ለተከበራቹህ ወገኖች
የኮሮና ልምድ ከጀርመን – የከረርው ሎክዳውን መላላት፣ ፈጣን ምርመራ እና ክትባት
ካለፈው በመቀጠል በ03.03.2021 ከዘጠኝ ሰዓታት ውይይቶች በኋላ የፌዴራል እና የሪጅናል ስቴት (ክልል) መንግስታት የኮሮና ጥብቅ ሎክ ዳውን እስከ መጋቢት ወር መጨረሻ እንዲቀጥል በመወሰን ተጨማሪ የኮሮና ሎክዳውን የማላላት የአፈጻጸም ሰሌዳ አጽድቀዋል። በዚህም መሰረት ሎክዳውኑ እስከ መጋቢት 28 2021 ተራዝሟል።
በጀርመን የኮሮና ቫይረስ ስርጭትም በዚህ ሳምንት መቀንሱን ቀጥሏል። በሰባት ቀናት ውስጥ ከ100,000 ነዋሪዎች መካከል የተገኝው ኢንፌክሽን በአማካይ 65 በመሆን ቀንሷል። (ለማነጻጸር ጎረቤት ሀገር ቼክ ሪፑብሊክ በመቶሺ ሰዎች መካከል ከ750 በላይ ነው።) የሟቾቹ ቁጠር በቀን ከ1ሺ በታች በመውረድ 04.03.2021 359 ደርሷል፣ ወረርሽኙ ከተከሰተበት ጊዜ አንስቶ በጀርመን 2,47 ሚሊዮን ሰዎች በኮሮና ቫይረስ ሲያዙ ከወረርሽኙ ጋረ በተያያዘ የሟቾች ቁጥር 71,240 ደርሷል። በቅርቡ ከተያዙት 46% የሚሆኑት ከእንግሊዝ ሀገር ከመጣው ራሱን በቀየርው የወረርሽኙ አይነት ነው። የጀርመን ሆስፒታሎች ዘርን ወይም ማንነት ተኮር የሆን ስታትስቲክስ መሰብስብ ባይፈቀድላቸውም ወረርሽኙ በቀጥር 8 ጽሁፌ ላይ እንደገጽኩት ከውጭ የሚመጡ ሰዎች የሚኖሩባቸው ቦታዋች ላይ የተስፋፋ እንደሆነ ይነገራል። ይህም የግንዛቤ ማነስ፣ በጋራ መኖሪያ ቤቶች የሚኖሩ፣ የመኖሪያ ቦታ ጥበት፣ ከፍተኛ የቤተሰብ ቁጥር እና ጠንካራ ማህብራዊ ግንኙነቶች ያሏቸው በመሆኑ እንደምክንያት ይጠቀሳል።
- ማህበርዊ ግንኙነት ከ08.03.2021 ጀምሮ
ከመጪው ሰኞ (ማርች 8) ጀምሮ ውስን የነበሩት የማህበራዊ ግንኙነት ግድበቶች ይነሳሉ። ከገዛ ቤተሰብ በተጨማሪም ከሌላ ቤተሰብ ጋር የሚደረጉ ማህበራዊ ግኑኝነቶች ሲፈቀዱ፣ ግን ይህ ከአምስት ሰዎች በላይ ማለፍ የለበትም። እስከ 14 ዓመት ዕድሜ ያላቸው ልጆች ከዚህ ነፃ ናቸው። ለሰባት ቀናት በተከታታይ ከ35 አዳዲስ ኢንፌክሽኖች በታች በሚከሰትባቸው ወረዳዎች ውስጥ ቢበዛ አሥር ሰዎች ካሏቸው ሁለት ቤተሰቦች ጋር ማህበራዊ ግንኙነት ይፈቀዳል።
- የመጽሐፍ መሸጫ መደብሮች፣ የአበባ መሸጫ ሱቆች፣ የመንጃ ፈቃድ ትምህርት ቤቶች
