ይድረስ ለልጀ ደባልቄ ቢተው    ( ዘ-ጌርሣም)

ክፍል አንድ

 

የሰማዩን  እርቀት የምድሩን ስፋት የባህሩን ጥልቀት ያህል ለጤናህ እንደ ምን ባጀህ።የሊቦው ጊወርጊስ የተመሰገነ ይሁንና አኔም ሆንኩ እናትህ ወይዘሮ ለሙሽ ማንያዘዋል፣ወንድሞችህ እንሙትና ይርጋ፤እህቶችህ ፍትፍቴና ዘርትሁን እንዲሁም እጎቶችህ ደብተራ ዋሴና መምህር መዝሙር፤ሌላውም ዘመድ ኣዝማዱ በሙሉ ደህና ነን።የንተ ናፍቆት ግን አኔን ጤና ነስቶ አናትህንም ክስት ጥቁር ኣድርጓታል።ወንድሞችህም ትዳር መስርተው ጨቅሎች ፍርተዋል፤እህትህ ፍትፍቴ ግን የብላታ ባይለየኝን ልጅ ዳምጤን  ልናጋባት ፍጥምጥም ተደርጎ፤ማጫውም ተወስኖ፤ቀን ተቆርጦ ድግሱ በመደገስ ላይ እንዳለ በውድቅት ሌሊት መንና ገዳም ገባችብን።እኛም የአባት እደሩን ካሣ ከፍለን ታረቅን። ዘርትሁን ግን ማለፊያ በለሴ የባለጠጋ ልጅ ግብታ ውባውብ ጉብሎች እድርሳልች፤ለእኔና ለእናትህም የዐይን ማረፊያ ሆነውናል።ምኞትና ጠሎታችንም ይህ ነበር።አንተም የአደባባይ ሰው ሆነህ ለምድረ ሊቦ ዋስ ጠበቃ ትሆናለህ ብለን ስንመኝህ የጧት ግንባርህ ሆነና ዳር ገር ጥለኽን ጠፋህ።

ልጀ ሆይ!

ለመሆኑ አንተስ ትዳር መሠረትክ፣ለፍሬስ በቅተህ ይሆን? መቸም የዘመኑ ልጆች የአባት አደሩን  ትታችሁ ሚስትም መራጮች እናንተው ሁናችኋል፣ይሁን እስቲ ዋናው ነገር የዘር ሐረጉ አለመቆረጡ አይደል! ወንድ ልጅ ወልደህ ክሆነ  የነገው ሰው ብየዋለሁ ሴት ከሆነችም የትና የት በላት።

አጎቶችህ ደብተራ ዋሴና መምህር መዝሙርም በትምህርታቸው እንዳንተው ትንኩሽት የሆኑ ልጆች አድርሰዋል።ማለፊያና ክፍት አንጎል አላቸው።ለነገሩማ ለአንተ እኮ ሊቀ ጠበብት ይባቤን ለልጀ አንጎሉን የሚከፍት ብሾ ያጠጡልኝ ብየ በጠየቅኋቸው መሠረት ስለኣጠጡህና ክማጅራትህ አከርካሪ ላይ በጥተው መድኃኒት ስለቀበሩልህ እንጅ እንኳንስ ፈረንጅ እገር ይፋግንም አትሻገር ነበር።

ሊቀ ጠበብት ይባቤ በአሁኑ ጊዜ የከምከምን ገበሬ ሞፈር አያሰቀሉ ናቸው፣ገበሬው በነቂስ በሬ ፈቷል፤አምርቶ ያቀና የነበረው ሸማች ሁኗል፤ግብርናውንም ተጠይፎታል፣በስማ ለው ተጠራርቶ  አስኳላ ትምህርት ቤት ይውላል።በአውራ አጣት ካርኒና ቀላጤ ላይ መፈረም ቀርቷል፣ድፍን ከምከሜ ስሙን ቆሎ አያስመሰለ መጣፍ ችሏል።ትምህርቱ ግን ከዚህ ያለፈ ያስገኘው ረብ(ፋይዳ) የለም።በንጉሡ ጊዜ አንኳን አስኳላ ትምህርት ቤት መማር ለጠቅላይ ገዥነት፣ለአውራጃ ገዥነት፣ለወረዳና ለምክትል ገዥነት ዝቅም ካለ ለአጥቢያ ዳኝነት ከወረደም የፈረሰኛ አለቃ ፣ጭቃ ሹምና የጎበዝ አለቅነት ያሾም ነበር፣ቦሊስና ያስኳላ መርጌታነትም ቢያንስ አይጠፋም ።ባሁኑ ዘመን ግን ተምረው ቢራቀቁም ጠብ የሚልላቸው የለም፣ከበዛም ክላሽ ታጣቂና ገበሬ እስጨናቂ  ከመሆን አይዘልም፣ውጤቱ ዋግ የበላው የጤፍ ቡቃያ ይነት ነው።

