ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)
ነሐሴ 28፣ 2018(September 03, 2026)
በአገራችንና በተቀሩት የአፍሪካ አገሮች ያለው ትልቁ ችግር ፖለቲካ የሚባለውን ፅንሰ-ሃሳብ ህብረተሰብአዊ ፕሮጀክትን ተግባራዊ ማድረጊያመሆኑን አለመረዳቱና፣ ከተለያዩ ለአንድ አገር ግንባታ ከሚያስፈልጉ፣ አንድን ህዝብ እንደማህበረሰብ ሊያይዙት ከሚችሉት ዕውቀቶች ጋር በጥብቅ የተያያዘ መሆኑን አለመረዳቱ ላይ ነው። ዕውቀትም ሲባል በሳይንስ ላይ የተመሰረተና በተግባርም ሲተረጎም የአንድን አገር ህዝብ ችግር ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ በመፍታት እያንዳንዱ ዜጋ ዕውነተኛ ነፃነት እንዲሰማው የሚያደርግ መሆን አለበት። ስለሆነም ፖለቲካ ማለት አንድን አገር በተሟላ መንገድ መገንባትና ታሪክ ሰርቶ ለተከታታዩ ትውልድ ማስተላለፍ የሚያስችል መሆን አለበት። በተለያዩ የአፍሪካ አገሮች መሪዎችና አገዛዞች ዘንድ ያለው ትልቁ ችግር፣ የአገራችንንም አገዛዞች ጨምሮ ፖለቲካ የሚባለው ፅንስ-ሃሳብ ሳይንስ መሆኑንና ከተለያዩ ዕውቀቶች ጋር በመያያዝ አንድን አገር በተሟላና ጥበባዊ በሆነ መልክ መገንቢያ መሳሪያ መሆኑን ለመገንዘብ አለመቻል ነው። የአብዛኛዎቹ የአፍሪካ አገሮች መሪዎች ሌላው ችግር ደግሞ በምን ዐይነት ፍልስፍና እንደሚመሩ አለማወቃቸው ነው። በተጨማሪም ቀኞች ይሁኑ ግራዎች፣ ወይም ሌላ ዐይነት ራዕይ ይኑራቸው አይኑራቸው በፍጹም የሚያውቁት ነገር የለም። ፖለቲካ የሚባለውን ነገር በጭፍኑ ነው የሚያካሂዲት ማለት ይቻላል። ከፖለቲካ ውጭ ባሉ ምሁራን ነን ባዮችም ዘንድ ይህ ለአንድ አገር እጅግ አስፈላጊ የሆነው ጥያቄ በመነሳት መሪዎችን ሲያፋጥጥና ለማስተማር ሲሞከርም በፍጹም አይታይም። ሰለሆነም አብዛኛዎች የአፍሪካ አገራት መሪዎች የአገራችንንም ጨምሮ ስለ አገር፣ ስለሰው ልጅና ስለ ህብረተሰብ ያላቸው አስተሳሰብ አልቦ ነው ማለት ይቻላል። ምንም ዐይነት ፍልስፍናና ሳይንሳዊ ዕውቀት የሌለው አገዛዝ ደግሞ በቀላሉ ኤክስፐርቶች ነን በሚሉ ከውጭ እየተንጋጉ በሚመጡም ዓለም አቀፋዊ ድርጅቶችና ግለሰቦች በቀላሉ ሊታለል ይችላል።
ከዚህ ሁኔታ ስንነሳ አብዛኛዎቹ የተለያዩ የአፍሪካ አገሮች መሪዎችና አገዛዞች፣ እንዲሁም በተለይም ኢትዮጵያን 27 ዓመታት ያህል የገዛው ህወሃትና፣ እሱን የተካው የአቢይ አህመድ አገዛዝ ፖለቲካን የሚረዱት አገርን መገንቢያ መሳሪያ ሳይሆን ስልጣን ላይ ብቻ ቁጥጥ በማለትና በሚሊተሪና በፀጥታ ኃይሎች በመታጀብ አገርን መበዝበዢያ መሳሪያ አድርገው ነው የሚቆጥሩት። በተጨማሪም የውጭ ኃይሎች ታዛዥ በመሆን የእርስ በርስ ጦርነት ማካሄጃ ያደርጉታል። ባጭሩ ፖለቲካ የሚባለውን ቅዱሱንና ሳይንሳዊውን ፅንሰ-ሃሳብ ወደ ተራ የተንኮል መሳሪያ በመለወጥ የእነሱን ሰይጣናዊ አስተሳሰብና ድርጊት የሚቃወመውን ሁሉ ማስወገጂያ መሳሪያ አድርገው ነው የሚተረጉሙት። በዚህም ምክንያት የተነሳ ቁጥራቸው የማይታወቅ የፖለቲካ አክቲቪስቶች ህይወታቸውን እንዲያጡ ተደርገዋል፤ ሌሎች ደግሞ እስር ቤት ውስጥ በመወርወር እንዲማቅቁ ተደርገዋል። ለ27 ዓመታት ያህል ኢትዮጵያን በከፋፍለህ ግዛው የተንኮል መሳሪያ የገዛው ከትግራይ ብሄረሰብ የተውጣጣ ማፊያዊ ቡድን፣ ቀጥሎ ደግሞ እሱን የተካውንና የኦሮሞን ብሄረሰብ ጥቅም አስጠብቃለሁ የሚለው አቢይ አህመድና አገዛዙ ስልጣን ላይ ቁጥጥ በማለት ፖለቲካን የተረዱት የቂም በቀል መወጫ መሳሪያ አድርገው ነው። ሁለቱም አገዛዞች ክወጭ ኃይሎች ጋር በማበርና የእነሱን ትዕዛዝ በመቀበልና ተግባራዊ በማድረግ በታሪካችን፣ በአገራችንና በህዝባችን ላይ የባህል ጦርነት ዘመቻ ነው ያካሄዱትና የሚያካሄዱት። በተለይም አንድን አገር በተሟላ መልክ ለመገንባትና ጤናማ ህብረተሰብ ለመገንባት የማያስችል “የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ” ተግባራዊ በማድረግ አገራችንን እንዳለች ወደ ብልግና መድረክ ቀይረዋታል ማለት ይቻላል። ይህ ዐይነቱ የኢኮኖሚ ፖሊሲ የሚሉት ነገር በ21ኛው ክፍለ-ዘመን እንደ ሞድ የተወሰደና በተወሰኑ ኢኮኖሚስቶች ነን በሚሉ የረቀቀ፣ ይሁንና ደግሞ የአንድን አገር የህብረተሰብ አወቃቀር፣ የፖለቲካ አደረጃጀትና የመንግስት አወቃቀር፣ እንዲያም ሲል የጠቅላላውን ህዝብ የኑሮ ሁኔታ በሚገባ ሳይጠና የውጭ ኤክስፐርቶች ነን በሚሉ የረቀቀና በጭፍኑ ተግባራዊ እንዲሆን የተደረገ ነው። እንደኛ ለመሰለው አገር እንደፍቱን መሳሪያ ሆኖ የሚቀርበውና ተግባራዊም የሚደረገው የኢኮኖሚ ፖሊሲ፣ በመሰረቱ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ያልሆነ በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ እንደ ትምህርት የማይሰጥና አንደኛውም የካፒታሊስት አገር በታሪኩና በህብረተሰብ ግንብታ ሂደት ውስጥ በፍጹም ተግባራዊ ያደረገው አይደለም። ስለሆነም ከተለያዩ ዕውቀቶች ጋር በመያያዝ አንድን ህብረተሰብና አገር በተሟላ መልክ ሊያስገነባ የሚያስችል ፖሊሲ አይደለም። ፖሊሲው ተግባራዊ በሚሆንበት ጊዜ የተለያዩ አገሮች የህዝቦች አኗናርና የፖለቲካው ሁኔታ እንደሚየረጋግጠው ሰፊውን ህዝብ ደሃ የሚያደርግና በጣም ጥቂቱን ደግሞ በሀብት እንዲናጥጥ በማድረግ የጥሬ-ሀብትን ማዘረፊያ መሳሪያ ለመሆን የበቃ ነው። በተጨማሪም የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ በሆነባቸው አገሮች በሙሉ ከፍተኛ ውንብድና በመስፋፋት፣ በተለይም ደካማውን የህብረተሰብ ክፍል የሚጠቃበትን ሁኔታ እንመለከታለን። ከዚህም በላይ መንግስታዊ አወቃቀሩ ከመጠን በላይ በወታደርና በስለላ ኃይሎች በመታጠቅና በመከበብ ወደ ተራ የመጨቆኛ መሳሪያነት የተለወጠበትን ሁኔታ እንመለከታለን። እንደሚታወቀው ይህ ዐይነቱ አስፈሪ በሆኑ መሳሪያዎች የታጠቀውና የተከበበው የመንግስት መኪና ምርታማ አይደለም። ሰለሆነም ለሳይንስና