ነሐሴ ፳፪ ቀን ፳፻፲፰ ዓ. ም. (8/28/2026)
እስከ መቼ ሕዝብ የመንግሥት አገልጋይ ሆኖ፤ የመጣ የሄደው ሹም የፈለገውን ሲያደርግበት ይኖራል!
መንግሥት የተቋቋመውና ዋና ዓላማው፤ በሕዝቡ ፈቃድና ሕዝቡን ማገልገል ነው። ይህ የሚገለበጥበትና በሥልጣን ላይ የተቀመጠ ቡድን ሕዝቡን እንዳሻው የሚያንገላታው፤ አምባገነኖች ሥልጣኑን በሚጨብጡበት ወቅት ነው። በኢትዮጵያ ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ የነገሠው ይሄ የአምባገነን ስርዓት ነው። አምባገነኖች መጨረሻቸው አይምርም፤ ያንን ግን ሲወድቁ ብቻ ነው የሚረዱት። ዘለዓለማዊ የሚመስላቸው የነሱ ንግሥና፤ ከእግራቸው ሥር ተቦርቦሮ መቆሚያ ሲያሳጣቸው፤ ኧረ! ብለው የሚነቁት የመሪያቸው አንገት በመስቀያው ሲገባ አለያም ደረታቸው ላይ ጥይት ሲያርፍ ነው። በዚያ ወቅት፤ እነሱ ብቻ ሳይሆኑ፤ ሕዝቡ ተደራጅቶ ካልተገኘ፤ ለቀጣይ አረመኔ አምባገነን መዳረግ ነው።
ሕዝቡ ተደራጅቶ፣ የሚሄደውን የሚተካ አዘጋጅቶ ባለመገኘቱ፤ የካቲት 66 መጣ፣ በመንግሥቱ ኃይለማርያም ደርግ ሥልጣኑን ተነጥቆ፣ የቀይ ሽብር ሬሳ ባደባባይ ሲጣል እየተመለከተ፤ ተሸማቆ ተቀመጠ። ደርግ በውስጥና በውጪ ተፈረካክሶ፣ ራሱን የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባር ብሎ የሚጠራ ጠባብ ዘረኛ ቡድን መጥቶ፤ ሕዝቡን በቋንቋና በአካባቢ የበረት አጥር ከፋፍሎ፣ ኢትዮጵያን የሚበታትን የፖለቲካ ፍልስፍናና የአስተዳደር መመሪያ አስቀምጦ፣ ይሄንም በሕገ መንግሥት ደንግጎ ሕዝቡን ሲያባላ፤ አሁንም አንገቱን ደፍቶ ተቀመጠ። እስከመቼ? ተረኞች ነን! ባዮች ተከተሉና፣ በሕዝቡ አመፅ የተሰናበተውን የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ነኝ ባይ ሹም ግለሰቦችን፤ ትግሬዎችን በኦሮሞዎች በመተካት፤ እንዳለ ስርዓቱን ወርሶ ሲገፋ፤ አሁንም ሕዝቡ ዝም ብሎ ተቀመጠ። ይባስ ብሎ ኢትዮጵያን ለማጥፋት ዐማራን ማጥፋት አለብኝ! ብሎ በዐማራ ላይ ሲዘምት፤ ዐማራ አምርሮ፣ ግፉ በዛ! ብሎ ትጥቅ ሲያነሳ፤ አዲስ አበባም ሆነ ሌላ ቦታ ያለው፤ የህልውና ጉዳዩ በራሱ ላይ ቢያንጃብብም፣ ዝም ብሎ ተቀመጠ! እስከመቼ!
ጊዜ ማንንም አይጠብቅም!
የኢትዮጵያዊያን ኑሮ ከዕለት ዕለት እየከፋ ነው። የኢትዮጵያ ወጣቶች በየዕለቱ ከያለበት እያጋፈፉ ለጦርነታቸው ማገዶ እየዳረጉት ነው። ይህ ጦርነት፤ አላስፈላጊና ለነሱ ፍላጎት ማስፈጸሚያ የተጀመረና የተገፋ የቅንጦት ጦርነት ነው። የስርዓቱ አሳላጭ ሹማምንቶች የሚችሉትን ያህል የአገራችንን ሀብት እየዘረፉ ነው። ይህ የጉቦውን እና ቀጥታ ከሕዝቡ በየምክኛቱ የሚዘርፉትን አይጨምርም። ስርዓቱ ዐማራን ከምድረ ገጽ ለማጥፋት ሙጭጭ ብሎ በደንታ ቢስነት ግፍና መከራውን እያወረደ ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ ከሥሩ እየለቀቀው ባዶውን እየቀረ ነው። እንዴት የአገርን ዋና ከተማ፤ ለአንድ ነገድ የብቻ መጠቀሚያ ብሎ ይነሳል? እንዴት የምክክር ኮሚሽን ብሎ ተቃዋሚዎቹን ያገላል? እንዴት የሱን አክራሪ ኦሮሞች እንደልባቸው እንዲፈነጩ የመንግሥቱን መዋቅርና ሀበት ያሸክማቸዋል? በምን ሂሳብ ይህ የአገር መሪ ይባላል? ይህ ስርዓት እንዳበቃለት የማያውቅ የለም። ታዲያ የምንጠብቀው ምንድን ነው! በቁንጮው ላይ የተቀመጡት መውጫቸውን እያዘጋጁ ነው። መዝረፍ የሚችሉትን ገንዘብ ሰባስበው ወደ ውጪ ልከዋል። የኢትዮጵያን ወጣት፣ እንደማይቆዩ አውቀውታል።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ!
በያለህበት ተደራጅ! ሶስትም አምስትም ሆነህ ተነጋገር! በየመንደርህ ተመካከር! በየመሥሪያ ቤትህ ሃሳብ ተለዋወጥ! ነገ አገር ፍርሻ ሆኖ፣ ዘራፊ ቤትህ ውስጥ ገብቶ፣ ንብረትህን ሲወርስና ቤትህን ሲደፍር፣ እስካልተቧደንክ ድረስ፤ መጫወቻ ነህ! ይሄ ስርዓት ሲወድቅ፣ በቁንጮ ላይ ያሉት አገር ለቀው ይሄዳሉ። ጀነራል ተብየዎቹ፤ የሚችሉትን አስባስበው ዘረፋ ይገባሉ። ዝቅተኛ ሹማምንቱ የመንደር ሹም ሆነው ዘረፋውን ያባብሱታል። አንቺ የት ነሽ! አንተስ ማን አለህ! የሚቀጥለው ሰላም የሚያመጣ፣ አገር የሚገነባ እንዲሆን ከፈለግህ፤ ተደራጅና አለሁ በል! በግልህ አትድንም! የፈለገ ገንዘብ ቢኖርህ፣ የፈለገ መሳሪያ ብታነግት፤ አንድ ሰው አንድ ነው። በያለህበት፤ ዘመዶችህን አሰባስበህ ሆነ መንደርተኞችህን መክረህ፤ ራሳችሁን ጠብቁ። አሁን ህልውናን መጥዕበቂያ ሰዓት ነው። በየመሥሪያ ቤቱ አድማ ምታ! በየጦር ግንባሩ መኮንኖችህን እሰር! በየትምህርት ተቋሙ ምክር ያዝ! ነገን ቁጭ ብለህ በመጠበቅ የተሻለ እንዲሆንሉ አታደርገውም። ዛሬ ስትዘጋጅ የነገ ባለቤት ትሆናለህ። እስከመቼ የመጣ የሄደው ይጫወትብሃል! እስከመቼ!