ትምህርት ቤቶች እና የፀጉር ማስተካካዮች አስቀድመው መከፈታቸው ይታወሳል። አሁን ደግሞ የመጽሐፍ መሸጫ ሱቆች፣ የአበባ ሱቆች እና የአትክልት ማዕከላት ቀጥለው ይከፈታሉ። ቢሆንም እንዚህ በአንዳንድ የፌደራል ሪጅኖች (ክልሎች) ውስጥ አስቀድመው የተከፈቱ አሉ። የመኪና እና የበረራ ትምህርት ቤቶችም በቅድመ ሁኔታዎች ሥራቸውን እንደገና ሊጀምሩ ይችላሉ። የመክፈት ቅድመ ሁኔታ የንፅህና ፅንሰ-ሀሳቦች እንደ የማስክ አጠቃቀም፣ የደንበኛ ማኔጅመንት፣ ምዝገባ፣ አየር ማናፍስ፣ እርቀትን መጠበቅ ወዘት ይይዛል።
- እጽዋት የአትክልት መናፈሻ ስፍራዎች (በታኒካ ጋርደን)፣ ሙዚያሞች፣ ታሪካዊ ቦታዎች እና ስፖርት
በተከታታይ ሰባት ቀን ከ 100,000 ነዋሪዎች መካከል አዳዲስ ኢንፌክሽኖች ከ100 በታች በሚሆኑባቸው ወረዳዎች፣ ሪጅኖች ውስጥ አስቀድሞ ቀጠሮ በመውሰድ ለዕለታዊ ፍጆታ ባልሆኑ ችርቻሮዎች፣ ጋለሪዎች፣ መካነ አራዊት ፓርኮች (ዙዎች)፣ የአትክልት ስፍራዎች እና ሙዚያሞች፣ ታሪካዊ ቦታዎች ለጎብኝዎች መክፈት ይችላሉ።
ከቤት ውጭ እስከ 14 ዓመት ዕድሜ ያላቸው እና እስከ አስር በማይበልጡ ሕፃናት/ታዳጊዎች የሚሰሩ ስፖርቶች ይፈቀዳሉ። በሰባት ቀናት ውስጥ ከ100,000 ነዋሪዎች መካከል ከ50 በታች አዳዲስ ኢንፌክሽኖች በተገኙባቸው ወረዳዎች እንደ ቴኒስ ያሉ ንኪኪ የሌላቸው ስፖርቶች ከቤት ውጭ እንደገና ይቻላል።
- ቀጣይ ውሳኔዎች
በውሳኔው መሠረት ቀጣዩ የመክፈቻ እርምጃዎች የሚሆኑት ለ 14 ቀናት ከ 100,000 ነዋሪዎች መካከል ከ50 በታች አዳዲስ ኢንፌክሽኖች በተገኙባቸው ወረዳዎች ከዝግ ቤት ውጭ በመናፈሻ ውስጥ ወይም በርንዳ ላይ የምግብ አቅርቦት፣ ሲኒማ ቤቶች፣ ቲያትሮች፣ ኮንሰርት እና ኦፔራ ቤቶች እንዲሁም ከቤት ውጭ ንክኪነት ያላቸው ስፖርቶች እና ከቤት ውስጥ ንኪኪነት የሌላቸው ስፖርቶች ይቻላል። ፈጣን የናሙና ምርመራ ማቅርብ የሚጠበቅባቸው ሁኔታዎችም አሉ።
- የተላለፉ ውሳኔዎች – ምግብ ቤቶች፣ የባህል ኢቨንት፣ የጉዞ ጉብኝት እና ከሆቴሎች መስኮች
እስካሁን ድረስ ያልተጠቀሱት እና በከባድ ሁኔት የተጎዱት ጋስትሮኖሚ ፣ የባህል ኢቨንት ፣ የጉዞ ጉብኝት እና የሆቴሎች መስኮች ጉዳይ በቀጣዩ የኮሮና ጉባኤ ላይ ይመከርባቸዋል።
- ክትባት