ውድ ልጀ ደባልቄ ሆይ!

ይኸውልህ ከከምከም ወጥተህ ፈረንጅ ገር የገባህበት ዘመን ቢቆጠር የሁለት ጥጃ ዕድሜ ሁኗል፣ላማችን ቀባሪ በየስድስት ዓመቱ ነው የምትወልደው፣ሁለት ወይፈኖች አድርሳለች፣አንግዲህ አንተ አገር ለቀህ የሄድክበት ጊዜ ቢቆጠር  በሁለት ወይፈን ሸርፍ አንድ ሙሉ በሬ ሁነሀል ማለት ነው።

እኔ አባትህ  የአባቴን ነፍስ ይማርና አብሾ አያጠጡኝ አንጅ በድፍን ከምከም ብቸኛ ሊቅ ነበርኩ፣ለጠሎት የሚነበበዉን ሁሉ በቃሌ ነበር የማነበንበው፣ችግሬ መጣፍ አልችልም ።ለነገሩማ የወረዳ ገዣችን የነበሩት ባላምባራስ አርምዴም  እንደ እኔ የጠሩ ጨዋ ነበሩ፣ጥሁፍ ከሆነ  የሁለታችንም ወዳጅ አውራ ጣት ነው፣ያም ሁኖ የሚሰጡት ብይን እንደ ጠገራ ብር የነጠረና ዝንፍ የማይል ነበር፣እረኛም በጊዜው “እርምዴ የፈረደው የእርብ ው የቀደደው ብሎ ዘፍኖላቸዋል” እናም አኔ አባትህ ድፍን ከምከም የተማረ አቅርብ ተብሎ ቢጠየቅ ከአኔ የሚያልፍ አይሆንም

ደባልቄ!

ለመሆኑ ክዚያ ከጀርመን አገር የሰው መስተዳድር አንዴት ይመስላል? በኢትዮጵያ ቋንቋስ ያወጋሉ? መብልና መጠጣቸውስ ምን ይመስላል? አስተራረሳቸውስ እንዴት ነው? የእህሉ ሸሬታስ፣ለመሆኑ ጤፍ ያመርታሉ?

ወደ ኢትዮጵያ አገር የሚመጡት ፈረንጆች  ግብጥ ወይም ጥሊያን ይሁኑ አይታወቅም ሁሉም ነጮች ናቸው፣ምድር ያፈራችዉን ሁሉ ይመገባሉ ማለትን ብሰማ ትንሽ በስጨት እልኩና ይ ደባልቄ ልጀ ይህን አይሠራም ብየ ከአናትህ ጋር አወጋን።አሁን አሁን የሚመጡት ነጮች ደግሞ ቁመታቸው ከችፍርግ ቁጥቋጦ የማይበልጥ፣ፊታቸው ጓጉንቸር የመሰሉና ሰባት ቀን አንዳልሞላው የውሻ ቡችላ ዓይኖቻቸው ያልተገለ፣የሰውነት ትክላቸውም እንደ ድግር በንድ መጥረቢያ የተጠረቡ የሚመስሉ፣ለምድር የቀረቡና ለሰማዩ የራቁ፣የሚመገቡትም ከርስ ምድር ያበቀለችውን ሁሉ ከይጠ መጎጥ ጀምረው የሀገራችን በግና ፍየል የተጠየፉትን ቅጠላ ቅጠል ሳይቀር ነው ይባላል፣ትላትሉም ለነሱ የደሮ ወጥና ዝግን ምትክ ነው ይላሉ፣አንዳንዶቹማ ከኢትዮጵ ሴቶች ጋርም  በመገናኘት ልጅ አስወልደዋል ይባላል።ድሮ ይመጡ የነበሩት ፈረንጆች ንደ ቅርቅሃና ባህር ዛፍ ጠምበለሎች ነበሩ፣መዋለዱ ግድ ከሆነ አይቀር እነሱ ሳይሻሉ አይቀርም ነበር፣አለዚያማ የሚወለደው ልጅ አንተ ጋፍ(ድንክ) አየተባለ ሲሰደብ ሊኖር  አይደል!

