ያለ ዴሞክራሲያዊ አርበኝነት  ዴሞክራሲያዊ ድል አይታሰብም! – ጠገናው ጎሹ

August 5, 2021
ጠገናው ጎሹ

በአጭርና ቀላል አገላለፅ አርበኝነት (patriotism) ሰፊና ጥልቅ የሆነው የአገር ፍቅር ምንነት፣ ለምንነት፣ እንዴትነት እና ወዴትነት  የሚገለለፅበት ሃያል ቃል (ፅንሰ ሃሳብ) ነው።

አርበኝነት ባርነትን የሚፀየፍና እና ነፃነትንና ፍትህን ከምር የሚሻ ትውልድ ሁሉ የሚቀባበለው እና የእየራሱን ድርሻ በመወጣት አገራዊ ክብሩንና ሁለንተናዊ የዜግነት መብቱን የሚያረጋግጥበት ታላቅ አገራዊ (ህብረተሰባዊ) እሴት እንጅ የቀደመው ትውልድ  ከውጭ ወራሪ ሃይሎች  ጠብቆ ያቆያትን አገር ለውስጥ ተኩላዎች (ለሸፍጠኛ ፣ ሴረኛና ጨካኝ  ገዥ ቡድኖች) አሳልፎ እየሰጠ በከንቱ የሚመፃደቅበት ቃል (ፅንሰ ሃሳብ) አይደለም።

አርበኝነት የጋራ አገርን  ልኡላዊነትና አንድነት በጋራ የመከላከል ፣የመጠበቅ እና ከትውልድ ወደ ትውልድ የማስተላለፍ ሰፊና ጥልቅ የጋራ እሴት እንጅ በጎሳና በቋንቋ ማንነት የሚመነዘር ፅንሰ ሃሳብ አይደለም።

የቀደመው ትውልድ የገርን ዳር ድንበርና ልኡላዊነት አስከብሮ ለትውልድ በማስተላለፍ ታላቅ የአርበኝነት ግዴታውን ተወጥቷል ። የዛሬው ትውልድ የአርበኝነት ተልእኮ   ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የተረጋገጠባት ፣ ሉአላዊነቷ የማይገሰስና በዓለም ፖለቲካም አመርቂ የሆነ ሚና የሚኖራት ኢትዮጵያን እውን የማድረግ እጅግ ታላቅ  ተልእኮ  እንጅ ለነውረኛና ጨካኝ የገዥ ቡድኖችና ግብረ በላዎቻቸው ርካሽ የፖለቲካ ፕሮፓጋንዳ የሚመች ፅንሰ ሃሳብ አይደለም።

የጎሳና የቋንቋ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ቁማርተኞች ይህን ድንቅ ፅንሰ ሃሳብ የርካሽ ፖለቲካ ጨዋታቸው ሰለባ ካደረጉት ይኸውና ከሦስት አሥርተ ዓመታት በላይ አስቆጠረ። ዛሬም የዚያው ሥርዓት ውላጆች የቀድሞ አለቃቸውን (ህወሃትን) በማስወገድ እና ስምና ጉልቻ በመቀያየር ሥልጣኑን በተረኝነት ከተቆጣጠሩ ጀምረው ይህንኑ ፅንሰ ሃሳብ ለርካሽ የፖለቲካ ጨዋታቸው ሽፋን ሰጭነት እየተጠቀሙበት ቀጥለዋል ።  በዴሞክራሲያዊ አርበኝነት የብልግና ሥልጣናቸውን ለመገዳደር የሚሞክርን ግለሰብ ወይም ድርጅት የጥቃታቸው ሰላባ ሲያደርጉ  አርበኝነትን የእነርሱ ርካሽና ጨካኝ ፖለቲካ ሽፉን ሰጭ ለማድረግ ፈቃደኛ የሆነውን ግን ይሾማሉ ፤ የሸልማሉ።