እስከዛሬ ወደ 4.6 ሚሊዮን ሰዎች አንድ ጊዜ ያህል ሲከተቡ 2.8 ሚሊዮን ሰዎች ደግመው ተከትበዋል። ይህም ዝግተኛ አካሄድ እንደተጠበቀው ሊፈጥን አልቻለም። ምክንያት ሆኖ የቀረበው የክትባት መጠን በተጠበቀው ብዛት አለመመረትን እና ደካማ አመራር ነወ። የጀርመን የጤና ሚኒስተር የንስ ስፋን በተፈጠረው ዝቅተኛ የኮሮና ክትባት ሂደት እና ተጓዳኝ ሁኔታዎች ከፍተኛ ተቃውሞ ሲቀርብባቸው የነበራቸው ተቀባይነትም ቀንሷል። በሌላ በኩል የኮሮናን ክትባት ያገኙት የባዮንቴክ መስራቾች የሆኑት ቱርክ-ጀርመናዊዎቹ ባልና ሚስት ከጀርመን ፕሬዚዳንት የሃገሪቱን ከፍተኛ የክብር መስቀል ኒሻን ተሸልመዋል።
የቤት ሀኪሞችም ከመጋቢት መጨረሻ ወይም ከሚያዚያ ጀምሮ ክትባቶች ማቅረብ አንደሚችሉ ተገልጿል።
ለሁሉም ዜጎች ነፃ የኮሮና ፈጣን ሙከራዎች ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ ይቻላል። የፌዴራል መንግሥት ወጪዎቹንም ይወስዳል፡፡ ለአንድ ሰው በሳምንት ቢያንስ አንድ ፈጣን የናሙና ሙከራ ይፈቀዳል።
ዕድሜያቸው በ18 ዓመት እና 65 ዓመት መካከል ያሉ ሰዎች ለወደፊቱ AstraZeneca እንደሚከተቡ ተገልጾ የነበር ቢሆንም አሁን እንደተገለጸው ከ65 ዓመት በላይ የሆኑትንም ይመለከታል። ቢሆንም ሰው AstraZeneca የመከተብ ፍላጎቱ ዝቅተኛ ነው። እንደሌሎች ክትባቶች ተደጋግሞ ሁለት ጊዜ ሳይሆን አንድ ጊዜ ብቻ የሚከተበው Johnson & Johnson በጀርመን ከመጋቢት ጀምሮ እንደሚፈቀድ ሲጠቀስ፣ ስፑትኒክ ቪ የተሰኘውን የራሽያን ክትባት የአውሮፓ ህብረት ለመፍቀድ እያጠናው ይገኛል።
የጀርመን ፓርላማ የኮሮና ክትባት ለማግኘት ሲሉ ያለተራቸው ክትባቱን በተለያየ ዘዴ እና ትውውቅ በመጠቀም የወሰዱትን በተለይም በታችኛው አስተዳደር ላይ የሚገኙ ፖለቲከኞችን ለመቅጣት እስከ 25,000 ዩሮ የቀረበውን ረቂቅ ደንብ ሳይቀበለው የመደበኛ የወንጀል ህግ የሚመለከተው ነው በማለት ዘግቶታል።
- ፈጣን የናሙና ምርመራ
ከመደሃኒት ቤቶች በመቀጠል በጀርመን እና በአውሮፓ አልዲ (Aldi) በመባል የሚታወቀው መሪ ሱፕርት ማርኬት ከቅዳሜ (06.03.2021) ጀምሮ ፈጣን የናሙና ምርመራ ለተጠቃሚዎች ሲያቀርቡ፣ ሮዝማን እና ሊድል የመሳሰሉት ችርቻሮችም ይከተላሉ።
