የኮሮናሻይረስ በሽታ ኮሮና በሚባል ቫይረስ አማካኝነት የሚከሰት ነው። ቫይረሱ ዓዲስና በአጭር ጊዜ የዓለማችንን ክፍሎች ማዳረስ ችሏል። አሚኮ በየጊዜው አድማሱን እያሰፋ ስለመጣው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ አስመልክቶ የጤና ባለሙያ አነጋግሯል።
የበሽታው ምልክት ከሰው ሰው ቢለያይም እንደማንኛውም ሕመም ሙቀት፣ ትኩሳት፣ ድካም፣ የሰውነት መገጣጠሚያ ቁርጥማት፣ የጉሮሮ ቁስለት፣ በተለይ ደረቅ ሳል፣ የትንፋሽ ማጠር እንዲሁም ጭራሽ መተንፈስ እስከማቆም ማድረስና ሌሎች ምልክቶችንም ጭምር እንደሚያሳይ በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የጥበበ ግዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የኮሮናቫይረስ ሕክምናና ለይቶ ማቆያ ማዕከል ኀላፊ ሳሙኤል ሁነኛው (ዶክተር) አስረድተዋል።
የኮሮናቫይረስ ሕመም አምስት ደረጃዎች እንዳሉት ኀላፊው ገልጸዋል። የመጀመሪያው ደረጃ በሽታው ኖሮባቸው ምንም አይነት ምልክት ሳያሳዩ ሊድኑ የሚችሉ ናቸው፤ አብዛኛው የማኅበረሰብ ክፍልም በዚህ ደረጃ እንደሚካተት ጠቅሰዋል። በዚህ ደረጃ ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ካልተመረመሩ በስተቀር ሕመም መኖሩንም አያውቁትም ነገር ግን በመጠኑም ቢሆን በሽታዉን ሊያስተላልፉ ይችላሉ ብለዋል።
ሁለተኛው ደረጃ ደግሞ መጠነኛ የሕመም ምልክት ያላቸው፣ የጉንፋን አይነት ምልክት፣ አፍንጫ ማፈን፣ ሙቀት፣ ብርድ ብርድ ማለት፣ የራስ ምታት ወይም የልብ ድካምን ሊያስከትል ይችላል ብለዋል።
ሦስተኛው ደረጃ መካከለኛ ደረጃ ሲሆን ቫይረሱ ወደ ሳምባ በመውረድ የሳምባ ቁስለት በማስከተል የሚታይ ምልክት ነው። በዚህ ደረጃ የሚገኙ ሕመምተኞች ደግሞ ሳል፣ ትንፋሽ ማጠር እንዲሁም በሕክምና ወቅት የኦክስጅን መጠን የመውረድ ምልክት እንደሚታይ አብራርተዋል።
አራተኛው ደረጃ ከፍተኛ ደረጃ የደረሰ ነው። በዚህ ደረጃ የሚገኙ ሕሙማን ደግሞ የኦክስጅን መጠናቸው በጣም የወረደ፣ ከፍተኛ ድካም ያለባቸው፣ ብዙ የኦክስጅን እርዳታና ሕክምና ካልተደረገላቸው ለሕይወታቸው አስጊ ደረጃ ላይ የሚያደርስ መሆኑን ገልጸዋል።
አምስተኛውና የመጨረሻው ደረጃ በጽኑ የሚታመሙ ናቸው። በዚህ ደረጃ የሚገኙ ሕመምተኞች የመተንፈሻ መሣሪያ እገዛ የሚያስፈልጋቸው መሆናቸውን ዶክተር ሳሙኤል አስረድተዋል።
በማዕከላቸው በቀን እስከ 500 ሰዎች ምርመራ እየተደረገላቸው እንደሆነ የጠቆሙት ኀላፊው ከግማሽ በላይ ተመርማሪዎች ቫይረሱ እንደተገኘባቸው ተናግረዋል። በአሁኑ ወቅት የኦክስጅን እጥረት እንዳለባቸውም አስረድተዋል።
ከ50 በላይ የመካከለኛና የጽኑ ሕመምተኞች በማዕከላቸው የሕክምና አገልግሎት እየተሰጣቸው እንደሆነም ገልጸዋል። ወረርሽኙ በመዘናጋት ምክንያት ዋጋ እያስከፈለ ስለሆነ ኅብረተሰቡ ከምንጊዜውም በላይ ጥንቃቄ ሊያደርግ እንደሚገባ ዶክተር ሳሙኤል መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ባሕር ዳር፡ (አሚኮ)