቃጠል ድርጊት፤ የመንግስት የጸጥታ አባላት መሳተፋቸውን ማረጋገጡን ኢሰመኮ አስታወቀ

በተስፋለም ወልደየስ

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ መተከል ዞን፣ ጉባ ወረዳ፣ አይሲድ ቀበሌ የተፈጸመው በሕይወት የነበረ ሰውን የማቃጠል ድርጊት፤ በመንግስት የጸጥታ አባላት ተሳትፎ ጭምር የተከናወነ መሆኑን ማረጋገጡን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አስታወቀ። ድርጊቱ በተፈጸመበት ዕለት፤ የመንግስት የጸጥታ ኃይል አባላት አስር ሰዎችን ተኩሰው መግደላቸውን እና አስክሬናቸውን ማቃጠላቸውን ኮሚሽኑ ገልጿል።

በሕይወት የነበረ ሰው በአሰቃቂ ሁኔታ በእሳት ሲቃጠል የሚያሳይ ቪዲዮ ከቀናት በፊት በማህበራዊ የትስስር ገጾች ከተሰራጨ በኋላ ድርጊቱ በኢትዮጵያውያን የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ዘንድ ከፍተኛ ቁጣን ቀስቅሶ ቆይቷል። ይህን ተከትሎ ኢሰመኮ አካሄድኩት ባለው “አፋጣኝ ማጣራት” ድርጊቱ የተከናወነው ባለፈው ሳምንት ሐሙስ የካቲት 24፤ 2014 መሆኑን አመልክቷል።

ኮሚሽኑ ለድርጊቱ መነሻ የሆነውን ክስተት እና እርሱን ተከትሎ ተፈጽመዋል ያላቸውን ግድያዎች ዛሬ እሁድ መጋቢት 4 ባወጣው ጋዜጣዊ መግለጫ አብራርቷል። እንደ ኢሰመኮ ገለጻ ድርጊቱ ለመፈጸሙ መንስኤ የሆነው፤ በዋዜማው የካቲት 23 በጉባ ወረዳ አይሲድ ቀበሌ አፍሪካ እርሻ ልማት ማህበር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በሲቪል ሰዎች እና በመከላከያ ሰራዊት አባላት ላይ የተፈጸመው ጥቃት ነው።

ጥቃቱ የተፈጸመባቸው ሰዎች፤ ከግልገል በለስ ከተማ በመኪና ተሳፍረው ወደ ታላቁ ህዳሴ ግድብ፣ ማንኩሽ እና አሶሳ ከተማ ሲጓዙ የነበሩ ግለሰቦች እንደሆኑ ኢሰመኮ በመግለጫው አስታውቋል። በአካባቢው ባለው የደህንነት ስጋት ምክንያት ግለሰቦቹ በመከላከያ ሰራዊት አባላት ታጅበው በሚጓዙበት ወቅት በተፈጸመባቸው ጥቃት ሶስት ሲቪል ሰዎች እና ቢያንስ 20 የመከላከያ ሰራዊት አባላት መገደላቸውን ማረጋገጡን ኢሰመኮ ገልጿል።

በዕለቱ ከተገደሉት ሰዎች ውስጥ የመከላከያ ሰራዊት ሻለቃ አመራር ጭምር እንደሚገኝበት ኮሚሽኑ አክሏል። በዚሁ ጥቃት 14 የመከላከያ ሰራዊት አባላት ላይ ቀላል እና ከባድ የአካል ጉዳት መድረሱንም ኢሰመኮ አመልክቷል። በዕለቱ በመንግስት የጸጥታ ኃይሎች እና ጥቃቱን ባደረሱት የታጠቁ ኃይሎች መካከል ከቀኑ ስምንት ሰዓት ጀምሮ እስከ ንጋት 12 ሰዓት የቆየ ውጊያ ሲካሄድ መቆየቱንም የኮሚሽኑ መግለጫ አትቷል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  በሰላማዊ መንገድ ተቃውሞን በመስጂድ ጊቢ ማሰማት ለሞት የሚያበቃ ወንጀል ነውን?