ለቴክኖሎጂ ዕድገት ሊውል የሚችለውና የተወሳሰብውን የህብረተስብ ችግር ሊፈታ የሚችለው ሀብት ከአለአግባብ ይባክናል ማለት ነው። ይህንን ዐይነቱን በመሰረቱ ወደ ፋሺስታዊ መዋቅር የተለወጠውን የመንግስት መኪና ደግሞ የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምና ግብረ-አበሮቹ ይፈልጉታል። ምክንያቱም አንድ ህዝብ ሲጨቆንና ደንቁሮ ሲቀር የአንድ አገር ሀብት መበዝበዙ ብቻ ሳይሆን ኋላ-ቀርነቱም ስር እየሰደደ ይሄዳል። ጠቅላላውም ህዝብ አቅመ-ቢስ በመሆን አቅጣጫው ጠፍቶበት የኑሮን ትርጉም ሳይረዳ እንዲኖር ይገደዳል ማለት ነው።
እንደሚታወቀው አንድ ህብረተሰብ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊ፣ በባህላዊ፣ በሀይማኖት፣ በልዩ ልዩ እሴቶችና ሙያዎች የሚገለጽ ነው። ከእነዚህ ውስጥ ፖለቲካና ኢኮኖሚ ወሳኝ ሚናን ይጫወታሉ። ፖለቲካ የአንድ አገር አጠቃላይ ፕሮጀክት የሚነደፍበት መመሪያና መሳሪያ ሲሆን፣ ፖለቲካው ስኬታማ እንዲሆን ከተፈለገ ዲሞክራሲና የመንፈስ ነፃነት ወሳኝ ሚናን ይጫውታሉ። ለዚህ ደግሞ የግዴታ ከፍተኛ የሆነ ምሁራዊ መሠረት እንዲኖር ያስፈለጋል። አንድ አገር ከፍተኛ የሆነ የምሁር መሠረት ካለውና አንድ አገዛዝም የመንፈስ ነፃነት የሚሰማውና አርቆ የሚያስብም ከሆነ ከየትኛውም አቅጣጫ የሚመጣበትን ትችትም ሆነ ገንቢ አስተያየት በፍጹም አይፈራም። ምክርንም ሆነ ገንቢ የሆነን ትችት ይቀበላል ማለት ነው። በአጭሩ ለአንድ አገር በተከታታይ ለማደግና ህብረተሰቡም በመተባበር አገሩን እንዲገነባ ከተፈለገ ፖለቲካ በጣም ወሳኝ ሚናን ይጫወታል። ስልጣን ላይ የሚቀመጡትና የአንድን ህዝብ ዕድል የሚወስኑትም የተገለፀላቸው መሆን አለባቸው። ከዚህ መሰረታዊ ሃሳብ ስንነሳ ፖለቲካ ስልጣን ላይ ቁጥጥ በማለት የራስን ውስጣዊ ፍላጎት ማሟያና መፈንጫ መሳሪያ ሳይሆን በሳይንስና በቴክኖሎጂ የሚገለጽ ሰፋ ያለ ህብረተሰብ መገንቢያ መሳሪያ ነው። ስለሆነም ፖለቲካ የሚባለው ነገር የዛሬውንና የነገውን ትውልድ የሚያገናኝና፣ ለተከታታዩ ትውልድ ታሪክ የሚሰራበት መሳሪያ ነው። መታወቅ ያለበት ነገር አንድ አገዛዝ ስልጣን ላይ በሚሆንበት ጊዜ ዛሬ ተግባራዊ የሚያደርጋቸው ፖሊሲዎች በሙሉ በተከታታዩ ትውልድ ላይም የራሳቸውን ተፅዕኖ አዎንታዊ ወይም አሉታዊ በሆነ መልክ ያሳድራሉ። ፖለቲካው በሰፊው ወይም ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ የሚታሰብ ከሆነ ተከታታዩም ትውልድ መሰረት ይኖረዋል ማለት ነው። የተጣለለትን ጥሩ መሰረት መመሪያ በማደረግና በማሻሻል እንደዚሁ ለሚቀጥለው ትውልድ የተሻለ ነገር ጥሎለት ማለፍ ይችላል ማለት ነው። በሌላ ወገን ግን በራስ ጥቅም ላይና ጎልቶ በመታየት ላይ የተመሰረተ ፖለቲካ ፖለቲካ ስለማይባል አስቸጋሪ ነገሮችን ጥሎ ነው የሚያልፈው። ልክ በአገራችንና በአብዛኛዎቹ የአፍሪካ አገሮች እንደምናየው ነገር ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ባህላዊ ነገሮች በመዘበራረቅ በተለይም ታዳጊው ትውልድ ሊመራበት የሚችል እሴት(Value) አይኖረውም ማለት ነው። ይህም ማለት በጎሳና በሃይማኖት ግጭት፣ በዘራፊዎችና በማጅራት መሪዎች፣ እንዲሁም በቆሻሻ መኖሪያዎች የሚገለጽና፣ ሰፊውም ህዝብ ተዝረክርኮ የሚኖርበትን ሁኔታ ጥሎ በማለፍ አዲስ አገዛዝ በሚተካበት ጊዜ ችግሩን ሊፈታው አይችልም ማለት ነው። ስለሆነም ስልጣን ላይ የሚወጡ ድርጅቶችና ግለሰቦች ከልጅነታቸው ጀምረው ያልተኮተኮቱ ከሆነ በአጋጣሚ ስልጣን ላይ በሚወጡበት ጊዜ፣ ልክ እንደ አገራችን ጠ/ሚኒስተር እንደ አቢይ አህመድ ማለት ስልጣንንና ፖለቲካን ህዝባዊ ፕሮጀክት መስሪያ ከማድረግ ይልቅ የውጭ ትዕዛዝ እየተቀበሉና ከአንዳንድ የውጭ አገር መሪዎችና ኤክስፐርቶች ነን ከሚሉ ጋር ፎቶግራፍ በመነሳትና በመዝናናት ፖለቲካ የሚባለው ነገር በዚህ መልክ የሚገለጽ ይመስላቸዋል። ለሌላውም ተከታዩ መሪና ትውልድ መጥፎ አርአያ በመሆን ለውጭ ኃይሎች አሽከር የሚሆን ሌላ መሪ ስልጣን ላይ ቁጥጥ በማለት ችግሩን ከመፍታት ይልቅ የባሰ ውስብስብ ያደርገዋል።
ስለሆነም ስለፖለቲካ በምናስብበት ጊዜ በመጀመሪያ ፖለቲካ የሚባለው ነገር በቀጥታ በፍልስፍና ላይ የተመሰረተ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል። ይህ ብቻ ሳይሆን ፖለቲካ በቀጥታ ሳይንስ ስለሆነ በአንድ አገር ውስጥ በግልጽ የሚታዩ ልዩ ልዩ ችግሮች በሙሉ ከሳይንስ አንፃር መመርመር አለባቸው። የችግሮችን ዋና ምክንያት ለመረዳት መሞከር ብቻ ሳይሆን ፍቱን መፍትሄም ለመፈለግ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል። ከዚህም በላይ ፖለቲካ ህዝባዊ ፕሮጀክት መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል። ይህም ማለት ፖለቲካ ችግር መፍጠሪያ ሳይሆን የአንድን ህዝብ የተወሳሰቡ ችግሮች መፍችያ መሳሪያ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል። ፖለቲካ ህዝብን የሚሰበስብና ከብሄረሰብና ከሃይማኖት ባሻገር እጅ ለእጅ በመያያዝ አገርን መገንቢያ መሳሪያ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል። የመጨረሻ መጨረሻ እያንዳንዱ ሰው ለመኖር ሲል ምግብ መብላት እንዳለበት፣ ንፁህ ውሃ መጠጣት እንዳለበት፣ መኖሪያ ቤት እንደሚያስፈልገውና፣ ለዚህም ደግሞ በደንብ የሚንቀሳቀስ ኢኮኖሚ እንደሚያስፈልገው ሁሉ የጎሳና የሃይማኖት ጉዳዮች እንደዋና አጀንዳ ሆነው በሚቀርቡበት አገር ውስጥ እነዚህን ለአንድ ህዝብ መሰረታዊ የሆኑ ነገሮችን በፍጹም መፍታት አይቻልም ማለት ነው። ስለሆነም አንድን አገር እንደ አገር ለማስጠራት፣ አንድን ህዝብ በጠንካራ መሰረት ላይ ለማቆም ከተፈለገ የግዴታ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ጉዳዮች