አሜሪካ የህዳሴው ግድብ ሁለተኛ ዙር ሙሌት “ውጥረትን የመጨመር አቅም አለው” አለች

የህዳሴውን ግድብ ሁለተኛ ዙር ሙሌት መጀመሩ፤ በኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብጽ መካከል “ውጥረትን ከፍ የማድረግ አቅም አለው” ስትል አሜሪካ አሳሰበች። ሀገሪቱ ሁሉም ወገኖች ውጥረትን ከሚያባብሱ የተናጠል እርምጃ እንዲታቀቡም ጥሪ አቅርባለች።

ይህንን የአሜሪካንን አቋም ዛሬ ማክሰኞ ምሽት ይፋ ያደረጉት የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ቃል አቃባይ ኔድ ፕራይስ ናቸው። ቃል አቃባዩ በዕለታዊ ጋዜጣዊ መግለጫቸው ላይ እንደተናገሩት፤ ሶስቱ ሀገራት በህዳሴው ግድብ ላይ ዘላቂ የሆነ ስምምነት ላይ እንዲደርሱ አሜሪካ “በትብብር መንፈስ የተሞላ እና ገንቢ” ጥረት ማድረጓን ትቀጥላለች።

“የአባይ ውሃ ለሶስቱ ሀገራት ያለውን ያለውን ዋጋ እንረዳለን” ያሉት ቃል አቃባዩ፤ ሀገራቱ በህዳሴው ግድብ ላይ ያቋረጡትን ውይይት እንዲቀጥሉ ሀገራቸው ማበረታቷን እንደምትቀጥል ተናግረዋል። ውይይቱ “ፍሬያማ፣ ተጨባጭ እና ገንቢ” ይሆናል የሚል ተስፋም እንዳላቸውም ገልጸዋል። በዚህ እሳቤ ላይ በመመስረትም አሜሪካ በአፍሪካ ህብረት የሚመራውን ሂደት ስትደግፍ መቆየቷንም አክለዋል።

የአፍሪካ ህብረት መር ሂደቱ “ውጥረትን ለመቀነስ፣ ፍሬያማ ድርድሮችን ለማመቻቸት እና ቀጠናዊ ትብብሮችን ለማጎልበት” ያለመ እንደሆነ በመግለጫቸው የጠቀሱት ፕራይስ፤ በሶስቱ ሀገራት የሚካሄድ የተናጠል እርምጃ ግን ከዚህ በተቃራኒው “ውጥረቶችን የሚጨምር ነው” ሲሉ ተችተዋል። ማንኛውም የተናጠል እርምጃ አሁን ጉዳዩ ባለበት ደረጃ እና ሰላማዊና ገንቢ መፍትሄ ማምጣት በሚለው እቅድ መካከል “ትልቅ ክፍተት” ይፈጥራል ሲሉም ስጋታቸውን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ያከናወነችው ሁለተኛ ዙር የህዳሴው ግድብ የውሃ ሙሌት “እንደ ተናጠል እርምጃ” ይቆጠር እንደው ከጋዜጠኛ ጥያቄ የቀረበላቸው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ቃል አቃባይ፤ ድፍን ያለ መልስ በመስጠት በቀጥታ ምላሽ ከመስጠት ለመቆጠብ ሞክረዋል። “የውሃ ሙሌቱ ውጥረቶችን የሚጨምር የተናጠል እርምጃ ሊባል ይችላልን?” የሚል ጥያቄ በድጋሚ የቀረበላቸው ቃል አቃባዩ፤ ለጥያቄው አዎንታዊ ምላሽ ሰጥተዋል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ምንም ብታደርጉ ሰዎች ከማውራት አይመለሱም

“እንደማስበው ይህ ጉዳይ ውጥረቶችን ከፍ የማድረግ አቅም አለው ማለት አግባብ ነው” ብለዋል ኔድ ፕራይስ በምላሻቸው።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ዛሬ ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጋር በነበራቸው የስልክ ውይይት፤ ከትግራይ ጉዳይ ባሻገር ስለ ህዳሴው ግድብ ተወያይተው እንደው የተጠየቁት ቃል አቃባዩ ማረጋገጫ ሳይሰጡ ቀርተዋል። (በተስፋለም ወልደየስ

ኢትዮጵያ ኢንሳይደር

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share