ተጨማሪ ያንብቡ:  ኦሮሙማ ሲገማና ሲገለማ   (ወይራው እርገጤ)

ውድ ልጀ ደባልቄ!

እኗኗራችንና ሁለንተናችን ሳያሳስብህ አይቀርም፣ነገር ዓለሙ ድብልቅልቅ ብሎብናል፡ነጣነት፣መሬት፣ቤትና ንብረት የድርቅ ቡቃያ ሆነዋል፣ያኔ በጨቅላነትህ የምታውቀው ሰፊዉ መሬታችንና የአርሻ ይዞታችን አንደ ሰንበቴ ዳቦ ተቆራርሶ የዳጉሣ አውድማ ያክል ቀርቷል፣ለከብቶች የግጦሽ ሣር፣የታቦትና የአስክሬን ማሳረፊያ፣ለሴቶች ውኃ መቅጃና ከብቶችን ውኃ ማጠጫ የሚባሉት ተረት ተረት ሆነዋል።የአርሻ መሬቱ ከልባምና ታታሪ ገበሬ ተነጥቆ ለቦለቲካ ደጋፊና ክላሽ ተሸካሚ የከተማ አውደልዳይ ተሰጥቷል፣ማረስ ካማረህ ተጠማኝና ሲሶ አራሽ መሆን ነው ፤በግና ፍየልም ከቤት ታስረው ነው የሚዉሉት እንጅ ማሰማሪያ ተራራና ሜዳም ጠፍቷል፣የሚቀጥለው የዶሮ ተራ ሳይሆን አይቀርም።

የኑሮ ውድነቱ አገር ጥላችሁ ጥፉ ያሰኛልጤፍ ፣ጥራጥሬ ፣ጎመንና ሁሉም ለምግብነት የሚያገልግሉ ቁሶች ሸሬታቸውን ሲጠሩት ለጆሮ ይከብዳል።የጓሮ እሸትና የሽምብራው ማሳ የጫት ማብቀያ ሁኗል”ሳይደግስ አይጣላም “ይሏል ይህን ነው።ይህ ጫት የሚባል ነገር ደግሞ የሰራ አከላትን አደንዝዞ ፣የረኃብ ወስፋትን ገሎ ወተቴ እንደያዘው ከብት አደንዝዞ ሲያነኋልል የሚያውል ዕፅ ነው፣አንዳንዶቹማ በጫቱ አንጎላቸውን ሲስቱ አንደ ጠንቋይም መሆን አየከጀላቸው ዝበ አዳሙን በማታለል፣ትዳር ሳይቀር እያፋቱ ይገኛሉ።በአብዛኛው ጫት ሲያመነዥጉ የሚታዩት የምግብ ፍላጎታቸውን ለመግደል ነው የሚሉም አሉ።በቅርቡ አዲስ አበባ አንድ በየቀኑ እራሱን በጫት እያነሆለለ አውቅላችኋሁ በማለት ብዙ ጥሪት ካፈራ ብኋላ በሕዝብ ጥቆማ በቦሊስ ተይዞ ለፍርድ በመቅረብ ዓለም በቃኝ ዘብጥያ ወረደ አሉኝ።በዚህ መርዘኛ ጫት ሰበብ በየቀኑ አያሌ ወንጀል እየተፈጠመ አገሩም ታውኳል፣መንግስትቤተክርስቲያንና መስጊድም ጆሮ ዳባ ልበስ ያሉ ይመስላል።

በድሮውና ደጉ ዘመን በግና ፍየል ተገዝቶ ከአንጋሬ መልስ ሥጋ በነጣ የነበረው ዛሬ የፍየልና በግ ዋጋ የአንድ የእርሻ በሬ መግዣ ያክል ሲሆን ዶሮም ፍየልና በግ ሁናለች።