በእጅጉ የሚያሳዝነውና የሚያስፈራው ደግሞ ውደቀቱ እንደ ግለሰብ ወይም እንደ ቡድን ብቻ ሳይሆን እንደ ትውልድ ወይም እንደ ማህበረሰብ እየሆነ የመምጣቱ አደጋ ነው። የአሁኖቹ ተረኛ ገዥ ቡድኖች ጥርሳቸውን ነቅለው ያደጉበትን እኩይ የፖለቲካ ሥርዓት በበላይነት ሲመሩት የነበሩትን ጌቶቻቸውን (ህወሃቶችን) ከቤተ መንግሥት አስወግደው ከነ መሠረታዊ አስተሳሰቡ ፣ ከነ ህገ መንግሥቱ ፣ ከነ መዋቅሩ እና ከነ አስከፊ ወንጀሉ እንዲቀጥል ያደረጉበትን አደገኛ አካሄድ ከዴሞክራሲያዊ አርበኝነት ተጋድሎ ( ከሰላማዊ እምቢ አልገዛም ባይነት) ውጭ ለማሸነፍ ጨርሶ አይቻልም።

የቀደምት ትውልድ አገር የማዳንና የማቆየት አርበኝነት ተጋድሎ ምእራፍን ዘመናችን ወደ እሚጠይቀው የዴሞክራሲያዊ አርበኝነት ተጋድሎ ምእራፍ ለማሸጋገር ባለመቻላችን ለዘመናት ከመጣንበት አስከፊ አዙሪት ውስጥ መልሰን ተዘፍቀንበታል ። ባለጌና ጨካኝ ገዥ ቡድኖችም ለልኡላዊነት መደፈር ዋነኛ ምክንያቶቹ እነርሱው እራሳቸው  ሆነው ሳለ በሸፍጥ፣ በሴራና በወንጀል የተበከለው ሥልጣነ መንበራቸው ሥጋት ላይ የወደቀ በመሰላቸው ቁጥር ልኡላዊነትህ ተደፈረ፤ እነ እገሌ ሊያፈራርሱህ ነው፤ የመፈንቅለ መንግሥት አደጋ አንዣቧል ፤ የውጭ ሃይሎች የባርነት  ጣልቃ ገብነት ደጅህ ላይ ቆሟል  ፣ለዛሬ ያልሆነ መስዋእትነት ለመቸ ሊሆን ? ወዘተ በሚል ስሜትን ኮርኳሪና ርካሽ የፖለቲካ ዲስኩር መከረኛውን ህዝብ ለምንና እንዴት? ብሎ እንኳ መጠየቅ በማይችልበት የተሳከረ ሁኔታ ውስጥ ዘፍቀውታል።

የህዝብን መሠረታዊ የግንዛቤ አቅም እጅግ ዝቅ የሚያደርግ ሰበብ እየደረደሩ ከትግራይ መውጣታቸውን ሲነግሩን “በመከራችን የመሳለቁ ፖለቲካ ጨዋታ በቃችሁ ” ከማለት ይልቅ አብይ አህመድ ከሌለ አገር ትፈርሳለች የሚል እጅግ አሳፋሪና ወራዳ አስተሳሰብ ሰለባዎች ሆነን ቀጥለናል ። ለዚህ ነው ከእንዲህ አይነት ልክ የሌለው የፖለቲካና የሞራል ድህነት ከተጠናወተው አዙሪት ሰብሮ ለመውጣት ብቸኛው መድህን የዴሞክራሲያዊ አርበኝነት  ተጋድሎ ብቻ ነው ማለት ትክክል የሚሆነው።

  ለምን? ቢባል፦

አርበኝነት በፅዕኑ አገራዊ ዓላማ፣ መርህና ግብ ላይ ፀንቶ የመገኘት ተግባራዊ የአገር ፍቅር እሴትን በውስጡ የተሸከመ ሃያል ቃል እንጅ የዲስኩር ወይ የንግግር ወይም የተረት ተረት ማሳመሪያ ቃል አይደለም።