አስፈላጊዎች መሆናቸው መረዳት ያስፈልጋል ማለት ነው። በአንፃሩ የሃይማኖትና የጎሳ ንትርክ በበዛበት አገር ውስጥ አንድን አገር በጠንካራ መሰረት ላይ በፍጹም መገንባት አይቻልም። ስለሆነም እያንዳንዱ ሰው ማሰብ ያለበት በጠባቡ ሳይሆን ሰፋ ባለ መልክ ብቻ ነው። ራሱን እንደሰው፣ ስነ-ምግባርና ሞራል እንዳለው፣ ሊፈጥር እንደሚችልና ራሱንም በመለወጥና ከሌላው ጋር እጅ ለእጅ በመያያዝ አንድን አገር ለመገንባት የሚችል መሆን አለበት። አንድም ሰው ሰው መሆኑን የሚያረጋግጠው ጥሩውንና ከፍተኛውን የመንፈሱን አካል በመጠቀም ከራሱ ባሻገርም ሊያስብ የሚችል ከሆነ ብቻ ነው። በሌላ ወገን ግን በራስ ጥቅምና ፍላጎት የተዋጠ፣ ራሱን አጉልቶ ለማሳየት የሚሯሯጥና፣ ሌላው ሲገደልና ሲበደል ደስ የሚለው ይህ ዐይነቱ ሰው ልክ ታላቁ ፈላስፋ ፕሌቶ እንዳለው “ከዕምብርቱ በታች በሚገኘው የመንፈስ አካል” የሚመራ ነው ማለት ነው። ፕሌቶ የሰውን ልጅ መንፈስ በሶስት ሲከፋፍል፣ መንፈሳችን በአንድ ቦታ የተቀመጠ ሳይሆን፣ አንደኛው በቆዳችን ውስጥ ሲሆን፣ ይኸኛው የመንፈስ አካል አርቀን እንድናስብና ትክክለኛ ዕውቀትን ለማግኘት ጥረት ለማድረግ የሚያስችለን ነው ይላል። ሁለተኛው የመንፈስ አካል ደግሞ በደረታችን ውስጥ የሚገኝ ሲሆን ይህ ዐይነቱ የመንፈስ አካል በድፍረትና በስራ አማካይነት በሀብት ከሌላው በልጦ ለመገኘት የሚገለጽ ሲሆን፣ ኢ-ፍትሃዊነትም ጎልቶ በሚታይበት አገር ውስጥ ዝም ብሎ የማይመለከትና ለመታገልም የማይሳሳ ነው። ይሁንና ትግሉ በጠበንጃ ሳይሆን በአርቆ አሳቢነትና በዕውቀት አማካይነት ብቻ ነው። ፕሌቶ በትክክል እንደሚለው የሰው ልጅ ዋናው ችግር ከትክክለኛ ዕውቀት ጋር አለመተዋወቅና መንፈስም በትክክለኛ ዕውቀት አለመኮትኮት የችግሮች ሁሉ ዋና ምንጭ ነው። ሶስተኛው የመንፈስ አካል ደግሞ ከዕምብርታችን በታች የሚገኝ ሲሆን፣ ይህ ዐይነቱ የመንፈስ አካል ስግብግብና ለብልጭልጭ ነገሮች የሚቁማጥና መንፈሱ ይበልጥ ሴቶችን በማማረጥ ላይ የሚያደላ ነው። ይህ ዐይነቱ ቅብዝብዙ የመንፈስ አካል የጦርነትም ምንጭ ነው። መመሪያው ዕውቀት ሳይሆን ስግብግብነትና መቋመጥ ስለሆነ በአንድ አገር ውስጥ ሰላም እንዳይኖር ያደርጋል ማለት ነው። ፕሌቶ ከሁለት ሺህ ዓመት ተኩል በፊት በምርምር የደረሰበት የሰው ልጅ ዋናው ችግር፣ በተለይም ስልጣን ላይ ቁጥጥ የሚሉ ኃይሎች ዋናው ችግር ከዕምብርታቸው በታች ያለው የመንፈስ አካል ጎልቶ በመውጣቱ ነው። ይህ ዐይነቱ የመንፈስ አካል በዓለም አቀፍ ደረጃ የተስፋፋና በፖለቲካ ውስጥ የሚሳተፈውንና፣ በአጠቃላይ ሲታይ ኤሊት ነኝ የሚለውን በሙሉ ያዳረሰና ዓለምን ወደ ጦር አውድማነት ለመቀየር የሚያስችል አደገኛ የመንፈስ አካል ነው። በግሎባል ካፒታሊዝም ዘመን ይህ ዐይነቱ የመንፈስ አካል አይሎ በመውጣት ጦርነትን ማራመጂያና አንድን አገር ማተረማመሻ ለመሆን በቅቷል ብሎ አፍን ሞልቶ መናገር ይቻላል። በተለይም ከሳይንሳዊ ምርምር፣ ከጥበብ፣ ከስነ-ጽሁፍ፣ ከሙዚቃና፣ በተጨማሪም ምርታማ ከሆኑ ነገሮች ጋር ምንም ግኑኘነት የሌለው የህብረተሰብ ክፍል በዚህ ዐይነቱ ከዕምብርት በታች በሚገኝ የመንፈስ አካል በመመራት በየአገሮች ውስጥ ከፍተኛ ትርምስ በመፍጠር አንድን አገር ታሪክ የሚሰራበት መድረክ ከማድረግ ይልቅ የባለጌዎች መፈንጪያ ያደርጋል ማለት ነው።