በማግስቱ የካቲት 24 ተጨማሪ የመንግስት የጸጥታ ኃይሎች በስፍራው ደርሰው እስከ ረፋዱ አራት ሰዓት ድረስ የዘለቀ የተኩስ ልውውጥ ቀጥሎ እንደነበር ኢሰመኮ አስታውቋል። በዚህም ውጊያ ከታጣቂዎቹ መካከል 30 የሚሆኑት መገደላቸውን እና ቀሪዎቹ ታጣቂዎቹ መሸሻቸውን መረዳቱን ኢሰመኮ ገልጿል።

ከጥቃቱ የተረፉት መንገደኞች እና የመከላከያ ሰራዊት አባላት ወደ አይሲድ ከተማ የገቡት የካቲት 24 ከቀኑ ስድስት ሰዓት አካባቢ እንደነበር የኢሰመኮ መግለጫ ጠቁሟል። በአካባቢው በተከሰተው አደጋ በከፍተኛ ውጥረት ውስጥ በነበረችው የአይሲድ ከተማ፤ የመንግስት የጸጥታ ኃይሎች ባደረጉት ፍተሻ ወደ አቅራቢያው ከተሞች ሲጓዙ ከነበሩ መንገደኞች መካከል በቅርቡ ከእስር የተፈቱ ስምንት የትግራይ ተወላጆችን ማግኝታቸውን ኢሰመኮ በመግለጫው ጠቅሷል።

“ከመተከል ዞን ማረሚያ ቤት ተፈትተው፣ የይለፍ ወረቀት በመያዝ ወደ መኖሪያቸው በመመለስ ላይ ነበሩ” የተባሉት እነዚህን የትግራይ ተወላጆች፤ “እናንተ ናችሁ መረጃ ሰጥታችሁ ጥቃቱን ያስፈጸማችሁት” በማለት የመንግስት የጸጥታ ኃይሎች ከተሳፈሩበት መኪና አስወርደው እንደፈተሿቸው ተገልጿል። በፍተሻውም “አንድ የወታደራዊ መገናኛ ሬዲዮ፣ የተለያዩ ፎቶግራፎች እና ከ40,000 ብር በላይ ገንዘብ እንደተገኘ” መገለጹ በኢሰመኮ መግለጫ ላይ ተካትቷል።

የመንግስት የጸጥታ አባላት ተጠርጣሪዎቹ “እየደበደቡ” የምርመራ ጥያቄ ይጠይቁ እንደነበር የገለጸው ኢሰመኮ፤ በዚህ ወቅትም ከተጠርጣሪዎቹ መካከል አንደኛው “በአካባቢው በተፈጸመው ጥቃት ላይ እጃችን አለበት፤ ባምዛ በሚባለውና በግልገል በለስ ቦታዎች ሰዎች አሉን” ማለቱን ጠቅሷል። ይህን ተከትሎም የመንግስት የጸጥታ ኃይሎች አስር ሰዎችን ተኩሰው መግደላቸውን ኢሰመኮ አስታውቋል። በጸጥታ ኃይሎቹ ከተገደሉት ውስጥ ሁለቱ “ሁኔታውን የተቃወሙ” የጉሙዝ ተወላጆች እንደሆኑ ኮሚሽኑ ገልጿል።

የመንግስት የጸጥታ ኃይሎች የሟቾቹን አስክሬን፤ ከከተማዋ ወጣ ብሎ ወደሚገኝ ጫካ ስፍራ በመውሰድ አስክሬናቸውን ማቃጠላቸውን የዓይን እማኞች እንደነገሩት ኢሰመኮ በመግለጫው አስፍሯል። “በዚህ መካከልም ከተጠርጣሪዎቹ ተገዳዮች ጋር ግንኙነት አለው የተባለን አንድ ሌላ የትግራይ ተወላጅ፤ የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች በተሳፈረበት መኪና ውስጥ ተደብቆ በጥቆማ ካገኙት በኋላ፤ በገመድ አስረው በመውሰድ ቀድሞ በመቃጠል ላይ ከነበሩት አስክሬኖች ላይ እንደጨመሩት እና በእሳት ተቃጥሎ እንደሞተ ምስክሮች ለኮሚሽኑ አስረድተዋል” ሲል ኢሰመኮ በቪዲዮ ስለ ተቀረጸው አሰቃቂ ግድያ የደረሰበትን ይፋ አድርጓል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ገዥዎቻችንና የሃይማኖት አባቶቻችን ከየት ነው የመጡት? - ፊልጶስ