የካሚዎን መንገድ በየደብሩ ተሠርቷል፣አህያና አጋስስን ያሳረፈ ቢመስልም ነዋሪዉን ግን ረድዔት አሳጥቶታል፣በየመንደሩና ደብሩ የተገኘውን ምርት አሟጦ ወደከተማ ይጭነዋል፣ሞኙ ባላገርም ጥሩ ሸሬታ ያገኘሁ መስሎት ለዘር ያስቀመጠውን ሳይቀር ጎተራውን አሟጦ በማቅናት ለካሚዎን ሲሳይ ያደርገዋል፣ክረምቱና የዘር ወቅት ሲመጣ  ደግሞ ሁሉም ለማኝና አራጣ ተበዳሪ ይሆናል፣ያልቀናውም ለሽቀላ ሥራ ከተማ ይሰደዳል።መተዛዘን የሚሉት ነገር ጠፍቶ መነቻቸፍ ሁኗል፣የከምክም ዉሾች እንኳን ለቆሎ ተማሪ ያዝኑ ነበር።

በመሬቱ ጥበት ምክንያት ገበሬው ጥማዱን፡ባል ሚስቱን ሚስትም ባሏን እየፈቱ ወደክተማ የሚፈልሱት ስፍር ቁጥር የለውም “ያላወቁት አገር ይናፍቃል”ሆነና ከዚያ ሲደርሱ ደግሞ በየጥርጊያ መንገዱ እንደ ፎግራ ክብቶች ተኮልኩለው ያድራሉ፣ኪስ አውላቂውም ጭንቅ ነው ይባላል፣የሚላስና የሚቀመስ የሚገኘው በአሳር ነው፣መጠጊያ ቤት ለመከራየት ህልም ነው፣መሬት እንደ ባሶንዳ ገበያ አቡጀዲ በክንድ ተለክቶ ስለሚሽጥ ተመኑም  አያሌ ነው፣ለዚያዉም ቤት ልስራ እንኳን ብትል ንብረትህ ዛኒጋባዋ ብቻ እንጅ ቤቱ የቆመበት ምሬት ያንተ አይሆንም፣ለዘጠና ዘጠ ዓመት ተጠማኝ የመሆን መብት ግን አለህ ይላሉ፣ስትሞትም ለምትቀበርበት ጉድጓድ ከፍለህ ነው።ይህ እንግዲህ በስማ በለውና በነጋሪት ጋዜጣ ተፈጥሞ  የተነገረ የመንግስት ቃል ነው፣ይሁን እንጅ  ሀብትና ንብረቱ በአዋጅ የታገደበት ሁሉ አፈርኩ ያለ ይመስላል፣ጀንበር ስትጠልቅም አየተጠራራ ይዶልታል፣በጠሃይማ ፊርማቶሪው እየጠቆመ ዓለም በቃኝ ያስዶለዋል፣ፊርማቶሪውም እንደ ክረምት አሸን ፈልቷል፣ሁሉም አፉን የተለጎመ ፈረስ  ይመስላል፣ የጎሪጥ መተያየት አንጅ በግልጥ ማውጋት አይደፍርም።የበለሳና መልዛ ጫካ ቢመነጠርም ቀሪዉ ቁጥቋጦና ተራራው ሆድ ለባሰው መደበቂያና መሸፈቻ መሆናቸው አይቀሬ ነው፣ባላገሩም በርዕስቱ መሸንሸን ጭስ እንደገባበት የንብ ቀፎ እምምም  አያለ በማጉረምረም ላይ ይገኛል።ጥንትም እኮ እንዲህ ይባል ነበር፥

ባላገር ካፈረ በሬውን ከፈታ

ጅረቱ  ከቆመ በቦይ ከተገታ

ጊዜ ነው ወሳኙ ማን አንደሚረታ

በዚህ ዋጅ አያሌ ሕዝብ ተጎድቷል ይባላል፣በተለይ እንዳንተ ባህር ማዶ ተቀማጭ የሆኑትን ግምኛ አካስሯቸዋል አሉ፣የኢትዮጵያን ገንዝብ አየር ባየር ሸርፈው  አያሌ ሀብት ካፈሩ ብኋላ በርካታ ቤቶችን ሰርተው ስለነበር ደላላና ወኪል ብዙ አጣፍቷቸዋል፣ ለኑሮውም መወደድ ሰበብ የሆኑት እነሱ ነበሩ፣ድኃውማ ሁሌም  መናጢ ድኃ ነው።ያሁኖቹ ገዝዎች በሁሉም ላይ ጨክነዋል፣ከመጠን ያለፈ ጥጋብና መፎርሸትም ይታይባቸዋል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደተለመደው ይወርፏቸዋል፤ እንደራሴዎቹ ግን በሳቅ ያጅቧቸዋል - ከመርሐጽድቅ መኮንን አባይነህ