አርበኝነት ትውልድ ተሻጋሪነት ያለው እጅግ ግዙፍና ጥልቅ የአገር ፍቅር መገለጫ ፅንሰ ሃሳብ እንጅ በውስን ወቅትና ሁኔታ የሚገለፅና የሚወሰን ክስተት አይደለም ።

አዎ! አርበኝነት እያንዳንዱ ትውልድ የሚያጋጥመውን ውጫዊና ውስጣዊ ፈተና በቆራጥነትና በጥበብ በማሸነፍ የሚቀባበለው እጅግ ውድ አገራዊ እሴት እንጅ በአንድ ወቅታዊ ሁኔታ የሚወሰን እና የአገርን ልኡላዊነት አጋልጠው ለሚሰጡ እኩይ ገዥ ቡድኖች  ረካሽ የፖለቲካ ፍጆታነት የሚውል ፅንሰ ሃሳብ በፍፁም አይደለም።

የአድዋውን እና ሌሎች መሰል የአርበኝነት ተገድሎዎችንና አኩሪ ተሞክሮነታቸውን አሁን ካለንበት አስከፊ የሆነ ሁለንተናዊ የውድቀት አዙሪት ወጥተን ይህ ዘመን የሚጠይቀውን  ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን ለማድረግ እንችል ዘንድ በአግባቡና ከምር መጠቀም  ባለመቻላችን እራሳችንን አሁን ከምንገኝበት ደጋግሞ የመውደቅ አባዜ ውስጥ አግኝተነዋል።

የገንዛ እራሳችንን ልክ የሌለው ደጋግሞ የመውደቅ አባዜ በመጋፈጥ ተገቢውን ማድረግ ሲሳነን እጅግ አሳፋሪ የሰበብ ድሪቶ የመደረት ክፉ ልማድ እየተጠናወተን በመቸገራችን እንጅ አሁን የምንገኝበት ግዙፉና መሪሩ እውነት ይኸው ነው።

አዎ! ነገረ ሥራችን ሁሉ በግልብ ስሜትና በክስተቶች ዙሪያ የሚሽከረከር ሆኖብን ልብ አንለውም እንጅ አሁንም የቀደምት ትውልድ የአርበኝነት ተጋድሎ አኩሪ ትምህርት ሰጭነትን (ተሞክሮነትን) ተጠቅመን የእራሳችን ዘመን የሚጠይቀውን የዴሞክራሲ አርበኝነት ተልእኮ ለመወጣት በሚያስችል ሁኔታ ውስጥ አይደለንም። እናም ልብ እንበል!

አሁን እያጋጠመን ላለው አስከፊ ውድቀት ዋነኛ ከሆኑት ምክንያቶች አንዱ በዴሞክራሲያዊ አርበኝነት  እና  ሸፍጠኛና ሴረኛ ገዥ ቡድኖችና ፖለቲከኞች  ለርካሽ የፖለቲካ ቁማራቸው ሽፋን ሰጭነት በሚደሰኩሩልን የአርበኝነት ዲስኩር መካከል ያለውን ልዩነት ከምር ለማስተዋልና ነውር ነው ለማለት ያለመቻላችን ውድቀት ነው። የዚህ እጅግ አስቀያሚ የፖለቲካና የሞራል ውድቀት  ቀዳሚ  ሰለባ እየሆነ ያለው  “አንቱ የተባልኩ  ምሁር ነኝ” የሚለው የህብረተሰብ ክፍል የመሆኑ መሪር  እውነታ ደግሞ በእጅጉ ያማል። በእጅጉ ያስጨንቃልም።