የአንድ ፈጣን የናሙና ምርመራ ፓኬት ዋጋ 25 ዩሮ ሲሆን በአንድ ፓኬት ውስት 5 ሙከራዎች ሲኖሩ፣ በአንድ ግዢ ለአንድ ደንበኛ አንድ ፓኬት ብቻ ይፈቀዳል።
- ኢኮኖሚ
የጀርመን ኢኮኖሚ ከመጀመሪያው ዙር በተሻለ ሁኔታ ሁለተኛውን ወረርሽኝ የሚያስከትለው አደጋን ተቋቁሟል። ቢሆንም የሪስቶራንቶች፣ የሆቴል፣ የቱሪዝም እና የአየር ሴክተር በከፍተኛ ሁኔታ ተመተዋል። ሉፍታንዛ 6.7 ቢሊዮን ዩሮ ኪሳራ ደርሶበታል። ከኮሮና በፊት በነበርው አመት ብቻ የ1.2 ቢሊዮን ዩሮ ትርፍ ነበረው፣ እስከ 36 ሚሊዮን መንገደኞችም ተሳፍረዋል። 2020 አመትን ከ2019 ጋር ሲነፃፀር የተጓዦቹ መጠን 75 በመቶ ያነሰ ሲሆን 28,000 ሰራተኞችን ከስራ ቀንሷል። ቢሆንም በካርጎ 700 ሚሊዮን ዩሮ ትርፍ በዘመነ ኮሮና አግኝቷል። የመኪና ኢንዱስትሪ በመልካም ሁኔታ እያገገመ ይገኛል።
የኮሮና ክትባት እና የፈጣን ናሙና ተስፋ በመስጠቱ የአየር አንዱስትሪ፣ የሆቴል ሲክትር አክስየኖች በከፍተኛ ፍጥነት እየጨመሩ ይገኛል።
በአለፈው እንደገለጽኩት ኢትዮጵያ ውስጥ የሚታዩት ምስሎች እጅግ ግራ የሚያጋቡ እና የሚያስጨንቁ ናቸው። ኢትዮጵያ ውስጥ በቅርብ የምናውቃቸው ሰዎች እጅግ እንደሚታመሙ ስንሰማ፣ ቅርባችን የሆኑ ሰዎች፣ የታወቁ ሰዎች በዚህ ወረርሽኝ እና በተያያዘ መልኩ ህይወት ሲያልፍ ስንሰማ እጅግ ያሳዝነናል፣ ያስደንግጠናል። ስለኮሮና መከላከል ጤና ጥበቃ ሚንስተር ብቻውን የቀረም ያስመስላል። በምርጫ የሚወዳደሩ ፓርቲዎችም የፓርቲ ፕሮግራማቸው ወረርሽኙን እና በወረርሽኙ የሚከሰትውን ማህበርዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ለመወጣት ያዘጋጁትን የመከላከል እቅድ ማቅረብ አስፈላጊ ይመስለኛል። በዚህ በምርጫ ቅስቀሳ ወቅትም ይህንን ፕሮግራማቸውን ለህዝብ ማስተዋወቅ፣ ደጋፊዎቻቸው በሚያደርጉት ስብሰባ፣ ሰልፍ ላይ ማስክ የማድረግ እና ርቀት መጠበቅን ማስተማር እና መቆጣጠር ቀዳሚ መለኪያ ይመስለኛል። በተለይም ህዝብ በከፍተኛ ሁኔታ በሚሰበሰብባቸው ቦታዎች እጅግ ጥቂት ሰዎች ብቻ ማስክ አድርገው አብዛኛውን ግን ያለማስክ ማየትን የተለመዱ ምስሎችን መቀየር ይገባል።
መልካም 125ኛ የአድዋ ድል ማግስት!
ቸልተኛነትን በተግባር ከማየት የበለጠ የሚያስፈራ ነገር የለም።
– ዮሃን ዎልፍጋንግ ጎተ
ከመልካም የጤንነት ሰላምታ ጋር
ፀጋዬ ደግነህ (ዶ/ር)