መቸም የመሬት ችግርን ከአንሳሁልህ አይቀር  በአኛ ላይ ከደረሰውም የከፋ በጠቅላላው አገርህና በወገኖችህ ላይ ብዙ መከራና የቸገረ ነገር እየተፈመ ነው፣ነገሩ”እናቱ የሞተችበትና ውኃ ልትቀዳ የሄድችበት እኩል ያለቅሳሉ”ዓይነት እንጅ የእኛስ መሬት ቢጠብና ቢሸነሸን የተካፈለው ያገሬው ሰው ነው፣አገሬውም  በጋብቻና በአበልዥነት ስለሚተሳሰር ዙሮ ዙሮ አብሮ መጠቃቀሙ አይቀርም፣ ሁሉም ከእጅ ወደ አፍ ኑሮ አያልፍም አንጅ።በሌሎች ጠቅላይ ግዛቶች ግን ክዚህ የከፋ ነው፣መሬቱ ከገበሬውና ከዘላኑ እየተነጠቀ ከዳር አገር ለመጡ ህዝቦች ፓኪስታን፣ሕንድ፣ዐረብ፣ጥሊያን እና ለሌሎች ፈረንጆች ለእያንዳንዳቸው ከአንድ ደብር  አገር ስፋት የሚልቅ መሬት በዝቅተኛ ሸሬታ እየተተመነ እየተሰጣቸው ነው።የአገሬውም ሰው “ባይሆን ለእኔም የገንፎ እንጨት አልሱኝ” እንደተባለው ያለውን ሽጦና አራጣ ተበድሮ እኔም ባይሆን የገንዛ መሬቴን እንድገዛ ይፈቀድልኝ ሲል ሰሚ ጆሮና ፈቃጅ ኃይል አያገኝም፣የመጨረሻ ምርጫውም ቀየውን ያለ ውዴታው እየለቀቀ እግሩ ወደ መራው መሰደድ ነው።ይህ ችግር ከፍቶ የሚታየው በወሎ፣በሸዋ  በሐረር፣በባሌ፣በሲዳሞ፣በገሙጎፋ፣በጅማ፣በኤሉባቦር፣በጋምቤላ፣በወለጋ፣በጎጃም፣በጎንደርና በአፋር አካባቢዎች ሲሆን በተለይ ጎንደርንማ ከውስጥም ከውጭም እንደ ቋንጣ እየለዘሉት ይገኛሉ፣አንተና ጓደኞችህም መሬት ለአራሹ ይሰጥ ብላችሁ ፍዳ ስታዩበት የነበረውና የከፈችሁት ምስዋዕትት ሁሉ አንዲህ ውኃ በልቶት ቀረ ።ወይ ነዶ ዛሬማ ወንድ ነኝ የሚል ሽፍታም ጠፍቷል፣ድሮ እንኳን አንድ ጀግና  አመረርኩ ብሎ ሸፍቶ  ጫካ ሲገባ ተከታዩ እየበዛ ብዙ ጀግኖችን ያፈራ ነበር፣ያ ለራሱም ያልሆነ ደርግ የሚሉት ጉግ ማንጉግ መንግሥት የኢትዮጵያን ህዝብ እንደባብ  አራስ አራሱን ቀጥቅጦ ሐሞተ ቢስ አርጎት ሄደ፣እኔ የአንተ አባት እርጅና ባይጫነኝ ኑሮ ተከታይም አላጣ ነበር ፣ይህን የአሁኑን አውሬ መንግስት ነኝ ተብየ ጉድ አፈላበት ነበር፣ምን ያድርግ “እንኳን መሞት አለ ማርጀት ” ተብሎ የለ! ይኽውልህ አንድ አንደኔ የተክፋ ባላገር እንዲህ ብሎ አቅራራ፣

ወይ ነዶ ወይ ነዶ ወይ ነዶ መሞት

እንደ ሻማ ቀልጦ ጭሶ እንደ ኩበት

ልጀ ደባልቄ!