አለመታደል ወይም እርግማን ሆኖብን ሳይሆን በእኛው በእራችን ልክ የሌለው የውድቀት ልክፍት ምክንያት ከእኛ ከእራሳችን አልፎ ለሌሎች አንፀባራቂ ምሳሌ የሆነው እንቁ የአገር ፍቅር ተጋድሎ (የአርበኝነት ውሎ) ታሪክ ከቶም ሊፋቅ የማይችል ቢሆንም እያደበዘዝነው የመሆኑን መሪር ሃቅ ግን ለመካድ የሚያስችል አሳማኝ ምክንያት የለም። ለምን? ቢባል የቀደምት ትውልድን የአርበኝነት ተጋድሎ ታሪክ አጥብቀን እየደሰኮርን ወይም እየሰበክን ከእኛው  ከእራሳችን ዘመን ታሪካዊ  የአርበኝነት ተልእኮ ሃዲድ ደጋግመን በመንሸራተታችን  ለዘመናት ከኖርንበት የውድቀት አዙሪት ሰብረን ለመውጣት አልቻልንምና። የጎሳ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ገዥ ቡድኖች ባዘጋጁልን ወጥመድ ውስጥ  እየገባን የመንድፋደፍ አስከፊ የፖለቲካና የሞራል ዝቅጠትን  በዴሞክራሲያዊ አርበኝነት መንፈስና ተጋድሎ ሰብረን እስካልወጣን ድረስ ኢትዮጵያን  እንኳን  የነፃነት ፣ የፍትህና የእድገት አገር ለማድረግ ወደ መሰነጣጠቅ እየገፏት ከሚገኙ ሸፍጠኛና ሴረኛ የፖለቲካ ቁማርተኞች ለመታደግ አይቻለንም ።

ሌሎች በተለያየ ጊዜና በተለያዩ ቦታዎች የተከናወኑ የአርበኝነት ተጋድሎ ውሎዎች ሳይዘነጉ ከዛሬ 125 ዓመት (እ.አ.አ 1896) በፊት የተከናወነው እና ከእኛ አልፎ በቅኝ ገዥዎችና ወራሪ ሃይሎች መከራውንና ውርደቱን ይቆጥር ለነበረው ህዝበ አዳም ሁሉ በድንቅ ምሳሌነቱ (አርአያነቱ) የሚጠቀሰው የአድዋ ድል ባለቤቶች ነን ስንል ከዚሁ እጅግ ግዙፍና ጥልቅ የአርበኝነት ትርጉምና እሴት ተነስተን ነው። ይህን አኩሪ የአርበኝነት ተጋድሎ ታሪክ ተሞክሮ ተጠቅመን የእኛ ዘመን የሚጠይቀውን የዴሞክራሲያዊ አርበኝነት ታሪክ ለመሥራት አለማቻል ነው ከባዱና አሳሳቢው ጉዳይ።

እስኪ እራሳችንን እንጠይቀው ፦

·        ይህን ድንቅ የቀደምት ትውልድ የአርበኝነት ተጋድሎ ታሪክ ዘመናችን ወደ እሚጠይቀው የዴሞክራሲያዊ አርበኝነት ተጋድሎ ለማሸጋገር ለምንና እንዴት ተሳነን?

·        ይህ አይነት እጅግ አስቀያሚ ውድቀታችን አይደለም እንዴ በእጅጉ አስከፊ ለሆነ ድህነት (abject poverty) ሰላባነት እና ምፅዋእት ለማኝነት (ተመፅዋችነት) ያጋለጠን?

·        የዴሞክራሲያዊ አርበኝነት ድህነት አይደለም እንዴ የሞራልና የመንፈስ ልእልናችንን  ከባድ ፈተና ላይ የጣለው?

·        ይህ ውስጣዊ የፖለቲካ ጎደሎነት አይደለም እንዴ በልፅገዋል የሚባሉት ብቻ ሳይሆኑ ትናንት አገራዊ ነፃነት እንዲጎናፀፉ ምሳሌ የሆናቸውና ያገዝናቸው አገሮች ጭምር መሳለቂያ ያደረጉን?

·        ይህ የዴሞክራሲያዊ አርበኝነት ድህነት አይደለም እንዴ የውስጥ ገመናችን ሁሉ በረጋግዶ የዓለም መሳለቂያና መሳቂያ ያደረገን?

·        ይህ አስከፊ ውድቀታችን አይደለም እንዴ የአሜሪካ እና የአውሮፓ መንግሥታት ጣልቃ ገቡብን፣ ተጫኑን፣ ታዛዥ አደረጉን፣በድህነታችን ተጫወቱብን፣ ሊያፈራርሱን ነው፣ አብይን ሊፈነግሉት ነው፣ ጁንታውን መልሰው ሊያመጡብን ነው፣ የነቀዘ ስንዴያቸው በአፍንጫችን ቢወጣ ይሻላል  ፣ በዚህ ወቅት አብይንና ገዥ ፓርቲውን መሞገት ባንዳነት ነው ፣ ወዘተ የሚል እጅግ መያዣና መጨበጫ የሌለው እግዚኦታ እግዚኦ እንድንል እያደረገን ያለው?

·        የገንዛ ቤትን (አገርን) በሚያከብር፣ በሚያስከብር ፣ በሚያሳድግ ፣ በዓለም የፖለቲካ መድረክ ንቁና የተከበረ ተሳታፊ በሚያስደርግ፣ መልካም ራእይ እና ዘላቂ ዓላማና ግብ ባለው ፣ወዘተ  የዴሞክራሲያዊ አርበኝነት ተጋድሎ  ሳያስከብሩ “ቤተን ተዳፈሩብኝ ወይም ሊያፈርሱብኝ ነው” እያሉ ያዙኝና ልቀቁኝ ማለት ምን ማለት ነው?

·        የዴሞክራሲያዊ አርበኝነት አውራ ጠላት የሆነውን ሥርዓተ ኢህአዴግ/ብልፅግና ተልካሻ ሰበብ በመደርደር በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ እሹሩሩ እያሉ “እነዚህ እና እነዚያ ሃይሎች አገሬን ሊያፈርሱብኝ ነው” የሚል የኡኡታ ፖለቲካ የት ያደርሳል?

አለመታደል ወይም የፈጣሪ ፈቃድ ባለመሆኑ ሳይሆን በእኛው እጅግ የተደጋገመና አስከፊ የፖለቲካና የሞራል  ውድቀት ምክንያት ይህንን ድንቅና ጥልቅ የቀደምት ትውልዶች አገርን እንደ አገር ከውጭ ገዥና ወራሪ ሃይል ተከላክሎና ጠብቆ  ለማቆየት የተከናወነ የመጀመሪያ የአርበኝነት የተጋድሎ ታሪክ  ምእራፍ  እኛነታችንን (ኢትዮጵያዊነታችንን) ይበልጥ የተሟላ ለማድረግ ወደ  የሚያስችለን አስተሳሰብና አካሄድ ለመውሰድ (ለማድረስ) ገና  አልተሳካልንም። አዎ! ይህ ትውልድ ቆም ብሎ እራሱን በመጠየቅ የሚበጀውን ነገ ሳይሆን ዛሬ ማድረግ ካልጀመረ በአስከፊ ሁኔታ የሚያበላሸው የእራሱን እጣ ፈንታ ነው ።

የአንድ እኩይ ሥርዓት ውላጅ የሆኑ ሁለት አንጃዎች ወይም ጁንታዎች (ብልፅግና እና ህወሃት) በመከረኛው ህዝብ መከራና ሰቆቃ ላይ የሚጫወቱት እጅግ አስከፊ የፖለቲካ ጨዋታ ፍፃሜ የሚያገኘውና ወደ ታሪክነት የሚቀየረው በዴሞክራሲያዊ የአርበኝነት ተጋድሎ ብቻ ነው።

ወደድንም ጠላንም እራሳችንን ለማታለል ካልፈለግን በስተቀር በዘመናት ፖለቲካ ወለድ ወንጀል የተጨማለቁ የኢህአዴግ/የብልፅግና እና የህወሃት ፖለቲከኞች በሚዘውሩት ወይም ለመዘወር በሚፈልጉት የፖለቲካ አውድ ውስጥ እንኳን ዴሞክራሲን እውን ማድረግ አገርን እንደ አገር ለማቆየትም እርግጠኛ መሆን ፈፅሞ አይቻልም።