በግለሰቦቹ ላይ የተፈጸመው እርምጃ “ከዳኝነት ውጪ የተፈጸመ ግድያ” (extra-judicial killing) እንደሆነ የገለጸው ኢሰመኮ፤ በአካባቢው የነበሩ የጸጥታ ኃይሎች “የነበራቸው የተለያየ የተሳትፎ መጠን በተጨማሪ የወንጀል ምርመራ ሊጣራ የሚገባው ነው” ሲል አሳስቧል። ድርጊቱን በቀጥታ በመፈጸም አሊያም አስገዳጅ ተግባሮችን ባለመፈጸም (by commission or omission)  ተሳትፈዋል በሚል በኢሰመኮ መግለጫ የተጠቀሱት፤ የመከላከያ ሠራዊት፣ የአማራ ክልል ልዩ ፖሊስ እንዲሁም የደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ልዩ ፖሊስ አባላት ናቸው።

መንግስታዊውን የሰብዓዊ መብት ተሟጋች በዋና ኮሚሽነርነት የሚመሩት ዶ/ር ዳንኤል በቀለ፤ በቁጥጥር ስር የዋሉ ተጠርጣሪዎችን ከዳኝነት ሂደት ውጭ መግደል እና በተለይም በእሳት አቃጥሎ መግደል “ፈጽሞ ከሕግ አስከባሪ አባሎች የማይጠበቅ ግፍና ጭካኔ የተሞላበት የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ነው” ሲሉ ድርጊቱን ኮንነዋል። ዋና ኮሚሽነሩ የሕግ ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ፤ በተጠርጣሪዎች ላይ ተገቢው የወንጀል ምርመራ በአፋጣኝ እንዲደረግም አሳስበዋል።

“የመንግሥት ሕግ አስከባሪ አባሎች እራሳቸው በግልጽ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ፈጻሚዎች ሆነው መታየታቸው፤ ሰዎች በሕጋዊ ሥርዓት ላይ የሚኖራቸውን እምነት የሚሸረሽርና ለተጨማሪ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት የሚያጋልጥ በመሆኑ፤ መንግሥት የምርመራውን ሂደትና ውጤት በተመለከተ የተሟላ መረጃ ለሕዝብ ይፋ ሊያደርግና ፍትሕን ለማረጋገጥም የሟች ቤተሰቦችን ሊክስ ይገባል” ብለዋል ዶ/ር ዳንኤል።

የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ትላንት ቅዳሜ መጋቢት 3፤ 2014 ባወጣው መገለጫ “መንግስት ይህን አይነት ፍፁም ከሰብአዊነት የራቀና ጭካኔ የተሞላበትን ድርጊት የፈጸሙ አካላትን አጣርቶ ህጋዊ እርምጃ ይወስዳል” ብሎ ነበር። ድርጊቱን “እጅግ አሰቃቂ እና ከሰብአዊነት ያፈነገጠ” ሲል የጠራው የኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት፤ ይህ እኩይ ድርጊት መጠፋፋትን ያፈጥን ካልሆነ በቀር ሰላምንም ሆነ ፍትህን እውን ሊያደርግ አይችልም። በመሆኑም ሊኮነንና ሊወገዝ ይገባል” ሲል የመንግስትን አቋም አስታውቋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

ተጨማሪ ያንብቡ:  ለመተከሉ ጭፍጨፋ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ቀጥተኛ ተጠያቂ ናቸው! - ያሬድ ኃይለማርያም

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share