ተወኝ እባክህ ልጀ የቱን ጀምሬ የቱን እጨርስልሀለሁ፣ሌላም አንገት አስደፊ ጉዳይ አጋጥሞናል፣በድሮው ዘመን ለትምህርት፣ለደጅ ጥናትና ለእንጀራ ፍጋ በአመዛኙ ቀየውን ለቆ የሚሰደደው ወንዱ ነበር፣ጥሪት አፍርቶ ወደ ትውልድ ሀገሩም አየተመለሰ ተጋግዞ መኖር የተለመደ ባህል ሆኖ ቆይቷል።በአሁኑ ጊዜ ደግሞ የተገላቢጦሽ ሆኗል፣ለአቅመ ዓዳም ያልደረሱ ልጃገረድ ጉብሎች ሳይቀር ለግርድና ሥራ ወደ ዐረብ አገሮች በደላላ እየተጭበረበሩ ተወልደው ያደጉበትን አገርና ወላጆቻቸውን እየተው ለአሰቃቂ አደጋዎችና ለሞት አየተጋለጡ ያሉበት ዘመን ደርሰናል።ሠርቶ መብላቱ ነውር ባይሆንም በነዚህ እምጉብሎች ሕይወት ላይ ኢሰብዓዊ ግፍ እንደሚፈፀምባቸው አያሌ ሰዎች በሀዘኔታ ይተርኩታል፣ለደላላው የሚከፍሉት መጠንም ከአቅማቸው በላይ ስለመሆ በይፋ ይነገራል”ወረቱ ስንቁ ልቁ “አንዲሉ! ደላላዎቹም ከመንግሥት ፈቃድ የተሰጣቸው ስለመሆናቸው በአደባባይ ይወጋል።ለግርድና ሙያ የሚቀጥራቸው ዐረባዊ ቤተሰብም አነዚህን ለሀገራችን ተስፋ ሊሆኑ ይችሉ የነበሩ ታዳጊ ጉብል ልጃገረዶች የተፈጥሮ የፀሐይ ሙቀትን እንኳን ለመሞቅ እንዲችሉ ፈቃድ አይሰጧቸውም ይባላል፣ጀንበር ወጥታ ተመልሳ እስከምትጠልቅ ድረስ ከአንዱ ቤት ወደ ሌላው እየተዘዋወሩ በሥራ ሲባዝኑ ነው የሚውሉት።እነዚህ ታዳጊ ወጣት ሴቶች በዚህም ይብቃችሁ አልተባሉም፣ፈጣሪ  ለኢትዮጵያ ሴቶች ያደላቸው የተፈጥሮ ውበት ተደራቢ ጠላት ሁኗቸዋል፣ቀጣሪዎቹ ዐረባዊ እመቤቶች ባሌን ቀና ብለሽ አየሽ ወይም ፈልጎሽ ይሆናል በሚል እርኩስና ሰይጣናዊ  ዕኩይ ስሜት በመገፋፋት በወጣቶቹ  ላይ የሚያደርሱባቸው ያአካልና የአዕምሮ ጉዳት እጅግ ዘግናኝ ስለመሆኑ በየገበያው ህዝቡ በአርምሞ ሲያወጋው መስማት ለህሊና  ዕረፍት የሚነሳ ጭንቀት ፈጥሮብናል።መከራው በዚህም ይብቃ አላላቸውም ፣በሚደርስባቸው የአካልና የአዕምሮ  ጉዳት ምክንያት ለሞት የበቁና የአልጋ ቁራኛ ሁነው የቀሩ ቁጥራቸው በርካታ ነው።ከመንግስት ዕውቅናና ፈቃድ ተሰጥቷቸው በውጣቶቹ  ላይ ይህን ሁሉ መከራና ግፍ የሚያደርሱት ስግብግብና ሆዳም ነጋዴዎችና የመንግስት ተቀጣሪ ሰራተኞች ናቸው። ለዜጎች መብት የሚቆረቆር ህግ ቢኖር ኖሮ ለፍርድ ሊቀረቡ በተገባ ነበር፤ለማን አቤት ይባላል?_ “ባላገር ተበድሎ ማሩኝ ይላል ዙሮ” የተባለው ዓይነት ሆነ።በኢትዮጵያ ወጣት ሴቶች ላይ እየተፈፀመ ያለው ግፍ የባሪያ ሽያጭ ዘመን ተብሎ ከሚታወሰው ጊዜ የከፋ ሁኗል፣በነዚህ ወጣት ጉብሎች ጉልበት ደላላው የባለ ትልልቅ ፎቅ ቤቶች ባለቤት ለመሆን በቅቷል፣ገንዘቡን ከየት አመጣኽው ብሎ የሚጠይቀውም የለም፣የጥቅሙ ተካፋይ ከላይ እስክ ታች ያለው የስልጣን ተዋረድ ነው ይባላል።ከቶ ይህ ቀን ያልፍ ይሆን? ለዚህም ነበር አንዷ አንዲህ  ብላ ያንጎራጎረችው