አዎ!  ኢትዮጵያን ኢትዮጵያ ብለው ለመጥራት በሚፀየፏ እና የልምላሜ ፣ የተስፋና የመስዋእትነት ምልክት የሆነውን ድንቅ ህብረ ቀለም ሰንደቅ ዓላማዋን ባዩ ቁጥር እብደት እየቃጣቸው ያዙንና ልቀቁን በሚሉ የጎሳና የቋንቋ አጥንት ቆጠራ  ፖለቲካ ቁማርተኞች በሚመራ ገዥ ፓርቲና መንግሥት ዴሞክራሲ ይወለዳል ብሎ ማሰብ የለየለት የፖለቲካ አታላይነት ወይም  ቂልነት ወይም ተንበርካኪነት ወይም አድርባይነት ወይም ልጣፍነት፣ ወይም ቀጣፊነት ነው።

ብቸኛውና ዘላቂው መፍትሄ ከመቃብር አፋፍ የተመለሰውንና ስያሜና ጉልቻን በመቀየር የቀጠለውን ሥርዓተ ኢህአዴግ እንደ ሥርዓት በዴሞክራሲያዊ አርበኝነት ተጋድሎ አስወግዶ ወደ እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መሸጋገር ነው።

የዴሞክራሲያዊ አርበኝነት ተምሳሌት መሆን የማይበዛበት እስክንድር ነጋ “ድል ለዴሞክራሲ! “ ሲል የዴሞክራሲያዊ አርበኝነትን ፍፁም አስፈላጊነት አብሮ እየነገረን መሆኑን የምንረዳው የመፅሐፉን ገፆች እየገለጥን ማንበብ ስንጀምር ነው።

እናም ያለ ዴሞክራሲያዊ አርበኝነት ዴሞክራሲያዊ ድል ከቶ አይታሰብምና ለዚህ እልህ አስጨራሽ ትግል ቀጣይነት ይበልጥ ዝግጁ ሆኖ መገኘትን ግድ ይላል ።

ይህ እንደሚሆን ያለኝን ተስፋ እየገለፅሁ አበቃሁ!

2 Comments

  1. አይ ጠገናው ጎሹ በአሁኑ ሰኣት ህገራችን በውሥጥ ቡቃያዎች በጦርነት እየተዋከብች በውጭ ጠላትም መከራዋን እያየች የኢትዮጵያ ልጆችም በአንድነት ሆነው የመጣውን ጠላት በመመከት ላይ እያሉ ይህንን የወረደ እና የወደቀ የአሳማ መተኛ ዝቃጭ አዛባ ጽሁፍ ማቀረብህ ለማነው? ከቻልክ ይህንን የ”ያለ ዲሞክራሲያዊ አርብርኝነት ዲሞክራሲያዊ ድል ከቶ አይታሰብም ያልከውን በኋላህ ያለውን ጠዋት ጠዋት ጥረግበት ከልሆነም ንፍጥህን አብስበት። የጁንታ እስካርባ እና ካልቾ እዳይበረታብህ በዚያው አይጥ ጉድጓድ ሆነህ ባቅላባ ቀቅልላቸው።ለአይምሮህም ሀኪም ጎብኝ።

  2. Ljij Ambaw, first of all thank you for taking your time to read my opinion and expressing you comment in any way you feel and based on the reason you may have ! I am a person of conviction that anyone can say his or her own say based on his or interest, affiliation, capacity, or any other unexplained motive and that is fine . I do nor write not expecting all kinds of comments including a very belittling or extremely unproductive ones like yours.
    The only thing I want to say is that this kind of political mentality and moral degradation type of ideas or views are very serious challenges of the politics of our country !
    Do not worry about my personal affairs ! Let’s try hard to think and behave in such a way that the politics of our country could move forward for the better!!
    I hope you would somehow and somewhat try to think and do the right thing !

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.