ከዚህ አጠር መጠን ብሎ ከቀረበ ሀተታ ስንነሳ በአገራችንና በተቀሩት የአፍሪካ አገሮች ያለው ትልቁ ችግር የፖለቲካ ቲዎሪ በደንብ አለመዳበሩ ብቻ ሳይሆን፣ ፖለቲካ የሚባለው መሰረተ-ሃሳብ ሳይንስ መሆኑን አለመገንዘቡ ላይ ነው። የፖለቲካ ቲዎሪን ሳይንስ መሆኑን አስመልክቶ ከጥንታዊቱ ግሪክ ጀምሮ በሶክራተስ፣ ፕሌቶና አርስቲቶለስ፣ ከዚያም በኋላ ከ16ኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ በሰፊው ተተንትኗል። ፖለቲካም በሰለጠነ መልክ መካሄድ እንዳለብትና የየግለሰቦች መፈንጫ መሳሪያ እንዳልሆነ ለማስተማር ተሞክሯል። የፖለቲካ ፅንሰ-ሃሳብም የፈለቀውና እንደሳይንስ መታየት የበቃው እንዳለ ጦርነትን፣ ጨቋኝነትንና የመሪዎችን መባለግ እንዳለ በመቃወም ለመዳበር በመቻሉ ነው። በአጭሩ ፖለቲካ ሳይንስ እንደመሆኑ መጠን እንዳለ ጦርነትን በመቃወም ሰብአዊነትን የሚያስተምር መሳሪያ ነው። በሌላ አነጋገር፣ ፖለቲካ በምንም ዐይነት ወደ መጨቆኝያ መሳሪያነት በመለወጥ ጦርነትን በማካሄድና የአንድን አገር ህዝብ በማፈናቀል ፍዳውን እያየ እንዲኖር ማድረጊያ መሳሪያ አይደለም። ሰለሆነም በፖለቲካ ውስጥ እንሳታፋለን የሚሉ ግለሰቦች በሙሉ የሞራልና የስነ-ምግባር ብቃት እንዲኖራቸው እንደሚያስፈልግ በበቂው ተተንትኗል። ይህም ማለት ፖለቲካ ሰፋ ያለ ሳይንሳዊ ግንዛቤንና አርቆ-አስተዋይነትን እንደሚጠይቅ ለማስተማር ተሞክሯል። ይህ ዐይነቱ ዕውቀት በአገራችን ምድር ቀድሞም ሆነ በ21ኛው ክፍለ-ዘመንም የማይታወቅ በመሆኑ ፖለቲካ የሚለው ቅዱሳዊ አስተሳሰብ የወንበዴዎች መጫወቻና መሸወጂያ መሳሪያ ለመሆን በቅቷል። ከዚህም በላይ አንድ ህዝብ ተረጋግቶና እፎይ ብሎ እንዳይኖር የአጭበርባሪዎች መሳሪያ ለመሆን በቅቷል። በተለይም የሚሊተሪውንና የስለላውን መዋቅር ተገን በማድረግና ከውጭ ኃይሎች ጋር በመተባበርና አሽከር በመሆን ፖለቲካ በቀጥታ ጦርነትን ማስኬጃ መሳሪይ ለመሆን በቅቷል ማለት ይቻላል።
ወደ ኢኮኖሚው ስንመጣም ያለው ትልቁ ችግር አንደ ፖለቲካው ግልጽ አይደለም። ለምሳሌ አንዳች ዐይነት የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ በሚደረግበት ጊዜ የፖሊሲው ዓላማ በፍጹም አይታወቅም። ነፃ የገበያ ኢኮኖሚ ነው ቢባልም ይህ ዐይነቱ ምኞት የየአገሬው ህዝብ ይፈልገው አይፈልገው ምንም የሚታወቅ ነገር የለም። መሠረታዊ ፍላጎቱን ይፍታለት ወይም አይፍታለት ከመጀመሪያውኑ ግልጽ አይደለም። ይሁንና “ፖሊሲው” ተግባራዊ ከሆነ በኋላ የምናየው ውጤት የባሰ ድህነትንና መመሰቃቀልን ነው። በዕዳ መተብተብንና የንግድ ሚዛን መዛባትን ነው የምንመለከተው።