ተጨማሪ ያንብቡ:  እየተደረገ ያለዉን በዘርኝነት ላይ የተመሠረተ የጥፋት ቃለ መሃላ ማክሸፍ የእያንዳንዱ እትዮጵያዊ ነኝ ባይ ሁሉ ግዴታ ነው ፤

ያልፍልኛል ብየ አረብ አገር ሂጀ

መጣሁ ተመልሸ እንደ በግ ታርጀ

ኢትዮጵያዊነቴን ክብሬን አዋርጀ

አዲስ አበባ የሚመላለሱ ሲራራ ነጋዴዎችና በይግባኝ ሙግት ምክኛት የሚንገላቱ ያገርህ ስዎች እንዳወጉኝ ወደ ዳር አገር ለሚሄዱና ከዚያም ለሚመለሱ የኬላ ማለፊያ ወረቀት (እናንተ ቢዛ ነው አሉ የምትሉት) ለማውጣት እንደ አርበኛ ዘማች ተሰልፈው የሚውሉና የሚያድሩ ዕድሜያቸው በአሥርና ሃያ ዓመት መካከል የሚካተቱ እምቡጥ አበባ የሚመስሉ ልጃገረዶች አብዛኞቹ የዐረቡን አገር አለባበስ በቅድሚያ ተለማመዱ የተበሉ ይመስላል ግማሽ ፊታቸውን ሽፍነው ዙሪያ ጥምጥም ሰልፍ ላይ ቁመው ሲታዩ አንጀትን ይበ አሉ፣ለማጋነንም አይደለም በግምት አስከ አምስትና ስድስት ዙሪያ ጥምጥም የቆሙበት ሰልፍ ተዘርግቶ በመጫኛ ቢለካ ከግማሽ በላይ  የሚደርሰዉን የአዲስ አበባ ወብ ርዝመት ሳይሸፍን አይቀርም።ይህ አንግዲህ የአንድ ቀን ክስተት ሳይሆን በየቀኑ የሚታይ ትይንት ነው።ከወጭ የኬላ መውጫ ፈቃድ ጠያቂው ባሻገር ቢያንስ በየቀኑ ከአሥር የማያንሱ አስከሬኖች በአወሮብላን አንደሚገቡ ምስጢር አዋቂዎች አበክረው ይናገራሉ።መቸም ጆሮ አይሰማው የለም አንዳንዶቹማ በቁማቸው እንደ አገርህ ዱር በእሣት እየተለበለቡና እንደ ዶሮ በፈላ ውኃ እየነፈሩ የተገደሉም አሉ ነው የሚባለው።አይ እርጅና አገሬና ወገኖቸ  እንዲህ ተዋርደው ልይ! በቁሙ የሞተ አለ ቢባል እኮ እኔ ነኝ።ለመሆኑ አንተ ከምትኖርበት አገር ያሉ ፈረንጆች ስለእኛ ምን ያወጋሉ፣መቸም መሳቂያና መሳለቂያ አንዳደረጉን ነው የምገምተው።

አየህ ደባልቄ

አንተ ያኔ አልተወለድክም አንጅ የምትኖርባቸው ጀርመኖች በሁለተኛው ዓለም ጦርነት ጅልኛ ስለተጎዱ ብዙ ሰውም አልቆባቸው ነበርና  ከጦርነቱ በኋላ አገራቸውን መልሶ ለማቋቋም እርካሽ የሰው ጉልበት ስላስፈለጋቸው የኛውን ንጉስ አጤ ኃይለ ሥላሴን  የርስዎን ሰዎች  ይስጡንና ክእኛ ሀገር ሂደው እኛንም ይረዱናል እኛም አስተምረን እራሳቸውን እንዲረዱ እናስችላቸዋለን ቢሏቸው ወገኖቻቸው የሚዋረዱባቸው መስሏቸው አይሆንም ለባርነት የማቀርበው ሕዝብ የለኝም አሏቸው ይባላል፣ያኔ ተስማምተው ቢሆን ኖሮ እኔም አፍላ ኮበሌ  ስለነበርኩ አንዱ እሆን ነበር።ያኔ ንጉሱ አይሆንም ያሉትም የህዝባቸውን መማር ጠልተው ሳይሆን እንደውርደት ስለቆጠሩትና ለሃይማኖታቸውም ቀናዒ ስለነበሩ ህዝቦቸ የፈረንጅ ሃይማኖት ተከታይ ይሆኑብኛል በሚል ወገናዊና አባታዊ መቆርቆርና ስጋት ነው።ጥሩና ተወዳጅ የሀገር መሪ መሆን ማለት ለባንዲራው ለህዝቦቹ ነፃነትና ክብር ተቆርቋሪ ሲሆን ነው፣ወርዳ ገዣችን የነበሩት ባላምባራስ አርምዴ እንኳን ባቅማቸው አንድ ሽፍታ ተነስቶ የባላገሩን ቤት እያቃጠለ ዝርፊያ ሲፈጥም  የማስተዳድረው ህዝቤና ወገኔ ተደፈረብኝ በማለት ክተት አዋጅ ተክተለኝ እያሉ በመዝመት ሽፍታዉን ካልገደሉ ወይም ከነነፍሱ ካልያዙ ዕረፍት አያገኙም ነበር፣የአባት አደሩና መልካም አስተዳደር ማለት ይህ ነበር፣እናማ ዛሬ ነበር ማለት ብቻ ሆነ።

ውድ ልጀ ሆይ

 ብዙ በሆዴ ውስጥ ያለ የማወጋህ ነበረኝ፣ያገሩ ዕርቀት ግን ገደበኝ፣አሁንም የቻልክ እንደሁ ክረምቱ ጨክኖ ሳይገባና እርብም እንደልማዱ ሞልቶ አላሻግርም ሳይል መጥተህ ዓይንህን አይተንህ ተመለስ።መቸም ያንተ ነገር ባዶ እጀን አልሄድም ብለህ እንደምታስብ ስለማውቅ እኛ የሊቦው ጊርጊስ የተመሰገነ ይሁንና ምንም የምንፈልገውና የጎደለብን የለም፣አንተም በየጊዜው ስለላክልን ሙሉ ጌቶች ነን፣የተሰየነው ዓይንህን ለማየት ብቻ ነውና ከቻልክ የእርሻው ሥራ ሳይጫነን በግንቦትና ሰኔው አካባቢ ለአጭርም ጊዜ ቢሆን አይተኽን ተመለስ፣ እናም ከእንግዲህ  አኔንም ሆነ እናትህን እርጅናው እየተጋፋን ነው፣መንገዳችን እኮ ከአሁን ወዲያ ቁልቁለት ነው ።በተመቸህ ጊዜም አምቦ ሜዳ ድረስ በቀጠሮ አስጠርትህ በስልኪ ድምጥህን ብንሰማ ደስ ይለናል፣በተለይ አናትህ በናፍቅትህ ተሰይታለች፣እስከምትመጣ ድረሰም አደራ ጣፍልን።

የአያት ቅድመ አያቶችህ አምላክ ጢናና ዕድሜ ሰጥቶ በሰላም ወደ ሀገርህ ይመልሰህ።

 

አባትህ  ባላምባራስ ቢተው አደፍርስ

አናትህ ወይዘሮ  አለሙሽ ማንያዘዋል

ቸር ይግጠመን

                                               ————–  ይቀጥላል 

1 Comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share