እንደሚታወቀው የአንድ ህዝብ የመኖርና አለመኖሮ ዕድል ሊወሰን የሚችለው በኢኮኖሚ አማካይነት ነው። ይህም ማለት አንድ ሰውም ሆነ ህዝብ በህይወት ሊኖሩና ሊሰሩ የሚችሉት ምግብ ሲያገኙ፣ ንጹህ ውሃ ሲጠጡ፣ መጠለያና ሌሎች ነገሮችን ሲሟሉላቸው ብቻ ነው። ለዚህ ደግሞ የአንድ አገር ኢኮኖሚ በስራ-ክፍፍል ላይ መዋቀር አለበት። ይህም ማለት የእርሻ፣ የኢንዱስትሪና የአገልግሎት፣ እንዲሁም የንግድ መሰኩ በደንብ መዘጋጀት አለባቸው። የህዝብን ፍላጎት እንዲያሟሉ ተብለው መታቀድ አለባቸው። ከዚህ ውስጥ ሳይንሰና ቴክኖሎጂ ወሳኝ ሚናን ይጫወታሉ። በሳይንስና በቴክኖሎጂ በመታገዝ ብቻ ነው በቁጥር እየጨመረ የሚሄድን ህዝብ መመገብ የሚቻለው። በሳይንስና በቴክኖሎጂ አማካይነት ብቻ ነው ልዩ ልዩ መሳሪያዎችን መፍጠርና ማምረት የሚቻለው። የሳይንሰና ቴክኖሎጂ መዳበር ደግሞ የባህልን ዕድገት ያፋጥናል። የሰውም የማሰብ ኃይል ከፍ ይላል። ስራው ሁሉ ፈጠራና የራሱን ህይወት መልክ በማሲያዝ ላይ እንዲያተኩር ይገደዳል። ስለሆነም በፈጠራና በስራ-ክፍፍል ላይ የተመሰረተ ኢኮኖሚ ህብረተሰቡን ያስተሳስረዋል። የአንድ አገርም ብሄራዊ ነፃነት መከበር ብቻ ሳይሆን ሰፊው ህዝብም ይከበራል። ይህንንም ለመተግበርና ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የኑሮን ትርጉም እንዲረዳ ከተፈለገ የግዴታ ከተማዎችና መንደሮች ጥበባዊ በሆነ መልክ መገንባት አለባቸው። ሰፊውን ህዝብ የሚያለያዩ ሳይሆኑ፣ ወይም ደግሞ በሀብታምና በደሃ የሚከፋፍሉ ሳይሆኑ ለመሰብሰብና እንደ አንድ አገር ህዝብ ተከባብረው ለመኖር የሚያስችሉ ከተማዎችና መንደሮች መገንባት አለባቸው። የቤቶችና የልዩ ልዩ ህንፃዎች አሰራርም ዘላቂነት እንዲ8ኖራቸው ያስፈልጋል። በተለይም ከአራትና ከስድስት ፎቆች በላይ ቤቶች መሰራት እንደሌለባቸው በህግ መደንገግ ያስፈልጋል።
ከላይ ለመተንተን የሞከርኩትን ፖለቲካዊ ችግር ስልጣን ላይ ካሉት አገዛዞች ባሻገር የግዴታ ስልጣን ላይ መውጣት አለብኝ ብሎ የሚጠባበቀውና ራሱን እንደተቃዋሚ ኃይል ለማሳየት የሚሞክረው የፖለቲካን ምንነት በምን መልክ እንደተረዳና እንደሚረዳ እስካሁን ድረስ ሰፊ ማብራሪያ የሰጠ ኢትዮጵያዊ ድርጅትም ሆነ ግለሰብ የለም። ቀድሞ የህወሃትን አገዛዝ፣ በአሁኑ ወቅት ደግሞ ስልጣን ላይ ያለውን የአቢይ አህመድን አገዛዝ በምን ዐይነት የፖለቲካ ርዕይ እንደሚመሩና፣ የኢኮኖሚ ፖሊሲያቸውም ምን ዐይነት እንደሆነ እስካሁን ድረስ ተቃዋሚ ነኝ ከሚለው ኢትዮጵያዊው የፖለቲካ ተዋናይ አንዳችም ሀተታ የሰጠ የለም። በተጨማሪም ቀድሞ የህወሃት አገዛዝ፣ ከዚያ በኋላ ደግሞ የአቢይ አህመድ አገዛዝ የውጭ ኃይሎች ታዛዦችና አገርን አተራማሽ እንደሆኑና ህዝባችንንም ፍዳ እንደሚያሳዩት ከአንዳቸውም ተቃዋሚ ነኝ ከሚለው ኢትዮጵያዊ ድርጅትና ግለሰብ ሳይንሳዊ በሆነ መልክ ተብራርቶ ቢያንስ የፓለቲካ ነገር ያገባኛል ለሚለው ኢትዮጵያዊው ኃይል ተሰራጭቶ ሲነበብ አይታይም። እኔ እስከማውቀው ድረስ ተቃዋሚ ነኝ የሚለውም በግለሰብም ሆነ በተደራጀ መልክ እዚህና እዚያ የሚሯሯጠው ልክ እንደህወሃትና እንደ አቢይ አህመድ አገዛዞች ምንም ዐይነት ፍልስፍናዊ መመሪያ የለውም። ይህም ማለት የአሁኑ የአቢይ አህመድ አገዛዝ በአንዳች ነገር ከስልጣን ላይ ቢወገድ የተተራመሰውን የአገራችንን የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የሰላም እጦት ሁኔታ እንዴትት መፍታት እንደሚቻል ግልጽ አይደለም። ከዚህም በተጨማሪም እንደነቀርሳ ከሚሰረስሩንና አልላቀቅ ካሉንና ህልውናችንን ከሚያዳክሙት እንደ አሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ከመሳሰሉት፣ ውንብድንና፣ ዘረፋንና ልዩ ልዩ ብልግናዎችን ከሚያስፋፉት ሰይጣናዊ ኃይሎች በመላቀቅ ቅዱስና የተከበረች ኢትዮጵያን እንዴት መገንባት እንደሚቻል ግልጽ አይደለም። ይህንን እንቆቅልሽ እስካልፈታን ድረስ የተከታታዩም ትውልድ ዕድል በጣም አስቸጋሪ ይሆናል ማለት ነው። ጦርነትና ድህነት፣ እንዲሁም ኋላ-ቀርነት መገለጫው ይሆናሉ ማለት ነው። ስለሆነም በዚህ ዐይነቱ አንገብጋቢ ጥያቄ ላይ መረባረብና መፍትሄም ለመስጠት ጥረት ማድረግ አለብን፣ በጥልቀትና በስፋት ለማሰብ መሞከር አለብን። መልካም ግንዛቤ!!
fekadubekele@gmx.de
www.fekadubekele.com
ማሳሳቢያ፦ ለስድስት ወራት ያህል ከመፃፍ የተቆጥብኩት በኮምፒዩተሬ መበላሽት የተነሳ ነው። እስከምገምተው ድረስ ከውጭ ሆነው ኮምፒዩተሬን የሚያበላሹ ጠላፊዎች የሚባሉ ሰዎች ኮምፕዩተሬ ውስጥ ሰርገው በመግባት ከአንዴም ሁለቴም ኮምፒዩተሬ ተበላሽቶ ማስራት ነበረብኝ። ብዙ ውጭም አስወጦቶኛል። ብዙ ያጠራቅምኳቸው ዳታዎችም ተሰውረውብኛል። በዚህም ምክንያት የተነሳ አንዳንድ አጠር አጠር ያሉ ጽሁፎችን በኋትሳፕ እየፃፍኩ ነበር ለአንዳንድ ለማውቃቸው ጓዶች የማሰራጨው።
ሁለተኛው ማሳሰቢያ እንደዚህ ዐይነቱን ሳይንሳዊ ጽሁፍ ለማዘጋጀት ብዙ ጊዜን ይጠይቃል። እንደሚታወቀው በሳይንሳዊ ዕውቀት ብቻ ነው አንድን አገር በተሟላ መልክ መገንባትና የተሟላ ሰላምም ለማሰፍን የሚቻለው። ይህም ማለት ሳይንሳዊ ስራዎች ወይም ጽሁፎች በሌሎችም እየተዘጋጁ መቅረብ አለባቸው። ባጭሩ የአንድ ግለሰብ ኃላፊነት ብቻ መሆን የለባቸውም። ከዚህም ባሻገር እንደዚህ ዐይነት ጽሁፎች ሲቀርቡ በተቻለ መጠን ማንበብና ለሌሎችም ማሰራጨት በጣም አስፈላጊ ነው። በተጨማሪም እንደዚህ ዐይነት የመሳሰሉ ሳይንሳዊ ጽሁፎች የራስን ጊዜ ስለሚጋሩ የበለጠ ፕሮፌሽናል በሆነ መልክ ለማቅረብ የግዴታ የፋይናንስ ርዳታ ማድረግ ያስፈልጋል። እስካሁን ድረስ አንድ ግለሰብ ብቻ ነው መጠነኛ ገንዘብ ያስተላለፈው። ስለሆነም የድረ-ገጼን በማገላበጥ አስፈላጊው ርድታ ቢደረግ በተከታታይ አጠር አጠር ባለመልክ ሳይንሳዊና ችግር ፈቺዎችን ጽሁፎች በተከታታይ መጻፍና ማስነበብ ይቻላል የሚል ዕምነት አለኝ። በጣም አመሰግናለሁ!!